Friday, October 19, 2012

‎ጥቂት የ ‹ A › መሪዎችና በርካታ የ ‹ A › በሽታ ‎



እገሌ የ ‹ A › ተማሪ ነው ከተባለ ቀለሜዋ መሆኑን እንረዳለን ፡፡ ፕሬዝዳንት እንቶኔ የ ‹ A › መሪ ናቸው ከተባለ ደስ የሚሉና የተባረኩ ናቸው ብሎ ማለፍ ያስቸግራል ፡፡  ‹ A › ማለት ምንድነው ?  የተከበረው ‹ A › እንዴት ይገኛል ?  የሚለውን ሀሳብ ማጦዝ ያስፈልጋልና፡፡


የ ‹ A › መሪነት በሽምደዳና በችከላ ብቻ አይገኝም ፡፡ አንድ የሀገር መሪ እዚህ ማዕቀፍ ውስጥ በክብር ሊቀመጥ የሚችለው ዴሞክራሲ የተባለውን መጠነ ሰፊ ባህር ዋኝቶ ባይጨርሰውም ውስጡ ምን እንዳለ ሲያውቅ ፣ የፕሬስ ነጻነት የተባለውን ጎምዛዛ ፣ አኞና ሆድ አጥጋቢ ማዕድ ቀምሶ ለብዙሃኑ ሲባርክ ፣ ሙስና በተባለው ‹ አሻፋጅ › ገላ ራሱም ሆነ ሌሎች ከመውደቃቸው በፊት ለሃጫቸውን እንዲቆጣጠሩ ሲሰራ ፣ የሰው ልማት የተባለውን መሰረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎት ለሟሟላት ቀን ከሌሊት ሲተጋ ነው ፡፡


የተማሪነት ዘመናቸውን በቀለሜዋነት አሳልፈው የህዝብ አስተዳደሩ ግዜም በዚሁ ካባ ደምቀው የታዩ የአፍሪካ መሪዎች ካሉ እንደመታደል  ይቆጠራል ፡፡ አንዳንድ ጎበዝ ተማሪ የነበሩ የአፍሪካ መሪዎች ሲጎለምሱ ጎበዝ ገዳይና ጀግና ፈላጭ ቆራጭ ሆነዋል ፡፡ አንዳንዶች በትምህርት ብዙም ያልተጓዙ ቢሆንም ትንሽ ከራርመው ባለብዙ ዲግሪ መሆናቸውን ያስነግራሉ ፡፡ ብዙዎቹ አዋቂና ዘመናዊ እንዲባሉ ስለሚፈልጉ የቀለም ቦሃቃ ውስጥ ገብተው አያውቁም የሚለው ወሬ እንዲነገርባቸው አይፈልጉም ፡፡

ባለኝ የንባብ መረጃ መሰረት ስለ ትምህርቱ ሳይደባብቅ ለጋዜጠኞች በይፋ የተናገረው አረመኔው ኢዲያሚንን ዳዳ ነበር ፡፡
እንዲህም አለ ፡፡ ‹‹ እኔ ምንም ዓይነት የመደበኛ ትምህርት የለኝም ፡፡ ሌላው ቢቀር የነርስ ትምህርት ቤት ሰርተፍኬት የለኝም ፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ግዜ ፒኤችዲ ካለው በላይ ነው የማውቀው !! ›› መቼም ይህ ደፋር ሰው አነስተኛ የትምህርት ዝግጅቴ ለመሪነት አያበቃኝም የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ፈልጎ እንዳልተናገረ ግልጽ ነው ፡፡

ዞሮ ዞሮ የ ‹ A › መሪነት በሽምደዳ አይገኝም ። በባዮሎጂ ትምህርታችን መረጃ መሰረት
የቫይታሚን  B  እጥረት - ቤሪ ቤሪ
የቫይታሚን  C  እጥረት - አስኮርቢክ አሲድ
የቫይታሚን  D  እጥረት - ሪኬት

ከጉዳያችን ጋር ግንኙነት ያለው የቫይታሚን  A እጥረት - በደብዛዛ ብርሃን የማየት በሽታ / Night Blindness / ያስከትላሉ ፡፡
የአፍሪካ መሪዎች ባህርያት አመቱ በጨመረ ቁጥር የሚለያይ ነው ። ወደ ስልጣን ሊመጡ አካባቢና ስልጣንን እንደያዙ ተቆርቋሪነታቸው ፣ የበዛ አዳማጭነታቸውና የተንዠረገገው ቃልኪዳናቸው ብዙዎችን የሚያማልል ነው ፡፡ ምነው ይህን ሰው አባቴ ፣ አጎቴ ፣ ወንድሜ ፣ ውሽማዬ ባደረገው ባዩ ቀላል አይደለም ፡፡ የዚህ ሰው ተወዳጅ አበባ ግን ዕድሜውን ጨርሶ ሳይሆን በትዕቢትና ጥጋብ ከወዲሁ ይረግፋል ፡፡ ቀጥ ያለውና የተከበረውም ‹ A › በጉዳትና በመከራ እንደ ‹ C › እና ‹ D › መጣመም ይጀምራል ፡፡

የ2011 መረጃዎች እንደሚያስረዱት ከሆነ ከ 54 የአፍሪካ ሀገሮች የ A › ን ቦታ ያገኙት የቦትስዋናው / jeretse jan khama / ፣ የኬፕቨርዱ / Jorge carlos fonseca / ፣ የሞሪሽየስ / Navin Chandra Ragoolan / እና የጋና / John Evans Atta mills / መሪዎች ናቸው ፡፡ ተስፋ ከሚጣልባቸው የ ‹ B › መሪዎች ውስጥ ናሚቢያ፣ ደቡብ አፍሪካና ማሊን መጥቀስ ይቻላል ፡፡ ኬኒያ ፣ ታንዛኒያ ፣ ላይቤሪያና ዛምቢያ ለክፉ አይሰጥም በሚባለው የ ‹ C › ማዕቀፍ ውስጥ ናቸው ፡፡ ናይጄሪያ ፣ ሩዋንዳና ኒጀር ‹ D › ን ታቅፈዋል ፡፡ ኡጋንዳ ፣ ጊኒ ፣ ኮሞሮስ ባንዲራ የሚባለውን ‹ F › እያውለበለቡ ይገኛሉ ፡፡ ሊቢያ ፣ አልጄሪያ ፣ ካሜሮንና ኢትዮጽያ ለየት ያለ ስያሜ ተሰጥቷቸዋል ፡፡ ICU የሚል ፡፡ ይህን ምህጻረ ቃል ስናፍታታው Health Service Intensive Care Unit የሚል ሆኖ እናገኘዋለን ፡፡ ጥሬ ትርጉሙስ ከተባለ እዚህ ክፍል የሚመደብ በሽተኛ ፤ በሽታው ለህይወቱ በጣም አስጊ በመሆኑ በዘመናዊ የህክምና መሳሪያና ሙያተኞች ርዳታ መደገፍ እንደሚገባው እንረዳለን ፡፡ ይህን ርዳታ ባግባቡ ካላገኘ ግን መሞቱ ነው ፡፡ ኤርትራ ፣ ሱዳንና ዙምባብዌ ደግሞ < MORGUE > ተብለዋል ፡፡ የሞተ ሰው የሚቀመጥበት ክፍል መሆኑ ነው ፡፡ 

በሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽንና በምስራቅ አፍሪካ መጽሄት ዝግጅት ክፍል ይህን የመሰለ የአፍሪካ መሪዎች ስኮር ካርድ ማዘጋጀት ከተለመደ ሰነባብቷል ፡፡ 75.2 አስመዝግባ ‹ A › ባገኘቸው ቦትስዋናና 32.05 አግኝታ ICU በምትገኘው ኢትዮጽያ መካከል የ43 ነጥብ ልዩነት አለ ፡፡ የነጥቡን ስፋት ያንቦረቀቀው የዴሞክራሲ ፣ የፕሬስ ነጻነት ፣ የሙስናና የሰብዓዊ ልማት መሰረታዊ አጀንዳዎች ናቸው ፡፡ ርግጥ ነው የሞህ ኢብራሂም ኢንዴክስና የጋዜጠኞች ቡድን ነጥብ አሰጣጥ ስርዓትም ይካተታል ፡፡

አሜሪካ በአንድ ወቅት ተስፋ የሚጣልባቸው የአፍሪካ ዴሞክራት መሪዎች በሚል ስያሜ የሩዋንዳውን ፓውል ካጋሜ ፣ የኡጋንዳውን ዩዌሪ ሙሴቬኒ ፣ የኢትዮጽያዊውን መለስ ዜናዊ እንዲሁም ኤርትራዊውን ኢሳያስ አፈወርቂ የላቀ ዕውቅና እንዲያገኙ አድርጋ ነበር ፡፡ የነዚህ መሪዋች ስኮርድ ካርድ ግን ስያሜያቸውን መምሰል አልቻለም ፡፡ ካጋሜ 47.6 በማግኘት D ፣ ሙሴቬኒ 42.7 በማግኘት F ፣ መለስ 32.05 በማግኘት ICU ፣ ኢሳያስ 22.23 በማግኘት MORGUE ውስጥ ተመድበዋል ፡፡ አንዳቸው እንኳን የማለፊያውን ወገብ አለመንካታቸው በእጅጉ ያስገርማል ፤ ተግባራውም ሲታወቅ ያስደነግጣል ። 

ይህን የቤት ስራ በአግባቡ ለመከወን የ ‹ A › መሪዎችን ተሞክሮ መጠቀም ያስፈልጋል ፡፡ በነገራችን ላይ የ ሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን ዘንድሮን ብቁ መሪ አላገኘሁም በሚል ሂሳብ ይዝለለው እንጂ እስካሁን ለሶስት መሪዎች የ 5 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት በመስጠት ዕውቅና አጎናጽፏል ፡፡ 
መሪዎቹ ፣
የኬፕቨርዱ - ፔድሮ ቬሮና ፓይረስ
የቦትስዋናው - ፌስተስ ጎንተባይ
የሞዛምቢኩ - ጃኪም ቺሳኖ ናቸው ፡፡
ህገ መንግስትንና ህጎችን በተፈለገ ግዜ በልክ መቅደድና መስፋት በጣም የተለመደ ፣ ቀላልና የማያሳፍር ተግባር በሆነባት አፍሪካ እነዚህ መሪዎች ከሁለት ግዜ በላይ ሀገር አንመራም በማለት በፈቃዳቸው በመልቀቅና የተሻለ መልካም አስተዳደር በመፍጠር ይመሳሰላሉ ፡፡ ሞዴል መሪዎች የተባሉትም በነዚህና በመሳሰለው የላቀ የአመራር ጥበባቸው ነው ፡፡ እንግዲህ ይህን የመሰለ ቅዱስ ተግባር በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጽያ እንዴት ይመጣል ? የሚለው ጥያቄ ነው የሚያስጨንቀው ፡፡ ምክንያቱም የነ ሙጋቤና ሙሴቬኒን መንገድ አጥብቀው የሚከተሉት አምባገነን የአፍሪካ መሪዎች የሚከተለውን ያልተበረዘና ያልተከለሰ ፖሊሲ እያቀነቀኑ ነውና

 ‹‹ እኛ መሪዎች ለህዝብ ጥቅም ሲባል በተወለድንበት አልጋ ላይ እስክንገነዝ ድረስ መቆየት እንፈልጋለን !! ››
ለማንኛውም  መሪዎቻችን ዳፍንት ገደልን መንገድ የሚያስመስል ክፉ በሽታ ስለሆነ ዘወትር በጠራ ሳሙና ፣ ውሃና ፎጣ ፊታቸውንና ጭንቅላታችሁን  ቢታጠቡ መልካም  ሳይሆን አይቀርም ፡፡ 

Sunday, October 14, 2012

‎ዋሊያዎቹ ከተራራ ወረዱ‎




‹‹ የቆየ ከሚስቱ ይወልዳል ይሉሃል ይሄ ነው ›› ብሄራዊ ቡድናችን ዋሊያዎቹ ከ 31 ዓመታት ቆይታ በኃላ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ አለፉ ፡፡ ይህን አባባል በሌላ ቅርጽ መድገም ያስፈልጋል  ‹‹ ዋሊያዎቹ ከ31 ዓመታት ቆይታ በኃላ የአፍሪካን ዋንጫ አሸነፉ ሳይሆን መከራ የሆነባቸውን የማጣሪያ ግንብ ደርምሰው አለፉት !! ›› ማጣሪያን የደፈረ ቡድን ማለት እንችላለን ፡፡

ኩሩው፣ አይናፋሩና ግርማ ሞገስ የተቸረው ዋሊያ በኢትዮጽያ ለዛውም በሰሜን ተራራዋች  ብቻ የሚገኝ አጥቢ እንስሳ ነው ፡፡ ይህን ብርቅ እንሰሳ ለመጎብኘት ከመላው ዓለም ወደ ሀገራችን የሚያቀናው ቱሪስት ቁጥር ቀላል አይደለም ፡፡ ግና ቱሪስቶቹ እንደ ጅብ፣ የሜዳ አህያና ሌሎቹም እንስሳት በቀላሉ በቅርበት ስለማያገኙት ትንፋሽ የሚያሳጥረውን የሰሜን ተራራዋች መውጣት ይጠበቅባቸዋል ፡፡ ዋልያዋች በአብዛኛው የሚኖሩት ከ 2500 ሜትር በላይ፣ ከ 4000 ሜትር በታች በሆኑ አካባቢዎች መሆኑ ይታወቃል ፡፡

ዋሊያ በዚህ ባህሪው እሱ ተራ ወደሚለው ‹ ሜዳማ ስፍራ › ለመውረድ ፍቃደኛ ሳይሆን ህይወቱን ይገፋል ፡፡

የብሄራዊ ቡድናችን ‹ ዋሊያም › ለ31 ዓመታት የአፍሪካም ሆነ የዓለም ዋንጫ አይመቸኝም የሚል የመሰለ አስተሳሰብ ወዶም ይሁን ተገዶ በማዳበሩ ‹‹ ብርቅና በኢትዮጽያ ብቻ የሚገኝ ብሄራዊ ቡድን ›› የሚል ቅጽል እስከማግኘት ደርሶ ነበር ፡፡ በርግጥ እንደ ቀንዳሙ ዋሊያ የሚጎበኙት ነጫጭ ሰዎች አልነበሩም ፡፡ በዚህ የተደፋፈሩት እነ ሶማሊያና ትናንሽ ቡድኖች ሁሉ ባገኙት ቁጥር የሚያቃጥል ጥፊና የሚያሳክክ ኩርኩም ሲያቀምሱት ቆይተዋል ፡፡ ህመሙ ቢጋባብንም ላለው ይጨመራል እንዲሉ ‹‹ ይሄ ውሽልሽል ! አሰዳቢ ! ወኔ ቢስ ! ቡድን ›› እያልን በጎን አገጩን ስናጣምም ነበር ፡፡

ዛሬ ተመስገን ሆነ ፡፡

‹ ቀንዳሙ ዋሊያ ታች ወርዶ የማይታየው ከስነ ፍጥረታዊ ግዴታው አኳያ ነው ፡፡ ታዲያ የኔ ተራራ ላይ መቆለል ምን ሊረባኝ ነው ? ተራራ ላይ ከመኖር አስተሳሰብን ተራራ ማሳከል ይሻላል › የሚል ጥሞና ውስጥ ቆየ ፡፡ ይኀው ስድቡን፣ ኩርኩሙን፣ ቁጭቱን በጉያው ይዞ የምሽት ድል አበሰረ ፡፡

በዚህም ምክንያት የአበሻ ምድር ቀውጢ ሆኖ አመሸ ፡፡ ህዝቡ አበደ ፡፡ ከመናገር ይልቅ መጮህ መረጠ ፡፡ መንገድ ሞልቶ እንዳለቀሰ ሁሉ መንገድ አጣቦ ጨፈረ ፡፡ ብርጭቆ እያጋጨ ዘመረ ፡፡ ከመተቃቀፍ  ይበልጥ አስፋልት ላይ ተንከባለለ ፡፡ ቀሪው ዓለም ‹ የኢትዮጽያ ህዝብ ምን ዓይነት ወገኛ ቢሆን ነው ለማጣሪያ እንዲህ መጠን የሚያልፈው ? › ቢል ‹ በሰው ቁስል እንጨት አይሰደደም ! › ብሎ ለመመለስ ግዜ ያጣረው መስሏል ፡፡  ‹ እረ እንደ አሪፎቹ ዋንጫ ቢያነሳ ምን ሊያሳየን ነው ? › የሚል አሽሙር ንፋሱ ቢያደርሰው የፍቅሩን፣ የአንድነቱን፣ የደስታውን፣ የድል ናፍቆቱን፣ የጥቃቱን ልክ በሀገርኛው ቀመር ለማስረዳት እንደሚያስቸግረው ይገመታል ፡፡

ሀገሬው ግን እንደ ዉጩ አይደለምና ራሱን ‹ ቃሉን የደፈረ ተመልካች ! › ብሎ የሳሳ ትከሻውን በኒሻን ሊያጥለቀልቀው ይችላል ፡፡ አምስት ጎል የገባበትን ቡድን ‹ ታሸንፋለህ ! › ብሎ ያነቃውና ያበረታታው እሱ ነውና ፡፡

እነሆ ዋሊያዎቹ ከተራራ ወረዱ ፡፡

አዲስ ታሪክ ሰሩ ፡፡

ለካስ ዋሊያ ሜዳ ላይም ሮጦ ማሸነፍ ይችላል ፡፡

ነገና ከነገ ወዲያ ደግሞ በነጮች ብቻ ሳይሆን በጥቁሮችም ቱሪስቶች ይታያሉ ፡፡

Wednesday, October 10, 2012

የተረሳው ባህል ትንሳኤ ያገኝ ይሆን ?




ኪነ ጥበብ ያዝናናል፡፡ የህብረተሰቡን አስተሳሰብ በአስደሳች መልኩ ቀርጾ መልሶ ለህብረተሰቡ ሲያቀርብ  ‹‹ ወቸው ጉድ ?! ›› ያሰኛል    ፡፡ ታዲያ ልንሰንቅ በምንችለው ግርምት ውስጥ  የመምህርነት ሚና አለው ፡፡ ባልተሰላቸ መልኩ የሚሰጠው ዕውቀት እንደኛ ባሉ ድሃ ሀገሮች ውስጥ ተጠናክሮ መቀጠሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ ዕድገታችንን ዕውን ለማድረግ ይጠቅማል ፡፡

በተረት ፣ በወግ፣ በስነቃልና በስነግጥም ሀብታም በሆነቸው ኢትዮጽያ ‹‹ ኪነ ጥበብ ›› ሲጫወት የቆየው ሚና ቀላል አለመሆኑ ርግጥ ነው ፡፡ ቅድመ አያቶቻችን  በማህበራዊ ትስስራቸው ውስጥ በጉልህ ሲያንጸባርቁት ቆይተዋል ፡፡ በዚህ ረገድ የ ‹‹ በልሐ - ልበልሃ ›› ስርዓት በዋናነት ሊጠቀስ ይችላል ፡፡

በታሪክ የመጀመሪያዎቹ ጠበቆች ካህናት፣ የህግ ምንጭ ደግሞ ብሉይ ኪዳን እንደነበሩ ይነገራል ፡፡ በሀገራችንም ተሟጋቾች የህግ ዕውቀት ያገኙ የነበረው በገዳማትና በሌሎች መንፈሳዊ ተቋማት ፍትሐ ነገስትን በማጥናት እንደነበር ‹‹ ጠበቃና ስነ ምግባሩ ›› የሚለው መጽሀፍ ያስረዳል ፡፡ በርግጥ የድሮ ጠበቆች እንደዛሬው ህግ የሚማሩበት ትምህርት ቤት አልነበራቸውም ፡፡ ትምህርት ቤታቸው አደባባይ ነው ፡፡ ጥብቅናን የሚማሩት ተረት፣ ወግ፣ ሰምና ወርቅ፣ ባህልና ስነ ግጥም በማጥናትና በመለማመድ ነበር ፡፡
የሚከተለው ክርክር ልጅነትን ለማሳወቅ የተደረገ ነው ፡፡ ተከራካሪዎቹ ምን ያህል የስነ ግጥም ብቃት እንዳላቸው እንመልከት ፡፡
ከቤት ክፉ ሰቀላ
ከልብስ ክፉ ነጠላ
ከእህል ክፉ ባቄላ
ከልጅ ክፉ ዲቃላ
መልኩ የእናሪያ / ጥቁር /
እግሩ መታረሪያ
እየው ፊቱን የተገዛበቱን
እናም አላውቅም ልጅነቱን ብሎ ይቃወማል ፡፡

መላሽም በተቃራኒው ወገን የተነሳውን እያንዳንዱ መሰረታዊ ነጥብ በመልቀም የማፍረሻ ወይም የመቃወሚያ ሀሳቦችን ይሰነዝራል ፡፡

ክረምት ያወጣል ሰቀላ
ከብርድ ያድናል ነጠላ
ቀን ያሰልፋል ባቄላ
ጠላት ይገፋል ዲቃላ
መልክም ቢጠቁር የዘር ነው
እግሩም ቢቀጥን ዘምቶ ነው
ስለዚህ ያለብህ ማወቅ ነው በማለት ጠንካራ የአጸፋ መልስ ይሰጣል ፡፡

የታወቁ ጠበቆች አደባባይ ሲሟገቱ ነጭ ልብስ ለብሰው፣ አደግድገው፣ አንዳንዴም ጎራዴ ታጥቀው፣ በቀጭን ዘንግ ወደፊት እየተወረወሩ ሲናገሩም እየጮሁ ነበር ይባላል ፡፡ ይህ እንግዲህ በክርክሩ ውስጥ ከስነ ግጥም ሌላ የትወና ጥበብም እንደሚንጸባረቅ ጠቋሚ ነው ፡፡

በአንድ ወቅት አባትና ልጅ ተጣልተው ተካሰሱ አሉ ፡፡ ይህ በሀገራችን ባህላዊ ልማድ ያልተለመደ ቢመስልም አንዳንዴ ወጣ ያለ አመለካከትና አተያይ  ያላቸው ልጆች አይፈጠሩም ማለት ግን አይቻልም ፡፡ እናም ልጅ ጉዳዩን ባህላዊው ፍርድ ቤት እንዲያይለት አመለከተ ፡፡ አባት ይህን የመሰለ ድፍረት ባይዋጥለትም ልጅ ተጠየቅ ማለቱ አልቀረም ፡፡ በህግ አምላክ ተጠየቅ !! አለ ልጅ  ወግድ !! እያለ አንገራገረ አባት ፡፡ በወቅቱ ለታዳሚው ያሰሙት ሙግትም የምጥቃታቸውን ደረጃ እንዴት አንጸባርቆ እንደነበር በቅንጭብታ እንመልከተው ፡፡

ልጅ ፤  ተጠየቅ ልጠይቅህ ?!
አባት ፤  አልጠየቅም
          ሰማይ አይታረስም
          ውሃ አይታፈስም
         መሬት አይተኮስም
         አባት አይከሰስም !!
ልጅ ፤  ሰማይ በመብረቅ ይታረሳል
         ውሃም በእንስራ ይታፈሳል
         መሬትም በማረሻ ይተኮሳል
         አባትም በጥፋቱ ይከሰሳል !!
አባት ፤ ፍረዱኝ ሰማይ ያለ መዓት ነጎድጓድ አያወርድ
         ፈጣሪ ያለ ክህደት ገሃነም አያወርድ
         ያለ እርሻ በመሬት ላይ እሳት አይነድ
         ሴትም ያለ እንስራ ውሃ አትወርድ
         አባትም ያለ ጥፋት ልጁን አይክድ
         አባት ለልጁ ዳኛ
         አትሞግተኝም ዳግመኛ !!

ልጅም በዋናነት የአባቱን የምላሽ ሰበዝ እየመዘዘ የማጣመም ወይም ሀሳቡን የማክሽፍ ተልዕኮውን ይቀጥላል ፡፡ ለምሳሌ ያህል አባት ልጄን የካድኩት ስላጠፋ ነው የሚል ሀሳብ ፈንጥቋል ፡፡ ልጅም ጥፋት የተባለውን ነገር በመዘርዘር ንጹህ መሆኑን ለማስረዳት እስከ መጨረሻው ይተጋል ማለት ነው ፡፡ ሌላው አስገራሚ ገጽታ ሁልግዜም ቢሆን ተከራካሪዎች ጥፋተኛ መሆናቸውን ልባቸው ቢነግራቸው እንኳን ከፍተኛ የራስ መተማመን እንዳላቸው የሚያሳዩበት መንገድ ነው ፡፡ ባላጋራቸውን በማስደንገጥ ከክርክሩ እንዲወጡ ከፍ ያለ ቃል ይገባሉ ፡፡ ለምሳሌ ያህል አንደኛው ፤

በልሀ ልበልሃ ልንዛብህ
የሙግት ዠሃ
ሀሰት ቢገኝብኝ በቃሌ
ቅቤ አምጥቼ በብርሌ
እሰጣለሁ ለሽማግሌ ሊል ይችላል ፡፡ ሌላኛውም

በላ ልበልሃ
ልንዛብህ የሙግት ዠሃ
ብትወነጅለኝ በሀሰቱ
ይበረታብሃል ቅጣቱ
የረታህኝ እንደሁ ተሟግቼ
ቀንጃ በሬዬን አምጥቼ
ለዕለት ጉርሴ እንኳን ሳልሳሳ
አገባታለሁ እምቦሳ


በማለት የጠነከረ ምላሽ ይሰጣል ፡፡ ከዚህ በኃላ ክርክሩን ራሳቸው ስላጦዙት ሰሚውም ሆነ ፍርድ ሰጪዎች ዳኞች ቀጣዩን ለመስማት ያቆበቅባሉ ፡፡

እስቲ ሌላ ዘወር ያለ አብነት ደግሞ እንመልከት ፡፡ አንድ በሬ የጠፋበት አርሶአደር በፍለጋ ረጅም ሰዓት ቢያሳልፍም በቀላሉ ማግኘት አልቻለም ፡፡ ሁኔታው አበሳጨው ፡፡ ጉዳዩን ዝም ብሎ መተው የለበትምና በፍለጋ ሰዓታት ያያቸውን ጥቃቅን ፍንጮች በማገጣጠም የሰፈሩን ሰው ጠረጠረ ፡፡ እናም ሊሞግተው አደባባይ አቆመው ፡፡ 

ከሳሽ ፤ የአጤ ስርዓቱን የመሰረቱን
         አልናገርም ሀሰቱን
         ሁልግዜ እውነት እውነቱን
         መጣሁ እንደ ውሃ ስፈስ
         እንደ ጋዣ ስነፍስ
         በቅሎዬ ሰጋሪ
         ሚስቴ ነጭ ጋጋሪ
         ለወታደር የለው ምሳ
         ለቀበሮ የላት ገሳ
         በሬዬ ጠፍቶ ከደጋ
         ስከተል  መጣሁ በደም ፍለጋ
         ብደርስ በፍለጋው ከደጅህ
         ሙዳ ስጋ ይዟል ልጅህ
        ስለዚህ በሬዬን ትከፍላለህ በግድህ !!

ተከሳሽ ፤ ፍየል መንታ ትወልዳለች አንዱ ለመጣፍ
           አንዱ ለወናፍ
           መጣፉ እኔ መናፉ አንተ
           እንደ ውሃ ብትፈስ በቦይ ትመለስ
           እንደ ጋዣ ብትነፍስ አጭዶ ለፈረስ
           ሚስትህ ነጭ ብትጋግር  አንድ እንግዳ አታሳድር
           በቅሎህ ብትሰግር እመሸበት ታድር
            እንዴት ለወታደር የለውም ምሳ
            እራት ጋግሮ ለራት ለምሳ
            እንዴት ለቀበሮ የላት ገሳ
            ትገባለች አርባ ክንድ ምሳ
            በሬህ ቢጠፋ ከደጋ
            አንተም ብትመጣ በደም ፍለጋ
            ከቤቴ በላይ አለ ተራራ
            መዘዋወሪያው የጅብ ያሞራ
            አሞራና ጅብ ሲጋፉ
            ሙዳ ስጋ ስጋ ስለተፉ
            ያላወቀ ልጅ ቢያነሳ
            አያስከፍለኝም ነገርህን አንሳ !!  ይለዋል ፡፡ 

ተሟጋቾቹ በግለት ሲከራከሩ ከየጎጡ መጥተው የታደሙ ሰዎች በክርክሩ መሃል    ‹‹ እውነት ነው !! በደንብ አርገህ ንገረው !! ይገባዋል !! ›› በማለት ደጋፊ ሀሳብ በማቅረብ አጋርነታቸውን ይገልጻሉ ፡፡

ይህን በመሰለ መልኩ የሚደረግ ክርክር ላይ መገኘት መንፈስን እንደሚያስደስት አያጠራጥርም ፡፡ ከዘመናዊ ህግ አሰራር አኳያ ‹‹ በልሀ ልበልሃ ›› አንዳንድ ክፍተቶች ሊኖሩበት ቢችልም ይህ ድንቅ ባህል እየተረሳና እየጠፋ መሄዱ በተለይም ኪነ ጥበብን የሚጎዳ ይመስለኛል ፡፡ ሰዎች ሀሳባቸውን በግጥምና ስነ ቃል መግለጻቸው ፣ በግጥም የሚቀርቡ ሀሳቦችን ደግሞ ያለ ምንም ችግር ማጣጣም መቻላቸው ለደራሲዎች ቀጣይና የጠነከረ ፈጠራ ምርኩዝ ይሆናል ፡፡ ጥሩ ልቦና ያላቸው ደራሲያን በበዙ ቁጥር ብዙ እንዲጽፉ ይገፋፋቸዋልና ፡፡

በልሀ ልበልሃ በአሁኑ ወቅት ለዘመናዊ ህግ አያስፈልግ ይሆናል ፡፡ ወይም አባት ነኝ ባዩ ህግ ያንተ ነገር በቃኝ በማለት ክዶት ይሆናል ፡፡ ግን በልሃውንና ዘመናዊውን ህግ እንደ ሀገራችንና እንደ ሌሎች ሀገሮች ፕሬዝዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር በንጽጽር ማየት ጠቃሚ ይመስለኛል ፡፡ በልሃውና ንጉሱ የመወሰን ስልጣናቸው አነስተኛ ቢሆንም ክብርና ሞገሳቸው ትልቅ ነው ፡፡ ፕሬዝዳንታችን ህጎችን በነጋሪት ጋዜጣ ያውጃል ፤ በልሃው የቀድሞው ማንነታችን አለመሞቱን ያውጃል ፡፡ ፕሬዝዳንታችን የሹመት ደብዳቤ ይቀበላል ፤ በልሃው ከገጠር ቅኔ ዘራፊዎችም ሆነ ከከተሜው ገጣሚዎች የተሳትፎ ጥያቄዎችን እየተቀበለ የተቀናጀ ተሳትፎ እንዲደረግ ሀሳብ ሊያመነጭ ይችላል ፡፡ ፕሬዝዳንታችን ኒሻኖችንና ሽልማቶችን ይሰጣል ፤ በልሃው በት/ቤት፣ በትያትር ቤት፣ በዩኒቨርስቲዎችና በኮንሰርቶች ውድድር እየተካሄደ ለሚያሸንፉት ሽልማት ይሰጣል ፡፡ ፕሬዝዳንታችን ይቅርታ ያደርጋል ፤ በልሃው ተሸናፊዎች በተጋነነ ቅጣት እንዳይጎዱ ይቅርታ ያደርጋል ፡፡

ታዲያ ማነው ይህ ጠቃሚ ባህል ተጠብቆ እንዲቆይ መስራት ያለበት ? እንደ እኔ እምነት ቢያንስ ይህን የህግ የበኩር ልጅ በጉዲፈቻነት ለማሳደግ የባህል መዋቅሮችና በደምሳሳው ከያኔዎች ግንባር ቀደም ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል ፡፡