Saturday, April 11, 2020

ከአዳም ረታ ‹ አፍ › እስከ መንጌ ‹ እንባ ›…



የኮሮና ቫይረስን ወረርሽኝ የመከላከያው አንደኛው መንገድ በራስ ላይ ማእቀብ መጣል ነው ፤ ቤት ውስጥ መከተት ። ቀኑን ለመግፋት ታዲያ በሆነ ስራ መጠመድ ግድ ይላል ። የቤት ስራ ባይሆንልኝም የማንበብ ልምዴ ድብርትን ታድጎታል ። ምክንያቱም ሁለት ተጋምሰው የነበሩ እና ሁለት ያልታዩ መጽሃፍትን እንዳጣጥም ስለረዳኝ ። ስራዎቹ የዶ/ር አለማየሁ ዋሴ « እመጓ » ፣ የአዳም ረታ « አፍ » ፣ የለምን ሲሳይ « My name is Why » እና የሀብታሙ አለባቸው « የቄሳር እንባ » ናቸው ። በአንዳንዶቹ ላይ ሰፊ ትንታኔ ከመስራቴ በፊት አጭር ምልከታዬን እንካችሁ ፤ ታነቧቸው ዘንድም ስሜቴን ለመጋባት ።

 በቀላል አቀራረብና ቋንቋ የተጻፈው « እመጓ » ምርጥ ሃሳብ የያዘ ስራ ሆኖ አግኝቸዋለሁ ። ይህ መጽሐፍ ያስታወሰኝ የግራም ሃንኩክን The Sign and The Seal  / ታቦተ ጽዮንን ፍለጋ / የተባለ ስራ ነው ። ሃንኩክ ቅዱስ ጽዋ ሊገኝባቸው ይችላል ብሎ ከሚጠረጥራቸው ሃገሮች አንደኛዋ ኢትዮጽያ ናት ። የአለማየሁ ዋሴ « እመጓ »ግን ቅዱስ ጽዋ መንዝ ውስጥ ይገኛል የሚለው በርግጠኝነት ነው ። ይህን የሚያዳብሩት ታሪካዊ ፣ ሃይማኖታዊና መላምታዊ መረጃዋች በሚያስደምም ቅንብር ይተረካሉ  ። ቅዱስ ጽዋ የሚገኘው ቫቲካን ፣ ለንደን ፣ ማርሴይ ፣ ቆጽሮስ ፣ ደማስቆ ወይም ኬብሮን ሳይሆን ኢትዮጽያ ነው ይላል ተራኪው ሲሳይ ። እመጓ በእንግሊዘኛ ተተርጉሞ ሃንኩክም ሆነ ያገባናል የሚሉ ሀገሮች ቢያነቡት እንዴት መልካም ነበር ብያለሁ ።

የአዳም ረታን « አፍ » የጨረስኩት እንቅፋት እየቦዳደሰኝ ነው ። ዋናውን ታሪክ ይዤ ስጓዝ ድንገት ብቅ ከሚለው « የግርጌ ማስታወሻ » ጋር እጋጫለሁ ። ማስታወሻው በጣም ረዝሞ ዋናውን ታሪክ ይገዳደራል ፣ አንዳንዴ ደግሞ ማስታወሻ አይደለም ራሱን የቻለ ተዛማጅ ታሪክ እንጂ የሚያሰኝ ቅርጽ ይታይበታል ። ለምሳሌ ያህል ዋናው ታሪክ ላይ የገለታ ጉንጭ ስንቡክ ነው ይላል ። ስንቡክ የሚለው ቃል አናት ላይ አንድ ቁጥር ተጽፏል ። እንግዲህ ይህን ስንቡክ ይረዱ ዘንድ ነው ሶስት ገጽ የሚያነቡት ። አዳም ሰላሳ ያህል የማስታወሻ / የታሪክ / ቁጥሮችን ተጠቅሟል ። አንዳንዴ ለብቻው ተሰምሮ የተቀመጠውን « የግርጌ ማስታወሻ » ጨርሼ ወደ ኋለ ስመለስ ዋናው ታሪክ ይጠፋብኛል ። ። የልቦለዱን ቅርጽ ለየት የማድረግ መንገድ የመሻት ሃሳብ ይመስላል ። እንደሚታወቀው አዳም ብዙ ቅርጾችን አሳይቶናል - ጥሩዎችም ነበሩ ። ይህኛው ግን በጣም ያደክማል ። እንደኔ እንደኔ አዳም ረታ ታላላቅ ሃሳቦች /ይዘት / ላይ ቢያተኩር እመርጣለሁ ።

የለምን ሲሳይ « My name is Why » በራሱ የልጅነት ህይወት ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን ስራ ነው ። መንግስት ልጅ ሰርቆ እስር ቤት ከቷል ፣ የህይወት ታሪኩም እንዳይታወቅ ድብቋል ይላል ደራሲው ገና ከመነሻው ። የሲሳይ እናት እንግሊዝ ለትምህርት የደረሰችው በ1966 ነበር ። በወቅቱ ነፍሰ ጡር ነበረች ። መውለጃዋ ሲደርስ ዊጋን አካባቢ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል በ1967 ደራሲውን ተገላገለች ። በወቅቱ አባቷ ስለሞቱ ወደ ሀገሯ መመለስ ነበረባት ፤ ያኔ ነው እንግዲህ ኖርማን ግሪንውድ ተበሎ ለአሳዳጊ የተሰጠው ። እናቱ ወደ ሀገሯ ስትመለስ ልጅዋ ለአሳዳጊ ተላልፎ እንዲሰጥ ፍቃድዋን አልሰጠችም ።

ለለምን ሲሳይ ህይወት ፈተና ነበረች ። ገና በ12 አመቱ ነበር አሳዳጊዎቹ ያባረሩት ። አሳዳጊዎቹ ለሁለቱ ልጆቻቸው የሚያሳዩት ፍቅር፣ ክብርና እንክብካቤ ለእሱ የራቀ በመሆኑ ነው ግጭቱ እንዲያድግ ምክንያት የሆነው ። ከ12 እስከ 17 አመቱ ደግሞ በአራት የተለያዩ ማሳደጊያ ቦታዎች ተወርውሯል ። በግራ እጁ ላይ NG የሚል ንቅሳት ቢያጽፍም እውነተኛ ስሙ ይህ ንቅሳት አለመሆኑን የተገነዘበው በ17 አመቱ ነበር ። ደራሲው ለ30 አመታት ከእንግሊዝ መንግስት ጋር ትግል ገጥሟል ። ትግል የገጠመው ከልጅነት እስከ እውቀት ሲመዘገብ የቆየው የህይወቱ ታሪክ ተላልፎ እንዲሰጠው ነበር ። በ2015 የዊጋን ካውንስል ሃላፊ አራት ትላልቅ ዶሴዎችን አስረከቡት ። ከዚህ በኋላ ነበር ይህ መጽሀፍ የተወለደው ። ማንነቱን ለአለም ለማብሰር ስሜ ኖርማን ሳይሆን ለምን ነው በማለት የሚደክመው MY Name is Why…

ስለ ልጅነቱ ፣ ስለትምህርቱ ፣ ስለ አሳዳጊዎቹ ስብእና ፣ ስለ ባህሪው ፣ እናቱ ከእንግሊዝ መንግስት ጋር ስለተፃፃፈቻቸው ደብዳቤዎች  ምን አለፋችሁ እያንዳንዱ ትንፋሹ ዶሴው ውስጥ እየተመዘገበ ነው የቆየው ። ደራሲው ድብዳቤዎቹን አባሪ በማድረግ ነው እንግዲህ ታሪኩን በቅደም ተከተል የሚተርክልን ። በአሳዳጊዎቹ ብቻ ሳይሆን በቆዳ ቀለሙ ይደርስበት ስለነበረው ዘረኛ ጥላቻ ይነግረናል ። አካላዊና ሞራላዊ ጥቃቱን ሳያማርር ተርኳል ። እዚህና እዚያ የምትላጋው ህይወቱ ከክፋት አንፃር ከአንደንዥ እፅ ጋር ያስተዋወቀችውን ያህል ፤ በጥሩ ጎን ሲታይ ደግሞ ገና በ12 አመቱ ብእርና ወረቀት አዋዶ መግጠም እንዲችል ጥሪውን አሳይታዋለች ። ዛሬ ይህ ሰው በምድረ እንግሊዝ አንቱ የተባለ ገጣሚ ነው ። በ2015 ታላቅ ተግባር ለፈፀሙ ሰዎች የሚሰጠውን Order of the British Empire ተሽልሟል ።

የሀብታሙ አለባቸውን « የቄሳር እንባ »ን እንደተለመደው በተመስጦ ነው ያነበብኩት ። የቄሳር እንባ የውድቀትና የስንብት እንባ ነው ። የመጽሀፉ ዛቢያ ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም ሲሆኑ በእሳቸው ዙሪያ ቤተሰባቸውና ዘመዶቻቸው ፣ ደርግና ጦር ሰራዊቱ ሲሽከረከሩ እንመለከታለን ። ጦርነት ፣ ንቅዘት፣ በስልጣን መባለግና ፖለቲካዊ ድንቁርና ለአብዮታዊ ስህተት መነሻ ሆነው ብዙ ዋጋ ሲያስከፍሉ እንታዘባለን ። ደራሲው በሱፍ አበባ ላይ « ገበርዲን » እንዳለው የፍልስፍና ሃሳብ እዚህ ስራ ላይም « ልግመት ሶሻሊዝም»ን አስተዋውቆን የፓለቲካውን ግለትና ቆፈን እንዲሁም መነሻና መድረሻውን ያብጠረጥረዋል ። የቄሳር እንባ የሴራ አወቃቀርና የገፀባህሪ አሳሳል ድንቅ ነው ። ፓለቲካዊ ትንታኔውና የፍቅር በከራው አንባቢን ላይና ታች ይንጣል ።

በነገራችን ላይ ሀብታሙ አለባቸውን ለመጀመሪያ ግዜ በስራው ያወኩት በ « አውሮራ » ነው ። የኢትዮ ኤርትራን ጦርነት መሰረት ባደረገው በዚህ ስራ ተደንቄ ነበር ። በድርጊትና በመረጃ የደነደነ ፈጣን ታሪክ አለው ። ፍቅርና ጦርነትን በእኩል ጥፍጥና ከሽኖ የቀረበ የምናብ ውጤት ነበር ማለት ይቻላል ። ቀጥሎ ደግሞ « የሱፍ አበባ» ን አነበብኩ ። የኢህአፓ ዘመንን ድብብቆሽና ፍልሚያ ። ይህም መጽሀፍ ፍልሚያና ፍቅርን ተራ በተራ እንኮኮ ሲያደርግ አይደነቃቀፍም ። በዚህ መጽሀፍ የፖለቲካ ቅኔ ብቻ ሳይሆን የፍልስፍና ጥብብም ሲደንስ ታይቷል -  የሚያምር ብእር ። ለሶስተኛ ግዜ ደግሞ የቄሳር እንባን ።

ደራሲዋች አንዳንዴ ጥሩ ስራ ሲያቀርቡ ሌላ ግዜ ደግሞ ከደረጃ ይወርዳሉ ። በሀብታሙ ስራዋች ላይ የወጥነት ችግር አላየሁም ። በተከታታይ ምርጥ መሆን መታደል ብቻ ሳይሆን ልዩ ችሎታን ይጠቁማል ። የሚያነሳቸው ርእሰ ጉዳዮች ወይም ጭብጦች ትላልቅ ናቸው ። በኢትዮጽያ ስነፅሁፍ ደረጃ ያጣናቸውን ወይም ያልታዩ ክፍተቶችን ነው እየሞላልን የሚገኘው ። ይህ ደራሲ ከምንም በላይ እውቀትን መሰረት አድርጎ ነው የሚጽፈው ። ብዙ ያነበበ ወይም ብዙ ለፍቶ የሚጽፍ መሆኑን ስራዎቹ አፍ አውጥተው ይናገራሉ ። ምናለፋችሁ የደራሲውን ቀሪ ስራዋች ማለትም ‹ ታላቁ ተቃርኖ › እና ‹ አንፋሮ ›ን ለማንበብ ቸኩያለሁ ።