Tuesday, March 25, 2014

ወደ ባልዲው ነዎት ወደ ተራራ ?


እህል ውሃዬ አዲስ ዘመን በነበረ አንድ ቀን ድድ ማስጫ የምንላት ቦታ ላይ ገሚሳችን የተበላሹ ሞተር ሳይክሎች ወገብ ላይ ፊጥ ብለን  ሌሎች እንደቆሙ ክፉ ደጉን እንቀድ ነበር ። አንዱ ደራሲ ወደቢሮ እየመጣ ነው ። ቢሮ ለመግባት ድድ ማሰጫውን ማለፍ አለበት ። ለካስ አንዱ ደራሲ አትኩሮ እየተመለከተው ኖሯል « እዩት እስኪ » አለን በአገጩ ወደ ሰውየው እየጠቆመን « የተገለበጠ ኤሊ አይመስልም ? » ያልጠበቅነውን ተረብ መሃላችን ዘረገፈው ። በአንድ በኩል ድንጋጤ ቢወረንም በአካባቢው ታላቅ ነውጥ የፈጠረውን ሳቅ መቆጣጠር አልቻልንም ። የተበላሹት ሞተሮቹ ሳይቀሩ ሲንተፋተፉ ተሰማ ።
እኔን በወቅቱ የገረመኝ እንዴት አሰበው ? የሚለው ጥያቄ ነበር ። መጀመሪያ ኤሊዋን አመጣት ፣ ይህ አልበቃው ብሎት ገለበጣት ። የተረገመ ! ከዚያ በኃላማ ለተወሰነ ግዜ ተቸግሬ ነበር - ሰውየውን ባየሁት ቁጥር ምስሉ እየመጣብኝ ። ዛሬ አንደኛው በኢትዮጽያ ምድር የለም ፣ ሌላኛው በመላው ዓለም አይገኝም ። ፓ ! ሁለቱም ታዲያ ምርጦች ነበሩ ።
አዲስ ዘመንን « የስጋ መጠቅለያ » እያሉ ቁምስቅሉን የሚያሳዩት ጸሀፊዎጭ ይኀው ተረብ አላጠግብ ብሏቸው አንዱን ደራሲና ባልደረባችንን « ወደ ስምንተኛው ገጽ ይዞራል ፊት » ማለታቸውን የሰማንና ያነበብን ግዜም እንዲሁ ለአንድ ሳምንት በሳቅ ተንፈቅፍቀናል - ሞራል ቢገርፍም መሳቅ ጥሩ ነው በሚል ። የጥንት ቻይናዊያን የሰው ልጆችን ፊት በመመልከት መተረብ ብቻ ሳይሆን ውስጣዊና ውጫዊ ባህሪያትንም ይተነትኑበት ነበር ። ንጉስ ሲን - ቺ - ዋንግ / 221 BC / ፊትን የማንበብ ጥበብ ተጽዕኖ አሳድሮበት እንደነበር ድርሳናት ያስረዳሉ ። የፈት ቅርጾች በስያሜ ተከፋፍለው የተቀመጡ ሲሆን አጠቃላይ የሆነ ምንባብም አላቸው ። ይህ አጠቃላይ ምንባብ የሚዘረዘረው ደግሞ ፊት ላይ ያሉት አነስተኛ አካላት ሲመረመሩ ነው ። በዚህ ረገድ ግንባር ፣ ሽፋሽፍት፣ አይን ፣ አፍንጫ፣ ጥርስ ፣ ጉንጭ ፣ ከንፈር ፣ ጀሮና አገጭ ምን ሲመስሉ ምን እንደሆኑ የሚያብራሩ ብይኖች ተቀምጠዋል ። ለምሳሌ በጋዜጠኞችም ሆነ በኪነጥበብ ሰዋች ብዙ ያልተዘመረለት ሽፋሽፍት ስስ ሲሆን ምን ማለት ነው ...  ወፍራም ሲሆንስ ? ሲራራቅ ... ሲገጥም ? የጨረቃ ቅርጽ ሲይዝ ... ትሪያንግል ሲመስል ? ቀጥ ሲል ... ሲንጨባረር ? ወደላይ ሲሰቀል ... ወደታች ሲደፋ ? አንድም እንዲህ የሆነበት አንድም ያዘለውን ትርጉም ለቀቅ ባለ መልኩ ያጫውቱናል ። ሌሎቹንም እንዲሁ ።
ይሄን ሁሉ የሚያወራውን መጽሀፍ  ያነበብኩት ባለፈው ሳምንት ነው ። ከዚያ በፊት ቤንጃሚን ዚፋኒያ የተባለ ጸሀፊ የኤርትራና ኢትዮጽያ ዜግነት ያለው የአንድ ቤተሰብ ቡድን በባድመ ጦርነት በሁለቱም ሀገሮች መንግስትና ህዝብ የደረሰበትን ድርብ ሰቆቃና ፈታኝ ህይወት በሚያስተክዝ መልኩ Refugee Boy በሚል ርዕስ ጽፎት አንብቤው ድብርት ወስጥ ነበርኩ - ግሩም ስራ ነው ።  ቀጣዩ መጽሀፍ ይህን የሚኮሰኩስ ስሜት ነበር በፈገግታ ብሩሽ ማሰማመር የቻለው « The Secret Language of Your Face » ይባላል ። ፈልገው ቢያነቡት ይዝናኑበታል ። ራስዎትንና ጔደኞችዎን መስታውት ውስጥ በማስገባትም ማነጻጸር ይችላሉ ። ያለማመን መብትዎ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው ። ለዛሬ ግን መጽሀፉ ስለፊታችን የሚለውን ብናነብስ ?
ጨረቃ ፊት ፣

ትልቅና ክብ ጭንቅላት አላቸው ። የጨረቃ ፊት ያላቸው ሰዎች ልፍስፍነት ፣ ንቁ ተሳታፊ ያለመሆንና እንደነገሩ መልበስ ይታይባቸዋል ። ብዙ በመብላትና በመጠጣት ደስታን መፍጠር ይፈልጋሉ ። ደረጃቸው ዝቅ ያሉ ምግቦችን ሁሉ በመውሰድ የሚታወቁ መሆኑ ብዙ ሊያስገርም አይችልም ። ያገኙትን ገቢ በማድረጋቸው የኃላ ኃላ ለአስቸጋሪ ክብደት መጨመርና ዘርጣጣነት  ይዳረጋሉ ።
ልዩ ክህሎታቸው ከሰዎች ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት ዲፕሎማት ሆነው መፈጠራቸው ነው ። በስራ ረገድ ወንዱ ጨረቃ ፊት ጥሩ የንግድ ሰው ይወጣዋል ። ፈጣን የገበያ ልውውጥና ውጤት በሚያሳዩት አይነቶቹ ስራ ላይ እንጂ ትላልቅ ስራዎች ውስጥ ኃላፊነት ወስደው ለመግባት ጠርጣራ ናቸው ። ሴቷ ጨረቃ ፊት በስራ ረገድ ግዴለሽነት ይታይባታል ። ጥቅሞቿን በመከታተልና በመቆጣጠር ረገድ ዝንጉ ናት ፣ የዚህም ዋናው ምክንያቱ ስለራሷ ለማሰብ ረጅም ግዜ የምታጠፋ በመሆኑ ነው ። ስለሆነም ከፍ ባለ አስተዳደራዊ ስራ ላይ ለመገኘት አትችልም ።
ከግል ህይወት አንጻር የተናጥል ኑሮን መምራት ያስደስታቸዋል ። ወንዶቹም ሆነ ሴቶቹ እስከ አርባዎቹ ድረስ ትዳር ላይዙ ይችላሉ ። የዚህ መነሻው ደግሞ በወጣትነት ግዜያቸው ተቃራኒ ጾታን ችላ ብለው ማሳለፋቸው ነው ።
ብረት ፊት ፣
ሁለት አይነት ብረት ፊቶች አሉ ። አንደኞቹ አጭር ፊትና የሞላ ጉንጭ ያላቸው ናቸው ። አነዚህኞቹ ጤናቸው የማያስተማምን ሲሆን በተለይም በሆድ ችግር ይጠቃሉ ። ሁለተኞቹ ረጅም ፊት ያላቸው ሲሆን ቁመታቸውም ከስድስት ኢንች ሊበልጥ ይችላል ። በባህሪ ረገድ ራስ ወዳድነትና ከነገሮች ጋር አብሮ ያለመሄድ እንከን ይታይባቸዋል ። ብረት ፊቶች ለፍትህና ትክክል ነው ብለው ላለመኑበት ጉዳዮች መስዋዕትነት ከመክፈል ወደ ኃላ አይሉም ። ራሳቸውን እንደማስገረምና ማስደነቅ የሚያስደስታቸው ነገር የለም ። ሌላው ቢቀር ሰዎችን ሰብሰብ አድርገው በቀልዶቻቸው እንዲደሰቱ ማድረግ ያስፈነጥዛቸዋል ።
ጥሩ የሚባል እውቀት ቢኖራቸውም ራሳቸውን የሚመሩት በደመነፍስ ነው ጥሪታቸውን ያለስጋትና ፍርሃት እንዴት ማዋል እንደሚገባቸው ቢያውቁም አሁንም የሚያዳምጡት እውቀታቸውን ሳይሆን ደመነፍሳቸውን ነው   ፖለቲከኛና የህግ ሰው የመሆን ዝንባሌያቸው የላቀ ነው ። በአማካኙም ይህን የመሰለ ፊት ያላቸውን ሰዎች ፍርድ ቤቶችና ፓርላማ አካባቢ መታዘብ ቀላል ነው ።
ጄድ ፊት ፣

የተመጣጠነና አይን ግቡ የሆነ ገጽታ ያላቸው ሲሆን ጉንጫቸው አካባቢ የክብነት ቅርጽ ይታይባቸዋል ። ሴት ጄድ ፊቶች ከአንድ በላይ የሆነ መታጠቢያ ክፍል እንዲኖራቸው ቢፈልጉ አይገርምም ። ምክንያቱም ክፍሎቹ ቁንጅናና ስነውበትን የሚያደምቁ ቁሳቁሶች የሚሞሉበት ስለሆነ ።
እነዚህ ሰዎች ለህይወት ያላቸው አመለካከት ቀናማ ሲሆን ስሜታቸውን በፍጥነት ለማሳየት ወደኃላ አይሉም ። ሴቶቹ ትልቅ ትጋትና ጥረት ስላላቸው በማህበራዊ ህይወት ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ ይደርሳሉ ። ይሁን እንጂ ማህበረሰቡ እብሪተኛ ወይም ይሉኝታ ቢስ በሚል ያልተገባ ሀሜት ያቆስላቸዋል ። ጄድ ፊቶች በስራ ረገድ ከፍተኛ ችግርና ውጤት ሲያጋጥማቸው እንኴ ተስፋ አይቆርጡም - እድሜ ለጠንካራ አቅማቸው ።
ወንድ ጄድ ፊቶች ከፍተኛ የሆነ የሀገር ፍቅር ስሜት አላቸው ። ለዚህም ይመስላል ብዙዎቹ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ የሚገኙት ። የፍቅር ግንኙነትን በተመለከተ ተጣማሪያቸው ከፍተኛ ፍቅርና እንክብካቤ እንዲያደርግላቸው ይሻሉ ። ይህ ፍቅራዊ ስሜት ካልተሟላ ሀዘናቸው ወዲያው ነው የሚታየው ።
ባልዲ ፊት ፣
 
ባልዲ ፊቶች ውሃ ፊትም በመባል ይታወቃሉ ። የሰፊ ግንባርና ትኩረት ሰራቂ አይን ባለቤት ናቸው ። ያላቸውን እውቀት በመጠቀም የሚከበር ውጤት ይጨብጣሉ ። ይሁን እንጂ በሀዘንና ትካዜ የተከበበ ህይወትም ይኖራሉ ፣ በዚህ ወቅት ውጤታማነታቸው በፍጥነት እያሽቆለቆለ ይወርዳል ። ከዚህ አሉታዊ ስሜት ውስጥ ለማውጣት የሚታገል ሰው ቢኖር እንኴ  ጥረቱ በቀላሉ እውን የሚሆን አይደለም ።
በቅርብ ጠጋ ብሎ ውስጣቸውን ለመረዳትም ረጅም ግዜያትን ይጠይቃል ። ባልዲ ፊቶች ብዙ ጔደኞች አሉን ብለው ቢያስቡም ይህን ጥበብ ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ ከሌላቸው አቅም ጋር ብዙ ግዜ ይጋጭባቸዋል ። ሴቶቹም እንዲሁ የፈጣሪነት ጸጋ የተላበሱ ናቸው ። ይህን ጸጋ በትክክል መጠቀም ከቻሉ በተለይም መድረክ ላይ በሚሰሩ ስራዎች ስመጥር ሊሆኑ ይችላሉ ።
ፋየር ፊት ፣

እንቁላል የመሰለ ጭንቅላት ፣ ሰፊ ግንባርና የሾለ አገጭ አላቸው ። እውቀታቸው የላቀና አስገራሚ ነው ። ባህሪያቸውም ተለዋዋጭ ነው ። ብዙ ግዜም በበርካታ ሀሳቦች የሚንተከተኩ ሲሆን ወደ ተግባር ለመለወጥም ጥረት ያደርጋሉ ።
የበርካታ አዎንታዊ ዝንባሌ ባለቤቶች ቢሆኑም ሁልግዜም ከመጥፎ ሰዎች ጋር በጔደኝነት ይወድቃሉ ። ይህም የሚሆነው ሰዎችን የሚያነቡት በውጫዊ ገጽታቸው ብቻ በመሆኑ ነው ። ከፍተኛ ችግራቸው ግን እፍረት የማያውቀው የማጋነን ባህሪያቸው ነው ። ፈጣን ብቃት ቢኖራቸውም አንዳንዴ የስልጣን ረሃባቸውን በግልጽ እስከማየት ሊደርሱ ይችላሉ ።
ፋየር ፊቶች የፍቅር ስሜታቸውንና ምኞታቸውን በመግለጽ ረገድ ችግር ያጋጥማቸዋል ። ይህን በቅጡ ከመረዳት ይልቅ በፍቅር ህይወት ረጅም ግንኙነት የሚያሳልፉት ሌሎች ናቸው በማለት እድላቸውን ይወቅሳሉ ። ይሁን እንጂ ዘግይተውም ቢሆን ጥልቅ ፍቅር እንዲያጡ መሰረት የሚሆናቸው የራሳቸው ተጠራጣሪነት መሆኑን ይቀበላሉ ።
መሬት ፊት ፣


ግንባራቸው ጠበብ ብሎ ጉንጭ አካባቢ ሰፋ ይላሉ ። መሬት ፊቶች ምስቅልቅል ባለ አቌም የሚገለጹ ናቸው ። በመጠኑም ቢሆን በፍቅር እጦት ያደጉ በመሆኑ ሊሆን ይችላል ። አክብሮት የማያሳዩ ሲሆን ምላሽ የሚሰጡትም ስርዓትን በጣሰ መልኩ ነው ። አንዳንዴም ስድብንና ኃይልን ከመጠቀም ወደ ኃላ አይሉም ። በዚህም ምክንያት ብዙ ግዜ ጔደኝነትን ለመመስረት ይቸገራሉ ።
ሊጠቀስ የሚችለው አዎንታዊ ባህሪያቸው ታላቅ የእውቀት ጥማት ያለባቸው መሆኑና ይህን ችሎታ በተግባር ለማስደገፍ በትዕግስት የመጠበቅ ዝግጁነታቸው ነው ። መሬት ፊቶች ከተጣማሪያቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት በግንፍልተኝነት የሚገለጽ ነው ።  ብዙ ግዜም በሰላም አውለኝን ከመግለጽ ይልቅ በቁጣ አለመስማማትን መግለጽ እለታዊ አጀንዳቸው ይመስላል ። ነገር ግን ሁለት ተቃራኒ መሬት ፊቶች በፍቅር የሚወድቁ ከሆነ አለምን ለመቀየር አያመነቱም ።
ግድግዳ ፊት ፣

ከግንባራቸው እስከ አገጫቸው ያለው ርቀት በጣም አጭር ነው ። ነገር ግን ፊታቸው ከጃልሜዳ ይዛመዳል - ሰፊና ደልዳላ ነው ። በል ያላቸው ግዜ ጠንክረው ይሰራሉ ። ነገር ግን ገልጃጃ የሚመስለው ጠባያቸው ወደ ስንፍናና ጭንቀት እንዲያመሩም ተጽዕኖ ይፈጥራል ። ለምሳሌ ጠንካራ ችግር በገጠማቸው ግዜ ራሳቸውን መቆጣጠር አይችሉም ። ይህም ነገሮችን ጠርጣሪዎች በመሆናቸው የሚፈጠር ሲሆን ትዕግስት አልባም ይሆናሉ ።
እንደዚህ አይነት ሰዎች ሃሳባቸውን ወደ ተግባር የመለወጥ ችሎታ ያንሳቸዋል ። ግድግዳ ፊቶች በፍጹም ባለስልጣን መሆናቸው ጥቅም የለውም ። ይሁን እንጂ በአንድ የሆነ ምክንያት ውስጣቸው ያለውን አቅም ጥቅም ላይ ማዋል ከቻሉ በጣም ታዋቂና የመገናኛ ብዙሃን ከከቦች ነው የሚሆኑት ።
በቤተሰብ ውስጥ ችግር ከተፈጠረ በአክብሮት የሚበረከተው ቀይ አበባም ሆነ ፍቅሩ እንዳይሞት የሚደረጉ ቃል የመግባት ስርዓቶች የተጋረጠውን አደጋ ፈቀቅ አያደርጉትም ። ግድግዳ ፊቶች ያለውን ግንኙነት ጠግኖ ወይም አጠናክሮ ጥቅም ላይ ከማዋል ይልቅ በእድላቸው በማለቃቀስ ሌላ ፍቅረኛ መፈለግን ይመርጣሉ ።
ተራራ ፊት ፣

ግንባራቸው ወደ ላይ እየጠበበ የሚወጣ ሲሆን በተቃራነው ጉንጫቸው ከመሬት ፊቶች የበለጠ ሰፊ ነው ። በወጣትነት ዘመን ያሳለፉት ግዜ ብዙም አርኪ ባለመሆኑ ፣ ከቤተሰብ ጋር የነበራቸው ቁርኝት ልል ስለነበር እንዲሁም በአቅም ውስንነታቸው ምክንያት የረባ ጔደኝነት ለመመስረት ሲያስቸግራቸው የቆየ ነው ።
ደካማ ጎናቸውን የሚቀበሉ ከሆነ ግን ውጤታማ ለመሆን ቅርብ ናቸው ። ለሚሰሩት እያንዳንዱ ነገር ክብርና ዋጋ ይፈልጋሉ ። ጠብ ጫሪታቸው ግን እንደ ማስታወቂያ አደባባይ የወጣ ነው ። በማህበራዊ ተሳትፎ ውስጥም የሚገኙት በጣም ውስን በሆነ ግዜ ነው ። ገለልተኛ መሆን ይፈልጋሉ ። በተለይም ሀሜትን ለመራቅ ጥረት ያደርጋሉ ። ተራራ ፊቶች ወደ ግንኙነት የሚገቡት በገንዘብ ድጋፍ ቃል ሲገባላቸው ብቻ ነው ።
ያልተመዛዘነ ፊት ፣

ብዙ ሰዎች ያልተመዛዘነ የፊት ገጽታ አላቸው ። ለምሳሌ ያህል ግማሹ የፊት ገጽታ ከሌላኛው ረጅም ወይም ሰፊ ሊሆን ይችላል ። ወይም ደግሞ አፍ ወይም አፍንጫ የተጣመመ ይሆናል ። ቻይናዎች ያልተመዛዘነ የፊት ቅርጽ ውጫዊ ማንነትን ብቻ ሳይሆን የውስጣዊ ገጽታችንም መስተዋት ነው ባዮች ናቸው ።
ያልተመዛዘነ ፊት ያላቸው ሰዎች ከፍተኛ የሆነ የፋሽን ፍላጎት አላቸው ። ገንዘብ ያባክናሉ ። ስራቸውን ግን በአግባቡ ያከናውናሉ ። የተዝናና የፍቅር ህይወት መምራት የትርፍ ግዜያቸው አቢይ ተግባር ይመስላል ። በቀላሉ ከተቃራኒ ጾታዎች ጋር መግባባት ይችላሉ ። አንዱ ቢያልቅ ወይም ባይሳካ እንኴ ቀጣዩን ለመያዝ ብዙ አይቸገሩም ። ደሞ ለሴት ... ደሞ ለወንድ የሚሉ አይነት መሆናቸው ነው ። ይሁን እንጂ ማንኛውም ሰው ሌላው ቀርቶ ራሳቸው ያልተመዛዘኑ ፊቶች ጋብቻ ለምን እንደማይሳካላቸው ወይም ለምን እንደማይስማማቸው አያውቁም ።
እህስ የለመዱትን አይነት ገደል ፊት ፣ ጅብ ፊት ፣ ጨ ፊት ፣ ፈረስ ፊት ወዘተ አላገኙትም ወይስ ተጠማዞ ነው የመጣው ? እስኪ ፊትዋን አትኩረው ይመልከቱት ... ማንም ቦሃቃ ፊት ተነስቶ ሽልጦ ወይም ተራራ ፊት ቢልዋት ፊትዋ ለራስዋ የማይጠገብና ውብ ነው ...


Tuesday, March 11, 2014

እረኞቹ ምን እያደረጉ ነው ?





ፓሰተር የሚለው ቃል ምንጩ ላቲን ሲሆን ትርጔሜውም ጠባቂ ወይም እረኛ ማለት ነው ። እረኛ የሚለው ቃል በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ 27 ግዜ ተጠቅሷል ።
በሀዲስ ኪዳን መጻህፍት ውስጥም በተለይም ወደ ኦፌሶን ሰዎች/ 4 ፡ 11 / በሀዋርያት ስራ / 20 ፡ 28 / እና የጼጥሮስ መልዕክት / 5 ፡ 2/ ላይ ፓስተር የሚለው ቃል ከመምህርነት ጋር ተያይዞ ቀርቧል ማለት ያስደፍራል ። ለአብነት ያህል በሀዋርያት ስራ ላይ « የእግዚአብሄርን ቤተክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጻጻሳት አድርጎ ለሾመበት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ » የሚለውን ጥቅስ እናነባለን ። በሌሎቹ ጥቅሶች ላይ ደግሞ መንጋውን ጠብቁ የሚላቸው ሽማግሌዎችንና አስተማሪዎችን ነው ።
ዞሮ ዞሮ በፈጣሪ ትልቅ ቦታ የተሰጣቸው ቄሶችም እንበላቸው ፓስተሮች የእግዚአብሄርን መንጋ እንዲጠብቁ ከፍተኛ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል ። በጼጥሮስ መልዕክት ምዕራፍ 5 ላይ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ የሚለውን ሀረግም ለዚህ አባባላችን ማጠናከሪያ መጠቀም እንችላለን ። ታዲያ እረኞቹ ምን እያደረጉ ነው ? እያስተማሩም እየተመራመሩም ... እያገዱም እያንጋደዱም ይመስላል ። በተለይ በአንዳንዶቹ ላይ
አፈንጋጭነት ፣
ራስን ቅዱስ አድርጎ መሾም
እና ያልተገባ ተግባር መፈጸም በተደጋጋሚ እየታየ ነው ። የጥቂት ወራቶችን ጥቂት አስገራሚ አብነቶችን እየመዘዝን ለምን ቆይታ አናደርግም ? በጣም ጥሩ ...
ደቡብ አፍሪካዊያኑን ፓስተር ሌሴጎ ዳንኤልን እንመልከት ። በቅርቡ « እግዚአብሄርን መቅረብ ከፈለጋችሁ ሳር ብሉ » የሚል ትዕዛዝ በማስተላለፉ ጉባኤተኛው ሳሩን ሲያሻምደው ውሏል ። አንዳንዶቹ ታመው ወደ ሆስፒታል ቢሄዱም አንዳንዶቹ የፓስተሩን ተግባር ደግፈው ሲከራከሩ ነበር « የፈጣሪ ኃያልነትን ማሳያ በመሆኑ ሳር በመብላታችን እንኮራለን ፣ ማንኛውንም ነገር እናደርጋለን » ብላለች አንዲት የህግ ተማሪ
እንግዲህ ይህ ፓስተር ትዕዛዙን የፈጸመው መንፈስ ቅዱስ በራዕይ ተገልጦለት መሆኑ ነው ። በከፋ የረሃብ ዘመን የሰው ልጆች ህይወታቸውን ለማቆየት ርስ በርስ ከመበላላት አልፎ ተሞክረው የማያውቁ ስራስሮችን ለጠኔ ማስታገሻነት ሙከራ አድርገዋል ። በመጽሀፍ ቅዱስ ታሪክም እንደ በሬ ሳር እንዲበላ የተፈረደበት ንጉስ ናቡከደነጾር ነበር ። እሱም ለዚህ ቅጣት ያደረሰው ስልሳ ክንድ የሚያህል የወርቅ ምስል አሰርቶ ለምስሉ እንዲሰግዱ የታዘዘውን አዋጅ የተላለፉ ሰዎችን በግፍ በእሳት በማቃጠሉ ነው ። ስለዚህ < ሳር > የቅጣት ምልክት እንጂ የፈጣሪ መቅረቢያ ስጦታ አይደለም ። የሰው ልጅ አንጀት ሊፈጨው የማይችለውና መጠነኛ መርዛማ ባህሪ ያለውን ሳር መመገብ ሳይንስም አይቀበለውም ።
ባለሁለት እግራሙ የሰው ልጅ ቀሪውን ሁለት እግር ከእጁ ተበድሮ እንደ በግ ሳር ሲግጥ ማየት ሞራላዊና ተፈጥሯዊ ውድቀት ነው ። በዚህ ስሌት ባልታሰበ ሰዓት ሽንት እያሸተተ እንደ በግ ሲያገጥና አባሮሽ ሲጫወት ማየት ይቻላል ። የፓስተሩ የፈጣሪ መቅረብ እሳቤ ሳርን ለአንድ ቀን እንደ ስለት ጧፍ አብርቶ ለማምኖ መለያየትን ብቻ የሚያሳይ አይመስልም ። ምናልባትም ከጥቂት ወራቶች በኃላ ደፋር ነውና  « በግ » ስለሆናችሁ ቤዛነትንም እንለማመድ ብሎ ካራ ሊያስታጥቅ ይችላል ። ይህን የሚደግፍ አንቀጽ ደግሞ አያጣም ። ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 22 ፡ 1 – 2  እንዲህ ይላል « የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሀቅን ይዘህ ወደ ሞሪያም ምድር ሂድ ፣ እኔም በምነግረህ በአንድ ተራራ ላይ በዚያ መስዋዕት አድርገህ ሰዋው » ፓስተር ሌሶጎ እኔ የአብርሃም እናንተ ደግሞ የይስሀቅ ምሳሌ መሆናችሁን አትዘንጉ ካለ የህግ ተማሪዋን ጨምሮ ሌሎቹም ድጋፍ ከመስጠት ወደ ኃላ አይሉም ማለት ነው ።
የኬንያው ፓስተር ኖሂ « ሃይማኖታዊ » ግኝት ደግሞ የሴቶች አለባበስ ላይ ያተኮረ ነው ። ፓስተሩ አንድ ቀን በ « lord ‘s propeller redemption church » የሚታደሙ ሴቶች በሙሉ ፓንት ማድረግ የለባቸውም ሲል ትዕዛዝ ሰጠ ። ምክንያት ሲባል ቅዱስ መንፈስን ለማቅረብ ፣ በአጠቃላይ አምልኮ ከጭንቅላትና ከሰውነት ነጻ ሆኖ ማሰብን ስለሚፈልግ የውስጥ ቁምጣቸውን ቤት ትተው መምጣት ይኖርባቸዋል ።
የፓስተሩን ግኝት የመነሻና መድረሻ ክር ይዤ ለማገናኘት ሌት ተቀን ብማስን ውሉን ማግኘት አልቻልኩም ።
ምን ለማለት ፈልጎ ነው ?
ከምን አንጻር ተመልክቶት ይሆን ? መንፈስ ቅዱስ የህሊናችንን በር ሲያንኴኴ ቶሎ የማናዳምጠው ፓንት መጥፎ ጋርድ እየሆነ ነው ? የሚል አስመስሎበታል ። ይህ ቦታ ከነስሙ « ሃፍረተ » እንጂ « ቤተልሄም » ወይም « ጎለጎታ » አይደለም ።
ታዲያ እንዴት መረጠው ? በጣም የሚያስደንቀው ደግሞ የፓንት ማውለቁ ትዕዛዝ ወንዶችን የማይመለከት መሆኑ ነው ።
ለነገሩ የአሜሪካዊውን ፓስተር አለን ፓርከር ግኝት ብናዳምጥ የላይኛውን « እረ ይሻላል » ማለታችን ይጠበቃል ። በቨርጂኒያ የ « white tail chapel » መሪ የሆኑት ፓስተር ትዕዛዝ ደግሞ ጉባኤተኛው ስብሰባውን ራቁቱን ሆኖ እንዲከታተል መገፋፋት ነው ።
የጼጥሮስ መልዕክት ምዕራፍ አምስት « ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ » ተፈጻሚ ይሆን ዘንድም ፓስተሩ ራቁታቸውን በመሆን ትምህርት ሰጥተዋል ። እረ ጥንዶችንም ለጋብቻ ራቁታቸውን  አማምለዋል ። ከተወለድን ከጥቂት ወራት በኃላ እረኞች ለክርስትናችን ውሃ ውስጥ ፣ እናቶች ለመጪው ህይወታችን ተድላ እንጀራ ላይ ሊያንከባልሉን እንደሚችሉ ነው መረጃው ያለን ። ይኀው ቃልኪዳንም የጸና ማህተም ይፈጥርልናል ብለን ነው ተስፋ የምናደርገው ። አድገን በውሃ የተረጨነውንም ሆነ እንጀራ ላይ « ግፍ » ሳይሆንብን የተንደባለልነውን ፎቶ ስንመለከት ያረካናል ። ራቁትነት የንጹህነት ፣ የፍጥረት መነሻነት ነው ብለን ልንወስደውም እንችላለን ። በትናንት ንጹህነትና በዛሬ ተጨባጭ ማንነታችን መሃል ያለውን አንድነትና ልዩነት ለማነጻጸርም ይረዳል ።
በጉርምስና እና በጉልምስና ወቅት ራቁታችንን የምንቀበለው ቃልኪዳን ልብስ ለብሰን ከምናደርገው ጋር በምን እንደሚለያይ ግልጽ አይደለም ። ተምሳሌትነቱም ስውር ወይም ድፍን ነው ። በራቁትነት ለመደናነቅ ከሆነ ባልና ሚስቱ በመኝታ ፣ በሻወር በወዘተ ግዜ የሚያገኙት ነው ። ይህን ለማድረግ ደግሞ አይተፋፈሩም ። ህግ የተላለፉት አዳምና ሄዋን የደረሰባቸውን የእፍረት መሸማቀቅ ይሄ ትውልድ ያካክሰዋል ነው የሚሉት - ፓስተሩ ? በጋብቻ ማግስት እየፈረሰ ያስቸገረውን ትዳር ለማጽናት ይሄኛውን ዘዴ እንሞክረው ነው የሚሉት - እረኛው ?
የኚህ ፓስተር ግኝት ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮችን የሚዳስስ ነው ። የመጀመሪያው  ጉባኤተኛው ሁሉ ራቁቱን መማር ከቻለ ሁሉም የሰው ልጆች እኩል መሆናቸውን ያሳያል የሚል ነው ። ርግጥ ነው ሰዎች በሚለብሱት ፣ በሚያጌጡበትና በሚጠቀሙባቸው ዕለታዊ ቁሶች የኑሮ ደረጃቸው ሊገመት ይችላል ። ችግሩ ይኀው ጉዳይ የሰዎችን ውስጣዊ ማንነት ፣ ጥንካሬ ፣ ባህሪ ፣ አስተሳሰብ እና ፍልስፍና በፍጹም ሊያሳይ አለመቻሉን ፓስተሩ የተረዱ አለመምሰላቸው ነው ወይም ባላወቀ ተራምደው ማለፋቸውም ይሆናል ።
ሁለተኛው መነሻቸው ቤተክርስቲያን በምሳሌ ማስተማር ይኖርባታል ከሚል ሀሳብ ይመነጫል ። ክርስቶስ ሲወለድም ሲሰቀልም ራቁቱን ነበር ያሉት ፓስተሩ ፈጣሪ በዛ መልክ ካሳየን እኔ እንዴት ነው ስህተት የምሆነው በማለት ሲኤንኤንን ሞግተዋል ። በርግጥ እድሜ ለአዳምና ሄዋን እንጂ ዛሬ የሰው ዘር በሙሉ መላመላውን ነበር ታች ላይ የሚለው ። ሆኖም እንደ ፓስተር አለን በመምህርነቱ የሚታወቀው እየሱስ በገጠር ፣ በከተማ ፣ በመንደር ፣ በገበያ ስፍራና በመስበኪያ ቦታዎች ሁሉ እየተዘዋወረ ያስተማረው ራቁቱን ሆኖ አይደለም ።
ሌላው ችግር ራቁት ሆኖ ትምህርት መማርና ማስተማር ከባድ ፈተና ላይ በግድ የመውደቅ ያህል መቆጠሩ ነው ። አእምሮ ከምዕራፍና ቁጥሮች ይልቅ ቅርጽንና ከርቮችን ማጥናትና ማድነቅ ላይ ማተከሩ ሳይታለም የተፈታ ነው ። የአካል ንኪኪ ባይፈጠር እንኴ በሃሳብ መመኘትን ለማስቀረት ምን ዋስትና አለ ? እና ራቁትነት ከሌሎች ለመለየትና ጀብዱ ለመፍጠር ካልሆነ በስተቀር ዘለቄታዊ መፍትሄ ነው ብሎ መስበክ ወንዝ የሚያሻግር አይደለም ።
ናይጄሪያዊው ፓስተር ኬንዲ ቦሉዋጂ ያደረገው ምርምር ደግሞ ከፓንት ነጻ በሆነው የሴት ልጅ ብልት ላይ ነው ። ለምርምሩ የተጠቀመባቸው ቁሶች የተፈጨ ጨው ፣ መሃረብና ጸሎት / ድግምት / ናቸው ። የዚህ አይነቱ ፓሰተሮች የሚሰሩትን ውስብስብ ጥናት « pastorization » ብሎ መጥራት ሳይቻል አይቀርም ። ፓስቸራይዜሽን እና ፓስተራይዜሽን ይቀራረቡ እንጂ አይመሳሰሉም ። 
እንደሚታወቀው ፓስቸራይዜሽን ከፈረንሳዊው ቀማሚና ማይክሮ ባዮሎጂስት ሉዊስ ፓስተር ተግባር ጋር የተያያዘ ነው ። በክትባትና እርሾ ዙሪያ ትልቅ ስራ የፈጸመው ሉዊስ ወይን ፣ ቢራና ወትት እንዲቆመጥጥ በሚያደርገው ባክቴሪያ ላይም አንድ ግኝት አፍልቌል ። ባክቴሪያውን ለማጥፋት ፈሳሹን በጣም ማሞቅ ፣ ቀጥሎም በጣም ማቀዝቀዝ የሚለውን ሂደት ነበር ያበረከተው ። ይህም ሂደት « ፓስቸራይዜሽን » ለሚለው ሳይንሳዊ ቃል መወለድ ምክንያት ሆነ ።
ፓስተር ኬንዲም እንግዳ በሆነ መንፈስ የሚሰቃዩ ሴቶች በተለይም አግብተው መውለድ ካልቻሉ ያለግዜያቸው እንደሚሞቱ አወቀ ወይም ተገለጠለት ። መንፈሱ ደግሞ ባል እንዳይገኝ ደንቃራ ይሆናል ። በዚህ ስሌት ተጎድታለች ብሎ ላሰባት አንዲት የ22 ዓመት ወጣት ሴት ጉዳዩን ያጫውታትና መፍትሄውም በእጄ ነው ይላታል ። < ከፈጣሪ በታች እናንተን ነው የምናምነው በእርሶ መጀን > ትላለች ልጅት በልቧ ። ወዲያው ፓስተሩ
 < ያዝ እጇን
  ዝጋ ደጇን >
የተባለውን ኢትዮጽያዊ ዘፈን ተተርጉሞ የሰማው ይመስል ወጣቷን አስገብቶ ክፍሉን ይጠረቅምና  ለምርምሩ ይዘጋጃል ። በገቢር አንድ ልብስዋን አውልቃ እርቃኗን ቁጭ እንድትል ተደረገች ። በገቢር ሁለት ጸሎት ይሁን ድግምት ለደቂቃዎች ማንበልበል ቀጠለ  ። በክፍል ሶስት በነጭ መሃረብ ጨው ካወጣ በኃላ ብልቷ ውስጥ እንድታስገባው ይነግራታል ። ያልተለመደ ነገር ነውና ይተናነቃታል ፣ የሷ ፈራ ተባ ማለት ሂደቱን ሊያጔትተው ስለሚችልና ተግባሩን ለማፋጠን ይቻል ዘንድ ጣቱን ብልቷ ውስጥ ይጨምራል ። በዚህ የሚያበቃ ግን አልሆነም ። ከግራ ወደ ቀኝ ፣ ከቀኝ ወደ ግራ ማማሰል ይጀምራል ። ምናልባት ይኀው ተግባር እንደ ሊዊስ ፓስተር ባክቴሪያ ፣ ክፉ መንፈሱንም ይገድለው ይሆን ? አነጋጋሪ ጉዳይ ነው ። ግራም ነፈሰ ቀኝ  ይህ ሂደት « pastorization » ለሚለው መንፈሳዊ ቃል መወለድ ምክንያት ሆነ ብሎ መሳለቅ ይቻላል ። ዞሮ ዞሮ ፓስተር ኬንዲ ወደ ሌላ ምዕራፍ ከመሸጋገሩ በፊት በሩን ሲጠረቅም አይተው በተጠራጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋል ችሏል ።
አንዳንድ ፓስተሮችም ልክ እንደ እየሱስ ተዓምር መስራት እንችላለን በማለት አሳፋሪ ተግባር ከመስራት አይቆጠቡም ። በዚህ ረገድ ተጠቃሽ የሚሆነው ናይጄሪያዊው ፓስተር ፍራንክ ካቢሌ ነው ።
ራዕይ ስለታየኝ የተአምሩ ታዳሚ ሁኑ በማለት ደቀመዛምሩን ኮምቦ ሃይቅ ሰበሰበ ። ከዚያም ማቲዎስ ምዕራፍ 14ትን በመጠቃቀስ የሰው ልጅ በቂ እምነት ካለው እንደ እየሱስ በውሃ ላይ መራመድ እንደሚችል ማብራሪያ ሰጠ ። በተለምዶ ሃይቁን ለማቌረጥ የሃያ ደቂቃ የጀልባ ጉዞ ማድረግ አስፈላጊ ቢሆንም ፓስተሩ ርቀቱ አላሳሰበውም ።
መቼም በውሃ ላይ እንደባለሞተር ጀርባ እየነጠሩ መራመድ በእጅጉ አስደሳች ነገር መሆን አለበት ። ብዙዎቹ ቢሸበሩም አንዳንዶቹ መምህራቸው የውሃውን ጫፍ በጫማው ሶል እያነጠረ ብዙ ርቀት ሴሄድ ማለም ጀምረው ነበር ። ዞር እያለም እጁን ሲያውለበልብላቸው ለማጨብጨብ ፣ ለማፏጨትና እልልታቸውን ለማቅለጥ ተቁነጥነጥዋል ። ምናልባትም ጫፍ ደርሶ ከመጣ በኃላ ተሰብሳቢውን ለጉዞ ሲጋብዝ ፍርሃት በማየቱ « እናንተ እምነት የጎደላችሁ ስለምን ትጠራጠራላችሁ ? » እንደሚላቸውም ከማሰብ ወደ ኃላ አላሉም ።
እውነት ነው ፓሰተሩ ጉዞ ጀመረ ለማለት እንኴ ይከብዳል ። በሁለተኛው ርምጃ ሰውነቱ ሰመጠ - በፍጹም ወደ ደቀመዛምሩም አልተመለሰም ። ምዕመናኑ በድንጋጤ ተውጠው « RIP » ለማለት እንኴ አልታደሉም ነበር ። እኔ ግን አሁን ትዝ ያለኝ የእንግሊዛዊው ገጣሚ ዊሊያም ኮስሞ ሞንክሃውስ ግጥም ነበር ። ርዕሱ There was a young lady of niger ይሰኛል ። በአምስት ስንኞች ጣጣውን የጨረሰውን ግጥም እነሆ ብያለሁ
There was a young lady of niger
Who smiled as she rode on a tiger
They returned from the ride
With the lady inside ,
And the smile on the face of the tiger .
እውነት እረኞቹ ምን እየፈጸሙ ነው ? ወዴትስ እየተሄደ ነው ? ዮሀንስ ወንጌል 10 ፡ 11 ላይ እየሱስ መልካም እረኛ እኔ ነኝ ፣ መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል ይላል ። ይህ ምሳሌ በሌሎቹም ላይ እንዲጋባ ነበር የተፈለገው ። ግን የምናያቸውና የምንሰማቸው ነገሮች ተስፋ ከመስጠት ይልቅ የሚያስፈሩ እየሆኑ ነው ። ብዙ እረኞች ተኩላና ቀበሮ ለመሆን እየቸኮሉ ይመስላል ።

« መንጋውን ለሚተው ለምናምንቴ እረኛ ወዮለት  ! » የሚለው ቃል የትኛው ትንቢት ላይ ነበር የሚገኘው ?