Wednesday, July 26, 2017

የጣና ነጋሪት መቼ ይጎሰማል ?


የህገ መንግስቱ አንቀጽ 93 የውጭ ወረራ ሲያጋጥም  ፣ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰት ፣ የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የህዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት የሚኒስትሮች ምክር ቤት እና የክልል መስተዳድሮች የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ሊያውጁ እንደሚችሉ ይደነግጋል ።

ከላይ በተገለጸው አንቀጽ ውስጥ አራት መሰረታዊ ሀረጎች ጎልተው ይታያሉ ። የውጭ ወረራ ፣ የስርአት አደጋ ፣ የተፈጥሮ አደጋ እና የጤንነት አደጋ ።

መንግስት እስካሁን የተመቸው ሀረግ የ ‹ ስርአት አደጋ › ነው ። በዚህ ለመጣበት አይደራደርም ። በዚህ የመጣበትን በብዙ ጆሮዎች የመስማትና በብዙ አይኖች የመመልከት ችሎታ አለው ። ይህን አደጋ በወንበር የመማለል አደጋ ይለዋል ። እረ ጥሩ ጥሩ ዘይቤያዊ አነጋገሮችንም ይጠቀማል ። መንግስት እንደ ኢያሪኮ ግንብ በጩኅት አይፈርስም የሚላት ነገር አንደኛዋ ናት ... መንግስት እንደ ሾላ ፍሬ በድንጋይ አይወርድምም ይልሃል ... ሌላም ሌላ ጥብቅ ማሳሰቢያዎች አሉት ። የስርዓቱን አደጋ ለማነቃነቅና ለመጣል የተሞከረን ሀገራዊ ‹ ብጥብጥና ሁከት › ጸጥ ለማድረግ ይቻል ዘንድ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ከታወጀ አያሌ ወራት ተቆጥረዋል ። ይህም የጥብቅ ማሳሰቢያው የመጨረሻ ደረጃ ነው ። ከዛሬ ነገ አዋጁ ይነሳል ሲባል የሰርዓቱ አደጋዎች ቅርጽ እና ይዘታቸውን እየቀየየሩ መፈልፈላቸው አሳሳቢ ነው ። አንዱ በአንዱ ቀለበት ውስጥ እየገባ ዛሬ የግብር አደጋ ተረኛ ጥያቄ ፈጣሪ ሆኗል ። እናም የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ታፍሮና ተፈርቶ ለማይታወቅ ዘመናት ሊውለበለብ ይችላል ።

የአዋጅ ነገር ከተነሳ በተፈጥሮ አደጋም ተጨማሪ ክተት ያስፈልገን ነበር ። መንግስት የሚመቸውን ብቻ አዳማጭ ስለሆነ እንጂ የጣና በእምቦጭ አረም የመወረር አደጋ ምታ ነጋሪት ክተት ሰራዊት የሚታዘዝበት ነበር ።

የመንግስትን ዳተኝነት የገነቡት ብዙ ምከንያቶች ሊሆኑ ቢችሉም ሁለቱን የጎሉ አስተሳሰቦች እንመልከት ። አንደኛው ችግሩን መፍታት ያለበት የክልሉ መንግስት ሲሆን ጉዳዩም ከክልሉ አቅም በላይ የሚዘል አይደለም የሚል ነው ። የክልሉ መንግስት ለበርካታ አመታት ሳይንሳዊ ውጤት ለማምጣት ባዝኗል ። ችግሩን መፍታት ቢኖርበት ይህን ሁሉ አመታት ያለ ተጨባጭ ነገር መራወጥ ባልተገባው ነበር ። እውነታው ግን የምርምርም ሆነ የገንዘብ አቅሙ ተፈላጊውን መፍትሄ ያስገኘለት አለመሆኑ ነው ።

ሁለተኛው መንግስታዊ አመለካከት የጣና ሃይቅ በአረም መወረር በውጭ ወራሪ መወረር አይደለም ወይም የተፈጥሮ አደጋ ነው ብሎ ለመቀበል የሚያስችል መደላድል የለም ከሚል ይመነጫል ። ሲጀመር ህገ መንግስቱ የተፈጥሮ አደጋ ምን ማለት እንደሆነ በግልጽ አላሰፈረም ። ሌላው ቀሮቶ ‹ የህዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት › የሚለው ሀረግ አሻሚና ግልጽነት የሌለው ነው ። በሽታ የሚለው ተላላፊዎችን ነው ... በሽታ የሚለው ግዜ የማይሰጡትን ነው ... በሽታው ኮሌራ ነው ? ኢቦላ ነው ? ማጅራት ገትር ነው ? ... አይታወቅም

በመሆኑም የ « ተፈጥሮ አደጋዋችም » ሆኑ « ጤንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ በሽታዋች» ን እውነተኛ ብይን መረዳት ያስፈልጋል ። የተፈጥሮ አደጋዋች ሰፊ ናቸው ። በአጭሩ ግን ስነ ምድራዊ ፣ ሰነ ውሃዊ ፣ ስነ አየራዊ ፣ ሰደድ እሳት እና የህዋ ጥፋት ብሎ ማሰቀመጥ ይቻላል ። ለአብነት መሬት መንቀጥቀጥን፣ የበረዶ ናዳ እና እሳተ ጎመራን ስነ ምድራዊ ውስጥ እናገኛቸዋለን ። ድርቅና የተለያዩ የአውሎ ንፋስ አደጋዋችን ሰነ አየራዊ ውስጥ ይመደባሉ ። በዚህ ሳይንሳዊ አካሄድ መሰረት የጣና ሃይቅ ችግር ስነ ውሃዊ / Hydrological Disasters / ውስጥ የሚገኝ ይሆናል ።

ሳይንቲስቶች ስነ ውሃዊ አደጋን A Violent , Sudden and destructive change either in the quality of earth’s Water or in the distribution or movement of water on land below the surface or in the atmosphere በማለት ይበይኑታል ።

ህገ መንግስቱ ዝርዝር መግለጫ ስለሌለው ከዚህ በመነሳት ሀሳብ መስጠት ግድ ይላል ። በመሆኑም በጣና ሃይቅ የደረሰው አደጋ የውሃውን መጠን ፣ ጥራትና ፍሰት የሚጎዳ ነው ። በውሃውና በአካባቢው የሚገኙ ስነህይወታዊ ስርአትን ያፋልሳል ። ከሃይቁ ቀጥተኛ የህልውና ትርጉምን እውን በሚያደርገው ማህበረሰብ ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና ይፈጥራል ።

ከዚህ ሁሉ በላይ ጣና የኢትዮጽያ ታላቅ ቅርስ ነው - በባህላዊ ፣ ታሪካዊ ፣ ሰነውበታዊ እና ስነ ምድራዊ ሃብቶች የበለጸገ ። በእኛም ብቻ ሳይሆን በዩኔስኮ ዳኝነት የተመሰከረለት ። እንግዲህ ይህ የሀገርና የአለም ሀብት ነው አደጋ ውስጥ ስለሆነ ምታ ነጋሪት ክተት ሰራዊት ያስፈልገዋል እየተባለ የሚገኘው ።

በቅርቡም ባለሙያዋች እንደገለጹት ሃይቁን ተረባርቦ ማከም ካልተቻለ በአደገኛው አረም ሊጠፋ ይችላል ። ከዚህ የላቀ ምስክርነት ታዲያ ከየት ሊመጣ ይችላል? ይህን አደጋ የተፈጥሮ አደጋ አይደለም ማለት ፣ ይህ አደጋ በህዝብ ሃብትና ማንነት ላይ የተጋረጠ ቀውስ አይደለም ማለት ራስን ከማታለል የሚቆጠር ነው ። እናም አደጋውን ለመቀልበስ በሚደረገው ጥረት መንግስት የዋና ገጸባህሪ ብቻ ሳይሆን የአዘጋጅነቱንም ሚና መጫወት ይኖርበታል ። መንግስት ልግመኛ ካልሆነ በስተቀር ‹ ኩራትም እራትም › ነው የሚለውን በርካታ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በቦታው ቢያሰማራ የማይናቅ ለውጥ ሊመጣ ይችላል ። በነገራችን ላይ መከላከያ ሰራዊት ህዝባዊነቱን እያሳየ ነው  ተብሎ ብዙ ግዜ አረም ሲነቅልና እህል ሲያጭድ በቲቪ ተመልክተናል እኮ ? ታዲያ ምነው እንቦጭን ለመንቀል አልከሰት አለ ?

መንግስት ጣና የሀገር ጉዳይ ነው ብሎ ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት ከሰራ ሀገራዊ መፍትሄ የሚጠፋ አይመስለኝም ። ከአቅም በላይ ከሆነም ወደ ውጭ ለማየት አሁንም የመንግስት አይን ጥቅም አለው ።  ቢያንስ A+ ባለው የእርዳታ ክህሎቱ ‹ ጎበዝ ተባበሩኝ ›  ቢል አውሮፓዋቹ የሚጨክኑ አይመስለኝም - ሌላው ቢቀር ቻይናዊ መፍትሄ አይጠፋም ። ለስርአት አደጋ ብቻ ሳይሆን ቀስ እያለ በተፈጥሮ ሊደርስ የሚችል ጥፋትን ለመከላከል ሳይቃጠል በቅጠል የተሰኘ ፖሊሲ መከተል ብልህነት ነው ።

ጣና የሁላችንም ጉዳይ ነው !

ቢረፍድ እንኳን ለጣና ምታ ነጋሪት ክተት ሰራዊት ያስፈልጋል !

Saturday, July 15, 2017

የአማረ አረጋዊ ልዩ ዋንጫ


አቶ አማረ አረጋዊ የኢትዮጽያ ፕሬስ ባለውለታ መሆናቸውን በማገናዘብ ሰሞኑን የእውቅና ሽልማት አግኝተዋል ። አንዳንዶች አቶ አማረ ከኢትዮጽያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ሽልማት ማግኘታቸውን አልወደዱትም ። ለምን ሲባሉ ሁለት ምክንያቶችን ያቀርባሉ ። የመጀመሪያው ምከር ቤቱ የማይገባውን ስራ በመስራቱ የሚል ነው ። የምክር ቤቱ ቀዳሚ ስራ የፕሬስ ነጻነት እንዲረጋግጥ ብሎም በስርጭት ወቅት ክህዝብ የሚቀርብ አቤቱታ ካጋጠመ እንዲታረም ማድረግ ነው  ። ከዚህ አንጻር አባላትን ለመሸለም የሚያስችል ህጋዊ ማእቀፍ እንደሌለው ይገልጻሉ ።

ሁለተኛው ምክንያት የአመራር አባል የሆነን ግለሰብ መሸለም በሽልማቱ አካሄድ ላይ ተጽእኖ እንዲፈጠር እድሉን ያሰፋል የሚል ነው ። የአቶ አማረ አመራር አባልነት በሽልማቱ አካሄድ ላይ ችግር ይፈጥራል የሚለው ህሳብ እንኳን በቀላሉ ቅቡልና የሚያገኝ አይመስለኝም ። ምክንያቱም የምክር ቤቱ አባላት በበርካታ እውቀት ጠገብ ድርጅቶች የታቀፈ ነው ።  ፎርቹን ፣ አዲስ አድማስ ፣ ሸገር ፣ ኢቢሲ ፣ ዛሚ ፣ ካፒታል ፣ ኢትዮጽያ ፕሬስ ኤጀንሲ ፣ ኢጋማ ፣ ኢትዮ ቻናል ፣ ቁም ነገር እና ሌሎች ማህበራት ይገኙበታል ። ሲጀመር እነዚህ ቡድኖች ጥራት ያለው ማንዋል አይኖራቸውም ማለት ይከብዳል ። ሲለጥቅ በግልጽ ፣ በማያሻማና ዴሞክራት በሆነ መልኩ የፈልጉትን የሚመርጡበት ስነ ሰርዓት ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል ።

የሆኖ ሆኖ አቶ አማረና ድርጅታቸው ከዚህ በፊትም አንድ ሀገራዊ ምርጫ አሸንፈው መጭበርበራቸውን ለሚያውቅ ለእኔ አይነቱ ሰው የአሁኑ ምርጫ አሸናፊነት ብዙም ላያስገርመው ይችላል ።

እንዴት ተጭበረበሩ ?

የቀዳማዊ ሃይለስላሴ የሽልማት ድርጅት ከተረሳ በርካታ አመታት በኋላ በሀገራችን አንድ የሽልማት ድርጅት ተቋቁሞ ነበር ። የኢትዮጽያ ስነጥበባትና መገናኛ ብዙሃን ድርጅት የሚባል ። ይህ ድርጅት በ 1994 ዓም ላካሄደው የሽልማት ተግባር አስቀድሞ ነበር በየዘርፉ ሊዳኙ ይችላሉ ብሎ ያመነባቸውን ግለሰቦች የመረጠው ። እናም የመጀመሪያው ትውውቅ ቀን በስብሰባ ማዕከል ተጠርተን በአቶ እቁባይ በርሄ የአሰራር መግለጫና ወፍራም አደራ ተሰጥቶን በየቡድናችን ስራውን ማሳለጥ ጀመርን ።

ጋዜጠኞችን ለመምረጥ ታሪካዊውን እድል ያገኘነው አምስት አባላት ነበርን ። ስብጥሩ ደግሞ ሁለት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አንጋፋ መምህራን ፣ አንድ የኢቲቪ አንጋፋ ጋዜጠኛ / ከእንግሊዘኛው ክፍል / ፣ አንድ የአትዮጽያ ሬዲዮ አንጋፋ ጋዜጠኛ እና እኔ ነበርን ።

ቢሮአችን ዩኒቨርስቲ ውስጥ ሆኖ ደከመን ሰለቸን ሳንል ተጋን ። ሊቀ መንበራችን ልምድ ያለው ሰው በመሆኑ እንዴት መሄድ እንዳለብንና ምን የተሻለ ስራ ማከናወን እንደሚኖርብን መንገድ አመላካች ነበር ማለት ይቻላል ። መጠይቆች ተሰርተው በመንግስትና በግልሚዲያ ተቋማት ተበተኑ ። የዚህ መጠይቅ ውጤት ተሰብስቦ እስኪቀመር ድረስ ደግሞ በየዘርፉ ያሉ ጋዜጠኞችን መዘርዘር ጀመርን ። የዳኞች ስብጥር ሁሉንም አካባቢ የሚወክል በመሆኑ ብዙም አልተቸገርንም ነበር ። ከዚያም በእያንዳንዱ ጋዜጠኛ ላይ ውይይትና ክርክር ይደረጋል ። ብዙ መቶዎችን ወደ መቶ ፣ መቶዎቹን ወደ ሃምሳ ፣ ሃምሳውን ወደ ቀጣዩ ግማሽ በመውሰድ ለፍጻሜ መድረስ ቻልን ። በመሃሉ ግን ‹ የስነጥበብ ዘርፍ ዳኞች እየጨረሱ ናቸው እናንተ ምን እያደርጋችሁ ነው ? › የሚለው የነ አቶ እቁባይ ጭቅጭቅ እረፍት ነሺ ሆነብን ። የኛ ጥያቄ ታዲያ ‹ በአጭር ግዜ የሚጨርሱት ምን አይነት ስልት ቢከተሉ ነው ? › የሚል ነበር ። በጥራት እሰራለሁ ብሎ ለሚነሳ ቡድን እያንዳንዱን እጩ በተጨባጭ አቅሙን መፈተሽ ግድ ይለዋል ። የራሱን ግምት ብቻ ሳይሆን የባለሙያውን አስተያየት ምርኩዝ ማድረግ ይኖርበታል ። ይህ ደግሞ ግዜ ይፈልጋል ።

በእውነት ከባድና አታካች ስራ ነበር ። ብዙ ግዜም የተሻሉትን ለመምረጥና ለማበላለጥ ስንቸገር ድምጽ መስጠቱ ነበር የሚገላግለን ። እናም በርካታ ወራት ከደከምን በኋላ የተሸላሚዎችን ስም ዝርዝር ከነ ምክንያቱና ማብራሪያው ጽፈን አስረከብን ።

ተጠባቂው ቀን ደረሰ ።

ሸራተን ሆቴል ልዩው ስነ ስርአት ሲካሄድ የመረጥናቸው ሁለት ሰዋች ተሰርዘው የማናውቃቸው ሁለት ጋዜጠኞች ክብሩንና 20ሺ ብሩን በእጃቸው ወሰዱት ፣ በአንገታቸው አጠለቁት ። የእኛ እንገት ግን በሃፍረት፣ በቁጭትና በህዘን አቀረቀረ ። ሁለት ዳኞችን አግኝቼ ስለ ሁኒታው አነጋገርኳቸው - እንደኔ ድንጋጤ አስክሯቸው ነበር ። ያ ሁሉ ልፋታችን ገደል ገባ ። « የዳኞች የመጨረሻ ውሳኔ የመጨረሻ ነው » በተባልነው ዲስኩር ላይ ለማላጋጥ ሞከርኩ - ይህን ማድረግ ግን አልቻልኩም ፤ ምክንያቱም በግልጽ ያላገጠብኝ እሱ መሆኑን ሰለተረዳሁ ።

ለዳኞች የተሳትፎ ወረቀት በሚሰጥበት ቀንም በነበረው አሰራር ላይ ውይይት ስለነበር በአጭበርባሪው ምርጫ ላይ የማላገጥ እድል አገኘሁ ። የተሰማኝን ሁሉ ተነፈስኩ ። ነገር ግን በእኔ ሀሳብ ላይ ምላሽ ወይም አስተያየት የሰጠ አልነበርም ። አንዱ በአንዱ ሲስቅ... እንደማለት ።

በእነ እቁባይ በርሄ ከተሰረዙት ተሸላሚዎች መካከል ብዙ ወንድማገኝ እና ሪፖርተር ጋዜጣ ይገኙበታል ። የተተኩት ደግሞ በኢትዮጽያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ የነበሩት ሳሙኤል ፍቅሬ እና የሃይለራጉኤል ታደሰ ባለቤት የሆነችው ሂሩት ናቸው ።

ያኔ ታዲያ ሪፖርተርን እንደ ጋዜጣ እንዲሸለም ያጨነው ህትመት ላይ ካሉ ጋዜጦች ጋር በማወዳደር ነበር ። ለማወዳደሪያነትም ተነባቢ ፣ አሳታፊ ፣ ወቅታዊ ፣ ተጽእኖ ፈጣሪ የሚሉና ሌሎች የጋዜጠኝነት መርህና መመሪያዎችን መሰረት እድርገናል ። ይህ ማለት የስታፉ ሁለገብ ተሳትፎን ጨምሮ የዋና አዘጋጁ አማረ አረጋዊ ሚና ትልቅ እንደነበር የሚያመላክት ነው ። አቶ አማረ ከ 97 በፊትና በኋላ አንድ አይደለም የሚሉ ሰፊ ሃሳቦች ቢኖሩም ፈተና ለበዛበት የሀገራችን ፕሬስ ያደረገው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ። ትናንት ያጣውን ሽልማት አሁን ማግኝቱ ማስደሰቱ ብቻ ሳይሆን እንደ ልዩ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ።

Tuesday, July 11, 2017

የዘመኑ ሥነ-ግጥም ያነሳውና የጣለው



የፌስ ቡክ ግድግዳ ከሚነግረን አንደኛው ጉዳይ በርካታ ገጣሚያን እያፈራን መሆኑን ነው ። ሰነጽሁፍ በማይበረታታበት ሀገር ወፈ - ሰማይ ስንኝ መታሪያዎች እንደምን ፈለቁ የሚለውን ጥያቄ በቀላሉ ማንሳት ቢቻልም ጥናት ላይ ሳይመሰረቱ ቀላልና የዋዛ ምላሽ ማግኘት አይቻልም ።

ግን ደግሞ ለጸሀፊዎች ወይም ለመስኩ ባለሙያዎች ትልቅ ርዕሰ ጉዳይ የተገኝ ይመስለኛል ። የወጣ መጽሀፍን እያደንኩ በማነብበት ዘመን አታሚዎችም ሆነ አከፋፋዮች ሥነ- ግጥምን ምናምን እንደነካው እቃ አፍንጫቸውን ይዘው ሲያርቁት አውቃለሁ ። ያኔ ብዙዎች እንደ ቀንድ አውጣ ኩምሽሽ ብለው ራሳቸውን ምሽግ ውሰጥ ይከቱ ነበር ።

ዛሬ ተመስገን ነው ። ቀንድ አውጣዎቹ አንገታችውን ስበው እየዳኹ ብቻ ሳይሆን ቢያንስ በፌስ ቡክ ግድግዳ ላይ ክንፍ አውጥተው እየበረሩ ናቸው ። በህትመት ደረጃ የሚታየውን የብዛት መሰላል ግራፍ ለማድረግ የቅርብ አስተውሎት / በርቀት ምክንያት / ባይኖረኝም አሁንም የፌስ ቡክ ግድግዳ የሚነግረኝ ዜና አለ ። ግጥም ጥቂት በማይባል መልኩ እየተመረቀ መሆኑን ።
ታዲያ እነዚህ የግጥም ስራዎች የሚያበስሩን ብዛታቸውን ብቻ ሳይሆን ያነሱትንም የጣሉትንም ጉዳይ ጭምር ነው ። በርግጥ ምን የተለየ ነገር እያነሱ ናቸው ?

1 . የዘመኑ ግጥሞች በሚያነሱት ሀሳብ በእጅጉ የበለጸጉ ናቸው ። ያልታሰቡና ያልተገመቱ ርዕሰ ጉዳዮችን ፈልፍለው በማውጣት በደማቅ ሲጽፏቸው እንመለከታለን ። ይህ የሚያሳየው ገጣሚው የመጻፊያ ርዕስ ችግር የሌለበት መሆኑን ነው ። ርዕስ ለመምረጥ አምስቱንም የስሜት ህዋሳቶች በደንብ ይጠቀማሉ ።

ከወደቀ ግዙፍ ግንድ ላይ የሚያማመሩ ጉማጆችን ለማውጣት በጭፍኑ አይደለም መጥረቢያቸውን የሚወረውሩት ። በስልትና በተገራ መልኩ ነው ጎኑን የሚኮረኩሩት ። ያኔ ተንሳጣጭ ሳይሆን የሚያስቅ ድምጽ ፈጥረው እኛንም የሳቅ ተጋሪ ያደርጉናል ።

2 . ጥበባዊ አጨራረስ የዘመኑ ግጥም ደማቅ ባህሪ እየሆነም ይመስላል ። ከተነሳው ሀሳብ በተጨማሪ የግጥሙ መዝጊያ አንዳንዴም የግጥሙ አንኳር መልዕክት አንባቢው ከሚጠብቀው በተቃራኒ ሁኔታ ሲያልቅ እንመለከታለን ። በስልቱም እንዝናናለን ። እንስቃለን - በሥስ ፈገግታ ሳይሆን ጮክ ብሎ ባመለጠን ሳቅ ። እንገረማለን - በአርምሞ ብቻ ሳይሆን ነገርና ጥያቄ በሚያመነጭ ትዝብት ። ይህ አይነቱ የፈጠራ አካሄድ ቀደም ባሉት የግጥም ስራዎች ጎልቶ የወጣ ነው ማለት አይቻልም ።

3 . ምጸታዊ ቅርጽም / Satirical poetry / ሌላኛው መለያ እየሆነ መጥቷል ። በዚህ ስልት ትልቅ ልምድ ያላቸው ሮማንስ ናቸው ። ስልቱ በተለይም ነባራዊውን የፖለቲካ መስመር ለመሸንቆጥና ለመተቸት ፣ በገሃድ የሚታየው ፍትህና ሞራል ላይ ለማላገጥ አመቺ  ስልት ነው ።

የዘመኑ ገጣሚ የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቦበት በየቤቱ እኽኽ ... የሚለውን ዜጋ ትንፋሽ በቅብብሎሽ አደባባይ ላይ እያሰጣው ይመስላል ። በፖለቲካው ምክንያት በየቤቱ የተወከለው የበገና ድምጽ ነው ። ለስለስ ያለና አንዳች ተአምር የሚለማምን ድምጽ ። ገጣሚዎቹ ይህን በገና አንዴ ትራምፔት ሌላ ግዜ ማሲንቆና ከበሮ እያደረጉት ነው - በደማቁ ።

ከላይ የተገለጹት  የፈጠራ አካሄዶችና ስልቶች ቀደም ባሉት የግጥም ስራዎች ጎልተው የወጡ አልነበሩም ። በሌላ በኩል የዘመኑ ገጣሚ እንዳነሳው ሁሉ ምን አይነት ስልቶችን እየጣለ መጥቷል የሚለውን ጥያቄ መቃኘት መልካም ነው ።

1 . የምሰላ / Imagery / መኮሰስን እንደ አንደኛው ችግር ማንሳት ይቻላል ። ገጣሚ በአንባቢ ጭንቅላት ውስጥ ምስልና ስሜትን መፍጠር ይኖርበታል ። ምሰላ ስንል የፎቶ ጉዳይ ብቻ አይደለም ። ምሰላ የሰእል ፣ የድምጽ ፣ የማሽተት ፣ የመቅመስና የመዳሰስ ህብረ ውጤት ነው ።

ከዚህ አንጻር የዘመኑ ግጥሞችን በአምስቱ ህዋሳታችን ለመረዳት እያስቸገረን ነው ። ለዚህ ትልቁ መንስኤ ደግሞ አንድ አይነትን ይተበሃል መከተላቸው ነው ። አብዛኛው ገጣሚ ግጥም በአራት፣ በስድስት እና ስምንት መስመር የሚያልቅ ጥበብ እንደሆነ የበየነ ይመሰላል ። እናም ጉዳዩን እንደጀመረ ጉዳዩን አሳጥሮ ይጨርሳል ። የግጥም መንገድ አጭርና የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው ነው ባይ መስሏል ። አንዳንዴ ግጥም ማንበብ ጀምራችሁ ማለቁን በግድ ታምናላችሁ ። በቃው ... ይሄው ነው ? ... ምን ለማለት ፈልጎ ነው የሚሉ ጥያቄዎች በምናባችሁ ይዥጎደጎዳል ። ያ ማለት ግጥሙ ወይም መልእክቱ አላሳመናችሁም ማለት ነው ። ግጥም እንደ አንባቢው መረዳት ነው ብሎ የቤት ስራውን ለእናንተ የሚቆልል ስንኝ ቋጣሪ ሳይውል ሳያድር ስራውን መፈተሽ ይኖርበታል ።

ውጤቱን በምሳሌ ላስረዳ -  በቡና መታደም ስርአት ። የበፊት ገጣሚዎች ስኒውን ፣ ቡና ቁርሱን ፣ የካዳሚዋን እንቅስቃሴ ኪናዊ በሆን መንገድ ሊያቀርቡት ይችላሉ ። ቡናው ከጀበናው ማማ ቁልቁል ስኒው ላይ እንደ ፏፏቴ ከመፈጥፈጡ በፊት ጢሱን ሊያሳዩንና እንድናሸተው ሊጋብዙን ይችላሉ ። በጢሱ ጠመዝማዛ ሰረገላ አሳፍረው የነገውን መጻኢ ማንነት ሊያመላክቱን ሁሉ ይችላሉ ። የአሁኑ ገጣሚ ዙሪያ ጥምጥሙን በመግደፍ በሞቀ ውሃ ውስጥ ዱቄት ጨምሮ እንደሚጠጣ እያሳየ ነው ።

ለአሁኑ ገጣሚ የሰርገኛ መኪና አደባባዩን ደጋግሞ መዞሩና አናስገባም ሰርገኛ እያሉ መገፋፋት ብዙም ጠቃሚ የሆነ አይመስልም ። ለመጋባት ከማዘጋጃ ፍቃድ ማግኘት ካልሆንም ያለምንም ግርግር ጠልፎ ጉዳዩን መጨረስ በቂ እንደሆነ እያሳየ ይመስላል ። ይህነኑ ብይንና እምነት ሰእላዊ በሆነ መንገድ ማቅረብ ቢቻልም አንድ ጥሩ መንገድ በሆነ ነበር - ሆኖም ቶሎ ወደ ጉዳዩ የመንደርደር ስልት ግን ምሰላን እያዳከመው ነው ። የዘመኑ ገጣሚ የግድ እንደ ሆሜር ኦሊያድ እና ኦዲሴ ረጅም ተራኪ ስታይል ይጠቀም ለማለት ሳይሆን ቢያንስ ስብጥራዊ መንገዶች ይኑሩት ነው ። ረጅም ሆኖ የሚመስጥ ግጥም መስራት እንደሚቻልም የከበደች ተክለአብ ፣ አበራ ለማ ፣ ክፍሌ አቦቸር እና የመሳሰሉ ስራዎችንም ያገላብጥ ነው ።

በቅርጽ አወራረድም የመመሳሰል በሽታ ይታያል ። ብዙ ግጥሞች እንደ ፋብሪካ ምርቶች ተመሳሳይ ፍሰት ፣ ዜማና ምት የሚጋሩ መስሎ ይሰማናል ። በጣም የወጡ ገጣሚዎች በሌሎች ላይ እያሳደሩ የመጡት ተጽእኖ ቀላል አለመሆኑ እስኪታወቅ ደረስ ። ገጣሚው ለምሳሌ እንደ በእውቀቱ እንጂ እንደ ጸጋዬ ፣ ሰይፉ መታፈሪያ ፣ ከበደ ሚካኤል ፣ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ወዘተ የራሱን መስመር ማስመር እንዳለበት አላመነም ።

2 . የቋንቋ ችግር ። የዘመኑ ገጣሚ ግጥም የሚጻፈው በቀላል ቋንቋ ነው የሚባለውን መረዳት በመያዝ ይመስላል የተለየ ትኩረት ሲሰጥ የማይታየው ። የግጥም ቋንቋ ከተራውና ከተለመደው መግባቢያ የላቀ ውበትና ዜማ የተጎናጸፈ ነው ።  የግጥም ቋንቋ የሚፈጥረው ውስጣዊ ወይም ሌላኛው ትርጉምም ማለታችን ነው ። የግጥም ቋንቋ ከሰዋሰውና ከቀበሌኛ ዘዬም በላይ ነው ።
ጠንካራና ውብ ቋንቋ ለመፍጠር ሰርካዝም የሚባሉትን ምጸት ፣ ሽሙጥና ውስጠ ወይራዎችን ማወቅና መጠቀም ይጠቅማል ። ሜታፎር የሚባሉትን ዘይቤያዊ አነጋገር ፣ አሊጎሪና ምሳሌዎችን ማወቅና መጠቀም ግድ ይላል ። ግጥም እነዚህን ዘይቤዎች አይነኬ የሚያደርጋቸው ከሆነ ተራ መደዴ ነው የሚሆነው ። ውበትና ልቀትን ነው የሚያደበዝዘው ።


እናም የሚነሳውን እያጠናከሩ የሚጣለውን ደጋግሞ እየመረመሩ መሄድ የሚያዋጣ ይመስለኛል ።

Tuesday, July 4, 2017

እየመጣ ያለው አስቀያሚ ስያሜ



ፊንፊኔ ስላሽ አዲስ አበባ
አዲስ አበባ ወይም ፊንፊኔ
ፊንፊኔ እና አዲስ አበባ 
አዲ ሃይፈን ፊን
ፊን ነጥብ አዲ
አ ወይም ፊ

የቱ ነው እየመጣ ያለው የከተማችን መጠሪያ ? የቱ ነው እውነቱ ? የሚያስከትለው ውጤትስ ? ታዋቂው አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ራልፍ ኤድዋርድ Truth and Consequences እንዲል ። ይህን Truth and Consequences የተባለውን የNBC ቴሌቪዥን ፕሮግራም የመመልከት እድል ያጋጠመው ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮችን ይገነዘባል ። እውነትን ማወቅ ስጋት ማራገፊያ መሆኑንና እውነታን መሳት ካልታሰበ ችግር ጋ የሚያላትም መሆኑን ።

የፕሮግራሙ ፈጣሪ ራልፍ ኤድዋርድ ከተመልካች ውስጥ የተወሰኑትን መድረክ ላይ በማቅረብ ነው ጥያቄውን የሚያቀርበው ። የጥያቄውን ምላሽ ያገኘ ነጻ ይወጣል ። እውነታውን የሳተ ግን በቀጣይ የሚቀርብለትን አስደናቂ ወይም አስቸጋሪ ወይም አሳፋሪ ትርዒት የማቅረብ ግዴታ አለበት ። ትርዒቱ ከአቅሙ በላይ ሊሆንይችላል ፣ ቢሆንም ከድርጊቱ ጋር መጋፈጥ አለበት ። ለምሳሌ ያህል አንድ ወቅት ያየሁት ተጠያቂው ባለ አንድ ጎማ ብስክሊት እንዲያሽከረክር ታዞ ነበር ። ሰውየውን እንደምንም ብለው የሳይክሉ ረጅም ወንበር ላይ ሰቀሉት ። ታዲያ ምን ያደርጋል ላይ ተንጠልጥሎ ራሱን ባላንስ ማድረግ አልቻለም ። እናም ፔዳሉን ወደፊትና ወደኋላ ከማባበል ይልቅ በሃይልና በድንጋጤ ሲንጠው ቀጥታ ወደ ተመልካቹ ተፈተለከ - ህዝቡ መሃል እንደ ቲማቲም ፈርጦ ክፉ የሽብር ተግባር ይፈጽማል ብዬ ስጠብቅ አምላክ ረድቶት አንድ ጥግ ምናምን ይዞ ዳነ ።  በሰውየው ድንጋጤና ያልተገራ ጥበብ ብዙ ሰአት እንደሳቅኩ አስታውሳለሁ ።

የዚህ ፕሮግራም አዘጋጅ ከመድረክ ኩምኩና በተጨማሪም ለአለማችን አስቂኝ የከተማ ስም በመፍጠርም ይታወቃል ። ነገሩ እንዲህ ነው ። በ1940 የተጀመረውን Truth and Consequences አስረኛ አመት ለማክበር በአዘጋጁ በኩል አንድ ጥሪ ይተላለፋል ። የከተማውን ስያሜ በፕሮግራሙ መጠሪያ ለሚቀይር ዝግጅቱ በቀጥታ ከከተማው እንዲተላለፍ ይደረጋል የሚል ። ይሄኔ የ < Hot Spring > ነዋሪዎች ፍቃደኝነታቸውን ይገልጻሉ ። ከተማዋ የበርካታ የተፈጥሮ ሙቅ ውሃ ባለቤት ናት ። እናም በመጋቢት 1 ቀን 1950 ዓም ህዝበ ውሳኔ ያከናውናሉ ።  295 ሰዎች ይህን እብደት አንደማይቀበሉ ሲገልጹ  1294 ያህሉ ግን ስማችን እንዲቀየር እንፈልጋለን አሉ ። በቀጣዩ ቀን ማለትም ሚያዚያ 1 1950 ፕሮግራሙ ከከተማዋ ተላለፈ - የከተማዋ አዲሱ መጠሪያም Truth or Consequences ሆነ ።

ይህ ስም በአለማችን ካሉት ረጅም እና ቀፋፊ ስሞች መካከል እንደ አንደኛው ሊቆጠር  የሚችል ነው ። የTruth or Consequences ከተማ ነዋሪዎች ይህ ቀፋፊ ስም እንዴት ከእናንተ ተግባር ጋር ይገናኛል ሲባሉ የሚከተለውን ሽፍንፍን ያለ ምላሽ ይሰጣሉ  « እውነታው / Truth /  በከተማችን ጤና ሰጪ ፍልውሃዎች ያለን መሆኑ ነው ፣ ይህ ያስከተለው ውጤት/ Consequences /  ከተባለ ደግሞ ሰዎች ተጠቃሚ መሆናቸው ነው » የሚል ነዋሪዎቹ ዛሬ ዛሬ በረጅሙ ስያሜ በመዳከማቸው  ቲ ኦር ሲ ወደሚል ምህፃረ ቃል ወርደዋል ።

ምናልባትም ሁለተኛው ረጅም እና ቀፋፊ ስም የአዲስ አበባው ፊንፊኔ ጥምረት ሊሆን ይችላል ። በህግ ፊት እኩል የመቆም መብት የተሰጣቸው አዲስ አበባና ፊንፊኔ በሚያስከትለው ውጤት / Consequences / ብዙ ሊፋተጉ ይችላሉ ተብሎ የተሰላ ይመስላል ። አዲስ አበባ ይቅደም ፊንፊኔ ? አቀማመጡ እና ጥምረቱስ ? በወይም ይቆለፍ ወይስ በ እና ሰረገላ ? በስላሽ ድንበር ያብጁ ወይስ  የዶት ታኮ ይሰራላቸው ?

ምፀታዊ ዋጋው የአዲስ አበባ ህዝብ መሰረታዊ ለውጥ በሚያመጣው በዚሁ ጉዳይ ሀሳብህ ምንድነው ተብሎ አለመጠየቁ ነው ። ስሙን በማስረዘሙ ልዩ ጥቅም ያገኛል ? የውሃ ፣ መብራት ፣ ስልክ ፣ ስራ እና የዋጋ ንረት ሰቆቃው በፊንፊኔ ስላሽ አዲስ አበባ ገመድ ይጠፈነጋል ? ከአንድ ወደ ሁለት ቃላት ያደረገውን ድንገተኛ ሽግግር ተመችቶት ይቀበለዋል ፣ ህጋዊና ስነልቦናዊ ግዴታስ አለበት ? ነው መንግስት ካለ አለ ነው- ተከተል አለቃህን አክብር አርማህን እንዲሉ ። ከቅርብ ግዜያት የፖለቲካ ተሞክሯችን ስንነሳ ግን በንግግርና መግባባት ላይ ያልተመሰረተ ውሳኔ ያልታሰበ ውጤት ለማስከተል ምንም የሚያግደው ነገር የለም ። በመሆኑም  የኦሮሞ ተወላጆች ፊንፊኔ ሲሉ የተቀሩት ደግሞ በአዲስ አበባ እንዲፀኑ መንገድ ይከፍታል  ። በአንድ ከተማ ሶስት ስያሜ መሆኑ ነው ።

ይህም ወደ ሌላ አላስፈላጊ ውጤት ይመራል ። ወደ ይዞታ ጉዳይ ። ከተማዋ ለእኛ ነው የምትገባው ወደሚለው  የኦሮሞ - አማራ ጭቅጭቅ ። በርግጥ ማነው ቀደምቱ ? ከአዲስ አበባ በፊት ፊንፊኔ ነበር ... ስለዚህ ከተማዋ የኛ ናት ፣ እናንተ እንግዶቹ በኛ ስር ልታድሩ ግድ ነው ይልሃል አንደኛው ጠርዝ ... ከፊንፊኔ በፊትስ እነማን በምን ስም ነበሩ ?... ኦሮሞዎቹስ ከየትና እንዴት መጥተው በሀገሪቱ ተስፋፉ ይልሃል ሌላኛው ጠርዝ   ። ጭቅጭቁና እንካሰላንቲያው በተዋረድ በሰፈርና አደባባይ ስሞች ግዘፍ ነስቶ ይመጣል ። ለመንገድ ስያሜ ከተሜው ግድ ላይኖረው ይችላል ። ግድ የሚሰጠው ግን እንደ ማተቡ ውስጡ የቆየውን የሰፈር ስያሜ ቀይር አትቀይር የሚል ሙግት ከተከተለ ነው ። መንግስት በቀጭን ትዕዛዝ አስራለሁ ቢል እንኳን ጥቁር ገበያው አይሎ ኢ- መደበኛው ኮሙኑኬሽን እንደሚልቅ አያጠራጠም ።

የአዲስ አበባን ደም መርምሮ ሁነኛ ብይን ማግኘት አይቻልም ። የደም ምርመራው ኦ ኔጌቲቭ ፣ ኦ ፖዘቲቭ ፣ ኤ ኔጌቲቭ ፣ ኤ ፖዘቲቭ ፣ ቢ ኔጌቲቭ ፣ ቢ ፖዘቲቭ ፣ ኤቢ ኔጌቲቭ እና ኤቢ ፖዘቲቭ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም ። ይህ የሚያሳየው ደግሞ አዲስ አበባ ከኦሮሞም ከአማራም በላይ መሆኗ ነው ። ከተማዋ የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ሃብት ናት ። የኢትዮጽያዊነት አሻራ ወይም ቅጂ ናት ። የአፍሪካዊነት መሰረት የዝማሬያቸውም  ሰንደቅ ናት ።

ከመቶ አመታት በላይ የዘመናዊ  አስተዳደር ጽንሰ ሃሳብን ስትገነባ የመጣችን ከተማ በምን ተአምር የብሄር ካፖርት ማልበስ ይቻላል ? የዘመናዊነት ትርፉ እኮ ትላልቅ ፎቆችንና ዘመናዊ ባቡሮችን ማስገኘት ብቻ አይደለም ። ዘመናዊነት ከሁሉም በላይ አስተሳሰባዊ ዝመናን ይመለከታል ። የከተማው ህዝብ ኑሮ አጉብጦት ይሆናል እንጂ በአስተሳሰቡ ሸንቃጣ ነው ። ብዙ ትርፍና ተቀማጭም ሀብት አለው - የገንዝብ ሳይሆን  የማመዛዘን ፣ የመቻቻልና የፈሪሃ እግዚአብሄርነት ። በዚህ መሰል ችግር ወቅት እየመነዘረ የሚያካፍለው ። የማይናድ ልዩ ጥቅም አለው ከተባለ ይኸው  ነው ።

 ግራም ነፈስ ቀኝ የአዲስ አበባን እውነታ አብጠርጥሮ ማወቅ ካልተቻለ የሚያስከትለው ውጤት ከባድ ሊሆን ይችላል ።