Saturday, January 12, 2013

የኮንዶ ጨበጣ



‹‹ ግንባታቸው የተጠናቀቀ ይህን ያህል ሺህ ቤቶች የዕጣ አወጣጥ ስነስርዓት ተከናወነ ››
ዕጣው ፍትሃዊና ግልጽ መሆኑን እናምን ዘንድ ድርጊቱ በአውራው ቴሌቪዥን በቀጥታ ስርጭት ተላለፈ፡፡

ሀ . ከንቲባው የዕድላችንን ሶፍትዌር ሲጫኑት ይጨበጨባል፡፡
ለ . በኮምፒውተር የተመረተው ዕድል ምርቱን በወረቀት አትሞ የከፊል እድለኞች ስም ሲዘረዘር ይጨበጨባል ፡፡
መ . የቤት የለሹን ነዋሪ ስቃይ ለመቅረፍ መንግስት ምርጡን ፓሊሲውን ምርኩዝ አድርጎ ጥራታቸውን የጠበቁ ቤቶችን እየገነባ መሆኑን ባለስልጣናት እያስጎመዡ ሲያቀርቡት ይጨበጨባል ፡፡
ሰ . ዕጣ የወጣላቸው ቤቶች  ቁልፍ ከሶስት ወራት በኃላ ለእድለኞቹ እንደሚሰጡ ሲገለጽ በጣም ይጨበጨባል ::
ረ . ቀሪዎቹም ሆድ እንዳይብሳቸው ‹ ይሄን ያህል ሺህ የሚደርሱ ቤቶች ግንባታ ደግሞ 80 ከመቶ ተጠናቀዋል › ሲባል ይጨበጨባል

ጭብጨባችን በቀላሉ የሚቆም አይደለም ፡፡ አንዳንዴ ጭብጨባችንና የህግ ሰዎች ጽሁፍ የትኛውን የዘር ሀረግ ቆጥረው ዘመዳሞች እንደሆኑ ይደንቀኛል ፡፡ የባለሙያዎቹን ጽሁፍ እያነበቡ ነው እንበል፡፡ አንዱ ረጅም ዓረፍተ ነገር አለቀ ሲሉ ‹ ወይም › የተባለው አማካኝ ቃል ሀሳቡን ይቀበልና ተጨማሪ ቁመት ይፈጥርለታል፡፡ ይኀው ‹ ወይም › እግሩ እስኪደክመው ድረስ ቃላቱን አንቀርቅቦ በረጅሙ ይለጋዋል ፡፡ ጎሽ በአራት ነጥብ ፋታ ልውሰድ  ነው ብለው ሲያስቡ ሌላ ‹ ወይም › ሀሳቡን ጎትቶ እንደ ሀረግ ሲያጥመለምለው ያያሉ ፡፡ እኔ የአራት ነጥብ ጥቅም ይበልጥ የሚገባኝ እንደዚህ አይነት ጽሁፎችን ሳነብ ነው ፡፡
የኮንዶ ጭብጨባም በማይታይ ‹ ወይም › የተሳሰረ ነው ፡፡ ስማቸው ጋዜጣ ላይ ለወጣ ዕድለኞች ዘመድ ወዳጅ ያጨበጭባል ፡፡ የነዎሪዎችን ደስታ የሚያብራራው የቲቪ/ሬዲዮ ፕሮግራም ሲታይና ሲደመጥ ይጨበጨባል ፡፡

ከላይ ይጨበጨባል ያልንባቸውን አንዳንድ አንቀጾች በአግባቡ ስንመረምር ግን በከንቱ የተጨበጨበላቸው ነገሮች መኖራቸውን እንረዳለን ፡፡

የማስረከቢያ ግዜ

መንግስት ቤቶችን ሲመርቅ ከ 3 ወር በኃላ ወይም በጣም በፈጠነ ሁኔታ ቁልፍ አስረክባለሁ ማለቱ የተለመደ ነው ፡፡ የፈጠጠው እውነታ ግን ይህ አይደለም ፡፡ ትልቅ ማሳያ የሚሆነው የአምስተኛና የስድስተኛ ዙር ቤቶች ጉዳይ ነው ፡፡ መንግስት ዕጣውን ያወጣው ቤቱ ሳያልቅ ምናልባትም ገና ከመሰረት ደረጃ ፈቅ ሳይል በመሆኑ የ5ኛ ዙር ዕድለኞች ሁለት ዓመት የ6ኞቹ ደግሞ ዓመት ገደማ ቤታቸውን ለመረከብ ግዜ ወስዶባቸዎል ፡፡ የአዲስ አበባ መስተዳድር በዚህ መሃል በጣም ቢያንስ ሁለት ወይም ሶስት ግዜ ቁልፍ ልናስረክብ ነው በማለት መግለጫ ሰጥቶ ዋሽቷል ፡፡

‹‹ ጨበጣው ›› ለምን አስፈለገ ?

በአንድ በኩል ከፍተኛ የህዝብ ፍላጎት የመኖሩን ያህል በሌላ በኩል መንግስትም ይህን ክፍተት ሞልቶ እውቅናና ድጋፍ ማግኘትን ይፈልጋል ፡፡ አቅርቦቱና ፍላጎቱን ግን ማጥበብ አልተቻለም ፡፡

መንግስት እንደ ህዝብ አገልጋይነቱ የሚለካው በሚታዩ ውጤቶች መሆኑ ይታወቃል ፡፡ ይሁን እንጂ ዓመት መጀመሪያ ላይ የሚታቀዱ ዕቅዶች ወሩ በፈጠነ ቁጥር በየደረጃው የሚገኙ አስፈጻሚዎችን ያስጨንቃሉ ፡፡ ታዲያ የአዲስ አበባ ቢሮዎች ዕቅድንና ውጤትን ለማጣጣም ወረቀት ላይ መደነስ ግድ ይላቸዋል ፡፡ ያልተሰራውን ተሰራ፤ የተጀመረውን ደግሞ ከዕቅድ በላይ ተከናወነ በማለት ዳንሱን ከጥሩ የቋንቋ ህብር ጋር ያዋህዱታል ፡፡ ላይ ያሉት ዳኞችም ‹‹ ለዛሬ ተሳክቶልሃል ! ›› በማለት በጥሩ ጭብጨባ ያሳልፉታል ፡፡ ይህን መሰሉ በወረቀት መወሻሸት በጣም የተለመደ ነው ፡፡ እናም ያላለቀውን ቤት አልቋል፤ ያልተጀመረው ቀጣይ ግንባታ 80 ከመቶ ደርሷል ተብሎ ሪፖርት የሚደረገው በዚህ ዓይነት የተለመደ ስልት በመሆኑ የማይፈለገውን ‹‹ ጨበጣ ›› እንዲወለድ አድርጓል ፡፡

ሌላው የአዲስ አበባ መስተዳድር ችግር ስራ ተረባርቦ እንደሚጀመር ሁሉ ተረባርቦ መጨረስ የሚባል ዕቅድ አለማወቁ ነው ፡፡ ግንባታዎች ሲጀመሩ አንድ ሁለቴ ሰብስብ ብሎ መጎብኘትና ቀጣይ አቅጣጫ መስጠት ተለምዷል ፡፡ ይህም ‹ ክትትልና ግምገማ › የተባለውን የቢኤስሲ ቅጽ ለማሳካት ግድ ስላለ ነው ፡፡ ይሁን እንጂ ክትትሉ 40 ከመቶው ላይ የተጀመረ ከሆነ እነ 80፤ 90 እና 100 ፐርሰንቶች ምን ይመስላሉ ብሎ የሚፈትሽ አይደለም ፡፡ ላይ ያለው አመራር አንድም በመሰላቸት አንድም ታች ያለውን አመራር በማመን / ምክንያቱም በእውቀት ሳይሆን በእምነት መምራት አስፈላጊ ነውና / የሚያመጣለትን ሪፖርት በመቀበል እንዲሳሳት ፤ ዋሾ እንዲሰኝ ብሎም እንዲታዘንበት መንገዱን ራሱ ያመቻቻል ፡፡

‹ ጨበጣው › የቱንም ያህል ሀሰት ቢሆን እንኳን አንዳንዴ ከፖለቲካ አንጻር አስፈላጊ እንደሚሆንም ግምት ውስት ማስገባት ያስፈልጋል ፡፡ ምክንያቱም የደረሱ ተስፋዎች የተራቡ ሰዎችን ወዳላስፈላጊ ተቃውሞ ወይም ግጭት ከመክተት ይልቅ ‹ ጠባቂነታቸውን › እንዲያለመልሙ የሚገፋፋ ነውና ፡፡

ሁለተኛ ዙር ‹‹ ጨበጣ ››

ሁለተኛው ጨበጣ ከቁልፍ መረከብ በኃላ ያለውን ገጽታ የሚመለከት ነው ፡፡ ‹‹ ቁልፍ ማስረከብ ›› ከሚለው ሀረግ ትርጓሜ እንጀምር
፡፡ እንግዲህ በአማርኛ መግባባት እንደምንችለው አንድ የኮንዶሚኒየም ዕድለኛ ከአስተዳደሩ የቤት ቁልፍ ተረከበ የሚባለው ቤቱ አስፈላጊ የተባሉትን ግብዓቶች አሟልቶ ከተጠናቀቀ በኃላ የተዘጋውን ቤት ከፍቶ በመግባት ሲረካና ጎርደድ - ጎርደድ እያለ ሲቃኝ ነው ፡፡ በዚያ ላይ ዘመድ ወዳጅ ከኃላ ሆኖ ያን የፈረደበት ጭብጨባ ሲያዘንብለት ነው ፡፡

ይሁን እንጂ  ይህ ትርጉም ዛሬ በሰሚት ሳይት ቤታቸውን ለተረከቡ 5ኛና 6ኛ ዙር ባለእድሎች አልሰራ ብሏል ፡፡ እንዴት አላችሁ ?

ዕድለኞች አስፈላጊውን ፎርማሊቲ ካሟሉ በኃላ ከሚመለከተው ክፍል ተሰልፈው ቁልፉን ተረከቡ ፡፡ ቤታቸው ሲደርሱ ግን አብዛኛዎቹ በሮች ክፍት ነበሩ ፡፡ ‹ እንዴ ቁልፍ ሳንረከብ ቤቱ አየር ባየር ተመረቀ እንዴ ?! › ቢሉም ተሳሳቱ አይባልም ፡፡ 

እየቆዩ ሲሄዱ ግን የበሮቹ መከፋፈትን እየደነገጡ  ይረዳሉ ፡፡ አብዛኛዎቹ ቤቶች በራቸው የውሃ ልክ ክፍተት ስላለበት ፣ የመስታውት አለመኖር ፣የመክፈቻና የመዝጊያ ቁልፎች ባለመሰራታቸውና በሌሎች ምክንያቶች ሊዘጋ የቻለ አልነበረም ፡፡

መንግስት እንዴት ነው ክፍቱን የሰነበተ ቤት ቁልፍ ተረከቡ ብሎ የሚያውጀው ? እንዴትስ ነው የተጣመመ በር ፣ መዝጊያና መክፈቻው የማይሰራ ቤት ላስረክብህ እያለ የሚቀልደው ? በሩን ዘግቶ ባለማስረከቡ ምክንያት መስታውቶች እንዲሰበሩ ፣ የሽንት ቤትና የኩሽና ዕቃዎች እንዲሰረቁ ምቹ ሁኔታዎች ፈጥሯል ፡፡ ዕድለኛው ቤቱ የደረሰው በዕድሉና በነጻ ብቻ ነው እንዴ ? ለከፈለው ገንዘብ ተመጣጣኝና ትክክለኛ ዋጋ የማያገኘውስ በምን ስሌት ነው ? 
አስተዳደሩ ቁልፍ ከማስረከቡ በፊት የእያንዳንዱን ቤት ችግርና ጉድለት መፈተሸ ቢኖርበትም ይህን ‹ አብይ  › ውሳኔ ‹ ብ ›ን ገድፎ  ‹ አይ › በሚል በማንበቡ የመጣ ህጸጽ አስመስሎበታል ፡፡

ኮንዶና ጥራት

የነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ የሚባለው ብሂል የነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው አግሮ ስቶን ወደሚለው መልክ በተጨባጭ ተቀይሯል ፡፡ ኮንዶሚኒየምና ጥራት ሲወራላቸው እንጂ ሲመስሉ ለማየት ገና ብዙ ርቀት መጓዝ ያስፈልጋል ፡፡

የግድግዳው ነገር ከተነሳ የቤቶቹ ክፍሎች የሚከፋፈሉት አግሮ ስቶን በተባለው ወጤት ነው ፡፡ ይህ ግድግዳ ደግሞ የሚሰራው አንዳንዶች የተስፋ ቡድን በሚሏቸው ጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፎች ነው ፡፡ ለነገሩ ማንም ቢሰራው ምክንያት አይሆንም ፡፡ የነገር ምክንያት የሚሆነው በምን ያህል ጥራት ሰሩት ? የሚለው ነው ፡፡ ይህ ምርት በተለይም በቻይና ፣ ማሌዥያና ሩቅ ምስራቆች ምን ያህል ውጤታማ / ከጥራትና ወጪ / እንደሆነ አንብቤያለሁ ፡፡ እውነቱን ለመናገር በኛ ሀገር ምርቱ የሚሰራው መኖሩን ለማሳወቅ ብቻ ይመስላል ፡፡  የበዛ የቸልተኝነት ጭቃ ምርቱ ፊት ላይ እንደተመረገበት ይታያል ፡፡ ምክንያቱም ብዙ ቤቶች ውስጥ ገብታችሁ አካፋዩን ግድግዳ ስትመለከቱ ልታዝኑ አሊያም ሳቅ ሁሉ ሊያመልጣችሁ ይችላል ፡፡

ግድግዳዎቹ የተንገዳገዱ ፣ በቀጭን ጀምረው እንደ ዝሆኔ በሽታ ያለቅጥ ያበጡ ፣ እዚህም እዚያም የአይጥ ጉድጓድ የመሰለ ቀዳዳዎችን ያራቡ ፣ እንደ ጀማሪ ወታደር ‹ አሳርፍ ! › ቢባሉም ለመስመር መዛነፍ ቁብ ያልሰጡ ፣ ማንም እንዳይነካቸው ልመና የሚያበዙ የሚመስሉ አይነቶች ናቸው ፡፡ ብር ያላቸው ሰዎች በርግጫ ሳይሆን በኩርኩም ከጣሏቸው በኃላ አካፋዩን ግድግዳ በብሎኬት እያስገነቡ ነው ፡፡ ህጉ መንግስት የሰራውን ቤት መቀጠልም ሆነ መቀነስ አይቻልም ቢልም ፡፡ አብዛኛው ‹ መናጢ › ግን ‹ አካል ጉዳተኞችን መንከባከብ የዜግነት ግዴታ ነው ! › ለሚለው  የቆየ መፈክር ዋጋ እየሰጠ መሆኑ ታይቷል ፡፡  ይህ መፈክር እንዴት ትዝ አለው ጃል ? ይህን መፈክርስ በምን መልኩ ነው ተግባራዊ እያደረገ ያለው ? የሚሉ ጥያቄዋች ተደራርበው መምጣታቸው አይቀርም ፡፡ ትዝታውን ያጫረው ችግሩ ሊሆን ይችላል -  እንዴት ተገበረው የሚል ጥያቄ ከቀረበ -  መጀመሪያ ግድግዳዎቹ በደንብ ተደርገው በጀሶ ታሽተዋል ፡፡ ጀሶው ከደረቀ በኃላ ደግሞ እንዳቅሚቲ ቀለም እንዲፈስባቸው ተደርጓል ፡፡ ይህን ስራ የጨረሱ አንዳንድ ሰዎች ታዲያ አካፋዩን ግድግዳ እየተመለከቱ ‹‹ እውነት ያ አግሮ ስቶን ነው እንዲህ የሆነው ? ወይ ማየት ደጉ ?! ›› ይላሉ አሉ ፡፡ አንድ ቀን ድንገት ሸብረክ እንዳይል እየሰጉ ጭምር ፡፡

ከላይ እንደተገለጸው ከፍተኛ የሆነ የውጭ በር አሰራር ችግር በዝቶ ይታያል ፡፡ ወደ ማብሰያ ክፍል ስንገባ ቀድሞ የሚተዋወቀን ለዕቃ ማጠቢያነት የተገጠመው ሳህን ቢጤ ነው ፡፡ ይሁን እንጂ በጣም በመሳሳቱና ሲገጠም በአንገቱ አካባቢ ጉዳት ስለደረሰበት እንደተጣመመ በሰለለ ድምጹ ነው ‹ ጌቶች/ እሜቴ እንኳን ለዚህ አበቃዋት ! › የሚለው ፡፡ ስስነቱና ኮሽኳሻነቱን እያገላበጡ ካጉረመረሙ ‹ ጌቶች/ እሜቴ እንዴ ቤት በማግኘትዋ ብቻ ሊደሰቱ ይገባል ! እንዴ ከስንት ሰልፈኛ ወይም ተስፈኛ መሃል ተመንጥቀው እንደወጡ ማሰብ ይገባል ?! › ሊልዎት ይችላል - ይኀው ሳህን ፡፡ አይልም ብለው ቅንጣት አይጠራጠሩ ! ከሁለትና ሶስት ዓመት በላይ ምን ሲሰማ የከረመ ይመስልዎታል ?!

ወደ መጸዳጃ ቤቱ ስናመራ የተሻለ ነገር እናያለን ፡፡ ግድግዳዎቹ በሴራሚክ የተለበጡ ናቸው ፡፡ መቀመጫዎቹና የእጅ መታጠቢያዎቹ ሳህኖች ለሀሜት የሚመቹ አይደሉም ፡፡ በእውነት ጥሩ ናቸው ፡፡ እዚህ ንዑስ ክፍል አቃቂር የሚወጣው ባድመ የኛ ትሁን የኤርትራ / ከህግ አንጻር / እንዳልተለየች ሁሉ የሽንት ቤቱ ሳህንና የገላ መታጠቢያው መኃል ወፈር ያለ ድንበር ሳይሰመር መቀላቀላቸው ነው ፡፡ ቀና ብለው የሚመለከቷት ትንሽ መስኮት ብዙ ቤቶች ላይ ተሰክታ እንጂ ተሰርታ ያለቀች አትመስልም ፡፡ እንደውም አንዳንድ ቤቶች የምትታየው መስኮት እና ኮፍያ ገልብጠው የሚዘንጡ የክፍለሃገር ልጆች ቁርጥ የአባት - የእናት ልጆች ይሆኑባችኃል ፡፡

ሁለተኛው ዙር ‹‹ ርክክብ ››

የከተማው አስተዳደር የነዋሪውና የመገናኛ ብዙሃን ግፊት ሲበዛበት በቅጡ ያላለቁ ቤቶችን ለማስረከብ የተገደደ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም ፡፡ ወይም ደግሞ  ‹ ጉጉው ነገር ግን ድሃው ነዋሪ ትንሽ ከጀመርኩለት ይጨርሰዋል › ከሚል ቀና አመለካከት በመነሳትም ሊሆን ይችላል ፡፡

ችግሩ ግን በዚህ ብቻ የሚያበቃ አለመሆኑ ነው ፡፡ የሰሚት ሳይት ቤቶቹ ብቻ ሳይሆን አካባቢውም ለምቶ ባለመጠናቀቁ አስተዳደሩ ለሌላ ዙር ርክክብ ሳይዘጋጅ እንደማይቀር ይገመታል ፡፡ አብዛኛው ህንጻዋች ዙሪያ ገባቸው ለመፋሰሻና ለመከለያ አጥር ጥቅም ተቆፍረዋል ፡፡ ተቆፍረው ግን አልተገነቡም ፡፡ ከየጉድጓዱ የወጣው አፈር እዚህም እዚያም ተቆልሏል ፡፡ እዚህ ቁልል ላይ የሆነ ነገር ጻፍ ጻፍ ቢደረግ ብዙ ‹‹ ትክል ድንጋዮች››ን መፍጠር የሚቻል ይመስላል ፡፡

ዋና ዋናዎቹን የመኪና መንገድ ማሰብ ከቅብጠት እንዳይቆጠርብን እንተወውና አንዱን ህንጻ ከሌላው ሊያገናኝ የሚችል ቀጭን የእግር መንገድ እንኳ አይታይም ፡፡ ከህንጻዎቹ ፊት ለፊትና ኃላ የሚገኙ ክፍት ቦታዎች የራሳቸው ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ይታወቃል ፡፡ ይሁን እንጂ ሜዳዎቹ የግንባታ ፍርስራሽ፣ አፈር፣ ድንጋይ ወዘተ የሞላባቸው በመሆኑ ዕጣ ፈንታቸው ገና አልታወቀም ፡፡

እነዚህና አነዚያን የመሳሰሉ ኮተቶች ገና አልተነሱም ፡፡ ክረምት ላይ ጉድ ከሚያፈላው ጭቃ ለመከላከል የሚያስችሉ መሰረታዊ የእግር መዝለያ መንገዶች የሉም ፡፡ ይህ በራሱ የነዋሪውን ደስታ የሚያጨፈግግ ነው ፡፡ ገና ብዙ ስራዋች ይቀረዋል በሚል ቤታቸውን አዲስ በርና ቁልፍ ቀይረው የጠፉም ጥቂቶች አይደሉም ፡፡ / ይህ የበር መዘጋት ደግሞ መድረሻ አጥተው ገና ከጠዋቱ ያለ መብራትና ውሃ እየኖሩ ለሚገኙ ነዋሪዋች ትልቅ ጉዳት ይፈጥራል ፡፡ ምክንያቱም መብራት ኃይልና ውሃና ፍሳሽ ብዙ ህዝብ ካልገባ አገልግሎቱን አንለቅም የሚል ብሂል አላቸውና / ለመሆኑ በዚህ መልኩ ነው እንዴ የርክክብን ‹‹ እርካታ ›› ማምጣት የሚቻለው ? ነው ኪራይ ሲቆነድደው ሮጦ ይገባል ፣ ከገባ በኃላ ደግሞ ለራሱ ጥቅም ሲል ‹ የኔን ስራ ይሰራልኛል › የሚል ስትራተጂ ተቀይሶ ነው ? ይህ ስልት አይፈጸምም - ተራ አሉባልታ ነው ከተባለ ግን አስተዳደሩ አሁን የተገለጹ ስራዎችን ለመጨረስ ቢያንስ ሁለት ዓመት ላይ የሚተኛ ይመስላል ፡፡ ምክንያቱም የአስተዳደሩ የፍጥነት ብቃት ወይም ቤዝላይን ይኀው ስለሆነ ፡፡ ነዋሪው እንደተለመደው ብዙ ካለቃቀሰ በኃላ ከእለታት አንድ ቀን ‹‹ ሁለተኛ ዙር ርክክብ ›› ያከናውናል ፡፡

ጠንጋራ አሰራሮችና ያልተወራረዱ ኪሳራዎች

የቤት ዕድለኞች ቤታቸውን የሚረከቡት ሁለት መሰረታዊ ገንዘብ ነክ ጉዳዮችን ሲያሟሉ ነው ፡፡ የመጀመሪያው ዕጣው በወጣላቸው ማግስት የተተመነባቸውን ቅድመ ክፍያ በተባለው ግዜ ውስጥ መክፈል ነው ፡፡ ሁለተኛው ቀሪውን ዕዳ በረጅም ዓመታት የሚከፍሉት ከባንክ ጋር የውል ስምምነት በማድረግ ይሆናል ፡፡ መቼም አባታችን መንግስት ያጣ የነጣነውን እንደ እውነተኛ ልጁ ቢመለከተን ኖሮ በባንክ በኩል የሚያስከፍለንን ተጨማሪ የወለድ ክፍያ ያስቀርልን ነበር ፡፡ የሆኖ ሆኖ ይህም ቢሆን ጥሩ ነው በሚለው ሀሳብ እንለፈው ፡፡

እዚህ አሰራር ውስጥ ግን ጥሩ ያልሆነ ወይም ጠንጋራ ነገር መብቀሉ ነው የሚያስከፋው ፡፡ መንግስት በሁለት መልኩ ተቃራኒ ጉዳዮችን ያከናውናል ፡፡ አንደኛው ወይም ቸር ገጽታው ቤት ተከራዮች ቤቱን ለማስጨረስ ብዙ ወጪ ስለሚያወጡ በየወሩ የሚከፍሉትን ክፍያ የሚጀምሩት ከዓመት በኃላ ነው ማለቱ ነው ፡፡ የእፎይታ ግዜ ይለዋል ሲያሰማምረው ፡፡ ዳሩ ግን ሁለተኛውን መልኩ ስንመለከት ‹ እፎይታው ወደ ወይዞታ / ወይኔ / ይቀየርብናል ፡፡

ሁለተኛው ወይም ክፉ ገጽታው ባንክ ከቤት ባለቤቶች ጋር የረጅም ግዜ ክፍያ ስምምነት ከተፈራረመ ማግስት ወለድ የማሰቡ አሰራር ነው ፡፡ መንግስት በአንድ በኩል ለዓመት ያህል ስለ ክፍያም ሆነ እዳ እንዳታስቡ አደርጋለሁ እያለ በሌላ በኩል ባንክ ገና ካልተገባበት ቤት ላይ ያለ ርህራሄ የደሃ ገንዘብን ይነጥቃል ፡፡ የእፎይታ ግዜ እያለ እንዴት ገንዘባችንን ትወስዳላችሁ ? ተብለው ሲጠየቁ ‹‹ እኛ አትራፊ ድርጅት እንጂ መንግስት አይደለንም ! ›› የሚል ያልታረመ ምላሽ ይሰጣሉ ፡፡ ‹‹ የእፎይታ ግዜ የተሰጠው ዕዳውን ለመክፈል የሚጀመርበት ነው ›› በማለትም ርስ በርሱ የሚጋጭ አስተያየት ያስከትላሉ ፡፡ በነገራችን ላይ ነዋሪዎች የአንድ ወር ዕዳችሁን ባንክ ሄዳችሁ ካልከፈላችሁ ቁልፍ አይሰጣችሁም ተብለውም ተገደዋል ፡፡ ይህ ግዳጅ ለምን እንደተፈጠረም ግልጽ አይደለም ፡፡ ይህም ለእፎይታ የተሰጠችውን ግዜ በጠረባ መትቶ የዘረጋ አስመስሎታል ፡፡

ብዙ የጨነቃቸው ሰዎች የሚከተለውን ጥያቄ ራሳቸውን እየጠየቁ ስለሆነ እስኪ ይሞክሩት ዘንድ ጉዳዩን ላጋራዎ ፡፡
ዕዳ መክፈል  ወይም አገልግሎት ማግኘት ሳይጀመር ወለድን ማስከፈል ማለት ምን ማለት ነው ?

ሀ . እየኮረኮሩ ኪስን መፈተሸ
ለ . እጅን መጠምዘዝ
ሐ . ማጅራት መምታት
መ . መልስ የለውም

የባንክን አሰራር የሚነድፈው መንግስት መሆኑ ይታወቃል ፡፡ መንግስት ለድሃው ካዘነ ብሎም አሰራሩ ሸፋፋ መሆኑን ከተገነዘበ ባንክን ማዘዝ ይችላል ፡፡ መንግስትን ከማርስ ባንክን ከጁፒተር የተገኙ አስመስሎ ማቅረብም ጅላጅነትን ከማጠናከር ውጪ ለእውነታው የሚጠጋ ምለሽ ሊሆን አይችልም ፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ቤቱን ቶሎ የማያስረክበው መንግስት ሆኖ ሳለ ያለግዜው ወለድ የሚያስከፍለውም መንግስት መሆኑ ነው ፡፡ ቤቱን በተባለው ግዜ አስረክቦ፣ ህዝቡ መኖር ቢጀምር እንኳን የወለዱ ሂሳብ ትንሽ በተሻለ ነበር ፡፡ ያው የአንድ አመቷን  ‹ እፎይታ - ወይዞታ › በሚለው ሂሳብ አልፈነው ማለት ነው ፡፡
በየትኛውም አሰራር ቢሆን ማንኛውም ሰው አገልግሎት ላላገኘበት ነገር ወለድም ሆነ ቀረጥ እንዲከፍል አይገደድም ፡፡ ታዲያ የኮንዶሚንየም ነዋሪዎች ‹‹ እጣ ስለወጣላቸው ›› ብቻ ነው ኢ- ፍትሃዊ የሆነ ጫና ያረፈባቸው ?

በአንድ ወቅት ይህን ኢ- ፍትሃዊ ጉዳይ አስመልክቶ የተጠየቁ ኃላፊዎች ‹‹ እናዝናለን ! ›› የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ከጋዜጣ አንብበናል ፡፡ በርግጥ ማዘን አንድ ነገር ነው ፡፡ ሀዘን ግን ኢኮኖሚያዊ ኪሳራውን በፍጹም አያካክስም ፡፡ በመንግስት ስህተትና ቸልተኛ አሰራር የሌለውን ድሃ መውቀጥ ኢ - ሞራላዊ ጉዳይ ነው ፡፡ መንግስት ከልቡም ይሁን ከአንገት በላይ ‹ እናዝናለን › ቢልም ለድሃው ግን ያልተወራረዱ ኪሳራዎች ናቸው ፡፡ ሲጀመር ድሃ ነው - በዚህ ድህነት ላይ ደግሞ ወደፊትም ድህነቱን የሚያወፍሩ ካፖርቶች እንዲደርብ ማስገደድ ፈጽሞ ትክክል ሊሆን አይችልም ፡፡ ይህን የመሰለ ጠንጋራ አሰራር ሳይውል ሳያድር መስተካከል ይኖርበታል ፡፡ ተናቦና ተማምኖ መስራት ያስፈልጋል ፡፡ ህጎችና ደንቦች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ቀጥተኛ እንጂ ያልተገባ ትርጉም እንዳያቅፉ መትጋት ግድ ይላል ፡፡

No comments:

Post a Comment