Saturday, January 12, 2013

‎ሁለተኛው ሶማሌ ተራ ‎?




ከ 15 ቀናት በፊት በቁም ነገር መጽሄት ላይ የወረወርኳት ‹‹ የኮንዶ ጨበጣ ›› የምትሰኝ ጽሁፍ ከግራና ከቀኝ ልዩ ልዩ ምላሾችን አስገኝታለች ፡፡

ግራው ፤

በዚሁ መጽሄት በጥር ወር ዕትም ላይ ጉዳዩ የከነከነው አንድ የኮንዶሚንየም ነዋሪ የደረሰበትን ችግር ዘርዝሮ የጽሁፉ ርዕስ ጨበጣ ሳይሆን ለበጣ ቢባል ይገባዋል ብሏል ፡፡

ሌላ አንድ ሰው ጥቂት የቀሩ ያልተዳሰሱ ነገሮችን አስታወሰኝ ፡፡ የሌብነት ወይም የሙስና ጉዳይ ልንለው እንችላለን ፡፡ እንዴት መሰላችሁ ?

በሰሚት ሳይት ያሉ ኮንዶዎች እንደ በርና ሌላ ዕቃ ሁሉ የኤሌትሪክ መሳሪያዎችም የተገጠመላቸው አይደለም ፡፡ እናም እድለኛው እንደተለመደው ተሰልፎ ነው ዕቃዎቹ ተቆጥረው የሚሰጠው - በመርህ ደረጃ ማለት ነው ፡፡ አነዚህ ዕቃዋች ባለሙያዎቹ ሶኬት ፣ ቱ ዌይ ስዊች ፣ ዋን ዌይ ስዊች ፣ ቆጣሪ የሚሏቸውን ማለቴ ነው ፡፡

በተግባር አይን ግን ንብረቱን የሚያስረክቡ ሰራተኞች ለህዝቡ የሚሰጡት እያጎደሉ ነው ፡፡ ከአንዳንዱ ግማሽ ያህል ፡፡ ነዋሪው በወቅቱ ስንት ሶኬት እንደሚያስፈልገው መረጃ አልነበረውም ፡፡ የሰጡትን ልክ እንደ እርዳታ ተቀባይ ‹‹ እግዜር ይስጥልኝ ! ›› ብሎ ነው የተቀበለው ፡፡ ይህ ህዝብ ስንቱ እየጋጠው ትህትናው አያልቅበትም ፡፡ ችግሩ አፍጥጦ የመጣው ቤቱ ገብቶ ለሶኬት የተሰሩ ቀዳዳዋችን ሲቆጥር ነው ፡፡ ቀዳዳዋቹና የተሰጡት ቁሳቁሶች እንደ ሰማይና ምድር የተራራቁ ናቸው ፡፡ ይህን ሲያውቅ ንብረት ሰጪዋች ላይ ማፍጠጥ ጀመረ ፡፡ እነሱም በዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ ‹‹ በስህተት ስለሆነ መጨረሻ ላይ ይሰጥሃል ! ›› እያሉ ሸኙት ፡፡ ህዝቡም አለ ‹‹ አዋ ! ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት አይጠፋም ! ›› የሚሰራ ሰው ሰው ይሳሳታል የሚል ጥቅስ በመጨመርም ነገረ ጉዳዩን እንደ አርማታ ያጠናከሩም ነበሩ ፡፡ ምክንያቱም ይህ ህዝብ ቡቡነቱ አያልቅበትም ፡፡

በኃላ መሳሪያውን የሚገጥሙ የኤሌትሪክ ሰራተኞች በየቤቱ ለስራ መንቀሳቀስ ሲጀምሩ አሁንም ህዝቡ ‹‹ እረ ማስገጠም አልቻልንም ፡፡ አገልግሎቱ ሊያልፍብን ስለሆነ ንብረታችን ይሰጠን ? ›› በማለት መጠየቅም መለመንም አስከተለ ፡፡

‹‹ ለሁሉም ሰው አድለን ስላልጨረስን አሁን መስጠት አንችልም ፡፡ የምትቸኩሉ ከሆነ እየገዛችሁ አስገጥሙ ››
‹‹ ታዲያ መቼ ይሰጠናል ? ››
‹‹ መጨረሻ ላይ ! ››
‹‹ ይሄ መጨረሻ መቼ ነው መጨረሻው ?! ››

መጨረሻው ቅርብ ሊሆን አልቻለም ፡፡ በዚህ የተበሳጨው ህዝብ ፍትህ በሌለበት ከተማ ጉሮሮን ከመሰንጠቅ ገዝቼ ላስገጥም ማለት ጀመረ ፡፡ ይህ ህዝብ ቢበሳጭም ቻይነቱ አያልቅበትም ፡፡ እናም የኤሌትሪክ ሰራተኞች ሀሳቡን ሲረዱ አንድ ሀሳብ ሹክ ማለት ጀመሩ ፡፡ ለነገሩ ሹክታ ሳይሆን ማማከር ጀመሩ ማለት ይሻላል

‹‹ አንድ ሶኬት ውጭ የሚሸጠው 35 ብር ነው ፡፡ እዚህ ግቢ ግን 25 ብር የሚሸጡ ሰዋች አሉ ››
‹‹ ይህማ ጥሩ ነው ፡፡ በል አሳየንና እንግዛ ››
‹‹ ቆይ ደውዬ ልጠይቅላችሁ ›› ባለሙያው አንድ ሰው  ጋ በመደወል ስለዕቃው መኖር ይጠይቃል ፡፡ቀዳዳውን ቆጥሮም የሚያስፈልገውን ብር አሰሪውን ይጠይቃል ፡፡ በሩጫ ብር ብሎ ይሄድና አዳዲስ እቃዋች ይዞ ይመጣል ፡፡  ‹ እንዴት ያለ ቸር ነው › የሚሉ ነበሩ - ምክንያቱም ይህ ህዝብ ምስኪንነት አያልቅበትም ፡፡

ጥቂት ለመጠየቅና ለመጠራጠር የተፈጠሩ ደግሞ ‹‹ ለምን ብቻውን መሄድ ፈለገ ? የህንጻ መሳሪያዎች ሱቅ ሳይኖር የሚገዛው ከነማን ነው  ? ሮጦ ሄዶ ለገዛበት የአገልግሎት የማይጠይቅ የቤቶች ልማት ሰራተኛ በቢኤስሲ ነው በካይዘን ሳይንስ የተገኘ ? ›› የሚሉ ጥያቄዎችን በውስጡ ያንሰላስል ነበር ፡፡

የዚህን እውነት ማወቅ ከባድ አይደለም ፡፡ ከብዙዎች ሆን ተብሎ እየጎደለ የተሰጠው ዕቃ የመጨረሻ ግቡ ለራሱ ለባለቤቱ እንዲሸጥ በመታቀዱ ነው ፡፡ በአዲስ አበባ ታሪክ የራሳቸውን ዕቃ ከሶማሌ ተራ የሚገዙት ባለመኪናዋች ነበሩ ፡፡ ዛሬ ይህ ልምድና ተሞክሮ ተስፋፍቶና ተቀምሮ ሰሚት ሁለተኛው ሶማሌ ተራ ሆኗል ፡፡ በመንግስት ሀገር ?!

በአሁኑ ወቅት በሰሚት ኮንዶ ሳይት ዋናውን የማብሪያና ማጥፊያ / ቆጣሪ / መግጠም አልተቻለም ፡፡ እቃው አስቀድሞ ከተገጠመ በሌቦች ይሰረቃል በሚል ቀድሞ እንዲሰራ አልተደረገም ፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ሶኬቶቹ እየተገጠሙ ቢሆንም የሚመለከተው ክፍል እነዚህን ዕቃዎች ለኤሌትሪክ ባለሙያዋች ማስረከብ ባለመቻሉ ስራው ቆሟል ፡፡ ሁልግዜም ሰራተኞቹ የሉም ፣ ስብሰባ ላይ ናቸው ወዘተ ነው የሚባለው ፡፡ ምናልባትም ያስፈልጋል የተባለውን ዕቃ ለመቸብቸብ እቅድ እየተነደፈለት ይሆን ? የሚል ጠርጣሪ መኖሩ ግልጽ ነው ፡፡ እረ ተቸብችቧል የሚል ርግጠኛም ጥቂት የሚባል አይደለም ፡፡ እና መብራት ኃይል ደግ ሆኖ እንኳ ለአካባቢው ኃይል ለመዘርጋት ቢፈልግ ቆጣሪው ካልተሰራ የህዝቡ ፍላጎት አይሟላም ማለት ነው ፡፡

ቀኙ ፤

‹‹ የኮንዶ ጨበጣ ›› የተሰኘው አርቲክል ያስገኘው ሌላ አዎንታዊ ምላሽም አለ ፡፡ ጽሁፉ በተለቀቀ ሳምንት የከተማው አስተዳደር ሰሚትን ጨምሮ ሌሎች የቤት ልማት ቦታዎችን ተዘዋውሮ ጎብኝቷል ፡፡ ጠበቅ ያለ ትዕዛዝም አስተላልፏል ፡፡ ‹‹ ስራችሁን እስከዚህ ወር ድረስ ካላጠናቀቃችሁ ኮንትራቱን እንቀማችኃለን  ! ››

አስተዳደሩ የህዝብን ስሜት ማንበብና ማዳመጥ ከቻለ አንድ ርምጃ ነው ፡፡ ርምጃው ሙሉ የሚሆነው ግን የመጨረሻውን ውጤት በፍጥነትም በጥራትም ማስገኘት ሲቻል ነው ፡፡ ሌላም ጥቅም አለው ፡፡ ዶ/ር መራራ ጉዲና ኢህአዴግ ጆሮ የለውም የሚል የሰላ ትችት አላቸው ፡፡ ግዜው የምርጫ ሰሞን ሆነም አልሆነም ህዝብ ፈጣን ምላሽ ይፈልጋልና መስማትና ማየት እንደሚቻል በተግባር ማረጋገጥም ፖለቲካዊ ፋይዳ ይኖረዋል ፡፡

አስተዳደሩ ሳይቶችን ከጎበኘ አራት ቀን በኃላ ወደ ሰሚት ሳመራ ሁለት አዳዲስ ነገሮችን ተመለከትኩ ፡፡ አንደኛው ዋና ዋና መንገዶችን ለመስራት ቁፋሮው መጧጧፉን ፡፡ ሁለተኛው በየብሎኩ የተቆፈሩ ጉድጓዶች ውስጥ የግንብ ስራው በተሻለ የሰው ኃይል እየተከናወነ መገኘቱን ፡፡ በርግጥ ጅምሩ እንደተለመደው የአንድ ሰሞን እንዳይሆን ጸሎት ያሰፈልገዋል ፡፡ ለማንኛውም አስተዳደሩ ስራውንም ማጧጧፍ፣ ሌብነቱንም ማስቆም፣ ዘራፊዎችንም መዳኘት ይጠበቅበታል ፡፡ ምክንያቱም ይህ ህዝብ በብዙ ሊካስ ይገባዋልና ፡፡

No comments:

Post a Comment