Friday, December 19, 2014

የሂትለርና ቸርችል ሌላኛው እጆች !


አዶልፍ ሂትለርና ዊንስተን ቸርችል በተቃራኒው መንገድም ቢሆን የሚመሳስል ነገር አላቸው ። ሁለቱም በውትድርና ሀገራቸውን አገልግለዋል ። ሁለቱም ሀገራቸውን መርተዋል ። ሁለቱም ሀገራቸውን < ለማስቀደም > የአባራሪና ተባራራሪን ሚና ወክለው ተፋልመዋል - ሂትለር ድመት ቸርችል አይጥ እንዲሉ ።
ሁለቱም ሃይለኛ ተናጋሪ ናቸው ። ሁለቱም ደራሲ ናቸው ። እንደውም ሁለቱም ታስረው በእስር ቤት ውስጥ መጽሀፍ መፍጠራቸው ገጠመኙን ጠንከር ያደርገዋል ። ቸርችል በቦየር ጦርነት ወቅት ወደ ደቡብ አፍሪካ ባመራበት ወቅት ተይዞ እስር ቤት ውስጥ ተወርውሮ ነበር ። እዛ ግን ስራ አልፈታም ። < London to lady smith via Pretoria  > የሚል ስራ ጨርሶ ለአንባቢያን አቅርቧል ። ሂትለር የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አድርገሃል ተብሎ ዘብጥያ በተላከ ግዜ  < Mein Kampf  > ወይም የኔ ትግል የሚል ጠንካራ ስራ ሰርቶ በኌላ ላይ አሳትሞታል ። ርግጥ ነው ሂትለር በስሙ አስር ስራዎች ቢታተሙለትም ሁሉም እንደ ቸርችል ጠብሰቅ ያሉና ሚዛን የሚደፉ አይደሉም ። ቸርችል 43 መጽሀፍት ለአለም አበርክቷል ። በዚህም ጥረቱ በ1953 የስነጽሁፍ ኖቤል ተሸላሚ መሆን ችሏል ። ምናልባትም በዘርፉ ትልቅ ክብር ያገኘ ብቸኛው የአለማችን መሪ ነው ።
በስልጣናቸው ዘመን ሁለቱም የራሳቸው መለያ የሆነ የሰላምታ አሰጣጥ ስርዓት ነበራቸው ። ቸርችል ሁለት ጣቱን በማውጣት ሰላም ይላል - እናሸንፋለን ለማለት ጭምር ። ሂትለር ቀኝ አጁን ወደፊት በመዘርጋት ሰላምታ ይሰጥ ነበር - <  Seig Heli > - እናሸንፋለን እንደማለት ። ሁለት ጣት ሲወጣ መሳቅም መጥቀስም ይቻላል ። ቀኝ እጅ ወደፊት እንደ ቀስት ሲወረወር ግን ምናልባት ሂትለር ! ከማለት ውጪ መፈገግ አይቻልም - ኮስተር ብሎ ሰኮንዶችን ማሳለፍ እንጂ ። የናዚ ሰላምታ በአሁኑ ወቅት በጀርመን ፣ ኦስትሪያ ፣ ስሎቫኪያ እና ቼክ የወንጅል ድርጊት በመሆኑ እስከ ሶስት ዓመት ያስቀጣል ። የቪ ምልክት የትም ሀገር ወንጀል ባይሆንም በአንድ ወቅት በኢትዮጽያ የብዙዎች መቀጣጫ ሆኗል ።
ሁለቱም መሪዎች ሰዓሊዎች ናቸው ። በቀውጢው ዘመን ብሩሽና እርሳስ ጨብጠው በቀለማት ዜማ ሃሳባቸውንና ፍልስፍናቸውን ሸራ ላይ ተንፍሰዋል ። ርግጥ ነው ሂትለር በ1905 ገና በ16 ዓመቱ ዳገት የሆነበትን ትምህርት ትቶ ነበር ፕሮፌሽናል ሰዓሊ የመሆን ህልሙን ፍለጋ የጀመረው ። የቸርችል ህልም ከሰዓሊነት ይልቅ የጦር ዘጋቢነትና ደራሲነት ነበር ማለት ወደ እውነታው መንደር ጠጋ ያደርገናል ። ለማሳያም በወቅቱ በትላልቅ ጋዜጦች ላይ ይጽፋቸው የነበሩትን መጣጥፎችና ብርሃን ያዩ የህትመት ስራዎቹን መመልከት በቂ ነው ። ተደብቆ የቆየው የሰዓሊነት ፍላጎት ብቅ ያለው እንደ ሂትለር በወጣትነት ዘመን አይደለም - በጉልምስና/ 40 /  እንጂ ።
ቸርችል በአንድ ወቅት የፖለቲካው ህይወት ሲያስጠላው ራሱን አግሎ ነበር ። ያኔ ራሱን ለማዝናናት ከጽሁፉ ጎን ለጎን መስመሮችን መገጣጠም ጀመረ ። አንዳንድ መረጃዎች እንደሚነግሩን ስእሉን መማር የጀመረው ከጓደኛው ፓወል ሜዞ ነበር ። አንዳንድ መረጃዎች ደግሞ የታዋቂዎቹ ሰዓሊዎች ማለትም የክላውድ ሞንት ፣ ቪንስንት ቫ ጎህ እና ዊሊያም ተርነር ስራዎች ትልቅ ተጽዕኖ ፈጥረውበት እንደነበር ያስረዳሉ ።
        
Churchill 'S works
ለሂትለር የስዕል መስመሮችን ለመጀመሪያ ማን እንዳሳየው የሚገልጽ መረጃ የለም ። ይሁን እንጂ የትምህርት ቤቱ ሰርተፍኬት እንደሚያሳየው በብዙ ትምህርቶች በቂና ከበቂ በታች ውጤት አሰመዝግቦ በስዕል ትምህርት ግን < እጅግ በጣም ጥሩ > የሚል የሞቀ መገለጫ ነው የሰፈረለት ። ይህም ገና በታዳጊነቱ ስዕል አፍቃሪ መሆኑን ያቃጥራል ። ያም ሆነ ይህ የሂትለር ተጽዕኖ ውስጣዊ ፍላጎትና የህይወት ችግር ነበር ። አባቱ አሎያስ ሂትለርን ለሶስተኛ ግዜ ካገባት ሚስቱ በ51 ዓመቱ ነበር የወለደው ። ሂትለር ስድስት ዓመት ሲሞላው ጡረታ በመውጣቱ የችግር ጥላ ቤቱን በወፍራም ግራጫ ቀለም ለቅልቆት ነበር ። ሂትለር 13 ዓመት ሲሞላው ግራጫው ቀለም ወደ ጥቁርነት ተቀየረ - አሎይስ አረፈ ። እናቱ ክላራም በ1908 በጡት ካንሰር ሞተች ። እናም ራሱን ለማሸነፍ እንደ ቀስት መወርወር ነበረበት ።
በ1907 በቬና የስነጥበብ አካዳሚ ለመማር አመልክቶ ያቀረብከው ስራ ብቁ አይደለም ተብሎ ነበር ። በ1908 ትም ወደዚሁ ማዕከል መወርወር ግድ ብሎት ነበር ። አሁንም ለመግቢያ ፈተና ያቀረበውን ስራ የገመገሙ መምህራን ብቃት እንደሌለው በግልጽ ነገሩት ። በብቃቱ ይተማመን የነበረው ሂትለር ጠማማውን ምላሽ አምኖ ለመቀበል አልቻለም ። ተቋሙ ሂትለር ከሰዓሊነት ይልቅ በአርክቴክቸር የበለጠ ተሰጥኦ እንዳለው ያምን ነበር ። ሂትለር በአይሁዳዊያኑ መምህራን ላይ ቂም ቋጠረ ።
እንደ ቸርችል ከሃብታም ቤተሰብ ባለመፈጠሩ ስዕሉን ችላ ብሎ ሌላ የህይወት ሰበዝ የመምዘዝ እድል አልነበረውም ። እናም መሳሉን ገፋበት ። በተለይም ከ1908 እስከ 1913 በቬና ህይወቱን ለማቆየት በመቶ የሚቆጠሩ ስዕሎችንና ፖስት ካርዶችን ሰርቶ ሸጧል ።
ቸርችል በአንደኛው ዓለም ጦርነት ወቅት በጦር ሰራዊትና ባህር ሃይል ከፍተኛ የሃላፊነት ቦታዎች ላይ አገልግሏል ። ሂትለር የአንደኛው ዓለም ጦርነት ሲጀመር በኦስትሪያ ዜግነት በቫሪያን ጦር በፍቃደኝነት ለማገልገል ተቀላቀለ ። የስዕል ስራዎቹን ጦር ሜዳ ይዞ በመሄዱ < አርቲስቱ > እየተባለ ነበር የሚጠራው ። ጦርነቱ ቸርችልን እስከ ሚኒስትር ደረጃ እንዳደረሰው ሁሉ ሂትለርም የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ የጀግና ሽልማቶችን ከሻምበልነት ማዕረግ ጋር አስገኝቶለታል ። በትርፍ ሰዓቱም ለጦር ሰራዊቱ ጋዜጣ የካርቱን ስዕሎችን በመመገብ የአዝናኝነትን ሚና ከፍ አድርጓል ።
                             






hitler 's  works
የሂትለርና ቸርችል የአብዛኛዎቹ ስራዎች ጭብጥ መልከዓምድር ፣ ተፈጥሮና የሰው ምስል መሆናቸውን ስንመለከት ብዙ ጥያቄዎች ሊፈጠሩብን ይችላሉ ። ምክንያቱም ወቅቱ የፖለቲካ ውጥረት የበዛበት ፣ ህይወት በጥይት የሚያልፍበት ፣ አንዱ ሌላውን ለማጥቃት እንቅልፍ የሚያጣበት በመሆኑ ነባራዊውን እውነታ ማንጸባረቅ ለምን እንዳልፈለጉ ግልጽ አይደለም ።  ስራዎቻቸው ከጭብጥ አንጻር ተቀራራቢ ቢመስልም የስዕሎቹ መኳኳያ መንገድ ግን ለየቅል ነው ። ቸርችል የዘይት ቅብን መሰረት ሲያደርግ ሂትለር የውሃ ቀለም ይመቸዋል ። የስዕልን ፍላጎት ለረጅም ግዜ ይዞ በመቆየትም ቸርችል ቅድሚያውን ይይዛል ። ለዚያም ነው አምስት መቶ የሚደርሱ ስራዎችን ያመረተው ። የእንግሊዙ ታዋቂ ሰዓሊ ሰር ኦስዋልድ በርሊ << ቸርችል ለፖለቲካው እንደሰጠው ሰፊ ግዜ ለስዕሉም ቢሰጥ ኖሮ ዓለማችን ታላቂ ሰዓሊ ታገኝ ነበር >> ሲል ተናግሯል ። በአሁኑ ወቅትም የቸርችል ስራዎች በጨረታ እየተጫረቱ በሚሊየን ዶላር እየተሸጡ ናቸው ። በሌላ በኩል < civil registry office and old town hall of munich > የሚል ርዕስ የያዘው የሂትለር ስራ በ 161 ሺህ ዶላር ተሸጧል ። አጫራቹ ድርጅት ለኒዊስክ እንደገለጸው ስራው በጥሩ ሁኔታ የሚገኝ ሲሆን የሰዓሊውንም ችሎታ ያሳየ ነው ። ምንም እንኳን ብዙዎች የዚህን ከይሲ ሰው ጥሩ ስራ መስማትም ማድነቅም ባይፈልጉም ።
ርግጥ ነው ሂትለር ለሁለተኛው ዓለም ጦርነትና ለ 11 ሚሊየን ዜጎች እልቂት ተጠያቂ ነው ። ሂትለር እጆቹ በደም ከመጨማለቃቸው በፊት በስዕል ህብረ ቀለማት የለመለሙ ነበሩ ። ስዕሎቹን ተራ በተራ የተመለከተ ሰው መገረሙና መመሰጡ አይቀሬ ነው ። ስሜታዊ ከሆነም የቬና የስነጥበብ አካዳሚ እውነት ምን ነክቶት ነው ሁለት ግዜ ጠልዞ ከግቢ ያባረረው ? ሊል ይችላል ። ምናልባት ሂትለር ሰዓሊ ሆኖ ቢቀጥል የሁለተኛው አለም ጦርነት ርዕሰ ጉዳይ ላይኖር ይችላል ። ይህ ጦርነት በመወለዱ ግን ሂትለር ጥበባዊ ልዕልናውን ሲያጣ ቸርችል የሞገስ ካባና አክሊሉን አጠልቋል ። ምክንያቱም በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ላይ የሚያትቱ ስድስት መጽሀፍት ደርሷልና ። ሂትለር አይጥ ቸርችል ድመት እንዲሉ ።
የሂትለር ጺም ፣ የቸርችል ሲጋራ ድንገት በምናብ ብቅ እንደሚልብን ሁሉ ፤ የሂትለርን ተሸናፊነት የቸርችልን አሸናፊነት ምሳሌ እንደምናደርገው ሁሉ ፤ ሂትለርን በጨካኝነት ቸርችልን በደፋርነት እንደምንበይነው ሁሉ ፤ የሁለቱንም  ሌሎች ተመሳሳይ እጆች ማወቅ ይኖርብናል ። እናም እንደእኔ እምነት የስዕል ስራዎቻቸውን አሰባስቦ በአንድ ሙዚየም ውስጥ ለማሳየት የሚተጋ ግለሰብ ወይም ተቋም ያስፈልጋል ባይ ነኝ ።