Wednesday, October 10, 2012

የተረሳው ባህል ትንሳኤ ያገኝ ይሆን ?




ኪነ ጥበብ ያዝናናል፡፡ የህብረተሰቡን አስተሳሰብ በአስደሳች መልኩ ቀርጾ መልሶ ለህብረተሰቡ ሲያቀርብ  ‹‹ ወቸው ጉድ ?! ›› ያሰኛል    ፡፡ ታዲያ ልንሰንቅ በምንችለው ግርምት ውስጥ  የመምህርነት ሚና አለው ፡፡ ባልተሰላቸ መልኩ የሚሰጠው ዕውቀት እንደኛ ባሉ ድሃ ሀገሮች ውስጥ ተጠናክሮ መቀጠሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ ዕድገታችንን ዕውን ለማድረግ ይጠቅማል ፡፡

በተረት ፣ በወግ፣ በስነቃልና በስነግጥም ሀብታም በሆነቸው ኢትዮጽያ ‹‹ ኪነ ጥበብ ›› ሲጫወት የቆየው ሚና ቀላል አለመሆኑ ርግጥ ነው ፡፡ ቅድመ አያቶቻችን  በማህበራዊ ትስስራቸው ውስጥ በጉልህ ሲያንጸባርቁት ቆይተዋል ፡፡ በዚህ ረገድ የ ‹‹ በልሐ - ልበልሃ ›› ስርዓት በዋናነት ሊጠቀስ ይችላል ፡፡

በታሪክ የመጀመሪያዎቹ ጠበቆች ካህናት፣ የህግ ምንጭ ደግሞ ብሉይ ኪዳን እንደነበሩ ይነገራል ፡፡ በሀገራችንም ተሟጋቾች የህግ ዕውቀት ያገኙ የነበረው በገዳማትና በሌሎች መንፈሳዊ ተቋማት ፍትሐ ነገስትን በማጥናት እንደነበር ‹‹ ጠበቃና ስነ ምግባሩ ›› የሚለው መጽሀፍ ያስረዳል ፡፡ በርግጥ የድሮ ጠበቆች እንደዛሬው ህግ የሚማሩበት ትምህርት ቤት አልነበራቸውም ፡፡ ትምህርት ቤታቸው አደባባይ ነው ፡፡ ጥብቅናን የሚማሩት ተረት፣ ወግ፣ ሰምና ወርቅ፣ ባህልና ስነ ግጥም በማጥናትና በመለማመድ ነበር ፡፡
የሚከተለው ክርክር ልጅነትን ለማሳወቅ የተደረገ ነው ፡፡ ተከራካሪዎቹ ምን ያህል የስነ ግጥም ብቃት እንዳላቸው እንመልከት ፡፡
ከቤት ክፉ ሰቀላ
ከልብስ ክፉ ነጠላ
ከእህል ክፉ ባቄላ
ከልጅ ክፉ ዲቃላ
መልኩ የእናሪያ / ጥቁር /
እግሩ መታረሪያ
እየው ፊቱን የተገዛበቱን
እናም አላውቅም ልጅነቱን ብሎ ይቃወማል ፡፡

መላሽም በተቃራኒው ወገን የተነሳውን እያንዳንዱ መሰረታዊ ነጥብ በመልቀም የማፍረሻ ወይም የመቃወሚያ ሀሳቦችን ይሰነዝራል ፡፡

ክረምት ያወጣል ሰቀላ
ከብርድ ያድናል ነጠላ
ቀን ያሰልፋል ባቄላ
ጠላት ይገፋል ዲቃላ
መልክም ቢጠቁር የዘር ነው
እግሩም ቢቀጥን ዘምቶ ነው
ስለዚህ ያለብህ ማወቅ ነው በማለት ጠንካራ የአጸፋ መልስ ይሰጣል ፡፡

የታወቁ ጠበቆች አደባባይ ሲሟገቱ ነጭ ልብስ ለብሰው፣ አደግድገው፣ አንዳንዴም ጎራዴ ታጥቀው፣ በቀጭን ዘንግ ወደፊት እየተወረወሩ ሲናገሩም እየጮሁ ነበር ይባላል ፡፡ ይህ እንግዲህ በክርክሩ ውስጥ ከስነ ግጥም ሌላ የትወና ጥበብም እንደሚንጸባረቅ ጠቋሚ ነው ፡፡

በአንድ ወቅት አባትና ልጅ ተጣልተው ተካሰሱ አሉ ፡፡ ይህ በሀገራችን ባህላዊ ልማድ ያልተለመደ ቢመስልም አንዳንዴ ወጣ ያለ አመለካከትና አተያይ  ያላቸው ልጆች አይፈጠሩም ማለት ግን አይቻልም ፡፡ እናም ልጅ ጉዳዩን ባህላዊው ፍርድ ቤት እንዲያይለት አመለከተ ፡፡ አባት ይህን የመሰለ ድፍረት ባይዋጥለትም ልጅ ተጠየቅ ማለቱ አልቀረም ፡፡ በህግ አምላክ ተጠየቅ !! አለ ልጅ  ወግድ !! እያለ አንገራገረ አባት ፡፡ በወቅቱ ለታዳሚው ያሰሙት ሙግትም የምጥቃታቸውን ደረጃ እንዴት አንጸባርቆ እንደነበር በቅንጭብታ እንመልከተው ፡፡

ልጅ ፤  ተጠየቅ ልጠይቅህ ?!
አባት ፤  አልጠየቅም
          ሰማይ አይታረስም
          ውሃ አይታፈስም
         መሬት አይተኮስም
         አባት አይከሰስም !!
ልጅ ፤  ሰማይ በመብረቅ ይታረሳል
         ውሃም በእንስራ ይታፈሳል
         መሬትም በማረሻ ይተኮሳል
         አባትም በጥፋቱ ይከሰሳል !!
አባት ፤ ፍረዱኝ ሰማይ ያለ መዓት ነጎድጓድ አያወርድ
         ፈጣሪ ያለ ክህደት ገሃነም አያወርድ
         ያለ እርሻ በመሬት ላይ እሳት አይነድ
         ሴትም ያለ እንስራ ውሃ አትወርድ
         አባትም ያለ ጥፋት ልጁን አይክድ
         አባት ለልጁ ዳኛ
         አትሞግተኝም ዳግመኛ !!

ልጅም በዋናነት የአባቱን የምላሽ ሰበዝ እየመዘዘ የማጣመም ወይም ሀሳቡን የማክሽፍ ተልዕኮውን ይቀጥላል ፡፡ ለምሳሌ ያህል አባት ልጄን የካድኩት ስላጠፋ ነው የሚል ሀሳብ ፈንጥቋል ፡፡ ልጅም ጥፋት የተባለውን ነገር በመዘርዘር ንጹህ መሆኑን ለማስረዳት እስከ መጨረሻው ይተጋል ማለት ነው ፡፡ ሌላው አስገራሚ ገጽታ ሁልግዜም ቢሆን ተከራካሪዎች ጥፋተኛ መሆናቸውን ልባቸው ቢነግራቸው እንኳን ከፍተኛ የራስ መተማመን እንዳላቸው የሚያሳዩበት መንገድ ነው ፡፡ ባላጋራቸውን በማስደንገጥ ከክርክሩ እንዲወጡ ከፍ ያለ ቃል ይገባሉ ፡፡ ለምሳሌ ያህል አንደኛው ፤

በልሀ ልበልሃ ልንዛብህ
የሙግት ዠሃ
ሀሰት ቢገኝብኝ በቃሌ
ቅቤ አምጥቼ በብርሌ
እሰጣለሁ ለሽማግሌ ሊል ይችላል ፡፡ ሌላኛውም

በላ ልበልሃ
ልንዛብህ የሙግት ዠሃ
ብትወነጅለኝ በሀሰቱ
ይበረታብሃል ቅጣቱ
የረታህኝ እንደሁ ተሟግቼ
ቀንጃ በሬዬን አምጥቼ
ለዕለት ጉርሴ እንኳን ሳልሳሳ
አገባታለሁ እምቦሳ


በማለት የጠነከረ ምላሽ ይሰጣል ፡፡ ከዚህ በኃላ ክርክሩን ራሳቸው ስላጦዙት ሰሚውም ሆነ ፍርድ ሰጪዎች ዳኞች ቀጣዩን ለመስማት ያቆበቅባሉ ፡፡

እስቲ ሌላ ዘወር ያለ አብነት ደግሞ እንመልከት ፡፡ አንድ በሬ የጠፋበት አርሶአደር በፍለጋ ረጅም ሰዓት ቢያሳልፍም በቀላሉ ማግኘት አልቻለም ፡፡ ሁኔታው አበሳጨው ፡፡ ጉዳዩን ዝም ብሎ መተው የለበትምና በፍለጋ ሰዓታት ያያቸውን ጥቃቅን ፍንጮች በማገጣጠም የሰፈሩን ሰው ጠረጠረ ፡፡ እናም ሊሞግተው አደባባይ አቆመው ፡፡ 

ከሳሽ ፤ የአጤ ስርዓቱን የመሰረቱን
         አልናገርም ሀሰቱን
         ሁልግዜ እውነት እውነቱን
         መጣሁ እንደ ውሃ ስፈስ
         እንደ ጋዣ ስነፍስ
         በቅሎዬ ሰጋሪ
         ሚስቴ ነጭ ጋጋሪ
         ለወታደር የለው ምሳ
         ለቀበሮ የላት ገሳ
         በሬዬ ጠፍቶ ከደጋ
         ስከተል  መጣሁ በደም ፍለጋ
         ብደርስ በፍለጋው ከደጅህ
         ሙዳ ስጋ ይዟል ልጅህ
        ስለዚህ በሬዬን ትከፍላለህ በግድህ !!

ተከሳሽ ፤ ፍየል መንታ ትወልዳለች አንዱ ለመጣፍ
           አንዱ ለወናፍ
           መጣፉ እኔ መናፉ አንተ
           እንደ ውሃ ብትፈስ በቦይ ትመለስ
           እንደ ጋዣ ብትነፍስ አጭዶ ለፈረስ
           ሚስትህ ነጭ ብትጋግር  አንድ እንግዳ አታሳድር
           በቅሎህ ብትሰግር እመሸበት ታድር
            እንዴት ለወታደር የለውም ምሳ
            እራት ጋግሮ ለራት ለምሳ
            እንዴት ለቀበሮ የላት ገሳ
            ትገባለች አርባ ክንድ ምሳ
            በሬህ ቢጠፋ ከደጋ
            አንተም ብትመጣ በደም ፍለጋ
            ከቤቴ በላይ አለ ተራራ
            መዘዋወሪያው የጅብ ያሞራ
            አሞራና ጅብ ሲጋፉ
            ሙዳ ስጋ ስጋ ስለተፉ
            ያላወቀ ልጅ ቢያነሳ
            አያስከፍለኝም ነገርህን አንሳ !!  ይለዋል ፡፡ 

ተሟጋቾቹ በግለት ሲከራከሩ ከየጎጡ መጥተው የታደሙ ሰዎች በክርክሩ መሃል    ‹‹ እውነት ነው !! በደንብ አርገህ ንገረው !! ይገባዋል !! ›› በማለት ደጋፊ ሀሳብ በማቅረብ አጋርነታቸውን ይገልጻሉ ፡፡

ይህን በመሰለ መልኩ የሚደረግ ክርክር ላይ መገኘት መንፈስን እንደሚያስደስት አያጠራጥርም ፡፡ ከዘመናዊ ህግ አሰራር አኳያ ‹‹ በልሀ ልበልሃ ›› አንዳንድ ክፍተቶች ሊኖሩበት ቢችልም ይህ ድንቅ ባህል እየተረሳና እየጠፋ መሄዱ በተለይም ኪነ ጥበብን የሚጎዳ ይመስለኛል ፡፡ ሰዎች ሀሳባቸውን በግጥምና ስነ ቃል መግለጻቸው ፣ በግጥም የሚቀርቡ ሀሳቦችን ደግሞ ያለ ምንም ችግር ማጣጣም መቻላቸው ለደራሲዎች ቀጣይና የጠነከረ ፈጠራ ምርኩዝ ይሆናል ፡፡ ጥሩ ልቦና ያላቸው ደራሲያን በበዙ ቁጥር ብዙ እንዲጽፉ ይገፋፋቸዋልና ፡፡

በልሀ ልበልሃ በአሁኑ ወቅት ለዘመናዊ ህግ አያስፈልግ ይሆናል ፡፡ ወይም አባት ነኝ ባዩ ህግ ያንተ ነገር በቃኝ በማለት ክዶት ይሆናል ፡፡ ግን በልሃውንና ዘመናዊውን ህግ እንደ ሀገራችንና እንደ ሌሎች ሀገሮች ፕሬዝዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር በንጽጽር ማየት ጠቃሚ ይመስለኛል ፡፡ በልሃውና ንጉሱ የመወሰን ስልጣናቸው አነስተኛ ቢሆንም ክብርና ሞገሳቸው ትልቅ ነው ፡፡ ፕሬዝዳንታችን ህጎችን በነጋሪት ጋዜጣ ያውጃል ፤ በልሃው የቀድሞው ማንነታችን አለመሞቱን ያውጃል ፡፡ ፕሬዝዳንታችን የሹመት ደብዳቤ ይቀበላል ፤ በልሃው ከገጠር ቅኔ ዘራፊዎችም ሆነ ከከተሜው ገጣሚዎች የተሳትፎ ጥያቄዎችን እየተቀበለ የተቀናጀ ተሳትፎ እንዲደረግ ሀሳብ ሊያመነጭ ይችላል ፡፡ ፕሬዝዳንታችን ኒሻኖችንና ሽልማቶችን ይሰጣል ፤ በልሃው በት/ቤት፣ በትያትር ቤት፣ በዩኒቨርስቲዎችና በኮንሰርቶች ውድድር እየተካሄደ ለሚያሸንፉት ሽልማት ይሰጣል ፡፡ ፕሬዝዳንታችን ይቅርታ ያደርጋል ፤ በልሃው ተሸናፊዎች በተጋነነ ቅጣት እንዳይጎዱ ይቅርታ ያደርጋል ፡፡

ታዲያ ማነው ይህ ጠቃሚ ባህል ተጠብቆ እንዲቆይ መስራት ያለበት ? እንደ እኔ እምነት ቢያንስ ይህን የህግ የበኩር ልጅ በጉዲፈቻነት ለማሳደግ የባህል መዋቅሮችና በደምሳሳው ከያኔዎች ግንባር ቀደም ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል ፡፡


No comments:

Post a Comment