ሰውየው ተይዘዋል ፡፡
ነፍሳቸውን ይማረውና አቶ መለስ ነበሩ በየጋዜጣዊ
መግለጫውና በፓርላማ ስብሰባ ላይ የሚያከናንቧቸው ፡፡ አተራማሹ ፣ ማፊያ፣ አሸባሪ ፣ ወሮበላ እረ ምን የማይሰጧቸው ስም ነበር
?
ዛሬ በህመም ተይዘው ‹‹ እረ ማን ይስደበኝ
? እረ ማን ይገስጸኝ ? ›› በማለት ትችቱንም ሆነ የቀደመውን የትግል ትዝታ ያንጎራጉራሉ ለማለት አይደለም ፡፡ በህመምና በጭንቀት
ክበብ ውስጥ መገኘታቸው ፈጣን የምላስም ሆነ የተግባር ምላሻቸውን አደበዘዘው ለማለት እንጂ ፡፡
እንጂማ እሳቸውስ ለማን ይመለሱ ነበር
?!
የኢትዮጽያ ባለስልጣናት የጥቅም ገመዳቸውን መበጣጠስ
ሲጀምሩ ባልታሰበ ፍጥነት አይደል ባድመን መያዣ ያደረጉት ፡፡ እየፈሩ በግልጽ ባይናገሩም በሆዳቸው ‹‹ የትልቋ እስር ቤት መሪ
! ›› እያሉ ሊያሽሟጥጡ በሚችሉ የአፍሪካ መሪዎች ላይ አጋጣሚን ሰበብ በማድረግ ከመዝለፍ መች ይቆጠባሉ ፡፡ ‹ የአፍሪካ ሰሜን
ኮሪያ › እያለ የሚያጣጥላቸውን ተመድ ጽ/ቤቱ ድረስ በመሄድ ያልተገባ መልስ ሰጥተዋል ፡፡ የትግሉ ዘመን ወጣ ውረድ ትዝ ሲላቸው
የመንን ፣ መዝናናት ሲፈልጉ ጅቡቲን ወረው እንካሰላንቲያ ለመጫወት መች ወደ ኃላ የሚሉ ነበሩ ፡፡
ዛሬ ግን በህመም ተፋዘዋል ፡፡
እንጂማ ምኑ የቆረጠው ነው የሚፈታተናቸው ?!
ለዛውም የሀገራቸው ሰው ፤ ለዛውም በእፍኝ ታንክ የሚታገዙ በመቶ የሚቆጠሩ ወታደሮች ፡፡ የአምስት ሚሊዮን ህዝብ መሪ ቢሆኑም በ
200 ሺህ ወታደሮች የተዋቀረ ጦር ሰራዊት ባለቤት መሆናቸውን ይህ ነገር ፈላጊ ቡድን አያጣውም ፡፡ ደግሞ ምናለበት የደመወዝና
የፋቲክ ጥያቄ ቢያነሳ ! የሀገሪቱን ማስታወቂያ ሚኒስቴር ከቦ ሁለት ህመም የሚጨምሩ ጥያቄዋችን ይለኩሳል እንዴ ?! በርግጠኝነት በነዚህ ጥያቄዎች ከሚፈተኑ በቢጫ ወባ ቢያዙ ይመርጣሉ ፡፡ ደረታቸው
ላይ የተቀረቀረው አንደኛው ጩቤ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ የሚለው ነው ፡፡ አንገታቸውን አላዞር ያለው ሁለተኛው ጥያቄ የ
1997ቱ ህገ መንግስት ስራ ላይ ይዋል የሚል ነበር ፡፡
ሰውየው በነዚህ ጥያቄዎች አተነፋፈሳቸው
ተዛብቷል ፡፡
ወይ ታሪክና ፖለቲካ አለማወቅ ! ይፈቱ ከተባሉ
የፖለቲካ እስረኞች መካከል 11 ዱ ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩ ሲሆን ወደ እስር ቤት የተወረወሩት የሰውየውን ህልውና ሊያቆም የሚችለውን
የ ‹‹ ፍትሃዊ ምርጫ ›› ጥያቄ በማንሳታቸው ነበር ፡፡ በ1997 የጸደቀው ህገ መንግስት ደግሞ ከኢትዮጽያ በሄደ ምርጥ የአወዳይ
ጫት ውብ ሆኖ ከተፈጠረ በኃላ ምርቃናው ከጠፋ በኃላ የግምግማ ጅራፍ የጮኀበት እንደነበር ሀገር ያውቀዋል ፡፡ የፕሬስ ፣ የሃይማኖት
፣ የፖለቲካ በአጠቃላይ ለኤርትራዊያን የሰጠው መብት በእጅጉ እንደ ውብ ሴት የቆነጀ ነበር ፡፡ እና ይህችን ህገ መንግስት ማሽኮርመምና
ፍቅር ማስያዝ ያለበት ወጪ ወራጁ ሁላ ነው ወይስ ሰላሳ ዓመት ቆስሎና ደምቶ እዚህ የደረሰው የሰውዬው ፓርቲ ? - መልሱ ፓርቲ
የሚለው ይሆናል ፡፡ እና ፓርቲዎ ምን ወሰነች ? - መልሱ የሚከተለው ይሆናል ፡፡ ‹‹ ይህችን ውብ ህገ መንግስት ከማፈራረስ እንደተዋበች
ትቆይና ቋሚ ሙዚየም ውስጥ በክብር ትቀመጥ ፡፡ ሁሉም አፈጣጠሯን ያድንቅ ፡፡ እሷን የማናገር ስልጣን ግን ለርዕሰ ብሄሩ ይሰጥ
›› ይህ ህግ እንዴት አለፈ ? - መልሱ በአክላሜሽን !!
ሰውየው ተዳክመዋል ፡፡
እንጂማ እንደ ሌሎች አፍሪካዊ ሀገሮች ‹‹ ተዋበች
›› የሚል ስያሜ ያገኘቸውን ህገ መንግስት ጥላሸት ለመቀባት የሚንቀሳቀሱ ጥቂት ወታደሮችን በለመደው ፍጥነታቸው ዘለው ጉብ አይሉባቸውም
ነበር ፡፡ ወታደሮቹ ጥያቄያቸውን በቴሌቪዥን ማስነገራቸው ብቻ ሳይሆን ለዚህ መ/ቤት ቁልፍ የሆነችውን የሰውየውን ሴት ልጅ ኤልሳን
እንደ መያዣነት መጠቀማቸው የድፍረቱን ደረጃ ከፍም ባደረገው ነበር ፡፡
ወታደሮቹ ተልኳቸውን ፈጽመው ከተመለሱ በኃላ እንኳ
የሰውየው ድምጽ የተሰማው ወሬው ከቆረፈደ በኃላ ነው ፡፡ ብዙና ዝርዝር ነገር እንደሚያወሩ ቢጠበቅም ‹‹ የከሰሩ ጠላቶች ናቸው
! ›› የምትል ብጣቂ ነገር ነው ወርወር ያደረጉት ፡፡ እነማን ናቸው ? ከጀርባቸው ማን አለ ? ፍላጎታቸው ምንድነው ? ሰውየው
ይህን በስድብም ሆነ በንቀት ለመመለስ አቅም በማጣታቸው መልሱ እንጃ ሆኗል ፡፡ ልክ እንደ አሁኑ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራም ይሁን የማስተካከያ ጥያቄ በአንድ
ወቅት ዓለም ስለ ሰውየው መሞት ይነጋገር ነበር ፡፡ አንዳንዶች በግላጭ በደስታ ጨፍረዋል ፣ አንዳንዶች በድብቅ የውስኪና ቢራ ብርጭቆ
አጋጭተዋል ፡፡ ታዲያ ሰውየው እንደምንም በገመምተኛ አካል ቴሌቪዥን መስኮት ላይ ብቅ ብለው ‹‹ የታመሙት አሉባልታውን የሚነዙት
ናቸው ! ›› በማለት ጠላቶቻቸውን ኩም አድርገዋል ፡፡ ጣታቸውንም ወደ አሜሪካና ኢትዮጽያ ቀስረዋል ፡፡ ዛሬ ግን ወታደሮቹን ባሰማራው
አካል ላይ ለመደንፋት አልፈለጉም ወይም አልቻሉም ፡፡
እነሆ ሰውየው ! …
ስም - ኢሳያስ አፈወርቂ
የእናት ስም - አዳነች በርሄ
የትውልድ ዘመን - 1965 / እአአ /
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት - ልዑል መኮንን
ዩኒቨርስቲ - ለሁለት ዓመት የምህንድስና ትምህርት
ማስት - ሳባ ኃይሌ
ልጆች - አብርሃም ፣ ኤልሳ እና ብርሃኔ
የሚያበሳጫቸው ጉዳይ - የወያኔ ክህደት
ሃይማኖት - ኦርቶዶክስ
ደርግ በወደቀ ማግስት በኤርትራዊያን ‹‹ ጀግና
! ›› ተብለው ሲሞገሱ የቆዩት አቶ ኢሳያስ የተቻኮለ ቢሆንም በብዙዎችም ሞገስና ክብር አግኝተው እንደነበር ይታወቃል ፡፡ ውሳኔ
ህዝብ ለመታዘብ የሄዱት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በራሳቸው መጽሀፍ ላይ ‹‹ የነጻነታቸው ቀን እኔ ፣ መለስና ኢሳያስ / በስሊፐር ጫማ
/ ከተማ ውስጥ ዞረናል ፡፡ በእውነት ትልቅ ነጻነት ነበር የተሰማኝ ፡፡ ሱቅ እየገባን ፣ ማታ ማታ እየዞርን አንድ ሁለት ቦታ
መጠጥ እየተጎነጨን ተዝናንተናል ›› በማለት በተዘዋዋሪ የሰውየውን ዲሞክራትነት አስረድተዋል ፡፡ የአሜሪካ መንግስት የወደፊቱ የአፍሪካ
ዴሞክራት መሪዎች በሚል በግልጽ ዕውቅና ከሰጣቸው አራት መሪዎች መካከል አንደኛው ኢሳያስ ነበሩ ፡፡ አቶ መለስም በደህናው ዘመን
‹‹ ከኢሳያስ ጋር አንድ ሰዓት ማሳለፍ አስር መጽሀፍ ከማንበብ በላይ ልበ ብሩህ ፣ አዋቂ እና ተጠቃሚ ያደርጋል ›› በማለት ታላቅነታቸውን
መስክረዋል ፡፡
ዛሬ የቀድሞው ምስክርነት መገልበጡ ብቻ ሳይሆን
ሚዛናዊነቱም ያልተመጣጠነ በመሆኑ የሰውየውን ሰብዓዊ ትከሻ እስከማጉበጥ ደርሷል ፡፡ ‹‹ ተዋበች ›› ላይ የሰፈረውን መርህ ከማስከበር
ይልቅ የሀገር ደህንነትን ማረጋገጥ ይቀድማል የሚለው ፍልስፍናቸው እየጠለፋቸው ነው ፡፡ በተለይም የፖለቲካ ፣ የፕሬስ ፣ የሃይማኖት
ነጻነቶችን መጨምደድና ‹‹ ሳዋን ›› የመለጠጡ አሰራር ያስከተለው ጦስ ሀገሪቱንና ራሳቸውን የመጨረሻ ጠርዝ ላይ እንዲገኙ አድርጓቸዋል
፡፡ እሳቸው በደምና አጥንት የተገነባውን አጥሬን አትነቅንቁ ሲሉ ፣ ሌሎች በአጥሩ ታፍነናል ፣ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚፈጸመው በደልና
ጭቆና አንገፍግፎናል በማለት ጀርባቸውን እያዞሩባቸው ይገኛሉ ፡፡ ታማኝ ይባል የነበረው ጦር ሰራዊታቸው እንኳ ዛሬ በእሳቸው መስመር
ለመሰለፍ እያንገራገረ ነው ፡፡ በርግጥ ሰሞኑን ያልተጠበቀ ድፍረት ያሳዩ ውስን ወታደሮች አዲስ የተቃውሞ ምዕራፍ መክፈታቸው ካልሆነ
በስተቀር የብዙሃኑን መለዮ ለባሽና ሲቪል ማህበረሰብ ስሜት ነው ያንጸባረቁት ፡፡
የሰውየው አዲሱ ጠላት ማነው ?
ኢሳያስ እአአ ህዳር 2012 የረጅም ግዜ ወታደራዊ
አማካሪ የነበሩትን ሜጀር ጄኔራል ፊሊጾስ ወልደ ዮሀንስ አስረዋል ፡፡ በቅርቡ አፍንጫቸው ስር ቀርቦ በጠመንጃ አፈሙዝ አፍንጫቸውን
ያለፍርሃት የጎረጎረው ቡድን መሪ እኚህ ጄኔራል መሆናቸውን አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ጽፈዋል ፡፡ እኚህ ጄኔራል ቀደም ባለው ግዜ
በምዕራባዊው የኢትዮጽያና ሱዳን ድንበር አካባቢ አዛዥ ሆነው አገልግለዋል ፡፡ ከፍተኛ የውጊያ ልምድ ያላቸው ጄኔራሉ በወታደሩ ዘንድም
ከፍተኛ የፖለቲካ ክብር አላቸው ነው የሚባለው ፡፡ ኢሳያስ ህዳር ወር ላይ ሲያስሯቸው በወታደሩ መካከል ክፍፍል እንደሚፈጠር ወይም
የተቃውሞ የመገለጥ ምዕራፍ ሊጀመር እንደሚችል ስሌት ወስጥ አልገባም ነበር ፡፡ ጄኔራሉ ሲታሰሩ የተኳቸው ጄኔራል ተክላይ/ ማንጁስ
ክፍላይ ይባላሉ ፡፡ እናም በቋፍ ላይ የሚገኙት ኢሳያስ ከሞቱ ወይም ጤናቸው የከፋ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ከታወቀ ፊሊጾስ የማንጁስን
ተግባር ለመገደብ ሲሉ ከታማኝ ወታደሮቹ ጋር ይህን ስራ ሊመሩ ይችላሉ - እንደ ተንታኞች መላምት ፡፡ እንደ ብዙዎች እምነት በቦታው
ላይ ጥቂት ወራት ያሳለፉት ማንጁስ የኢሳያስን ቦታ ሊሸፍኑ ይከብዳቸዋል ፡፡ ፊሊጾስ ቦታውን ከተረከቡ ግን በሀገሪቱ ጠንካራ ወታደራዊ
ተቋም ይዘረጋል ፡፡
ሁለተኛው ግምት ያነጣጠረው ኮማንደር ሳላህ ኦስማን
ላይ ነው ፡፡ እኚህ ሰው ከ1998- 2000 ከኢትዮጽያ ጋር በተደረገው ደም አፋሳሽ ጦርነት እንደ ጀግና ይቆጠራሉ ፡፡ እንዴት
ቢሉ በውጊያው ወቅት ደቡባዊ አሰብን ለቀው እንዲወጡ ቢታዘዙም ትዕዛዙን ባለመቀበል የኢትዮጽያን ጦር ወደ ኃላ እንዲያፈገፍግ አድርገዋልና
፡፡ እኚህ ሰው ሌላው የሚታወቁበት ጉዳይ ሀገሪቱ ወደ ዴሞክራሲያዊ ጎዳና እንድትገባ ለመንግስታቸው ሀሳብ የሚያቀርቡ መሆናቸው ነው
፡፡
እነዚህ ሁለት ወታደሮች የሰውየው አዲሱ ጠላት
ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገመት እንጂ ኢሳያስ በቁጭትም ሆነ በህመም ጥላ ስር ሆነው ጠላታቸው ላይ ማንባረቅ አልፈለጉም ፡፡ በመሆኑም
አዲሱን ጠላት በግምት እንጂ በበቂ ማስረጃ ማረጋገጥ አልተቻለም ፡፡
የሰውየው ጅራፍ !
ኢሳያስ አፈወርቂ ‹ ጭር ሲል አልወድም ! ›
የሚለውን ኢትዮጽያዊ ዜማ ይወዳሉ እየተባሉ ይታማሉ ፡፡ የመን ያስጮሁት ጥይት ቀዝቀዝ ካለ ጅቡቲ ፣ የጅቡቲው መፋዘዝ ሲጀምር በሶማሌ
፣ የሶማሌው ቃናው መጎምዘዝ ሲጀምር በባድመ መስማት አለባቸው ይሏቸዋል - ስም አጥፊዎች ፡፡ ይህ ሁሉ ካልሆነ ደግሞ አስመራ ላይ
እውነተኛ ጅራፍ ገምደው ያስጮሁታል አሉ ፡፡ ጅራፉ በጣም ካቆሰላቸው መካከል ሁለቱን የነጻነት ልጆች ፕሬስ እና ሃይማኖትን መጠቃቀስ
ይቻላል ፡፡
ሀ . የፕሬስ ነጻነት
አንድ አይናማው የኤርትራ ፕሬስ ወደ ማየት የተሳነው
የተቀየረው መስከረም 2001 ነበር ፡፡ ቀደም ብሎ 11 የሚደርሱ የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት በንቃት ሲሳተፍ በነበረ አንድ የግል
ጋዜጣ ላይ መንግስት ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ እንደሚገባው የሚያስገነዝብ ጽሁፍ አወጡ ፡፡ ፈጣን ምላሽ በመስጠት የሚታወቁት
ኢሳያስ 11 ዱን ባለስልጣናትንና ደብዳቤውን ያተሙ 10 ጋዜጠኞችን ወህኒ ቤት ወረወሯቸው ፡፡
ከዚያ የግል ሚዲያ ከህትመት ዉጪ እንዲሆኑ ተደረገ
፡፡ ማንኛውም የህትመት ዉጤት ከመታተሙ በፊት በመንግስት የጹሁፍ ዘበኞች እንዲመረመር ታዘዘ ፡፡ ጋዜጠኞች በሚደረግባቸው ወከባና
የማስፈራራት ተግባር ከሀገር መሰደድ አበዙ ፡፡ ዓለማቀፉ ፕሬስ ፋውንዴሽን በ 2012 ባወጣው መረጃ መሰረት ኢሳያስ 30 የሚደርሱ
ጋዜጠኞችን አስረው በመጥፎ ሁኔታ ላይ እንዲገኙ አድርገዋቸዋል ፡፡ ‹‹ ማንኛውንም የውጭ ሚዲያ መረጃ እንዲያገኝ አንፈቅድም
›› የሚሉት ኢሳያስ ሀገራቸው ፍቃድ የምትሰጠው ስለ ሀገሪቱ መልካም ገጽታ ለማውራት ፍቃደኛ ለሚሆኑት ብቻ መሆኑን በአንድ ወቅት
ተናግረዋል ፡፡ በአንዳንድ የተመረጡ ካፌዎች ውስጥ ኢንተርኔት የሚጠቀሙ ዜጎች ጥብቅ ክትትል ይደረግባቸዋል ፡፡ በቅርቡ የወጣው
የፕሬስ ነጻነት ኢንዴክስም በኤርትራ የመናገር ፣ የመጻፍና የመሰብሰብ መብቶች የተከለከሉ በመሆናቸው የመጨረሻውን 179 ኛ ደረጃ
ለማግኝት ግድ ብሏታል ፡፡ ይህም ዜጎች ምን ያህል በአፈና እየተሰቃዩ መሆኑን ያመለክታል ፡፡
ለ . የሃይማኖት ነጻነት
ቁስለኛው ሃይማኖት በኤርትራ ህዝብ ሲመነዘር
40 ከመቶው ክርስትያን 60 ከመቶው ደግሞ የሱኒ ሙስሊሞች ሆኖ ይገኛል ፡፡ ከክርስትያኑ ውስጥ 24 ከመቶው ኦርቶዶክስ ፣ 10
ከመቶ የሮማን ካቶሊክ ፣ 4 ከመቶው ፕሮቴስታንትና ጆባ ሲሆኑ 2 ከመቶው እምነት የለሽ ነው ፡፡ መንግስት ዕውቅና ሰጥቶ የመዘገባቸው
ኦርቶዶክስ ፣ ሉተራን ፣ ሱኒ ሙስሊም እና ሮማ ካቶሊክ ናቸው ፡፡
የኢሳያስ መንግስት ጅራፍ ግን ዕውቅና በሌላቸውም
ሆነ ባላቸው ጀርባ ላይ እያረፈ በመሆኑ 3 ሺህ የሚደርሱ ክርስትያኖች እስር ቤቶችን አጣበዋል ፡፡ ብዙዎች ወደ እስር ቤት የተወረወሩት
ደግሞ በብሄራዊ ውትድርና መሳተፍ ባለመፈለጋቸው ነው ፡፡ በተለይም እምነታቸው ውትድርናን የማይፈቅድላቸው ጆባዎች ዋነኛው የጥቃቱ
ዒላማ ሆነዋል ፡፡
ኢሳያስ በ 1994 ባወጡት አዋጅ ለጆባ እምነት
ተከታዮች የዜግነት ፍቃድ አይሰጥም ፡፡ የመንግስት ሰራተኛ ከሆኑ ከስራ ይባረራሉ፣ የንግድ ፈቃዳቸው ይቀማል ፣ ከመንግስት ቤት
እንዲባረሩ ይደረጋል ፡፡ በርግጥ ሰውየው ጥርሱን የነከሰባቸው ኤርትራን ለማሰገንጠል ድምጸ ውሳኔ ያዘጋጁ ግዜ ነበር ፡፡ ያኔ እነሱ
ከፓለቲካ ተሳትፎ ዉጪ ነን ቢሉም ‹ ማን በሞተለት ሀገር ላይ ማን ገለልተኛ ይሆናል ! › በሚል ስሌት እንዲገረፉ ፣ እንዲገለሉና
እንዲታሰሩ ሀገራዊ አድማ አስደርገውባቸዋል ፡፡
የመንግስትን ጣልቃ ገብነት የኮነኑት ፓትርያክ
አቡነ አንቶኒዮስ ከቦታቸው ተነስተው የመንግስት ሹመኛ ጉብ ብሏል ፡፡ ከ 1700 በላይ የሚሆኑ ካህናት ከቤተክርስትያን አገልግሎት
እንዲገለሉ ተደርገዋል ፡፡ የሃይማኖት እስረኞች ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ ወይም እንዲተው ባዶ እግራቸውን በሹል ድንጋይና በእሾህ
ላይ በቀን ለአንድ ሰዓት እንዲራመዱ ይደረጋል ፡፡
የሰውየው ካምፕ
ሳዋ ሀምሌ 1994 ስራ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ማለትም
ግንቦት ወር ላይ ኢሳያስ የብሄራዊ ውትድርናን ጠቀሜታ አስመልክቶ ሶስት መሰረታዊ ነጥቦችን አስቀመጡ ፡፡
. ሀገሪቱን ከጥቃት ለመከላከልና አንድነት ለመፍጠር
. ወጣቱ ክፍል ለስራ ያለውን አዎንታዊ ስነልቦና
ለማጠናከር
. የሻዕቢያን የ 30 ዓመት ልምድ ፣ ማንነትና
ውርስ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ
በዚሁ መሰረት በአዋጅ ቁጥር 82/1995 አንቀጽ
8 መሰረት ሁሉም ዕድሜው ከ18 – 40 ዓመት የሆነው ዜጋ ብብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት ውስጥ ለ18 ወራት ማገልገል ግድ ይለዋል
፡፡
ኢሳያስ የሀገሪቱ ዜጎች በተለይም ወጣቱ በአመርቂ
ሁኔታ እየተሳተፈ አለመሆኑን በግምግማ ሲያረጋግጡ ‹‹ ብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት ያልገባ ተማሪ የከፍተኛ ትምህርቱን መከታተል
አይችልም ›› የሚል ህግ አወጡ፡፡ በመሆኑም የሁለተኛ ደረጃ የመጨረሻ ትምህርት በሳዋ እንዲሰጥ ተደረገ ፡፡ ተማሪው ለግዜው በዚህ
ዘዴ ተጠፍንጎ ካምፑን ቢያጣብብም በቦታው የነበረው ኢ - ሰብዓዊ አያያዝ ፣ እስራትና ግርፊያ የሰፋ ጥላቻና ስደት እንዲባባስ አድርጓል
፡፡ በተለይም ወጣት ሴቶች በወታደሮች ፣ አሰልጣኞችና አዛዦች መደፈር እጣ ፈንታቸው ሆነ ፡፡ በዚህም የተነሳ ሳዋ ‹‹ የወሲብ
ካምፕ ›› የሚል ስያሜ እስከማግኘት ደረሰ ፡፡
ይህም ሴቶች ከሳዋ ለመዳን ሌሎች ያልተገቡ ዘዴዎችን
እስከመፍጠር አደረሳቸው ፡፡ እነዚህ ህሊናን የሚነኩ ዘዴዎች ሆን ብሎ ማርገዝ ፣ ለምኖም ቢሆን ማግባት እና ትምህርትን ከ 10ኛ
ና 11 ኛ ክፍል ማቋረጥ ናቸው ፡፡ በዚህም ምክንያት በሳዋ የሴቶች ቁጥር ከወንዶች በሶስት እጥፍ እስከማነስ ደርሷል ፡፡
በአጠቃላይ እኔና ሀገሬን በምስራቅ አፍሪካ ግዙፍና
ተጽዕኖ ፈጣሪ ያደርጋል ብለው የገነቡት ሳዋ በሰልጣኙም ሆነ ተራውን በሚጠብቀው ትውልድ አስፈሪ ምስል በመፍጠሩ የታሰበውን ግብ
ሊመታ አልቻለም ፡፡ ባለፉት 13 ዓመታት ከአንድ ሚሊየን ዜጎች በላይ ተሰደዋል ፡፡ ሳዋን የኢሳያስ ከፍተኛ ባለስልጣናትና የፓርቲ
አባላት ከፍተኛ የገቢ ማሰባሰቢያ ምንጭ እያደረጉት ይገኛሉ ፡፡ ከሀገር ውስጥ ወደ ሱዳን ፣ ግብጽና እስራኤል የሚሰደዱ ዜጎችን
ከድንበር ጥበቃዎች ለማሳለፍ በሚል ከ 3 – 20 ሺህ ዶላር ይቀበላሉ ፡፡
የሰውየው መልኮች
የኢትዮጽያ ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ከአልጀዚራ
ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ ‹‹ የኢሳያስ መልካም ፍቃድ ካለ አስመራ ድረስ ሄጄ በሰላም ጉዳይ እደራደራለሁ ›› ብለው ነበር ፡፡
አንዳንዶች ጥያቄው የጠ/ሚኒስትሩን ቀናነት ያሳያል ሲሉ ሌሎች ሀሳቡን ለማቅረብ የመቻኮላቸው ፣ ጥያቄው ከጋዜጠኛው ሳይመጣ ነገር
አስታከው መመለሳቸውን አልወደደውም ነበር ፡፡
ሰውየውም እንዲህ አሉ
‹‹ ኤርትራ ስልጣን ላይ ካሉ ግለሰቦች መቀያየር ጋር የምታያይዘው አንዳችም ነገር አይኖርም … ››
ይህን የመሰለ አስገራሚ ምላሽ እንደሚመጣ በአንዳንዶች
መገመቱ ትክክል ነበር ፡፡ ለምን ከተባለ የኢሳያስን ተቃራኒ መልኮች በልምድ ከማየት ፡፡ ሰውየው ተቃራኒ ጉዳዮችን በማከናወን አቶ
መለስን ጨምሮ አፍሪካ ህብረትን ፣ ተመድንና አሜሪካንን ሲያበሽቁ መኖራቸው ይታወቃል ፡፡ አቶ ሃይለማርያም የኢሳያስ ምለሽ ከተሰማ በኃላ በፓርላማ ሪፖርት
ሲያቀርቡ የሰውየውን አተራማሽነት አስረግጠው ተናግረዋል ፤ አላርፍ ካለ ደግሞ ተመጣጣኝ ቅጣት እንደሚጠብቀው በአጽንኦት አስገንዝበዋል
፡፡ መቼም አቶ ሃይለማርያም ስለ ሰላም በሰበኩ ማግስት ይህን የመሰለ ሃይለ ቃል ለመተንፈስ የተገደዱት ዝም ብሎ አይደለም - ተረኛው
የኢሳያስ በሻቂ በመሆናቸው እንጂ ፡፡
አቶ ኢሳያስ ያልተጠበቁ ወይም የማይገቡ ንግግሮችን
ብቻ ሳይሆን ተግባራትንም በማከናወን ይታወቃሉ ፡፡ እንደሚታወቀው ኢሳያስ በ2008 ከኢራን ጋር ሁነኛ ስምምነት ተፈራርመዋል ፡፡ በስምምነቱ መሰረት ኢራን በአሰብ
ወታደራዊ ተቋም በመገንባት የነዳጅ ማደያውን ስትጠብቅ ኤርትራም ለዚህ ልግስናዋ ገንዘብና ወታደራዊ መሳሪያዎችን ታገኛለች ፡፡ ይችው
ሀገር የኢራንን የኒውክለር ፕሮግራም በመደገፏ ብቻ 35 ሚሊዮን ዶላር ተሸልማለች ፡፡ በሌላ በኩል እስራኤል በዳህላክ ደሴት ፣
በምጽዋና በአምባይሶራ አካባቢ የባህር ኃይል ተቋም ለመገንባት ያቀረበቸውን ጥያቄም ሰውየው በደስታ ተቀብለዋል ፡፡ ኢራንና እስራኤል
የማይታረቅ የነገር ኮሮዋጆችን ለዘመናት የተሸከሙ ባላንጣዎች ናቸው ፡፡ ታዲያ ኢሳያስ ለሁለቱ ተቃራኒ ሀገሮች በአንድ አካባቢ የስራ
ፍቃድ ሰጥተው የኤደን ባህረ ሰላጤ ሌላ የፍጥጫና የግጭት ማዕከል እንዲሆን ለምን ፈለጉ ? የቁርጥ ቀን አጋር ለሆነቸው ኢራን ፍላጎት
ለምን ተገዢ አልሆኑም ? የሚሉ ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀርም ፡፡
የእስራኤል ዓላማ የቀይ ባህር አካባቢንና የኢራንን
እንቅስቃሴ በመሰለል መረጃ ማሰባሰብ ነው ፡፡ የኢሳያስ ግብ ግን ብዙ ነው ፡፡ የእስራኤልን ጓደኛነት በመጠቀም የአሜሪካንን ሆድ
ማባባት ይፈልጋሉ ፡፡ ለእደሳ ፡፡ ብዙ ግዜ ከኢትዮጽያ በሚወሰድባቸው የአየር ኃይል ብልጫ ይንገበገባሉና አየር ኃይላቸውና ዘመናዊና
ብድር መላሽ ማድረጊያው ግዜ አሁን መሆኑን ያልማሉ ፡፡ ኤርትራን ወደ እናት ሀገሯ እንመልሳለን በማለት ፖሊሲ ቀርጸው የሚንቀሳቀሱ
የፖለቲካ ድርጅቶች ከእንግዲህ የሚጋፉት ከእነማን ጋር መሆኑን በእግረ መንገድ እንዲያውቁትም ይፈልጋሉ ፡፡ ኢሳያስ ይህ ዓላማቸው
እንዲሳካላቸው እንጂ የባንጣዎቹ መፋጠጥ አጀንዳቸው አይሆንም ፡፡ ምክንያቱም ነብር መልኩን አይቀይርምና …
የሰውየው መጨረሻ
ከተራራ የሚገዝፉ ሀሳቦችና ውጥኖች ቢኖራቸውም
ቀስፈው የያዟቸው ህመምና ጭንቀት አሜኬላ መሆናቸው አይቀርም ፡፡ አድልዋና መገለል ያብቃ በሚባልበት ዘመን አሸባሪና አተራማሽ ተብለው
በተመድ በተጣለባቸው እገዳ ምክንያት ከዓለማቀፉ ማህበረሰብ ተገለዋል ፡፡ ይህም ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን እየቦረቦረው ይገኛል ፡፡
እገዳው እንዲነሳላቸው ቢጠይቁም ትኩረት የሰጣቸው ወዳጅ አላገኙም ፡፡ 30 ዓመት ደሙን አፍሶ ነጻነት ያስገኘለት ህዝብ የጀግንነት
ውርሱን በ ‹‹ ሳዋ ›› አማካኝነት በጸጋ መቀበል ሲገባው ክህደት መፈጸሙ መጠቃታቸውን ያንረዋል ፡፡ በፕሬስና ነጻነት አፈና ፣
በአምባገነንነት የመጨረሻዋ ሀገር ኤርትራ ነች እያሉ ዓመታዊ ሰንጠረዥ የሚለጥፉ ክፍሎች ተግባር ያንገበግባቸዋል ፡፡
ሰውየው ተወጥረው ተይዘዋል ፡፡
በአንድ በኩል ለስለላ በሌላ በኩል የውጭ ምንዛሪ / Remittance man / በመላክ ተሳትፎ እንዲያበረክቱ አውሮፓና አሜሪካ ከተላኩ ወገኖች ገሚሱ ተልዕኳቸውን
ዘንግተው በየአደባባዩና በየኤምባሲው ‹‹ ኢሳያስ ይውደም ! ›› የሚል መፈክር አሰሚ መሆናቸው ሆድ አስብሷቸዋል ፡፡
ያልታገሉበትን ስልጣን ለመቀራመት በየሀገሩ
‹‹ ተቃዋሚ ›› ብለው ራሳቸውን ያደራጁ ማፈሪያ ዜጎች ተግባር ሳያንስ የሚያምንባቸው ጦር ሰራዊት መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ
ሴራ መጎንጎን ደረጃ መድረሱ ጩህ ጩህ ያሰኛቸዋል ፡፡
የነዚህ ሁሉ ድምር ዉጤት የደም ብዛትን ያፋጥናል
፡፡ ውጥረትን ያንራል ፡፡ የአእምሮ ሽቦዎችን ያላላል ፡፡ ፍርሃትና ጥርጣሬን ያነግሳል ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ሰውየው እንደ
ሀገራችን ድሃ ጎጆ ሺህ ቦታ ላይ ተሰነጣጥቀዋል ፡፡ እናም የቱ ተይዞ የቱ ይለሰናል ? አንዱን ስንጥቅ ሲደፍኑ በመድረቅ ላይ ያለው
ይንጣጣል ፡፡ በመሆኑም ነባሩ ህመም ሊቀለበስ ወደሚችል ጤናማ አካልና አስተሳሰብ የመምጣቱ ዕድል የመነመነ መሆኑን ይጠቁማል ፡፡
ሌላኛው መጨረሻ ‹‹ የተነቃነቀ ጥርስ መውለቁ
አይቀርም ! ›› የሚለውን ነባራዊ እውነት ከማክበር የሚነሳ ነው ፡፡ የጭቆናና የግፍ ጽዋ ሲፈስ ደካሞች ጠንካራ ይሆናሉ ፡፡ እዚህና
እዚያ የወደቀው የደካሞች ድር እያበረ አስቸጋሪውን ተኩላ ለማሰር ይበቃል ፡፡ ሰውየው ምናልባት የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ
ለማቆም የሚችሉት ህዝባዊውንና አዲስ ሀሳቦችን ይዘው ቢያንስ 270 ዲግሪ መዞር ከቻሉ ነው ፡፡ ይህ እውነት ደግሞ ለአምባገነኖች
ሰርቶ እንደማያውቅ ከልምድ እናውቃለን ፡፡ እናስ ? እናማ የሰውየውን አጓጉል መጨረሻ ለመመልከት የግድ ቴሌስኮፕ የማያስፈልግበት
ደረጃ ላይ ተደርሷል ፡፡
ክፍሉ ሁሴን የተባሉ ጸሀፊ ‹‹ በጎ
ምኞት ለወዲ አፈወርቅ ›› በሚል ርዕስ ያቀረቡትን ግጥም
እንደ ማጠቃለያ ሳይሆን እንደ አስደማሚ ምርቃት በመቁጠር ርዕሰ ጉዳዬን
ላጠናቅ
የማይቀረው
የኢሳያስ አፈወርቂ ሞት
በምን
ይሆን በጉበት ወይስ በጥይት
በእናቴ
ወገን የሆኑት
መነኩሴው
አያቴ እንደነገሩኝ ጥንት
ምን
ቢሆን ሃጢያተኛ
እንደ
ዳቢሎስ ከዳተኛ
ይሰረይለታል
አሉ
የሰራው
ግፍ በሙሉ
በሰው
እጅ ከጠፋ ነፍሱ ፡፡
እንዲህ
ከሆነ ነገሩ
በሰማይ
ቤት የቅጣት ድልድሉ
ይንቀልቀል
ዘንድ ዘላለም በእቶን እሳት
ሰበበኛ
በሆነው ጉበቱ ምክንያት ፡፡
ማስታወሻ፡- ይህ ፅሑፍ በቁም ነገር መፅሔት ቅፅ 12 ቁጥር 147 ላይ የወጣ ፅሑፍ ነው፡፡ ፅሑፉን በሌላ ሚዲያ ላይ የምትጠቀሙ ከሆነ ምንጩን እንድትጠቅሱ ትለመናላችሁ፡፡