Tuesday, August 13, 2013

የአቅጣጫ ለውጥ --- በማህበራዊ ሚዲያዎች ?




ታይም መጽሄት ፡፡

የፌስ ቡክ መስራች የሆነውን ማርክ ዙከርበርግን የ2010 የአመቱ ምርጥ ሰው በማለት ሰየመ ፡፡
የመጽሄቱ ውዳሴ ፡፡

ለፌስ ቡክ  --

‹‹ በአሁኑ ወቅት ከምድራችን ሶስተኛው ትልቅ ሀገር ነው ፡፡ በርግጠኝነትም ለዜጎቹ ከሌላው መንግስት በተሻለ መረችን ይሰጣል ››

ለማርክ ዙከርበርግ  --  


‹‹ ከሃርቫርድ ትምህርቱን ያቋረጠው ይህ ወጣት ቲሸርት የሚለብስ የሀገሪቱ ርዕሰ ብሄር ነው ››

››››                               ››››                                    ›››››                                  ››››

አንጋፋውና ታዋቂው መጽሄት ታይም ብዙዎችን ያስደመመውን ፈጠራና ፈጣሪ በዚህ መልኩ ቢያደንቀውም አትዮጽያን ጨምሮ በርካታ ሀገሮች ፌስ ቡክንና ማህበራዊ ሚዲያን የሚመለከቱት በታላቅ ጥርጣሬና ስጋት ነው ፡፡

በርግጥ ስጋቱ ከዘርፈ ብዙ አስተሳሰቦች የሚመነጭ ነው ፡፡ በዋናነት ግን የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ፣ ብሄርና ጎሳ ተኮር ግጭቶች እንዲጫሩ ፣ አክራሪ ሃይማኖታዊ አጀንዳዎች ስር እንዲሰዱ መንገድ ይከፍታል የሚሉት ሊጠቀሱ ይችላሉ ፡፡ ወረድ ሲባልም የግለሰቦች መብት ሊጣስ ፣ የስራ ባህል ሊዳከም ፣ ምርታማነት ሊያሽቆለቁል ይችላል የሚሉ መከራከሪያዎች ይቀርቡበታል ፡፡

በቴክኖሎጂው ዙሪያ የወፈረ ቅሬታ ያላቸው ሀገሮች በአብዛኛው ራሳቸውን ከሂደቱ ውስጥ ለማውጣት ግን የሚደፍሩ አይደሉም ፡፡ አካሄዳቸው አገም ጠቀም አይነት ነው ፡፡ ከቴክኖሎጂው መሸሽ እንደማይቻል ሁሉ ለዓለም ስል ትችትም ራስን አጋልጦ ላለመስጠት ሂደቱን በስሱ ወይም ለራሳቸው በሚመቻቸው መልኩ ያከናውኑታል ፡፡

እገዳ
 
‹‹ Nigeria Good People Great Nation ›› በሚል ርዕስ የሚጽፈው ብሎገር አማኑኤል አጁቡሉ የማህበራዊ ሚዲያ ቀበኛ ሀገሮችን ዘርዝሮ ጽፏል ፡፡ ፌስ ቡክ ፣ ዩቲዩብ ፣ ትዊተር እና ዊኪፒዲያን በመዝጋት ቻይናን የሚያህል የለም ሲል ያደረገቸውን ሚዛናዊነትንም ለመግለጽ በመሞከር ነው ፡፡ ቻይና ሚዲያዎቹን የዘጋችው የምዕራቡን ዓለም ተጽዕኖ ለመቋቋም ሲሆን በተነጻጻሪ የራሷን ሳይበር ኢንዱስትሪ በመፍጠር ተደራሽነቷን አረጋግጣለች ፡፡ ለአብነት ያህል Ozone የተባለው ማህበራዊ ገጽ 600 ሚሊየን አባላት አሉት ፡፡ Weibo የተባለው ሌላኛው ድረ ገጽ የቻይናን መልክ መላበሱ እንጂ ልክ እንደ ትዊተር ነው የሚሰራው ፡፡

እንደ ናይጄሪያዊው አማኑኤል ሁሉ ፍሪደም ሀውስ የተባለው ድርጅት በ 2012 ያጠናው መረጃ ኢትዮጽያን የብሎገር ፎቢያ እንዳለባት ጠቋሚ ነው ፡፡ 65 የዜናና አስተያየት፣ 14 የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ 7 የድምጽና ምስል ዌብሳይቶች፣ 37 ብሎጎችና 37 የፌስ ቡክ ገጾች ተዘግተዋልና ፡፡

ኢትዮጽያና አለምን ሲያጨቃጭቅ የነበረ ሌላ ክስተትም መጨመር ይቻላል ፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት ባጸደቀው አንድ ህግ በሀገሪቱ ውስጥ ስካይፒና ጎግል ቮይስን መጠቀም እስከ 15 ዓመታት እንደሚያሳስር ተገልጾ ነበር ፡፡ በሌላ በኩል መንግስት ስካይፒ መጠቀም ህገወጥ ድርጊት አለመሆኑን ፣ ህገወጥ የሚሆነው ህገወጥ ጥሪዎችን ማከናወን መሆኑን አስተባብሏል ፡፡ በተለይ ከዚህ አጨቃጫቂ ዜና በኃላ ሀገሪቱ ፌስ ቡክ ፣ ትዊተርና የመሳሰሉ ማህበራዊ ገጾችን ልትዘጋ እንደምትችል በስፋት ሲወራ ቆይቷል ፡፡ የኢህአዴግ አባላትም ከስብሰባ በኃላ ፌስ ቡክ ላይ የተጣዱ ሰራተኞችን በመታዘብ ‹‹ ግድየም ለጥቂት ግዜ ተመልከቱ ?! ›› በማለት ጉዳዩ እያበቃለት መሆኑን ያረዱ ነበር ፡፡

ፌስ ቡክ በተለይም ከአቶ መለስ ዜናዊ ሞት በኃላ ብዙ የድርጅቱ ደጋፊዎችን አቁስሏል ፡፡ በአቶ መለስ ሞት ህልፈት ኢትዮጽያዊ ብቻ ሳይሆን ዓለም ማዘን ይገባዋል ብለው ራሳቸውን በማሳመናቸው በሳቸው ላይ ይሰጥ የነበረውን ትችት ባለመቀበል ይህን የአሉባልታ ማናፈሻ ማሽን ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ መከርቸም እንደሚገባ በትንሹም ሆነ በትልቅ ስብሰባ ላይ አጠንክረው አስተያየት ሰጥተዋል ፡፡ በፌስቡክ ላይ የተማረሩ አንዳንድ መ/ቤቶች ሚዲያው እንዲዘጋ ያደረጉ ሲሆን በምሳ ሰዓት ብቻ መጠቀም የሚቻልበትን መንገድ ያመቻቹም ድርጅቶቸች አሉ ፡፡ የወረደ አፈጻጸም አሳይተዋል የተባሉ አንዳንድ ሰራተኞችም    ‹‹ ፌስ ቡክን በማባረር ቢሆን አንደኛ ነህ ! ›› የሚል ግምገማዊ ፌዝ ተቀብለዋል ፡፡ የኢንተርኔት መስመር ለመዘርጋት ያቀዱ አንዳንዶች ደግሞ በፌስ ቡክ ተጠቃሚዎች እንዳንወረር በሚል ስጋት እቅዳቸውን አዘግይተውታል ፡፡ በተለይም እንደ ሀገራችን በምግብ እህል ራሳቸውን ያልቻሉ ታዳጊ ሀገሮች ልማትን እንጂ ፌስ ቡክንና ግብረ አበሮቹን በፍጹም ማስቀደም እንደሌለባቸው  የሚያስረዱ ምሁራዊ ጥናቶችም እዚህና እዚያ ቀርበዋል ፡፡ በዚህና በመሳሰሉ ምክንያቶች መንግስት ፌስ ቡክን ከርችሞ ስሙን ከነፓኪስታን ፣ ኢራን ፣ ሶርያ ፣ ቱርክ ፣ ታይላንድና የመሳሰሉት ተርታ እንደሚያሰልፍ ብዙዎች እየጠበቁ ነበር ፡፡

ያልተጠበቀ ለውጥ
 
ታዲያ ምን ተፈጠረ ?
ታይም መጽሄት በ2010 ያደነቀውን ፌስ ቡክ ዛሬ የኢትዮጽያ መንግስት እንዴትና ለምን ሊቀበለው ቻለ ? ማለት እንዴት ሊሰራበት ፈለገ ?

በቅርቡ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጸ/ቤት በፌደራል ደረጃ ለሚገኙ ኮሙኒኬተሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጥቶ ነበር ፡፡ በስልጠናው በርካታ ጥናታዊ ወረቀቶች የቀረቡ ቢሆንም በውይይት ጎልቶ የወጣው ‹‹ አዲሱና ማህበራዊ ሚዲያ እንደ ተግባቦት ዘዴ ›› የሚለው ምዕራፍ ነበር ፡፡ ይህ ወረቀት በአጭሩና በጥቅሉ ሚዲያው ችግር ቢኖርበትም ጥቅሙን አጠናክሮ ለገጽታ ግንባታ መስራት የማይሸሽና የግዜው አማራጭ መሆኑን አስረድቷል ፡፡ የኮሙኒኬተር ባለሙያዎች የመ/ቤታቸውን ተግባር ብቻ ሳይሆን አጨቃጫቂውን የአባይ ግድብ የተመለከቱ መረጃዎችን ማሰራጨት እንደሚገባቸውም ተመልክቶ ነበር ፡፡
የፌስ ቡክና ማህበራዊ ሚዲያ ጉዳይም ተወካዮች ም/ቤት ደርሶ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ግንዛቤ እንዲያገኙበት ተደርጓል ፡፡ ዲፕሎማትና የአለም አቀፍ ባለሙያ የሆኑት አምባሳደር ቶፊክ አብዱላሂም በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ‹‹ የግብጽ ወጣቶች ፌስ ቡክና ትዊተር በጣም ይጠቀማሉ ፡፡ ኢትዮጽያዊያን ከግብጻዊያን ጋር እነዚህን ሚዲያዎች በመጠቀም በአባይ ወንዝ ፍትሀዊ አጠቃቀም ላይ መወያየት አለብን ፡፡ ወጣቱና የተማረው ትውልድ የግብጽ ህዝብን ለማሳመን መነሳት አለበት ›› በማለት አቅጣጫ ጠቋሚ አስተያየት ሰጥተዋል ፡፡
ግራም ነፈሰ ቀኝ የመንግስት አቋም እየተቀየረ መጥቷል ፡፡ የአቅጣጫውን ለውጥ ያመነጨው አባይ ወይስ ነባራዊው እውነት የሚል መከራከሪያ ማንሳት ግን አሁንም ይፈቀዳል ፡፡ መንግስት ከማህበራዊ ሚዲያዎች ጋር ሙሉ ለሙሉ መጋባት ባይፈልግ እንኳ ከተጨባጩ እውነት ጋ አዛምዶ ፍላጎቱን ለማሳካት እንደ አጋር ሊጠቀምበት ግድ ይለዋል ብሎ ማስቀመጥ ይቻላል ፡፡

የማይሸሸው እውነት
 
በአሁኑ ወቅት ተለምዷዊ በሚባሉት ሚዲያዎች / ጋዜጣ ፣ ሬዲዮ፣ ቴሌቭዥን / ብቻ በመታገዝ ማንነትን ለዓለም ማስተዋወቅ አይቻልም ፡፡ ማህበራዊ ሚዲያን ለመጠቀም የሚያስገድዱ በርካታ እውነቶችን ቴክኖሎጂው እያቀበለን ይገኛል ፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት 751 ሚሊየን ህዝብ ሞባይል ይጠቀማል ፡፡ በ20 ደቂቃዎች አንድ ሚሊየን መረጃዎች ሼር ይደረጋሉ ፡፡ በ20 ደቂቃዎች ሁለት ሚሊየን 176 ሺህ መልዕክት ይላካል ፡፡ በ20 ደቂቃዎች 10 . 2 ሚሊየን እስተያየቶች ይጻፋሉ ፡፡ በ20 ደቂቃዎች አንድ ሚሊየን 484 ሺህ የሁነት ማስታወቂያዎች ይለጠፋሉ ፡፡

ይህን አሐዝ ወደ አህጉራችን ጠጋ አድርገን መመልከትም ይገባል ፡፡ እንደ ‹‹ The internet coaching library ›› መረጃ መሰረት በአፍሪካ ከኢንተርኔት አልፎ የፌስ ቡክ ተጠቃሚው ቁጥር በሚያስገርም ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል ፡፡ በዚህ መሰረት ፣

ግብጽ - 12 ሚሊየን 173 ሺ 540
ናይጄሪያ - 6 ሚሊየን 630 ሺ 200
ደቡብ አፍሪካ - 6 ሚሊየን 269 ሺ 600 ፌስ ቡክ ተጠቃሚዋችን በማስመዝገብ ትልቁን ደረጃ ይዘዋል ፡፡ ሞሮኮ ፣ አልጄሪያና ቱኒዚያ በቀጣዩ ቅደም ተከተል ውስጥ የሚገኙ ሀገሮች ሲሆኑ ኢትዮጽያ በ 10 ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች ፡፡ 902 ሺ 440 በማስመዝገብ ፡፡

በአጠቃላይ ከሁለት መቶ በላይ ድረ ገጾችን ከምታስተናግደው ዓለም ርቆ ፖለቲካንም ሆነ መረጃን በሚፈለገው ልክ ማሰፋት አይሞከርም ፡፡ በተለይም 1 . 11 ቢሊየን ተጠቃሚ ካለው ፌስ ቡክ ፣ 500 ሚሊየን ተመልካች ካለው ትዊተር ፣ 225 ሚሊየን ከሚጎበኘው ሊንክደን ፣ 345 ሚሊየን ተመልካች ካለው ጎግል ፕላስ ቁርኝት አለመፍጠር የነገን መንገድ ካለማወቅ ጋር የሚገናኝ ነው ፡፡ እንግዲህ መንግስት እየቆየም ቢሆን በግድ መቆርጠም እንዳለበት የተረዳው እውነት ይህን ያህል ከድንጋይ የጠጠረ እንደሆነ መረዳት አይከብድም ፡፡

የመንግስት የቤት ስራ
 
‹ ወንድ ወደሽ ጺም ጠልተሸ አይሆንም › እንዲሉ ትግሬዎች ማህበራዊ ሚዲያዎችን ለገጽታ ግንባታ የመጠቀም ፍላጎት ካየለ ግራና ቀኙን ለመቀበል ዝግጁ መሆንን ይጠይቃል ፡፡ ቀኙ ከአዎንታዊ ውጤት ጋር የተያያዘ በመሆኑ የአደናቃፊነት ሚና ላይታይበት ይችላል ፡፡ ምናልባት የኮብል ስቶኑ መንገድ ካልተመቸ አስፋልት የማድረግ ስራ ይጠበቅ ይሆናል ፡፡ በርግጥ ማህበራዊ ሚዲያ ገጽታን ለመገንባት ፣ የገቢ ምንጭ ለማስፋት ፣ የሚዲያዎቻችንን ክፍተት ለመሙላት ፣ የዴሞክራሲና ስርዓቱን ለማጠናከር ፣ የገለሙ አሰራሮችን ለማጋለጥና ለመለወጥ ፣ የጦር ወንጀለኞችን ለማደን / ጆሴፍ ኮኒን ያስታውሷል / ፣ ምርጫን ፍትሃዊ ለማድረግም ሆነ ለማሸነፍ ፣ አምባገነኖችን ለመፈንገልና ለመሳሰሉ ጉዳዮች የላቀ ጥቅም ይሰጣል ፡፡

 ከላይ ለመጠቃቀስ እንደተሞከረው ጥቃቅኑ ችግር ገለል ሲደረግ ከስር አድፍጦ የሚገኘው ትልቁና ፖለቲካዊ ስጋቱ ወይም የግራ / ግራጋቢው / ክፍል ነው ፡፡ ማህበራዊ ሚዲያ በከፍተኛ ደረጃ የትግል መሳሪያ መሆን የጀመረው የ 26 ዓመቱ ቱኒዚያዊው ሞሀመድ ቦዋዚዝ መልካም አስተዳደር ማስፈን ያልቻለውን መንግስት ለመቃወም ራሱን በአደባባይ ካቃጠለ በኃላ ነበር ፡፡ እነዚህ ሚዲያዎች በአረብ አገራት ጭቆናና ኢ-ፍትሃዊ አሰራርን ለመዋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ የፈጠሩ ናቸው ፡፡ በግብጽ፣ ቱኒዝያና የመን በመሳሰሉ ሀገሮች በርካታ የተቃውሞና የአመጽ ጥሪዎች ተቀናብረው የተሰራጩት በፌስ ቡክና ትዊተር ነው ፡፡ አንድ የግብጽ አክቲቪስት ‹‹ ፌስ ቡክን ለተቃውሞ ፣ ትዊተርን ለማስተባበር ዩትዩብን ደግሞ ለዓለም ለመንገርና ለማሳየት እንጠቀምበታለን ›› ማለቱን ማስታወስ ይጠቅማል ፡፡ 

በግብጽ የሚታየውን ተደጋጋሚ ትግል መነሻ በማድረግም ብዙ ዘጋቢዎች ‹‹ የፌስ ቡክ አብዮት ›› እስከማለት ደርሰዋል ፡፡ በማህበራዊ ድረ ገጾች ጥናት ያደረገቸው ማርቲን ማህበራዊ ሚዲያ የትግል መነሳሳቱ እንዲጠናከርና የግዜ ማዕቀፍ እንዲያበጅ እገዛ አድርጓል ባይ ናት ፡፡ ዜጎች የጭካኔ ተግባራት ፣ የፍትህ መጣስና መዛባት፣ የሰቆቃ ህይወት በስፋት መኖሩን እንዲገነዘቡ ብሎም የፍርሃት ስነ ልቦናቸው እንዲወገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ፡፡ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው በርካታ አክቲቪስቶችም ‹‹ እነዚህ መሳሪያዎች ባይኖሩ የሙባረክ መንግስትን የመገልበጡ ሂደት በርካታ አመታቶችን ይፈልግ ነበር ›› ብለዋል ፡፡

ስለሆነም መንግስት በሁለቱ ጥቅሞቹና ጉዳቶቹ መካከል መንገዱን አስተካክሎ መጓዝ ይኖርበታል ፡፡ ችግሩን ተቀብሎ ሊያስተካክል ፣ ብርታቱን ሊመረኮዝበት እንደሆነ ሊያጤን ግድ ይለዋል ፡፡ ‹ ወንድ ወደሽ ጺም ጠልተሸ አይሆንም › የሚባለው ተረትም ቅርጹና መልዕክቱ ይኀው ነው ፡፡

››››                               ››››                                    ›››››                                  ››››

አዲስ ራዕይ መጽሄት ፡፡

የፌስ ቡክ ተጠቃሚ የሆነውን ከተማ ቀመስ ህዝብ የ 2006 ምርጤና  ነውጤ በማለት ስያሜ ይሰጣል ፡፡ ምርጦቹ  ‹ ልማታዊ ተጠቃሚዎች › የሚል የክብር ማዕረግ የሚያገኙ ሲሆን ነውጤዎቹ  ‹ ጥገኛ ተጠቃሚዎች › የሚል  ባርኖስ ይከናነባሉ ፡፡

የመጽሄቱ ውዳሴ ፡፡

ልማታዊ ተጠቃሚዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚወጡ ጸረ ልማት ዜናዎችን ፣  ዘገባዎችን ፣ ፎቶዎችንና ፊልሞችን ከፍተኛ ትዕግስት በመጠቀም አይቶ እንዳላየ በመዝጋት … እነዚህን ተውሳክና ተዛማች ሀሳቦች ባሉበት ቀጭጨው እንዲቀሩ LIKE እና  SHARE ባለማድረግ እንዲሁም COMMENT ባለመስጠት ሀገራዊ ግዴታቸውን ተወጥተዋል ፡፡

ዘላለማዊ ክብር ለመስመርተኞች !!




No comments:

Post a Comment