Tuesday, August 28, 2012

ሞትና ንግድ





ታዋቂ ሰዋች ሲሞቱ የብዙዋች ትኩረት ወደ ሟቾቹ ይሳባል  ፤ ይህ የሚሆነው ደግሞ በብዙ ምክንያቶች ነው ፡፡ ሰዋቹ በሰሯቸው ታላላቅ ስራዋች ክብርና ሞገስ ስለሚያገኙ እንዲሁም ከብዙዋቹ ታላላቅ ሰዋች ጀርባ አከራካሪና አወዛጋቢ ጉዳዮች በመኖራቸው  ብሎ መጥቅለል ይቻላል ፡፡

አንዳንድ ሰዋች ታዋቂዋቹ በህይወት እያሉ ግልብ በሆነ አድናቆትና ፍቅር ውስጥ ነው የሚያስቧቸው ፡፡ ለአድናቆታቸውና ለፍቅራቸው መሰረት የጣለላቸውን አብይ ጉዳይ ካወቁ በቂ ነው ፡፡ ታዋቂዋቹ በሞት ሲለዩ ግን ከመደናገጥና ከመሸበር ባሻገር የመጸጸትና የጥፋተኝነት ስሜት ያበቅላሉ ፡፡ ስለ ሰውዬው ማንነት የሚገልጹ ስራዋችን ከዛሬ ነገ አያለሁ፣ አነባለሁ፣ ለማወቅ ጥረት አደርጋለሁ እያሉ የቆዩበትን መንገድ ይተቻሉ ፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የታዋቂ ሰዋች ህይወት ባለ ሁለት መስተዋት መሆኑ ይታወቃል ፡፡ ህዝቡም ሆነ አድናቂው የሚያውቀው የፊት ለፊት ገጽታቸውን ነው ፡፡ የጀርባ ህይወታቸው ከባህል፣ ፓለቲካ፣ ስነ ልቦናና ማህበራዊ ህይወት አንጻር ያፈነገጠና በግጭቶች ውጤት ያበጠ በመሆኑ በብዙ መልኩ ደብቀውት ይጓዛሉ ፡፡ ስለዚህ ህብረተሰቡ አንድም ይህን የተደበቀ ማንነታቸውን በሌላ በኩልም አጉድሎ ያቆየውን ፕሮፋይል ለማወቅ በብርቱ ይፈልጋል ፡፡ ከሞቱ በኃላ የሚያገኛቸው ልዩ ልዩ መረጃዋች ስሎ የቆያቸውን ጀግኖች ይበልጥ ለማክበርና ለመዘከር ይረዳዋል ፡፡ ተቃራኒ በሆነው ስብዕናቸውም ለመደመም፣ ሚዛናዊ ምስክርነቱን ለመስጠት ብቻ ሳይሆን እይታውን በማስፋት ትምህርትና ልምድ ለመውሰድ ይጠቀምበታል ፡፡

ይህ የሰው ልጆች የጋለ ባህሪ ነው ፡፡ እንግዲህ ይህን  ተዝቆ የማያልቅ ፍላጎት በማንበብ ነው ‹ አቅርቦት › ፈጣሪዋች ምናባቸውን የሚያሰሩት ፡፡ ለምሳሌ ያህል የማይክል ጃክሰን ልጆች ምግብ ማዘጋጃ ክፍል ውስጥ ባለ ጥቁር ሰሌዳ ላይ ‹ I Love Daddy › ብለው የጻፉት የተለመደ ስሜትን መግለጫ ሃሳብ  ከሞተ በኃላ በ 5 ሺህ ዶላር ተሸጧል ፡፡ አርቲስቱ ጠዋትና ማታ ፊቱን የሚያይበት የቁም ሳጥን ደግሞ 25 ሺህ 750 ዶላር አውጥቷል ፡፡ የሙዚቃ ስራው  ተለቆ 170 ሚሊዮን ዶላር አስገኝቷል ፡፡ 

ስፔናዊውን ስመ ጥር ሰዓሊ ፓብሎ ፒካሶን ብዙዋች ያውቁታል ፡፡ ግንቦት 2010  Nude, Greeen Leaves and Bust የተሰኘው ስራው ለጨረታ ቀርቦ በ105 ሚሊዮን ዶላር ተሸጧል ፡፡ ይህ ስራ በ1951 የተሸጠው በ19 ሺህ 800 ዶላር ብቻ ነበር ፡፡ የዊትኒ ሀውስተን ቀሚስ 20ሺህ 480 ዶላር፣ የኤልቪስ ፕርስሊ የሞተር ሳይክል ጃኬት 41 ሺህ 600 ዶላር አውጥቷል ፡፡ በወቅቱ ብዙም ልብ ያልተባሉ ንግግሮች፣ መሸጥ ያቆሙ ካሴቶች ወይም የፎቶ አልበሞች ተጠርዘው ለህትመት ሲበቁ ሚሊዮኖች ያለ ጥያቄ ይገዟቸዋል ፡፡ አንድም ድሮ የዘለልኩትን መረጃ አገኛለሁ በሚል አንድም ለማፍቀርና ለመዘከር ፡፡

የአገራችን የሙዚቃ ንጉስ ጥላሁን ገሰሰ ሲሞት ያልደነገጠና ያላዘነ ሰው አልነበረም ፡፡ ጥላሁን እጅግ የሚከበር የመሆኑን ያህል አነጋጋሪ ማንነቶች እየተከተሉት የቆየ አርቲስት ነበር ፡፡ በተለይም በራሱ አንደበት የተገለጸው ‹‹ የሆድ ይፍጀው ! ››ን እውነተኛ ታሪክ ብዙዋች ማወቅ ይፈልጉ ነበር ፡፡ ከደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሄር፣ ማሞ ውድነህና አፈወርቅ ተክሌ በበለጠ መልኩ በጥላሁን ላይ የንግድ ስራዋች በስፋት ተከናውነዋል ማለት ይቻላል ፡፡ ልዩ ልዩ ፎቶዋቹ  ‹የዝነኛው…የአንደኛው …የንጉሱ .. › በሚል ማስታወቂያ ታጅበው እንደ ጉድ ተሽጠዋል ፡፡ ፎቶውን የያዙ የቁልፍ መያዣዋች፣ የማይጠገቡ ድምጾቹን ያቀፉ ዘፈኖች ፣ ማንነቱን የሚተርኩ የህትመት ውጤቶች ገበያ ላይ ውለው ብዙ አልቆዩም ፡፡ የስብሃት ገ/ እግዚአብሄር የተወሰኑ መጻህፍት ጀትን መወዳደር በቻለ ፍጥነት ታትመው አንባቢው ያለበትን ክፍተት ብቻ ሳይሆን የነጋዴዋችንም ኪስ መሙላት ችለዋል ፡፡

በቅርቡ አቡነ ጻውሎስና ጠ/ሚ/ር መለስ በሞት ተለይተዋል ፡፡ የአቶ መለስ እልፈት አቡኑን በመሸፈኑ ማየት የሚገባንን ንግዳዊ ትርዒት ገድቦብናል የሚል እምነት አለኝ ፡፡ የአቶ መለስን ሞት ተከትሎ እየታየ ያለው ንግዳዊ ስርዓት ግን የሚገርም ሆኗል ፡፡ በከተማችን በሁሉም ማዕዘን ሌላ ነገር ሲሰሩ የነበሩ ወይም ስራ ያልነበራቸው ወጣቶች የመለስን ፎቶ በተለያዩ መጠን በማሳተም ከሁለት እሰከ አስር ብር ይሸጣሉ ፡፡ በተለይም የቀብር ስነ ስርዓቱ እንደ ሀገራችን ፍርድ ቤቶች ረጅም ቀጠሮ የተያዘለት መሆኑን መሰረት በማድረግ አቀራረባቸውን አሳድገዋል ፡፡ የመጀመሪያዋቹ ቀናት ሲሸጡ የነበሩ ፎቶዋች ልሙጦች ነበሩ ፡፡ በሂደት ግን ፎቶዋቹ ላይ ሳቢ ጥቅሶች እንዲጨመሩበት አድርገዋል ፡፡ በአንድ ወረቀት ላይ ሁለትና ሶስት ፎቶዋችን በማካተትም የገዢውን ትኩረት ለመሳብ ጥረዋል ፤ አነጋገራቸውስ ብትሉ !! በፊት ‹ የጀግናው መሪ ማስታወሻ አያምልጣቸሁ ! › የሚል ነበር ፡፡ አሁን ደግሞ ‹ ሞቶም ስራ የፈጠረውን መለስ ዜናዊን በእጅዋ ያስገቡ ! › ወደሚለው ማዕረግ ተሸጋግሯል  ፡፡

እንደ ፎቶው አይብዙ እንጂ ሰው የበዛበት ቦታ ላይ ጥቅስ እያነበቡ በመሸጥ የሚተዳደሩ ሰዋች እንዳሉ ይታወቃል ፡፡ የነዚህ ሰዋች ስነ ልቦና የማንበብ ትጋት በጣም የሚያስገርም ነው  ፡፡ ድሃ የበዛበት አካባቢ

‹‹ ድሃና አክተር ይንገላታል እንጂ አይሞትም ! ››

‹‹ ምንም ድሃ ቢሆን ባይኖረው ሀብት
ከደጃፍ ሲቀመጥ ደስ ይላል አባት ›› የሚሉ ዓይነት ጥቅሶችን ለገበያ ያቀርባሉ ፡፡ መርካቶ መንገድ ላይ የሚነግዱ እናቶች ጋ ጠጋ ብለው ደግሞ     

‹‹ እናት ለምን ትሙት ትሂድ አጎንብሳ
   ቅማል ታገኛለች በጨለማ ዳብሳ ›› ካሉ መሃረብና መቀነቶች የግድ መላላታቸው አይቀርም ፡፡
ቤተክርስትያን አካባቢ ‹ እግዚአብሄርን ፈልጉት ትጸናላችሁም !! › የሚል ዓይነት ጥቅሶችን ከነመገኛ ቁጥራቸው ሲያንበለብሉ መልስና ብርታት የሚሹ ልቦች በፈገግታ ይቀበሏቸዋል ፡፡  ዐስርቱ ትዕዛዛትን ከሚያምር ስዕል ጋር አስደግፈው ያቀርባሉ ፡፡ በሰሙነ ህመማት ግዜ ከሰኞ እስከ እሁድ ያሉ ቀናቶች ያላቸውን ሚና በመጻፍ ጮክ ብለው ያስተዋውቃሉ ፡፡ ታዲያ ለዚህ መሰሉ አስታዋሽ ጥቅስን መግዛት አይደለም ‹ ይባርክህ ! › የተሰኘውን ብሩክ ምርቃት መጨመርስ ምን ይጎዳል ? ምንም ነው መልሱ ፤ ሰዋቹ ድንገት እንኳን አፈንግጠው

‹‹ በማያልቀው እቃ እየተነገደ
  ሴቱ በማርቼዲስ ወንዱ በእግሩ ሄደ ››  ቢሉ አንዴ በበጎ ያወጡትን ‹ ይባርክህ - ይድፋህ ! › በሚለው ለመለወጥ አቅም አይኖሮትም ፣ ባይሆን በስሱ ፈገግ ይላሉ እንጂ ፡፡ የነሱም ዓላማ ሳቅና ትኩረትን በጅምላ ማጋባት ነው - ቻይናዋች ፈገግ የማይል ሱቅ አይክፈት እንደሚሉት ፡፡ ጥቅሰኞቹ በትዕዛዝም ሊሰሩ ይችላሉ ፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው ሃይገር ባስ ላይ ያየነው ‹‹ ጎበዝ የአባይ ቃል ስላለብን ጠጋ ጠጋ በሉ ! ›› የሚለው ልመናዊ ትዕዛዝ ነው ፡፡ የሰሞኑ ወቅታዊ ጥቅሳቸው ደግሞ መልኩ ተቀይሮ

‹‹ አባይ ይገደባል ፤ መለስ ይታወሳል ! ››
‹‹ የሞተው ታጋይ እንጂ ትግል አይደለም ! ››
‹‹ ቆራጡ መሪ እናከብርሃለን ! ›› የሚሉና የመሳሰሉ ሆነዋል ፡፡ ጥቅሱ ብቻ ሳይሆን አነባበባቸው ረጋ ያለና ሀዘንን አቀጣጣይ በመሆኑ ደንበኞች አላጡም ፡፡

የጠ/ሚ/ር መለስን ሞት ምክንያት በማድረግ የልብስ ነጋዴዋችም የአቅጣጫና የቀለም ለውጥ ያደረጉ ይመስላሉ ፡፡ ጥቁር ልብስ ለክፉ ቀን እንደሚፈለግ ቢታወቅም  ጥቁር መዘዝን ሊጠራ ይችላል በሚል ልማዳዊ መመሪያ ድንበር ከልለው እንደሁኔታው ብቻ የሚወዳጁት ጥቂቶች አይደሉም ፡፡ ዛሬ ግን ገለልተኛ ፖሊሲያቸው እንደተጠበቀ መሆኑን በማሳየት የአሰቸኳይ ግዜ አዋጁን ዕውን ለማድረግ ተነስተዋል ፡፡ ጥቁር ሻሽ፣ ቢትልስ፣ ነጠላ፣ ሸሚዝ፣ ኮፍያ፣ ቀሚስ፣ ሱሪ ወዘተ ተፈላጊነታቸው በመጨመሩ ደፋ ቀናውን በእጥፍ አሳድገዋል  ፡፡ ፎቶ ቤቶች ቢታዘዙም ባይታዘዙም በትልቁ አጥበው መስቀል ከያዙ ቀናት አስቆጥረዋል ፡፡ በአነስተኛና ጥቃቅን በህትመት ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶች ቲሸርት ፣ ኮፍያ፣ የደረት ባጅ ፣ ፓስተር ወዘተ በብዛት እያመረቱ ይገኛሉ ፡፡

በየግዜው ዋጋ በመጨመር የሚታወቁት ስጋቤቶች ራሳቸውን ከወቅታዊው ሁኔታ ጋር ለማዛመድ እያሶመሰሙ ይመስላል ፡፡ የት አካባቢ እንደሆነ ባይታወቅም አንድ ስጋ ቤት መጠሪያውን ‹‹ ጀግናው አይሞትም ስጋ ቤት ›› ብሎታል ፡፡ ከስያሜው አጠገብም        ‹‹ ለሀዘን የሚሆን ጥሬና ጥብስ አለ ›› በማለት ያስረዳል ፡፡  ነገና ከነገወዲያም የኢህአዴግን ስትራቴጂዋችንና የትኩረት አቅጣጫዋች እየመዘዙ ለንግድ ስራቸው ስያሜ የሚሰጡ ሰዋች እንደሚኖሩ መገመት ትክክል ነው ፡፡ ጥያቄው ግን ስያሜዋቹ የሚያስተላልፉት መልዕክት ምን ያህል በአግባቡ ተቀናጅቷል የሚለው ነው ፡፡

አንድ ለአምስት የተባለውን አደረጃጀት አንስቶ ‹‹ አንድ ለአምስት ዳቦ ቤት ›› ብሎ መጥራት አሻሚነትን በአዋጅ እንደማስነገር ይቆጠራል ፡፡ የኔ አንድ ዳቦ የአምስት ሰዋችን ጉሮሮ ያረካል ለማለት ከሆነ ጠዋት ጠዋት ከውሃ ጋር የምንውጠውን ኪኒን ዳቦ እያስታወስን በአላጋጭ ፈገግታ ልንደምቅ ነው ፡፡ በርግጥ በተቃራኒው ማሰብ የሚቻል ከሆነ አምስቱ ዳቦ ለአንድ ሰው ረሃቡን ተንፈስ ሊያደርግለት ይችላል ፡፡ በየቀኑ ይህን እንዳናደርግ ግን የተቀደደው ኪሳችን እስካሁን አልተሰፋልንም ፡፡

አንድ ሌላ ነጋዴ ንግድ ቤቴ ጨዋታ በጣም የሚዳመቅበት ስለሆነ ከዛሬ ጀምሮ ‹‹ ሂስና ግለሂስ ጠጅ ቤት ›› ብየዋለሁ ሊል ይችላል ፡፡ አንባቢው ሲተረጉመው ደግሞ ‹ ይህ ሂስና ግለሂስ በጠጅ የደነበዡ ሰዋች የሚንጫጩበት መድረክ ነው ለካ ? › በማለት ቢያፍታታው ትርጉሙ አውዱን ስቷል ብሎ ለመከራከር አያስችልም ፡፡ እንዲህና እንዲህ የመሳሰሉ ነገሮች ተጠባቂ ይመስላሉ ፡፡ ነጋዴዋች በሃሳብ    ‹ በቅርብ ቀን  › የሚል ማስታወቂያ እያዘጋጁ ይመስለኛል ፡፡ ምን ሊሉ  ? ከተባለ

‹ ውሃ ማቆር ግሮሰሪ ›
‹ ድሃ ተኮር ጋዜጣ ›
‹ ቢፒአር ሁለገብ መናፈሻ ›
‹ ትራንስፎርሜሽን ጫማ ቤት › የመሳሰሉትን ፡፡

ጋዜጦችና መጽሄቶች መረጃ ከማድረስ አንጻር ወቅታዊ ሁኔታን መዘገብ ኃላፊነትና ግዴታቸው መሆኑ ይታወቃል ፡፡ ሆኖም የፓለቲካውና የሃይማኖቱ  መሪዋች ማለፍ አቅጣጫዋችንና ገቢያቸውን አለወጠውም  ብሎ መናገር ያስቸግራል ፡፡ አዳዲስ ጉዳዮችን ለመጠቆም የሚጥረውን መረጃ ከላይ በመግቢያዬ እንደገለጽኩት ህብረተሰቡ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ይፈልገዋል ፡፡ ይህም የህትመቶቹ ኮፒ እንዲያድግ አይነተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ፡፡ በሌላ በኩል ድርጅቶችና ግለሰቦች ከወትሮው በተለየ ምልከታ የሀዘን መግለጫቸው ጋዜጣ ላይ እንዲወጣ ይፈልጋሉ ፡፡ ይህም ለጋዜጦች ያልታሰበ በረከት ነው ፡፡ እነሆ በግማሽ ዓመት ስራቸውን ሲገመግሙ ‹‹ ከዕቅድ በላይ አትርፈናል ! ›› የሚል የደስ ደስ ያለው ንግግር ይጠቀማሉ ፡፡

የባንዲራ፣ የአበባ፣ የጧፍና ሻማ ገበያም በቀላሉ የሚታይ አይደለም ፡፡ ወቅታዊውን ሞት አዘል ንግድ መዘርዘር ስለሰለቸኝ ወደፊት የሚጠበቁትን አንዳንድ ሁኔታዋች ላመላክት ፡፡ ድርጅቶች ለአዲሱ ዓመት አጀንዳ፣ ፓስት ካርድ፣ የቀን መቁጠሪያ ወዘተ ያሳትማሉ ፡፡ መረጃውን አስቀድመው ወደ ማተሚያ ቤት የላኩ ካሉ መከለሳቸው አይቀሬ ነው ፡፡ መንገድ ላይ ያሉት የፈጀው ግዜ ፈጀቶም ቢሆን ስለ መሪዋቹ ብዙ እንደሚዘክሩ ይጠበቃል ፡፡ ደብተር አሳትመው የሚያከፋፍሉ ድርጅቶች ከከባድ ይቅርታ ጋር በእቅድ የያዟቸውን ታዋቂ ስፖርተኞችና ምርጥ እጆች የተጨነቁባቸውን ስዕሎች ላልተወሰኑ ግዜ ያስተላልፋሉ ፡፡ እነሆ በግማሽ ዓመት ስራቸውን ሲገመግሙ ‹‹ ማቀድ ብቻ ሳይሆን ደራሽ ስራዋችም ያበለጽጋሉ ! ›› የሚል አባባል ያንጸባርቃሉ ፡፡

 ፊልም፣ ቲያትር፣ የቴሌቪዥን ድራማ፣ ሙዚቃ፣ የሙዚቃ ኮንሰርት መነሻውና መድረሻው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የጠ/ሚ/ር መለስ ተጽዕኖ እንደሚያርፍበት ይገመታል ፡፡ በእንቁጣጣሽ ክብረ በዓል ስፖርተኛ፣ አክተርና መላዕክትን ማዕከል አድርገው ሲጓዙ የቆዩ ወጣቶች በአቡነ ጻውሎስና በአቶ መለስ ህይወት ዙሪያ ያነጣጠሩ ስዕሎች ላይ ቢያተኩሩ ምንም አይገርምም ፡፡

እንደሚታወቀው ሙዚቃ ቤቶች ከበሮው ወፈር ያለ ሙዚቃ ማሰማት አቁመዋል ፡፡ በምትኩ በድምጽ መሳሪያ ብቻ የተቀነባበሩ ሙዚቃዋች እየተሰሙ ናቸው ፡፡ ለዚህ የጥበብ ስራ በርካታ ሰዋች ያን ያህል በቂ ትኩረት ይሰጣሉ ማለት ያስቸግራል ፡፡ እኔ ሳነብም ሆነ ስጽፍ በአብዛኛው የምጠቀመው በክላሲካል በመሆኑ ሊሆን ይችላል  ይህ የጥበብ ስራ ሳይታሰብ በከተማው ገኖ መውጣቱ አስደስቶኛል ፡፡ ይህ ስልት ለዘመናት አላፈናፍን ያሉትን የነሮክ፣ ሬጌ፣ ራፕ፣ ጃዝ ወዘተ የጭቆና ቀንበር የሰበረ ሁሉ መስሎኛል ፡፡ ድሮንስ አንድ ዓይነት ነገር ሲበዛ ይጎመዝዝ የለ ! ጥበቡ ልክ እንደ ቋንቋ በራሱ ሙሉ በኩልሄ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለጥሞና ፣ ለፍቅርና ራስን ለመመርመር ምን ያህል ፍቱን መድሃኒት መሆኑን እያሳየ ነው ፡፡

 ክላሲካል ህይወት ከጫጫታና ግርግር ወጪ ያላትን የማይፋጅና የማይበርድ ገጽታን በሚያስደምም መልኩ የሚያንጸባርቅ ጥበብ ነው ፡፡ የሙዚቃ የዓለም ቋንቋነት ይበልጥ ደምቆ የሚታየው በክላሲካል ነው ማለት ይቻላል ፡፡ እስኪ ለአብነት የቻይና፣ የጃፓን ፣ የሱዳንና የግብጽን ክላሲካሎች ያዳምጡ ፡፡ የሰሟቸውን ሀገሮች ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅን ረቂቅ ማንነት እንደ ቴሌቪዥን ይመለከታሉ፣ እንደ ሬዲዮ ያዳምጣሉ፣ እንደ መጸሀፍ ያነቡታል ፡፡ ፓለቲከኞች ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ መምህራን የሚሰብኳቸውንና የሚመኟቸውን ሰላም፣ ፍቅር፣ መተሳሰብና አንድነት በረቂቅ ድምጾቹ ውስጥ ገዝፈው ያገኟቸዋል ፡፡

ነፍስ ይማር !!

No comments:

Post a Comment