Saturday, March 23, 2013

የድሃው ፕሬዝዳንት ሀብታም አእምሮ





‹‹ ጫማ የለኝም ብለህ አትዘን
እግር የሌለው ሰው አለና ! ››

ይህች መሳጭ አባባል ከቆራጥ ድሃዋች አእምሮ በኑሮ ፍትጊያና ውጣ ውረድ ምክንያት የተፈነጠቀች ትመስላለች ፡፡ አንድ ሰው ግን ይህን አባባል የድህነት አባል ነው ብሎ ለመከራከር የሚያስችል መሰረት የለም በማለት ሞግቶኛል ፡፡

እንዴት ? - እኔ ፡፡

‹‹ ተረቱ የሚያገለግለው ለሌላ ተምሳሌት እንደ መወጣጫ እንጂ በራሱ ምሉዕ ሆኖ ለመቆም አይደለም ››

አልገባኝም ! - እኔ ፡፡

በምሳሌ ባስረዳህ ይሻላል ያለኝ ወዳጄ ትንሽ አሰብ በማድረግ የሚከተለውን ተመሳሳይ ነገር ግን የወገቡ ቁጥር ሰፊ የሆነ ጥቅስ ወረወረልኝ

‹‹ G + 1 የለኝም ብለህ አትዘን
ወያኔ ዲኤክስ የሌለው አለና ! ››

ፈገግ አልኩ ፡፡ የሞተሯ ድምጽ እየቆየ ከፍ እያለ እንደሚሄድ ቮልስዋገን ሳቄ መቦተራረፍ አበዛ - የእኔ ፡፡ ባለጸጋዎችም ሲገናኙ ከ ‹ ተመስገን › ይልቅ ብዙ አላገኘሁም ፣ ብዙ አላደግኩም የሚል ምሬትና ቅናት አቀፍ መዝሙር እንደሚያስቀድሙ ይታወቃል ፡፡ ይህ ተፈጥሯዊ ስለሆነ ክፋት የለውም ብሎ ማለፍም ይቻላል ፡፡ ሆኖም የድሃዎችን መሳጭና ስሜት አንኳኪ ጥቅስ ሰርቀው ለማይገባ ጥቅም ያውሉታል ብሎ መጠበቅ ከባድ ነው ፡፡

እንዴት ? - አንተ / አንባቢው /

የላይኛው ጥቅስ ጓደኛዬ እንደሚለው የህይወትን ከፍታ የሚያሳየው በጥቂት የደረጃዎች ልዩነቶች ከፋፍሎ አይደለም ፡፡ ምቾት ሳይሆን እሾህ ፣ ቆንጥር ፣ ድንጋይና ውርጭን ለመከላከል የጠየቀ እግር ነው ማጽናኛ ተብሎ እግር የሌለው ሰው የተጠቀሰለት ፡፡ ይህም የኑሮን ገደልንም ሆነ ግሽበት አድምቆ ያሳያል ፡፡ ምነው ትንታኔው ከአጽናኝነት ይልቅ አደንዛዥነቱ ላቀ ብትል ሃሳብህ አልተጋነነ ይሆናል ፡፡ ግን ለግዜውም ቢሆን ከደረጃ በታችና ከጤና ጎዳና የወደቀን ህይወት አንድ ሀሙስ ለማስቀጠል ማደንዘዣ መጠቀም ሳይንሳዊ ድጋፍ ሳይኖረው እንደማይቀርም መገመት ሊኖርብህ ነው ፡፡

ጫማ የሌለው ድሃ እግር በሌለው ሰው ከተጽናና አነሰም አደገ ሀብት ያለው ባለጸጋ ለምን የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 25 ቁጥር 29 ጥቅስ እንደማያጽናናው ግልጽ አይደለም ፡፡

ምን ይላል ? - አንተ / አንባቢው /

‹‹ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና ይበዛለትማል
ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል ››

ስለዚህ በማለት የመግቢያ ዲስኩራችንን እንደሚከተለው ብታጠቃልለው ስለ ቀጣዩ ርዕሰ ጉዳይ ምን ያህል እንደተቀራረብን ሊያሳብቅህ ይችላል ፡፡ < ስለዚህ  የለኝም  ብሎ አላግባብ ከማንቋረር የያዘው እንዲበዛለት ስም ያለው ተግባር ማከናወን ህሊናዊም መንፈሳዊውም ርካታ ያጎናጽፈዋል >

     +++++                                              +++++++                                               ++++++++

እንደሚታወቀው የዓለማችን ባለጸጋዎች በሁለት ዋና ዋና ምድብ ውስጥ ነው ተሰልፈው የሚገኙት ፡፡ በንግድና አስተዳዳሪነት ፡፡ በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት እነ ቢል ጌትስ ፣ ዋረን ቡፌት ፣ የኢንቴል ተባባሪ መስራች ጎርደን ሙርና ሌሎችም የማቲዎስን ጥቅስ በልካቸው አሰፍተው የለበሱ ይመስላል ፡፡ ሃብታቸው በቦሌም መጣ በባሌ በቢሊየን የሚቆጠረውን ገንዘባቸውን ‹‹ ጫማና እግር ›› ሌላቸው ቡድኖች እየሰጡ በተቃራኒው የሰጡትን ያህል ያገኛሉ ፡፡

አስተዳዳሪዎቹ ልዩ መጠሪያቸው ‹‹ ፕሬዝዳንት ›› ወይም ‹‹ ጠ/ሚ/ር ›› ይባል እንጂ የሀገር ሀብትንም ጭምር ነው ወደ ግል ካዝናቸው በአግባቡ መግባቱን ነው የሚያስተዳድሩት ፡፡ በርግጥ ይህ አባባል ሁሉንም መሪ አይወክልም በማለት ማሰተካከያ እንዲገባ አስበህ ይሆናል - በውስጥህ ፡፡ እኔም በመርህ ደረጃ ትክክል ነው እንዳልኩህ ገብቶሃል ብዬ ሃሳቤን ልቀጥል ፡፡ ብዙ መሪዎች ከሚያገኙት የሚታይና የማይታይ ጥቅማጥቅም በተጨማሪ ዓመታዊ ደመወዛቸው እንደ ተራራ የተቆለለ መሆኑ ይታወቃል ፡፡ ምናልባትም ተራራ ተንዶ ይግደልህ ወይስ የተቆለለ የመሪ ገንዘብ የሚል አጣብቂኝ ምርጫ ውስጥ ብትገባ  መልስህ ‹ እሳት ካየው ምን ለየው › ቢሆን ይመረጣል ፡፡ ካላመንክ ጥቂት የምሳሌ ብቻ ሳይሆን የተራራ ዘሮችን ልበትንልህ ፡፡ ሙአመር ጋዳፊ 200 ቢሊየን ፣ ሆስኒ ሙባረክ 70 ቢሊየን ፣ ቭላድሚር ፑቲን 70 ቢሊየን ፣ ስባስቲያን ፒኒራ /ቺሊ/ 2.4 ቢሊየን ፣ አሲፍ አሊ ዛርዳሪ/ፓኪስታን/ 1.8 ቢሊየን ዶላር ያገኛሉ ፡፡ ጥቂት ባለ ሚሊኒየኖርችንም እንቀላቅል ፡፡ ፊደል ካስትሮ 900 ሚሊየን ፣ ፓወል ቢያ 200 ሚሊየን ፣ ሊሙንግ ባክ/ ደ.ኮሪያ/ 23.6 ሚሊየን ፣ ማንዴላ 15 ሚሊየን ፣ አንጄላ መርክል 11.5 ሚሊየን ፣ ሮበርቱ ሙጋቤ 10 ሚሊየን ፣ መህመድ አህመዲንጃድ 5 ሚሊየን ዶላር ያገኛሉ ፡፡ ባለሺዎቹ ለምን ይቀርባቸዋል ከተባለ የባራክ ኦባማና የ ሁ ጂንታኦ /ቻይና/ 4 መቶ ሺህ ዶላርን ዋቢ ማድረግ ይቻላል ፡፡

ዞሮ ዞሮ ብዙዎቹ የስልጣን መሰረቱ የሚመነጨው ክብር ፣ ሃይልና ሀብትን ማግኘቱ ላይ በመሆኑ እንደ አንዳንድ ነጋዴዎች ‹‹ ለጋስነት የልቦና ጉዳይ ›› መሆኑን አይቀበሉም ፡፡ እምነትና ፍልስፍናቸው ‹ ጭብጦህን በአግባቡ ሰብስብ ፤ ይህም ሃብት እንዳይነጠቅ አምርረህ ጠብቅ ! › የሚል ነው ፡፡

መሪዎቹ ከላይ የጠቀስናቸው ሁለት መሰረታዊ ጥቅሶች ማለትም የድሃዎችን ‹‹ ጫማ የለኝም ብለህ አትዘን ›› እና የሀብታሞቹን ‹‹ ላለው ይጨመራል ›› በቀና ልቦና መመርመር ምን ያህል ጠቃሚ መሆኑን አልተረዱም ፡፡ ከቢሊየንና ሚሊየን ሰፊ እርሻ ወስጥ ለዘር የሚያገለግሉ ጥቂት ‹‹ ሺዎችን ›› መበተን ምን ያህል ይከብዳል ?

‹‹ አይከብድም ! ›› - ይላሉ
‹‹ ማን ? ›› - እኔና አንተ
‹‹ የኡራጋይ ፕሬዝዳንት ጆሴ ሙጂካ / jose mujica / ?/ ››
‹‹ እንዴት ? ›› - እኔና አንተ

እኚህ ፕሬዝዳንት የዓለማችን ድሃው ፕሬዝዳንት ቢሆኑም በማይታመን ልግስና ‹‹ ጫማ ከሌላቸው ›› ጎን በመሰለፋቸው ታላቅነትን ተጎናጽፈዋል ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እንደ ሌሎቹ ‹‹ አስተዳዳሪዋች ›› ዓመታዊ ደመወዛቸውን ቢሊየንና ሚሊየን ለማድረስ አልፈለጉም ፡ ሺህ ድሃ መሃል የአንድ ሃብታም መገኘት በስነልቦና ድሃ ከመሆን ወጪ ትርፍ የለውም በማለት ይሆን ? ወርሃዊ ደመወዛቸው 7985 ፓውንድ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 7 ሺ 500 ፓውንዱን ወዲያው የሚሰጡት ድሃዎችን ለመርዳት ለተቋቋሙ ፕሮጄክቶች ነው ፡፡  ይህ ልግስና የደመወዛቸውን 90 ከመቶ ድርሻ  እንደሚሸፍን ልብ በል ፡፡ እኛ በየወሩ 2 እና 3 ከመቶ ለጤና ፣ ለልማት ፣ ለግድብ ወዘተ እየተባለ ሲቆረጥብን እንዴት ነው የምንሆነው ?
‹ እኛ የምንፈራው መቆረጡን ሳይሆን የሚቆረጥብን የት እንደሚገባ አለማወቃችን ነው › - ነው ያልከው ፡፡ በርግጥ ተገቢ ስጋት ነው ፡፡ በዚህ መንገድ ስንት ሰብዓዊነት የሌለውን ጅብ ስንቀልብ ነው የኖርነው ፡፡

ግን ጎበዝ ያለውን በሙሉ ሳይሳሳ የሚሰጥ ፈጣሪ ብቻ አልነበር እንዴ ? እንዲህ የሚያደርግ የሀገር መሪ አይደለም ጫካ የገባ መናኝ በቀላሉ ይገኛል እንዴ ? ሰምታችሁስ ታውቁ ይሁን ? ለመተዳደሪያ ይበቃኛል ብለው የሚያስቀሩት 485 ፓውንድ ወይም አስር ከመቶውን ብቻ ነው ፡፡

 ‹‹ በርግጥ መሪዎች ለህዝብ ፍቅር አንዲህ የቀረቡ ናቸው ? ››
‹‹ ራሳቸውንስ ይህን ያህል ይጎዳሉ ? ››
 ‹‹ ለመሆኑ እኚህ ሰው ማናቸው ? ››

አእምሮህ በተደራራቢ ጥያቄ ተጨናነቀ አይደል ?!  ለማንኛውም  ሰውየውን ለማጥናት እንሞክር ፡፡

ጆሲ ሙጂካ የተወለዱት ግንቦት 20 ቀን 1935 ነበር ፡፡ አባታቸው ስፔናዊ ሲሆኑ እናታቸው የጣሊያን ዝርያ አላቸው ፡፡ ቤተሰባቸው በስትሪላ አምስት ሄክታር መሬት ገዝተው በወይን እርሻ ይተዳደሩ ነበር ፡፡  ሙጂካ አምስት ዓመት ሲሞላቸው ማለትም በ1940 አባታቸውን በሞቱ ተነጠቁ ፡፡  ሙጂካ ወጣት በነበሩበት ግዜ ሁለት ጉዳዮች ትኩረታቸውን ስቦት ነበር ፡፡ አንደኛው ፓለቲካ ሲሆን በብሄራዊ ፓርቲ የወጣቶች ሊግ ውስጥ ንቁ ተሳተፎ አደርገዋል ፡፡ ሁለተኛው ስፖርት ሲሆን ለተለያዩ ክለቦች በተለያዩ ካታጎሪዎች የብስክሌት ውድድር ሲያደርጉ ቆይተዋል ፡፡

በ1960ዎቹ ፋኖ ተሰማራ … የሚለው የኩባ አብዮት በሀገራቸውም ተጸዕኖ በመፍጠሩ ለመጀመሪያ ግዜ ከተደራጀውና ከታጠቀው የቱፓማሮ እንቅስቃሴ ውስጥ  ተቀላቀሉ ፡፡ በ1969 አካባቢ ፓንዶን ለመያዝ በተደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ትልቅ ተሳተፎ የነበራቸው ሙጂካ አራት ግዜ ያህል በመንግስት ወታደሮች እጅ ወድቀዋል ፡፡ ስድስት ግዜ ያህል በፖሊስ ጥይት ተመተዋል ፡፡ በ1971 ፑንታ ካሬታስ ከተባለ እስር ቤት ያመለጡ ሲሆን ከእንደገና በ1972 ተይዘዋል ፡፡ በ1973 ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ሲካሄድ ለ 14 ዓመታት ወደታሰሩበት ወታደራዊ እስር ቤት እንዲዘዋወሩ ተደርጓል፡፡ በእስር ቤት ቆይታቸው ከቱፓማሮ ፓርቲ በርካታ መሪዎች ጋር ትውውቅ ያደረጉበት ነበር ፡፡

በ1985 በሀገሪቱ ህገ መንግሰታዊ ዴሞክራሲ ሲመሰረት ከ 1962 ጀምሮ በፖለቲካና እና ወታደራዊ ወንጀሎች የታሰሩ ሰዎች ምህረት ሲደረግላቸው  እሳቸውም የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ሆኑ ፡፡ ራሳቸውን ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ሰፊ ህብረት እንደሚያስፈልግ የተገነዘቡት ሙጂካና ጓደኞቻቸው ከግራ ክንፈኛ ድርጅቶች ጋር በመተባበር Movement of Popular Participation የተባለ ድርጅት መሰረቱ ፡፡ በ1994 በተደረገው አጠቃላይ ምርጫ ምክትል ሆነው የተመረጡ ሲሆን በ1999 ደግሞ ሴናተር መሆን ችለዋል ፡፡ ከ 2005 እስከ 2008 ድረስም የወቅቱ ፕሬዝዳንት ታባሬ የሙጂካን የኃላ ታሪክ በማጥናት የሀገሪቱ የእንስሳት እርሻና አሳ ሚንስትር አድርገው ሾመዋቸዋል ፡፡ በ2009 በተደረገ ሀገራዊ ምርጫ ፓርቲያቸው ለፕሬዝዳንትነት ዕጩ አድርጎ አቅርቧቸው ማሸነፍ ችለዋል ፡፡ የመጀመሪያ ቀን ንግግራቸውም በአስገራሚነቱ ተመዝግቧል

‹‹ ምን አሉ ? ›› አልክ

 ‹‹ በውድድሩ ያሸነፈም ሆነ የተሸነፈ ስለሌለ በአንድነት እንነሳ ፡፡ ስልጣን ከሰማይ ይመጣል የሚባለው አስተሳሰብ የተሳሳተ ነው ፤ ስልጣን የሚመጣው ከብዙሃኑ ልብ መካከል ነው ››

ሙጂካ በስልጣን ቆይታቸው ከፈጸሙት አስገራሚ ተግባር አንዱ ማሪዋና የተባለውን አደገኛ ዕጽ በህጋዊ መንገድ እንዲሸጥ ማድረጋቸው ነው ፡፡ እጹ በህጋዊ መንገድ እንዲያልፍ መደረጉ ሀገሪቱ ከፍተኛ ገቢ እንድታገኝ ብሎም የወንጀልና የጤና እንከኖች እንዲቀንሱ አድርጓል ፡፡ የተመሳሳይ ጾታን ጋብቻን ህጋዊ ምላሽ እንዲያገኝ ያደረጉ ሲሆን ተከልክሎ የቆየውን እስከ 12 ሳምንት ዕድሜ ያለውን ጽንስ የማስወጣት ህግም ፍቃድ ሰጥተዋል ፡፡ አንድ ፕሬዝዳንት ከአንድ ግዜ በላይ መመረጥ የለበትም የሚል የጸና አቋም በማራመድ ይታወቃሉ ፡፡

የ 77 ዓመቱ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዛሬ ሞንቲቮዶ በተባለ የከተማ ዳርቻ የፓርላማ ተመራጭ ከነበሩት ሚስታቸው ሉሲያ ቶፓላንኪና ከባለሶስቱ እግር ውሻቸው ማንዌላ ጋር ህይወታቸውን ይመራሉ ፡፡ የህይወታቸው መሰረት ልክ እንዳባታቸው ግብርና ሲሆን መኖሪያ ቤታቸውን የተመለከቱ ጋዜጠኞች ለአንድ ፕሬዛዳንት የማይገባና ፍጹም በመፈራረስ ላይ የሚገኝ በማለት ገልጸውታል ፡፡ መንግስት ያቀረበላቸውን ከቤተመንግስት የሚተካከል ህንጻ ብቻ ሳይሆን የከተማውን ህይወት ንቀው ነው አፈር ገፊነትን የመረጡት ፡፡

እኚህ ሰው የዚያ ሀገር ፕሬዝዳንት ነበሩ ለማለት የሚያስችሉ ሀብትም ሆነ ድባብ በቤታቸው ዙሪያ የለም ፡፡ ምናልባት ደህንነታቸውን የሚጠብቁ ሁለት ፖሊሶች መገኘታቸው ካልሆነ በስተቀር ፡፡ የዕለት ስራቸውን የሚያከናውኑት በአንድ ትራክተር ሲሆን አልፎ አልፎ ወደ ከተማ የሚሄዱባት ድክም ያለች የ1987 ሞዴል ቮልስዋገን አላቸው ፡፡ ትልቁ ሀብታቸውም እነዚህ ናቸው ፡፡ አንድ በህዝቡ ሲወደድ የነበረ መሪ ለምን እንዲህ በማይጠበቅና ዝቅ ባለ የህይወት ቦይ ውስጥ ማለፍ ፈለገ ? የሚል ጥያቄ መፍለቁ ግድ ነው ፡፡መልሱ የሰውየው ሰብዓዊነትና ሩህሩህነት የላቀ ደረጃ ላይ መድረሱ እንዲሁም ለሌሎች ጥቅምና ዕድገት መኖር ራስንም አሳልፎ መስጠት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ሳያንገራግሩ በመቀበላቸው ነው ፡፡

ይህን ከባድ ውሳኔ ለማሳለፍ በርካታ ጥቅማጥቅሞችን በመርዘም ሆነ በንቀት ማውደም ያስፈልጋል ፡፡ ስንት ነገር ያሳለፉት ፕሬዝዳንት ለእርሻቸው ውሃ የሚቀዱት ረጅም ጉድጓዶችን ቆፍረው ነው ፡፡ በቀን ለብዙ ግዜ ይቀያየሩ የነበሩትን ልብሶች ዛሬ ላውንደሪ ለማስገባት እንኳ ባለመቻል በእጃቸው ነው የሚያጥቡት ፡፡ በቤተመንግስታቸው ይቀርብላቸው የነበረው ምግብና መጠጥ ፣ ክብርና መሽቆጥቆጥ ፣ ውዳሴና የታላቅነት ስሜት ፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ዛሬ የሉም ፡፡ ቢያማቸውም ሆነ ጫና ሲበዛባቸው ለእረፍት ሀገር አቋርጠው የሚሄዱበት አግባብ አሁን ዝግ ነው ፡፡ ገንዘቡስ የታለና ፡፡ ባለፈው ዓመት ያላቸው አጠቃላይ ሀብት ሲሰላ 135ሺህ ፓውንድ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡ ይህ ገንዘብ በሀብታሞቹ መሪዎቹ አይን ከታዩ የአንድ ቀን ራት ቢጋብዝ ነው ፡፡ ገንዘብ ደስታን አይገዛም የሚሉት ሙጂካ የባንክ አካውንት የሌላቸው መሆኑም ሌላ አስገራሚ ጉዳይ ነው ፡፡
በወር የገቢን 90 ከመቶ ለችግረኞች አሳልፎ መስጠት ይከብዳል ፡፡ ግን ለምን ? ተብለው በጋዜጠኞች ሲጠየቁ ‹‹ ይህን ያህል መርዳት አለብኝ ፡፡ ምክንያቱም በጣም አነስተኛ በሆነ ገቢ የሚተዳደሩ በርካታ ኡራጋዊያን አሉና ›› በማለት መልሰዋል ፡፡ ምናለ ይቺን አባባል በየደረጃው ለሚገኘው የኛ ሀገር ትንሽና ትልቅ ስግብግብ አመራር ግልባጭ አድርገው ቢልኳት ? ለማንኛውም እነዚህን አማላይ ፈታኝ ምዕራፎች ለመዝጋት መቻል ምን ያህል ጀግና መሆንን ያሳብቃል ፡፡

ሙጂካ ለቢቢሲ ‹‹ የቁሳቁስ ሃብት ደስታን መግዛት አይችልም ፡፡ ብዙዎች ድሃው ፕሬዝዳንት እያሉ ይጠሩኛል ፤ እኔ ግን ድህነት አይሰማኝም ፡፡ ድሃ ሰዎች ህይወታቸውን በውድ የአኗኗር ዘይቤ ውስጥ የሚያሳልፉና ዘወትር ብዙና ብዙ ለማግኘት ብቻ የሚሰሩት ናቸው ›› በማለት ገልጸዋል ፡፡

እንደ መግቢያችን ሁሉ ለመዝጊያችንም መቀርቀሪያ እንፈልግለት፡፡

ለጋስ መሪዎች መስዋትነት የሚከፍሉት ምክንያቱ ላይ ነው ፡፡ ድሃ ህዝቤን እንዴት ከችግር ላውጣው እንጂ እኔ እንዴት ልበልጽግ የሚል ሀሳብ አያስቀድሙም ፡፡ እንዴት የዴሞክራሲ ፣ ፍትህና ነጻነት ጥያቄውን ሙሉ ላድርግለት እንጂ ምን ዓይነት የፍርሃት ቆብና ቱታ ላልብሰው በማለት አይጨነቁም ፡፡ ለጋስ መሪዎች ለተቋማትም ሆነ ለሀገር እንደ ቃል አቀባይ ስለሚቆጠሩ የህዝቡን የመረዳት፣ የመቀበልና የመተግበር ስሜት መማረክ ይችላሉ ፡፡ ለጋስ መሪዎች ልዩ ክህሎትና ጥበብ ያላቸውን ሰራተኞች ልብና አእምሮ መቆጣጠር አያስቸግራቸውም  ፡፡ እናም ብዙዎች ከሚጠበቀው በላይ በራሳቸው ተነሳሽነት ለመስራት አያቅማሙም ፡፡ ለአንድ መሪ ትልቁ ፈተና ህዝባዊ ፍቅር የማግኘቱ ጉዳይ በመሆኑ ብዙ ሊሰራበት የተሰጠውን አእምሮ ሳይበርዝ እንደ ማዕድን መቆፈር አለበት ፡፡

‹‹ ምን ሊያገኝ  ? ›› አልክ

እንደ አልማዝ ውድና አጓጊ የሆነውን - ቅንነት
እንደ ወርቅ ልብ የሚያሞቀውን - ሩህሩህነት
እንደ ብረት የጠነከረን - ህዝባዊነት ፡፡


No comments:

Post a Comment