Sunday, March 24, 2013

‎ከሜዳ አህዮቹ የምንማረው . . .‎





ዋሊያዋቹ የቦትስዋናዎቹን ‹ የሜዳ አህያ › በአጣብቂኝ ሰዓትም ቢሆን አሸንፈው መውጣታቸው ያስደስታል ፡፡ ለእነሱም ሆነ ለደጋፊው ፌሽታ መፍጠር ትልቅ ጉዳይ ነውና ‹ የደስታ ስካር አይለያችሁ › ብሎ መመረቅ ይገባል ፡፡

እቺ ተሸናፊዋ ሀገር ቦትስዋና በኳስ ያላት ደረጃ ዝቅተኛ ቢሆንም የብዙ የላቁ ጉዳዮች ባለቤት በመሆኗ በእጅጉ ማክበር ያስፈልጋል ፡፡ ምክንያቱም ትልቁና ቋሚው ፌሽታ እነሱ ዘንድ አለና ፡፡

‹ የሜዳ አህያ › በነገራችን ላይ የቡድኑ መጠሪያ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱ ብሄራዊ ምልክትም ጭምር ነው ፡፡ ከጨዋታው በፊት ቀድሞ የተዘመረላቸው ብሄራዊ መዝሙርን ደግሞ ‹‹ የእኛ ምድር / ሀገር ›› ይሉታል ፡፡

እንዳልኩት የቦትስዋና ፌሽታዎች ብዙ ናቸው ፡፡ ከሚከተሉት ረጅም ኳስ አንጻር ከዋሊያዎቹ ኳስን ይዞ ውብና ማራኪ ጨዋታ እንዴት መምራት እንደሚቻል ሳይማሩ አይቀርም ፡፡ እኛ ከእነሱ ልንማራቸው የሚገቡ መሰረታዊ ጉዳዮች ግን ይልቃሉ ፡፡ አንዳንዶቹን እናንሳ ፡፡

. ቦትስዋና ከአፍሪካ ከ 1965 ጀምሮ ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ከመጡ ሀገሮች የመጀመሪያዋ ናት ፡፡ 9 ከመቶ የሚደርሰው አማካይ እድገቷ እንደ እኛ ሀገር ዝናብ መጣሁ - ቀረሁ እያለ የሚያስፈራራ አይደለም ፡፡ ቀጣይነቱ የተረጋገጠ እንጂ ፡፡

. የአፍሪካ አስከፊ ሙስና ሲነሳ ይቺ ሀገር በተቃራኒው ትዘከራለች ፡፡ በትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት መሰረት የለም ከማለት የዘለለ ጥቂት የሙስና እንቅስቃሴ የሚታይባት የጨዋዎች ሀገር ናት ፡፡ እንዴት ቢያሳድጓት ነው ? ያስብላል ፡፡

. በሰበብ አስባቡ የፖለቲካ ፓርቲዎቿን ተሳትፎ የምትጎነትል ሳይሆን የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን ለረጅም ግዜ ሳታቋርጥ የተገበረች አፍሪካዊ ኩራት ናት ፡፡

. የዓለማችን ውድ ማዕድን አልማዝን በገፍ ለአለም ገበያ ታቀርባለች ፡፡ የሚያስገርመው የማዕድንና ነዳጅ ሀብት አናውዟቸውም ሆነ በዚሁ ኢ - ፍትሃዊ ክፍፍል ተማረው ወደማያባራው ጦርነት እንደገቡ በርካታ የአፍሪካ ሀገሮች ሳትሆን በፍጹም ሰላማዊና የተረጋጋ ጎዳና እየጋለበች መገኘቷ ነው ፡፡

. እቺ ሀገር ስትነሳ ፍጹም ከአእምሮዬ የማይጠፉት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ፌስተስ ሞይ ናቸው ፡፡ በአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ወቅት ጋዜጠኞች በተናጥል ቃለመጠይቅ ካደረግናቸው መሪዎች አንደኛው ነበሩ ፡፡ ትህትናቸው ፣ አካብዴ አለመሆናቸው ፣ ነጻ ሆነው በሚሰጡት ቀልዶች ተገርመን ነበር ፡፡ ለካ የእኚህ ሰው ባህሪ ልዩ የሆነው ወቅታዊውን ስብሰባ ብቻ መሰረት አደርጎ ሳይሆን ለዴሞክራሲ የተፈጠሩ በመሆናቸው ነው ፡፡ ይህንን የተረዳሁት ግን በጣም ዘግይቼ ነው ፡፡ ሀገራቸውን ለሁለት ግዜ ካስተዳደሩ በኃላ ስልጣን በቃኝ ብለው ወንበሩን ለሌላ ተመራጭ አስረከቡ ፡፡ በአፍሪካዊ ትህትናና እግዚዮታ ቢለመኑ ቢለመኑ ውስጣቸውን እንጂ ማንንም ማዳመጥ አልፈለጉም ፡፡ እሳቸው ስለ አፍሪካ የዴሞክራሲ ጥማት በጣም ይጨነቁ ኖሯል ፡፡ ይህ ለአፍሪካ ፍጹም የማይታመንና ብርቅ ሆነ ፡፡ ለካስ እንደኛ የገረማቸው ሁለት ሰዎች ነበሩ ፡፡ አንደኛው የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኒኮላ ሳርኮዚ ሲሆኑ ሁለተኛው ሱዳናዊ ቱጃር ኢብራሂም ናቸው ፡፡ ሳርኮዚ የዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ምሳሌ በማለት የሀገራቸውን ትልቅ ሽልማት ሸለሟቸው ፡፡ የአፍሪካን መሪዎች ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማበረታታት ተቋም የመሰረቱት ሞ ኢብራሂም ደግሞ በ 2008 የአፍሪካ ምርጥ ዴሞክራት መሪ በማለት 5 ሚሊዮን ዶላር አበረከቱላቸው ፡፡

ከኚህ መሪ በኃላ ቦትስዋና እንዴት ሆነች ? ካላችሁ መልሱ ዴሞክራሲ የበለጸገባት የሚል ይሆናል ፡፡ ምክንያቱም የማይናወጠውን መሰረት ሞይ ጥለውታልና ፡፡ የ 2011 የሞ ኢብራሂም ተቋም መረጃ እንደሚጠቁመውም የወቅቱ ፕሬዝዳንት ጀርሲ ጃን ካማ 75.2 ከመቶ በማግኘት ‹‹ ኤ ›› ካገኙ አራት መሪዎች አንደኛው ሆነዋል ፡፡ ለማስታወስ ብቻ የኛ ነጥብ ተጠጋግቶ 33 ነበር ፡፡

የሀገራችን ቴሌቪዥን የኳሱን ቁጥራዊ መረጃ እንደውጪዎቹ ተንትኖ አላሳየንም እንጂ በሌላ ሌላ ያጣነውን በኳሱ ሳናካክሰው የቀረን አይመስለኝም ፡፡ እንግዲህ ኳስ ወንድማማችነት መፍጠሪያ መድረክ ብቻ ሳይሆን መማማሪያም በመሆኑ ከሜዳ አህዮቹ የምንወስዳቸው ስልጠናዎች አሉ ፡፡ ስልጠናው የማያስፈልገን ቢሆን እንኳን የሜዳ አህዮቹን በያዙት የተቀደሰ መንገድ ልናከብራቸው ግድ ይለናል ፡፡

‹‹ ኖር ብለናል ባለ ዴሞክራሲያዎቹ / ዴሞክራቶቹ / !! ››

No comments:

Post a Comment