Sunday, June 10, 2012

‎የአከራካሪው አባት ‹ ፕሮፋይል ›‎




‹‹ ሐውልት እንደቆመላቸው አያውቁም ነበር፡፡ ሐውልቱን ለመመረቅ ሲመጡ እንኳን ሌላ ዝግጅት እንዳለ ተደርጎ ነበር የተነገራቸው፡፡ ሪቫኑን በመቀስ ቆርጠው የተሸፈነውን ሲከፍቱት በጣም ደነገጡ፡፡ ››
ከቆይታ ቅጭምታ በኃላ የሚከተለውን በሀዘን የተዋጠ ንግግር አደረጉ
‹‹ ይህ ነገር ለእኔ አይገባኝም፡፡ ምን ስላደረግኩ ?  ማን ነኝና ? ››
ትህትናው ደስ ይላል ፡፡ የዚህ ንግግር ባለቤት ገ/መድህን ገ/ዮሐንስ ናቸው፡፡ ይህ ስም ግር ካላችሁ ብጽአ ወቅዱስ አቡነ ጻውሎስ በሚል ማስተካከል ትችላላችሁ፡፡

አከራካሪ ሀሳብ፣ አከራካሪ መጽሀፍ፣ አከራካሪ ፓለቲከኛ እንዳለ ሁሉ አከራካሪ የሃይማኖት አባትም አለ፡፡ አቡነ ጻውሎስ ምናልባትም ጥሩ ምሳሌ እንደሚሆኑ ይገመታል፡፡ በህይወታቸውና በስራቸው ዙሪያ ሰሜንና ደቡብ ጫፍ የሚረግጡ ሀሳቦች በየሰፈሩ፣ በሚዲያ ፣ በየገዳሙ፣ በአምልኮ ስፍራዋች ሁሉ ተነግረዋል፡፡ ዛሬም እየተነገሩ ናቸው ፡፡

ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ ግን በዓለማቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዝናና አክብሮት ያላቸውን አቡነ ጻውሎስ ሀገሬው ሊያከብራቸው ወይም ሊረዳቸው አልቻለም ባይ ናቸው፡፡ የዛሬውን አያድርገውና ወ/ሮ እጅጋየሁ የታዋቂው አቀንቃኝ መሀሙድ አህመድ ባለቤት ነበሩ፡፡ እናም እሳቸው ራሳቸው በአንድ ወቅት ብዙ ያነጋገሩ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ እጅጋየሁ ይህን ጠንካራ መግለጫ ያስተላለፉት በመገናኛ ብዙሃን አይደለም - በመድብል እንጂ፡፡ ጥር 2004 ያሳተሙት መጽሀፍ  ‹‹ በሃይማኖት ሽፋን እስከ መቼ ? ›› የሚል ርዕስ አንግቧል፡፡ ጸሀፊዋ ለአቡነ ጻውሎስ በቆመው ሀውልት ዙሪያ የሚሰጠው የተሳሳተ አስተያየት እንዳስቆጫቸውና የእውነታውን ምስል የማሳየት ተልዕኮ በማንገብ ይመስላል ብዕራቸውን ያጠበቁት ፡፡

ይህን ለማስረዳት ደግሞ የትንሹን ገ/መድህን ታታሪነት፣ ሰው ወዳድነትና ጉብዝና ሳይቀር ያሳዩናል፡፡ ገ/መድህን በአካልም ሆነ በመንፈስ እየጠነከረ ሲመጣ ያተረፈውን ዝና፣ የትምህርትና የቋንቋ ችሎታ በቀጣዩ ደረጃ እንመለከታለን፡፡ ይህ ደረጃ ስፋት አለው፡፡ ዞሮ ዞሮ ወደ መጨረሻው እየተጠቀለለ ሲመጣ አቡነ ጻውሎስ ለራሳቸውም ሆነ ለሌላ አካል ጥቅም ያልቆሙ፣ ይልቁንም እንደ አቡነ ሺኖዳ የአርአያ አባት ሊባሉ እንደሚገባቸው ይሞግታሉ ፡፡

በመጽሀፉ አቡነ ጻውሎስ ከፓትርያርክነትም በኃላም ሆነ በፊት ታላቅ ስራ መስራታቸውን እናነባለን፡፡ በስደት ወቅት በተለይም በአሜሪካ ከሰባት በላይ የሚሆኑ ቤተክርስትያናትን መስርተው በዚያ ለሚገኙ ኢትዮጽያዊያንና የውጭ ዜጎች ለ10 ዓመታት መንፈሳዊ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡

በፓትሪያርክነት ዘመናቸው የወንጌል አገልግሎት እንዲስፋፋ በርካታ ጻጻሳትን ሾመዋል፡፡ የሀገረ ስብከቶች ቁጥር እንዲጨምር፣ተወርሶ የነበረው የቅድስት ስላሴ ኮሌጅ እንዲመለስ አድርገዋል፡፡ የአብነት ት/ቤቶችና የካህናት ማሰልጠኛ እንዲጠናከሩ ሰርተዋል፡፡ ከእሁድ ት/ቤት ኃላፊነት ጀምሮ የልማት ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር ሆነው የሰሩት አቡነ ጻውሎስ 3 የሀገር ውስጥና 6 የውጭ ሀገር ቋንቋዋችን አቀላጥፈው የሚናገሩ ናቸው፡፡ መረጃው የጋዜጦች፣ የመጽሄቶችና የሬዲዮ መምርያ የበላይ ሆነው እንደሰሩም ያስረዳል፡፡ በዚህ ወቅት የነበራቸውን አመራርና ሙያዊ ብስለት ማወቅ ቢቻል ሌላውንም ስብዕናቸውን ለመገመት ያስችል ነበር፡፡ ምክንያቱም ይህ ቦታ ፈታኝ በመሆኑ ውስጣዊ ማንነትና ብቃት እንደ ድርቆሽ አደባባይ ላይ እንዲሰጣ ያደርጋልና፡፡

አቡነ ጻውሎስ ባከናወኑት ተግባር ከሀገር ወስጥና ከውጭ የተለያዩ ኒሻንና ሜዳሊያዋችን ተሸልመዋል፡፡ ከአሜሪካ ኤምባሲ የተሰጣቸው ላንድ ክሩዘር፣ ከስፔን ኤምባሲ ያገኙት ሊሞዚን፣ ለ18ኛው በዓለ ሲመት ከህዝብ የተበረከተላቸውን መኪና በቤተክርስትያን ስም እንዲዛወር አድርገዋል፡፡ እስካሁንም እንዲህ ያደረገ ፓትርያርክ የለም ነው የሚሉት  - ወ/ሮ እጅጋየሁ ፡፡
በርግጥ ወ/ሮ እጅጋየሁ ይህን መጽሀፍ የጻፉት እንደ ጋዜጠኛ ወይም ዳኛ መሃል ላይ ቆመው ሳይሆን አንደኛው ጫፍ ላይ ሆነው ነው፡፡ ዓላማቸው የአቡነ ጻውሎስን በእጅ ስራ የተሰራ መልክ ማሳየት በመሆኑ ጥሩ የህዝብ ግንኙነት ስራ አከናውነዋል፡፡ ዋናው ጥያቄ ግን በመጽሀፉ የቀረቡት አንዳንድ መረጃዋች በሌላኛው ጫፍ ለሚገኙት ምን ያህል አሳማኝ ናቸው ? የሚለው ነው፡፡ አሁንም በጥልቀት እንየው ካልን መረጃዋቹ በርግጥ የታሹና ናቸው ? ለሚለው ጥያቄ በቂ ምላሽ መስጠት ግድ ይላል፡፡

ለአብነት ያህል ሁለት ሜትር ርዝመት ያለው ባለ ነሀስ ሐውልት ሲሰራላቸው እንደማያውቁ ተገልጾል፣ የሄዱትም ሌላ ዝግጅት እንዳለ ተደርጎ ስለተነገራቸው ነው ተብሏል፡፡  የሃገራችን የሃላፊ አማካሪዋች በርግጥ መረጃን ደብቀው ወይም አሳስተው ለመንገር ብቃት አላቸው ከተባለ በራሱ ጥሩ ወደሆነ ደረጃ ደርሰናል የሚያስብል ነው፡፡ በወቅቱ በህዝቡም ሆነ በሚዲያ የተገለጸው ሀውልቱ የተሰራው የ18ኛ ዓመት ሲመት በዓላቸውን ምክንያት በማድረግ ነው፡፡ ወ/ሮ እጅጋየሁ ይችን ጥያቄ አንስተው መተንተን ወይም ባለጉዳዩ የእምነት - ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ማድረግ ነበረባቸው፡፡ በርግጥ የመጀመሪያው ፓትርያርክ ብጽዐ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስም በህይወት እያሉ ራሳቸው ያሰሩት ሀውልት በደብረ ጽጌ ማርያም ቤ/ክ ቅድስት ውስጥ መቆሙን ማጣቀሻ በማቅረብ እስካሁን እሳቸው ላይ ጥያቄ ለምን አልተነሳም ? በማለት ይሞግታሉ፡፡ ለአቡነ ሺኖዳም 3 ሐውልቶች መቆሙን በመጥቀስ ፣ ቢሰራም አሳማኝ እንጂ አሳፋሪ አለመሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ይህ ሀሳብ በራሱ መጥፎ ባይሆንም መሰረታዊው ውል እንዲተበተብ ግን ያደርጋል፡፡

ሌላኛው መሰረታዊ ነጥብ ሹመቱን የሚመለከተው ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ አምስት ሊቃነጻጻሳትን ለፓትርያርክ ምርጫነት አወዳድሮ እሳቸው ማለፋቸውን እናነባለን፡፡ ይሁን እንጂ ቀድመው ስለነበሩት አቡነ መርቆርዮስና ሌሎች ጻጻሳት የስደት ሁኔታ መረጃ አልተሰጠንም፡፡  የዚህ መረጃ ተጠናክሮ አለመቅረብ አቡነ መርቆርዮስን በማባረር ጻውሎስን የሾመው ኢህአዴግ ነው የሚለውን ሰፊ አስተያየት እንዳይተባበል አድርጓል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ምዕመናን ሀሳብ ውስጥ ያለውን ‹ ህጋዊው ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ ናቸው ወይስ አቡነ ጻውሎስ ? › የሚለውን ብዥታ ለማጥራት ይረዳ ነበር፡፡ ይህ ጉዳይ አሁንም አከራካሪ ሆኖ እንዲቀጥል ይለፍ የተሰጠው ይመስላል፡፡

 
አቡነ ጻውሎስ የቤተክርስትያን ገንዘብ ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው ጥቅም እንደሚያውሉም ይነገራል፡፡ ጸሀፊዋ ከዚህ መነሻ ተነስተው ባይመስልም ጥሩ ማስተባበያ ሰጥተዋል፡፡ በስማቸው የመጡትን በርካታ ሽልማቶች በቤተክርስትያን  ስም እንዲዛወር አድርገዋልና፡፡ የራስ ንብረት የራስ ነው ከሚለው አሰራር በወውጣት ይህን ማድረግ በርግጥም ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
ጸሀፊዋ  የአቡነ ጻውሎስን ታላቅነትና ንጽህና ለማስረገጥ ነው አልመው የተነሱት፡፡ ለዚህም እገዛ ያደርግልኛል ያሉት ፕሮፋይላቸውን ማጉላት ነው፡፡ ብዙ ምዕራፍ የያዘው ይህ መረጃ ግን ህዝቡ ውስጥ ያሉትን ጥያቄዋች በተፈለገው መልኩ የሚመልስ አልሆነም፡፡

·         በ1997 ዓም በልደታ ቤ/ክ የሞተው ባህታዊና የቆሰሉት ሰዋች ጉዳይ መነሳት ነበረበት፡፡ ለምን ይነሳል ካልን አቡነ ጻውሎስ የዚያን ወቅት ነበር ሽጉጥ ተኮሱ የተባለውና፡፡ ባህታዊው አቡነ ጻውሎስን በጎራዴ እገድላለሁ ሲል ይዝት ነበር ቢባልም የአይን እማኞች ሰውየው በእጁ ምንም እንዳልያዘ ተናግረዋል፡፡ የሟች ጓደኛም ፔቲሽን የያዘ ወረቀት ሊሰጣቸው ነበር ብሏል፡፡ እና የትኛው ነው ታማኝ ሀሳብ ?

·         የእንግሊዝ መንግስትም ለአቡነ ጻውሎስ የትራንዚት ቪዛ ከልክሎ እንደነበር በአንድ ወቅት አንበናል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በሀገሪቱ ከሚኖሩ ኢትዮጽያዊያን ጋር ግጭት  ይፈጠራል የሚል ነው፡፡ ይህ ሃሳብ ምን ያህል መሰረት እንዳለው በመጽሀፉ ውስጥ ቢታይ በጣም ጠቃሚ ነበር፡፡

·         አቡነ ጻውሎስ ሚዛናዊ አይደሉም የሚባሉት በብዙ ወገኖች ነው ፡፡ ተቃዋሚዋች ለገዢው ፓርቲ ይወግናሉ፣ ጥብቅና ይቆማሉ ይሏቸዋል፡፡ አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች ፍትሃዊ አስተዳደር እንዳይሰፍን ወገናዊ አሰራር ይከተላሉ ባይ ናቸው፡፡ የማህበረ ቅዱሳን አባላት ነጻነታችንን ይጋፉናል ይላሉ፡፡ ቅልጥ ያሉ ፓለቲከኛ ሆነዋል የሚላቸው መንገደኛማ ስፍር ቅጥር የለውም፡፡ በዚህ ዙሪያ የእሳቸው አስተሳሰብና ምልከታ መንጸባረቅ ነበረበት፡፡ እነዚህ ጉዳዮች አልታሰበባቸውም ወይስ የማርያም መንገድ እንዲሆኑ ተፈልጎ ነው ?

·         ኢትዪጽያን የማያት እንደ ሁለተኛ ሀገሬ ነው የምትለው ቢዮንሴ ለ4 ቁጥርም ያላት ፍቅር ልዩ ነው፡፡ እናቷ የተወለዱት ጥር 4 ነው፡፡ ያገባችው ሚያዝያ 4 ነው፡፡ ልደቷ የሚከበረው መስከረም 4 ነው፡፡ የባልዋ ልደት ታህሳስ 4 ይከበራል፡፡ ወደ ሀገራችን የመጣችው ግን በዚህ ቀን አይደለም፡፡ ስራዋቿን በሚሊኒየም አዳራሽ በማቅረብ ዘፈን አፍቃሪውን ህዝብ አስደስታለች፡፡ በአቡነ ጻውሎስ ጋባዥነት የተደረገላት ስነስርዓት ግን ብዙ ምዕመናን አስቆጥቶ ነበር፡፡ መንፈሳዊ ቃና የሌለውን ዘፈን የምታቀነቅንን አርቲስት እንዴት ይጋብዛሉ ? እንደ ታቦትስ እንዴት ጥላ ተያዘላት ? ራቁት ገላን በማስተዋወቅ  ከምታቀነቅን ሴት ክርስትያኖች ምን ያማራሉ ? ዓለማዊ ዘፈንና ቤተክርስትያንስ ምንና ምን ናቸው ? እነዚህና የመሳሰሉ ጥያቄዋች ምላሽ ሳያገኙ ቆይተዋል፡፡ በምዓመናኑና በአቡነ ጻውሎስ መካከል ያለው ልዩነትም እንዲሰፋ አድርጓል ፡፡ ጸሀፊዋ በዚህ አጋጣሚ ይህን ሰበዝ መዘዝ ቢያደርጉት ማለፊያ በሆነ ነበር፡፡


ለማንኛውም ቃለ- ህይወት ያሰማልን


ገ/መድህን አርብ ጥቅምት 25 ቀን 1928 ዓም ነው የተወለዱት፡፡ አባታቸው ገ/ዮሀንስ ገ/ስላሴ ፣ እናታቸው አራደች ተድላ ይባላሉ ፡፡ ድቁና፣ ምንኩስናና ቅስናን አልፈው ወደ ቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የገቡት በ1949 ዓም ነው፡፡ ሶስት ግዜ ብልጫ በማምጣት ከንጉስ አጼ ሃይለስላሴ እጅ ሽልማት ተቀብለዋል፡፡ለ15 ዓመታት በዲቁና፣ ቅስናና ምንኩስና አገልግለዋል ፡፡ በመንበረ ጽባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል መደበኛ ቀዳሽ በመሆን ለ 8 ዓመታት ሰርተዋል ፡፡  ጻውሎስ በሚል ስያሜ የኤጺስ ቆጾስነት ማዕረግ የሰጧቸውአቡነ ቴዋፍሎስ መስከረም 17 ቀን 1968 ዓም ነበር፡፡ በነገረ መለኮት ዲፕሎማ፣ ባችለርና ዶክትሬት አላቸው፡፡ የማስትሬት ዲግሪያቸው በክርስትያን ስነ ምግባር ነው ፡፡

ለሁላችንም ጥሩ ስነ ምግባር ይስጠን፡፡


አሜን !!

No comments:

Post a Comment