Friday, June 15, 2012

‎ከምናብ ጋር መነጋገር‎


በሃሳብ ተቀፍድጄ… በጭንቀት ናውዤ… ውል ያለው ጉዳይ መጨበጥ ሲያቅተኝ እንደተጫነች አህያ እተነፍሳለሁ፡፡ አንድ የዳጎሰ የኪነጥበብ ማዕድን ፈልፍሎ ለማውጣት ውስጤ በሃሳብ ትራክተር ይታመሳል፡፡ ጉቶው - አለቱ ይተረማመስ እንጂ እንደ ምንጭ ኮለል ብሎ በእርጋታ የሚፈስ ምናባዊ ውጤት ማግኘት ያስቸግራል፡፡ ግም…ግም…ጓ… የሚል ባዶ ጩኸት ብቻ፡፡ እንደሚመስለኝ ትራክተሩና ምናቤ ይገጫጫሉ፡፡ ምናልባትም የጉቶው ስለት ስብዕናዬን ሲወጋው እባንናለሁ፡፡ ይሄኔ ይጨንቀኝና በረጅሙ እተነፍሳለሁ፡፡  ትንፋሼ ከበስተኃላዬ በስሱ ሲንኳኳ የሚሰማውን ባዶነቴን ውጦ ለማስቀረት እንኳን አልታደለም፡፡

 እ . ፎ . ይ .  !   ብቻ ፡፡
 የተወጣጠረ ግን የማይቀደድ ትንፋሽ ፡፡

ከጠባቧ ምናቤ እወጣና ጠባቧን ቢሮዬን እቃኛለሁ፡፡ አንድ ብልጭታ አገኝ ዘንድ ፡፡ ኮርኒሱን… አምፖሉን… ግድግዳ ላይ የተለጠፉ ስዕሎችን… የቢሮ ተጓዳኞቼን አንድ በአንድ እቃኛለሁ፤ እመረምራለሁ፡፡ ድንገት አይኔ ኮርኒስ ላይ ሲቀር እንደሚከተለው አስባለሁ፡፡

‹ ከኮርኒሱ ጀርባ አይጥ ብትኖር… ከሰው ጋር የምታደርገውን ግብግብ ፣ ውጣ ውረድ ፣ ድብብቆሽ ፣ ብልጠቷንና ቅልጥፍናዋን ብቀርጽ … ›

‹‹ ኮርኒሱ አልተቀደደ ! ድርጊቱን የምትስለው በተጨባጩ ምልከታ ወይስ በአይነ ልቦና ጉዘት ? ማን ነበር ካላየሀው በመነሳት አትቀባጥር ያለው ? በርግጥ የአይጥና የጦጣ ብልጠት ዓለማቀፋዊ በመሆኑ የተረት ተረቱ መነሻነት በቂ ይሆናል፡፡ ግን በየትኛው ፍጥነትህ ነው እንደርሷ ከአንዱ ማዕዘን ወደ ሌላኛው ሸረረረር …. የምትለው ? ››

ምናቤ ሲጠይቀኝ ‹ ይህ አንፖል › ስል አንሰላስላለሁ

 ‹ ብርሃኑና ሊፈጥር የሚችለው ተምሳሌት ዕጹብ ነው፡፡ ከጀርባው ምን ሊጠና ይችላል ? ስታርተር ? ስታርተር የፈጠራ አብነት ነው፡፡ ይህን አስፈላጊ ነገር ማን ፈጠረው ? ቶማስ አልፋ ኤዲሰን ? ›

‹‹ ከዛስ ?! ›› ይለኛል የሆነ ድምጽ

‹ ኤዲሰን ማነው ? በህጻንነቱ ረባሽ ነበር ወይስ የልጅ አዋቂ ? ምን ያህል ግኝቶች አበርክቶ ይሆን ? ›

‹‹ ለምን ትጃጃላለህ ?! ››

‹ ምነው ? ›

‹‹ መጻፍ የፈለከው ታዋቂ ሰዋችና ስራዋቻቸው ነው ወይስ ወጥ ፈጠራ ? ››

ቢሮው ግድግዳ ላይ የተለበጡት ስዕሎች ያማምራሉ፡፡ በአንድ በኩል በውስጥ ቁምጣ ብቻ የሚታዩ ቆነጃጅት በሌላ በኩል የተፈጥሮ ውበት ያማልላል፡፡ ከኮረዶቹ ጀርባ ምራቅ የሚውጡ ሰዋች፣ የፈዘዙ ዓይኖች ሊታዩ ይችላሉ፡፡

‹  እርስ በርስ እንዲቦጫጨቁ ቢደረግስ ?!  ቢያሻ ተፈጥሮን እንደ ጨው መነስነስ፡፡ ተራራው፣ ወንዙ፣ ደኑና አየሩን በብዕር እጆች መኮርኮር፡፡ ከዚያም ውበት፣ ተፈጥሮና አድናቆቶችን በአንድነት ማሰናሰል ፤ በልዩነቱ ደግሞ ማገጫጨት  ›

‹‹ ከግጭቱ ምን እንዲመዘዝ ነው ያቀድከው ? ትግሉና ውጤቱ የሚፈጥሩትን ህብረ ቀለም ታውቀዋለህ ? ያ ነገርስ አዲስነት እንዳለው ርግጠኛ ነህ ? ››

ደግሞ ሲጨንቀኝ ጓደኞቼን እቃኛለሁ፡፡ አቀርቅረው ይጽፋሉ፡፡ አፍላፍ ገጥመው ያወራሉ፡፡

‹ እንደ መልካቸው ባህሪያቸውም ይለያያል፡፡ እና ለተለያዩ ገጸ ባህርያት ምስል ብጠቀምባቸውስ ? ሴራ፣ መዋቅር፣ ቅብርጥሶ ከሚባለው ድንጋጌ ጋር ማዋሃድ … ለውህደቱ ግዜ ጠብቆ የፈጠራ እንጀራ መጋገር፡፡ መቼም በከፊል አውቃቸዋለሁ ፡፡ የሳቃቸው ለዛ፣ የግንባራቸው ሙዝዣ ምንነታቸውን ሹክ አይለኝ ይሆን ? ይሄኛው ውጫዊ መገለጫ ነው፡፡ ለታሪኩ ፍሰት ግን ውስጣዊ እምነታቸውና አመለካከታቸው ነው ወሳኙ ፡፡ ማነው እኩዩ ? የቱ ነው ሰናይ  ? ሽርጉድ አብዢው  ? አፋሽ አሽርጋጅ ?  ከኔ ወዲያ ላሳር ባዩስ ? አውቆ የተኛው ? ስራን ያጌጠስ  ? በርግጥ ይህን ብቻ ማወቅ ለጀርባ ንባብ በቂ ነው ? ማህበራዊ ትስስር ፣ ከቢሮ ውጭ ያላቸው ማንነት… ይህን ሁሉ ግትልትል መረጃ ማሰባሰብ አስፈላጊ ነው ለካ  ! አዲዮስ !! ቁንጽል ነገር ይዞ መንጦልጦል ሰፊው የጭንቀት ባህር ውስጥ ይዘፍቃል ›

‹‹ለምን አርፈህ ቁጭ አትልም ?! ››

‹ ለምን ተብሎ ? ›

‹‹ ጥሩ ፈጣሪ ሳይሆን ጥሩ አንባቢ መሆን ይቻላላ ! ምናብህ ያምጣል፤ የመፍጠር ነጎድጓድ ያሰማህ እየመሰለህ ብዕር ትቀስራለህ ፡፡ ጩሐቱ ግን ዳመና ያላዘለ ነው ፡፡ ያለ ዳመና ጠብታ አይኖርም ፤ ምናብህ ውስጥ ያሉ ሴሎች ጠብታ ! እያሉ ወደ ላይ ያንጋጥጣሉ ፡፡ የደረቀው አፋቸው ጫማ አይቶ እንደማያውቅ እግር ተሰነጣጥቋል፡፡ ስንጥቁ ውስጥ የገባው ለሃጭ እንደ ደም ረግቶ ይኮሰኩሳቸዋል፡፡ ያካሉ፡፡ ጠ . ብ . ታ . ! ጩኀታቸው እንደ ነጎድጓድ ይባርቃል፡፡ አጅሬ ምናቤ ውስጥ ትራክተር አለ እያልክ ታወራለህ ››

‹ ወዲያ ! የማይረባ ፍልስፍና አትደስኩር ! ስሙን ያላስታወስኩት አንድ ደራሲ አዕምሮህ ታጥኖ ያልተቀመጠ ጋን ከሆነ አርፈህ ተቀመጥ ይላል፡፡ እንደ ገ . ዱ ሞፓስ ያሉ ደግሞ ጭንቅላት የጠጅ መጥመቂያ ይመስል ሁሌ በወይራ መቀቀሉን አይቀበሉም፡፡ ስላዩት ይጽፋሉ፡፡ አንዳንድ የዛፍ አይነቶቸን በመጥረቢያ ስለቀጠቀጥክ ብቻ አይፈለጡም፡፡ ውርወራህ ብልቱን ካገኘው ዛፉ የኮረኮሩት ያህል ፈከክ ይላል፡፡ እና የተዋበ ፈጠራ ለመስራት አያሌ መጻህፍትን መዋጥ ወይም አሊያም የኮሌጅን በር ማንኳኳት የግድ አይደለም፡፡ አነስተኛ ዕውቀትም ቢሆን ቦታ አለው፡፡ ዋናው ግብ እውቀቱ ከብርቱ ፍላጎት ጋር የሚቀጣጠልበትን የትጋት ፈንጂ ማጥመድ ነው፡፡ በርግጥ እስኪፈነዳ ድረስ ያለህን ስሜትና ፍርሃት በትክክል ለመመዝገብ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ሲፈነዳ በፍርሃት አብሮ የመፈንዳቱን ሰዋዊ ባህሪ ተቋቁሞ ተፈላጊውን ጭብጥ ለማሳየት በመጀመሪያ የጀገነ ሀሞት ለጥቆ ያልጎለደፈ ብዕር ካለህ ሁሉ ነገር አለቀ ›

‹‹ ከዛስ ? ›› የሹፈት ድምጽ

‹ የአፍዝ የአደንግዝን ለመንቀል ፈንጂ መጠመዱ ለምን አስፈለገ ማለት የዋህነት ነው ፡፡ ማለት ያለብህ ዘመቻ አንድ እንጂ ! በዘመቻ ሁለት ራስንና ሌሎችን መመልከት፡፡ ከተናጥል ግንዛቤና ልምድ፣ ከማህበረሰባዊ ትዝብትና ገጠመኝ… እንዲህ እንዲህ ከሚሰኙ አብነቶች በመነሳት የዳበረ ጭማቂ ለመፍጠር መጠበብ ፡፡ ይህ ማለት ምንም ማለት አይደለም፡፡ የምታየውን በሚገባ ማስተዋል፡፡ በተለያዩ ሁኔታና ለሰሜት ቅርበት ያላቸውን ድርጊቶች መዝግቦ መያዝ ፣ በተለይ የተመዘገቡ ድርጊቶች ምን ሊወጣቸው እንደሚችል ስትሄድ ስትቀመጥ ማንሰላሰል… የድርሰት ኩታን ለማበጀት በምናባዊ ቀሰም ማዳወር … እስኪሞሉ መግመድ… እንደገና መፍታት … በይሆናል አይሆንም እሳቤ መዋቅሩን ማዳበር … የሴራው ጡዘት እንደ ዕለት ከእለቱ ደውር እንዲከር እድል መስጠት… በመጨረሻም መጻፍ ፡፡ ይኀው ነው ፡፡ ›

‹‹ ወይ ይኀው ነው ! ጥሬ ሀሳብ ሳይገረደፍ፣ ሳይሰለቅ፣ ሳይደለዝ ኪነጥበባዊ ፋይዳ ሊኖረው አይችልም ፡፡ መወሰንማ መች ይገዳል ? ድርጊትንና ምናባዊ ምጥቀትን ማቆራኘት እንጂ ፡፡ በዚህ መሃል ደግሞ አያሌ መሰናክሎች ሊያጋጥሙ ያችላሉ ፡፡ ያልተረጋጋ መንፈስ ይዞ ብእር መጨበጥ የመሸከም ያህል ይከብዳል ፡፡ በዚህ መልኩ ማዕድን ቆፍሬ አወጣለሁ ማለት አይቻልም ፡፡ ››

‹ ለምን አይቻልም ? የሚቆፈረውም እኮ ይኀው ነው፡፡ ያልተመቸውን ፍቅር… የተጎሳቀለ ህይወትን… የገረጣ ረሃብን… በአጠቃላይ እንግልት ሲያቅስት መሳል፡፡ ይህ ነጸብራቅ ለሌሎችም ይሆናል ፡፡ ›

‹‹ ግን ለማን ብለህ ነው እርስ በርስህ የምትገጫጨው ? ነጋ መሸ የምታቃስተው  ? ፈጥሮ ያለፈለትስ ማነው  አንዳንዶች ለህሊና ርካታ ይላሉ ፤ እኔ ደግሞ የማይጥም መዘየጃ እለዋለሁ ፡፡ በቃ ተወው ! ተራ ፈጣሪ ሆኖ በጉራ ከማበጥ እጅን ለሽንፈት መስጠት፡፡ ››

‹ ግን እኮ የፈጠራ ትርፉ ጭንቀት ብቻ አይደለም ፡፡ ለሌሎች ቤዛ መሆንንም ያሳያል፡፡ ግን እኮ እንደዛ ፍልጥ እንጨት ብልቱን ካወክ ሁሉም ነገር ወከክ ነው የሚለው ! ›

‹‹ ይህን ሚስጢር ለማወቅ  ታዲያ ተራራ መናድ ይጠበቃል እኮ ?! ››

‹ በቃ ጭንቀት ወደዚያ !!!  -  ውጥረት ገለል በል !!! ›

No comments:

Post a Comment