Tuesday, June 5, 2012

‹ በሁመራ ኖራ ይዘንባል … ሙቀት ይዘንባል … ›


ተከዜና ድልድዩ

ወታደሮች ላብ ደምን ይተካል የሚሉት ብሂል አላቸው፡፡ በሁመራ እንደ ጉድ የሚያዘንቡትን ላብ ለመተካት ውስጥዋን የሚነግሩት ‹‹ ጠጣ ! ›› የሚለውን ቃል ነው፡፡ ቀዝቃዛ ውሃ እንደ ጉድ ይጠጣሉ… ቀዝቃዛ ቢራ እንደ ጉድ ይጠጣሉ… እንደ ጉድ እየጠጡ ፊኛን ለማስተንፈስ በተደጋጋሚ ቁጭ ብድግ በማለት መከራ አይበሉም፡፡ በሁመራ የብልትን ሚና ተክተው የሚጫወቱ ቀዳዳዋች መዓት ናቸው፡፡ የተጣራ ሽንት ከብብት እየመነጨ ቁልቁል ይንደረደራል፡፡ አናትዋ፣ ግንባርዋ፣ ወገብዋ፣ እግርዋ ሁሉ ፈሳሹን እያስተነፍሱ ያግዝዋታል፡፡ ከርስዋ የሚጠበቀው መምጠጥ ብቻ ነው፡፡ በሁመራ ተማሪዋች አስካሪ ነገሮችን ዘርዝሩ ተብለው ቢጠየቁ ሙቀትን እንጂ ቢራና ድራፍትን በልበ ሙሉነት ለመጻፍ የሚያስችላቸው መሰረት ያለ አይመስልም፡፡ የማስከር ተግባሩን የተነጠቀው ቢራ ‹ ትግሌን በሰላማዊ መንገድ አፋፍማለሁ › የሚል አዲስ ስትራተጂ ቀይሶ እየተንቀሳቀሰ ይመስላል ፡፡ በርግጥም በሁመራ  እንደ በሶ ደረት ላይ ደስታ ጭሮ የሚወርድ ቢራ ይዘንባል …ኖራ ይዘንባል… ሙቀት ይዘንባል… ስጋት ዳምኗል …

·        የኖራው ጉዳይ ፤

ርግጥ ነው የኖራ ወይም የሲሚንቶ ፋብሪካ አላየሁም፡፡ ሰው ሰራሽ ኖራ እንዲፈጠር ወይም የሲሚንቶ ፋበሪካ እንዲቋቋም የሚያግዙ ባለሀብቶችና አስተዳዳሪዋች የሉም ማለት ግን አይደለም፡፡

እንደሚታወቀው የሁመራ መሬት ለሰሊጥና ለጥጥ ምርት የሰጠ በመሆኑ ከተማዋን ቱባ ባለሀብቶች ወረዋታል፡፡ ባለሀብቶች ለምርታቸው ማስቀመጫ ያስገነቡት ሽንጠ ረጃጅም መጋዘኖች በርካታ ናቸው፡፡ የባለሀብቶችን እርሻ የሚያርሱ ትራክተሮችና ምርታቸውን ወደ አ/አበባም ሆነ ወደ ሱዳን የሚያመላልሱ ትልልቅ የጭነት መኪናዋች ያን አቧራማ መንገድ ሲተረትሩት ይውላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ነዋሪው፣ ቢሮዋች፣ መጋዘኖች ሁሉ አቧራውን ያለ ስስት ይጠጣል፡፡

ሲስልም ሆነ ሲያስነጥስ አቧራን ያፈልቅ የነበረው ነዋሪ መንገዱ እንዲሰራለት ጮሆ ጮሆ ሲታክተው ትቶታል፡፡ የአካባቢው በለሀብትም ሆነ ባለስልጣናት እስካሁን ኖራ ሆነው ለመቀጠል እንዴት እንደፈቀዱ አንድዬ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ እንግዲህ መንገዱ ባያድግ አቧራው ማደግ ስላለበት - ስለሚገባውም  ዛሬ ደረጃውን ወደ ኖራነት የቀየረ ይመስለኛል፡፡ ባለሀብቱ የሰሊጥ ትርፍ ባይሳብጣቸው ኖሮ እጅግ ተፈላጊ የሆነውን ሲሚንቶ ለማምረት ፍቃድ ከመጠየቅ ወደ ኃላ አይሉም ነበር፡፡ ጥሬ ዕቃው የት አለና  ? አትበሉ፡፡ ምድረ ኖራ እያደር ሲሄድ ሲሚንቶ አይወጣውም እንዴ ? ብቻ መስሎኛል - የመሰለኝ ሌላም ነገር  አለ
….. አይኑን ጨፍኖ ብር የሚቆጥር ባለሀብት ያየሁ መስሎኛል
….. ጫማው በአቧራ ተውጦ ስለ ፈጣን ልማት የሚሰብክ ካድሬ ያየሁ መስሎኛል
….. በጦርነት ሳይሆን በቢሮክራሲ ተሸንፎ እንደ አቅሙ ሙቅ ሻይ ወይም ቀዝቃዛ ቢራ ታቅፎ የሚውል ነዋሪ ያየሁ መስሎኛል

·        የሙቀቱ ጉዳይ ፤

የሁመራ ሙቀት ያስጨንቃል ፡፡ በተለይም እንግዶች ስምንተኛው ዙር እንደደረሰ የቦክስ ተጫዋች ሁለመናቸው ሊሰክር ይችላል፡፡ ሙቀቱ ዓይን ስለሚያጠብ ጥቁር ቻይናዋች በብዛት እንዲታዩም ያደርጋል፡፡

በየቤቱ፣ ሆቴልና ቢሮዋች  ቋ… ቋ… እያለ የሚሽከረከረው ፋን ራዕይና ተልዕኮው ለነዋሪው የተሻለና ቀዝቀዝ ያለ ንፋስ መፍጠር ቢሆንም የተሳካለት አይመስልም፡፡ ሞቃታማ አየርን በዘመናዊ መልኩ ለአካል ማቅረቡን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ አልፎ አልፎ ሀሴት ጣራ ላይ የሚያደርስ ውብ ንፋስ ሊመገቡ ይችላሉ - የበረሃ ዛፎች ስር ቁጢጥ ካሉ ፡፡

የበረሃ ዛፍ እንዳለ ይታወቃል፡፡ አንዳንድ ዛፎች ጥቂት ኖረው የሚሞቱ ናቸው ፡፡ ዘራቸው ግን ለረጅም ዓመታት አፈር ውስጥ ሊቀመጥ ይችላል፡፡ ሞተ የተባለው ዘር ጥቂት ዝናብ ሲያገኝ በፍጥነት ያብባል፡፡ ግመልና ዔሊን የመሳሰሉ በረሃ ተኮር እንስሳትም እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እንስሳቱ ሙቀት ቀን ይሰበስቡና ማታ ያስወጣሉ፡፡ የተፈጥሮ ጥቃትን በተፈጥሮኛ የመቋቋም አቅም አላቸው፡፡

ለበረሃ የተሰራ ሰው አለ  ? ነው ሰው በቆይታው ነው  ቅዝቃዜንም ሆነ ሙቀትን መለማመድ የሚችለው ? ብዙዋች በሙቀቱ ሲቀልጡ ምንም የጭንቀትም ሆነ የሙቀት ምልክቶች የማይታይባቸው ሰዋችን አስተውያለሁ፡፡ ሙቀቱ የሚያቀልጠው የሰውነታቻው  ስብ ስላለቀ ወይስ የግመልን ስጦታ በሆነ መንገድ ስላገኙ ? ትዝብት ነው - የታዘብኩት ሌላ ነገርም አለ
….  ፍቅረኛሞች እንደ ፍላጎታቸው ተቃቅፈው እንዳይዝናኑ ተጽዕኖ ፈጥሯል
….. በስራ መኃል ደጋግሞ እንቅልፍን ስለሚጣራ የሚጃጃሉ ቡድኖችን ማየት ቀላል ነው
….. በአንድ ጣራ ስር፣ በአንድ አልጋ ላይ ተቃቅፈው መገኘት የሚገባቸው ባልና ሚስቶች እንዲነፋፈቁ አድርጓል
….. ህጻናት እንደ ዶሮ ጫጩት ወይም እንደ ድመት ግልግል ያለ እድሜያቸው እንዳይቀጩ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የማይተናነስ ጥበቃ ማድረግን ግድ ይላል


·        የስጋቱ ጉዳይ ፤

ቴዲ አፍሮ በቅርቡ ባወጣው አልበሙ ስለ አስመራ ማዜሙ ይታወቃል፡፡
            ጋራው ቢከልለን ያ ተራራ
            አትወጣም ከልቤ ጓል አስመራ በማለት

እዚህ ሁመራና ኤርትራ አፍና አፍንጫ ሆነው ይታያሉ ፡፡ የከለላቸውም ርቆ የሚታየው ጋራ ሳይሆን ሰፊው የተከዜ ወንዝ ነው፡፡ ከተከዜ ማዶ ኤርትራ ከተከዜ ወዲህ የኢትዮጽያ ግዛት ነው፡፡ ከተከዜ ማዶ የኤርትራ ወዲህ ደግሞ የኢትዮጽያ ወታደሮች ይታያሉ፡፡ ከተከዜ ማዶ አንዳንድ ቤቶች ወዲህ ደግሞ ለ G + 1 ታቅደው ጂ - ዜሮው አልቆ ፎቁ ላይ ያገጠጡ ብረቶች የሚታይባቸውን የሁመራ ቤቶች ይመለከታሉ፡፡

የተከዜን ውሃ ከዳር ለማንቦጫረቅ፣ አጠገቡ ፎቶ ለመነሳት፣ ዳሩ ላይ ቁጭ ብሎ ‹ ወይ ኤርትራ ያንቺ ነገር እንዲህ ሆኖ ቀረ ? › በሚል ቁዘማ እንዲሰምጡ ይፈቀዳል ፡፡ ርግጥ ከተወሰነ ሰዓት በኃላ ወደ አካባቢው ዝር ማለት ይከለከላል ፡፡ ለመዋኘትም ሆነ ወደ ማዶ ለመሻገር ግን አይሞከርም፡፡ እንዲህ እንደዛሬው ፊትና ጀርባ ሳንሆን ወደ አስመራ የሚያሻግር ረጅም ነጭ ድልድይ ይታያል፡፡ ምናልባት መወጠሪያ ቢኖረው ኖሮ አዲሱን የአባይ ድልድይ የመምሰል አቅሙን ያጠናክር ነበር፡፡ ግን አሁንም ድልድዩ የጋራችን እስከሆነ ድረስ እስከ መሃል መሄድ ቢፈቀድ ጥሩ ነበር፡፡ ድልድዩ ላይ ሆኖ ለተከዜ ማንጎራጎር ወይም አንት አራም ስንኝ ለመወርወር የሚመች መስሎ ታይቶኛል ፡፡ የሆኑ መኳል የሚቀራቸው ስንኞች ወንዙን እያየሁ እንኳን ውር ውር እያሉብኝ መሰለኝ - ይኀው ብዘረግፋቸው …

ግዜ ያደናበረህ ሽንጣሙ ተከዜ
ዛሬ ግን ምንድነህ ? የማነህ ጎበዜ ?
ድንበር ነው ዓላማህ - የእሾህ መስመር
ወዲህ ወዲያ የሚሾልከውን ነፍስ ማሳጠር
ወንዝ ነህ እንዳልል ውስጤን ተናነቀው
ሀገሬው ሲጠጣህ ሲዋኝብህ አላየው
ለመሆኑ ማን ሆንክ ? ዘር ሀረግህ የት ወደቀ ?
ምርጫ  - ሪፈረንደምህ እንደምን አለቀ ?
ተናገር እንደ እኛ በካርድህ አትፍራ
‹ ሀገርን ያስማማ › ላንተ አይሆን ኪሳራ፡፡
  • o          
‹‹ በእናቴ ኢትዮጽያ - በአባቴ ኤርትራ ! ››
     ምናልክ አንተ ?!?! ማለት ነበር…

በሁለቱም አቅጣጫ የድንበር ጠባቂዋች ቢኖሩም እስካሁን ከመፋጠጥ የዘለለ የትንኮሳና የምላሽ ወጎች አለመደረጋቸውን ጠባቂዋቹ ነግረውኛል፡፡ አያድርገውና ከፍ ካለው የኤርትራ አካባቢ የትልቅ መሳሪያ ቃታ ቢሳብ ሁመራንና ነዋሪዋቿን በቀላሉ ማጣት ይከሰታል፡፡ ይህን ስጋት ይዤ ለጠባቂዋቹ ጥያቄ አቀረብኩ

‹‹ ሻዕቢያ እንዲህ ያደርጋል ብለን አናስብም፤ በፍጹም ! ›› የሚል ምላሽ ሰጡኝ፡፡ መልዕክቱ ትንኮሳ ከጀመረ የአጸፋ ጥቃቱን አይችለውም የሚል ይመስላል፡፡ በተቃራኒው ያነጋገርኳቸው አንዳንድ ነዋሪዋች ሁሌም በጥርጣሬ፣ ሁሌም በስጋት፣ ሁሌም በተጠንቀቅ እንደሚገኙ ነው ያጫወቱኝ፡፡ ለዚህም መነሻ አላቸው፡፡ አሁን በማጫውታችሁ ቦታ ባይሆንም ኤርትራዊያን ወደ ኢትዮጽያ ክልል ሰውን አይደለም ከብቶችን የሚያስገቡበት ሁኔታ አለና፡፡ ኢሳያስ ሞተ የሚለው ዜና የተሰማ ግዜ በመቀሌ ብቻ ሳይሆን በሁመራም ብዙዋች ጮቤ ረግጠዋል፡፡ የዚህ ስጋት መቋጫ እንዴትና መቼ ይገኝ ይሆን ?



1 comment:

  1. በጣም ተመስጬ አነበብኩት። በጣም ያሳቀኝ ተልኮው ያልተሳካለት ቤንትሌተር አገላለጽ ሲሆን፣ ስለ ተከዜ የተቋጠረው ግጥምህና ተከዜን የገለጽክበት መንገድ ስነ ውበት የተሞላው ሆኖ አገኝቸዋለሁ። እኔም ድልድዩ ላይ ቁም ቁም ብሎኝ ነበር። ግን ግን ተከዜ እስከመቼ በዚህ ይቀጥላል?

    ReplyDelete