Friday, April 19, 2013

‎በመተካካት የተጎዳው ጢስ አባይ ! ‎




የአማራ ባህል፣ ቱሪዝምና ፓርክ ልማት ቢሮ ለቱሪስቶች በሚያሰራጨው ብሮሸር ላይ ስለ ጢስ አባይ ፏፏቴ ግሩም ጽሁፍ አስፍሯል ፡፡ በየቀኑ ጢስ አባይን ለመመልከት የሚሄደው ደቀመዛምርም መምህሩ የጻፈውን ቅኔ በልቡ እያጠና ወደ ቦታው ይጓዛል ፡፡ በነገራችን ላይ ወደ ፏፏቴው ለመሄድ ሁለት አማራጮች አሉ ፡፡ አንደኛው የአባይን ወንዝ በጀልባ ተሻግሮ 15 ደቂቃ የእግር መንገድ መጓዝ ነው ፡፡ በጎዞዬ ላይ ምን አያለሁ ካሉ በመስኖ የሚበቅሉ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ፣ ጋሽዬ ልከተሎት ላስጎበኝዎትም ካሜራ ካልያዙ እንኳ በፌስ ቡክ ላይ የሚለቁትን ምርጥ ፎቶ በሞባይልዎ ላነሳዎት እችላለሁ የሚሉ በርካታ ማቲዎችን ፣ ሻርፕና ጌጣጌጦችን ካልገዙኝ በማለት እስከመዳረሻዎ ሳይታክቱ የሚሸኝዎትን ሰዎች እንዲሁም ‹  የሰው ነገር › የሚል ስም የተሰጠውን ቅጠል ይመለከታሉ ፡፡ ይህ ቅጠል በእጅ ሲነካ ሽምቅቅ ብሎ መጠኑን ይቀንሳል ፡፡ በሌላ አነጋገር የቅጠል ኤሊ መሆኑ ነው ፡፡ ድንጋይ ውስጥ ባይሆንም ሁለመናውን ግንዱ ላይ ይለጥፋል - ከሶስት ደቂቃ ቆይታ በኃላ ደግሞ ወደቀድሞው ይዞታው ይለጠጣል ፡፡

 ሁለተኛው መንገድ መኪናዋን እስከተወሰነ ርቀት ከነዱ በኃላ ከ 30 እስከ 40 ደቂቃ በእግር ሊጓዙ ግድ የሚልዋት ነው ፡፡ ይህኛውን በዳገት የታጀበ አድካሚ መንገድ ቱሪስቶች ይመርጡታል ፡፡ ምክንያቱም አካባቢውን በአግባቡ ለመቃኘት ፣ በ 17ኛው ክፍለ ዘመን የተሰራውን ጥንታዊ የአላታ ድልድይና ሸለቆ ለመመልከት ስለሚረዳ ነው ፡፡ እኔ ሁለተኛውን አማራጭ ስለማውቀው አንደኛውን ምርጫ በመጠቀም ቦታው ተገኝቻለሁ ፡፡ እናም የብሮሸሩ ምንባብ ከጉብኝት በኃላ የሆነ አጭር መልመጃ ቢኖር እንኳ በአግባቡ አስታውሶ ለመመለስ ስለሚረዳ ጎብኚው ደጋግሞ ከኪሱ እያወጣ ያያታል ፡፡ እንዲህ ትላላች ፡፡

The Falls are found at 30 km to south of Bahir Dar near Tis Abay town. Here there is a spectacular basalt cliff Where the Nile form an incredible falls of 45 meters high, known as the Blue Nile Falls. The noise, the force and the smoke created by this fall is really worth discovering. The Blue Nile Falls is locally called the Tis Isat , meant water that smokes .

ቱሪስቱ ከጉብኝት በኃላ ወደ መረጃ ክፍል ተመልሶ ቢገባ ግን መምህሩ ሊፈትነው አይሞክርም ፤ ምናልባትም ትምህርትም ሆነ መረጃ ሰጪዎችን ላያገኝ ይችላል ፡፡ ግን በትምህርቱና በብሮሸሩ ንባብ መሰረት ራሱን መፈተኑ ይጠበቃል - እንዲህ እያለ ፡፡ ‹ በንባቡ መሰረት ትክክለኛ የሆነውንና ያልሆነውን ለይተህ አውጣ ! ትክክለኛ ባልሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ አብሮህ ከጎበኘው ሰው ጋር በድፍረት ተወያይበት ፡፡ የመፍትሄ ሀሳቦችህንም ሀሳብ መስጫ ሳጥን ውስጥ ጨምር ! ›

ሀ . ትክክለኛ የሆነው ፤

1 . ጢስ አባይ ከባህር ዳር 30 ኪሜ ርቀት ላይ ይገኛል
2 . 45 ሜትር ቁልቁል ይወረወራል

ለ . ትክክለኛ ያልሆነው ፤

1 . የሚገርም ፏፏቴ ሊባል አይችልም
2 . ድምጹና ሁካታው እንደተባለው የተጋነነ አይደለም
3 . ታች ሲወርድ የሚፈጠር ልዩ ጢስ የለም
4 . የሚፈጠር ቀስተ ዳመና የለም
5 . ግርማ ሞገሳም ሳይሆን ቆሌ የራቀው መሆኑ ይታያል ፡፡

የመፍትሄ ሀሳብ ፤

. የሰው ነገር የተባለው ቅጠል አባባል አሁን ገና በአግባቡ ገብቶናል

በርግጥም ቱሪስቶች ብዙ ተወርቶላቸው ግዜ ፣ ገንዘብ እና ጉልበታቸውን መስዋዕት አድርገው ጢስ አባይ ዳገት ላይ ሲደርሱ ‹‹ እንግዲህ ጢስ አባይ ፏፏቴ ማለት ይህ ነው ! ›› ይላቸዋል ወጣት አስጎብኚው

‹‹ የቱ ? ››
‹‹ ይኀው ፊት ለፊት የምታዩት ! ››
‹‹ መቼም እየቀለድክ አይደለም ! ››
‹‹ እረ በስራ አንቀልድም ››
‹‹ ካልቀለድክ ታዲያ የታለ  የፏፏቴው ግዝፍና ? የቱ ነው ግርማ ሞገሱ ? የታለ ዳገት ላይ የሚደርሰው የውሃ ፍንጥቅጣቂ ? ቀስተ ዳመና የተባለውስ ? የታለ አስደማሚው ጢሱ ? ››

አስጎብኚው ያለው ብቸኛ እድል የሰው ነገር እንደተባለቸው ቅጠል ቀስ እያለ መሸማቀቅ ብቻ ነው ፡፡ ሳር እንዳጣ ከብት እንዲህ የገረጣውን ጢስ አባይ ለሃይል ማመንጫ ስለተገደበ ወዘተ … እያለ ማሳበቡ ለቱሪስቱ በቂ ምላሽ እንደማይፈጥርለት እሙን ነው ፡፡ ምክንያቱም የኃይል ጥያቄ ለሀገሬው እንጂ ለቱሪስቱ ጉዳዩ አይደለምና ፡፡ የእሱ መሰረታዊ ጉዳይ ብዙ ያወጣበትና የለፋበትን መስህብ አይቶ መርካት ነው ፤ እርካታው ከሞላ ደግሞ ወደ ሀገሩ ሲሄድ ያየውን በማውራት እግረ መንገዱን ማስታወቂያ መስራት ነው ፡፡ ዛሬ ግን አያሌ አስጎብኚዎች እንግዳቸውን ለማሳመን ሳይችሉ በርካታ ጎብኚዎች በሚሰጣቸው ምክንያት ሳይረኩ እየተበሳጩ መመለስ ግዴታቸው ሆኗል ፡፡

የፏፏቴው ጉዳይ አሳሳቢ ነው ፡፡ 75 ከመቶ ያህሉ ለሃይል ጥቅም ስለተገደበ ወደ ፏፏቴው የሚወርደው የውሃ መጠን የወፍራም ሰው ሽንት አክሏል ፡፡ ይህን ኢምንት ውሃ ደግሞ በሌላ ቦታ ማየት ይቻላል ፡፡ ወይ ያለቅጥ የሚሰማውን የተንዠረገገ ማስታወቂያ እንደ ጎጃም ልጅ ቁንጮ አስቀርቶ መከርከም አሊያም በድንጋይ ፋንታ ሙሉ ዉሃ የሚታይበትን ፕሮግራም ነድፎ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ፡፡ ለምሳሌ ያህል ቅዳሜና እሁድ በርከት ያለ የውሃ መጠን ከግድቡ ቢለቀቅ ጎብኚው ሳምንቱን እየጠበቀ እየረካ ሊመለስ ይችላል ፡፡ የማይቻል ከሆነ ግን በቴሌቪዥን የሚታየውና በቃል የሚነገርለትን ጢስ አባይ ለሁለት ከፍሎ ማየት ሊገባ ነው ፡፡ የሚያስጎመጀውን ‹ የቀድሞው ጢስ አባይ › በማለት የአሁኗን ‹ በመተካካት የተገኘች › ማለት ይሻላል ፡፡ 
ምክንያቱም ዉሸት ስለሚያሳፍር ፡፡ ባይሆን እቺ የተተካቸው ‹ አቅም እየፈጠረች ስትሄድ መፈርጠሟና ማስደመሟ አይቀርም › እያሉ መስበክ ይሻላል ፡፡ የቱሪዝሙም ገቢ አይቅርብኝ ፣ የሃይል ጉዳይም የግድ ነው ብሎ ውሃ ውሃ የሚል ወጥ መስራት ግን መጨረሻው የበሰለውን ማበላሸት ይሆናል ፡፡ 

Tuesday, April 9, 2013

‎ሰላማዊ ሰልፍ በየዓይነቱ !‎


mexico
.


ሰላማዊ ሰልፍ ዴሞክራሲ ከወለዳቸው የነጻነት ልጆች አንደኛው ነው ፡፡ በርግጥ እንደ ልጅና እንጀራ ልጅ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰልፎች መኖራቸው ይታወቃል ፡፡ እንደ ልጅ የሚቆጠረው የደገፈውም ሆነ የተቃወመው ሰልፋዊ ጥያቄ ይፈታለታል ወይም ባይፈታለት እንኳ በጥሞና ይደመጥለታል ፡፡ የእንጀራ ልጅ ዓይነቱ ግን ሶስት ዓይነት መንገድ የሚከተል ይመስላል ፡፡

. ትንሽ በሚራራ ወላጅ ያለው - ያለ ምንም አዳማጭ አደባባይ ተንጫጭቶ እንዲመጣ ይፈቀድለታል ፡፡
. በተረገመ ወላጅ ስር ያለው - ሰላማዊ ሰልፍ የሚሰማ እንጂ የሚነካ አይደለም እየተባለ ያድጋል ፡፡
. በብልጣ ብልጥ ወላጅ መዳፍ ስር ያለው - አባቱ ሲፈቅድና ደስ ሲለው ብቻ ለድጋፍ የሚወጣበት ምርጥ መሳሪያ መሆኑን ጸጉሩ እየተደባበሰ በተመስጦ ይነገረዋል ፣ ይማራል ፡፡

በዚህና በመሳሰሉ ስሌቶች የዓለማችን ህዝቦች ሰላማዊ ሰልፍ አከናውነዋል ፤ እያከናወኑም ይገኛሉ ፡፡ የሰልፎቹ መነሻም ሆነ የሚንጸባረቁበት መንገድ ጠንካራ ፣ ረጅም ግዜ የሚቆይ ፣ ልዩና ገራሚ እንዲሁም ለውጥ አምጪ ሊሆን ይችላል ፡፡ በዚህ ረገድ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአንዳንድ ሀገሮች የሚታየውን ተጠቃሽ ሰላማዊ ሰልፍ ገጽታ በስሱ እንቃኝ ፡፡

. ደቡብ አፍሪካ  - ከአፓርታይድ ትግል ወዲህ በዚች ሀገር የጠንካራ ሰላማዊ ሰልፍ ምንጮች የማዕድን ሰራተኞች ናቸው ፡፡ ጉልበታችን አላግባብ እየተበዘበዘ ስለሆነ የላባችን ውጤት ይከፈል በማለት ሞትን ያስከተለና መንግስትን ያጨናነቀ ሰልፍ አድርገዋል ፡፡

. ቻይና  - ገባ ወጣ ቢሆንም በዚች አፋኝ ሀገር የሰላማዊ ሰልፉ መሰረታዊ ጥያቄ ቅድመ ምርመራና አፈናን መቃወም ነው ፡፡

. ሶሪያ ፣ ቱኒዝያ ፣ ግብጽ ፣ ሊቢያ፣  አልጀሪያ ፣ ሞሮኮ ፣ የመን ፣ ባህሪን  - መንግስትና የሚከተለው ፓለቲካዊ ስርዓት ቤተሰባዊ እንጂ ህዝባዊ ጥቅም የሌለው በመሆኑ መንግስትም አሰራሩ ይቀየርልን በሚል በብዙ ሰልፍና ተቃውሞ ደክመዋል ፡፡ የተሳካላቸው እንዳሉ ሁሉ ገና በመንገድ ላይም ያሉ ብዙ ናቸው ፡፡

. አሜሪካ  - በተለይም ዋል ስትሬት በተባለው ተቃውሞ እኛ 90 ከመቶ ነን ያሉ ሰልፈኞች የድሃውን እኩል አኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ይረጋገጥ በሚል ሰፊ ድምጽ አሰምተዋል ፡፡

. ፍልስጤም  - አሷፊዎች ለተቃውሞና ሰልፍ የተፈጠሩ ይሏቸዋል - ተገራሚዎች የመብትና የነጻነት ታጋዮች ይሏቸዋል ፡፡ ሰው በጥይት ሲሞት ይሰለፋሉ፣ ሞት ለእስራኤልና አሜሪካ በማለት ባንዲራ ለማቃጠል ይሰባሰባሉ ፣ ለመሬትና ድንበር ጥያቄ ያልተሰለፉበትና ያልተጋጩበት ቀን ኢምንት ነው ፡፡

. ቤልጂየም  - የወተት ሽያጭ ዋጋ አሽቆለቀለ በማለት የአውሮፓን ገበሬዎች በሙሉ አስተባብረው የተቃውሞ ሰልፍ ያከናውናሉ ፡፡ በሰልፉ ላይ አንድ ሺህ የሚደርስ ትራክተር ሊያሰልፉ ይችላሉ ፡፡

. ስፔን  - ሀገሪቱ ከቅርብ ግዜ ወዲህ የገጠማትን የኢኮኖሚ መላሸቅ ተከትሎ በርካታ እንጀራ ነክ ኡኡታዎችን ብታስተናግድም እቺ ሀገር ለየት ባለ ሰልፍም ትታወቃለች ፡፡ ይኅውም እጅግ ተስፋፍቶ የሚታየውን የ ‹ ቡል ፋይት › ከእንስሳት መብት አንጻር በመቃወም ሴቶች ራቁታቸውን አስፓልት ላይ የመተኛታቸው ጉዳይ ነው ፡፡

. ህንድ  - በሀገሪቱ ፍጹም እየተስፋፋ የሚገኘው የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ይቁም ! አጥፊዎች አስተማሪ ቅጣት ይሰጣቸው  ! በሚል በየግዜው ታላላቅ ሰልፎች ይደረጋሉ ፡፡

ሩሲያ  - የሩሲያ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ትልቁ ጥያቄ ልክ እንደ ጣሊያናዊው ቤርለስኮኒ / Basta Berlusconi እንደተባሉት / የፑቲንም ስርዓት ማብቂያ ይበጅለት ፣ የመንግስት ስርዓት እንደፈለጉ የሚገቡበትና የሚወጡበት የግል ቤት አያድርጉት ! ፍትህ ይስፈን ! የሚል ነው ፡፡ የፑሲ ተቃውሞ / pussy Riot / በሚል አዲስና ልዩ ስልት ሴቶች ብልታቸውን በዘግናናኝ መልኩ ቆልፈው በየአደባባዩና ቤተ እምነት ሳይቀር የተቃወሙበት ሂደት ነው ፡፡

. ቺሊ - ልጆቻችን ጥራት ያለው ትምህርት እያገኙ አይደለም በሚል ጥንዶች ተቃውሞያዊ ሰልፋቸውን ያቀርባሉ ፡፡ በምን መንገድ ከተባለ ግን በመሳሳም ይሆናል ምላሹ ፡፡

. ኢትዮጽያ  - ኢትዮጽያኖች ሁልግዜም ጠዋትና ማታ ትላልቅና በሰው የተጨናነቀ ሰላማዊ ሰልፍ ያደርጋሉ ፡፡ ሰልፋቸው መስቀል አደባባይን ንቆ በየሰፈሩ ሆኗል ፡፡ የሰላማዊ ሰልፉ ምክንያት ታክሲ አጣን ፣ በትራንሰፖርት እጦትና ኢ ፍትሃዊ ታሪፍ ተንገላተን  በማለት አይደለም - በቃ ታክሲ ጥበቃ ነው ፡፡

Sunday, April 7, 2013

‎የወላጅ አልባ አንበሶች ያልተነገረ ታሪክ‎


ስለ ወላጅ አልባ ህጻናት እንጂ ስለ ወላጅ አልባ እንስሳት ብዙዎች ብዙ እንዳልሰሙ ግልጽ ነው ፡፡ ብይኑ እነዚህን እንስሳት ወላጅ የሌላቸው እንስሳት ሆነው ራሳቸውን ማስተዳደር የማይችሉ ይላቸዋል ፡፡ ለሀገራችን ወላጅ አልባ ህጻናት መፈረጃ ትልቁ ምክንያት ድህነትና ኤችአይቪውን ጥቂት ከጎናቸው በማራቅ በምትኩ በሽታን ይወስዳሉ ፡፡ በመኪናና በተፈጥሮ አደጋ በተለይም ደግሞ በአዳኞች ርጉም ጥይት መሞት አብይ መንስኤያቸው ሆኗል ፡፡

ትልቅ ሆነው ፍርሃት ከሚያነግሱ እንስሳት አንበሳን በዋናነት መጥቀስ እንችላለን ፡፡ ይህ የስልጣን ፣ የኃይል ፣ የድፍረትና የዝና ምልክት የሆነው እንስሳም ክፉ ቀን ከመጣበት ወላጅ አልባ መጠለያ ውስጥ ፊቱን ጥሎ ሊታይ ይችላል ፡፡ መቼም እነ ጎሽ ፣ የሜዳ አህያ ፣ ሚዳቆ ፣ አጋዘን የመሳሰሉት በአጋጣሚ በሽቦ አጥር የተከለለ መጠለያ ውስጥ ቢያዩት መቶ ፐርሰንት ተስማምቶም ሆነ ተገዶ እዚህ መገኘቱን አያምኑም ፡፡

‹ ወይ ጋሽ አንበሶ ? እንዲህ ዓይነት ማዘናጊያ ጀመረ ደግሞ ! › ልትል ትችላለች ሚዳቆ
‹ ቆይ ግን ምን ለማለት ነው ? በመላመድ ከሌሎች ጋ በሰላም መኖርም እችላለሁ እያለን ነው ? › አጋዘን እየበሸቀ መናገሩ ይጠበቃል ፡፡
‹ ሌባ በለው አጭበርባሪ ! › ከጎሽ ኃይለ ቃል አይጠፋም ፡፡

ሌሎቹም ቢሆኑ በጣም እየፈሩና እይተጠነቀቁም ቢሆን የበዛ ስልቂያ እንደሚያሰሙ አያጠራጥርም ፡፡ ምክንያቱም የደኑ ንጉስ ከፈለገ አጥሩን በጣጥሶ አሊያም ብዙም ሳይንደረደር ከለላውን እንደሚዘላት ይገባቸዋልና ፡፡ እንኳን እነሱ ‹ ከኔ በላይ ላሳር › የሚለው የሰው ልጅ ከእሱ በላይ መኖሩን የሚያስመሰክር ዘፈን ዘወትር እንደሚከተለው እንደሚያሰማ የወሬ ወሬ ሰምተዋል ፡፡

          ‹‹ አንበሳው አንበሳው አንበሳው ልጅሽ
                              ይኅው መጣልሽ !!! ››

ይህን የሚዘምረው በጣባብ የጎል ልዩነት ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈ ብሄራዊ ቡድን ብቻ አይደለም ፡፡ ይህን የሚዘምረው ወገቡ በዝናር ጥይትና በእጅ ቦንብ ፤ እጁ አውቶማቲክ ጠመንጃና ጸረ ታንክ የተሸከመ ስልጡን ወታደር ጭምር እንጂ ፡፡ ዓለምን የሚያደባይ መሳሪያ የጨበጠ ሰው እንኳ ከመሳሪያው ይልቅ ለአንበሳ ትልቅ ክብር እንደሚሰጥ ይረዳሉ ፡፡
ታዲያ የነጎሽና አጋዘን መላምት እንዴት ትክክል ላይሆን ይችላል ? እረ ለቁጥር የሚታክቱ ማሳያዋችና ማስረጃዋችንም አንድ ሁለት እያሉ መዘርዘር አይከብድም ፡፡ ምን ዘፈን ፣ ሙገሳና ቀረርቶ ብቻ ?

ማነው የአንበሳው ክፍለጦር እያለ ስያሜ የሚሰጠው ?
አንበሳ ግቢ ?
አንበሳ አውቶብስ ?
አንበሳ ጫማ ?
አንበሳ ባንክ ?
አንበሳ ኢንሹራንስ ?
ጥቁር አንበሳ ?
አቶ አንበሴ ?

የአውጉስታ ሸሚዝ ፋብሪካ ምልክት የሆነው የሜዳ አህያም ሆነ የፈጣንና ዘመናዊ መኪናዋች ምስል የሆነው አቦሸማኔ አንበሳ በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጽያ የብዙ ነገሮች ምልክት መሆኑን የሚያውቁት ገና ጥርስ ከማውጣታቸው በፊት ነው ፡፡
አንበሳ በቀድሞዎቹ የኢትዮጽያ ባንዲራ ላይ
በአሁኑ ፍራንክ ላይ
በቀድሞ ጽሁፎች ላይ
በኢትዮጽያ ንግድ መርከብ
በቀድሞው አየር መንገድ
በኢትዮጽያ መንገዶች ባለስልጣን
በቴሌኮሙኒኬሽን

ባልጠቀስናቸው መ/ቤቶች እንደ ሎጎ አገልግሏል ፤ ዛሬም በገሃድ እያገለገለ ይገኛል ፡፡ በሚንሊክ ዘመነ መንግስት መስቀል በእግሩ የያዘና ዘውድ የደፋ አንበሳ ባንዲራ ላይ ይታይ ነበር ፡፡ ይህ ምልክት በንጉስ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስትም ሰርቷል ፡፡ የይሁዳ አንበሳ ይሉታል ፡፡ ደርግ ስልጣን ሲይዝ አናቱ ላይ የደፋውን ዘውድ በሞርታር ጥይት አሽቀንጥሮ በዚያው ይቀጥላል ቢባልም አንበሳው የያዘው መስቀልና እሱ የሚከተለው ርዕዮት ሊዛመድለት አልቻለም ፡፡ በአጠቃላይ ‹ አንበሳ አያስፈልገኝም › በማለት ገፈተረው ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ግን አንበሳው ክፍለጦርን አቋቁሞ አንበሳውን ደጋግሞ ማሞገስ ተያያዘ ፡፡

አንበሳ ከዚህም በላይ ሊወራለት እንደሚችል ይታወቃል ፡፡ ከዚህ አንጻር አንበሳ በወላጅ አልባ እንስሳት ስም መጠለያ ገባ የሚለው ዜና የማይመስል ሊመስል ቢችል አያስገርምም ፡፡ ወይም የማይታወቅ ፡፡

ከአዲስ አበባ በ25 ኪሎ ሜትር ርቀት ማለትም ሆለታ አካባቢ የሚገኘው የእንስሳት መጠለያ ግን የስድስት አንበሶች ልዩ ታሪክ ይዟል ፡፡ ቦርን ፍሪ በሰዎች ተይዘው የሚሰቃዩ እንስሳትን ተግባር በማስቀደም ከችግር የሚላቀቁበትንና እንክብካቤ የሚያገኙበትን ሁኔታ የሚያመቻች አለማቀፍ ድርጅት ነው ፡፡ የዚህ ድርጅት የኢትዮጽያ ተጠሪ ሆለታ አካባቢ የሚገኘውን መጠለያ ‹‹ የእንስሳት ኮቴ ›› የሚል ስያሜ በመስጠት በሀገራችን የመጀመሪያውን የዱር እንስሳት ጥበቃ ፣ ልማትና ትምህርት ማዕከል በመሆን እየሰራ ይገኛል ፡፡

ግቢው 77 ሄክታር መሬት የሚያካልል ሲሆን በደን የተሸፈነ ነው ፡፡ በቀጣዮቹ አንቀጾች ከምንገልጻቸው ጥንድ - ጥንድ አንበሶች በተጨማሪ አቦሸማኔ ፣ ጉጉት ፣ ጦጣ ፣ ኤሊ ፣ ተራውና በሀገራችን ብቻ የሚገኘው ዝንጀሮዋችም ይገኙበታል ፡፡

ዶሎና ሶፍያ

ዶሎና ሶፍያ

ዶሎ የተባለው አንበሳ አንድ ሜትር ርዝመት ባለው ሰንሰለት በደቡብ ኢትዮጽያ በሶማሌ ድንበር አካባቢ በአንድ ሰው እጅ ነበር ፡፡ ይህ ሰው ለአራት ዓመታት ያህል በፍልጥ እንጨት በተሰራ ጠባብ ክፍል ውስጥ እንዲኖር አስገድዶታል ፡፡ የአካባቢው ሰዎች እንዳስረዱት አንበሳው ብቸኛ በመሆኑና አያያዙም ጥሩ ስላልነበር ዘወትር ጠዋት የሚያሰማው የሰቆቃ ጩኀት በከተማው ሙሉ  ይሰማ ነበር፡፡

ሰቆቃወ ወ ዶሎ ከአዛማጅ ትርጉም አንጻር እንደሚከተለው የሚገለጽ መስሎኛል . . .

‹ እረ የአንበሳ ያለህ ?! እረ የእንስሳት ያለህ ?! ዛሬስ ጠረናችሁ ናፈቀኝ !! ›
‹ አይ እናቴ ! ነጻ በሆነው ጫካ ተወልደሃል የምትይው መዝሙር እንዴት ተቀይሮ ከባርነት ጫማ ስር ተገኘሁ ?! ›
‹ እረ የነጻነት ያለህ ?! እረ የፍትህ ያለህ ?! በምን ጥፋቴ ነው ሰንሰለት የሚበላኝ ?! በምን ተፈጥሮ ነው በሰው ልጅ የምዳኝ ?! ›
ይህ ሁኔታ ብዙዎችን ስላሳሰበ ጉዳዩን ለሚመለከተው ክፍል አሳወቁ ፡፡

ዶሎ በዱር እንስሳትና በቦርን ፍሪ ትብብር መጀመሪያ የተወሰደው ወደ አዋሽ ብሄራዊ ፓርክ ነበር ፡፡ እዚያ የተሻለ እንክብካቤ አግኝቷል ፡፡ አንበሳ ያልነበረው የእንስሳት ኮቴ ዶሎን የመጀመሪያ እንግዳ አድርጎ ለመቀበል ብዙ ጥረት አድርጓል ፡፡ ደረጃውን የጠበቀ ግቢ ለመስራት ፣ የተሻለ ምግብ በቀጣይነት ለማቅረብና  ህክምናውን ለመከታተል የሚያስችሉ ዝግጅቶች ከተከናወኑ በኃላ ጉዞ ወደ ሆለታ ሆነ ፡፡ ዶሎን ለማጓጓዝ ሰባት ሰዓታትን ማሳለፍም ግድ ብሏል ፡፡

ዶሎ አሳድገዋለሁ ባለው ሰው እጅ እያለ ምን እንደሆነ ባይታወቅም አይኖቹ ተጎድተዋል ፡፡ ሩቅ የማየት ችግር እንዳለበትም ተረጋግጧል ፡፡ ሀኪሞች በልጅነቱ በምግብ እጥረት በመጎዳቱ ለአይን በሽታ ሳይጋለጥ አይቀርም የሚል ሀሳብ አላቸው ፡፡ በሰንሰለቱ ምክንያትም ግርማ ሞገስ ሊፈጥርለት የሚገባው የጋማው ጸጉር ሊረግፍ ችሏል ፡፡

ዶሎ በሰፊው ግቢ፣ በምግቡና በተፈጠረለት አንጻራዊ ነጻነት ቢረካም ‹  አንድ ውሃ አጣጪ ባገኝ ምን አለበት ? › እያለ እንደሚያስብ ይገመታል ፡፡ የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖ ኡደት በተባለ ቦታ የሚገኙ ልጆች ሴት አንበሳ ይዘው በአነስተኛ እንጨት ውስጥ መቀመጧ ሪፓርት ይደረጋል ፡፡ አንበሳዋ ስትገኝ እድሜዋ ገና ሰባት ወር ብቻ ነበር ፡፡ እናትየው ልጆቿ ወንዶች ከሆኑ ትልቁ አንበሳ በመቅናትና የነገ ባላንጣዬ ነው በማለት እንደሚገድላቸው ስለምታውቅ ከአጠገቧ እንዲርቁ አታደርግም ፡፡ አንበሶች ልጃቸውን ለመንከባከብ ግድ የማይኖራቸው የምግብ ችግር ባለበት ግዜ ነው ፡፡ ምናልባትም በኃላ ላይ ‹‹ ሶፍያ ›› የሚል ስም የተሰጣት አንበሳ በህጻናቱ እጅ የወደቀችው ይህን በመሰለ ችግር ሊሆን ይችላል ፡፡

ዞሮ ዞሮ ዶሎ ከሶፍያ ጋር መጣመር መቻሉን እንደ ሁለተኛ ዕድልም ድልም ነው የሚመለከተው ፡፡ የመጀመሪያው ሰንሰለቱን የማስቆረጡ ተግባር ነው ፡፡ ሰንሰለት በውሻ እንጂ በአንበሳ አንገት ላይ ቦታው አይደለምና ፡፡ ሁለተኛው ዕድል / ድል በረዶ የሰራበትን ብቸኝነት ብቻ ሳይሆን እንደ አለት የጠጠረውን የፍቅር ጥያቄ ቀስ በቀስ እያቀለጠች ምላሽ ልትሰጥ የምትችል ተቃራኒ ጾታ የማግኘቱ ሚስጢር ነው ፡፡ በርግጥ ጾታዊ ግንኙነቱ ‹ ብዙ ተባዙ ! › እስከማለት የሚያደርስ አይደለም ፡፡ ምክንያቱም የግቢው ህግ የተጎዱ እንስሳትን ለመንከባከብ እንጂ ለማራባት የሚፈቅድ አይደለምና ፡፡ ለምን ከተባለ የዱር እንስሳትን በተወሰነ አጥር ውስጥ ከልሎ ማራባት ከተፈጥሯዊ የኑሮ ዘይቤያቸው አንጻር ስለማይቻል ፡፡ አደኑ ፣ መሯሯጡ ፣ ምግብ ፍለጋው ፣ መደበቂያው ፣ መራቢያው እና ሌላውንም ጉዳይ የሽቦው ቤታቸው አይመልስምና ፡፡ በዚያ ላይ የተራቡትን ሁሉ ለማሳደግ የኢኮኖሚ አቅም አይፈቅድም ፡፡ ይህን ሳይንሳዊ የተባለ የሰው ልጅ ምክንያት እነ አንበሶ አይቀበሉትም ፡፡ አንዳንዶች ስለ ሙሉ ነጻነት ነው የሚያስቡት ፤ ሰዎች ደግሞ እነዚህ አንበሶች ወደ ጫካው ቢለቀቁ የመገለልና የመጠቃት ዕጣ ስለሚያጋጥማቸው ጉዳቱ ይብስባቸዋል ነው የሚሉት ፡፡ አንበሶቹ ግን የፈለገ ቢሆን ማን እንደ ቤት … ማን እንደ ዘር ባይ ናቸው ፡፡ አንዳንዶቹ ተቃውሟቸውን በጩኃት ይገልጻሉ ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ የማንዴላን መጽሀፍ ያነበቡ ይመስል ‹‹ LONG ROAR TO FREEDOM ›› የሚል ድርሰት ለመጻፍ በዝምታ ያደፈጡ ይመስላል ፡፡

ሜጀርና ጄኔራል


ሜጀርና ጄኔራል

በወታደራዊ አጠራር ሜጀር ጄኔራል ትልቅ ስልጣን ነው ፡፡ በሀረር የሚገኝ አንድ የጦር ካምፕ ለ13 አመታት ሲያሳድጋቸው ለቆየው ሁለት አንበሶች ወታደራዊ መጠሪያ ለመስጠት ባያመነታም ትልቁን ወታደራዊ ማዕረግ ለሁለት መሰንጠቁ ግን ግራ አጋቢ መስሏል ፡፡ አንዱን ሜጀር ሌላውን ጄኔራል በማለት ፡፡

እነዚህን ጀርባ ጥቁር አንበሶች የተመለከተ በግርማ ሞገሳቸው ይማረካል ፡፡ ከነዶሎና ሶፍያ ግቢ በተወሰነ ርቀት ላይ በሌላ የሽቦ አፓርታማ ውስጥ ነው የሚኖሩት ፡፡ በርግጥም እንደ ወንድማማችነታቸው ተሳስበው በሰላም የሚኖሩ ይመስላሉ ፡፡ አልፎ አልፎ ግን ከአንዱ ጥግ ወደ ሌላው እየተንጎማለሉ የሚያሰሙት ልዩና አሳዛኝ ድምጽ አላቸው ፡፡ ባለሙያዎቹ የተለመደና ተፈጥሯዊ ጉዳይ ነው ቢሉም እኔ ግን ምናልባትም ስለ ሶፍያ የሚያሰሙት የፍቅር መወድስ ሊሆን ይችላል ባይ ነኝ ፡፡ የአንበሳ የፍቅር ዘለቄታነት እስከመጨረሻው ቢሆንም ሴት እጅግ ብርቅ በሆነበት በዚህ ጫካ መንግስት እንደሚለው ወጪን ብቻ ሳይሆን ሁሉን ነገር ተጋርቶ መኖር እንደ ስርዓት አልበኝነት አያስቆጥርም ፡፡ እናም ዶሎ ቢከፋው እንኳ … ሜጀርና ጄኔራል እንደሚከተለው  እያሉ መስሎኛል …

                  ኦ ! ሶፍያ . . .
                  መች ይሆን የፍቅርሽ ገበያ
                  የሚውለው ከጠረንሽ አልፎ
                  ልፍያና ጉንተላን አሰልፎ
                  ከኛም ግቢ … ከኛ መንደር
                  የሚወደስ  … የሚከበር
                  ኦ ! ሶፍያ . . .
                  ከለለን አጥሩ
                  አነቀን ድንበሩ
                  እንዲህ ነበር እንዴ ወጉ ?!
                  የባህል ልምዳችን ማእረጉ
                  ታዲያ መች ይጸድቃል ቀኑ ?
                  ‹ ፓሪ › መጨፈሪያችን ‹ ዩኒየኑ ›
                   ኦ ! ሶፍያ . . .                           

የዛሬን አያድርገው እንጂ ወንድማማቾቹ የተፈጠሩት ሶስት ሆነው ነበር ፡፡ በአንድ ክፉ ቀን ሶስት የአንበሳ ግልገሎች በባሌ አካባቢ በወታደሮች ተገኙ ፡፡ ወይም በወታደራዊ ቋንቋ ተማረኩ ፡፡ የግልገሎቹ ወላጆች የት ጥለዋቸው እንደሄዱ ፣ ወይም ምን እንደሆኑ አይታወቅም ፡፡ አንደኛዋ ግልገል ሴት ነበረች ፡፡ ይሁን እንጂ ማራኪዎቹ ወደ ካምፓቸው ባደረጉት ጉዞ ሴቷ በፋቲክ ለባሾች እጅ ከመውደቅ በሚል ነው መሰለኝ ከመኪና በመዝለሏ ወዲያው ሞተች ፡፡ ሁለቱ ወንድማማቾች ከመሞት መሰንበትን መርጠው ካምፕ ውስጥ በአነስተኛ መጠለያ ለመቀመጥ በቁ ፡፡

ግልገሎቹ እያደጉ ሲመጡ ማራኪዋቻቸው የየዕለት ተግባራቸውን መቆጣጠር አልቻሉም ፡፡ በመሆኑም የዱር እንስሳት ባለስልጣን እንዲታደጋቸው ጥሪ አቀረቡ ፡፡  ቦርን ፍሪ በበኩሉ የአንበሶቹን መኖሪያ በመገንባት የሶስት ወራት ግዜ ወሰደ ፡፡ ትላልቆችን አንበሶች በትልቅ የጭነት መኪና የእንስሳት ኮቴ ግቢ ለማድረስ 16 ሰዓታት መንዳት አስፈልጓል ፡፡ ዛሬ የሜጀርና ጄኔራልነት ተክለ ሰውነት ብቻ ሳይሆን ስለ ፍቅር ፣ ወንድማማችነትና ስለ ህይወት የሚያቀነቅኑትን ፉከራዎችንና አርምሞዎችን መስማት የሆነ ስሜት ይፈጥራል ፡፡

አንድሪያና ጃኑ


አንድሪያና ጃኑ

ስማቸው እንደሚጠቁመው እነዚህ ሁለት አንበሶች ዜግነታቸው ከጣሊያን ነው ፡፡ አስተዳደጋቸው ደግሞ ኢትዮጽያ ፡፡ አንበሶቹ በሆነ ወቅት አነጋጋሪ ጉዳይ መፍጠር ችለው ነበር ፡፡

ነገሩ እንዲህ ነው ፡፡

እአአ በ2006 ሁለቱ ቤተሰብ አልባ ግልገል አንበሶች ጣሊያን ኤምባሲ ውስጥ ተገኙ ፡፡ የመጡት የአንድ ልዑክ ቡድን ምክትል ኃላፊ በሆኑ ሰውና ሚስታቸው አማካኝነት ነበር ፡፡

ሁለቱ ወንድማማች አንበሶች እያደጉ ሲመጡ ጣሊያኖቹ አንበሶቹ ማግኘት ስለሚገባቸው ትክክለኛ ቤትና የወደፊት ዕጣ ፈንታ በተመለከተ ቦርን ፍሪን ማነጋገር ጀመሩ ፡፡ አንደኛው ሀሳብ አንበሶቹ ወደተወለዱበት ጣሊያን መመለስ ይኖርባቸዋል የሚል ነበር ፡፡ጣሊያን መቼም የራሷን ንብረት አይደለም የወረረችውንም ሀገር ሃውልት ሳይቀር ተሸክማ ሄዳለች ፡፡ በነገራችን ላይ ወራሪዎች የከበሩ ማዕድናትንና ውድ ቅርሶችን በመዝረፍ አልሆን ካላቸውም አውድመው በመሄድ ይታወቃሉ ፡፡ ጣሊያን ግን ያን ትልቅ ሃውልት ስንት ባህር አቋርጣ ተሸክማ መሄድዋ ይገርመኛል ፡፡ እንደውም አንዳንዴ እኛ በተረት የምናውቀው አህያ ተሸክሞ የሚሄደውን ማሞ ቂሎ ሁሉ የሆነች ይመስለኛል ፡፡ እያደር ግን ድንጋይና ኃውልት ላይ ሃይለኛ ፍቅር እንዳላቸው ተገንዝቤያለሁ ፡፡

መቼም ፍትሃዊ ህዝብና መንግስት ሀገር ላወገዘው ወንጀለኛ / ግራዚያኒ / የጀግና ሃውልት ያቆማል ተብሎ አይታሰብም - ልክ ብልጥ መንግስት የሰማይ ስባሪ የሚያህል ሃውልት ተሸክሞ እንደማይሄደው ሁሉ ፡፡ ጣሊያን ግን ከነዚህ እውነት ጀርባ በኩራት ቆማለች ፡፡ እናም አንበሶቻችን ይመለሱ ብለው መጠየቃቸው የኃላ ታሪካቸውን ለሚያውቅ አያስገርምም ፡፡

የኢትዮጽያ መንግስት ግን ከብዙ ሁኔታዎች አንጻር ይህን ሀሳብ ለመቀበል ተቸገረ ፡፡ ይሄኔ ቦርን ፍሪ ከፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ መነጋገር ጀመረ ፡፡ ይህ ውይይትም ትውልደ ጣሊያን አንበሶቹ ለግዜው በፕሬዝዳንቱ ቤ/መንግስት ይቀመጡ የሚል ውሳኔ ሀሳብ እንዲመነጭ አስቻለ ፡፡

ቤተ መንግስቱ ግን የተሻለና የመጨረሻ አማራጭ ባለመሆኑ ዘለቄታዊ ማረፊያ ወደሆነው የእንስሳት ኮቴ በህዳር 2011 እንዲጓዙ ተደረገ ፡፡

አንድርያና ጃኑ እንደ ሜጀርና ጄኔራል የመቅበጥበጥም ሆነ እረ ጎራው የማለት ባህሪ አይታይባቸውም ፡፡ ምናልባት እንደ ጌቶቻቸው አድፋጭነት ተጋብቶባቸው ይሆናል ፡፡ ምናልባት ጸብ አጫሪነት ፋይዳ ቢስ መሆኑን በመረዳት በነጭ ባንዲራ ስር ለመኖር ቆርጠው ይሆናል ፡፡ ምናልባትም መወለድ ቋንቋ ነው እንዲሉ ላደጉበት ሀገር ሰላምና ፍቅር በመመኘት ቋሚ ‹ አርምሞ › ውስጥ ገብተው ይሆናል ፡፡ ምናልባትም በቅርቡ  ይፋ የሆነውን ሰበር ዜና አስቀድመው ስለሚያውቁት በራስ የመተማመን ስሜታቸው ተሰብሮ ይሆናል ፡፡

የቅርቡ ዜና  የኢትዮጽያ አንበሶች ዝርያ ከመላው አፍሪካ አንበሶች ይለያል የሚል ነው ፡፡ ከ 20 አንበሶች ውስጥ የዲ ኤን ኤ ምርመራ የተደረገላቸው 15ቱ ልዩነት ማሳየታቸው ታውቋል ፡፡ ይህ ማለት እንግዲህ አንበሳ ‹ አንበሳ › ከሚለው አስፈሪና ሞገሳም ዝናው በተጨማሪ ‹‹ በኢትዮጽያ ብቻ የሚገኝ ! ›› የሚለው ማዕረግ በሰዎች ክብር ሊጨመርለት ነው ማለት ነው ፡፡ ለነገሩ ነገሩ ቀድሞ የተገለጠላቸው የሚመስሉት አንዳንድ የሀገራችን መሪዎች ለአንበሳ የሚገርም ፍቅርና አክብሮት ነበራቸው ፡፡ አጼ ቴዎድሮስ መቅደላ ተራራ ላይ በአንበሳ ተከበው ይውሉ ነበር ፡፡ ንጉስ ሃይለስላሴ አንበሳ እያረቡ መሳጭ ወዳጅነት መፍጠር ችለዋል ፡፡ የሀገራችን አርበኞች በህቡዕ ሲደራጁ ስማቸውን  ‹ የጥቁር አንበሳ አርበኞች እንቅስቃሴ › ማለት ነው የወደዱት ፡፡ አንበሳ ብቻ አይደለም - ጥቁር አንበሳ ፡፡  አንበሳ ወደ ዳለቻና ቡኒ ቀለም መጠጋቱ እየታወቀ በሀገራችን ብዙ ነገሮች ‹ ጥቁር አንበሳ › የሚል ስያሜ እንዴት ሊያገኙ ቻሉ ? የሚሉትን ጥያቄዎች ጆሮውን መጠምዘዝ ከተፈቀደ ቀደም ያሉትን አባቶቻችንን ምናባዊ ዕውቀት ልናድቅ ግድ ይለናል ፡፡ የመገለጥ ብቃት ፡፡

ርዕሰ ዜናውን አንድ ግዜ ላስታውስና ልቀጥል ፡፡ ይህ ማለት እንግዲህ አንበሳ ‹ አንበሳ › ከሚለው አስፈሪና ሞገሳም ዝናው በተጨማሪ ‹‹ በኢትዮጽያ ብቻ የሚገኝ ! ›› የሚለው ማዕረግ በሰዎች ክብር ሊጨመርለት ነው ማለት ነው ፡፡ በሌላ አነጋገር ዶሎ ፣ ሶፍያ ፣ ሜጀርና ጄኔራል እንደ ሳሞራ የኑስ ብቸኛውን ማዕረግ ትከሻቸው ላይ ሊጭኑ ነው  - ሙሉ ጄኔራል ወይም ልዩና ብርቅዬ አንበሳ ፡፡ አንድርያና ጃኑ ደግሞ ባለ ሌላ ማዕረግተኛ  - ወይም ተራው አንበሳ ፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጽያዊ ደም ስለሌላቸው ሳይንሳዊው እርከን አይመለከታቸውም ፡፡ ይህ ኮምፕሌክስ በጫካው ሰፈር አይኖርም ለማለት ማረጋገጫ አይኖርም ፡፡ 
ተመራማሪዋቹ በነካ እጃቸው ይህ ኮምፕሌክስ እየቆየ ሲሄድ ‹ አንበሳዊ ፍርሃት › ይፈጥራል የሚል ጥናት ያሰሙን ይሆናል ፡፡

ለማንኛውም  ተሷሚዎቹንም ሆነ ባለ ሌላ ማዕረግተኞቹን  ወላጅ አልባ አንበሶች በእንሰሳት ኮቴ ተገኝቶ መጎብኘት ስለሚቻል አንድ እሁድ ጎራ ብለው ይዝናኑ ፡፡

ማስታወሻ፡ይህ ፅሑፍ በቁም ነገር መፅሔት ቅፅ 12 ቁጥር 149 ላይ የወጣ ፅሑፍ ነው፡፡ ፅሑፉን በሌላ ሚዲያ ላይ የምትጠቀሙ ከሆነ ምንጩን እንድትጠቅሱ ትለመናላችሁ፡፡ 

Wednesday, April 3, 2013

ፓራdox







ኮሌጅ ገብተው ስነ ጽሁፍ የሚማሩ ተማሪዎች ለ ‹‹ PARADOX ›› ‹‹ አያዎ ›› የሚል ትርጉም ይሰጡታል ፡፡ ‹ አይ › እና ‹ አዎ › እንደማለት ፡፡ መዝገበ ቃላታችን ደግሞ እንደወረደ ‹‹ ርስ በርሱ የሚጋጭ ›› በማለት ይበይነዋል ፡፡

የስነ ጽሁፍ ጉዳይ በእግረ መንገዱ ከተነሳ የሶስት ምርጥ ደራሲያንን ‹‹ አያዎ ›› ሀረጎች ማስታወስ ለርዕሰ ጉዳያችን ቅመምነት ሳይጠቅም አይቀርም ፡፡ አየርላንዳዊ ጸሀፊና ገጣሚ ኦስካር ዋይልድ ‹‹ I can resist anything but temptation ›› የሚላት ነገር አለችው  ፡፡ ዊሊያም ሼክስፒር በሃምሌት ላይ ‹‹ Be cruel to be kind ›› ሲል እናገኘዋለን ፡፡ ጆርጅ ኦርዌል በአኒማል ፋርም ላይ ‹‹ All animals are equal, but some are more equal than others ›› ሲል ይቀኛል ፡፡

የሶስቱንም ታዋቂ ብዕረኞች አባባል ስንመረምር ጥልቅ ትርጉም የያዙ መሆናቸውን እንረዳለን ፡፡ ሶስቱም ብዕረኞች በአሽሟጣጭና ግራ ገብ በሆነ ስራዎቻቸው የተጠቃና የቆሰለ አንጀትን በቅቤ ለማራስ የገዘፈ አቅም አላቸው ፡፡

ጥናት ቢያስፈልገውም ‹ paradox › በድሃና የሶሻሊዝምን ስርዓት በሚከተሉ ሀገሮች / ምስኪን ህዝቦች / ይበልጥ የሚበዛ ይመስለኛል ፡፡ በኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ ደግሞ ፓራዶክስ ‹‹ በየዓይነቱ ›› እንደማለት ነው ፡፡ በውዴታ ግዴታችን የምንመርጠው ፡፡

ወጋችንን  በአንድ ሁለት ቆጠራ ለማሳመር  ወደ ጉሮሮ የሚወረወር ነገር እንያዝ ፡፡ ብሂሉም ነገር በምሳሌ ጠጅ በብርሌ አይደል የሚለው ፡፡

አንድ  .

በቅርቡ በሚከናወነው የወረዳና የክልል ምክር ቤቶች ምርጫ በርካታ ተቃዋሚ ድርጅቶች ‹‹ የምርጫ ቦርድና ኢህአዴግ አሰራር አልተመቸንም ›› በሚል ምክንያት ለራሳቸው ቀይ ካርድ አሳይተዋል ፡፡ ምርጫ ቦርድ በየሰፈሩ ግድግዳ ላይ የለጠፈው የተወዳዳሪዎች ስምም የሚጠቁመው  ከ90 እስከ 95 ፐርሰንት የሚሸፍኑት ዕጩዎች የተገኙት በኢህአዴግ አቅራቢነት ነው ፡፡ 

በኢህአዴግ በኩል የሚታየው የምረጡኝ ቅስቀሳ መጠን ሰማይ ጥግ መድረሱ ግን ሳያስገርም አይቀርም ፡፡
መቼም እንደ ዘንድሮ  በተወዳዳሪዎች ማነስ በእጅጉ ኮስምኖና ገርጥቶ የታየ ምርጫ መኖሩ ያጠራጥራል ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በምርጫ ቦርድና ኢህአዴግ መልካም ፍቃድ እንደ ዘንድሮ ምርጫ ለተቃዋሚ ድርጅቶች መቀስቀሻ የሚውል ሰፊ የአየርና የህትመት ግዜ ተሰጥቶ አያውቅም ፡፡ 50 ከመቶ ፡፡ ይህን ቁጥር የሰሙ የተወሰኑ ተቃዋሚዎችም ቋንቋ እየቀያየሩ ‹ አስገራሚ ነው › ‹ fair ነው › ሁሉ ብለውታል ፡፡

ሁለት .

ህንጻና መንገድ እያበዛች የምትገኘው አዲስ አበባ አስጸያፊ ቆሻሻዋንም እንደ ኩይሳ ከመቆለል ወደ ኃላ አላለችም ፡፡ በአዲስ አበባ መንደሮች ውስጥ ስታልፉ ለቆሻሻ ማስወገጃ የተሰሩት ፍሳሾች የሚሰቀጥጥ ክርፋት ይመግቧችኃል ፡፡ በየሰፈሩና አስፋልት ዳር የተሰየሙት ገንዳዎች እንደ ከተማው ታክሲዎች ከጭነት በላይ የሚሸከሙ በመሆናቸው የቅርናታቸው ከበሮ ከሩቅ ለአፍንጫ ይሰማል ፡፡ 

አይነምድሩ ፣ አተላውና የፋብሪካው ተረፈ ምርት ምንም ሳይሳቀቅ ወደ ተገኘው ወንዝ በዝግታ እየገማ ሲቀላቀል ይመለከታሉ ፡፡ ህግ የለም እንጂ ህግ አስከባሪ ‹‹ እጅ ወደላይ ! ›› ብሎ ቢጠይቃቸው ከጤና ቢሮና ከአካባቢ ጥበቃ የተሰጣቸውን ፍቃዶች በኩራት የሚያሳዩ ነው የሚመስሉት ፡፡

የከተማችን ቆሻሻ ፣ ግማትና ክርፋት የጥጋቡ ጥጋብ ጨረቃ ቤት ሰርቶ ያለምንም ፍርሃት እየኖረ የሚገኘው በማዘጋጃ አጥር ዙሪያ በሙሉ መሆኑ ነው ፡፡ ግቢያቸውን እንኳ ማጽዳት ያልቻሉት የከተማው አስተዳደሮች በየዕለቱ ስለ ሩቁ ይሰብካሉ ፡፡ ጽዳትና ውበት ፣ ደረቅና ፍሳሽ ፣ ጸረ ቆሻሻ ማህበራት ወዘተ በማለት ሪፖርት ላይ ይደንሳሉ ፡፡

እንግዲህ እያኖረችን የምትገኘውና ከ ሀ እስከ ፐ የምናውቃት አዲስ አበባ ይቺ ናት ፡፡ አንድ  ቡድን ግን በ 2013 ሊጎበኙ ከሚገባቸው አስር ምርጥ ከተሞች አንዷ አዲስ አበባ ናት በማለት ገራሚ ወሬ አሰማን ፡፡ ለ ‹ ቀባሪው አረዱት › ን ከጠቀሱ ላይቀር በዚህ መልኩ ነው ፡፡


ሶስት  .

የሳኡዲ አረቢያ ምክትል መከላከያ ሚ/ር የሆኑት ካሊድ ቢን ሱልጣን በሶስተኛው የአረብ ውሃ ካውንስል ስብሰባ ላይ ‹‹ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ውሃ የመያዝ አቅሙ 70 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ይደርሳል ፤ ይህን ውሃ ለመያዝ ደግሞ የግድቡ ከፍታ ወደ ላይ እስከ 700 ሜትር ሊረዝም ይችላል ፡፡ ይህ ግድብ የሚደረመስ ከሆነ ካርቱም በሙሉ በውሃ ትጥለቀለቃለች ፡፡ ጦሱም ለአስዋን ግድብ ይተርፋል ›› በማለት አስተያየት ሰጡ ፡፡

የኢትዮጽያ መንግስት ብዙ ግዜ የሚናገራት ‹‹ ትዕግስት ›› አሁን በፍጹም አልሰራችም ፡፡ በአምባሰደሩ ፣ በውጭ ጉዳይ ሚ/ርና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀር አስተያየቱ ጸብ አጫሪና ያልተገባ በመሆኑ ማብራሪያ እንዲሰጥ የሳዑዲ አረቢያ መንግስትን ማጨናነቅ ያዘ ፡፡ ቢፒአርና ቢኤስሲ ላይ የሚታወቀው ‹‹ ፈጣን ምላሽ ›› እንደዚህ ተግባራዊ ሆኖ ማወቁ ያጠራጥራል ፡፡

በሌላ በኩል የ30 ሺህ ኢትዮጽያዊያንን ደም ያፈሰሰውና አያሌ ቤቶችን ያቃጠለው የሮዶልፎ ግራዚያኒ ወንጀለኝነቱ ተፍቆ የጀግና አክሊል ሊደፋ አይገባም በሚል ከፍተኛ ተቃውሞ በኛም ሆነ በምድረ ጣሊያን ተነስቶ ነበር ፡፡ ጉዳዩ ያሳሰባቸው ሸገሬዎችም  የተቃውሞ ሰልፍ በ የካቲት 12 መታሰቢያ ሃውልት አደባባይ ለማድረግ ሞክረዋል ፡፡

የግራዚያኒን አረመኔነትና ጭካኔ በሰብዓዊነት ሚዛን መለካት ያልፈለጉ የአፊሌ መንደር ነዋሪዎች ናቸው 127 ሺ ዩሮ በማውጣት ሃውልት ያሰሩለት ፡፡ ሃውልቱ ላይም ‹‹ Father land ›› እና ‹‹ Honour ›› የሚሉ ቃላቶችን  አጽፈዋል ፡፡ ይህ መቼም ለኢትጽያ መንግስትም ሆነ ህዝብ ከፍተኛ ንቀትና ውርደት ነው ፡፡ ለነጻነት የታገሉ ሰማዕታትን ክብር  የተለየ ግምት ያለመስጠትም ያስመስላል ፡፡ መንግስት የወንጀለኛና ጨፍጫፊ ኃውልት በምድረ ጣሊያን ሲቆም የዝምታ ዲፕሎማሲ ተጠቀመ  ፡፡ 

እንዳቅማቸው በጉዳዩ ላይ ያገባናል ያሉትን ደግሞ ያልተፈቀደ ሰልፍ አድርገዋል በማለት በተነ ወይም አሰረ አሉ ፡፡ የአራዳ ልጆች ‹‹ ፈጣን ምላሽ ›› አሁን የት ገባች እያሉ ነው  ፡፡

አራት  .

የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን በኢህአዴግ ስብሰባ ላይ አቶ መለስ 4 ሺህ እና 6 ሺህ ብር በፔሮል የሚከፈላቸው ብቸኛ ድሃ መሪ መሆናቸውን ይፋ አድርገዋል ፡፡ የእሳቸውን ዜና ስሰማ በቅርቡ ቢቢሲ ይፋ ያደረገው ፣ እረ እኔም አርቲክል ከጻፍኩባቸው የዓለማችን ድሃ ፕሬዝዳንት ወሬ ጋር ተጋጨብኝ ፡፡ ቢቢሲ የዓለማችን ድሃ ፕሬዝዳንት ብሎ ይፋ ያደረጋቸው የ 77 ዓመቱን የኡራጋይ ፕሬዝዳንት ጆሴ ሙጂካን / José Mujica / ነው ፡፡ በወር የሚያገኙት እውነተኛ ደመወዝ 7 ሺ 500 ፓውንድ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 7 ሺህ 15 ፓውንዱን ማለትም 90 ከመቶውን ለድሃዎች መቋቋሚያ ነው የሚሰጡት ፡፡ ይበቃኛል ብለው ወደ ቤታቸው ይዘውት የሚገቡት ገንዘብ 485 ፓውንድ ወይም 10 ከመቶውን ብቻ ነው ፡፡

ወ/ሮ አዜብ የነገሩን እውነት ከሆነ የቢቢሲውን ዜና አስተባብለው ስለ አቶ መለስ ድሃነት እንዲዘገብ ማድረግ ነበረባቸው ፡፡ ይህን የመሰለ ወርቅ መረጃ ይዞ ፍጆታውን ለሀገር ውስጥ ብቻ ማድረግ ተገቢ አይመስልም ፡፡ የአራዳ ልጆች የጊነስ ወርልድ ሪከርድንም ጉሮሮ ማሰብ ያስፈልጋል ባይ ናቸው ፡፡ ‹‹ እሱስ እኛ ካልደረስንለት ምን ይሆናል ? ››


Sunday, March 24, 2013

‎ከሜዳ አህዮቹ የምንማረው . . .‎





ዋሊያዋቹ የቦትስዋናዎቹን ‹ የሜዳ አህያ › በአጣብቂኝ ሰዓትም ቢሆን አሸንፈው መውጣታቸው ያስደስታል ፡፡ ለእነሱም ሆነ ለደጋፊው ፌሽታ መፍጠር ትልቅ ጉዳይ ነውና ‹ የደስታ ስካር አይለያችሁ › ብሎ መመረቅ ይገባል ፡፡

እቺ ተሸናፊዋ ሀገር ቦትስዋና በኳስ ያላት ደረጃ ዝቅተኛ ቢሆንም የብዙ የላቁ ጉዳዮች ባለቤት በመሆኗ በእጅጉ ማክበር ያስፈልጋል ፡፡ ምክንያቱም ትልቁና ቋሚው ፌሽታ እነሱ ዘንድ አለና ፡፡

‹ የሜዳ አህያ › በነገራችን ላይ የቡድኑ መጠሪያ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱ ብሄራዊ ምልክትም ጭምር ነው ፡፡ ከጨዋታው በፊት ቀድሞ የተዘመረላቸው ብሄራዊ መዝሙርን ደግሞ ‹‹ የእኛ ምድር / ሀገር ›› ይሉታል ፡፡

እንዳልኩት የቦትስዋና ፌሽታዎች ብዙ ናቸው ፡፡ ከሚከተሉት ረጅም ኳስ አንጻር ከዋሊያዎቹ ኳስን ይዞ ውብና ማራኪ ጨዋታ እንዴት መምራት እንደሚቻል ሳይማሩ አይቀርም ፡፡ እኛ ከእነሱ ልንማራቸው የሚገቡ መሰረታዊ ጉዳዮች ግን ይልቃሉ ፡፡ አንዳንዶቹን እናንሳ ፡፡

. ቦትስዋና ከአፍሪካ ከ 1965 ጀምሮ ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ከመጡ ሀገሮች የመጀመሪያዋ ናት ፡፡ 9 ከመቶ የሚደርሰው አማካይ እድገቷ እንደ እኛ ሀገር ዝናብ መጣሁ - ቀረሁ እያለ የሚያስፈራራ አይደለም ፡፡ ቀጣይነቱ የተረጋገጠ እንጂ ፡፡

. የአፍሪካ አስከፊ ሙስና ሲነሳ ይቺ ሀገር በተቃራኒው ትዘከራለች ፡፡ በትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት መሰረት የለም ከማለት የዘለለ ጥቂት የሙስና እንቅስቃሴ የሚታይባት የጨዋዎች ሀገር ናት ፡፡ እንዴት ቢያሳድጓት ነው ? ያስብላል ፡፡

. በሰበብ አስባቡ የፖለቲካ ፓርቲዎቿን ተሳትፎ የምትጎነትል ሳይሆን የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን ለረጅም ግዜ ሳታቋርጥ የተገበረች አፍሪካዊ ኩራት ናት ፡፡

. የዓለማችን ውድ ማዕድን አልማዝን በገፍ ለአለም ገበያ ታቀርባለች ፡፡ የሚያስገርመው የማዕድንና ነዳጅ ሀብት አናውዟቸውም ሆነ በዚሁ ኢ - ፍትሃዊ ክፍፍል ተማረው ወደማያባራው ጦርነት እንደገቡ በርካታ የአፍሪካ ሀገሮች ሳትሆን በፍጹም ሰላማዊና የተረጋጋ ጎዳና እየጋለበች መገኘቷ ነው ፡፡

. እቺ ሀገር ስትነሳ ፍጹም ከአእምሮዬ የማይጠፉት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ፌስተስ ሞይ ናቸው ፡፡ በአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ወቅት ጋዜጠኞች በተናጥል ቃለመጠይቅ ካደረግናቸው መሪዎች አንደኛው ነበሩ ፡፡ ትህትናቸው ፣ አካብዴ አለመሆናቸው ፣ ነጻ ሆነው በሚሰጡት ቀልዶች ተገርመን ነበር ፡፡ ለካ የእኚህ ሰው ባህሪ ልዩ የሆነው ወቅታዊውን ስብሰባ ብቻ መሰረት አደርጎ ሳይሆን ለዴሞክራሲ የተፈጠሩ በመሆናቸው ነው ፡፡ ይህንን የተረዳሁት ግን በጣም ዘግይቼ ነው ፡፡ ሀገራቸውን ለሁለት ግዜ ካስተዳደሩ በኃላ ስልጣን በቃኝ ብለው ወንበሩን ለሌላ ተመራጭ አስረከቡ ፡፡ በአፍሪካዊ ትህትናና እግዚዮታ ቢለመኑ ቢለመኑ ውስጣቸውን እንጂ ማንንም ማዳመጥ አልፈለጉም ፡፡ እሳቸው ስለ አፍሪካ የዴሞክራሲ ጥማት በጣም ይጨነቁ ኖሯል ፡፡ ይህ ለአፍሪካ ፍጹም የማይታመንና ብርቅ ሆነ ፡፡ ለካስ እንደኛ የገረማቸው ሁለት ሰዎች ነበሩ ፡፡ አንደኛው የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኒኮላ ሳርኮዚ ሲሆኑ ሁለተኛው ሱዳናዊ ቱጃር ኢብራሂም ናቸው ፡፡ ሳርኮዚ የዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ምሳሌ በማለት የሀገራቸውን ትልቅ ሽልማት ሸለሟቸው ፡፡ የአፍሪካን መሪዎች ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማበረታታት ተቋም የመሰረቱት ሞ ኢብራሂም ደግሞ በ 2008 የአፍሪካ ምርጥ ዴሞክራት መሪ በማለት 5 ሚሊዮን ዶላር አበረከቱላቸው ፡፡

ከኚህ መሪ በኃላ ቦትስዋና እንዴት ሆነች ? ካላችሁ መልሱ ዴሞክራሲ የበለጸገባት የሚል ይሆናል ፡፡ ምክንያቱም የማይናወጠውን መሰረት ሞይ ጥለውታልና ፡፡ የ 2011 የሞ ኢብራሂም ተቋም መረጃ እንደሚጠቁመውም የወቅቱ ፕሬዝዳንት ጀርሲ ጃን ካማ 75.2 ከመቶ በማግኘት ‹‹ ኤ ›› ካገኙ አራት መሪዎች አንደኛው ሆነዋል ፡፡ ለማስታወስ ብቻ የኛ ነጥብ ተጠጋግቶ 33 ነበር ፡፡

የሀገራችን ቴሌቪዥን የኳሱን ቁጥራዊ መረጃ እንደውጪዎቹ ተንትኖ አላሳየንም እንጂ በሌላ ሌላ ያጣነውን በኳሱ ሳናካክሰው የቀረን አይመስለኝም ፡፡ እንግዲህ ኳስ ወንድማማችነት መፍጠሪያ መድረክ ብቻ ሳይሆን መማማሪያም በመሆኑ ከሜዳ አህዮቹ የምንወስዳቸው ስልጠናዎች አሉ ፡፡ ስልጠናው የማያስፈልገን ቢሆን እንኳን የሜዳ አህዮቹን በያዙት የተቀደሰ መንገድ ልናከብራቸው ግድ ይለናል ፡፡

‹‹ ኖር ብለናል ባለ ዴሞክራሲያዎቹ / ዴሞክራቶቹ / !! ››

Saturday, March 23, 2013

የድሃው ፕሬዝዳንት ሀብታም አእምሮ





‹‹ ጫማ የለኝም ብለህ አትዘን
እግር የሌለው ሰው አለና ! ››

ይህች መሳጭ አባባል ከቆራጥ ድሃዋች አእምሮ በኑሮ ፍትጊያና ውጣ ውረድ ምክንያት የተፈነጠቀች ትመስላለች ፡፡ አንድ ሰው ግን ይህን አባባል የድህነት አባል ነው ብሎ ለመከራከር የሚያስችል መሰረት የለም በማለት ሞግቶኛል ፡፡

እንዴት ? - እኔ ፡፡

‹‹ ተረቱ የሚያገለግለው ለሌላ ተምሳሌት እንደ መወጣጫ እንጂ በራሱ ምሉዕ ሆኖ ለመቆም አይደለም ››

አልገባኝም ! - እኔ ፡፡

በምሳሌ ባስረዳህ ይሻላል ያለኝ ወዳጄ ትንሽ አሰብ በማድረግ የሚከተለውን ተመሳሳይ ነገር ግን የወገቡ ቁጥር ሰፊ የሆነ ጥቅስ ወረወረልኝ

‹‹ G + 1 የለኝም ብለህ አትዘን
ወያኔ ዲኤክስ የሌለው አለና ! ››

ፈገግ አልኩ ፡፡ የሞተሯ ድምጽ እየቆየ ከፍ እያለ እንደሚሄድ ቮልስዋገን ሳቄ መቦተራረፍ አበዛ - የእኔ ፡፡ ባለጸጋዎችም ሲገናኙ ከ ‹ ተመስገን › ይልቅ ብዙ አላገኘሁም ፣ ብዙ አላደግኩም የሚል ምሬትና ቅናት አቀፍ መዝሙር እንደሚያስቀድሙ ይታወቃል ፡፡ ይህ ተፈጥሯዊ ስለሆነ ክፋት የለውም ብሎ ማለፍም ይቻላል ፡፡ ሆኖም የድሃዎችን መሳጭና ስሜት አንኳኪ ጥቅስ ሰርቀው ለማይገባ ጥቅም ያውሉታል ብሎ መጠበቅ ከባድ ነው ፡፡

እንዴት ? - አንተ / አንባቢው /

የላይኛው ጥቅስ ጓደኛዬ እንደሚለው የህይወትን ከፍታ የሚያሳየው በጥቂት የደረጃዎች ልዩነቶች ከፋፍሎ አይደለም ፡፡ ምቾት ሳይሆን እሾህ ፣ ቆንጥር ፣ ድንጋይና ውርጭን ለመከላከል የጠየቀ እግር ነው ማጽናኛ ተብሎ እግር የሌለው ሰው የተጠቀሰለት ፡፡ ይህም የኑሮን ገደልንም ሆነ ግሽበት አድምቆ ያሳያል ፡፡ ምነው ትንታኔው ከአጽናኝነት ይልቅ አደንዛዥነቱ ላቀ ብትል ሃሳብህ አልተጋነነ ይሆናል ፡፡ ግን ለግዜውም ቢሆን ከደረጃ በታችና ከጤና ጎዳና የወደቀን ህይወት አንድ ሀሙስ ለማስቀጠል ማደንዘዣ መጠቀም ሳይንሳዊ ድጋፍ ሳይኖረው እንደማይቀርም መገመት ሊኖርብህ ነው ፡፡

ጫማ የሌለው ድሃ እግር በሌለው ሰው ከተጽናና አነሰም አደገ ሀብት ያለው ባለጸጋ ለምን የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 25 ቁጥር 29 ጥቅስ እንደማያጽናናው ግልጽ አይደለም ፡፡

ምን ይላል ? - አንተ / አንባቢው /

‹‹ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና ይበዛለትማል
ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል ››

ስለዚህ በማለት የመግቢያ ዲስኩራችንን እንደሚከተለው ብታጠቃልለው ስለ ቀጣዩ ርዕሰ ጉዳይ ምን ያህል እንደተቀራረብን ሊያሳብቅህ ይችላል ፡፡ < ስለዚህ  የለኝም  ብሎ አላግባብ ከማንቋረር የያዘው እንዲበዛለት ስም ያለው ተግባር ማከናወን ህሊናዊም መንፈሳዊውም ርካታ ያጎናጽፈዋል >

     +++++                                              +++++++                                               ++++++++

እንደሚታወቀው የዓለማችን ባለጸጋዎች በሁለት ዋና ዋና ምድብ ውስጥ ነው ተሰልፈው የሚገኙት ፡፡ በንግድና አስተዳዳሪነት ፡፡ በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት እነ ቢል ጌትስ ፣ ዋረን ቡፌት ፣ የኢንቴል ተባባሪ መስራች ጎርደን ሙርና ሌሎችም የማቲዎስን ጥቅስ በልካቸው አሰፍተው የለበሱ ይመስላል ፡፡ ሃብታቸው በቦሌም መጣ በባሌ በቢሊየን የሚቆጠረውን ገንዘባቸውን ‹‹ ጫማና እግር ›› ሌላቸው ቡድኖች እየሰጡ በተቃራኒው የሰጡትን ያህል ያገኛሉ ፡፡

አስተዳዳሪዎቹ ልዩ መጠሪያቸው ‹‹ ፕሬዝዳንት ›› ወይም ‹‹ ጠ/ሚ/ር ›› ይባል እንጂ የሀገር ሀብትንም ጭምር ነው ወደ ግል ካዝናቸው በአግባቡ መግባቱን ነው የሚያስተዳድሩት ፡፡ በርግጥ ይህ አባባል ሁሉንም መሪ አይወክልም በማለት ማሰተካከያ እንዲገባ አስበህ ይሆናል - በውስጥህ ፡፡ እኔም በመርህ ደረጃ ትክክል ነው እንዳልኩህ ገብቶሃል ብዬ ሃሳቤን ልቀጥል ፡፡ ብዙ መሪዎች ከሚያገኙት የሚታይና የማይታይ ጥቅማጥቅም በተጨማሪ ዓመታዊ ደመወዛቸው እንደ ተራራ የተቆለለ መሆኑ ይታወቃል ፡፡ ምናልባትም ተራራ ተንዶ ይግደልህ ወይስ የተቆለለ የመሪ ገንዘብ የሚል አጣብቂኝ ምርጫ ውስጥ ብትገባ  መልስህ ‹ እሳት ካየው ምን ለየው › ቢሆን ይመረጣል ፡፡ ካላመንክ ጥቂት የምሳሌ ብቻ ሳይሆን የተራራ ዘሮችን ልበትንልህ ፡፡ ሙአመር ጋዳፊ 200 ቢሊየን ፣ ሆስኒ ሙባረክ 70 ቢሊየን ፣ ቭላድሚር ፑቲን 70 ቢሊየን ፣ ስባስቲያን ፒኒራ /ቺሊ/ 2.4 ቢሊየን ፣ አሲፍ አሊ ዛርዳሪ/ፓኪስታን/ 1.8 ቢሊየን ዶላር ያገኛሉ ፡፡ ጥቂት ባለ ሚሊኒየኖርችንም እንቀላቅል ፡፡ ፊደል ካስትሮ 900 ሚሊየን ፣ ፓወል ቢያ 200 ሚሊየን ፣ ሊሙንግ ባክ/ ደ.ኮሪያ/ 23.6 ሚሊየን ፣ ማንዴላ 15 ሚሊየን ፣ አንጄላ መርክል 11.5 ሚሊየን ፣ ሮበርቱ ሙጋቤ 10 ሚሊየን ፣ መህመድ አህመዲንጃድ 5 ሚሊየን ዶላር ያገኛሉ ፡፡ ባለሺዎቹ ለምን ይቀርባቸዋል ከተባለ የባራክ ኦባማና የ ሁ ጂንታኦ /ቻይና/ 4 መቶ ሺህ ዶላርን ዋቢ ማድረግ ይቻላል ፡፡

ዞሮ ዞሮ ብዙዎቹ የስልጣን መሰረቱ የሚመነጨው ክብር ፣ ሃይልና ሀብትን ማግኘቱ ላይ በመሆኑ እንደ አንዳንድ ነጋዴዎች ‹‹ ለጋስነት የልቦና ጉዳይ ›› መሆኑን አይቀበሉም ፡፡ እምነትና ፍልስፍናቸው ‹ ጭብጦህን በአግባቡ ሰብስብ ፤ ይህም ሃብት እንዳይነጠቅ አምርረህ ጠብቅ ! › የሚል ነው ፡፡

መሪዎቹ ከላይ የጠቀስናቸው ሁለት መሰረታዊ ጥቅሶች ማለትም የድሃዎችን ‹‹ ጫማ የለኝም ብለህ አትዘን ›› እና የሀብታሞቹን ‹‹ ላለው ይጨመራል ›› በቀና ልቦና መመርመር ምን ያህል ጠቃሚ መሆኑን አልተረዱም ፡፡ ከቢሊየንና ሚሊየን ሰፊ እርሻ ወስጥ ለዘር የሚያገለግሉ ጥቂት ‹‹ ሺዎችን ›› መበተን ምን ያህል ይከብዳል ?

‹‹ አይከብድም ! ›› - ይላሉ
‹‹ ማን ? ›› - እኔና አንተ
‹‹ የኡራጋይ ፕሬዝዳንት ጆሴ ሙጂካ / jose mujica / ?/ ››
‹‹ እንዴት ? ›› - እኔና አንተ

እኚህ ፕሬዝዳንት የዓለማችን ድሃው ፕሬዝዳንት ቢሆኑም በማይታመን ልግስና ‹‹ ጫማ ከሌላቸው ›› ጎን በመሰለፋቸው ታላቅነትን ተጎናጽፈዋል ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እንደ ሌሎቹ ‹‹ አስተዳዳሪዋች ›› ዓመታዊ ደመወዛቸውን ቢሊየንና ሚሊየን ለማድረስ አልፈለጉም ፡ ሺህ ድሃ መሃል የአንድ ሃብታም መገኘት በስነልቦና ድሃ ከመሆን ወጪ ትርፍ የለውም በማለት ይሆን ? ወርሃዊ ደመወዛቸው 7985 ፓውንድ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 7 ሺ 500 ፓውንዱን ወዲያው የሚሰጡት ድሃዎችን ለመርዳት ለተቋቋሙ ፕሮጄክቶች ነው ፡፡  ይህ ልግስና የደመወዛቸውን 90 ከመቶ ድርሻ  እንደሚሸፍን ልብ በል ፡፡ እኛ በየወሩ 2 እና 3 ከመቶ ለጤና ፣ ለልማት ፣ ለግድብ ወዘተ እየተባለ ሲቆረጥብን እንዴት ነው የምንሆነው ?
‹ እኛ የምንፈራው መቆረጡን ሳይሆን የሚቆረጥብን የት እንደሚገባ አለማወቃችን ነው › - ነው ያልከው ፡፡ በርግጥ ተገቢ ስጋት ነው ፡፡ በዚህ መንገድ ስንት ሰብዓዊነት የሌለውን ጅብ ስንቀልብ ነው የኖርነው ፡፡

ግን ጎበዝ ያለውን በሙሉ ሳይሳሳ የሚሰጥ ፈጣሪ ብቻ አልነበር እንዴ ? እንዲህ የሚያደርግ የሀገር መሪ አይደለም ጫካ የገባ መናኝ በቀላሉ ይገኛል እንዴ ? ሰምታችሁስ ታውቁ ይሁን ? ለመተዳደሪያ ይበቃኛል ብለው የሚያስቀሩት 485 ፓውንድ ወይም አስር ከመቶውን ብቻ ነው ፡፡

 ‹‹ በርግጥ መሪዎች ለህዝብ ፍቅር አንዲህ የቀረቡ ናቸው ? ››
‹‹ ራሳቸውንስ ይህን ያህል ይጎዳሉ ? ››
 ‹‹ ለመሆኑ እኚህ ሰው ማናቸው ? ››

አእምሮህ በተደራራቢ ጥያቄ ተጨናነቀ አይደል ?!  ለማንኛውም  ሰውየውን ለማጥናት እንሞክር ፡፡

ጆሲ ሙጂካ የተወለዱት ግንቦት 20 ቀን 1935 ነበር ፡፡ አባታቸው ስፔናዊ ሲሆኑ እናታቸው የጣሊያን ዝርያ አላቸው ፡፡ ቤተሰባቸው በስትሪላ አምስት ሄክታር መሬት ገዝተው በወይን እርሻ ይተዳደሩ ነበር ፡፡  ሙጂካ አምስት ዓመት ሲሞላቸው ማለትም በ1940 አባታቸውን በሞቱ ተነጠቁ ፡፡  ሙጂካ ወጣት በነበሩበት ግዜ ሁለት ጉዳዮች ትኩረታቸውን ስቦት ነበር ፡፡ አንደኛው ፓለቲካ ሲሆን በብሄራዊ ፓርቲ የወጣቶች ሊግ ውስጥ ንቁ ተሳተፎ አደርገዋል ፡፡ ሁለተኛው ስፖርት ሲሆን ለተለያዩ ክለቦች በተለያዩ ካታጎሪዎች የብስክሌት ውድድር ሲያደርጉ ቆይተዋል ፡፡

በ1960ዎቹ ፋኖ ተሰማራ … የሚለው የኩባ አብዮት በሀገራቸውም ተጸዕኖ በመፍጠሩ ለመጀመሪያ ግዜ ከተደራጀውና ከታጠቀው የቱፓማሮ እንቅስቃሴ ውስጥ  ተቀላቀሉ ፡፡ በ1969 አካባቢ ፓንዶን ለመያዝ በተደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ትልቅ ተሳተፎ የነበራቸው ሙጂካ አራት ግዜ ያህል በመንግስት ወታደሮች እጅ ወድቀዋል ፡፡ ስድስት ግዜ ያህል በፖሊስ ጥይት ተመተዋል ፡፡ በ1971 ፑንታ ካሬታስ ከተባለ እስር ቤት ያመለጡ ሲሆን ከእንደገና በ1972 ተይዘዋል ፡፡ በ1973 ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ሲካሄድ ለ 14 ዓመታት ወደታሰሩበት ወታደራዊ እስር ቤት እንዲዘዋወሩ ተደርጓል፡፡ በእስር ቤት ቆይታቸው ከቱፓማሮ ፓርቲ በርካታ መሪዎች ጋር ትውውቅ ያደረጉበት ነበር ፡፡

በ1985 በሀገሪቱ ህገ መንግሰታዊ ዴሞክራሲ ሲመሰረት ከ 1962 ጀምሮ በፖለቲካና እና ወታደራዊ ወንጀሎች የታሰሩ ሰዎች ምህረት ሲደረግላቸው  እሳቸውም የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ሆኑ ፡፡ ራሳቸውን ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ሰፊ ህብረት እንደሚያስፈልግ የተገነዘቡት ሙጂካና ጓደኞቻቸው ከግራ ክንፈኛ ድርጅቶች ጋር በመተባበር Movement of Popular Participation የተባለ ድርጅት መሰረቱ ፡፡ በ1994 በተደረገው አጠቃላይ ምርጫ ምክትል ሆነው የተመረጡ ሲሆን በ1999 ደግሞ ሴናተር መሆን ችለዋል ፡፡ ከ 2005 እስከ 2008 ድረስም የወቅቱ ፕሬዝዳንት ታባሬ የሙጂካን የኃላ ታሪክ በማጥናት የሀገሪቱ የእንስሳት እርሻና አሳ ሚንስትር አድርገው ሾመዋቸዋል ፡፡ በ2009 በተደረገ ሀገራዊ ምርጫ ፓርቲያቸው ለፕሬዝዳንትነት ዕጩ አድርጎ አቅርቧቸው ማሸነፍ ችለዋል ፡፡ የመጀመሪያ ቀን ንግግራቸውም በአስገራሚነቱ ተመዝግቧል

‹‹ ምን አሉ ? ›› አልክ

 ‹‹ በውድድሩ ያሸነፈም ሆነ የተሸነፈ ስለሌለ በአንድነት እንነሳ ፡፡ ስልጣን ከሰማይ ይመጣል የሚባለው አስተሳሰብ የተሳሳተ ነው ፤ ስልጣን የሚመጣው ከብዙሃኑ ልብ መካከል ነው ››

ሙጂካ በስልጣን ቆይታቸው ከፈጸሙት አስገራሚ ተግባር አንዱ ማሪዋና የተባለውን አደገኛ ዕጽ በህጋዊ መንገድ እንዲሸጥ ማድረጋቸው ነው ፡፡ እጹ በህጋዊ መንገድ እንዲያልፍ መደረጉ ሀገሪቱ ከፍተኛ ገቢ እንድታገኝ ብሎም የወንጀልና የጤና እንከኖች እንዲቀንሱ አድርጓል ፡፡ የተመሳሳይ ጾታን ጋብቻን ህጋዊ ምላሽ እንዲያገኝ ያደረጉ ሲሆን ተከልክሎ የቆየውን እስከ 12 ሳምንት ዕድሜ ያለውን ጽንስ የማስወጣት ህግም ፍቃድ ሰጥተዋል ፡፡ አንድ ፕሬዝዳንት ከአንድ ግዜ በላይ መመረጥ የለበትም የሚል የጸና አቋም በማራመድ ይታወቃሉ ፡፡

የ 77 ዓመቱ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዛሬ ሞንቲቮዶ በተባለ የከተማ ዳርቻ የፓርላማ ተመራጭ ከነበሩት ሚስታቸው ሉሲያ ቶፓላንኪና ከባለሶስቱ እግር ውሻቸው ማንዌላ ጋር ህይወታቸውን ይመራሉ ፡፡ የህይወታቸው መሰረት ልክ እንዳባታቸው ግብርና ሲሆን መኖሪያ ቤታቸውን የተመለከቱ ጋዜጠኞች ለአንድ ፕሬዛዳንት የማይገባና ፍጹም በመፈራረስ ላይ የሚገኝ በማለት ገልጸውታል ፡፡ መንግስት ያቀረበላቸውን ከቤተመንግስት የሚተካከል ህንጻ ብቻ ሳይሆን የከተማውን ህይወት ንቀው ነው አፈር ገፊነትን የመረጡት ፡፡

እኚህ ሰው የዚያ ሀገር ፕሬዝዳንት ነበሩ ለማለት የሚያስችሉ ሀብትም ሆነ ድባብ በቤታቸው ዙሪያ የለም ፡፡ ምናልባት ደህንነታቸውን የሚጠብቁ ሁለት ፖሊሶች መገኘታቸው ካልሆነ በስተቀር ፡፡ የዕለት ስራቸውን የሚያከናውኑት በአንድ ትራክተር ሲሆን አልፎ አልፎ ወደ ከተማ የሚሄዱባት ድክም ያለች የ1987 ሞዴል ቮልስዋገን አላቸው ፡፡ ትልቁ ሀብታቸውም እነዚህ ናቸው ፡፡ አንድ በህዝቡ ሲወደድ የነበረ መሪ ለምን እንዲህ በማይጠበቅና ዝቅ ባለ የህይወት ቦይ ውስጥ ማለፍ ፈለገ ? የሚል ጥያቄ መፍለቁ ግድ ነው ፡፡መልሱ የሰውየው ሰብዓዊነትና ሩህሩህነት የላቀ ደረጃ ላይ መድረሱ እንዲሁም ለሌሎች ጥቅምና ዕድገት መኖር ራስንም አሳልፎ መስጠት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ሳያንገራግሩ በመቀበላቸው ነው ፡፡

ይህን ከባድ ውሳኔ ለማሳለፍ በርካታ ጥቅማጥቅሞችን በመርዘም ሆነ በንቀት ማውደም ያስፈልጋል ፡፡ ስንት ነገር ያሳለፉት ፕሬዝዳንት ለእርሻቸው ውሃ የሚቀዱት ረጅም ጉድጓዶችን ቆፍረው ነው ፡፡ በቀን ለብዙ ግዜ ይቀያየሩ የነበሩትን ልብሶች ዛሬ ላውንደሪ ለማስገባት እንኳ ባለመቻል በእጃቸው ነው የሚያጥቡት ፡፡ በቤተመንግስታቸው ይቀርብላቸው የነበረው ምግብና መጠጥ ፣ ክብርና መሽቆጥቆጥ ፣ ውዳሴና የታላቅነት ስሜት ፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ዛሬ የሉም ፡፡ ቢያማቸውም ሆነ ጫና ሲበዛባቸው ለእረፍት ሀገር አቋርጠው የሚሄዱበት አግባብ አሁን ዝግ ነው ፡፡ ገንዘቡስ የታለና ፡፡ ባለፈው ዓመት ያላቸው አጠቃላይ ሀብት ሲሰላ 135ሺህ ፓውንድ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡ ይህ ገንዘብ በሀብታሞቹ መሪዎቹ አይን ከታዩ የአንድ ቀን ራት ቢጋብዝ ነው ፡፡ ገንዘብ ደስታን አይገዛም የሚሉት ሙጂካ የባንክ አካውንት የሌላቸው መሆኑም ሌላ አስገራሚ ጉዳይ ነው ፡፡
በወር የገቢን 90 ከመቶ ለችግረኞች አሳልፎ መስጠት ይከብዳል ፡፡ ግን ለምን ? ተብለው በጋዜጠኞች ሲጠየቁ ‹‹ ይህን ያህል መርዳት አለብኝ ፡፡ ምክንያቱም በጣም አነስተኛ በሆነ ገቢ የሚተዳደሩ በርካታ ኡራጋዊያን አሉና ›› በማለት መልሰዋል ፡፡ ምናለ ይቺን አባባል በየደረጃው ለሚገኘው የኛ ሀገር ትንሽና ትልቅ ስግብግብ አመራር ግልባጭ አድርገው ቢልኳት ? ለማንኛውም እነዚህን አማላይ ፈታኝ ምዕራፎች ለመዝጋት መቻል ምን ያህል ጀግና መሆንን ያሳብቃል ፡፡

ሙጂካ ለቢቢሲ ‹‹ የቁሳቁስ ሃብት ደስታን መግዛት አይችልም ፡፡ ብዙዎች ድሃው ፕሬዝዳንት እያሉ ይጠሩኛል ፤ እኔ ግን ድህነት አይሰማኝም ፡፡ ድሃ ሰዎች ህይወታቸውን በውድ የአኗኗር ዘይቤ ውስጥ የሚያሳልፉና ዘወትር ብዙና ብዙ ለማግኘት ብቻ የሚሰሩት ናቸው ›› በማለት ገልጸዋል ፡፡

እንደ መግቢያችን ሁሉ ለመዝጊያችንም መቀርቀሪያ እንፈልግለት፡፡

ለጋስ መሪዎች መስዋትነት የሚከፍሉት ምክንያቱ ላይ ነው ፡፡ ድሃ ህዝቤን እንዴት ከችግር ላውጣው እንጂ እኔ እንዴት ልበልጽግ የሚል ሀሳብ አያስቀድሙም ፡፡ እንዴት የዴሞክራሲ ፣ ፍትህና ነጻነት ጥያቄውን ሙሉ ላድርግለት እንጂ ምን ዓይነት የፍርሃት ቆብና ቱታ ላልብሰው በማለት አይጨነቁም ፡፡ ለጋስ መሪዎች ለተቋማትም ሆነ ለሀገር እንደ ቃል አቀባይ ስለሚቆጠሩ የህዝቡን የመረዳት፣ የመቀበልና የመተግበር ስሜት መማረክ ይችላሉ ፡፡ ለጋስ መሪዎች ልዩ ክህሎትና ጥበብ ያላቸውን ሰራተኞች ልብና አእምሮ መቆጣጠር አያስቸግራቸውም  ፡፡ እናም ብዙዎች ከሚጠበቀው በላይ በራሳቸው ተነሳሽነት ለመስራት አያቅማሙም ፡፡ ለአንድ መሪ ትልቁ ፈተና ህዝባዊ ፍቅር የማግኘቱ ጉዳይ በመሆኑ ብዙ ሊሰራበት የተሰጠውን አእምሮ ሳይበርዝ እንደ ማዕድን መቆፈር አለበት ፡፡

‹‹ ምን ሊያገኝ  ? ›› አልክ

እንደ አልማዝ ውድና አጓጊ የሆነውን - ቅንነት
እንደ ወርቅ ልብ የሚያሞቀውን - ሩህሩህነት
እንደ ብረት የጠነከረን - ህዝባዊነት ፡፡


Sunday, March 10, 2013

‎የሰውየው ሀገር . . . የሰውየው ነገር . . .‎




ሰውየው ተይዘዋል ፡፡
ነፍሳቸውን ይማረውና አቶ መለስ ነበሩ በየጋዜጣዊ መግለጫውና በፓርላማ ስብሰባ ላይ የሚያከናንቧቸው ፡፡ አተራማሹ ፣ ማፊያ፣ አሸባሪ ፣ ወሮበላ እረ ምን የማይሰጧቸው ስም ነበር ?
ዛሬ በህመም ተይዘው ‹‹ እረ ማን ይስደበኝ ? እረ ማን ይገስጸኝ ? ›› በማለት ትችቱንም ሆነ የቀደመውን የትግል ትዝታ ያንጎራጉራሉ ለማለት አይደለም ፡፡ በህመምና በጭንቀት ክበብ ውስጥ መገኘታቸው ፈጣን የምላስም ሆነ የተግባር ምላሻቸውን አደበዘዘው ለማለት እንጂ ፡፡

እንጂማ እሳቸውስ ለማን ይመለሱ ነበር ?!
የኢትዮጽያ ባለስልጣናት የጥቅም ገመዳቸውን መበጣጠስ ሲጀምሩ ባልታሰበ ፍጥነት አይደል ባድመን መያዣ ያደረጉት ፡፡ እየፈሩ በግልጽ ባይናገሩም በሆዳቸው ‹‹ የትልቋ እስር ቤት መሪ ! ›› እያሉ ሊያሽሟጥጡ በሚችሉ የአፍሪካ መሪዎች ላይ አጋጣሚን ሰበብ በማድረግ ከመዝለፍ መች ይቆጠባሉ ፡፡ ‹ የአፍሪካ ሰሜን ኮሪያ › እያለ የሚያጣጥላቸውን ተመድ ጽ/ቤቱ ድረስ በመሄድ ያልተገባ መልስ ሰጥተዋል ፡፡ የትግሉ ዘመን ወጣ ውረድ ትዝ ሲላቸው የመንን ፣ መዝናናት ሲፈልጉ ጅቡቲን ወረው እንካሰላንቲያ ለመጫወት መች ወደ ኃላ የሚሉ ነበሩ ፡፡

ዛሬ ግን በህመም ተፋዘዋል ፡፡
እንጂማ ምኑ የቆረጠው ነው የሚፈታተናቸው ?! ለዛውም የሀገራቸው ሰው ፤ ለዛውም በእፍኝ ታንክ የሚታገዙ በመቶ የሚቆጠሩ ወታደሮች ፡፡ የአምስት ሚሊዮን ህዝብ መሪ ቢሆኑም በ 200 ሺህ ወታደሮች የተዋቀረ ጦር ሰራዊት ባለቤት መሆናቸውን ይህ ነገር ፈላጊ ቡድን አያጣውም ፡፡ ደግሞ ምናለበት የደመወዝና የፋቲክ ጥያቄ ቢያነሳ ! የሀገሪቱን ማስታወቂያ ሚኒስቴር ከቦ ሁለት ህመም የሚጨምሩ ጥያቄዋችን ይለኩሳል እንዴ ?!  በርግጠኝነት በነዚህ ጥያቄዎች ከሚፈተኑ በቢጫ ወባ ቢያዙ ይመርጣሉ ፡፡ ደረታቸው ላይ የተቀረቀረው አንደኛው ጩቤ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ የሚለው ነው ፡፡ አንገታቸውን አላዞር ያለው ሁለተኛው ጥያቄ የ 1997ቱ ህገ መንግስት ስራ ላይ ይዋል የሚል ነበር ፡፡

ሰውየው በነዚህ ጥያቄዎች አተነፋፈሳቸው ተዛብቷል ፡፡
ወይ ታሪክና ፖለቲካ አለማወቅ ! ይፈቱ ከተባሉ የፖለቲካ እስረኞች መካከል 11 ዱ ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩ ሲሆን ወደ እስር ቤት የተወረወሩት የሰውየውን ህልውና ሊያቆም የሚችለውን የ ‹‹ ፍትሃዊ ምርጫ ›› ጥያቄ በማንሳታቸው ነበር ፡፡ በ1997 የጸደቀው ህገ መንግስት ደግሞ ከኢትዮጽያ በሄደ ምርጥ የአወዳይ ጫት ውብ ሆኖ ከተፈጠረ በኃላ ምርቃናው ከጠፋ በኃላ የግምግማ ጅራፍ የጮኀበት እንደነበር ሀገር ያውቀዋል ፡፡ የፕሬስ ፣ የሃይማኖት ፣ የፖለቲካ በአጠቃላይ ለኤርትራዊያን የሰጠው መብት በእጅጉ እንደ ውብ ሴት የቆነጀ ነበር ፡፡ እና ይህችን ህገ መንግስት ማሽኮርመምና ፍቅር ማስያዝ ያለበት ወጪ ወራጁ ሁላ ነው ወይስ ሰላሳ ዓመት ቆስሎና ደምቶ እዚህ የደረሰው የሰውዬው ፓርቲ ? - መልሱ ፓርቲ የሚለው ይሆናል ፡፡ እና ፓርቲዎ ምን ወሰነች ? - መልሱ የሚከተለው ይሆናል ፡፡ ‹‹ ይህችን ውብ ህገ መንግስት ከማፈራረስ እንደተዋበች ትቆይና ቋሚ ሙዚየም ውስጥ በክብር ትቀመጥ ፡፡ ሁሉም አፈጣጠሯን ያድንቅ ፡፡ እሷን የማናገር ስልጣን ግን ለርዕሰ ብሄሩ ይሰጥ ›› ይህ ህግ እንዴት አለፈ ? - መልሱ በአክላሜሽን !!

ሰውየው ተዳክመዋል ፡፡
እንጂማ እንደ ሌሎች አፍሪካዊ ሀገሮች ‹‹ ተዋበች ›› የሚል ስያሜ ያገኘቸውን ህገ መንግስት ጥላሸት ለመቀባት የሚንቀሳቀሱ ጥቂት ወታደሮችን በለመደው ፍጥነታቸው ዘለው ጉብ አይሉባቸውም ነበር ፡፡ ወታደሮቹ ጥያቄያቸውን በቴሌቪዥን ማስነገራቸው ብቻ ሳይሆን ለዚህ መ/ቤት ቁልፍ የሆነችውን የሰውየውን ሴት ልጅ ኤልሳን እንደ መያዣነት መጠቀማቸው የድፍረቱን ደረጃ ከፍም ባደረገው ነበር ፡፡

ወታደሮቹ ተልኳቸውን ፈጽመው ከተመለሱ በኃላ እንኳ የሰውየው ድምጽ የተሰማው ወሬው ከቆረፈደ በኃላ ነው ፡፡ ብዙና ዝርዝር ነገር እንደሚያወሩ ቢጠበቅም ‹‹ የከሰሩ ጠላቶች ናቸው ! ›› የምትል ብጣቂ ነገር ነው ወርወር ያደረጉት ፡፡ እነማን ናቸው ? ከጀርባቸው ማን አለ ? ፍላጎታቸው ምንድነው ? ሰውየው ይህን በስድብም ሆነ በንቀት ለመመለስ አቅም በማጣታቸው መልሱ እንጃ ሆኗል ፡፡  ልክ እንደ አሁኑ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራም ይሁን የማስተካከያ ጥያቄ በአንድ ወቅት ዓለም ስለ ሰውየው መሞት ይነጋገር ነበር ፡፡ አንዳንዶች በግላጭ በደስታ ጨፍረዋል ፣ አንዳንዶች በድብቅ የውስኪና ቢራ ብርጭቆ አጋጭተዋል ፡፡ ታዲያ ሰውየው እንደምንም በገመምተኛ አካል ቴሌቪዥን መስኮት ላይ ብቅ ብለው ‹‹ የታመሙት አሉባልታውን የሚነዙት ናቸው ! ›› በማለት ጠላቶቻቸውን ኩም አድርገዋል ፡፡ ጣታቸውንም ወደ አሜሪካና ኢትዮጽያ ቀስረዋል ፡፡ ዛሬ ግን ወታደሮቹን ባሰማራው አካል ላይ ለመደንፋት አልፈለጉም ወይም አልቻሉም ፡፡

እነሆ ሰውየው ! …
ስም - ኢሳያስ አፈወርቂ
የእናት ስም - አዳነች በርሄ
የትውልድ ዘመን - 1965 / እአአ /
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት - ልዑል መኮንን
ዩኒቨርስቲ - ለሁለት ዓመት የምህንድስና ትምህርት
ማስት - ሳባ ኃይሌ
ልጆች - አብርሃም ፣ ኤልሳ እና ብርሃኔ
የሚያበሳጫቸው ጉዳይ - የወያኔ ክህደት
ሃይማኖት - ኦርቶዶክስ

ደርግ በወደቀ ማግስት በኤርትራዊያን ‹‹ ጀግና ! ›› ተብለው ሲሞገሱ የቆዩት አቶ ኢሳያስ የተቻኮለ ቢሆንም በብዙዎችም ሞገስና ክብር አግኝተው እንደነበር ይታወቃል ፡፡ ውሳኔ ህዝብ ለመታዘብ የሄዱት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በራሳቸው መጽሀፍ ላይ ‹‹ የነጻነታቸው ቀን እኔ ፣ መለስና ኢሳያስ / በስሊፐር ጫማ / ከተማ ውስጥ ዞረናል ፡፡ በእውነት ትልቅ ነጻነት ነበር የተሰማኝ ፡፡ ሱቅ እየገባን ፣ ማታ ማታ እየዞርን አንድ ሁለት ቦታ መጠጥ እየተጎነጨን ተዝናንተናል ›› በማለት በተዘዋዋሪ የሰውየውን ዲሞክራትነት አስረድተዋል ፡፡ የአሜሪካ መንግስት የወደፊቱ የአፍሪካ ዴሞክራት መሪዎች በሚል በግልጽ ዕውቅና ከሰጣቸው አራት መሪዎች መካከል አንደኛው ኢሳያስ ነበሩ ፡፡ አቶ መለስም በደህናው ዘመን ‹‹ ከኢሳያስ ጋር አንድ ሰዓት ማሳለፍ አስር መጽሀፍ ከማንበብ በላይ ልበ ብሩህ ፣ አዋቂ እና ተጠቃሚ ያደርጋል ›› በማለት ታላቅነታቸውን መስክረዋል ፡፡

ዛሬ የቀድሞው ምስክርነት መገልበጡ ብቻ ሳይሆን ሚዛናዊነቱም ያልተመጣጠነ በመሆኑ የሰውየውን ሰብዓዊ ትከሻ እስከማጉበጥ ደርሷል ፡፡ ‹‹ ተዋበች ›› ላይ የሰፈረውን መርህ ከማስከበር ይልቅ የሀገር ደህንነትን ማረጋገጥ ይቀድማል የሚለው ፍልስፍናቸው እየጠለፋቸው ነው ፡፡ በተለይም የፖለቲካ ፣ የፕሬስ ፣ የሃይማኖት ነጻነቶችን መጨምደድና ‹‹ ሳዋን ›› የመለጠጡ አሰራር ያስከተለው ጦስ ሀገሪቱንና ራሳቸውን የመጨረሻ ጠርዝ ላይ እንዲገኙ አድርጓቸዋል ፡፡ እሳቸው በደምና አጥንት የተገነባውን አጥሬን አትነቅንቁ ሲሉ ፣ ሌሎች በአጥሩ ታፍነናል ፣ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚፈጸመው በደልና ጭቆና አንገፍግፎናል በማለት ጀርባቸውን እያዞሩባቸው ይገኛሉ ፡፡ ታማኝ ይባል የነበረው ጦር ሰራዊታቸው እንኳ ዛሬ በእሳቸው መስመር ለመሰለፍ እያንገራገረ ነው ፡፡ በርግጥ ሰሞኑን ያልተጠበቀ ድፍረት ያሳዩ ውስን ወታደሮች አዲስ የተቃውሞ ምዕራፍ መክፈታቸው ካልሆነ በስተቀር የብዙሃኑን መለዮ ለባሽና ሲቪል ማህበረሰብ ስሜት ነው ያንጸባረቁት ፡፡

የሰውየው አዲሱ ጠላት ማነው ?
ኢሳያስ እአአ ህዳር 2012 የረጅም ግዜ ወታደራዊ አማካሪ የነበሩትን ሜጀር ጄኔራል ፊሊጾስ ወልደ ዮሀንስ አስረዋል ፡፡ በቅርቡ አፍንጫቸው ስር ቀርቦ በጠመንጃ አፈሙዝ አፍንጫቸውን ያለፍርሃት የጎረጎረው ቡድን መሪ እኚህ ጄኔራል መሆናቸውን አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ጽፈዋል ፡፡ እኚህ ጄኔራል ቀደም ባለው ግዜ በምዕራባዊው የኢትዮጽያና ሱዳን ድንበር አካባቢ አዛዥ ሆነው አገልግለዋል ፡፡ ከፍተኛ የውጊያ ልምድ ያላቸው ጄኔራሉ በወታደሩ ዘንድም ከፍተኛ የፖለቲካ ክብር አላቸው ነው የሚባለው ፡፡ ኢሳያስ ህዳር ወር ላይ ሲያስሯቸው በወታደሩ መካከል ክፍፍል እንደሚፈጠር ወይም የተቃውሞ የመገለጥ ምዕራፍ ሊጀመር እንደሚችል ስሌት ወስጥ አልገባም ነበር ፡፡ ጄኔራሉ ሲታሰሩ የተኳቸው ጄኔራል ተክላይ/ ማንጁስ ክፍላይ ይባላሉ ፡፡ እናም በቋፍ ላይ የሚገኙት ኢሳያስ ከሞቱ ወይም ጤናቸው የከፋ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ከታወቀ ፊሊጾስ የማንጁስን ተግባር ለመገደብ ሲሉ ከታማኝ ወታደሮቹ ጋር ይህን ስራ ሊመሩ ይችላሉ - እንደ ተንታኞች መላምት ፡፡ እንደ ብዙዎች እምነት በቦታው ላይ ጥቂት ወራት ያሳለፉት ማንጁስ የኢሳያስን ቦታ ሊሸፍኑ ይከብዳቸዋል ፡፡ ፊሊጾስ ቦታውን ከተረከቡ ግን በሀገሪቱ ጠንካራ ወታደራዊ ተቋም ይዘረጋል ፡፡

ሁለተኛው ግምት ያነጣጠረው ኮማንደር ሳላህ ኦስማን ላይ ነው ፡፡ እኚህ ሰው ከ1998- 2000 ከኢትዮጽያ ጋር በተደረገው ደም አፋሳሽ ጦርነት እንደ ጀግና ይቆጠራሉ ፡፡ እንዴት ቢሉ በውጊያው ወቅት ደቡባዊ አሰብን ለቀው እንዲወጡ ቢታዘዙም ትዕዛዙን ባለመቀበል የኢትዮጽያን ጦር ወደ ኃላ እንዲያፈገፍግ አድርገዋልና ፡፡ እኚህ ሰው ሌላው የሚታወቁበት ጉዳይ ሀገሪቱ ወደ ዴሞክራሲያዊ ጎዳና እንድትገባ ለመንግስታቸው ሀሳብ የሚያቀርቡ መሆናቸው ነው ፡፡
እነዚህ ሁለት ወታደሮች የሰውየው አዲሱ ጠላት ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገመት እንጂ ኢሳያስ በቁጭትም ሆነ በህመም ጥላ ስር ሆነው ጠላታቸው ላይ ማንባረቅ አልፈለጉም ፡፡ በመሆኑም አዲሱን ጠላት በግምት እንጂ በበቂ ማስረጃ ማረጋገጥ አልተቻለም ፡፡

የሰውየው ጅራፍ !
ኢሳያስ አፈወርቂ ‹ ጭር ሲል አልወድም ! › የሚለውን ኢትዮጽያዊ ዜማ ይወዳሉ እየተባሉ ይታማሉ ፡፡ የመን ያስጮሁት ጥይት ቀዝቀዝ ካለ ጅቡቲ ፣ የጅቡቲው መፋዘዝ ሲጀምር በሶማሌ ፣ የሶማሌው ቃናው መጎምዘዝ ሲጀምር በባድመ መስማት አለባቸው ይሏቸዋል - ስም አጥፊዎች ፡፡ ይህ ሁሉ ካልሆነ ደግሞ አስመራ ላይ እውነተኛ ጅራፍ ገምደው ያስጮሁታል አሉ ፡፡ ጅራፉ በጣም ካቆሰላቸው መካከል ሁለቱን የነጻነት ልጆች ፕሬስ እና ሃይማኖትን መጠቃቀስ ይቻላል ፡፡

ሀ . የፕሬስ ነጻነት

አንድ አይናማው የኤርትራ ፕሬስ ወደ ማየት የተሳነው የተቀየረው መስከረም 2001 ነበር ፡፡ ቀደም ብሎ 11 የሚደርሱ የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት በንቃት ሲሳተፍ በነበረ አንድ የግል ጋዜጣ ላይ መንግስት ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ እንደሚገባው የሚያስገነዝብ ጽሁፍ አወጡ ፡፡ ፈጣን ምላሽ በመስጠት የሚታወቁት ኢሳያስ 11 ዱን ባለስልጣናትንና ደብዳቤውን ያተሙ 10 ጋዜጠኞችን ወህኒ ቤት ወረወሯቸው ፡፡

ከዚያ የግል ሚዲያ ከህትመት ዉጪ እንዲሆኑ ተደረገ ፡፡ ማንኛውም የህትመት ዉጤት ከመታተሙ በፊት በመንግስት የጹሁፍ ዘበኞች እንዲመረመር ታዘዘ ፡፡ ጋዜጠኞች በሚደረግባቸው ወከባና የማስፈራራት ተግባር ከሀገር መሰደድ አበዙ ፡፡ ዓለማቀፉ ፕሬስ ፋውንዴሽን በ 2012 ባወጣው መረጃ መሰረት ኢሳያስ 30 የሚደርሱ ጋዜጠኞችን አስረው በመጥፎ ሁኔታ ላይ እንዲገኙ አድርገዋቸዋል ፡፡ ‹‹ ማንኛውንም የውጭ ሚዲያ መረጃ እንዲያገኝ አንፈቅድም ›› የሚሉት ኢሳያስ ሀገራቸው ፍቃድ የምትሰጠው ስለ ሀገሪቱ መልካም ገጽታ ለማውራት ፍቃደኛ ለሚሆኑት ብቻ መሆኑን በአንድ ወቅት ተናግረዋል ፡፡ በአንዳንድ የተመረጡ ካፌዎች ውስጥ ኢንተርኔት የሚጠቀሙ ዜጎች ጥብቅ ክትትል ይደረግባቸዋል ፡፡ በቅርቡ የወጣው የፕሬስ ነጻነት ኢንዴክስም በኤርትራ የመናገር ፣ የመጻፍና የመሰብሰብ መብቶች የተከለከሉ በመሆናቸው የመጨረሻውን 179 ኛ ደረጃ ለማግኝት ግድ ብሏታል ፡፡ ይህም ዜጎች ምን ያህል በአፈና እየተሰቃዩ መሆኑን ያመለክታል ፡፡

ለ . የሃይማኖት ነጻነት

ቁስለኛው ሃይማኖት በኤርትራ ህዝብ ሲመነዘር 40 ከመቶው ክርስትያን 60 ከመቶው ደግሞ የሱኒ ሙስሊሞች ሆኖ ይገኛል ፡፡ ከክርስትያኑ ውስጥ 24 ከመቶው ኦርቶዶክስ ፣ 10 ከመቶ የሮማን ካቶሊክ ፣ 4 ከመቶው ፕሮቴስታንትና ጆባ ሲሆኑ 2 ከመቶው እምነት የለሽ ነው ፡፡ መንግስት ዕውቅና ሰጥቶ የመዘገባቸው ኦርቶዶክስ ፣ ሉተራን ፣ ሱኒ ሙስሊም እና ሮማ ካቶሊክ ናቸው ፡፡
የኢሳያስ መንግስት ጅራፍ ግን ዕውቅና በሌላቸውም ሆነ ባላቸው ጀርባ ላይ እያረፈ በመሆኑ 3 ሺህ የሚደርሱ ክርስትያኖች እስር ቤቶችን አጣበዋል ፡፡ ብዙዎች ወደ እስር ቤት የተወረወሩት ደግሞ በብሄራዊ ውትድርና መሳተፍ ባለመፈለጋቸው ነው ፡፡ በተለይም እምነታቸው ውትድርናን የማይፈቅድላቸው ጆባዎች ዋነኛው የጥቃቱ ዒላማ ሆነዋል ፡፡

ኢሳያስ በ 1994 ባወጡት አዋጅ ለጆባ እምነት ተከታዮች የዜግነት ፍቃድ አይሰጥም ፡፡ የመንግስት ሰራተኛ ከሆኑ ከስራ ይባረራሉ፣ የንግድ ፈቃዳቸው ይቀማል ፣ ከመንግስት ቤት እንዲባረሩ ይደረጋል ፡፡ በርግጥ ሰውየው ጥርሱን የነከሰባቸው ኤርትራን ለማሰገንጠል ድምጸ ውሳኔ ያዘጋጁ ግዜ ነበር ፡፡ ያኔ እነሱ ከፓለቲካ ተሳትፎ ዉጪ ነን ቢሉም ‹ ማን በሞተለት ሀገር ላይ ማን ገለልተኛ ይሆናል ! › በሚል ስሌት እንዲገረፉ ፣ እንዲገለሉና እንዲታሰሩ ሀገራዊ አድማ አስደርገውባቸዋል ፡፡
የመንግስትን ጣልቃ ገብነት የኮነኑት ፓትርያክ አቡነ አንቶኒዮስ ከቦታቸው ተነስተው የመንግስት ሹመኛ ጉብ ብሏል ፡፡ ከ 1700 በላይ የሚሆኑ ካህናት ከቤተክርስትያን አገልግሎት እንዲገለሉ ተደርገዋል ፡፡ የሃይማኖት እስረኞች ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ ወይም እንዲተው ባዶ እግራቸውን በሹል ድንጋይና በእሾህ ላይ በቀን ለአንድ ሰዓት እንዲራመዱ ይደረጋል ፡፡

የሰውየው ካምፕ

ሳዋ ሀምሌ 1994 ስራ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ማለትም ግንቦት ወር ላይ ኢሳያስ የብሄራዊ ውትድርናን ጠቀሜታ አስመልክቶ ሶስት መሰረታዊ ነጥቦችን አስቀመጡ ፡፡
. ሀገሪቱን ከጥቃት ለመከላከልና አንድነት ለመፍጠር
. ወጣቱ ክፍል ለስራ ያለውን አዎንታዊ ስነልቦና ለማጠናከር
. የሻዕቢያን የ 30 ዓመት ልምድ ፣ ማንነትና ውርስ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ
በዚሁ መሰረት በአዋጅ ቁጥር 82/1995 አንቀጽ 8 መሰረት ሁሉም ዕድሜው ከ18 – 40 ዓመት የሆነው ዜጋ ብብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት ውስጥ ለ18 ወራት ማገልገል ግድ ይለዋል ፡፡

ኢሳያስ የሀገሪቱ ዜጎች በተለይም ወጣቱ በአመርቂ ሁኔታ እየተሳተፈ አለመሆኑን በግምግማ ሲያረጋግጡ ‹‹ ብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት ያልገባ ተማሪ የከፍተኛ ትምህርቱን መከታተል አይችልም ›› የሚል ህግ አወጡ፡፡ በመሆኑም የሁለተኛ ደረጃ የመጨረሻ ትምህርት በሳዋ እንዲሰጥ ተደረገ ፡፡ ተማሪው ለግዜው በዚህ ዘዴ ተጠፍንጎ ካምፑን ቢያጣብብም በቦታው የነበረው ኢ - ሰብዓዊ አያያዝ ፣ እስራትና ግርፊያ የሰፋ ጥላቻና ስደት እንዲባባስ አድርጓል ፡፡ በተለይም ወጣት ሴቶች በወታደሮች ፣ አሰልጣኞችና አዛዦች መደፈር እጣ ፈንታቸው ሆነ ፡፡ በዚህም የተነሳ ሳዋ ‹‹ የወሲብ ካምፕ ›› የሚል ስያሜ እስከማግኘት ደረሰ ፡፡

ይህም ሴቶች ከሳዋ ለመዳን ሌሎች ያልተገቡ ዘዴዎችን እስከመፍጠር አደረሳቸው ፡፡ እነዚህ ህሊናን የሚነኩ ዘዴዎች ሆን ብሎ ማርገዝ ፣ ለምኖም ቢሆን ማግባት እና ትምህርትን ከ 10ኛ ና 11 ኛ ክፍል ማቋረጥ ናቸው ፡፡ በዚህም ምክንያት በሳዋ የሴቶች ቁጥር ከወንዶች በሶስት እጥፍ እስከማነስ ደርሷል ፡፡

በአጠቃላይ እኔና ሀገሬን በምስራቅ አፍሪካ ግዙፍና ተጽዕኖ ፈጣሪ ያደርጋል ብለው የገነቡት ሳዋ በሰልጣኙም ሆነ ተራውን በሚጠብቀው ትውልድ አስፈሪ ምስል በመፍጠሩ የታሰበውን ግብ ሊመታ አልቻለም ፡፡ ባለፉት 13 ዓመታት ከአንድ ሚሊየን ዜጎች በላይ ተሰደዋል ፡፡ ሳዋን የኢሳያስ ከፍተኛ ባለስልጣናትና የፓርቲ አባላት ከፍተኛ የገቢ ማሰባሰቢያ ምንጭ እያደረጉት ይገኛሉ ፡፡ ከሀገር ውስጥ ወደ ሱዳን ፣ ግብጽና እስራኤል የሚሰደዱ ዜጎችን ከድንበር ጥበቃዎች ለማሳለፍ በሚል ከ 3 – 20 ሺህ ዶላር ይቀበላሉ ፡፡

የሰውየው መልኮች

 
የኢትዮጽያ ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ከአልጀዚራ ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ ‹‹ የኢሳያስ መልካም ፍቃድ ካለ አስመራ ድረስ ሄጄ በሰላም ጉዳይ እደራደራለሁ ›› ብለው ነበር ፡፡ አንዳንዶች ጥያቄው የጠ/ሚኒስትሩን ቀናነት ያሳያል ሲሉ ሌሎች ሀሳቡን ለማቅረብ የመቻኮላቸው ፣ ጥያቄው ከጋዜጠኛው ሳይመጣ ነገር አስታከው መመለሳቸውን አልወደደውም ነበር ፡፡ 

ሰውየውም እንዲህ አሉ  ‹‹ ኤርትራ ስልጣን ላይ ካሉ ግለሰቦች መቀያየር ጋር የምታያይዘው አንዳችም ነገር አይኖርም … ››
ይህን የመሰለ አስገራሚ ምላሽ እንደሚመጣ በአንዳንዶች መገመቱ ትክክል ነበር ፡፡ ለምን ከተባለ የኢሳያስን ተቃራኒ መልኮች በልምድ ከማየት ፡፡ ሰውየው ተቃራኒ ጉዳዮችን በማከናወን አቶ መለስን ጨምሮ አፍሪካ ህብረትን ፣ ተመድንና አሜሪካንን ሲያበሽቁ መኖራቸው  ይታወቃል ፡፡ አቶ ሃይለማርያም የኢሳያስ ምለሽ ከተሰማ በኃላ በፓርላማ ሪፖርት ሲያቀርቡ የሰውየውን አተራማሽነት አስረግጠው ተናግረዋል ፤ አላርፍ ካለ ደግሞ ተመጣጣኝ ቅጣት እንደሚጠብቀው በአጽንኦት አስገንዝበዋል ፡፡ መቼም አቶ ሃይለማርያም ስለ ሰላም በሰበኩ ማግስት ይህን የመሰለ ሃይለ ቃል ለመተንፈስ የተገደዱት ዝም ብሎ አይደለም - ተረኛው የኢሳያስ በሻቂ በመሆናቸው እንጂ ፡፡

አቶ ኢሳያስ ያልተጠበቁ ወይም የማይገቡ ንግግሮችን ብቻ ሳይሆን ተግባራትንም በማከናወን ይታወቃሉ ፡፡ እንደሚታወቀው ኢሳያስ በ2008  ከኢራን ጋር ሁነኛ ስምምነት ተፈራርመዋል ፡፡ በስምምነቱ መሰረት ኢራን በአሰብ ወታደራዊ ተቋም በመገንባት የነዳጅ ማደያውን ስትጠብቅ ኤርትራም ለዚህ ልግስናዋ ገንዘብና ወታደራዊ መሳሪያዎችን ታገኛለች ፡፡ ይችው ሀገር የኢራንን የኒውክለር ፕሮግራም በመደገፏ ብቻ 35 ሚሊዮን ዶላር ተሸልማለች ፡፡ በሌላ በኩል እስራኤል በዳህላክ ደሴት ፣ በምጽዋና በአምባይሶራ አካባቢ የባህር ኃይል ተቋም ለመገንባት ያቀረበቸውን ጥያቄም ሰውየው በደስታ ተቀብለዋል ፡፡ ኢራንና እስራኤል የማይታረቅ የነገር ኮሮዋጆችን ለዘመናት የተሸከሙ ባላንጣዎች ናቸው ፡፡ ታዲያ ኢሳያስ ለሁለቱ ተቃራኒ ሀገሮች በአንድ አካባቢ የስራ ፍቃድ ሰጥተው የኤደን ባህረ ሰላጤ ሌላ የፍጥጫና የግጭት ማዕከል እንዲሆን ለምን ፈለጉ ? የቁርጥ ቀን አጋር ለሆነቸው ኢራን ፍላጎት ለምን ተገዢ አልሆኑም  ? የሚሉ ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀርም ፡፡

የእስራኤል ዓላማ የቀይ ባህር አካባቢንና የኢራንን እንቅስቃሴ በመሰለል መረጃ ማሰባሰብ ነው ፡፡ የኢሳያስ ግብ ግን ብዙ ነው ፡፡ የእስራኤልን ጓደኛነት በመጠቀም የአሜሪካንን ሆድ ማባባት ይፈልጋሉ ፡፡ ለእደሳ ፡፡ ብዙ ግዜ ከኢትዮጽያ በሚወሰድባቸው የአየር ኃይል ብልጫ ይንገበገባሉና አየር ኃይላቸውና ዘመናዊና ብድር መላሽ ማድረጊያው ግዜ አሁን መሆኑን ያልማሉ ፡፡ ኤርትራን ወደ እናት ሀገሯ እንመልሳለን በማለት ፖሊሲ ቀርጸው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ከእንግዲህ የሚጋፉት ከእነማን ጋር መሆኑን በእግረ መንገድ እንዲያውቁትም ይፈልጋሉ ፡፡ ኢሳያስ ይህ ዓላማቸው እንዲሳካላቸው እንጂ የባንጣዎቹ መፋጠጥ አጀንዳቸው አይሆንም ፡፡ ምክንያቱም ነብር መልኩን አይቀይርምና …

የሰውየው መጨረሻ
ከተራራ የሚገዝፉ ሀሳቦችና ውጥኖች ቢኖራቸውም ቀስፈው የያዟቸው ህመምና ጭንቀት አሜኬላ መሆናቸው አይቀርም ፡፡ አድልዋና መገለል ያብቃ በሚባልበት ዘመን አሸባሪና አተራማሽ ተብለው በተመድ በተጣለባቸው እገዳ ምክንያት ከዓለማቀፉ ማህበረሰብ ተገለዋል ፡፡ ይህም ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን እየቦረቦረው ይገኛል ፡፡ እገዳው እንዲነሳላቸው ቢጠይቁም ትኩረት የሰጣቸው ወዳጅ አላገኙም ፡፡ 30 ዓመት ደሙን አፍሶ ነጻነት ያስገኘለት ህዝብ የጀግንነት ውርሱን በ ‹‹ ሳዋ ›› አማካኝነት በጸጋ መቀበል ሲገባው ክህደት መፈጸሙ መጠቃታቸውን ያንረዋል ፡፡ በፕሬስና ነጻነት አፈና ፣ በአምባገነንነት የመጨረሻዋ ሀገር ኤርትራ ነች እያሉ ዓመታዊ ሰንጠረዥ የሚለጥፉ ክፍሎች ተግባር ያንገበግባቸዋል ፡፡

ሰውየው ተወጥረው ተይዘዋል ፡፡
በአንድ በኩል ለስለላ በሌላ በኩል የውጭ ምንዛሪ / Remittance man / በመላክ ተሳትፎ እንዲያበረክቱ አውሮፓና አሜሪካ ከተላኩ ወገኖች ገሚሱ ተልዕኳቸውን ዘንግተው በየአደባባዩና በየኤምባሲው ‹‹ ኢሳያስ ይውደም ! ›› የሚል መፈክር አሰሚ መሆናቸው ሆድ አስብሷቸዋል ፡፡

ያልታገሉበትን ስልጣን ለመቀራመት በየሀገሩ ‹‹ ተቃዋሚ ›› ብለው ራሳቸውን ያደራጁ ማፈሪያ ዜጎች ተግባር ሳያንስ የሚያምንባቸው ጦር ሰራዊት መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ ሴራ መጎንጎን ደረጃ መድረሱ ጩህ ጩህ ያሰኛቸዋል ፡፡
የነዚህ ሁሉ ድምር ዉጤት የደም ብዛትን ያፋጥናል ፡፡ ውጥረትን ያንራል ፡፡ የአእምሮ ሽቦዎችን ያላላል ፡፡ ፍርሃትና ጥርጣሬን ያነግሳል ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ሰውየው እንደ ሀገራችን ድሃ ጎጆ ሺህ ቦታ ላይ ተሰነጣጥቀዋል ፡፡ እናም የቱ ተይዞ የቱ ይለሰናል ? አንዱን ስንጥቅ ሲደፍኑ በመድረቅ ላይ ያለው ይንጣጣል ፡፡ በመሆኑም ነባሩ ህመም ሊቀለበስ ወደሚችል ጤናማ አካልና አስተሳሰብ የመምጣቱ ዕድል የመነመነ መሆኑን ይጠቁማል ፡፡

ሌላኛው መጨረሻ ‹‹ የተነቃነቀ ጥርስ መውለቁ አይቀርም ! ›› የሚለውን ነባራዊ እውነት ከማክበር የሚነሳ ነው ፡፡ የጭቆናና የግፍ ጽዋ ሲፈስ ደካሞች ጠንካራ ይሆናሉ ፡፡ እዚህና እዚያ የወደቀው የደካሞች ድር እያበረ አስቸጋሪውን ተኩላ ለማሰር ይበቃል ፡፡ ሰውየው ምናልባት የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማቆም የሚችሉት ህዝባዊውንና አዲስ ሀሳቦችን ይዘው ቢያንስ 270 ዲግሪ መዞር ከቻሉ ነው ፡፡ ይህ እውነት ደግሞ ለአምባገነኖች ሰርቶ እንደማያውቅ ከልምድ እናውቃለን ፡፡ እናስ ? እናማ የሰውየውን አጓጉል መጨረሻ ለመመልከት የግድ ቴሌስኮፕ የማያስፈልግበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ፡፡
ክፍሉ ሁሴን የተባሉ ጸሀፊ ‹‹ በጎ ምኞት ለወዲ አፈወርቅ  ›› በሚል ርዕስ ያቀረቡትን ግጥም እንደ ማጠቃለያ ሳይሆን እንደ አስደማሚ ምርቃት  በመቁጠር ርዕሰ ጉዳዬን ላጠናቅ

የማይቀረው የኢሳያስ አፈወርቂ ሞት
በምን ይሆን በጉበት ወይስ በጥይት
በእናቴ ወገን የሆኑት
መነኩሴው አያቴ እንደነገሩኝ ጥንት
ምን ቢሆን ሃጢያተኛ
እንደ ዳቢሎስ ከዳተኛ
ይሰረይለታል አሉ
የሰራው ግፍ በሙሉ
በሰው እጅ ከጠፋ ነፍሱ ፡፡
እንዲህ ከሆነ ነገሩ
በሰማይ ቤት የቅጣት ድልድሉ
ይንቀልቀል ዘንድ ዘላለም በእቶን እሳት
ሰበበኛ በሆነው ጉበቱ ምክንያት ፡፡


ማስታወሻ፡- ይህ ፅሑፍ በቁም ነገር መፅሔት ቅፅ 12 ቁጥር 147 ላይ የወጣ ፅሑፍ ነው፡፡ ፅሑፉን በሌላ ሚዲያ ላይ የምትጠቀሙ ከሆነ ምንጩን እንድትጠቅሱ ትለመናላችሁ፡፡