[ ICFJ ከጤና ጥበቃ ሚ/ር ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የክትባት ውድድር ላይ ያሸነፈ ጽሁፍ ]
አምቦ
ከአዲስ አበባ በ 95 ኪሜ በቅርብ ርቀት የምትገኝ
የደስ ደስ ያላት ከተማ ናት ፡፡ አንድ ሰው ከተማዋ በጣም ጎልታ የምትታወቅበትን ጉዳዮች ቢያስስ ቢያንስ ሁለት ነገሮችን ጎልተው
ያገኛቸዋል ፡፡
አንደኛው በርካታ ኢትዮጽያዊያን ስብሰባ ውለው
ምሳ ከተጋበዙ በኃላ ለመጠጥነት በአንድ ድምጽ የሚመርጡት አምቦ ውሃ መሆኑን ነው ፡፡ በተለምዶ ምግብ ያንሸራሽራል ፣ ያስገሳል
፣ የውሃ ጥምን ይቆርጣል የሚባለው ይህ አንጋፋ መጠጥ የሚመረተው በዚህ ከተማ ነውና ፡፡ ሁለተኛው ሀገሪቱን ለ 22 ዓመታት እያስተዳደራት
ከሚገኘው የኢህአዴግ መንግስት ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው ፡፡ የዛሬው ኢህአዴግ የትላንትናው ወያኔ በመጨረሻው ሰዓት ደርግን በየከተማው
እየጣለ የመጣው ፈጣን ማርሽ በመጠቀም ነበር ፡፡ እዚች ትንሽ ከተማ ሲደርስ ግን ሩጫውን አቁሞ በአንደኛ ማርሽ ‹ ባላንስ › ለመስራት
ተገደደ ፡፡ ህዝቡ ሀገር ሻጭና ከፋፋይ ፖለቲካን የሚያራምድ አማጺ ወደ መሃል ሀገር አናስገባም በማለት በጦርነት ገትሮት ያዘው
፡፡ ሀገሬው በውጊያው ብዙ እንደጣለ ሁሉ ከእሱም ወገኞች ብዙውን አጣ ፡፡ እናም በአምቦ ከተማ ይህን ግብግብ የሚያሳይ ህዝባዊ
ኀውልት መታየት ባይችልም በህዝቡ ልቦና ግን በማይታይ ማህተም የተቀረጸ ልዩ ታሪክ አለ ፡፡
ወ/ሮ መገርቱ በዚች የውሃና ደም ታሪክ ባላት
ከተማ መኖር ከጀመሩ 38 ዓመታትን አስቆጥረዋል ፡፡ የሁለት ሴትና አንድ ወንድ ልጅ እናት ናቸው ፡፡ የሶስት ዓመት ዕድሜ ያለው
የመጨረሻ ልጃቸው በኩፍኝ በሽታ መያዙን ቢያወቁም ወደ ጤና ጣቢያ ማምራት አልፈለጉም ፡፡ ህጻኑ ላይ የሚታየው የሳል ፣ ንፍጥ ፣
ትኩሳትና ሽፍታ ህመሞች ያን ያህል አላስጨነቃቸውም ፡፡ የከተማው ህዝብ ያለው የጀግንነት ስሜት ተጋብቶባቸው አይደለም - የቆየ
የህክምና ልምዳቸው እንጂ ፡፡ ኩፍኝ ለሳቸውም ሆነ ለቀድሞ ቤተሰቦቻቸው ተራና የማይቀር የልጅ በሽታ በመሆኑ እንዴት ማጥፋት እንደሚቻልም
በአግባቡ ያውቃሉ ፡፡
እናም የእናት - አባታቸውን ከራማ እያስታወሱ
ትርክክ ባለው የከሰል ፍም ላይ ደግመው ደጋግመው የተለያዩ ጢሳ ጢሶችን ያጉራሉ ፡፡ ትንሷ የጭቃ ቤት ከአቅሟ በላይ የሆነ የጢስ
ምርት ማምረት ጀመረች ፡፡ ሁለቱ ኩፍኝን በግዜያቸው ያሸነፉ ሴት ልጆቻቸው በስራ ተጠምደዋል ፡፡ አንዷ ቡና ትቆላለች ፣ ሌላዋ
ገና ያልበረደው ትኩስ ቂጣ ላይ በዘይት የተለወሰ በርበሬና ኑግ ትለቀልቃለች ፡፡ ጎረቤቶችና የቅርብ ዘመዶችም የውጭ በር ላይ ተኮልኩለው
ፈጣሪ ለህጻኑ ፈጣን ምህረት እንዲልክለት ይለማምናሉ ፡፡
የቡናው ስነ ስርዓት ከተፈጸመ በኃላ ቆሎ ፣ ቂጣ
፣ ኑግ ፣ ለምለም ሳር የያዙ ሴቶች ምህረት እየለመኑ አቅራቢያቸው ወደሚገኝ ወንዝ አመሩ ፡፡ ወንዙን ከተሻገሩም በኃላ የያዙትን
ወደ ወንዙ ዳር ወርውረው ተመለሱ ፡፡ በቃ ! በእምነቱ አስተሳሰብ መሰረት በኩፍኝ የተያዘው ልጅ በቅርብ ቀን ይፈወሳል ፡፡ ምክንያቱም
የህጻኑ ገላ በሳሩም በቂጣውም በአሪቲውም ተሻሽቶ የተወረወረ በመሆኑ ጦስ ጥንቡሳሱም እዛው ተጣብቆ ይቀራል ፡፡
ፀለምት
የአማራ ክልል አንድ አካል የሆነች ከአዲስ አበባ
በ 800 ኪ.ሜ ርቀት አካባቢ ላይ የምትገኝ ቆዛሚ ምስኪን ከተማ ናት ፡፡ አቶ ጥጋቡ በዚችው ከተማ ተወልደው ያደጉ የመንግስት
ሰራተኛ ናቸው ፡፡ ዛሬ አድራሻቸው ጎንደር ቢሆንም ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅ በየግዜው ወደ ከተማዋ ይመላለሳሉ ፡፡
የአቶ ጥጋቡ ሀገር ሰው ከወ/ሮ መገርቱ ሀገር
ሰው የሚመሳሰልበትም የሚለያይበትም መንገዶች አሉት ፡፡ ፀለምቶች ኩፍኝን ‹ ፎረፎር › እያሉ ሲጠሯት ብዙዎቹ ሀኪም ቤት መሄድ
ሳያስፈልግ ልትድን የምትችል ሞኛ ሞኝ በሽታ መሆኗን ይስማማሉ ፡፡ ከወ/ሮ መገርቱ ሀገር ህዝብ ግን የሚለዩት በሰፈሩ አንድ ህጻን
በፎረፎር ታመመ ከተባለ አስገራሚ የመከላከል ስራ መስራት መቻላቸው ነው ፡፡ ከነ ስያሜው መድሃኒቱን ‹‹ ክትባት ›› ነው የሚሉት
፡፡
በፍጥነት ወደታመሙት ልጆች በመሄድ ከሽፍታው ላይ
መግል እያፈረጡ ይወስዳሉ ፡፡ ከዚያም ያልታመሙ ልጆች የግራ እጅ በምላጭ ይቀደድና መግሉ ከዝንብ ጋር ተጨፍልቆ በጨርቅ እንዲታሰር
ይደረጋል ፡፡ አቶ ጥጋቡ 50ኛ የዕድሜ ሻማቸውን ቢለኩሱም ዛሬም
ይህ የክትባት ስርዓት በአካባቢው እንደሚከናወን ይገልጻሉ ፡፡ ግራ እጃቸውን አንስተው አሳዩኝ ፡፡ ለባህላዊው የኩፍኝ ክትባት የተቀደዱት
ጠባሳ አሁንም የታሪክ አሻራውን ይዞ ግዜ ሳያደበዝዘው ይታያል ፡፡
‹‹ የአካባቢውን ተወላጆች እጅ እያነሳህ ብታይ
ይህን ምልክት ታያለህ ›› በማለት በፈገግታ መለሱልኝ ፡፡
‹‹ የሆነውስ ይሁን ?! የዝንቧ ምስጢር አልገባኝምና
ጠቀሜታው ምንድነው ? ›› ስል ጠየቅኳቸው
‹‹ ልጅ እያለሁ አይገባኝም ነበር ፡፡ አሁን
የሚመስለኝ ግን ዝንብ በሽተኛዎች ደጃፍ መድረሷ ስለማይቀር የበሽታው ፈሳሽ አለባት በሚል ነው ›› አሉና ቅዝዝ ብለው ወደ ኃላ
በሃሳብ ተመነጠቁ ፡፡ ከአፍታ በኃላም የሚያወሩልኝ እንባ በሚተናነቅ የሳቅ ድምጽ ነበር ፡፡ ‹‹ በጣም ይገርመኛል ፤ መድሃኒቱ
እጅ ላይ ሊታሰር ሲል ዝንብ አድኑ ! የሚባሉት ህጻናት ናቸው ፡፡ ግማሹ የሚበር ዝንብ በትንሽ እጁ ለመጨበጥ ሲታገል ፣ ሌላው
ዝንብ ያዝኩ ብሎ ዕቃ ሲሰብር ፣ ግማሹ ፊቱ ላይ ዝንብ ለመደፍጠጥ ፊቱን ሲጠፈጥፍ ይውላል … ››
ሳይንስ እንደሚለው ከሆነ የኩፍኝ ክትባት የሚሰራው
ከተዳከመ የ ‹‹ ሚዝልስ ቫይረስ ›› ነው ፡፡ የአቶ ጥጋቡ ሀገር ህዝብም ባህላዊውን መንገድ ይከተል እንጂ መድሃኒቱ ያለው በሽታው
ላይ መሆኑን አውቋል ፡፡ ሌላው ባህላዊው ስርዓት በኩፍኝ የተያዙ ልጆችን ለመጠየቅ የሚጣለው ገደብ ነው ፡፡ በነአቶ ጥጋቡ ሀገር
መሰረት የግብረ ስጋ ግንኙነት ያደረጉ ሰዎች ታማሚዎችን ወደ ቤት ሄደው መጠየቅ አይችሉም ፡፡ ምክንያቱም ይህን ሁሉ ልፋት ያረክሳሉና
፡፡ በነወ/ሮ መገርቱ አካባቢ ኩፍኝ አንዴ ወንዝ በመሻገሩ ተመልሶ ስለማይመጣ ማንኘውም ሰው ቤት ገብቶ ቢጠይቅ ችግር የለውም ፡፡
ኩፍኝን ‹‹ አለሜ ›› እያሉ በሚጠሯት ‹‹ አለሜ በዓለም ያውጣሽ ! ›› እያሉ በሚለማምኗት የአዲስ ዘመን አካባቢ ነዋሪዎች ደግሞ
በሽተኞች በር ላይ የሆነ ቅጠላ ቅጠል ነገር ይሰቀላል ፡፡ ይህን ምልክት የሚያይ እንግዳም ወደ ውስጥ ከመግባት ይታቀብና ደጅ ሆኖ
ምህረት ይጠይቃል ፤ ከፈለገ ደግሞ ስለ ቀሪው ቤተሰብ ፣ ስለ እርሻና የዝናብ መጥፋት፣ ስለ እነ ላሜቦራ ጤንነት ሁሉ ድምጹን ከፍ
አድርጎ መወያያት ይችላል ፡፡
አዲስ አበባ
ቆሼ ፡፡
ይህን የከተማውን ቆሻሻ በሙሉ ሰብስቦ ለመያዝ
የተስማማውን ሰፈር ‹‹ ገብረ ክርስቶስ ›› ማለት የሚቀናቸውም አሉ ፡፡ በአካባቢው የስጋ ደዌ ህክምና መስጫ ሆስፒታል ከመኖሩ
ጋር ተደራርቦ በርካታ በስጋ ደዌ በሽታ የተጠቁ ሰዎች ይኖሩበታል ፡፡ ስያሜው የመነጨው ግን በአካባቢው የአቡነ አረጋዊ / ገብረ
ክርስቶስ / ቤተክርስትያን ከመገኘቱ አንጻር ነው ፡፡
በዚህ አካባቢ የሚኖሩ በሽተኞች ከሁሉም የሀገሪቱ
ጥግ ለህክምና ሲሉ የሚፈልሱ ናቸው ፡፡ ብዙዎቹ ታክመው ወደ ትውልድ ሀገራቸው ከመመለስ ይልቅ እዚሁ መቅረትን የሚመርጡ ናቸው ፡፡
የዚህም አካባቢ ሰዎች ልክ እንደ አምቦ ሰዎች በሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ይታወቃሉ ፡፡ አንደኛው ከበሽታቸው ከተፈወሱ የማንንም ድጋፍ
ሳይጠብቁ ራሳቸውን ለመቻል የሚያደርጉት ያላሰለሰ ጥረት ነው ፡፡ እንዳቅማቸው ቤት ተከራይተው ሽንኩርትና ጎመን ለመቸርቸር ወይም
ጠላና አረቄ ለመሸጥ የማይቦዝኑ መሆናቸው ልዩ ያደርጋቸዋል ፡፡ በሽታቸው ጎድቷቸው አካላቸው መድከም ከጀመረ ደግሞ የገበያ ጥናት
በማጥናት በልመና ስራ ይሰማራሉ ፡፡ እነሱን ጠጋ ብላችሁ ብትጠይቁ ልመናን አስጸያፊ ሳይሆን ራስን ለመቻል የሚደረግ መፍጨርጨር
በማለት ነው ብይን የሚሰጡት ፡፡ ሁለተኛው ልዩ ባህሪያቸው በህክምናና ጤና ዙሪያ ለሚነገሩና ለሚሰሩ ጉዳዮች የተለየ ትኩረት ሰጪ
የመሆናቸው ጉዳይ ነው ፡፡ ምናልባትም ስጋ ደዌ የፈጠረባቸው ተጽዕኖ ወይም በሌላ መልኩ ያስገኝላቸው የአዳማጭነት ጸጋ ሊሆን ይችላል
፡፡
በቅርቡ ወደ አረብ ሀገር የሚጓዘውን ባልደረባዬ
ቤተሰብ ‹‹ እንዴት ይዟችኃል ? ›› ለማለት በአካባቢው ተገኝቼ ነበር ፡፡ በርካታ ሴቶች ተሰብስበው ዳቦ ቆሎ ፣ ኩኪስ ፣ ቋንጣ ፣ የመሳሰለውን ቀለብ በመስራት ስራ ላይ ተጠምደዋል
፡፡ የኢትዮጽያ ቴሌቪዥን የሰባት ሰዓት ዜና እወጃ ላይ ስለ ሶስተኛው የአፍሪካ ክትባት ሳምንት በስፋት ሲያወራ የሴቶቹ ጫጫታ ቀነሰ
፡፡ የዘንደሮው ክትባት ‹‹ ህይወት እናድን ፣ አካል ጉዳተኝነትን እንከላከል ፣ እንከተብ ›› በሚል ጭብጥ ላይ ይተኮረ ነበር
፡፡ ከዜናው በኃላ የሴቶቹ አብይ መወያያ ጉዳይ ክትባት ሆነ ፡፡
አንዳንዶች በክትባት በርካታ ህጻናት ከሞት እየተረፉ
መሆኑን በመጥቀስ መንግስትን ማወደስ ጀመሩ ፡፡ አንድ እናት ‹‹ ልጄ የደነቆረው በመከተቡ ነው ! ›› በማለታቸው ቤቱ በድጋፍና
ተቃውሞ ተጋጋለ ፡፡ ‹‹ ከክትባት በኃላ የአእምሮ በሽተኛ የሆነ ልጅ አውቃለሁ ›› የምትል ወጣት ሴት ብቅ አለች ፡፡ ሌላ ወጣት
‹‹ እንዴት ፊደል ቆጥረሽ እንዳልተማረ ሰው በግምት አስተያየት ትሰጫለሽ ! ›› በማለት በግልምጫም በማሽሟጠጥም አፈረጠቻት ፡፡
ሴቶቹ ቀስ በቀስ መደማመጥ ወደማይቻልበት ደረጃ ተሸጋገሩ ፡፡ ይባስ ብሎ ‹‹ ምን ይሄ ይገርማችኃል ! የኛ ሀገር ክትባት በሉት
መርፌ ሰው እየገደለ እኮ ነው ›› የሚሉ ሴት ከወደ ጓዳ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ብቅ አሉ ፡፡
አሁን ቤቱ በአንድ እግሩ ቆመ ፡፡
እነዚህ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክንፍ ወደ ከተማ የመጡ
ሴቶች አስተያየት የህብረተሰባችንን የንቃተ ህሊና የሚያንጸባርቅ ወይም የሚመረምር ቴርሞ ሜትር ነው ማለት ይቻላል ፡፡ ስለ ክትባት
፣ ኩፍኝም ሆነ ሀኪሞች ብዙ የሰሙ እና ብዙ የተመለከቱ በመሆናቸው ስጋታቸው ከጠርዝ የወጣ ነው ነው ማለት አያስችልም ፡፡ ምክንያቱም
በሀገራችን ህጻናትና እናቶች ከመጠን በላይ መድሃኒት ተሰጥቷቸው መሞታቸው አዲስ አይደለም ፡፡ ምክንያቱም በስህተት የማይገባ መርፌ
ተወግተው ያለጥፋታቸው የሚያሸልቡ ጥቂቶች አይደሉም ፡፡ ምክንያቱም በኛ ሀገር ቀኝ እግራቸው ታሞ በእንዝላልነት ግራ እግራቸውን
ለመጋዝ የሰጡ ምስኪን በሽተኞች መኖራቸውን አሳምረን እናውቃለን ፡፡ ምክንያቱም የሀገራችን ሀኪሞች ድራማን ለማየት በማስቀደም የነፍሰ
ጡር እናት ብርቅ እስትንፋስን ከድራማው ፍጻሜ ጋር እንዲደመደም እንደሚያደርጉ እናውቃለን ፡፡ ስራ በዝቶባቸው ብቻ ሳይሆን ትኩረት
ባለመስጠት የቀደዱት ሆድ ውስጥ መቀስና ፋሻ የሚረሱ ሀኪሞች መኖራቸውንም እናውቃለን ፡፡
መንግስትና የሚወዳቸው ቁጥሮቹ
መንግስት ከላይ የተገለጸውን አይነት አስተሳሰብ
፣ እምነትና አሰራሮች ትኩረት ሰጥቶ ከመመርመር ይልቅ በዘመቻ የሚገኙ ቁጥሮችን ማጉላት የመረጠ መስሏል ፡፡ የአሁኑ የውጭ ጉዳይ
ሚ/ር የቀድሞው ስመ ጥሩው የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ክትባቱ በተጀመረበት ወቅት ያጎሉትም ይሄንኑ ሃሳብ ነው
፡፡ ‹‹ በኢትዮጽያ የልጆች የጤና ክትባት ሽፋን 95 ከመቶ ደርሷል ›› በማለት ፡፡ ይህ አኀዝ በገለልተኛ ወገን ያልተረጋገጠና
ፍጹም የተጋነነ በመሆኑ አሳሳች መስመር እንዳይዝ ያሰጋል ፡፡
በኢትዮጽያ እድሜና ደመወዝ እንጂ ሪፖርቶችን ከፍ
አድርጎና አጋኖ ማቅረብ ከቀበሌ እስከ ቤተ መንግስት ድረስ የተለመደ አሰራር ነው ፡፡ ያጋነነው አካል ‹ ውሸታም ! › ተብሎ አይፋጠጥም
፤ ሳይጨምር ሳይቀንስ የቀረበው ግን ‹ እንዴት ይህን ብቻ ሰራህ ? › ተብሎ በግምገማ ዱላ ሊወገር ይችላል ፡፡ በዚህም ምክንያት
የትኛውም መንግስታዊ መ/ቤት ብትሄዱ የምታነቡትና የምትሰሙት የሚያስጎመዡ ቁጥሮችን ነው ፡፡ በሀገራችን እየቀረበ ያለው የኩፍኝ
ክትባት አኀዝም በተለመደው ምቹ የቻይና አስፋልት ሮጦ የመጣ እንጂ ዘወትር ከሚቆፋፈረውና እግርና ጎማ ከሚለምጠው የአውራጎዳና ባለስልጣን
ኮሮኮንቻማ መንገድ ጋር የሚተዋወቅ አይደለም ፡፡
አንድ ነርስ ለ 2 ሺ 500 ሰዎች በሚደርስበት
ሀገር ኩፍኝን ለማጥፋት ጥቂት ሽርፍራፊ አሃዝ ነው የቀረን ማለት ለጤና ጣቢያ እጅግ ርቀው የሚገኙ የህብረሰብ ክፍሎችን ፣ ባህላዊ
እምነትና የልምድ አዋቂዎችን እንደ ካስማ ይዞ የቆየን ማህበረሰብ ስነ ልቦና ዘልቆ ያለመረዳት ዉጤትን ያንጸባርቃል ፡፡
በርግጥ በጤና መስኩ አበረታች ውጤት አልታየም
ለማለት አይደለም ፡፡ የአሁኑ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ከሰተ ብርሃን አድማሱ በቅርቡ ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጋር ባደረጉት
ቃለ ምልልስ ከሰባት ዓመት በፊት 600 የነበሩት ጤና ጣቢያዎች ዛሬ 3 ሺህ መድረሳቸውን ፣ 34 ሺህ የሚደርሱ የጤና ኤክስቴንሽን
ሰራተኞችም መቀጠራቸውን ነግረውናል ፡፡ ይህ ቁጥር በተደራሽነት ላይ የነበረውን ሰፊ ክፍተት በጥቂትም ቢሆን እንደሚያጠብ ይጠበቃል
፡፡ ይህ ማለት ግን በክትባት እጦትና ባለመከተብ ፍላጎት የሚደርሰውን የህጻናትና እናቶች አስከፊ ሞት እንደሚነገረው የሚታደግ አይደለም
፡፡
ርግጥ ነው የዓለም ጤና ድርጅት የቅርብ መረጃ
እንዳረጋገጠው በዓለም አቀፍ ደረጃ በኩፍኝ በሽታ የሚሞተው ህጻናት ቁጥር 71 ከመቶ ቀንሷል ፡፡ ይህ የሆነውም ከ2000 እስከ
2011 ባሉት ሰፊ ግዜያት ነው ፡፡ በሌላ በኩል በዓለም አቀፍ ደረጃ 20 ሚሊየን የሚደርሱ ህጻናት የመጀመሪያ ደረጃ ክትባት እንኳ
ያልወሰዱ ናቸው ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሚገኙት በአምስት ሀገሮች ነው ፡፡ በኮንጎ ፣ ህንድ ፣ ናይጄሪያ ፣
ፓኪስታንና ኢትዮጽያ ፡፡ ይህም መንግስት ሰፊ የቤት ስራ እንደሚጠብቀው በአግባቡ ያመላክተዋል ፡፡
መንግስት ሊጠቀምበት የሚገባው ሌላኛው የማንቂያ
ደውል ወይም የስጋት ቴርሞሜትር በሀገራችን የኩፍኝ ወረርሽኝ በየአመቱ እንደተለመደው ድርቃችን ተከሳች ጉዳይ የመሆኑን ምስጢር ነው
፡፡ የቅርብ ግዜያትን መረጃዎች ብቻ ብንወስድ እኤአ በ2009 – 1519 ፣ በ2010 – 2401 እንዲሁም በ2011 – 3255
የኩፍኝ ምልክቶች በተለያዩ ክልሎች ተመዝግበዋል ፡፡ በ2011 ከተጠቁ ሰዎች መካከል ደግሞ 114 ህጻናት መሞታቸው በይፋ ታውቋል
፡፡
ያልታረቁ የህክምና መንገዶች
በአንድ በኩል መንግስት ኩፍኝ በህክምና የሚድን ቀላል በሽታ ነው ይላል ፡፡ በሌላ በኩል ህብረተሰቡ ኩፍኝ በቀላሉ
የምትድን በሽታ በመሆኑ ከቤቴ አላሳልፋትም ባይ ነው ፡፡ መንግስት ክትባት ተጠቃሚው መቶ ከመቶ ሊሆን አንድ እፍኝ ቀርቶናል ይላል
፡፡ ክትባት የማያውቀውና ለባህላዊው መንገድ እጁን የሰጠው ደግሞ ብዙ እፍኝ ሆኖ ይታያል ፡፡ ይህም የጤና ጣቢያ ችግር ከሌለበት
አዲስ አበባ እስከ አንድ ሺህ ኪ.ሜ ርቀት የሚገኙትን አርሶአደርና አርብቶአደር ነዋሪዎችን ያካትታል ፡፡ መንግስት የክትባት ሽፋኑ
ከ 90 ከመቶ በላይ ደረሰ የሚል ከሆነ የህብረተሰቡ የመረዳት አቅምና ግንዛቤ አድጓል ማለቱ ነው ፡፡ ይሁን እንጂ የኩፍኝ ክትባት
ኦቲዝም ያስከትላል ፣ የኩፍኝ ክትባት መውለድ ላይ ችግር ይፈጥራል ፣ ለአካል ጉዳተኝነትና የአእምሮ ችግር ይዳርጋል የሚል መረጃ
የታጠቀው የሀገራችን ህዝብ ቁጥር ደግሞ የትየለሌ ነው ፡፡
እናም በሚጋጭ እውነታ ውስጥ እየተደነቃቀፉ መጓዝ
ዋጋ ያስከፍላል ፡፡ በመሆኑም እየኖርን ያለበትንና መኖር የምንፈልግበትን ስርዓት በአግባቡ መገንዘብ ብሎም አብሮ እየተጓዙ ማጣጣም
በመጨረሻም ሳይንሳዊውን የብረት ቆብ ኬሻና ገመድ የለመደው ጭንቅላት ላይ የማኖር ብሂልን መላበስ ግድ ይላል ፡፡
መሬት የሚቆነጥጥ ስልት
የኢትዮጽያ የክትባት ፕሮግራም በዓለም አቀፍ ደረጃ
የተያዙትን የፖሊዮ በሽታ የማጥፋት ፣ የመንጋጋ ቆልፍ የመቆጣጠርና የመቀነስ ፣ የኩፍኝ በሽታን የማስወገድ ስራዎችን ይዞ ይንቀሳቀሳል
፡፡ በከተሞች አካባቢ የተሻለ የክትባት ሽፋን ቢኖርም አብዛኛው ህዝብ የሚኖርበት ገጠሩ ክፍል በተለያዩ ምክንያቶች ተደራሽ አለመሆኑን
ከመቀበል መነሳት ይኖርበታል - ስልቱ ፡፡
ኩፍኝ በረቂቅ ቫይረስ አማካኝነት የሚመጣና በትንፋሽ
የሚተላለፍ በሽታ አንጂ የፈጣሪ ቁጣ ፣ የተፈጥሮ ሂደት ውጤትና የሌሎች እምነትና ባህል መገለጫ አለመሆኑን በአንድ ሰሞን ዘመቻ
ሳይሆን በዝርዝር መንገድ ለማስተማር ኃላፊነትን መቀበል ግድ ይላል ፡፡ ኩፍኝ ድህነት ፣ ተፋፍጎ የመኖር ችግርና ያልተከተቡ ህጻናት
ባሉበት ቦታ የሚስፋፋና በከፍተኛ ደረጃ የሚገድል በሽታ መሆኑን የትምህርቱ አቢይ ምዕራፍ ማድረግ ያስፈልጋል ፡፡ ምክንያቱም የምንኖረው
በወራዳ የድህነት ቀለበት ውስጥ ነው ፤ የአኗኗር ስልታችንም ከተነጠላዊ ይልቅ እንደ ዳመራ የተጃመለና የተደጋገፈ ነው ፡፡ ይህም
አብሮ ለመስራትና ጠላትን ለማባረር አስፈላጊ ቢሆንም ቫይረስና ባክቴሪያ እንደ ጣሊያን መላልሰው ሲወሩን ግን በቀላሉ ለመጨፍጨፍ
ያመቻልና ፡፡
ኩፍኝ ርጉዝ በሆነች ሴት ላይ ከተከሰተ ልታስወርድ
እንደምትችል ፣ ህጻኑ ሊደነቁር ፣ ሊታወር እንዲሁም የአእምሮ ጉዳተኛ ሁሉ ሊሆን ይችላል ፡፡ አብዛኛው ህብረተሰባችን የሚያስበው
ግን በሽታው የህጻናት ብቻ መሆኑን ነው ፡፡ ለዚህም ነው የቆሼ ሰፈር ሴቶች የኩፍኝ ክትባትን መጠቀም ህጻናትን ለሞትና ለአካል
ጉዳተኝነት ይዳርጋል በማለት በግልባጩ የሚያስቡት ፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች የሚያገለግሉት
የአካባቢያቸውን ህብረተሰብ በመሆኑ ግንዛቤ ለመፍጠርና ልማዳዊ ልምዶችን ለመሰባበር ምርጥ ስትራቴጂ መሆኑን በልበ ሙሉነት ይናገራሉ
፡፡ ይህን አስተሳሰብ የመጨረሻ አድርጎ መቀበል ግን የክትባት ሽፉኑ 95 ከመቶ ደርሷል ብሎ በድፍረት የመናገር ያህል የሚያስቆጥር
ነው ፡፡
ምክንያቱም በየትኛውም የገጠሪቱ ክፍል የሚገኙ ዜጎች ከአንድ ጤና ባለሙያ ይልቅ የጎሳ መሪዎችን ፣ ታዋቂ ሽማግሌዎችን
፣ የእምነት አባቶችንና አዋቂዎችን ነው የሚያከብሩት … የሚፈሩትና ትዕዛዛቸውንም የሚፈጽሙት ፡፡ በመሆኑም ይህን ጠቃሚ ስልትም
በአግባቡ ፈትሾ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ፡;
ከ 80 በላይ ብሄር ብሄረሰቦች በሚገኙባት ሀገር
ለኩፍኝ ያለው አመለካከትም ሆነ ባህላዊና እምነታዊ የመከላከል ስትራቴጂው 80 ዓይነት የበዛ ነው ፡፡ አንዱ በጢሳጢስ ፣ ሌላው
በዝማሬ ፣ አንዱ ወንዝ በማሻገር ፣ ሌላው ስራ ስር በመቀመም ሊጠቀም ይችላል ፡፡ ምክንያቱም የነወ/ሮ መገርቱን ባህላዊ እምነት
የሚከተሉ ሰዎች ዛሬም በየትኛውም ጥግ ይገኛሉ ፡፡ የእነ አቶ ጥጋቡ መግልና ዝንብ የቀላቀለ ባህላዊ የህክምና መስጫ ተቋማት የቀራቸው
ከመንግስት ህጋዊ የንግድ ፍቃድ ማውጣት እንጂ በዘልማድ የሚሰሩበትና የሚያምኑት የገጠር ወገኖቻችን ዛሬም በርካታ ናቸው ፡፡ ክትባት
በራሱ ለመሃንነትና ለሌሎች ተዛማጅ ችግሮች ይዳረጋል የሚል የእምነት ጋቢ የደረበው የህብረተሰብ ክፍልም ቁጥሩ ጥቂት አይደለም ፡፡
መንግስት የያዘው አኀዝና ህብረተሰቡ ጋ ያለው ተጨባጭ እውነት የተጣረሰ በመሆኑ
የማስተካከያ ስራ ሊሰራ ይገባል ፡፡ የገነገነውን ባህላዊ ልምድንና እያቆጠቆጠ የሚገኘውን ዘመናዊ አሰራር ማጣጣምና ማስታረቅ ግድ
ይላል ፡፡ በአጠቃላይ ኩፍኝንና ወረርሽኙን ለመከላከል ፤
እውነትን - ማካፈል
ግነትን - መቀነስ
ክትባትን - መደመር
ግንዛቤን - ማብዛት
የተሰኘ ቀላል ነገር ግን ጠቃሚ ሂሳባዊ ቀመርን
መከተል ያስፈልጋል ፡፡