Monday, February 25, 2013

የ 12 ሰዓት ፍቅር


ልክ 12 ሰዓት ሲሆን ነቀምት ወይም የኦሮሚያ ክልል ማብቃቱን መንገዱ ላይ የተዘረጋው ገመድ ጠቆመን ፡፡ እዚህ ገመድ አጠገብ ‹‹ እንኳን ወደ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በደህና መጣችሁ ! ›› የሚል ታፔላ አልተሰቀለም ፡፡ ሁለት ጥቋቁር ረጃጅም ፖሊሶች በአካባቢው መታያታቸው በጀ እንጂ የቀጭኑ ገመድ ውክልና ለኬላ ነው ብሎ መከራከር በፍጹም አያዋጣም ፡፡ የረጅም ርቀትን አሸናፊ አትሌት ደረት የሚጠብቅ እንጂ ፡፡

የቤኒሻንጉልን ምድር ስንረግጥ መልካም አቀባበል ያደረገችልን በመጥለቅ ላይ የምትገኘው ፀሃይ ነበረች ፡፡ ከተራራው አናት ላይ ፍም ውበቷን ያለ ንፍገት በትናዎለች ፡፡ ዛፍና ዳመና ካልገረዷት አይን የሚስብ ክብነቷና ድምቀቷ ነው የሚጎላው ፡፡ በዛፍና ዳመና ስር አጮልቀን ስንመለከታት ግን በርካታ ጨረሮቿ ሌላ የውበት ህብር ፈጥረው ይታያሉ ፡፡

መኪናው ወዲህና ወዲያ ሲጠማዘዝ አንዴ በግራ አንዴ በቀኝ ጠርዝ የምትገኝ በመሆኑ እንደ ጦጣ እየዘለሉ መከታተል ግድ ይላል ፡፡ ለግዜው የቤኒሻንጉልታፔላየሆነቸው ፀሃይ ትመስጣለች ፡፡ ለጥ ባለ ሜዳ ከርቀት ስትታይ ደግሞ የውበቷን ምስጢር አንድ ሁለት እያሉ ለመቁጠር የሚገርም ዕድል ይፈጠራል ፡፡ በፀሃይዋ አካባቢ የሚገኘው ዳመና ብቻ ሳይሆን የምድር አካላቱም ማለትም ተራራው ሜዳው የገበሬ ቤቶች ደኑና ሳሩ ሁሉ አብረቅራቂ ውበት ይጎናጸፋሉ ፡፡ የዚህን ውበት መነሻና መድረሻ እንደ ኬላ ገመዱ ከዚህ እስከዚያ ድረስ ነው ብሎ ማየት መቻሉ ያስገርማል ያፍነከንካል ፡፡

ውበቱን መቋደስ ያልቻለው የደመና ክፍል ጠቋቁሮ ይታያል ፡፡ ሜዳና ተራራዎችም አጠገባቸው ከሚገኘው አብረቅራቂ አካባቢ በሶስት ሰዓት ርቀው ከምሽቱ ሶስት ሰዓትን ያስቆጠሩ ይመስላሉ ፡፡ ይህ ተቃርኖ ያስደምማል ፡፡ ይህ ተቃርኖ የፈጠረው ውበት የመምሸትና የመንጋትን ብቻ ሳይሆን የጥቁርና ነጭነት ተፈጥሯዊ ማንነታችንንም ጭምር መሆኑ ሌላው ብስራት ነው ፡፡

በዚህ ሰዓት የሚታየው ምድራዊ ገጽታም አሰደማሚ ነው ፡፡ ከብቶች ወደ ማደሪያቸው ፀጥ ባለ መንፈስ መስመር ይዘው ይጓዛሉ ፡፡ በሳር የተጎነጎኑ ድንክዬ የገበሬ ቤቶች አናት ላይ ደግሞ ቀኑን እየተሰናበቱ ይሁን ወይም የማስተዛዘኛ ጥሬ ፍለጋ ላይ የተሰማሩ ቁራዎች ለዘብ ባለ ድምጽ ያንቋርራሉ ፡፡ ቤታቸው የደረሱ ከብቶች ደግሞ ውጭ ተኮልኩለው የምሽቱን ድባብ እንደሚቃኙ አሳዳሪያቸው አጥር ጥጉን መታከክ መርጠዋል ፡፡

እዚህ እንደ ከተማ ውክቢያና መንቀዥቀዥ የለም ፡፡ ዳመናው በዝግታ ነው የሚጓዘው ፡፡ ፀሃይ ወደ ተራራ ቂጥ ስር የምንትሸራተተው በጣም በሚታይ ዝግመት ነው ፡፡ ከብቶች ወደ መስክ ሴቶች ወደ ምንጭ ሲካለቡ አይታይም ፡፡ በዚህ ጠይም የአየር ንብረትና ወርቀዘቦ ብርሃን ስር ተገኝቶ ከሰማይ እስከ ምድር ያለውን እንቅስቃሴ መቃኘት በርግጠኝነት ፍቅር ያሲዛል ፡፡ የጂጂ ዘፈን በእንደዚህ ዓይነት ስሜት ውስጥ ለሚገኝ ሰው ምን ያህል ሚዛን ደፊ ሆኖ እንደሚገኝ ማረጋገጥ አይከብድም ፡፡ደህና ሁን ከተማ ነው ያለቸው 

በፀሃይዋ ዙሪያ የሚገኘው ዳመና ሲሰባሰብና ሲበታተን ከዚያኛው ወገን በተሻለ መልኩ ይታያል ፡፡ በዚህ ግልጽ ጉዞው ደግሞ የተለያዩ ቅርጾችንና ስዕሎችን ሲያደምቅና ሲኩል መመልከት ይቻላል ፡፡

የደከመችው ሞባይሌ ስራ አልፈታችም የማታ ጀንበር የምታሳየውን ረቂቅ ውበት አንዳቅሟ ደጋግማ ታነሳለች ፡፡ ያነሳሁትን መላልሼ በማየት ደብዛዛውን እሰርዛለሁ ፡፡ ለተሻለው ደግሞ ማምሻም እድሜ ነው እንዲሉ ጋለሪ ውስጥ እንዲቆይ ይለፍ ይሰጠዋል ፡፡ ድንገት ግን አንድ ፎቶ ላይ አይኔ ፈጠጠ ፡፡ ከጀንበርዋ በላይ ከጥቁሩ ዳመና በስተቀኝ አናት ላይ ከአንገት በላይ የሆነ ስዕል ተመለከትኩ ፡፡ አይኖቹ አፍንጫው አፉ ገባ ያለ አናቱና ወረድ ያለው ፀጉሩ በግልጽ ይታያል ፡፡ ማመን ከበደኝ ፡፡ ሶስት ፎቶዎች ላይ ይኀውን ምስል ተመለከትኩ ፡፡

ገራሚና ደስ የሚል ስሜት ውስጥ ገብቻለሁ ፡፡ በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ያታከተኙ አምስት w አንድ H የተባሉ ጥያቄዎች ስርዓት ባጣ መልኩ አእምሮዬ ውስጥ ይነጥሩ ጀመር ፡፡
ይህን ስዕል ማን ሳለው ?
ይህ ስዕል ምንድን ነው ?
ይህ ስዕል እንዴት ተሳለ ?
ይህ ስዕል መቼ ተሳለ ?

በርግጥ የዚህ ስዕል ጉዳይ የተራ ግጥምጥሞሽ ውጤት ወይስ አንድ ያልታወቀ ምስጠራዊ መልዕክት መግለጫ ? እጠይቃለሁ እንጂ በቂ ምላሽ ውሰጤ ማመንጨት አልቻለም ፡፡ እኮ የምን ሚስጢር ? ከዳመናው ላይ አዘቅዝቆ የሚያየው ሰው ማነው ? አንድ ቤኒሻንጉላዊ  / በርታ፣ ጉምዝ፣ ሺናሻ… / አይኔ የፈጠረው ተራ ምስል ? 12 ሰዓት ዘወትር ሊገኝ የሚችል ተዓምር ? እኮ የምን ተዓምር ? … 12 ሰዓት ፍቅር ? የጠይም ፈጣሪ ምስል ? ወይስ በሌላኛው ዓለም የሚገኙ ሰዓሊዎች የደመና ቅብ ? ይህ ዓይነት ልዩ ፈጠራ እነሆ በረከት የሚለው ዳቬንቺ ፒካሶ ወይስ ገብረክርስቶስ ?
እንደዚህ አይነት ጉዳዮች ጥያቄ እንደሚበዛባቸው ብቻ ሳይሆን ምላሽም በቀላሉ እንደማይገኝላቸው ከልምድ ይታወቃል ፡፡ ብቻ 12 ሰዓቷ ጀንበር ከየትኛውም አዋቂ በተሻለ መልኩ ፍቅር ምን እንደሆነ በተግባራዊ ዘዴ ያስተማረች መስሎ ተሰምቶኛል ፡፡ 

ፍቅር ዕውር ነው የሚሉ ሰዎች አሉ - እውነት ከሆኑ መንገዱን ጨርቅ ያድርግላቸው ፡፡
እግዚአብሄር ፍቅር ነው የሚል አባባል አለ - ይህ 12 ሰዓት ፍቅር የፈጣሪ ስራ አለመሆኑን ማን ማረጋገጥ ይችላል ? ማንም !

ለማንኛውም ሁለቱን በተከተታይ 12 ሰዓት በፍቅር የተነሱ ፎተዎቼን ይመርምሯቸው ፡፡



Sunday, February 10, 2013

የአፍሪካ መሪዎች አይነኬ አጀንዳዎች



የአፍሪካ ማሊያ በጦርነት ፣ አምባገነንነትና ድርቅ ቀለማት የተሰራ ነው ፡፡ ቁምጣው ላይ የስደት … ጋምባሌው ላይ የመፈንቅለ መንግስት… ታኬታው ላይ የበሽታ መንፈሶችን መመልከት የሚቻል ይመስለኛል ፡፡ አፍሪካዊያን ነጻ በወጡ ማግስት ለዚህ ሁሉ የዳረገን መሰረታዊ ነቀርሳ የቅኝ አገዛዝ እባጭ ነው የሚል መከራከሪያ አቅርበው ነበር ፡፡ አሳማኝ ይመስላል ፤ እረ መሰሏልም ፡፡

ከነጻነት በኃላስ  የአህጉሪቷ እድሜ ስንት ቆጠረ ? ሃምሳ !... ይኅው ሰሞኑን አዲስ አበባ ውስጥ ያካሄዱት 20ኛ መደበኛ ጉባኤያቸው የህብረቱን 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤሊዩ ለማክበር በተነሳሳ መንፈስ አይደል ? ግን እኮ አህጉራችን ዛሬም በኢኮኖሚ ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ  መስኮች ውጤታማ አክሊሎችን አልደፋችም ፡፡ ታዲያ ለዛሬው ተጨባጭ ችግር የበፊቱን የምክንያት ኩታ ማልበስ ይቻላል ? ማለት ቅኝ አገዛዝ የሚል ? መቼም ለፈገግታ ካልሆነ በስተቀር አያዋጣም ፡፡ ታዲያ ችግሩ ምንድነው ብለን በአንክሮ ከጠየቅን ነገር አለሙ ሁሉ መሪዋቹ ትከሻ ላይ ወድቆ ቁጭ ይላል ፡፡

በርግጥ መሪዎቹ እንዲህ አያስቡም ፡፡ ያስባሉ ብሎ መጠበቅም ከስጋ ለበስ ሰብዓዊነት አንጻር እንጂ ፖለቲካዊ መላ ሆኖ አይደለም ፡፡ የስብሰባቸው ውሎም የሚነግረን አፍሪካ ተስፋ ያላት አህጉር የመሆኗን ጉዳይ ነው ፡፡ ምክንያቱም  ጥቂት ቢሆኑም ዓመታዊ እድገታቸው በሁለት ዲጂት የሚራመድ ሀገሮች ባለቤት መሆን ጀምራለች ፡፡ ይህን ውጤት ቀምሮ ለማስፋፋትም ይቻል ዘንድ በኢኮኖሚና ንግድ ዙሪያ ተነጋግረዋል ፡፡ የስትራቴጂ ዕቅድም ነድፈዋል ፡፡ በላዩ ላይም የአዲሱ የአፍሪካ ልማት አጋርነት / NEPAD / እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል የሪፖርት ካፖርትን ጣል አድርገዋል ፡፡ ማሊያው ላይ ከሚገኙት ቀለማት በተለይም ‹‹ ድርቅ ›› ቋሚ ተሰላፊ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ይመስላል እንዴት በአሰቸኳይ ግዜ እርዳታ ሊፈታ እንደሚችል መክረዋል ፡፡ በአፍሪካ በአራቱም ማዕዘናት የባሩድ ሽታ ተለይቶ ባያውቅም በዚህ ስብሰባቸው ይበልጥ ያስነጠሳቸው የሚሊ የጸጥታ ችግር ሆኗል ፡፡ እና ጉዳዩን ለመፍታት 50 ሚሊዮን ዶላር ከካዝናቸው መዥረጥ እስከማድረግ ደርሰዋል ፡፡

ታዲያ ወሬ ብቻ ሳይሆን መፍትሄም እየሰጠ የሚጓዝ የመሪዎች ስብስብ የምስጋና ሰርተፍኬት እንጂ እንዴት የማስጠንቀቂያ ካርድ ይመዘዝበታል ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ አይደለም ሊባል አይችልም ፡፡ በዚህ ላይ የሰሞኑ ስብሰባ የሃምሳ አመት አፍሪካዊ ትግልን የሚዘክር ነው ፡፡ የውይይቱ ማጠንጠኛ ‹‹ ፓን አፍሪካኒዝም እና የአፍሪካ ህዳሴ ›› በሚል ወርቃማ ሰንሰለት የተሞሸረውም ለዋዛ አይደለም ፡፡ እንዴት ካልክ ሰንሰለቱን ቀስ በቀስ ስትፈታ ነው የትግሉን ውጣ ውረድና የውጤቱን ግዙፍነት ልትረዳ የምትችለው ፡፡ እነዚህ በተደጋጋሚ የተወቀጡ ሁለት ጽንሰ ሀሳቦች እውነት መሪዎቹ ያለባቸውን ክፍተት የመሸፈን አቅም አላቸው ?  በፍጹም የላቸውም  ፡፡ ለማንኛውም ከመፍረዳችን በፊት ጥቅልሎችን እንፍታ ፡፡

‹‹ ፓን አፍሪካኒዝም ››

አፍሪካን በቅኝ ግዛት የተቆራመቷት የውጭ ሃይሎች እምቅ ሀብቷን ከመበዝበዝ በተጨማሪ የህዝቡን ነጻነት በማፈን ሲሸጡና ሲለውጡት ቆይተዋል ፡፡ በተለያዩ ሀገራት ተበትነው የሚገኙ አፍሪካዊያን የቅኝ ግዛት እና የባሪያ ንግድ እንቅስቃሴን መነሻነት በመቃወም በአህጉሪቱ ነጻነት ፣ ብሄራዊ ስሜት፣ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ትብብር ፣ የታሪክና ባህል ግንዛቤ እንዲሁም አንድነት እንዲፈጠር ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርገዋል ፡፡ ይህ እንቅስቃሴም ፓን አፍሪካኒዝም ይባላል ፡፡ በ1900 አካባቢ የተመሰረተው ይህ ርዕዮተ አለም መላው አፍሪካን አንድ ማድረግ ላይ ያተኩራል ፡፡ የፓን አፍሪካ መሪ የሚባሉት እነ ኩዋሜ ንክሩማህ ፣ ጆሞ ኬንያታ ፣ አጼ ሃይለስላሴ ፣ ሙአመር ጋዳፊና ሌሎችም የአፍሪካ አንድ መሆን አህጉሪቷ በራሷ እንድትተማመንና የራሷን እምቅ ሀብት በነጻነት በራሷ በማልማት የህዝቦቿን የዘመናት ጥያቄ እንድትመልስ ያደርጋል ባይ ናቸው ፡፡

‹‹ የአፍሪካ ህዳሴ ››

የአፍሪካ ሀገራትና ህዝቦች በወቅቱ እያጋጠማቸው የሚገኘውን ዘርፈ ብዙ ችግር ተቋቁመው የባህል ፣ ሳይንስና ኢኮኖሚያዊ ውጤት ማስመዝገብ እንዲችሉ ማድረግ ነው ፡፡ ይህ ጽንሰ ሃሳብ በ1946 ብቅ ያለው በቼክ አንታ ዲውፕ ‹‹  Towards The African renaissance  ›› በተሰኘው መጽሀፍ ውስጥ ነው ፡፡ ይህ የተዳፈነ ሀሳብ ይበልጥ ቦግ ያለው ታቦ ምቤኪ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው በተሾሙበት ወቅት ነበር ፡፡ ‹‹ I am an African ››  በተሰኘው ታዋቂ ንግግራቸው ውስጥ የአፍሪካ ህዳሴ መጀመር ከድህረ አፓርታይድ ዘመን በኃላ ትልቅ የአፍሪካ አጀንዳ እንደሚሆን ገልጸው ነበር ፡፡

እኤአ በጥር 11 ፣ 1999 የአፍሪካ ህዳሴ ተቋም በፕሪቶሪያ ተመስርቷል ፡፡ የተቋሙ ጽ/ቤት የሚገኘው ቦትስዋና ጋቦሬኒ ነው ፡፡ ይህ ተቋም እንዲፈጽም የተሰጠው ተግባር ሰፊና ከአቅሙ በላይ ይመስላል ፡፡ የቅድሚያ ተግባሩ ምርጥ የአፍሪካ ሳይንቲስቶችን ማፍራት ነው ፡፡ ምሁራኑ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ላይ የተጋረጡ ችግሮችን በመፍታት የኢንዱስትሪ ውጤቶች የሚጎመሩበትን ሁኔታ ያመቻቻል ፡፡ የሰው ኃይል ልማት ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ፣ ግብርና ፣ ምግብና ጤና ፣ ባህል ፣ ንግድ ፣ ሰላም እና መልካም አስተዳደርም የትኩረት አቅጣጫዎቹ ናቸው ፡፡ ይህ ተቋም የፖለቲካና የፍልስፍና ማራመጃ በመሆኑ ከአፍሪካ ግጭት ፣ ሙስና ፣ ድህነትና ጥቅማጥቅም ለባለግዜዎች ይገባል /  Elitism  / ብሎ ማመን እንዲጠፋ ሌት ተቀን ይሰራል ፡፡

በጀ ! በማለት…  ጥቅልሎቹ እንደተከፈቱ አንዳንድ ሀሳቦችን እንወርውር ፡፡ ፓን አፍሪካኒዝም በዛ በራቀ ዘመን መወለዱ ድንቅ ነው ፡፡ የቅኝ አገዛዝና የባሪያ ንግድን ካቴና አውልቆ ማሽቀንጠሩ አሪፍ ነው ፡፡  የዛሬን የግሎባላይዜሽን ሁኔታ ተንብዮ ስለ አንዲትና የተባበረች አፍሪካ ማሰቡም ማለፊያ ነው ፡፡ ራስን በራስ የማስተዳደርና የነጻነት ብርሃን እንዲወጣም አዎንታዊ ሚና ነበረው ፡፡ ጽንሰ ሃሳቡ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሀሳቦች ግን በአፍሪካዊያን ጥርስ የሚቆረጠሙ አይደሉም ፡፡ ለምሳሌ ስለ እኩል መብትና አንድነት በዛሬይቱ አፍሪካ ማለም እንጂ ማረጋገጥ እንዴት ይቻላል - አይቻልም ፡፡ ይቻላል የሚሉትም እነዛው መሪዎች ብቻ ናቸው - በመክፈቻ ዲስኩር ወቅት ፡፡

በነገራችን ላይ የአፍሪካ ህዳሴ የሚባለው ጽንሰ ሃሳብና የሀገራችን አንዳንድ ህጎች ሳይመሳሰሉ አይቀርም ፡፡ በወረቀት ደረጃ እንከን የለሾች ሲሆኑ በተግባር ግን  የማይተገበሩ ናቸው ፡፡ ህዳሴው የአፍሪካን ግጭትና ሙስናን የሚከላከል ፤ መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን የሚያሰፍን  ነው - ነኝ ስለሚል ማለት ነው ፡፡ ይህ ታፍረውና ተከብረው በቆዩ የአፍሪካ መሪዎች ዘንድ ቃል በቃል ነው ወይስ ተገልብጦ የሚነበበው  ? እረ ለመሆኑ

1.      የትኛው መሪ ነው እጁን ከካዝና የሚያርቀው ?
2.     የትኛው መሪ ነው ግጭቶችን ለፓለቲካ መጠቀሚያ የማያውለው ?
3.     የትኛው መሪ ነው ስልጣኑን በግዜው ለመልቀቅ ፍቃደኛ የሚሆነው ?

እንግዲህ ፓን አፍሪካኒዝምም ሆነ የአፍሪካ ህዳሴን የሚፈታተኑ መሰረታዊ ጉዳዮች እነዚህ ናቸው ፡፡ ሃምሳኛው ዕድሜው ላይ የሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ስለ መሪዎች የከፋ ሙሰኝነት ፣ ስለ ስልጣን ገደብ ፣ ስለ ዴሞክራሲና ነጻነት ፣ ስለ ግጭቶች መንስኤ በድፍረት መወያየት ያልቻለው ለምንድነው ? በሌላ አገላለጽ እነዚህ ጥያቄዎች ሃምሳ ዓመት ያስቆጠረው የህብረቱ ህንጻ ስር የሚገኙ የመሰረት ድንጋዮች ናቸው ፡፡ ድንጋዩን መሳብ ደግሞ ቤቱን ያፈርሳል ፡፡ እና ማነው ተቀብሮ ለመሞት ዝግጁ የሚሆን ? ለዚህም ነው የአፍሪካ መሪዎች ቀይ በሚያበሩ መስመሮች / ፈንጂ ወረዳዎች / ዙሪያ መወያያት የማይደፍሩት ፡፡

አይነኬ አጀንዳ ቁጥር አንድ

‹‹ ለረጅም ዓመታት ሀገሪቱን ገዙ ፡፡ መቼ ነው ስልጣንዎትን የሚለቁት ? ››
‹‹ በህይወት እስካለሁ ድረስ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት እኔ ነኝ ! ››
ይህ ምላሽ በባለቤትነት የተመዘገበው በዙምባብዌው ሮበርቱ ሙጋቤ ነው ፡፡ ይህን የመሰለ አስገራሚ ምላሽ የሚሰጡ የአፍሪካ መሪዎች የትየለሌ ናቸው ፡፡ ከ42 ዓመት በላይ ስልጣን ላይ የቆዩት ሙአመር ጋዳፊ በህዝብ ማዕበል ተጠራርገው ቢወሰዱም እሳቸውን የመሰለ መሪ ለመፍጠር የመለዋወጫ ዕቃ ችግር በአፍሪካ ምድር አይታሰብም ፡፡ ምርቱን በጥራት የሚያቀርበው የአፍሪካ ህብረት በርካታ አማራጮችን ከበርካታ ዓመታት ዋስትና ጋር ያቀርብሎታል ፡፡

30 ዓመታት የተፈተኑት ፓውል ቢያ ይሻሎታል ወይስ 22 ዓመታት ጋራዥ የማያውቁት ኦማር አልበሽር ? ሊባሉ ይችላሉ ፡፡ እና አማራጩ ሰፊ ነው ፡፡ የአፍሪካ መሪዎች የሚደርስባቸውን የስግብግበነት ትችት ለመቅረፍ ይመስላል በ19990 ዎቹ አካባቢ የስልጣን ዘመናቸውን በሚገድብ እንቅስቃሴ ውስጥ ሰምጠው ነበር ፡፡ 30 የሚደርሱ መሪዎች አንድ መሪ ከሁለት ግዜ በላይ መመረጥ አይችልም የሚል ሀሳብ በህገ መንግስታቸው ውስጥ አሰፈሩ ፡፡ ጉድ ! አፍሪካ በዴሞክራሲ እጦት ከሚከሰተው የልምሻ በሽታ ልትፈወስ ነው ተባለ ፡፡ ተጨበጨበ ፡፡

አንዳንዶቹ ግን በዚህ ህጋዊና ሰላማዊ የዴሞክራሲ መረብ ውስጥ መጠመድ አልፈለጉም ፡፡ በፈር ቀዳጅ አጋሮቻቸው ላይም ‹‹ አይነጋ መስሏት… ›› የሚል ተረት ብጤ ወረወሩ ፡፡ እውነትም የመምራት ሳይሆን የመፍለጥ - መቁረጥ ክፍለ ግዜው ማለቅ ሲጀምር ብዙዎቹ ምላሳቸው ሬት ሬት ይላቸው ጀመር ፡፡ በጠባቡ ጭንቅላታቸው የስኳር ተገቢነትን በማረጋገጣቸው ለገቡት ቃልና ለህገመንግስቱ ተገዢ መሆን ከበዳቸው ፡፡ አያይዘውም ለተከበረው ህዝባቸው ሳይሆን እንደ ማስታወሻ ደብተራቸው ለሚቆጥሩት ህገ መንግስት አጭርና ጓዳዊ ደብዳቤ በመጻፍ ማሻሻያውን በፊት ወይም በኃላ ገጹ እንዲሸከም አደረጉት ፡፡ የአፍሪካ ህገ መንግስቶች ‹‹ ለህዝብ ጥቅም ሲባል … የተጀመሩ የልማት ውጥኖች ዳር እንዲደርሱ ሲባል … የጎመራው ዴሞክራሲያዊ ስርአት እንዳይጨናገፍ… የህዝብን ይሁንታ ለማክበር ሲባል … እንደሳቸው በሳልና ታላቅ መሪ እስኪፈራ ድረስ … ›› በሚሉ ጅላጅል ሀረጎች መሳቅ እየፈለጉ እንኳ ይፈራሉ ይባላል ፡፡ የህጎች ሁሉ የበላይ እየተባሉ መፍራት ካለ - በርግጥም ራሱ ፍርሃት ያስፈራል ፡፡

ቃላቸውን ቅርጥፍ አድርገው ከበሉ መሪዎች መካከል የቡርኪናፋሶው ብሌስ ካምፓወሬ ፣ የኡጋንዳው ዩዌሪ ሙሴቬኒ ፣ የካሜሮኑ ፓወል ቢያና የጋቦኑን ኦማር ቦንጎን ለአብነት ማንሳት ይቻላል ፡፡ እናም ዛሬ በውጊያ ፣ በኩዴታና ካርድ በማጭበርበር ወንበሩን የያዙ መሪዎች እስከመቼ እገዛለሁ የሚለው ጥያቄ አያስጨንቃቸውም ፡፡ የአባቶቻቸውን ፈለግ ይከተሉ ዘንድ በውስጥ ታዋቂነት ተፈቅዷልና ፡፡ የስዋዚላንዱ ምስዋቲ 25 ፣ የቻዱ ኢድሪስ ዲባይ 22 ፣  የኢትዮጽያው መለስ ዜናዊ 21 .... የኤርትራው ኢሳያስ 21 ፣ የጋምቢያው ያህያ ጃማ 18 ፣ ሌሎቹም ኢኮኖሚው ቢያቅታቸው አገዛዛቸውን በሁለት ዲጂት ማሳደግ ችለዋል ፡፡ ታዲያ እነዚህን የመሳሰሉ መሪዎችን ያሰባሰበው የአፍሪካ ህብረት ‹‹ ስልጣናችሁን ገድቡ !! ›› እያለ በየግዜው አጀንዳ ቢይዝ ከምጸታዊው ፈገግታ የሚወጣውን ጨረር በሙሉ ዓይን ማየት ይችላል ?

አይነኬ አጀንዳ ቁጥር ሁለት

በአንድ ወቅት የአልጄሪያው ፕሬዝዳንት አብዱልአዚዝ ቡተፍሊካ ለዋሽንግተን ታይምስ እንደገለጹት በ1991 የተጀመረው የርስ በርስ ጦርነት ለመቶ ሺህ ህዝብ እልቂትና ለ20 ቢሊዮን የኢኮኖሚ ኪሳራ ዳርጓል ፡፡

አፍሪካ ነጻ ከወጣች / 1960 / በኃላ 19 ሚሊዮን ዜጎቿን በጦርነት አጥታለች ፡፡ ይህ ህዝብ ያለቀው በቅኝ ገዢዎች አረር ቢሆን ለማሳበብ በተመቸ ነበር ፡፡ ግን አይደለም -  በራሱ ዜጎች ነው ፡፡ አንዳንድ ማሳያዎችን እንሰንዝር ፡፡

በናይጄሪያ የቢያፍራ ጦርነት           - 1 ሚሊዮን
በሞዛምቢክ የሲቪል ጦርነት           - 1 ሚሊዮን
በአንጎላ       ››         ››              - 1.5 ሚሊየን
በሱዳን        ››         ››              - 4 ሚሊየን
በኮንጎ ጦርነት                          - 6 ሚሊየን
በላይቤሪያ፣ ሴራሊየንና አይቮሪኮስት  - 2 ሚሊየን
በሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ               - 800 ሺህ
በኢዲያሚን ዳዳ ጭፍጨፋ             - 200 ሺህ
በሲያድባሬ                               - 500 ሺህ
በመንግስቱ                               - 400 ሺህ 
በመለስ ዜናዊ                                    - በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ብቻ 125 ሺ ሰዋች አልቀዋል ።

ጦርነት ከሚያስከትለው ሰብዓዊ ቀውስ በተጨማሪ ኢኮኖሚውን ሽባ ያደርጋል ፡፡ ህዝቦች ጦርነት ሲጀመር ስለሚሰደዱ የምርታማነት መጠን ይቀንሳል ፡፡ የአህጉሪቱ ምርታማነት መጠን በ1960ዎች በ 7 ከመቶ ፣ በ1970ዎቹ በ 15 ከመቶ ፣ በ1980 ዋቹ በ 8 ከመቶ ቀንሷል ፡፡ በዚህም ምክንያት አፍሪካ ሁሌም ትፎክራለች እንጂ በምግብ እህል ራሷን መመገብ አልቻለችም ፡፡
ለዚህ አሰቃቂ ግድያና ለሚያስከትለው ክስረት በዋናነት ተጠያቂ የሚሆኑት ስልጣን ላይ የሚገኙት አምባገነን መሪዋች ናቸው ፡፡ 

የአፍሪካ ህብረት ዘወትር ግጭትና ጦርነት የማይለያት አህጉር ይዞ በጦርነቶቹ መሰረታዊ መንስኤዎች ላይ ደፍሮ ለመወያየት አጀንዳ መያዝ አይፈልግም ፡፡ የጦርነት መንስኤዎች የዴሞክራሲ ፣ የመልካም አስተዳደር ፣ የዘረኝነት ፣ የልማት ፣ የስልጣን ክፍፍልና የመሳሰሉ ጥያቄዎች መሆናቸው ይታወቃል ፡፡ ይሁን እንጂ ስልጣን ላይ የሚገኙ መሪዎች በአምባገነንነትና ሙስና ጡንቻ የፈረጠሙ በመሆናቸው የሌላኛውን ወገን ሀሳብ ጤናማ አድርጎ ለመመልከትና ለማስተናገድ ፍቃደኛ አይሆኑም ፡፡ ሃያና ሰላሳ አመት ስልጣን ላይ ቢቆዩም ወንበራቸውን ለማካፈል በሚነሳ የሂሳብ ጨዋታ ላይ በራቸውን የሚዘጉት በቢኤም ጥይቶች ነው ፡፡ እናም ጦርነትን የስልጣን መመከቻ ጋሻ የሚደረገውን ስልት ለማቆም አይፈልጉም ፡፡

 በአሁኑ ሰዓትም በርካታ የአፍሪካ ሀገሮች ግጭት ውስጥ በመሆናቸው አሰቃቂው የእልቂት ሰንሰለት አልተበጠሰም ፡፡ ተተኪዎቹም በዚህ ሻምፒዮን ውስጥ ሳይሳቀቁ መሳተፍ ጀምረዋል ፡፡ አንጋፋው የአፍሪካ ህብረት ግን ለዓመታዊው ሪፖርቱ የሚሆን መረጃ ማሰባሰብ እንጂ በመሰረታዊው ምክንያት ዙሪያ ውይይት እንዲካሄድ መንገድ አያመቻችም ፡፡ ይህን ለማድረግ የሚያስችል መሰረትም የለውም ፡፡

አይነኬ አጀንዳ ቁጥር ሶስት

ብዙዎቹ የአፍሪካ መሪዎች ከገዳይነትና አምባገነንነት በተጨማሪም በዘራፊነትም ፒ ኤችዲአቸውን ሰርተዋል ፡፡ በአስደናቂ የሌብነት ስልቶች ዙሪያ ጥናታዊ ወረቀቶችን አቅርበው የቲፍ - ፌሰር ማዕረግ ያገኙም በርካታ ናቸው ፡፡ 40 ቢሊየን ዶላር  የዘረፈው ሙባረክ ፣ 14 ቢሊየን ያስደነገጠው ቤን አሊ፣ 10 ቢሊየን ያስመዘገበው ሞቡቱ ፣ 9 ቢሊየን ያስቆጠረው ባባጊንዳ ፣ የ 7 ቢሊየን ባለቤቱ ኦማር አልበሽር ፣ የ3 ቢሊየኑ ጌታ የቶጎው ኢያዴማን ፣ የበርካታ ሚሊየኑ ባለሀብት የኢትየጽያው መለስ
 በዋናነት መጠቃቀስ ይቻላል ፡፡

አንዳንድ የአፍሪካ መሪዎች ለዚህ ዓይነቱ አስነዋሪ ስነምግባር ግድ ያላቸው አይደሉም ፡፡ ለምሳሌ ያህል ሞቡቱ ሴሴኮ ለኮንግረስ ማን ማርቬን ዳይማሊ ‹‹ በዚህ ትልቅ ሀገር ለ 22 ዓመታት መሪ ሆኖ ለቆየ ሰው ያለኝ ገንዘብ / 10 ቢሊየን ዶላር / ምንም ማለት አይደለም ›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል ፡፡ ዛሬም ስልጣን ላይ ያሉ መሪዎች በአንድ በኩል ሀገር ውስጥ ስለ ህዳሴ እየሰበኩ በሌላ በኩል በውጭ ሀገራት አያሌ ንብረታቸውን እያደሱ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ ፡፡ አንዳንዶቹ እንደውም የራሳቸው አልበቃ ብሏቸው  ቤተሰብና ቤተዘመድ ሁሉ በሀገሪቱ የሀብት ገንዳ ውስጥ እንዲዋኙ ፍቃድ ሰጥተዋል ፡፡

የኢኳቶሪያሉ ጊኒ ፕሬዝዳንት ልጅ ቱዎዶር ጉማ ኦቢያንግ የሀገሪቱን የነዳጅ ገቢ የራሱ በማድረግ ወሲባዊ ህይወቱን ይመራል ፡፡ ይህ ማፈሪያ 38.5 ሚሊየን ዶላር የወጣበት የግል ጀት፣ 30 ሚሊን ዶላር የፈሰሰበት ትልቅ ህንጻ ፣ 4 ሚሊየን ዩሮ የተቆረጠለት ተሸከርካሪ ፣ 18 ሚሊየን ዩሮ ያወጣ የስዕል ስብስቦች ባለቤት ነው ፡፡

የአለማቀፉ ሪፓርቶች እንደሚጠቁሙት ለኮንጎ ብራዛቪል ፕሬዝዳንት ዴኒስ ሳሶ ንጌሶ ወንድ ልጅ ክሪስትል የሚወጣው ወርሃዊ ወጪ በኩፍኝ በሽታ ለሚሰቃዩ 80 ሺህ ህጻናት መድሃኒት መግዣ አሳምሮ ይበቃል ፡፡ የአንጎላው ፕሬዝዳንት ጆሴ ኤድዋርድ ዶስሳንቶስ ሴት ልጅ ኢሳቤል የአባቷን ስልጣን ጋሻ በማድረግ በምታከናውነው የአልማዝና ሌሎች ንግድ ስራዎች 550 ሚሊየን ዶላር ሃብት በማስመዝገቧ በአፍሪካ ሀብታም ሴት ተብላለች ፡፡ ሀብታም ሌባ ለማለት የደፈረ ግን የለም ፡፡

አፍሪካዊያን በቀን ከአንድ ዶላር በታች በማግኘት በድህነት ፣ በሽታ ፣ ድንቁርና ማቅ ውስጥ እየሰመጡ ቢሆንም እናስተዳድርሃለን የሚሉት መዥገር መሪዎች ሀብቱን  የመመዝበሩን ዕቅድ አጠናክረው ቀጥለዋል ፡፡ ሙስና የሀገርና እድገት ጸር መሆኑን የሚለፍፈው የአፍሪካ ህብረት ሚሊኒየርና ቢሊኒየር መሪዎች ፊት ስለ አስጸያፊ ተግባራቸው በጥልቀት ለመወያየት ደፍሮ አያውቅም ፡፡ ይህም ለአፍሪካ ህብረት አይነኬ አጀንዳ ሆኖ ተከብሯል ፡፡

እነዚህን አይነኬዎች በደንብ ነካክቶ ህገ ወጥ አሰራሮችን ከአናት ማስተካከል ካልተቻለ ፓን አፍሪካኒዝምንና ህዳሴን እውን ማድረግ ያስቸግራል ፡፡ ለአፍሪካ የሚያስጎመዡ ህልም የሆኑት እነ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደርም እንቁልልጬያቸውን ይቀጥላሉ ፡፡ ውጤት ይገኛል ቢባል እንኳ ኮስሞቲካዊ እንጂ ስር ነቀል አይሆንም ፡፡



Sunday, January 13, 2013

‎የ ‹‹ ዋሊያዎቹ ›› ስያሜ ምን ያህል ፍትሃዊ ነው ?‎







የእግር ኳስ መጠሪያ በአፍሪካ
ሁሉም የአፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች ልዩ መጠሪያ አላቸው ፡፡ ሀገሮች የቡድናቸውን መጠሪያ ከባንዲራ ፣ ከጥንካሬ ፣ ከማሊያ ፣ ሀገራቸው ጎልታ ከምትታወቅበት ጉዳይ ፣ ቡድኑ እንዲሆን ከሚፈለገው አንጻርና ከመሳሰሉ ጉዳዮች ተነስተው ይሰይማሉ፡፡
ይህ ማለት ግን ያለምንም አሳማኝ ምክንያት ስም የለጠፉ የሉም ማለት አይደለም ፡፡ ለምሳሌ የኮንጎ ብሄራዊ ቡድን Red Devils ነው የሚባለው ፡፡ ይህን ስያሜ የቤልጂየም ብሄራዊ ቡድንና ማንችስተር ዩናይትድ ይጋሩታል ፡፡ ሰይጣን ጥቁር ነው በሚባልበት ዓለም ቀያዮቹ ማንቸስተሮች ተምሳሌቱን የተጠቀሙበት ለምን እንደሆነ ይገባናል ፡፡ በመልክ ከሆነ ለሰይጣን የቀረቡት ኮንጎዎች ራሳቸውን ቀይ ሰይጣን የሚሉበት አግባብ አለ ቢባል እንኳን በአሳማኝነቱ ዙሪያ ዕድሜ ልክ ሊያከራክር የሚችል ነው ፡፡

የስያሜ እጥረት ያለ ይመስል የሌላውን ሀገር የደገሙም አሉ ፡፡ የኮትዲቭዋር ‹ the elephant › በጊኒ < the national elephant > ሆኖ ይገኛል ፡፡ ለአብዛኛው አፍሪካዊያን ቡድን መጠሪያ የሆኑት ግን የዱር እንስሳት ናቸው ፡፡ ርግጥ ነው አፍሪካ በዱር እንስሳት ሃብት አትታማም ፡፡ ይህ በራሱ መነሻ ሆኖ ሊሆን ይችላል ፡፡ በሌላ በኩል የአፍሪካዊያንና የዱር እንስሳት ትስስር ስናጤን ግን መነሻው ተግባር ላይ መዋል እንዳቃተው ህግ ሽባ ሆኖ ይታየናል ፡፡  አፍሪካዊያን የዱር እንስሳትን ቢወዱም ለስጋቸው ፣ ለጀብዱ ፍለጋ ፣ ኪሳቸውን ለማደለብ ሲሉ ያለ ርህራሄ ይገድሏቸዋል ፡፡ አፍሪካዊያንና የዱር እንስሳት እንደ ኦቴሎና ዴዝዲሞና የሚመሳሰሉ ናቸው ፡፡ እየወደዱ የሚገድሉ ፡፡

ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ ከሀገራችን ዋሊያ ጋር የሚደረገውን ግብግብ እናንሳ ፡፡ ዋሊያ ለመጀመሪያ ግዜ የታየው በ1835 ነበር ፡፡ በ1960ዋቹ ለስሊ ብራውን በተባለ ሰው በተደረገው ጥናት ቁጥራቸው ከአንድ ሺህ በላይ ነበር ፡፡ ይሁን እንጂ ጣሊያን ሀገራችንን ሲወር እጅ አንሰጥም ያሉ አርበኞች ተራራው ላይ መሽገው ይዋጉ ነበር ፡፡ በአካባቢው የታየው ዋሊያም ‹‹ ምን እንበላለን ? ›› ለሚለው ወቅታዊ ጥያቄያቸው ሁነኛ አማራጭ ሆነ ቀረበ ፡፡ በዚህም ሳቢያ ቁጥሩ አሽቆለቆለ ፡፡

ጣሊያን ሀገሪቱን ለቆ ከወጣ በኃላም ዋሊያ በአካባቢው ነዋሪዋች ለስጋውና ለቀንዱ ይታደን ነበር ፡፡ ደገኛው ስጋውን እያጣጣመ በቀንዱ ኩባያ ሰርቶ ጠላ ይጠጣበታል ፡፡ ይህ ገደላ ጋብ ያለው በተፈጥሮ ጥበቃ ላይ የሚሰራው The International union for conservation of nature / IUCN / ቀጭን ማስጠንቀቂያ ከሰጠ በኃላ የኢትዮጽያ መንግስት ብሄራዊ ፓርኩን በ1966 በማቋቋሙ ነው ፡፡ ዋሊያ ዛሬም ድረስ በመጥፋት ላይ የሚገኝ እንስሳት ዝርዝር ውስጥ ቢገኝም ቁጥሩ ከ 500 በላይ መድረስ ችሏል ፡፡

አንበሳ አፍቃሪዎች
 የዚህን ድንቅ እንስሳ ለብሄራዊ ቡድናቸው መጠሪያ ያደረጉት ግን ካሜሮን ፣ ሞሮኮና ሴኔጋል ናቸው ፡፡

ዘንድሮ ማጣሪያውን ማለፍ ያቃታቸው ካሜሮን Indomitable lions ይባላሉ ፡፡ የማይሸነፉ አንበሶች እንደማለት ፡፡ ርግጥ ነው የኛ ሀገር የስፖርት ጋዜጠኞች የማይበገሩ አንበሶች እያሉ ነው የሚጠሯቸው ፡፡ ካሜሮን በ1972 ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ማለፍ አለመቻሉ የሀገሪቱን ፖለቲከኞች አነጋግሮ ነበር ፡፡ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አህመዱ አሂዶ የሀገሪቱ የስፖርት መዋቅር በአዲስ መልክ እንዲገነባ ትዕዛዝ አስተላለፉ ፡፡ የስፖርት ሚኒስትሩ በጉዳዩ ዙሪያ ሲሰሩ ከተነሱት አጀንዳዋች መካከል የቡድኑ ስያሜ ነገር ይገኝበታል ፡፡ ቡድኑ ጥንካሬን እንዲላበስ ‹ አንበሳ › ማለት እንደሚገባ ቢያስቡም ይህ አንበሳ ከሌሎቹ ሀገሮች በምን ይለያል የሚለውን ጥያቄ መመለስ አስፈልጎ ነበር ፡፡ እናም ‹ Indomitable › የሚል ቃል ከፊቱ እንዲገባ ስምምነት ተደረገ ፡፡ ዘንድሮ ግን አንበሶቹ የሉም ፡፡ ይህ ያስቆጫቸው የቀድሞዎቹ እነ ሮጀር ሚላ ባለጌ ወንበር ላይ ተሰይመው ‹‹ አንበሳ ሲያረጅ የዝምብ መጫዎቻ  ይሆናል ! ›› እያሉ ነው አሉ ፡፡

የሴኔጋል ብሄራዊ ቡድን ስያሜ ‹ The lion of Terenga › የሚል ነው ፡፡ በሀገሪቱ ቋንቋ ‹ Terenga › እንግዳ ተቀባይ ማለት ነው ፡፡ ጥሬ ትርጉሙ እንግዳ ተቀባዩ አንበሳ ሊሆን ነው ፡፡ ስምን አንበሳ ብሎ ተግባሩን ለማዳና የዋህ ማድረግ ሊጋጭ ይችላል ፡፡ ግን ደግሞ ሴኔጋሎች ስፖርት ዝምድናን ማጠናከሪያ መሆኑን በመረዳት ከአስፈሪ ይልቅ ሰላማዊ ስያሜ የመስጠታቸው ሀሳብ ከዚህ የመነጨ ሊሆን ይችላል ፡፡

የሞሮኮዎቹ ‹ The lion of the Atlas › የሚለው ስያሜ ደግሞ ከሴኔጋሉ በተቃራኒ የሚተነተን ነው ፡፡ ሞሮኮዎቹ የሚያምኑት አንበሳ በጫካ ውስጥ ሃይለኛና ጠንካራ መሆኑን ነው ፡፡ ይህ አንበሳ ደግሞ በሀገራቸው ጎልቶና ደምቆ በሚገኘው የአትላስ ተራራ ውስጥ እንደ ድምጻዊው አሸብር በላይ ‹ ይሰለፍና ፈረስ ከእግረኛ
                             እኔ ነኝ ያለ ይሞክረኛ ! › እያለ የሚፈነጭ ነው ፡፡ እናም ቡድናቸውም የማይደፈር እንዲሆን ከመፈለግ አንጻር የተነሱ ይመስላል ፡፡ ከአፍሪካ ዉጪም ቡልጋሪያ ‹ the lions › ፣ ኢራቅ ‹ the Babylon lions › ፣ ሉክሰምበርግም ‹ the lions › የሚል መጠሪያ ያላቸው መሆኑን ስንረዳ ልንገረም እንችላለን ፡፡

አዳኝ አእዋፋት


ማሊ / The eagles / ፣ ናይጄሪያ / The super eagles / ፣ ሱዳን / Desert Hawks / ፣ እና ቱኒዚያ / The eagles of Carthage /               ንስር አሞራና ፋልኮን ከረጅም ርቀት መሬት ላይ ያለ እንቅስቃሴን አጥርተው ይመለከታሉ ፡፡ አይናቸው ለአጉሊ መነጽር መፈብረክ መንስኤ ሆኖ ቢገኝ እንኳ አይበዛበትም ፡፡ በሚገርም ፍጥነት ወደ ታች ተምዘግዝገው የሚበሉትን ነገር ገቢ ማድረጋቸው ሲታይ ለሚሳይል መፈጠር ለምን መነሻ አልሆኑም ብሎ እስከ መከራከር ያደርሳል ፡፡

ንስር አሞራ ረጅም እድሜ ከሚኖሩ አእዋፋት መካከል አንደኛው ነው ፡፡ 70 ዓመት ይኖራል ፡፡ እዚህ እድሜ ላይ የሚደርሰው ግን ጠንካራ ውሳኔዋችን በማሳለፍ ነው ፡፡ በተለይም 40 ዓመት ሲሞላው እንስሳትን ሰቅስቆ የሚይዝበት ረጅም ጥፍሩ መያዝ ያቅተዋል ፡፡ ስጋን ቦጭቆ የሚያነሳው የአፉ መንቆር ይጣመማል ፡፡ ትልቁ ክንፉ ለመብረር ያስቸግረዋል ፡፡ ስለዚህ መሞት ወይም በአስቸጋሪ ፈተና ውስጥ ማለፍ ከተባሉ አማራጮች ጋር ይፋጠጣል ፡፡ ቀጣይ ዕድሜ ያስፈልገኛል ካለ የአፉን መንቆር ከድንጋይ ጋር እያጋጨ ማስወገድ ይኖርበታል ፡፡ ክንፎቹንም ነቅሎ መጣል ፡፡ ይህንን ተግባር በከባድ ስቃይ ውስጥ አልፎ ከከወነ ከአምስት ወራት አስቸጋሪ ጉዞ በኃላ አዲስ ክንፍና መንቆር ያወጣል ፡፡ እናም ቀጣዩን ሰላሳ ዓመታት በአስተማማኝ ሁኔታ ይኖራል ፡፡

ይህን አስቸጋሪ የህይወት ጉዞና ጥንካሬ በማሰብ ለቡድናቸው ስያሜ የሰጡ ሀገሮች መነሻቸው ለክፉ አይሰጥም ፡፡ ችግሩ ዉጤት ላይ ነው፡፡ ቱኒዝያ አንድ ግዜ ፣ ናይጄሪያ ደግሞ ሁለት ግዜ ብቻ ነው የአፍሪካን ዋንጫን ያነሱት ፡፡ ከዚህ አንጻር ባለ ስያሜዋቹ ሀገሮች ዛሬም መንቁራቸውንና ጥፍራቸውን ከድንጋይ ጋር በመጋጨት ላይ የሚገኙ ይመስላል ፡፡

የሀገራችን ‹‹ ዋሊያዋች ›› የስያሜ መነሻ

የኢትዮጽያ ብሄራዊ ቡድን ‹‹ ዋሊያዋቹ ›› የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ከምን አንጻርና መመዘኛ እንደሆነ የሚያብራራ መረጃ ማግኘት አልቻልኩም ፡፡ ይሁን እንጂ ለእውነት በጣም የቀረበ ግምት መሰንዘር ይቻላል ፡፡ ስም አውጪዎቹ ለመረጣ መነሻ የሆናቸው ሀገራችንን የሚያስጠራ ነገር የመፈለጋቸው ጉዳይ ነው ፡፡ ከዚህ አንጻር ኢትዮጽያ ሲባል ምንድነው ገዝፎ ሊነሳ ወይም ሊታይ የሚችለው መገለጫ የሚለው ሀሳብ - ሀሳባቸውን እንዳፋፋመው አይጠረጠርም ፡፡
በወቅቱ ባንኖርም የወደቁና የተወሰኑ ነገሮችን እንገምት ፡፡

. ኢትዮጽያ ነጻነቷን ጠብቃ የቆየች ብቸኛ አፍሪካዊ ሀገር ናት
. ኢትዮጽያ የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎችን በጦርነት በማሸነፍ የምትታወቅ ብቸኛ ሀገር ናት
. ኢትዮጽያ የሰው ልጅ መገኛ ሀገር ናት
. ኢትዮጽያ የቡና መገኛ ሀገር ናት
. ኢትዮጽያ 13 ወራት ጸሃይ የምታበራ ሀገር ናት
. ኢትዮጽያ የራሷ የሆነ ፊደል ያላት ብቸኛ አፍሪካዊ ሀገር ናት
. ኢትዮጽያ በሌላው ዓለም የማይገኙ ብርቅዬ እንስሳት ባለቤት ናት
እናም አንዱን ካንዱ  የግድ አበላለጡና ብርቅዬ የዱር እንስሳቱ ነገር ቀልባቸውን አሸነፈው ፡፡ በሀገራችን ብርቅዬ የሚባሉት አጥቢ እንስሳት ደግሞ ዋሊያ ፣ ቀይ ቀበሮ ፣ የስዋይን ቆርኬ ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ ፣ የሚኒሊክ ድኩላ እና የደጋ አጋዘን ናቸው ፡፡ እነዚህን ሲያወዳድሩ ደግሞ ምርጫቸው ዋሊያ አይቤክስ ላይ አረፈ ፡፡ እናም የብሄራዊ ቡድኑን መጠሪያ ‹‹ ዋሊያዎቹ ! ›› አሉት ፡፡

ዋሊያ ምኑ ይስባል ?

ወንዱ ዋሊያ ክብደቱ በአማካኝ 120 ኪሎግራም ነው ፡፡ በጣም ከሚስበው ሰውነቱ አንደኛው ጠመዝማዛውና ጉጣሙ ቀንዱ ነው ፡፡ የቀንዱ ርዝመት 110 ሴ.ሜ ያህል ሲሆን በቀንዱ ላይ ያሉ ጉጦች የእድሜ ክቦች ናቸው ፡፡ ዋሊያ ትልቁ ዕድሜው ከ 12- 15 ነው ፡፡ ቀንዱ ላይ አስር ጉጦች ከታዩ አስር አመት አካባቢ እንደሆነ ይገመታል ፡፡ ይህ ስሌት የፈረንጆቹ እንጂ በሀገራችን የተደገፈ ማስረጃ አላየሁም ፡፡ ቸኮሌት የመሰለው መልኩና ጺሙም አይን ወጣሪዋች ናቸው ፡፡ የሚኖረው ከ2500 እስከ 4000 ሜትር በሚደርስ ተራራ ላይ ነው ፡፡ ብዙ ውሃ ባያገኝ ግድየለውም ፡፡ ሳሩ ላይ የማይጠፋውን ጤዛ ከላሰ ‹‹ ተመስገን ! ›› ለማለት ይበቃል ፡፡ 

አካባቢው በብርድ ወራት በረዶ የሚሰራ መሆኑ ለዋሊያ አይስክሬም እንደ መላስ ሳይጠቅመው አይቀርም ፡፡ ዋሊያ ልክ እንደ ጭላዳ ዝንጀሮ ገደል ለገደል ሲሮጥ እወድቃለሁ ብሉ አይሰጋም ፡፡ ይህም ጠላቶቹ እንዳይደርሱበት ሁነኛ ምሽግ ሆኖታል ፡፡

የዋሊያ ውክልና ነገር ?
ዋሊያ በስሪያ ወቅት ካልሆነ በስተቀር ብቸኛ ነው ፡፡ ሲበላና ሲንቀሳቀስ የሚታየው በማለዳና ሲመሻሽ ነው ፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉ ግዜያትን የሚያሳልፈው ጥሻና ገደላ ገደሉ ውስጥ በመደበቅ ነው ፡፡ ማህበራዊ ህይወቱ እጅግ የተቆጠበ ፣ በጥርጣሬ ላይ የተመሰረተ ነው ፡፡ ከሰሜን ትላልቅ ተራራዋች ወደ ታች ወርዶ ለመኖር ፣ አካባቢውን ለመጎብኘትና የሌሎችን ህይወት በአንክሮ ለማጤን ፍቃደኛ አይደለም ፡፡ ‹‹ አትድረሱብኝ- አልደርስባችሁም ! ›› የሚል ሎጎ አሰርቶ ዘወትር የሚያውለበልባት ይመስላል ፡፡ 

የዚህ ብሂል መነሻን ለመፈተሸ ስብሰባ ቢጤ ቢዘጋጅ የዋሊያ ምላሽ የአካባቢዋቹን ሰዋች መሰረት ያደረገ ሊሆን ይችላል ‹‹ የራሷን የማትሰጥ የሰው የማትነካ ኢትዮጽያ መሆኗን አልተረዱም ለካ ! ›› ስለሚሉ ፡፡ መሬትም ዳገትም ላይ የሚኖረው ጭላዳ ዝንጀሮ ግን ለዚህ የዋሊያ መፈክር ‹‹ አይሰማም ! ›› የሚል ምላሽ ሰጥቶ ተጎራብቶታል ፡፡ ዋሊያ ማህበራዊ መስተጋብሩ ቁጥብና ገለልተኛ ከሆነ እንዴት ለምሳሌነት ሊበቃ ቻለ የሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት ይኖርበታል ፡፡ በኢትዮጽያ ብቻ የሚገኙትን ሌሎች ብርቅዬ እንስሳት ትተን ከቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮ አንጻር ልናነጻጽረውና ልናወዳድረው እንችላለን ፡፡

እንደሚታወቀው ቀይ ቀበሮ አይጥ እየተመገበ የሚኖር እንስሳ ነው ፡፡ ማህበራዊ ህይወታቸው ጠንካራ ነው ፡፡ ለማህበራዊ ሰላምታና ድንበራቸውን ለመቃኘት ማለዳ ፣ ከሰዓትና ሊመሻሽ ሲል ይሰባሰባሉ ፡፡ ሌሊቱንም አብረው ያሳልፋሉ ፡፡ የጋራ ምግባራቸውም የሚገርም ነው ፡፡ ምግብ መካፈል ፣ ወዳጅነትን የሚያሳይ መተሻሸትና በጥርስ መነካካት ፣ መባረርና የቀልድ ጸብ በዝቶ ይታይባቸዋል ፡፡ ድንበራቸውን የሚከልሉት በሽንታቸው ፣ በዓይነምድራቸውና መሬቱን በመቧጨር ነው ፡፡ የበሉትንም በማስመለስ ቡችሎቻቸውን ይቀልባሉ ፡፡

የቀይ ቀበሮ ልዩ ባህሪ በእጅጉ አዳኝ መሆኑ ነው ፡፡ አይጥ ለማደን በትዕግስት ያደፍጣል ፡፡ ታዳኙ ቀለበት ውስጥ ገብቷል ብሎ ሲያስብ ሁለት እግሮቹን ወደ ላይ አንስቶ ወደ መሬት በመወርወር በአፍንጫው ሰርስሮ በመግባት አይጡን አንጠልጥሎ ያወጣል ፡፡ ይህን ተግባር 90 ዲግሪ ላይ ያረፈ ምርጥ የቅጣት ምት ፣ ከማዕዘን የተሻማ ኳስን ነቅንቆ በጭንቅላት እንደማስገባት አሊያም ወደ ጎል የተመታች አደገኛ ኳስን ተወርውሮ እንደመያዝ ሊመሰል ወይም ሊቆጠር ይችላል ፡፡ ታዲያ ቀይ ቀበሮ በጥሩ ምሳሌነቱ ለምን ቀዳሚ የብሄራዊ ቡድናችን ስያሜ አልሆነም ብንል እንደመሳሳት አያስቆጥርም ፡፡

ጭላዳ ዝንጀሮም ለቡድናችን ስያሜ ተመራጭ የሚሆንበት አግባብ አለ ፡፡ አንደኛው ልክ እንደ ዋሊያ የመልኩና የአቋሙ ጉዳይ ነው ፡፡ ጸጉር የሌለው ቀይ ደረቱ በእጅጉ ይስባል ፡፡ ወንዱ አንበሳን ያስታውሳል ፡፡ በጎፈሬው ማለት ነው ፡፡ የጅራቱ ጫፍም ልክ እንደ አንበሳ ጎፈሬያም ነው ፡፡ አፉን እየከፈተ ሲራመድ ያስደነግጣል ፡፡ የጭላዳ ልዩ ባህሪ በጋራና በመንጋ መኖራቸው ነው ፡፡ ቀኑን የሚያሳልፉት እንደ ዋሊያ በመተኛት ሳይሆን በእጃቸው ሳር በመጫር ነው ፡፡ በጣም ‹ ቢዚ › ናቸው ፡፡ አንዳንዴ ርስ በርስ ለመፈታተሸና ሚስት ለመጥለፍ የሚያደርጉት ሩጫና ትግል ምን ያህል ጠንካራ አትሌትና ቡጠኛ መሆናቸውን ያስረዳል ፡፡ ነገረ ስራቸው ሁሉ ስፖርታዊ ነው ፡፡ ታዲያ ለምን ከስፖርቱ ጋር አልተያያዙም ቢባል ከላይ የቀረበው ማስረጃ ያዋጣል ፡፡

በርግጥ ጭምቱ ዋሊያ ፣ ሜዳ ሳይሆን ተራራ ይመቸኛል የሚለው ዋሊያ ፣ ከሌሎች እንስሳት ጋር በሰንበቴና ዕቁብ መገናኘት ያልፈለገው ዋሊያ እንዴት ከኳስ ጋር ተያያዘ ? ከብርቅዬዋቹ እንስሳት ጋርስ በአግባቡ ተወዳድሮ ነው ያሸነፈው ? ይህ ውክልናስ ከሌሎች አፍሪካ ሀገራት አንጻር ሲታይ ምን ያህል የሰመረ ነው ?  ምክንያቱም አዳኝ አይደለም ! ራሱንና ጓደኞቹን አስተባብሮ የሆነ ተዓምር ወይም ለውጥ ለማምጣት ተነሳሽነት የሚታይበት አይደለም ! እንቅልፋም እንጂ ሰራተኛ አይደለም ! ግልጸኝነት ይጎድለዋል ! በቡድን ለመኖርም ሆነ ለመተጋገል የፈጠነ አይደለም ፡፡ ውድ የኢትዮጽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ‹ ፈሪ ለእናቱ › ብሎ የተደበቀን እንስሳ ፣ በዘመኑ ሂስና ግለ ሂስ ግምገማ ሂሳብ ቢታይ C- ሊያገኝ የሚችልን እንስሳ እንዴት ለብሄራዊ ቡድን መጠሪያነት አበቃችሁት ?  በቀለሙ ? በቀንዱ ? በጺሙ ? በተራራ አፍቃሪነቱ ? ነው ዋሊያም በእውቀት ሳይሆን በእምነት የመስራት ሳይንስ ልዩ ዋጋ እንዳላት ተረድቷል ፡፡

የተዘነጉ አማራጮች
‹‹ ዋሊያዋቹ ›› የተባለው ብሄራዊ ቡድናችን ልክ እንደ ዋሊያ ለ 31 ዓመታት ወደ አፍሪካ ውድድር አልወጣም በማለት ተደብቆ ነበር ፡፡ የእንስሳው ተግባር ተጋብቶባቸው ይሆን ; ደቡብ አፍሪካ ላይስ በ ‹ ዋሊያ › ተግባር ነው ፍልሚያውን እንዲያካሂዱ የሚጠበቀው ? ህብረትና ወረራ ፈጥረው ዝሆን ፣ ነብር ፣ ንስር አሞራ ፣ የበረሃ ተኩላንና የመሳሰሉትን ለማጥቃት የተለየ ስነ ልቦና ሰንቀው ይሆን ? አይታወቅም ፡፡

ኢትዮጽያ ለብሄራዊ ቡድንዋ ልዩ ስያሜ ለማውጣት እንደ ባህር የሰፋ አማራጭ ውስጥ የተቀመጠች ሀገር መሆኗም መጠቀስ ይኖርበታል ፡፡ ብቸኛ ባለ ቋንቋ ሀገር በመሆኗ ‹‹ ፊደል ›› ፣ የቡና መፈጠሪያ በመሆኗ ‹‹ ቡና ›› ፣ ተራራማ ሀገር በመሆኗ ‹‹ ራስ ዳሽን ›› ፣ ጀግና የበቀለባት በመሆኗ ‹‹ አድዋ ›› የሚል ስያሜ ለማውጣት ማን ይከለክላታል ፡፡
ቀደምት የስልጣኔ ባለሟል በመሆኗ ‹‹ አክሱም ›› ፣ የትልቅ ወንዝ ባለሃብት በመሆኗ ‹‹ አባይ ›› ፣ በተአምረኛ ሃውልቷ ‹‹ ላሊበላ ›› ፣ ብሎ ለመጥራትም አማራጭ አለ ፡፡

ተአምር ከሚያሳዩና በቱሪስት በብዛት ከሚጎበኙ ብሄር ብሄረሰቦች ተግባር ውስጥ የጎላውን ማውጣትም ይቻላል ፡፡ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ዘጠኝ ቅርሶቻችንም እኛን ለማስተዋወቅ ዓለማቀፍ መታወቂያ ያላቸው መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል ፡፡

ኢትዮጽያ በተፈጥሮ ድሃ ሳትሆን ድሃ ሆና ቆይታለች ፡፡ በርካታ ወንዞች እያሏት በውሃ ጥም ፣ በኤሌትሪክ ሃይልና በድርቅ ቅጥል ብላለች ፡፡ በዚህ የተለመደ አባባል መሰረት ቆይታችንን ብንገመግመው ከሚከተለው አባባል ጋር ያላትመናል ‹‹ በርካታ ድንቅና ውብ መወኪያ ስም ቢኖራትም ስም ማውጣት አልቻለችም ! ››

ስምን መልዓክ ያወጣዋል የሚባለው አባባላችንና ‹‹ ዋሊያዋቹ ›› ምንና ምን ናቸው ?

ለማንኛውም መልካም ጥቅስ ሳይሆን መልካም ዕድል - ለዋሊያዋች !!!

ይህ ጽሁፍ በቁም ነገር መጽሄት የጥር ወር ዕትም ላይ የወጣ ነው

Saturday, January 12, 2013

የኮንዶ ጨበጣ



‹‹ ግንባታቸው የተጠናቀቀ ይህን ያህል ሺህ ቤቶች የዕጣ አወጣጥ ስነስርዓት ተከናወነ ››
ዕጣው ፍትሃዊና ግልጽ መሆኑን እናምን ዘንድ ድርጊቱ በአውራው ቴሌቪዥን በቀጥታ ስርጭት ተላለፈ፡፡

ሀ . ከንቲባው የዕድላችንን ሶፍትዌር ሲጫኑት ይጨበጨባል፡፡
ለ . በኮምፒውተር የተመረተው ዕድል ምርቱን በወረቀት አትሞ የከፊል እድለኞች ስም ሲዘረዘር ይጨበጨባል ፡፡
መ . የቤት የለሹን ነዋሪ ስቃይ ለመቅረፍ መንግስት ምርጡን ፓሊሲውን ምርኩዝ አድርጎ ጥራታቸውን የጠበቁ ቤቶችን እየገነባ መሆኑን ባለስልጣናት እያስጎመዡ ሲያቀርቡት ይጨበጨባል ፡፡
ሰ . ዕጣ የወጣላቸው ቤቶች  ቁልፍ ከሶስት ወራት በኃላ ለእድለኞቹ እንደሚሰጡ ሲገለጽ በጣም ይጨበጨባል ::
ረ . ቀሪዎቹም ሆድ እንዳይብሳቸው ‹ ይሄን ያህል ሺህ የሚደርሱ ቤቶች ግንባታ ደግሞ 80 ከመቶ ተጠናቀዋል › ሲባል ይጨበጨባል

ጭብጨባችን በቀላሉ የሚቆም አይደለም ፡፡ አንዳንዴ ጭብጨባችንና የህግ ሰዎች ጽሁፍ የትኛውን የዘር ሀረግ ቆጥረው ዘመዳሞች እንደሆኑ ይደንቀኛል ፡፡ የባለሙያዎቹን ጽሁፍ እያነበቡ ነው እንበል፡፡ አንዱ ረጅም ዓረፍተ ነገር አለቀ ሲሉ ‹ ወይም › የተባለው አማካኝ ቃል ሀሳቡን ይቀበልና ተጨማሪ ቁመት ይፈጥርለታል፡፡ ይኀው ‹ ወይም › እግሩ እስኪደክመው ድረስ ቃላቱን አንቀርቅቦ በረጅሙ ይለጋዋል ፡፡ ጎሽ በአራት ነጥብ ፋታ ልውሰድ  ነው ብለው ሲያስቡ ሌላ ‹ ወይም › ሀሳቡን ጎትቶ እንደ ሀረግ ሲያጥመለምለው ያያሉ ፡፡ እኔ የአራት ነጥብ ጥቅም ይበልጥ የሚገባኝ እንደዚህ አይነት ጽሁፎችን ሳነብ ነው ፡፡
የኮንዶ ጭብጨባም በማይታይ ‹ ወይም › የተሳሰረ ነው ፡፡ ስማቸው ጋዜጣ ላይ ለወጣ ዕድለኞች ዘመድ ወዳጅ ያጨበጭባል ፡፡ የነዎሪዎችን ደስታ የሚያብራራው የቲቪ/ሬዲዮ ፕሮግራም ሲታይና ሲደመጥ ይጨበጨባል ፡፡

ከላይ ይጨበጨባል ያልንባቸውን አንዳንድ አንቀጾች በአግባቡ ስንመረምር ግን በከንቱ የተጨበጨበላቸው ነገሮች መኖራቸውን እንረዳለን ፡፡

የማስረከቢያ ግዜ

መንግስት ቤቶችን ሲመርቅ ከ 3 ወር በኃላ ወይም በጣም በፈጠነ ሁኔታ ቁልፍ አስረክባለሁ ማለቱ የተለመደ ነው ፡፡ የፈጠጠው እውነታ ግን ይህ አይደለም ፡፡ ትልቅ ማሳያ የሚሆነው የአምስተኛና የስድስተኛ ዙር ቤቶች ጉዳይ ነው ፡፡ መንግስት ዕጣውን ያወጣው ቤቱ ሳያልቅ ምናልባትም ገና ከመሰረት ደረጃ ፈቅ ሳይል በመሆኑ የ5ኛ ዙር ዕድለኞች ሁለት ዓመት የ6ኞቹ ደግሞ ዓመት ገደማ ቤታቸውን ለመረከብ ግዜ ወስዶባቸዎል ፡፡ የአዲስ አበባ መስተዳድር በዚህ መሃል በጣም ቢያንስ ሁለት ወይም ሶስት ግዜ ቁልፍ ልናስረክብ ነው በማለት መግለጫ ሰጥቶ ዋሽቷል ፡፡

‹‹ ጨበጣው ›› ለምን አስፈለገ ?

በአንድ በኩል ከፍተኛ የህዝብ ፍላጎት የመኖሩን ያህል በሌላ በኩል መንግስትም ይህን ክፍተት ሞልቶ እውቅናና ድጋፍ ማግኘትን ይፈልጋል ፡፡ አቅርቦቱና ፍላጎቱን ግን ማጥበብ አልተቻለም ፡፡

መንግስት እንደ ህዝብ አገልጋይነቱ የሚለካው በሚታዩ ውጤቶች መሆኑ ይታወቃል ፡፡ ይሁን እንጂ ዓመት መጀመሪያ ላይ የሚታቀዱ ዕቅዶች ወሩ በፈጠነ ቁጥር በየደረጃው የሚገኙ አስፈጻሚዎችን ያስጨንቃሉ ፡፡ ታዲያ የአዲስ አበባ ቢሮዎች ዕቅድንና ውጤትን ለማጣጣም ወረቀት ላይ መደነስ ግድ ይላቸዋል ፡፡ ያልተሰራውን ተሰራ፤ የተጀመረውን ደግሞ ከዕቅድ በላይ ተከናወነ በማለት ዳንሱን ከጥሩ የቋንቋ ህብር ጋር ያዋህዱታል ፡፡ ላይ ያሉት ዳኞችም ‹‹ ለዛሬ ተሳክቶልሃል ! ›› በማለት በጥሩ ጭብጨባ ያሳልፉታል ፡፡ ይህን መሰሉ በወረቀት መወሻሸት በጣም የተለመደ ነው ፡፡ እናም ያላለቀውን ቤት አልቋል፤ ያልተጀመረው ቀጣይ ግንባታ 80 ከመቶ ደርሷል ተብሎ ሪፖርት የሚደረገው በዚህ ዓይነት የተለመደ ስልት በመሆኑ የማይፈለገውን ‹‹ ጨበጣ ›› እንዲወለድ አድርጓል ፡፡

ሌላው የአዲስ አበባ መስተዳድር ችግር ስራ ተረባርቦ እንደሚጀመር ሁሉ ተረባርቦ መጨረስ የሚባል ዕቅድ አለማወቁ ነው ፡፡ ግንባታዎች ሲጀመሩ አንድ ሁለቴ ሰብስብ ብሎ መጎብኘትና ቀጣይ አቅጣጫ መስጠት ተለምዷል ፡፡ ይህም ‹ ክትትልና ግምገማ › የተባለውን የቢኤስሲ ቅጽ ለማሳካት ግድ ስላለ ነው ፡፡ ይሁን እንጂ ክትትሉ 40 ከመቶው ላይ የተጀመረ ከሆነ እነ 80፤ 90 እና 100 ፐርሰንቶች ምን ይመስላሉ ብሎ የሚፈትሽ አይደለም ፡፡ ላይ ያለው አመራር አንድም በመሰላቸት አንድም ታች ያለውን አመራር በማመን / ምክንያቱም በእውቀት ሳይሆን በእምነት መምራት አስፈላጊ ነውና / የሚያመጣለትን ሪፖርት በመቀበል እንዲሳሳት ፤ ዋሾ እንዲሰኝ ብሎም እንዲታዘንበት መንገዱን ራሱ ያመቻቻል ፡፡

‹ ጨበጣው › የቱንም ያህል ሀሰት ቢሆን እንኳን አንዳንዴ ከፖለቲካ አንጻር አስፈላጊ እንደሚሆንም ግምት ውስት ማስገባት ያስፈልጋል ፡፡ ምክንያቱም የደረሱ ተስፋዎች የተራቡ ሰዎችን ወዳላስፈላጊ ተቃውሞ ወይም ግጭት ከመክተት ይልቅ ‹ ጠባቂነታቸውን › እንዲያለመልሙ የሚገፋፋ ነውና ፡፡

ሁለተኛ ዙር ‹‹ ጨበጣ ››

ሁለተኛው ጨበጣ ከቁልፍ መረከብ በኃላ ያለውን ገጽታ የሚመለከት ነው ፡፡ ‹‹ ቁልፍ ማስረከብ ›› ከሚለው ሀረግ ትርጓሜ እንጀምር
፡፡ እንግዲህ በአማርኛ መግባባት እንደምንችለው አንድ የኮንዶሚኒየም ዕድለኛ ከአስተዳደሩ የቤት ቁልፍ ተረከበ የሚባለው ቤቱ አስፈላጊ የተባሉትን ግብዓቶች አሟልቶ ከተጠናቀቀ በኃላ የተዘጋውን ቤት ከፍቶ በመግባት ሲረካና ጎርደድ - ጎርደድ እያለ ሲቃኝ ነው ፡፡ በዚያ ላይ ዘመድ ወዳጅ ከኃላ ሆኖ ያን የፈረደበት ጭብጨባ ሲያዘንብለት ነው ፡፡

ይሁን እንጂ  ይህ ትርጉም ዛሬ በሰሚት ሳይት ቤታቸውን ለተረከቡ 5ኛና 6ኛ ዙር ባለእድሎች አልሰራ ብሏል ፡፡ እንዴት አላችሁ ?

ዕድለኞች አስፈላጊውን ፎርማሊቲ ካሟሉ በኃላ ከሚመለከተው ክፍል ተሰልፈው ቁልፉን ተረከቡ ፡፡ ቤታቸው ሲደርሱ ግን አብዛኛዎቹ በሮች ክፍት ነበሩ ፡፡ ‹ እንዴ ቁልፍ ሳንረከብ ቤቱ አየር ባየር ተመረቀ እንዴ ?! › ቢሉም ተሳሳቱ አይባልም ፡፡ 

እየቆዩ ሲሄዱ ግን የበሮቹ መከፋፈትን እየደነገጡ  ይረዳሉ ፡፡ አብዛኛዎቹ ቤቶች በራቸው የውሃ ልክ ክፍተት ስላለበት ፣ የመስታውት አለመኖር ፣የመክፈቻና የመዝጊያ ቁልፎች ባለመሰራታቸውና በሌሎች ምክንያቶች ሊዘጋ የቻለ አልነበረም ፡፡

መንግስት እንዴት ነው ክፍቱን የሰነበተ ቤት ቁልፍ ተረከቡ ብሎ የሚያውጀው ? እንዴትስ ነው የተጣመመ በር ፣ መዝጊያና መክፈቻው የማይሰራ ቤት ላስረክብህ እያለ የሚቀልደው ? በሩን ዘግቶ ባለማስረከቡ ምክንያት መስታውቶች እንዲሰበሩ ፣ የሽንት ቤትና የኩሽና ዕቃዎች እንዲሰረቁ ምቹ ሁኔታዎች ፈጥሯል ፡፡ ዕድለኛው ቤቱ የደረሰው በዕድሉና በነጻ ብቻ ነው እንዴ ? ለከፈለው ገንዘብ ተመጣጣኝና ትክክለኛ ዋጋ የማያገኘውስ በምን ስሌት ነው ? 
አስተዳደሩ ቁልፍ ከማስረከቡ በፊት የእያንዳንዱን ቤት ችግርና ጉድለት መፈተሸ ቢኖርበትም ይህን ‹ አብይ  › ውሳኔ ‹ ብ ›ን ገድፎ  ‹ አይ › በሚል በማንበቡ የመጣ ህጸጽ አስመስሎበታል ፡፡

ኮንዶና ጥራት

የነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ የሚባለው ብሂል የነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው አግሮ ስቶን ወደሚለው መልክ በተጨባጭ ተቀይሯል ፡፡ ኮንዶሚኒየምና ጥራት ሲወራላቸው እንጂ ሲመስሉ ለማየት ገና ብዙ ርቀት መጓዝ ያስፈልጋል ፡፡

የግድግዳው ነገር ከተነሳ የቤቶቹ ክፍሎች የሚከፋፈሉት አግሮ ስቶን በተባለው ወጤት ነው ፡፡ ይህ ግድግዳ ደግሞ የሚሰራው አንዳንዶች የተስፋ ቡድን በሚሏቸው ጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፎች ነው ፡፡ ለነገሩ ማንም ቢሰራው ምክንያት አይሆንም ፡፡ የነገር ምክንያት የሚሆነው በምን ያህል ጥራት ሰሩት ? የሚለው ነው ፡፡ ይህ ምርት በተለይም በቻይና ፣ ማሌዥያና ሩቅ ምስራቆች ምን ያህል ውጤታማ / ከጥራትና ወጪ / እንደሆነ አንብቤያለሁ ፡፡ እውነቱን ለመናገር በኛ ሀገር ምርቱ የሚሰራው መኖሩን ለማሳወቅ ብቻ ይመስላል ፡፡  የበዛ የቸልተኝነት ጭቃ ምርቱ ፊት ላይ እንደተመረገበት ይታያል ፡፡ ምክንያቱም ብዙ ቤቶች ውስጥ ገብታችሁ አካፋዩን ግድግዳ ስትመለከቱ ልታዝኑ አሊያም ሳቅ ሁሉ ሊያመልጣችሁ ይችላል ፡፡

ግድግዳዎቹ የተንገዳገዱ ፣ በቀጭን ጀምረው እንደ ዝሆኔ በሽታ ያለቅጥ ያበጡ ፣ እዚህም እዚያም የአይጥ ጉድጓድ የመሰለ ቀዳዳዎችን ያራቡ ፣ እንደ ጀማሪ ወታደር ‹ አሳርፍ ! › ቢባሉም ለመስመር መዛነፍ ቁብ ያልሰጡ ፣ ማንም እንዳይነካቸው ልመና የሚያበዙ የሚመስሉ አይነቶች ናቸው ፡፡ ብር ያላቸው ሰዎች በርግጫ ሳይሆን በኩርኩም ከጣሏቸው በኃላ አካፋዩን ግድግዳ በብሎኬት እያስገነቡ ነው ፡፡ ህጉ መንግስት የሰራውን ቤት መቀጠልም ሆነ መቀነስ አይቻልም ቢልም ፡፡ አብዛኛው ‹ መናጢ › ግን ‹ አካል ጉዳተኞችን መንከባከብ የዜግነት ግዴታ ነው ! › ለሚለው  የቆየ መፈክር ዋጋ እየሰጠ መሆኑ ታይቷል ፡፡  ይህ መፈክር እንዴት ትዝ አለው ጃል ? ይህን መፈክርስ በምን መልኩ ነው ተግባራዊ እያደረገ ያለው ? የሚሉ ጥያቄዋች ተደራርበው መምጣታቸው አይቀርም ፡፡ ትዝታውን ያጫረው ችግሩ ሊሆን ይችላል -  እንዴት ተገበረው የሚል ጥያቄ ከቀረበ -  መጀመሪያ ግድግዳዎቹ በደንብ ተደርገው በጀሶ ታሽተዋል ፡፡ ጀሶው ከደረቀ በኃላ ደግሞ እንዳቅሚቲ ቀለም እንዲፈስባቸው ተደርጓል ፡፡ ይህን ስራ የጨረሱ አንዳንድ ሰዎች ታዲያ አካፋዩን ግድግዳ እየተመለከቱ ‹‹ እውነት ያ አግሮ ስቶን ነው እንዲህ የሆነው ? ወይ ማየት ደጉ ?! ›› ይላሉ አሉ ፡፡ አንድ ቀን ድንገት ሸብረክ እንዳይል እየሰጉ ጭምር ፡፡

ከላይ እንደተገለጸው ከፍተኛ የሆነ የውጭ በር አሰራር ችግር በዝቶ ይታያል ፡፡ ወደ ማብሰያ ክፍል ስንገባ ቀድሞ የሚተዋወቀን ለዕቃ ማጠቢያነት የተገጠመው ሳህን ቢጤ ነው ፡፡ ይሁን እንጂ በጣም በመሳሳቱና ሲገጠም በአንገቱ አካባቢ ጉዳት ስለደረሰበት እንደተጣመመ በሰለለ ድምጹ ነው ‹ ጌቶች/ እሜቴ እንኳን ለዚህ አበቃዋት ! › የሚለው ፡፡ ስስነቱና ኮሽኳሻነቱን እያገላበጡ ካጉረመረሙ ‹ ጌቶች/ እሜቴ እንዴ ቤት በማግኘትዋ ብቻ ሊደሰቱ ይገባል ! እንዴ ከስንት ሰልፈኛ ወይም ተስፈኛ መሃል ተመንጥቀው እንደወጡ ማሰብ ይገባል ?! › ሊልዎት ይችላል - ይኀው ሳህን ፡፡ አይልም ብለው ቅንጣት አይጠራጠሩ ! ከሁለትና ሶስት ዓመት በላይ ምን ሲሰማ የከረመ ይመስልዎታል ?!

ወደ መጸዳጃ ቤቱ ስናመራ የተሻለ ነገር እናያለን ፡፡ ግድግዳዎቹ በሴራሚክ የተለበጡ ናቸው ፡፡ መቀመጫዎቹና የእጅ መታጠቢያዎቹ ሳህኖች ለሀሜት የሚመቹ አይደሉም ፡፡ በእውነት ጥሩ ናቸው ፡፡ እዚህ ንዑስ ክፍል አቃቂር የሚወጣው ባድመ የኛ ትሁን የኤርትራ / ከህግ አንጻር / እንዳልተለየች ሁሉ የሽንት ቤቱ ሳህንና የገላ መታጠቢያው መኃል ወፈር ያለ ድንበር ሳይሰመር መቀላቀላቸው ነው ፡፡ ቀና ብለው የሚመለከቷት ትንሽ መስኮት ብዙ ቤቶች ላይ ተሰክታ እንጂ ተሰርታ ያለቀች አትመስልም ፡፡ እንደውም አንዳንድ ቤቶች የምትታየው መስኮት እና ኮፍያ ገልብጠው የሚዘንጡ የክፍለሃገር ልጆች ቁርጥ የአባት - የእናት ልጆች ይሆኑባችኃል ፡፡

ሁለተኛው ዙር ‹‹ ርክክብ ››

የከተማው አስተዳደር የነዋሪውና የመገናኛ ብዙሃን ግፊት ሲበዛበት በቅጡ ያላለቁ ቤቶችን ለማስረከብ የተገደደ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም ፡፡ ወይም ደግሞ  ‹ ጉጉው ነገር ግን ድሃው ነዋሪ ትንሽ ከጀመርኩለት ይጨርሰዋል › ከሚል ቀና አመለካከት በመነሳትም ሊሆን ይችላል ፡፡

ችግሩ ግን በዚህ ብቻ የሚያበቃ አለመሆኑ ነው ፡፡ የሰሚት ሳይት ቤቶቹ ብቻ ሳይሆን አካባቢውም ለምቶ ባለመጠናቀቁ አስተዳደሩ ለሌላ ዙር ርክክብ ሳይዘጋጅ እንደማይቀር ይገመታል ፡፡ አብዛኛው ህንጻዋች ዙሪያ ገባቸው ለመፋሰሻና ለመከለያ አጥር ጥቅም ተቆፍረዋል ፡፡ ተቆፍረው ግን አልተገነቡም ፡፡ ከየጉድጓዱ የወጣው አፈር እዚህም እዚያም ተቆልሏል ፡፡ እዚህ ቁልል ላይ የሆነ ነገር ጻፍ ጻፍ ቢደረግ ብዙ ‹‹ ትክል ድንጋዮች››ን መፍጠር የሚቻል ይመስላል ፡፡

ዋና ዋናዎቹን የመኪና መንገድ ማሰብ ከቅብጠት እንዳይቆጠርብን እንተወውና አንዱን ህንጻ ከሌላው ሊያገናኝ የሚችል ቀጭን የእግር መንገድ እንኳ አይታይም ፡፡ ከህንጻዎቹ ፊት ለፊትና ኃላ የሚገኙ ክፍት ቦታዎች የራሳቸው ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ይታወቃል ፡፡ ይሁን እንጂ ሜዳዎቹ የግንባታ ፍርስራሽ፣ አፈር፣ ድንጋይ ወዘተ የሞላባቸው በመሆኑ ዕጣ ፈንታቸው ገና አልታወቀም ፡፡

እነዚህና አነዚያን የመሳሰሉ ኮተቶች ገና አልተነሱም ፡፡ ክረምት ላይ ጉድ ከሚያፈላው ጭቃ ለመከላከል የሚያስችሉ መሰረታዊ የእግር መዝለያ መንገዶች የሉም ፡፡ ይህ በራሱ የነዋሪውን ደስታ የሚያጨፈግግ ነው ፡፡ ገና ብዙ ስራዋች ይቀረዋል በሚል ቤታቸውን አዲስ በርና ቁልፍ ቀይረው የጠፉም ጥቂቶች አይደሉም ፡፡ / ይህ የበር መዘጋት ደግሞ መድረሻ አጥተው ገና ከጠዋቱ ያለ መብራትና ውሃ እየኖሩ ለሚገኙ ነዋሪዋች ትልቅ ጉዳት ይፈጥራል ፡፡ ምክንያቱም መብራት ኃይልና ውሃና ፍሳሽ ብዙ ህዝብ ካልገባ አገልግሎቱን አንለቅም የሚል ብሂል አላቸውና / ለመሆኑ በዚህ መልኩ ነው እንዴ የርክክብን ‹‹ እርካታ ›› ማምጣት የሚቻለው ? ነው ኪራይ ሲቆነድደው ሮጦ ይገባል ፣ ከገባ በኃላ ደግሞ ለራሱ ጥቅም ሲል ‹ የኔን ስራ ይሰራልኛል › የሚል ስትራተጂ ተቀይሶ ነው ? ይህ ስልት አይፈጸምም - ተራ አሉባልታ ነው ከተባለ ግን አስተዳደሩ አሁን የተገለጹ ስራዎችን ለመጨረስ ቢያንስ ሁለት ዓመት ላይ የሚተኛ ይመስላል ፡፡ ምክንያቱም የአስተዳደሩ የፍጥነት ብቃት ወይም ቤዝላይን ይኀው ስለሆነ ፡፡ ነዋሪው እንደተለመደው ብዙ ካለቃቀሰ በኃላ ከእለታት አንድ ቀን ‹‹ ሁለተኛ ዙር ርክክብ ›› ያከናውናል ፡፡

ጠንጋራ አሰራሮችና ያልተወራረዱ ኪሳራዎች

የቤት ዕድለኞች ቤታቸውን የሚረከቡት ሁለት መሰረታዊ ገንዘብ ነክ ጉዳዮችን ሲያሟሉ ነው ፡፡ የመጀመሪያው ዕጣው በወጣላቸው ማግስት የተተመነባቸውን ቅድመ ክፍያ በተባለው ግዜ ውስጥ መክፈል ነው ፡፡ ሁለተኛው ቀሪውን ዕዳ በረጅም ዓመታት የሚከፍሉት ከባንክ ጋር የውል ስምምነት በማድረግ ይሆናል ፡፡ መቼም አባታችን መንግስት ያጣ የነጣነውን እንደ እውነተኛ ልጁ ቢመለከተን ኖሮ በባንክ በኩል የሚያስከፍለንን ተጨማሪ የወለድ ክፍያ ያስቀርልን ነበር ፡፡ የሆኖ ሆኖ ይህም ቢሆን ጥሩ ነው በሚለው ሀሳብ እንለፈው ፡፡

እዚህ አሰራር ውስጥ ግን ጥሩ ያልሆነ ወይም ጠንጋራ ነገር መብቀሉ ነው የሚያስከፋው ፡፡ መንግስት በሁለት መልኩ ተቃራኒ ጉዳዮችን ያከናውናል ፡፡ አንደኛው ወይም ቸር ገጽታው ቤት ተከራዮች ቤቱን ለማስጨረስ ብዙ ወጪ ስለሚያወጡ በየወሩ የሚከፍሉትን ክፍያ የሚጀምሩት ከዓመት በኃላ ነው ማለቱ ነው ፡፡ የእፎይታ ግዜ ይለዋል ሲያሰማምረው ፡፡ ዳሩ ግን ሁለተኛውን መልኩ ስንመለከት ‹ እፎይታው ወደ ወይዞታ / ወይኔ / ይቀየርብናል ፡፡

ሁለተኛው ወይም ክፉ ገጽታው ባንክ ከቤት ባለቤቶች ጋር የረጅም ግዜ ክፍያ ስምምነት ከተፈራረመ ማግስት ወለድ የማሰቡ አሰራር ነው ፡፡ መንግስት በአንድ በኩል ለዓመት ያህል ስለ ክፍያም ሆነ እዳ እንዳታስቡ አደርጋለሁ እያለ በሌላ በኩል ባንክ ገና ካልተገባበት ቤት ላይ ያለ ርህራሄ የደሃ ገንዘብን ይነጥቃል ፡፡ የእፎይታ ግዜ እያለ እንዴት ገንዘባችንን ትወስዳላችሁ ? ተብለው ሲጠየቁ ‹‹ እኛ አትራፊ ድርጅት እንጂ መንግስት አይደለንም ! ›› የሚል ያልታረመ ምላሽ ይሰጣሉ ፡፡ ‹‹ የእፎይታ ግዜ የተሰጠው ዕዳውን ለመክፈል የሚጀመርበት ነው ›› በማለትም ርስ በርሱ የሚጋጭ አስተያየት ያስከትላሉ ፡፡ በነገራችን ላይ ነዋሪዎች የአንድ ወር ዕዳችሁን ባንክ ሄዳችሁ ካልከፈላችሁ ቁልፍ አይሰጣችሁም ተብለውም ተገደዋል ፡፡ ይህ ግዳጅ ለምን እንደተፈጠረም ግልጽ አይደለም ፡፡ ይህም ለእፎይታ የተሰጠችውን ግዜ በጠረባ መትቶ የዘረጋ አስመስሎታል ፡፡

ብዙ የጨነቃቸው ሰዎች የሚከተለውን ጥያቄ ራሳቸውን እየጠየቁ ስለሆነ እስኪ ይሞክሩት ዘንድ ጉዳዩን ላጋራዎ ፡፡
ዕዳ መክፈል  ወይም አገልግሎት ማግኘት ሳይጀመር ወለድን ማስከፈል ማለት ምን ማለት ነው ?

ሀ . እየኮረኮሩ ኪስን መፈተሸ
ለ . እጅን መጠምዘዝ
ሐ . ማጅራት መምታት
መ . መልስ የለውም

የባንክን አሰራር የሚነድፈው መንግስት መሆኑ ይታወቃል ፡፡ መንግስት ለድሃው ካዘነ ብሎም አሰራሩ ሸፋፋ መሆኑን ከተገነዘበ ባንክን ማዘዝ ይችላል ፡፡ መንግስትን ከማርስ ባንክን ከጁፒተር የተገኙ አስመስሎ ማቅረብም ጅላጅነትን ከማጠናከር ውጪ ለእውነታው የሚጠጋ ምለሽ ሊሆን አይችልም ፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ቤቱን ቶሎ የማያስረክበው መንግስት ሆኖ ሳለ ያለግዜው ወለድ የሚያስከፍለውም መንግስት መሆኑ ነው ፡፡ ቤቱን በተባለው ግዜ አስረክቦ፣ ህዝቡ መኖር ቢጀምር እንኳን የወለዱ ሂሳብ ትንሽ በተሻለ ነበር ፡፡ ያው የአንድ አመቷን  ‹ እፎይታ - ወይዞታ › በሚለው ሂሳብ አልፈነው ማለት ነው ፡፡
በየትኛውም አሰራር ቢሆን ማንኛውም ሰው አገልግሎት ላላገኘበት ነገር ወለድም ሆነ ቀረጥ እንዲከፍል አይገደድም ፡፡ ታዲያ የኮንዶሚንየም ነዋሪዎች ‹‹ እጣ ስለወጣላቸው ›› ብቻ ነው ኢ- ፍትሃዊ የሆነ ጫና ያረፈባቸው ?

በአንድ ወቅት ይህን ኢ- ፍትሃዊ ጉዳይ አስመልክቶ የተጠየቁ ኃላፊዎች ‹‹ እናዝናለን ! ›› የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ከጋዜጣ አንብበናል ፡፡ በርግጥ ማዘን አንድ ነገር ነው ፡፡ ሀዘን ግን ኢኮኖሚያዊ ኪሳራውን በፍጹም አያካክስም ፡፡ በመንግስት ስህተትና ቸልተኛ አሰራር የሌለውን ድሃ መውቀጥ ኢ - ሞራላዊ ጉዳይ ነው ፡፡ መንግስት ከልቡም ይሁን ከአንገት በላይ ‹ እናዝናለን › ቢልም ለድሃው ግን ያልተወራረዱ ኪሳራዎች ናቸው ፡፡ ሲጀመር ድሃ ነው - በዚህ ድህነት ላይ ደግሞ ወደፊትም ድህነቱን የሚያወፍሩ ካፖርቶች እንዲደርብ ማስገደድ ፈጽሞ ትክክል ሊሆን አይችልም ፡፡ ይህን የመሰለ ጠንጋራ አሰራር ሳይውል ሳያድር መስተካከል ይኖርበታል ፡፡ ተናቦና ተማምኖ መስራት ያስፈልጋል ፡፡ ህጎችና ደንቦች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ቀጥተኛ እንጂ ያልተገባ ትርጉም እንዳያቅፉ መትጋት ግድ ይላል ፡፡

‎ሁለተኛው ሶማሌ ተራ ‎?




ከ 15 ቀናት በፊት በቁም ነገር መጽሄት ላይ የወረወርኳት ‹‹ የኮንዶ ጨበጣ ›› የምትሰኝ ጽሁፍ ከግራና ከቀኝ ልዩ ልዩ ምላሾችን አስገኝታለች ፡፡

ግራው ፤

በዚሁ መጽሄት በጥር ወር ዕትም ላይ ጉዳዩ የከነከነው አንድ የኮንዶሚንየም ነዋሪ የደረሰበትን ችግር ዘርዝሮ የጽሁፉ ርዕስ ጨበጣ ሳይሆን ለበጣ ቢባል ይገባዋል ብሏል ፡፡

ሌላ አንድ ሰው ጥቂት የቀሩ ያልተዳሰሱ ነገሮችን አስታወሰኝ ፡፡ የሌብነት ወይም የሙስና ጉዳይ ልንለው እንችላለን ፡፡ እንዴት መሰላችሁ ?

በሰሚት ሳይት ያሉ ኮንዶዎች እንደ በርና ሌላ ዕቃ ሁሉ የኤሌትሪክ መሳሪያዎችም የተገጠመላቸው አይደለም ፡፡ እናም እድለኛው እንደተለመደው ተሰልፎ ነው ዕቃዎቹ ተቆጥረው የሚሰጠው - በመርህ ደረጃ ማለት ነው ፡፡ አነዚህ ዕቃዋች ባለሙያዎቹ ሶኬት ፣ ቱ ዌይ ስዊች ፣ ዋን ዌይ ስዊች ፣ ቆጣሪ የሚሏቸውን ማለቴ ነው ፡፡

በተግባር አይን ግን ንብረቱን የሚያስረክቡ ሰራተኞች ለህዝቡ የሚሰጡት እያጎደሉ ነው ፡፡ ከአንዳንዱ ግማሽ ያህል ፡፡ ነዋሪው በወቅቱ ስንት ሶኬት እንደሚያስፈልገው መረጃ አልነበረውም ፡፡ የሰጡትን ልክ እንደ እርዳታ ተቀባይ ‹‹ እግዜር ይስጥልኝ ! ›› ብሎ ነው የተቀበለው ፡፡ ይህ ህዝብ ስንቱ እየጋጠው ትህትናው አያልቅበትም ፡፡ ችግሩ አፍጥጦ የመጣው ቤቱ ገብቶ ለሶኬት የተሰሩ ቀዳዳዋችን ሲቆጥር ነው ፡፡ ቀዳዳዋቹና የተሰጡት ቁሳቁሶች እንደ ሰማይና ምድር የተራራቁ ናቸው ፡፡ ይህን ሲያውቅ ንብረት ሰጪዋች ላይ ማፍጠጥ ጀመረ ፡፡ እነሱም በዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ ‹‹ በስህተት ስለሆነ መጨረሻ ላይ ይሰጥሃል ! ›› እያሉ ሸኙት ፡፡ ህዝቡም አለ ‹‹ አዋ ! ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት አይጠፋም ! ›› የሚሰራ ሰው ሰው ይሳሳታል የሚል ጥቅስ በመጨመርም ነገረ ጉዳዩን እንደ አርማታ ያጠናከሩም ነበሩ ፡፡ ምክንያቱም ይህ ህዝብ ቡቡነቱ አያልቅበትም ፡፡

በኃላ መሳሪያውን የሚገጥሙ የኤሌትሪክ ሰራተኞች በየቤቱ ለስራ መንቀሳቀስ ሲጀምሩ አሁንም ህዝቡ ‹‹ እረ ማስገጠም አልቻልንም ፡፡ አገልግሎቱ ሊያልፍብን ስለሆነ ንብረታችን ይሰጠን ? ›› በማለት መጠየቅም መለመንም አስከተለ ፡፡

‹‹ ለሁሉም ሰው አድለን ስላልጨረስን አሁን መስጠት አንችልም ፡፡ የምትቸኩሉ ከሆነ እየገዛችሁ አስገጥሙ ››
‹‹ ታዲያ መቼ ይሰጠናል ? ››
‹‹ መጨረሻ ላይ ! ››
‹‹ ይሄ መጨረሻ መቼ ነው መጨረሻው ?! ››

መጨረሻው ቅርብ ሊሆን አልቻለም ፡፡ በዚህ የተበሳጨው ህዝብ ፍትህ በሌለበት ከተማ ጉሮሮን ከመሰንጠቅ ገዝቼ ላስገጥም ማለት ጀመረ ፡፡ ይህ ህዝብ ቢበሳጭም ቻይነቱ አያልቅበትም ፡፡ እናም የኤሌትሪክ ሰራተኞች ሀሳቡን ሲረዱ አንድ ሀሳብ ሹክ ማለት ጀመሩ ፡፡ ለነገሩ ሹክታ ሳይሆን ማማከር ጀመሩ ማለት ይሻላል

‹‹ አንድ ሶኬት ውጭ የሚሸጠው 35 ብር ነው ፡፡ እዚህ ግቢ ግን 25 ብር የሚሸጡ ሰዋች አሉ ››
‹‹ ይህማ ጥሩ ነው ፡፡ በል አሳየንና እንግዛ ››
‹‹ ቆይ ደውዬ ልጠይቅላችሁ ›› ባለሙያው አንድ ሰው  ጋ በመደወል ስለዕቃው መኖር ይጠይቃል ፡፡ቀዳዳውን ቆጥሮም የሚያስፈልገውን ብር አሰሪውን ይጠይቃል ፡፡ በሩጫ ብር ብሎ ይሄድና አዳዲስ እቃዋች ይዞ ይመጣል ፡፡  ‹ እንዴት ያለ ቸር ነው › የሚሉ ነበሩ - ምክንያቱም ይህ ህዝብ ምስኪንነት አያልቅበትም ፡፡

ጥቂት ለመጠየቅና ለመጠራጠር የተፈጠሩ ደግሞ ‹‹ ለምን ብቻውን መሄድ ፈለገ ? የህንጻ መሳሪያዎች ሱቅ ሳይኖር የሚገዛው ከነማን ነው  ? ሮጦ ሄዶ ለገዛበት የአገልግሎት የማይጠይቅ የቤቶች ልማት ሰራተኛ በቢኤስሲ ነው በካይዘን ሳይንስ የተገኘ ? ›› የሚሉ ጥያቄዎችን በውስጡ ያንሰላስል ነበር ፡፡

የዚህን እውነት ማወቅ ከባድ አይደለም ፡፡ ከብዙዎች ሆን ተብሎ እየጎደለ የተሰጠው ዕቃ የመጨረሻ ግቡ ለራሱ ለባለቤቱ እንዲሸጥ በመታቀዱ ነው ፡፡ በአዲስ አበባ ታሪክ የራሳቸውን ዕቃ ከሶማሌ ተራ የሚገዙት ባለመኪናዋች ነበሩ ፡፡ ዛሬ ይህ ልምድና ተሞክሮ ተስፋፍቶና ተቀምሮ ሰሚት ሁለተኛው ሶማሌ ተራ ሆኗል ፡፡ በመንግስት ሀገር ?!

በአሁኑ ወቅት በሰሚት ኮንዶ ሳይት ዋናውን የማብሪያና ማጥፊያ / ቆጣሪ / መግጠም አልተቻለም ፡፡ እቃው አስቀድሞ ከተገጠመ በሌቦች ይሰረቃል በሚል ቀድሞ እንዲሰራ አልተደረገም ፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ሶኬቶቹ እየተገጠሙ ቢሆንም የሚመለከተው ክፍል እነዚህን ዕቃዎች ለኤሌትሪክ ባለሙያዋች ማስረከብ ባለመቻሉ ስራው ቆሟል ፡፡ ሁልግዜም ሰራተኞቹ የሉም ፣ ስብሰባ ላይ ናቸው ወዘተ ነው የሚባለው ፡፡ ምናልባትም ያስፈልጋል የተባለውን ዕቃ ለመቸብቸብ እቅድ እየተነደፈለት ይሆን ? የሚል ጠርጣሪ መኖሩ ግልጽ ነው ፡፡ እረ ተቸብችቧል የሚል ርግጠኛም ጥቂት የሚባል አይደለም ፡፡ እና መብራት ኃይል ደግ ሆኖ እንኳ ለአካባቢው ኃይል ለመዘርጋት ቢፈልግ ቆጣሪው ካልተሰራ የህዝቡ ፍላጎት አይሟላም ማለት ነው ፡፡

ቀኙ ፤

‹‹ የኮንዶ ጨበጣ ›› የተሰኘው አርቲክል ያስገኘው ሌላ አዎንታዊ ምላሽም አለ ፡፡ ጽሁፉ በተለቀቀ ሳምንት የከተማው አስተዳደር ሰሚትን ጨምሮ ሌሎች የቤት ልማት ቦታዎችን ተዘዋውሮ ጎብኝቷል ፡፡ ጠበቅ ያለ ትዕዛዝም አስተላልፏል ፡፡ ‹‹ ስራችሁን እስከዚህ ወር ድረስ ካላጠናቀቃችሁ ኮንትራቱን እንቀማችኃለን  ! ››

አስተዳደሩ የህዝብን ስሜት ማንበብና ማዳመጥ ከቻለ አንድ ርምጃ ነው ፡፡ ርምጃው ሙሉ የሚሆነው ግን የመጨረሻውን ውጤት በፍጥነትም በጥራትም ማስገኘት ሲቻል ነው ፡፡ ሌላም ጥቅም አለው ፡፡ ዶ/ር መራራ ጉዲና ኢህአዴግ ጆሮ የለውም የሚል የሰላ ትችት አላቸው ፡፡ ግዜው የምርጫ ሰሞን ሆነም አልሆነም ህዝብ ፈጣን ምላሽ ይፈልጋልና መስማትና ማየት እንደሚቻል በተግባር ማረጋገጥም ፖለቲካዊ ፋይዳ ይኖረዋል ፡፡

አስተዳደሩ ሳይቶችን ከጎበኘ አራት ቀን በኃላ ወደ ሰሚት ሳመራ ሁለት አዳዲስ ነገሮችን ተመለከትኩ ፡፡ አንደኛው ዋና ዋና መንገዶችን ለመስራት ቁፋሮው መጧጧፉን ፡፡ ሁለተኛው በየብሎኩ የተቆፈሩ ጉድጓዶች ውስጥ የግንብ ስራው በተሻለ የሰው ኃይል እየተከናወነ መገኘቱን ፡፡ በርግጥ ጅምሩ እንደተለመደው የአንድ ሰሞን እንዳይሆን ጸሎት ያሰፈልገዋል ፡፡ ለማንኛውም አስተዳደሩ ስራውንም ማጧጧፍ፣ ሌብነቱንም ማስቆም፣ ዘራፊዎችንም መዳኘት ይጠበቅበታል ፡፡ ምክንያቱም ይህ ህዝብ በብዙ ሊካስ ይገባዋልና ፡፡

Thursday, November 22, 2012

የአምባገነኖች ቀልድ



ለተለያዩ ስራዎች የተለያዩ መረጃዎችን ሳገላብጥ ካሰባሰብኳቸው አምባገነናዊ ቀልዶች የተወሰኑትን እነሆ ብያለሁ ፡፡ ካዝናኗችሁ ዘና በሉባቸው ፡፡

ሂትለር በገነት

አዶልፍ ሂትለር  እንደሞተ ራሱን ከሲኦል በር ጋ አገኘው ፡፡ ሲያንኳኳ በሩን ከፍቶ የወጣው ሰይጣን ‹‹ ስምህ ማነው ? ›› ሲል ጠየቀው
‹‹ አዶልፍ ሂትለር ››
 ሰይጣን በጣም እየተገረመ  ‹‹ በምድር ላይ ምን እንደሰራህ አውቃለሁ ፤ ወደ ውስጥ እንዳላስገባህ ቦታ የለም ፡፡ በርግጥ ሲኦል ቢሆንም ለሁሉም ነገር ወሰን አለው፡፡ ለምን ወደ ገነት አትሄድም  ?››
‹‹ አላውቀውም ! ››
‹‹ ይህን መንገድ ተከተል ፡፡ በስተቀኝ በኩል ትልቅ በር ታገኛለህ ፡፡ አታጣውም ››
ሂትለር ባልጠበቀው ጥሩ እድል እየተደሰተ ወደ ገነት ተጓዘ ፡፡ በቀጣዩ ቀን የሲኦል በር ተንኳክቶ ሰይጣን በሩን ሲከፍት እየሱስን ቆሞ ተመለከተ
‹‹ እየሱስ ! እዚህ ምን ታደርጋለህ ?! ›› በግርምት ጠየቀው
‹‹ ከካምፕ ጠፍቼ ነው የመጣሁት ! አመጣጤም የፖለቲካ ጥገኝነት ለመጠየቅ ነው ›› ሲል እየሱስም መለሰ

የስታሊን ግርፍ

            ከጆርጂያ የመጡ የልዑካን ቡድን አባላት ለረጅም ሰዓታት ከስታሊን ጋር ስለ ልማትና እርዳታ ከተወያዩ በኃላ በሚደረግላቸው ትብብር  በመርካት ቢሮውን ለቀው ወጡ ፡፡ ስታሊን ሲጋራ የሚያጨስበትን ትቦ መሳይ ነገር በማጣቱ  ወዲያው አንድ ስራውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ደህንነት  ሰው ጋ ደውሎ ሲጋራ ማጨሻውን ነጥቆ እንዲያመጣ ያዘዋል ፡፡ ነገር ግን  ከ30 ደቂቃ በኃላ ዕቃውን ጠረጼዛ ስር በማግኘቱ የላከው ሰው ጋ በመደወል ትዕዛዙን ትቶ እንዲመጣ ይነግረዋል ፡፡
‹‹ አዝናለሁ ጓድ ስታሊን ! ››
‹‹ምን ተፈጠረ ?! ››
‹‹ ከልዑካን ቡድኑ ግማሽ ያህሉ እኮ ዕቃውን መውሰዳቸውን አምነዋል ፡፡ የተቀሩት ደግሞ ጥያቄው  በሚከናወንበት ወቅት አልፈዋል ›› በማለት ምላሹን በስልክ አሰማ

የመሪዎች ፉክክር

           ንግስት ኤልሳቤጥ፣ ቢል ክሊንተንና ሮበርቱ ሙጋቤ እንደሞቱ ቀጥታ ወደ ሲኦል አመሩ ፡፡ ወዲያው ንግስት ኤልሳቤጥ ‹‹ እንግሊዝ በጣም ናፍቃኛለች፣ መደወል እፈልጋለሁ፡፡ ሁሉም ሰው ምን እያደረገ መሆኑን ማወቅ እፈልጋለሁ ›› በማለት ለ 5 ደቂቃ ያህል አወራች፡፡ ከዚያም ‹‹ ሰይጣን ስንት ነው የምከፍለው ? ›› ስትል ጠየቀች
‹‹ አምስት ሚሊዮን ዶላር ›› አላት ፡፡ ቼክ ጽፋ ሰጠቸውና ወደ ቦታዋ ተመለሰች፡፡ ክሊንተን በኤልሳቤጥ ተግባር በመቅናቱ ‹‹ እኔም ወደ አሜሪካ መደወል እፈልጋለሁ ›› አለ፡፡ ለሁለት ደቂቃም አውርቶ ሂሳብ ሲጠይቅ 10 ሚሊዮን ዶላር ተጠየቀ፡፡ እሱም ቼክ ጽፎ ሰጠ፡፡
ሮበርቱ ሙጋቤም ከማን አንሳለሁ በሚል ስሜት ተነሳስቶ ‹‹ እኔም ወደ ዙምባብዌ መደወል እፈልጋለሁ ፣ ከቤተሰቤና ሚንስትሮቼ ጋር ማውራት እፈልጋለሁ ›› አለ ፡፡ ሙጋቤ ወሬውን ማቋረጥ ባለመቻሉ ለ10 ሰዓታት ያህል አወራ፡፡ ኤልሳቤጥና ክሊንተን ከየት አባቱ አምጥቶ ሊከፍል ነው በማለት መጨረሻውን ለማየት ቋመጡ ፡፡ ሙጋቤ እንደጨረሰ ሂሳብ ሲጠይቅ
‹‹ አንድ ዶላር ! ›› ሲል ሰይጣን መለሰለት
‹‹ ሂሳብ አትችልም እንዴ ?  ይህን ሁሉ አውርቼ  አንድ ዶላር ትለኛለህ ?! ››
‹‹ ባክህ እችላለሁ ! ሂሳቡ ይሔው ስለሆነ ወዲህ በል ! ››
‹‹አዝናለሁ አትችልም ! ››
‹‹ ሰውዬ ምን ነካህ ! ከሲኦል ወደ ሲኦል  እኮ ነው የደወልከው ! ይህ ደግሞ የሀገር ውስጥ ጥሪ ነው ! ›› ሲል አምባረቀበት

የቴይለር ርህራሄ

ቻርልስ ቴይለር እና ሾፌራቸው በመኪና ወደ ዋና መንገድ ሲያመሩ አንድ አሳማ ገጩ ፡፡ አሳውም ወዲያው ሞተ ፡፡ ቴይለርም ለሾፌራቸው ‹‹ እዛ ወዲያ ወዳለው የእርሻ ቦታ ሂድና አሳማው ምን እንዳጋጠመው አስረዳ›› አሉት
ከአንድ ሰዓት በኃላ ሾፌራቸው ከእርሻው ቦታ ከሴቶች ጋር ሲመለስ ተመለከቱ ፡፡ በአንድ እጁ የወይን ጠርሙስ ፣ በሌላ እጁ ሲጋራ ጨብጧል
‹‹ ምን ሆንክ አንተ ;! ››
‹‹ ገበሬው ጠርሙስ ወይን፣ ሚስቱን፣ ሲጋራና ከእኔ ጋር ፍቅር የያዛትን የ 19 ዓመት ልጁን ሰጠኝ ››
‹‹ እንዴት ? ምን ብለህ ነግረሃቸው ነው ? ›› ቴይለር አፈጠጡ
‹‹ እንደምን አመሻቸሁ ! እኔ የቴይለር ሾፌር ነኝ ፣ እናም አንድ አሳማ ገድያለሁ ! ››

የፑቲን ስጋ

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መጥፎ ህልም በሌሊት ቀሰቀሳቸውና እየተጨናበሱ ወደ ፍሪጅ አመሩ፡፡ ልክ ፍሪጁን እንደከፈቱ በመልክ በመልክ ተደርድረው የተቀመጡ ስጋዎች መንቀጥቀጥ ጀመሩ፡፡ በድርጊታቸው በመናደዳቸውም እንደሚከተለው ገሰጽዋቸው
‹‹ አትንቦቅቦቁ !! እኔ የመጣሁት ቢራ ለመጠጣት ብቻ ነው !! ››


የመለስ የጾታ ፍቃድ

አንድ ዝነኛ አርቲስት ክስ ተመስርቶበት ከታሰረ ትንሽ ቆየት ብሎ ነበር ። በዚህን ወቅት አንድ ታዋቂ አትሌት በውጭ ሀገር አስደናቂ ድል ተቀዳጅቶ ወደ አገሩ ሲገባ ጠ/ሚኒስትር መለስ አድናቆታቸውን ለመግለጽ ኤርፖርት ድረስ ሄደው ይቀበሉታል ። አትሌቱም አጋጣሚውን በመጠቀም አንድ አንገብጋቢ ጥያቄ እንዳለው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይናገራል ።
« ምን ችግር አለ ጠይቃ » አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቀለል አድርገው
« ቴዲ አፍሮ የተባለው አርቲስት ካልተፈታ በመጣሁበት አውሮፕላን እመለሳለሁ »
« ወዴት ? »
« ወደ ሌላ ሀገር ፣ ጥያቄዬ ምላሽ ካላገኘ ዜግነቴንም ለመቀየር እገደዳለሁ »
« ወንድም ፣ እንኴን ዜግነትህንም ጾታህንም መቀየር ትችላለህ » አሉት ቆምጨጭ ብለው

የሙሻራፍ ፈተና

ፔርፔዝ ሙሻራፍ ወደ ደልሂ ለስብሰባ ሲያመራ ከህንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ቫጅፔይ ጋር አጭር ቆይታ አደረገ ፡፡ ቫጅፔይ ‹‹ ስለ ካቢኔ አባላትህ እውቀት ምን እንደምታስብ አላውቅም፡፡ የኔ ሰዎች ግን በእጅጉ ጎበዞች ናቸው ›› ይለዋል
‹‹ እንዴት አወቅክ ? ›› ሙሻራፍ ይጠይቃል
‹‹ ቀላል ነው፡፡ ሁሉም ሚንስትር ከመሆናቸው በፊት ልዩ ፈተናዎችን ይወሰዳሉ ፡፡ ቆይ አንድ ግዜ ›› ይልና አድቫኒ የተባለውን ሚኒስትር ጠርቶ ይጠይቀዋል
‹‹  ያንተ ወንድም አይደለም፣ ያንተ እህት አይደለችም ፣ የአባትህ ልጅና  የእናትህ ልጅ ማነው ? ››
‹‹ ይህማ ቀላል ነው፡፡ እኔ ነኛ ! ›› ሲል አድቫኒ ይመልሳል
‹‹ ጎበዝ አድቫኒ ! ›› ቫደፓዬና ሙሻራፍ ተገረሙ
ሙሻራፍ ወደ ኢስላማባድ ሲመለስ ስለ ሚንስትሮቹ አዋቂነት በጣም እየተገረመ ነበር ፡፡ በመጀመሪያ ስብሰባውም በጣም የሚወደውን የካቢኔ አባል ጠርቶ ‹‹ የአባትህ ልጅና የእናትህ ልጅ ማነው ? ያንተ ወንድም አይደለም ፣ ያንተ እህት አይደለችም.፣ እሱ ማነው ? ›› ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ሰውየው ቢያስብ መልሱ ለመጣለት አልቻለም፡፡
‹‹ ትንሽ አስቤ ነገ መልሱን ባመጣስ ? ›› ሲል ያስፈቅዳል
‹‹ እንዴታ ! 24 የማሰቢያ ሰዓታት ተሰጥቶሃል ! ›› ሙሻራፍ መለሰ
ባለስልጣኑ ሚኒስትሮች፣ የካቢኔ ጸሃፊዎችና ትላልቅ ሰዎች ጋ እየደወለ ቢጠይቅ መልሱን ማግኘት አልቻለም ፡፡ ባለቀ ሰዓት ቤናዚር ቡቶ ብልህ ስለሆነች ታውቃለች በሚል ስልኩን መታና ‹‹ የአባትሽና የእናትሽ ልጅ የሆነ፤ ወንድምሽና እህትሽ ያልሆነ ማነው ?›› ሲል ጠየቃት
‹‹ በጣም ቀላል እኮ ነው ፡፡ እኔ ነኛ !! ›› ስትል መለሰችለት ፡፡ የካቢኔው አባል ደስ ብሎት ወደ ሙሻራፍ ደወለ ፡፡
‹‹ ጌታዬ መልሱን አግኝቼዋለሁ ፤ ቤናዘር ቡቶ ናት ›› አለ
‹‹ አንተ ደደብ ! አይደለም ›› አሉ ሙሻራፍ በቁጣ ‹‹ መልሱ አድቫኒ ነው !! ››
አይ ሙሻራፍ ???

የአህመዲንጃድ ቆምጫጫ ምላሽ

የኢራኑ ፕሬዝዳንት መሀመድ አህመዲንጃድ በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ተጋብዘው ስለ ሀገራቸው ወቅታዊ ሁኔታ ንግግር አድርገው ነበር፡፡ ከንግግራቸው በኃላ የተለያዩ ጥያቄዎችን ማስተናገድ ጀመሩ ፡፡
‹‹ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ችግር እንዳለባችሁ ምእራባዊያን ይናገራሉ፡፡ እውነት ነው ; ››
‹‹ ወረኛ በላቸው ! ዛሬ የተሻለ መብትም ሆነ ዴሞክራሲ ያለው ኢራን ውስጥ ነው ››
‹‹ እሺ እዛጋ ጆሮህን እንደ ሴት የተበሳሐው ! ›› ፕሬዝዳንቱ ለሌላ ጠያቂ ዕድል ሰጡ
‹‹ አመሰግናለሁ ፡፡ በሀገራችሁ ምን ያህል ግብረ ሶዶማዊያን ይገኛሉ ; ››
‹‹ በታላቋ አራን ይህን የሚፈጽሙ ሰዎች የሉም ! ››
‹‹ መረጃዎች የሚጠቁሙት ግን በግብረሶዶማዊያን ላይ ኢ- ሰብዓዊ ድርጊት እንደምትፈጽሙ ነው ›› ሌላ ጠያቂ
‹‹ ወንድሜ ጥያቄ መደጋገም ለምን ያስፈልጋል! በሀገራችን የሉም አልኩህ እኮ ! ምክንያቱም ሁሉንም ጨርሰናቸዋል ! ››

የአሳድ ትዕዛዝ

በሀገሪቱ ከተደረገ አጠቃላይ ምርጫ በኃላ አንድ ሚንስትር እየተቻኮለ ወደ ሶርያው ፕሬዝዳንት ሃፌስ አሳድ ቢሮ ይገባል
‹‹ እሺ ! ›› አለ አሳድ ካቀረቀረበት ቀና ሳይል
‹‹ የተከበሩ ፕሬዝዳንት! እጅግ በጣም ደስ የሚል ዜና ይዤ መጥቻለሁ ፡፡ በምርጫው 98.6 ከመቶ አሸንፈዋል፡፡ እርስዎን ያልመረጡት ከ 2 በመቶ በታች የሚያንሱ ሰዎች ናቸው ፤ ከዚህ በላይ ምንም የሚፈልጉ አይመስለኝም ጌታዬ ;! ››
‹‹ እፈልጋለሁ ! እፈልጋለሁ እንጂ አንተ !! ›› አለ አሳድ ካቀረቀረበት ቀና ብሎ እያፈጠጠ ‹‹ በአስቸኳይ ያልመረጡኝን ሰዎች ስም ዝርዝር ለቅመህ አምጣ !!! ››

የማኦ ፈስ

አንድ ቀን የቻይናው ሊቀ መንበር ማኦ የግል ሀኪማቸውን ዶ/ር ዣንግን ጠርተው የሚከተለውን አዘዙት
‹‹ ሆዴን በሚገባ መርምር! ካለፉት ጥቂት ሳምንታት ጀምሮ በጣም እንግዳ ነገር እየገጠመኝ ነው ፡፡ በተደጋጋሚ ያስፈሳኛል ፤ ማለትም በየአምስት ደቂቃው ልዩነት… ይህ ከይሲ ነገር ሊቆም አልቻለም፡፡ እንግዳው ነገር ደግሞ ፈሱ ድምጽ የሌለው እንዲሁም ሽታው የማይታወቅ መሆኑ ነው ››
ማኦ ንግግራቸውን ከጨረሱም በኃላ ፈሱ ፡፡ ዶ/ር ዣንግን ከመድሃኒት ማስቀመጫ ሳጥናቸው ውስጥ የሆነች ጠርሙስ አወጡና
‹‹ ሊቀመንበር ማኦ ይህን መድሃኒት ለአምስት ቀናት በየአራት ሰዓቱ ልዩነት አንድ- አንድ በመውሰድ ተጠቀሙ ›› ብሎ ተሰናብቶ ወጣ
ከአምስት ቀናት በኃላ ማኦ ዶክተሩን አስጠርተው ይጮሁበት ጀመር ፡፡
‹‹አንተ የተረገምክ !! ምን ዓይነት መድሃኒት ነው የሰጠኀኝ ? አሁን ደግሞ በጣም ነው የባሰብኝ ፡፡ ትናንት በወጣቶች ስብሰባ ላይ ንግግር ሳደርግ ያለማቋረጥ እየፈሳሁ ነበር ፡፡ ድምጹ በጣም የሚጮህ ስለነበር አሳፍሮኛል ! ››
‹‹ ሊቀመንበር ማኦ አሁን የመስማትዎ ችግር ተቀረፈ ማለት ነው ›› አለ ዶክተሩ ኮስተር ብሎ ‹‹ አሁን የሚቀረኝ እንደምንም ብዬ የአፍንጫዎን ችግር ማስተካከል ይሆናል !! ››