የባለታሪኩ በኩር ስም አማረ ነው ። አማረ ህዳር
11 ቀን 1926 ዓም በድሬደዋ ተወለደ ። ወ/ሮ ትበልጫለሽ አማረን የወለዱት ለቁልቢ ገብርኤል ተስለው ነው ። ግሪካዊው አባቱ
አማረ መወለዱን ይወቁ እንጂ እንደ አባት ተንከባክበው የማሳደግ ግዴታ እንዳለባቸው ያላወቁ መስለዋል - ወይም ባላወቀ ሸሽተዋል
።
ወ/ሮ ትበልጫለሽ ምን የመሰለውን የሚያምር ስም
ከአማረ ወደ ጻውሎስ የቀየሩት በመጽሀፍ ቅዱስ አዘውታሪ አንባቢነታቸው ነው ። ከዚህ ይልቅ ሁለት ነገሮችን ማሳካት ቢችሉ እንዴት
ጥሩ ነበር ? የባለቤታቸውን የሽሽት ሃሳብ ማስቆምና የባለቤታቸውን ስም እንደ ልጃቸው ማስቀየር ። በጣም ሳስበው አብረው ቢቆዩ < ኞኞ
> ለሚባል ገራሚ ስም ከዚህም ከዚያም ብለው ኢትዮጽያዊ አቻ ማፈላለጋቸው አይቀርም ነበር ።
የአባቱን ናፍቆት በእናቱ ፍቅር ውስጥ ሲያገኝ
የቆየው ጻውሎስ ገና በለጋ እድሜው ራሱን ብቁ ለማድረግ አባታዊ ሃላፊነትን ደርቦ እውን አድርጓል ። የአባትን ክፍተት በራሱ ጥረት
የሚሞላ ልጅ ማግኘት የተለመደ አይደለም ። ዞሮ ዞሮ ጻውሎስን በዘልማድ እስከ አራተኛ ነው የተማረው እንላለን እንጂ በንባብ ምጥቀቱ
እስከ ስንተኛ እንደደረሰ አፋችንን ሞልተን መንገር አንችልም ። ለማንኛውም የዚህ ድንቅ ሰው የህይወት ታሪክ በደረጄ ትዕዛዙ ተዘጋጅቶ
ለንባብ ቀርቧል ። የገጹ ብዛት 308 ሲሆን ዋጋው 84 ብር ነው ።
አምባሰደር ዘውዴ ረታ
ጋዜጠኛ ንጉሴ አክሊሉ
ጋዜጠኛ ማዕረጉ በዛብህ
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ
አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ
አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ
ሃያሲ አስፋው ዳምጤ
ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት የባለታሪኩን ታሪከኛነት
ምስክር ከሚሰጡ ታዋቂ ሰዋች መካከል የተወሰኑት ናቸው ።
በጻውሎስ ኞኞ የህይወት ታሪክ ላይ የሚያጠነጠነው
መጽሀፍ በዘጠኝ ምዕራፍ የተከፋፈለ ነው ። በምዕራፍ አንድ የልጅነትና ጉርምስና ፣ በምዕራፍ ሁለት የጋዜጠኝነቱ ህይወቱ ተዳሶበታል
። በምዕራፍ ሶስት ሰብዓዊ ተግባራቱ ፣ በምዕራፍ አራት የድርሰትና ታሪክ ጸሀፊነቱ ፣ በምዕራፍ አምስት የፖለቲካና ሃይማኖታዊ አመለካከቱ
ይወሳበታል ። በምዕራፍ ስድስት ቤተሰባዊና ማህበራዊ ገጽታው ፣ በምእራፍ ሰባት ጻውሎስ ስለ ራሱ የተናገረውና ሌሎች ስለ እሱ የመሰከሩበት
ሃሳቦች የተንሸራሸሩበት ነው ። በምእራፍ ስምንት እና ዘጠኝ ሽልማቶቹና የህይወት ፍጻሜው ተገልጾበታል ።
እነዚህ የምዕራፍ ሃዲዶች ትንሹን ጻውሎስ ከትልቁ
ጻውሎስ ጋር እየተጠማዘዙ ያገናኙ በመሆናቸው የገጸ ባህሪውን አጠቃላይ ቁመና ለማሳየት በእጅጉ የረዱ ናቸው ። ደራሲው እያንዳንዱ
ምዕራፍ አዳዲስና ልብ የሚሞላ መረጃ እንዲኖራቸው ብዙ የጣረ መሆኑን የሚያሳየው በርካታ የመረጃ ምንጮችን መጠቀሙ ብቻ ሳይሆን ከ25
በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ቃለመጠይቅ ማድረጉም ጭምር ነው ።፡ይህም ስለ ጻውሎስ አውቃለሁ ብሎ የሚናገር ሰው ሁላ መጽሀፉን ሲያነብ
<< እንዴ እንዲህም አድርጎ ነበር እንዴ ? >> የሚል የኌላ ግርምታ እንዲፈጥር ማስገደዱ ነው ።
ለምሳሌ ብዙዎች ጻውሎስ እስከ አራተኛ ክፍል ብቻ
መማሩን ፣ ጋዜጣ ፣ ፓስቲና እንቁላል ይሸጥ እንደነበር ያውቃሉ ። ይሁን እንጂ በእርሻ ሚኒስቴር ውስጥ በወር 8 ብር እየተከፈለው
የከብት መርፌ ወጊ ሆኖ መስራቱ ቢነገራቸው ይገረማሉ ። ቆየት ብሎም በዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል በ80 ብር ደመወዝ ድሬሰር ሆኖ
አገልግሏል ቢባሉ እረ አትቀልድ ማለታቸው አይቀርም ። እንደው የጋዜጠኝነት ባቡር ሃዲዱን አሳተው እንጂ በዚህ አካሄዱ የነርስና
ዶክተርነትን ጎራ አይቀላቀልም ለማለት አያስደፍርም - አስገራሚው ነገር ለከብት ወጊነትም ሆነ ለድሬሰርነት ያገኘው ሰርተፍኬት መኖሩን
መጽሀፉ አለማተቱ ነው ።
በድምጽ ጋዜጣ በአራሚነት ጋዜጠኝነትን የተቀላቀለው
ጻውሎስ በአራተኛ ክፍል ደረጃው እስከ ምክትል ዋና አዘጋጅነት ደረጃ ሰርቷል ። በስራዎቹ ህዝባዊ ፍቅርና ዝና እንዲሁም በርካታ
ሽልማቶች ያገኘበትን ያህል በደፋር ትችቱ ብዙ መከራ ደርሶበታል ። በአንድ ወቅት ለኢትዮጽያ እድገት አለመሰፋፋት ተጠያቂዎች ባለስልጣናት
ብቻ ሳይሆኑ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጭምር ናት የሚል ጽሁፍ በማሳተሙ ከፍተኛ አመጽ ተነሳ ። ጉዋደኞቹ አስተባብል ቢሉትም ያመንኩበትን
ነው የጻፍኩት ብሎ አሻፈረኝ አለ ። ሊበቀሉት የሚፈልጉት ሰዎች በመበራከታቸው ጓደኛው ቤት ሶስት ቀናት መደበቅ ነበረበት - ኌላ
በዓሉ ግርማና አጥናፍ ሰገድ ይልማ በእሱ ስም አስመስለው በጋዜጣ ላይ ይቅርታ በመጠየቃቸው ህይወቱ ተርፏል ። ከመንግስትም ብዙ
ተጽዕኖ ፣ መገለልና ቅጣትን ተቀብሏል ። በዚህም ምክንያት ነበር ከአንዱ መ/ቤት ወደሌላው ሲወረወር የኖረው ። አዲስ ድምጽ ፣
አዲስ ዘመን ፣ ቴሌቪዥን ፣ ሬዲዮና ዜና አገልግሎት የመገኘቱም ምስጢር የዚህ ውጤት ነበር ።
ጻውሎስ ጥሩ ጋዜጠኛ ብቻ ሳይሆን ጮሌ የማስታወቂያና
ህዝብ ግንኑነት ሰራተኛም ነበር ማለት ይቻላል ። ድምጽ ጋዜጣ በገቢ ራስዋን መቻል አለባት ሲባል እንደ ሌሎች ሰራተኞች በፍርሃት
ከመደናገር ይልቅ ብልሃትን ነበር የፈጠረው ። በቀጣዩ ቀን የምትወጣውን ጋዜጣ ለማስተዋወቅ ጥሩንባ እየነፋ ያልሰማህ ስማ ማለት
ጀመረ ።
<< ኢትዮጽያ የመጀመሪያውን ሮኬት ተኮሰች
! ዝርዝሩን በነገው ጋዜጣ ተመልከቱ ! >> ሲል ብዙዎች ሌሊቱ በግድ ነበር የነጋላቸው ። አርባ ሺህ ኮፒ ጋዜጣ የተሸጠው
ግን ተማሪዎች ኩራዝ ቢጤ ለኩሰው የተኮሱትን ቀላል ነገር ነበር ።
<< የገንዘብ ሚንስትሩ ታሰሩ !
>> አለ በሌላ ቀን ደግሞ ድምጹን ጎላ አድርጎ ። ጋዜጣዋ ስትነበብ ግን የታሰሩት የጋናው ሚንስትር ናቸው ። ጻውሎስ
በማስታወቂያው ሽወዳ በማብዛቱ ከተቀናቃኞቹ አዲስ ዘመን ተቃውሞ ቢፈጠርበትም ህዝቡ በሌላው ጹሁፉ እየተካሰ ጋዜጣዋን ይበልጥ ወደዳት
። ለአብነት ያህል የካቲት 25/1951 ይድረስ ለእግዚአብሄር በሚል ርዕስ ስር ያወጣው ጽሁፍ በአይነቱና ይዘቱ ለየት ያለ በመሆኑ
ህዝባዊ ገረሜታና ፍርሃትን ጎን ለጎን አስተናግዷል ።
<< እንደምን ከርመሃል እንዳልልህ የምታሳምም
እንጂ የምትታመም አይደለህም >> ሲል በአግቦ ይጀምራል << እኔ ደህና ነኝ እንዳልልህ ደህንነቴን ታውቃለህና
አልደክምም ። አንተ አናደህኛል ፤ መቼም ሁሉን ነገር ተቆጣጣሪ ነህና በመናደዴ ተቆጥተህ እንዳታስጨረግደኝ አደራህን ። እንዲያወም
አቦን የመብረቅ ክፍል ሹም አድርገህ ሾመሃል አሉ ... >> እያለ ይቀጥላል ስነጹሃዊው ሽሙጥ ። ስነጽሁፋዊው ውበት ያስደስታል
- ሽሙጡ ደግሞ አንባቢ ላይ ፍርሃት እንዲጋባ መንገድ ይከፍታል ።
ጻውሎስ ወደ አዲስ ዘመን ሲዛወር ዝም ለማሰኘት
ነበርና የሴቶችና የልጆች ዓምድ እንዲሰራ ተደርጓል ። በኌላ ግን አንድ ጥያቄ አለኝ የሚል የጥያቄና መልስ አምድ በመክፈቱ በዚሁ
ጋዜጣም ዳግማዊ የዝና አክሊልን ደፋ ። ወደ ኢትዮጽያ ቴሌቪዥንም ሲዛወር የበሰለ ስራ መስራት ችሏል ። በተለይም የአባይና አዋሽ
ወንዝን ከመነሻው እስከ መድረሻው ያለውን ሁኔታ በማጥናት ዘጋቢ ፊልም አቅርቧል ። ይህ የውጭ ጋዜጠኞች አቀራረብ በኛ ሀገር መሞከሩ
የጋዜጠኛውን ሰፊ ምናብ ያመላክታል ። ኢትዮጽያ ሬዲዮ ሲዛወር አብዛኛውን ግዜውን ለራሱ መጽሀፍት ስራ ቢያውለውም አልፎ አልፎ ጣፋጭ ታሪኮችን ያቀርብ ነበር ። ራሱን ጨምሮ ብዙ አድማጮችን
ያስለቀሰውን የአለማየሁ ቴዎድሮስን ታሪክ እንደጥሩ አብነት ማንሳት ይቻላል ።
የጻውሎስ ሌላው ግዙፍ ሰውነት ሰብዓዊነቱ ነው
። ረሃብ የጠናበት የወሎ ህዝብ ወደ አ/አ የፈለሰ ግዜ ህዝቡን አስተባብሮ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል ። አርባ ሺህ እንጀራ
፣ አራት ሰንጋ ፣ 800 ሊትር ወተት ተሰባስቦ ረሃብተኛው ፋሲካን መፈሰክ ችሏል ። ከአንድ ሺህ በላይ ልብሶች የታደሉ ሲሆን
159 ሺህ ብርም ተሰብስቧል ። ርዳታውን ለማጠናከርም በስሙ የሙዚቃ ባንድ ተቋቁሞ ከጓደኞቹ ጋር ሙዚቀኛ ለመምሰል ጥረት አድርጓል
። ሙሉጌታ ሉሌ በማራካሽ ፣ ጌታቸው ደስታ በፒያኖ ፣ ሳሙኤል ፈረንጅ በድምጽ ፣ ታደሰ ሙሉነህ በቶምቶም ፣ ራሱ ጻውሎስ ከበሮ
በመምታት ታዳሚውን አዝናንተው የሚፈለገውን ገንዘብ ሰብስበዋል ።
ጻውሎስ በድርሰት አለም ውስጥም አይነተኛ ሚና
መጨወት ችሏል ። ከ 20 በላይ የታተሙና ያልታተሙ ስራዎች አሉት ። በዘርፉም ሲመደቡም ልቦለድ ፣ አስደናቂ ታሪኮች ፣ ታሪክና
ኢ- ልቦለዶች ናቸው ። አንዳንዶቹማ ስማቸው ራሱ ፈገግታ ይፈጥራል ። የኔዎቹ ገረዶች ፣ ያራዳው ታደሰና የጌታቸው ሚስቶችን ለአብነት
ማንሳት ይቻላል ። የሰካራሞች ሸንጎ የተሰኘው ድርሰቱ ተቆራርጦም ቢሆን ለመድረክ በቅቶለታል ። የጻውሎስን የጽሁፍ ሚዛን ይበልጥ
ከፍ ያደረጉት ግን ታሪክ ቀመስ ስራዎቹ ናቸው ። አጤ ሚኒሊክና አጤ ቴዎድሮስን እንደ ማሳያ መጠቆም ይቻላል ። ርግጥ ነው የልቦለዱ
ስራዎቹ ብዙ ይቀራቸዋል ። በርግጥ ጻውሎስ ራሱ በአንድ ወቅት << ባለቺኝ ጠንባራ እውቀት እያጠናበርኩ ጠንባራ ድርሰት
ቢጤ ካቀረብኩ አይበቃኝም >> በማለት ሙከራዎች መሆናቸውን የመሰከረ < ጠንባራ > ንግግር አድርጓል ።
የመጽሀፍ ነገር ሲነሳ << አጤ ሚኒሊክ
ከሀገር ውስጥና ከወጭ የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች >> የሚል መጽሀፍ ለማሳተም በተዘጋጀበት ወቅት ከመንግስት የደረሰበት የሳንሱር
አፈናና የርሱን የድፍረት ግብግብ ሳይጠቀስ የሚታለፍ አይሆንም ። መጽሀፉን ሰርቶ እንደጨረሰ ለኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ለግምገማ ይልካል
። ይሁን እንጂ ገና መጽሀፉን እንዳስመዘገበ መጽሀፉ < ከበላይ ይፈለጋል > ተብሎ ተወሰደበት ። ይህንን ወሬ እንደሰማም
አሳታሚ ድርጅቶቹን መጽሀፌን መልሱ ብሎ ያፋጥጣቸዋል ፤ ተወስዷል ይሉታል ።
<< ማነው የወሰደው ?
>>
<< የበላይ አካል >>
<< ንገሩኝና ሄጄ ልጠይቅ
>> ቢልም < ታስበላናላህ > በማለት ምለሽ ይነፈገዋል ። ይሄኔ ግን የፈለገ ይምጣ በሚል ለመንግስቱ ሃይለማርያም
የሚከተለውን ደብዳቤ ጻፈ
<< መጽሀፉን ካለችኝ ደመወዜ ፣ ለቤቴ
እንኳን ከማይበቃው ደመወዜ ለፍቼ ያዘጋጀሁት ነው ። ለሳንሱር ሰጥቼ
ብጠይቅ የበላይ አካል ወስዶታል ታስበላናለህ አሉኝ ። የሚበሉት የመጨረሻ አካል እርስዋ ስለሆኑ መጽሀፌን ይመልሱልኝ
>> ዳሩ ምን ያደርጋል ምላሽ ሳያገኝ የኢህአዴግ መራሹ ቡድን ወንበሩን ወረሰ ። ጻውሎስ የመጽሀፉን የመጨረሻ እጣ ፈንታ
ሳያይም ነው ሞት የወሰደው ።
መጽሀፉ የጻውሎስን ገጠመኝና ትዝታዎች በአስደማሚ
መልኩ በስፋት ይዳስሳል ። ቀልድና ፌዞቹ ብብትን ኮርኩረው የሳቅ ፈንዲሻን ይበትናሉ ። ቁምነገሩ ፣ ሀገራዊ ስሜቱ ፣ ድፍረቱ ፣
ለማወቅ የሚያደርገው ጥረትና ተቆርቋረነቱ በእጅጉ ይመስጣል ። በርግጥም ደራሲው ስለ ጻውሎስ መባል ያለበትን ሁሉ በማለቱ ምስጋና
ይገባዋል ። ከአንባቢው የሚጠበቀው የተባለውን ነገር ዛሬ ነገ ሳይል ማጣጣም ብቻ ።