Monday, May 27, 2013

‹‹ ጉድ በል ቢሊየን ዶላር !! ››




አቶ መለስ ዜናዊ በፔሮል የሚከፈላቸው ብቸኛ የአለማችን መሪ መሆናቸውና ክፍያቸውም ከ 4 እስከ 6 ሺህ እንደማይበልጥ በባለቤታው በወ/ሮ አዜብ መስፍን ተነግሮን ነበር ፡፡

በዚሁ መሰረት የወ/ሮ አዜብ ጡረታ ቢያንስ በግማሽ ካነሰ በቀጣዩ ህይወታቸው ላይ እክል እንዳያጋጥም እየሰጋን ነበር ፡፡ ለነገሩ መንግስት ያደረጉትን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ግምት ውስጥ በማስገባት ሙሉ ደመወዛቸው ሳይሸራረፍ እንደሚሰጣቸው የብዙዎቻችን እምነት ነው ፡፡ ቀጣዩን ኑሮ ለመደጎም ከታሰበ ብዙ አማራጮችን መጠቀምም ይቻላል ፡፡ ለምሳሌ ያህል በተለያዩ ቦታዎች የቦርድ ሰብሳቢ ማድረግ ፣ ከቅርብ ሰዎችና ከልማታዊ ባለሀብቶች ሚኒ ቴሌ ቶን ማሰባሰብ ወዘተ ይቻላል ፡፡

በዚህ ስጋት ውስጥ እያለን The Richest የተባለ ዌብ ሳይት / www.the richest. org / የዓለማችን ሀብታም ጠ/ሚኒስትሮች በሚል ለእኛ አስገራሚ ለቤተሰቦቸቸው ደግሞ አስደሳች ዜና ለቀቀ ፡፡ አቶ መለስ ዜናዊን ከሀብታሞቹ ጎራ አሰልፏቸው የተጣራ 3 ቢሊየን ዶላር በዉጭ ሀገር እንዳላቸው ነገረን ፡፡

‹ ጉድ በል ጎንደር! ›  አለ የጎንደር ሰው የአማርኛ መምህር ከደቡብ ክልል መጥቶልሃል ሲባል ፡፡ እኛ ስንት እየተጨነቅን …  እረ ይህን ሁሉ ሃብት ከወዴት አመጡት ? አቶ መለስ ቀደም ሲል ደጋግመው ስለ ቁጠባ ባህል ጠቃሚነት ብዙ ይነግሩን የነበረው ከራሳው ተሞክሮ ተነስተው ነበር ማለት ነው ? ይህ ወሬ እውነት ከሆነ ‹‹ ጉድ በል የሀገሬ ፓርላማ  የድሮውን የሀገሪቷን ዓመታዊ በጀት አንድ ሰው ላይ ስታገኝ ! ›› መባሉ ነው ።

እኔማ ቢቸግረኝ … የገንዘባውን አመጣጥ ለማወቅ የማያልቅና የማይደረስበት የሂሳብ ስሌት ውስጥ ገባሁ ። እስኪ ሳይቆራረጥ 6 ሺ ብራቸውን በፔሮል ይወሰዱ እንበል ፡፡ ለ 21 ዓመታት በዚሁ ብር አገለገሉ እንበል ፡፡ በ21 ዓመታት ውስጥ 252 ወሮች አሉ፡፡ ለ ጠ/ሚ/ር ጻጉሜም ሊከፈለው ይችል ይሆን በሚል እሳቤ 21 ዓመቱን በ13 ወራት አባዛሁት - 273 ወራቶች መጡልኝ ፡፡ እነዚህን ወራቶች በ 6 ሺህ ደመወዝ አባዛዋቸው ፡፡ ቁልጭ ያለ 1 ሚሊየን 638 ሺህ የኢትዮጽያ ብር ሰጡኝ ፡፡ መቼም የሀገር መሪ ከፍተኛ ኃይልም ክብርም አለውና ለቤት ኪራይ ፣ ለምግብ ፣ ለትራንስፖርት፣ ለሻይ ቡና ፣ ለውስኪ ፣ ለልጆች የትምህርት ወጪ ፣ ለእሱና ለቤተሰቦቹ አልባሳት ፣ ደስ ላለው ቁሳቁስ ወዘተ እንደማይከፍል ገመትኩ ፡፡ ስለዚህ 6 ሺውን ብር ሳይሸራርፉ እንዳለ መቆጠብ ችለዋል  ፡፡ ብሩ ግን ሁለት ሚሊየን እንኳን መሙላት አልቻለም ፡፡

ታዲያ ከየት አመጡት ? ሌላ የገቢ ምንጭ ማፈላለግ ያዝኩ ፡፡ እ… አበል ተገኘ ፡፡ አበል ለአንዳንድ ኃላፊዎች ወር ማዳረሻ ሳይሆን ራሱን የቻለ ደመወዝ መሆኑ ትዝ አለኝ ፡፡ ስለዚህ አቶ መለስ ለሀገራዊ ጉዳይ በዓመት 12 / አይበዛም ? / ግዜ ወደ ዉጭ ቢመላለሱ በ21 ዓመታት ውስጥ 252 ግዜ ወጥተዋል ማለት ነው ፡፡ ለአንድ ግዜ ጉዞ በሀብታም ሀገር እይታ 3 ሺህ ዶላር ቢከፈላቸው ለ252 ግዜ 756 ሺህ ዶላር አግኝተዋል ፡፡ ይህን ዶላር ለመዘርዘር በአማካኝ በ 17 ብር ሳባዛው / ጥቁር ገበያን መቼም አይሞክሩትም በሚል ነው / 12 ሚሊየን 852 ሺህ ብር መቆጠብ ችለዋል ማለት ነው ፡፡ አሁን የብራቸው መጠን 14 ሚሊየን 490 ሺህ ደረሰ ፡፡ ቢሆንም ገና ብዙ ይቀራል ። እስካሁን እየቆጠቡ እንጂ ብር እያወጡ አለመሆኑንም ልብ በሉ ፡፡

ሌላ የገቢ ምንጭ ትዝ አለኝ ፡፡ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑ ባለስልጣናት ከደመወዛቸው በላይ ከፍተኛ ጥቅማጥቅም ያገኛሉ ይባላል ፡፡ አቶ መለስ ምንም እንኳ በስራ የተጨናነቁ መሪ ቢሆኑም ከእንቅልፋቸው ሰዓት ቀንሰው  40 የሚደርሱ  ቁልፍ መ/ቤቶችንና ድርጅቶችን በቦርድ ሰብሳቢነት ያገለግላሉ እንበል ፡፡ ከአንዱ መ/ቤት በዓመት 20 ሺህ ብር ብር ያገኛሉ ቢባል ከአርባው 8 መቶ ሺህ ብር አላቸው ማለት ነው ፡፡ ይህን ብር ላገለገሉበት 21 ዓመታት ስናባዛው 16 ሚሊየን 8 መቶ ሺህ ብር ይሆናል ፡፡ አሁን ደግሞ አጠቃላይ ገንዘባቸው 31 ሚሊየን 290 ሺህ ብር ደርሷል ፡፡

በተለያዩ ግዜያት ከሚያገኙት የእውቅና ክብር ጋር የ 100 ሚሊየን ብር ስጦታም አግኝተዋል ቢባል / የተወሰነ ብር ለሆነ ደርጅት የለገሱ ቢሆንም / የብሩ መጠን 131 ሚሊየን 290 ሺህ ብር ነው ፡፡ ሌላ ገንዘብ የሚያገኙበት ምን ምንጭ አለ ?

አንዳንድ መ/ቤቶች በተለይ አትራፊ ድርጅቶች ዓመቱ መጨረሻ ላይ ለሰራተኛ ቦነስ ይሰጣሉ ፡፡ ታዲያ አትራፊ ያልሆነው ቤ/መንግስት ለሚያፈሰው የቤቱ ጣሪያ እንኴን ማደሻ ጥሪት አልነበረውም ፡፡ ‹ ቦነስ በቤተመንግስት › እያልን ብናወራ አሪፍ የሲኒማ ርዕስ ካልሆነ በስተቀር እንዴት ይታመናል ?  ለነገሩ ስፖንሰር በመጠየቅም የአትራፊነት የበጀት ርዕስ መትከል ይቻላል ፡፡ በቃ ! እንዲህ ሊሆን ይችላል ብለን ኦዲታችንን እንቀጥል ፡፡ ቦነስ ያው ደመወዝን ስለሚያክል 273 ወራቶችን በ6 ሺህ ብር ማባዛት ይጠበቃል ፡፡ 1 ሚሊየን 638 ሺህ ብር መጣ ፡፡ አጠቃላይ ሃብታቸው ስንት ሆነ መሰላችሁ 132 ሚሊየን 928 ሺህ ብር ፡፡

ታዲያ The Richest የተባለው ዌብ ሳይት ምንድነው የሚነግረን ? የሳቸውን ገንዘብ በጣም አብዝተነው እንኴ በዶላር ቢታሰብ ከ 8 ሚሊየን አይዘልም ፡፡ አላቸው የሚለው ግን 3 በሊየን ዶላር ነው ፡፡ ወይ አቶ መለስ ጨዋ ናቸው እያልን እንደ አፍሪካ መሪዎ ድርሻውን ወስደዋል ማለት ነው ? አያደርጉትም  ይህን ሂሳብ ለማምጣት ርግጠኛ ነኝ 24 ሰዓት ብደምርና ባካፍል አላገኘውም ፡፡ ታዲያ ማነው የዋሸን ? ዌብ ሳይቱ ወይስ ወ/ሮ አዜብ ፡፡ በርግጥ በሁለቱም በኩል አነጋጋሪ ክፍተቶች አሉ ፡፡ ዌብ ሳይቱ መረጃውን ያገኘበት ምንጭ አልጠቀሰም  ፡፡ ወ/ሮ አዜብም ምንም እንደሌላቸው ሲነግሩን ግድ የለም እንመናው በማለት እንጂ ያጡ የነጡ ለመሆናቸው ምን መረጃ ያቀርባሉ ? ታዲያ የወሬው አመጣጥ የአቶ መለስን ስም ለማጥፋት ነው ወይስ እሳውንም  እንደሌሎ ባለስልጣናት በሙስና ተጠያቂ ለማድረግ ? ያም ሆነ ይህ ወደፊት የሚታይ ይሆናል ። 

ደግሞ እኮ አሳምሮ ነው ያስቀመጠው ፤

የተጣራ ገቢ - 3 ቢሊየን ዶላር
የሀብት ምንጭ - ፖለቲካ
የመለስ ዜናዊ ዕድሜ - 58
የመለስ ዜናዊ የትውልድ ቦታ - አድዋ
የጋብቻ ሁኔታ - ያገባ / አዜብ መስፍን/ ን ይላል ፡፡

‹‹ ጉድ በል ቢሊየን ዶላር !! ›› አለ የሀገሬ ሰው ፡፡

Wednesday, May 8, 2013

የተሰቀለው ሪፖርትና የተደፈጠጠው እውነት

[ ICFJ ከጤና ጥበቃ ሚ/ር ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የክትባት ውድድር ላይ ያሸነፈ ጽሁፍ ]



አምቦ

ከአዲስ አበባ በ 95 ኪሜ በቅርብ ርቀት የምትገኝ የደስ ደስ ያላት ከተማ ናት ፡፡ አንድ ሰው ከተማዋ በጣም ጎልታ የምትታወቅበትን ጉዳዮች ቢያስስ ቢያንስ ሁለት ነገሮችን ጎልተው ያገኛቸዋል ፡፡

አንደኛው በርካታ ኢትዮጽያዊያን ስብሰባ ውለው ምሳ ከተጋበዙ በኃላ ለመጠጥነት በአንድ ድምጽ የሚመርጡት አምቦ ውሃ መሆኑን ነው ፡፡ በተለምዶ ምግብ ያንሸራሽራል ፣ ያስገሳል ፣ የውሃ ጥምን ይቆርጣል የሚባለው ይህ አንጋፋ መጠጥ የሚመረተው በዚህ ከተማ ነውና ፡፡ ሁለተኛው ሀገሪቱን ለ 22 ዓመታት እያስተዳደራት ከሚገኘው የኢህአዴግ መንግስት ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው ፡፡ የዛሬው ኢህአዴግ የትላንትናው ወያኔ በመጨረሻው ሰዓት ደርግን በየከተማው እየጣለ የመጣው ፈጣን ማርሽ በመጠቀም ነበር ፡፡ እዚች ትንሽ ከተማ ሲደርስ ግን ሩጫውን አቁሞ በአንደኛ ማርሽ ‹ ባላንስ › ለመስራት ተገደደ ፡፡ ህዝቡ ሀገር ሻጭና ከፋፋይ ፖለቲካን የሚያራምድ አማጺ ወደ መሃል ሀገር አናስገባም በማለት በጦርነት ገትሮት ያዘው ፡፡ ሀገሬው በውጊያው ብዙ እንደጣለ ሁሉ ከእሱም ወገኞች ብዙውን አጣ ፡፡ እናም በአምቦ ከተማ ይህን ግብግብ የሚያሳይ ህዝባዊ ኀውልት መታየት ባይችልም በህዝቡ ልቦና ግን በማይታይ ማህተም የተቀረጸ ልዩ ታሪክ አለ ፡፡

ወ/ሮ መገርቱ በዚች የውሃና ደም ታሪክ ባላት ከተማ መኖር ከጀመሩ 38 ዓመታትን አስቆጥረዋል ፡፡ የሁለት ሴትና አንድ ወንድ ልጅ እናት ናቸው ፡፡ የሶስት ዓመት ዕድሜ ያለው የመጨረሻ ልጃቸው በኩፍኝ በሽታ መያዙን ቢያወቁም ወደ ጤና ጣቢያ ማምራት አልፈለጉም ፡፡ ህጻኑ ላይ የሚታየው የሳል ፣ ንፍጥ ፣ ትኩሳትና ሽፍታ ህመሞች ያን ያህል አላስጨነቃቸውም ፡፡ የከተማው ህዝብ ያለው የጀግንነት ስሜት ተጋብቶባቸው አይደለም - የቆየ የህክምና ልምዳቸው እንጂ ፡፡ ኩፍኝ ለሳቸውም ሆነ ለቀድሞ ቤተሰቦቻቸው ተራና የማይቀር የልጅ በሽታ በመሆኑ እንዴት ማጥፋት እንደሚቻልም በአግባቡ ያውቃሉ ፡፡
እናም የእናት - አባታቸውን ከራማ እያስታወሱ ትርክክ ባለው የከሰል ፍም ላይ ደግመው ደጋግመው የተለያዩ ጢሳ ጢሶችን ያጉራሉ ፡፡ ትንሷ የጭቃ ቤት ከአቅሟ በላይ የሆነ የጢስ ምርት ማምረት ጀመረች ፡፡ ሁለቱ ኩፍኝን በግዜያቸው ያሸነፉ ሴት ልጆቻቸው በስራ ተጠምደዋል ፡፡ አንዷ ቡና ትቆላለች ፣ ሌላዋ ገና ያልበረደው ትኩስ ቂጣ ላይ በዘይት የተለወሰ በርበሬና ኑግ ትለቀልቃለች ፡፡ ጎረቤቶችና የቅርብ ዘመዶችም የውጭ በር ላይ ተኮልኩለው ፈጣሪ ለህጻኑ ፈጣን ምህረት እንዲልክለት ይለማምናሉ ፡፡

የቡናው ስነ ስርዓት ከተፈጸመ በኃላ ቆሎ ፣ ቂጣ ፣ ኑግ ፣ ለምለም ሳር የያዙ ሴቶች ምህረት እየለመኑ አቅራቢያቸው ወደሚገኝ ወንዝ አመሩ ፡፡ ወንዙን ከተሻገሩም በኃላ የያዙትን ወደ ወንዙ ዳር ወርውረው ተመለሱ ፡፡ በቃ ! በእምነቱ አስተሳሰብ መሰረት በኩፍኝ የተያዘው ልጅ በቅርብ ቀን ይፈወሳል ፡፡ ምክንያቱም የህጻኑ ገላ በሳሩም በቂጣውም በአሪቲውም ተሻሽቶ የተወረወረ በመሆኑ ጦስ ጥንቡሳሱም እዛው ተጣብቆ ይቀራል ፡፡

ፀለምት

የአማራ ክልል አንድ አካል የሆነች ከአዲስ አበባ በ 800 ኪ.ሜ ርቀት አካባቢ ላይ የምትገኝ ቆዛሚ ምስኪን ከተማ ናት ፡፡ አቶ ጥጋቡ በዚችው ከተማ ተወልደው ያደጉ የመንግስት ሰራተኛ ናቸው ፡፡ ዛሬ አድራሻቸው ጎንደር ቢሆንም ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅ በየግዜው ወደ ከተማዋ ይመላለሳሉ ፡፡

የአቶ ጥጋቡ ሀገር ሰው ከወ/ሮ መገርቱ ሀገር ሰው የሚመሳሰልበትም የሚለያይበትም መንገዶች አሉት ፡፡ ፀለምቶች ኩፍኝን ‹ ፎረፎር › እያሉ ሲጠሯት ብዙዎቹ ሀኪም ቤት መሄድ ሳያስፈልግ ልትድን የምትችል ሞኛ ሞኝ በሽታ መሆኗን ይስማማሉ ፡፡ ከወ/ሮ መገርቱ ሀገር ህዝብ ግን የሚለዩት በሰፈሩ አንድ ህጻን በፎረፎር ታመመ ከተባለ አስገራሚ የመከላከል ስራ መስራት መቻላቸው ነው ፡፡ ከነ ስያሜው መድሃኒቱን ‹‹ ክትባት ›› ነው የሚሉት ፡፡

በፍጥነት ወደታመሙት ልጆች በመሄድ ከሽፍታው ላይ መግል እያፈረጡ ይወስዳሉ ፡፡ ከዚያም ያልታመሙ ልጆች የግራ እጅ በምላጭ ይቀደድና መግሉ ከዝንብ ጋር ተጨፍልቆ በጨርቅ እንዲታሰር ይደረጋል ፡፡ አቶ ጥጋቡ  50ኛ የዕድሜ ሻማቸውን ቢለኩሱም ዛሬም ይህ የክትባት ስርዓት በአካባቢው እንደሚከናወን ይገልጻሉ ፡፡ ግራ እጃቸውን አንስተው አሳዩኝ ፡፡ ለባህላዊው የኩፍኝ ክትባት የተቀደዱት ጠባሳ አሁንም የታሪክ አሻራውን ይዞ ግዜ ሳያደበዝዘው  ይታያል ፡፡

‹‹ የአካባቢውን ተወላጆች እጅ እያነሳህ ብታይ ይህን ምልክት ታያለህ ›› በማለት በፈገግታ መለሱልኝ ፡፡
‹‹ የሆነውስ ይሁን ?! የዝንቧ ምስጢር አልገባኝምና ጠቀሜታው ምንድነው ? ›› ስል ጠየቅኳቸው
‹‹ ልጅ እያለሁ አይገባኝም ነበር ፡፡ አሁን የሚመስለኝ ግን ዝንብ በሽተኛዎች ደጃፍ መድረሷ ስለማይቀር የበሽታው ፈሳሽ አለባት በሚል ነው ›› አሉና ቅዝዝ ብለው ወደ ኃላ በሃሳብ ተመነጠቁ ፡፡ ከአፍታ በኃላም የሚያወሩልኝ እንባ በሚተናነቅ የሳቅ ድምጽ ነበር ፡፡ ‹‹ በጣም ይገርመኛል ፤ መድሃኒቱ እጅ ላይ ሊታሰር ሲል ዝንብ አድኑ ! የሚባሉት ህጻናት ናቸው ፡፡ ግማሹ የሚበር ዝንብ በትንሽ እጁ ለመጨበጥ ሲታገል ፣ ሌላው ዝንብ ያዝኩ ብሎ ዕቃ ሲሰብር ፣ ግማሹ ፊቱ ላይ ዝንብ ለመደፍጠጥ ፊቱን ሲጠፈጥፍ ይውላል … ››

ሳይንስ እንደሚለው ከሆነ የኩፍኝ ክትባት የሚሰራው ከተዳከመ የ ‹‹ ሚዝልስ ቫይረስ ›› ነው ፡፡ የአቶ ጥጋቡ ሀገር ህዝብም ባህላዊውን መንገድ ይከተል እንጂ መድሃኒቱ ያለው በሽታው ላይ መሆኑን አውቋል ፡፡ ሌላው ባህላዊው ስርዓት በኩፍኝ የተያዙ ልጆችን ለመጠየቅ የሚጣለው ገደብ ነው ፡፡ በነአቶ ጥጋቡ ሀገር መሰረት የግብረ ስጋ ግንኙነት ያደረጉ ሰዎች ታማሚዎችን ወደ ቤት ሄደው መጠየቅ አይችሉም ፡፡ ምክንያቱም ይህን ሁሉ ልፋት ያረክሳሉና ፡፡ በነወ/ሮ መገርቱ አካባቢ ኩፍኝ አንዴ ወንዝ በመሻገሩ ተመልሶ ስለማይመጣ ማንኘውም ሰው ቤት ገብቶ ቢጠይቅ ችግር የለውም ፡፡ ኩፍኝን ‹‹ አለሜ ›› እያሉ በሚጠሯት ‹‹ አለሜ በዓለም ያውጣሽ ! ›› እያሉ በሚለማምኗት የአዲስ ዘመን አካባቢ ነዋሪዎች ደግሞ በሽተኞች በር ላይ የሆነ ቅጠላ ቅጠል ነገር ይሰቀላል ፡፡ ይህን ምልክት የሚያይ እንግዳም ወደ ውስጥ ከመግባት ይታቀብና ደጅ ሆኖ ምህረት ይጠይቃል ፤ ከፈለገ ደግሞ ስለ ቀሪው ቤተሰብ ፣ ስለ እርሻና የዝናብ መጥፋት፣ ስለ እነ ላሜቦራ ጤንነት ሁሉ ድምጹን ከፍ አድርጎ መወያያት ይችላል ፡፡

አዲስ አበባ
ቆሼ ፡፡

ይህን የከተማውን ቆሻሻ በሙሉ ሰብስቦ ለመያዝ የተስማማውን ሰፈር ‹‹ ገብረ ክርስቶስ ›› ማለት የሚቀናቸውም አሉ ፡፡ በአካባቢው የስጋ ደዌ ህክምና መስጫ ሆስፒታል ከመኖሩ ጋር ተደራርቦ በርካታ በስጋ ደዌ በሽታ የተጠቁ ሰዎች ይኖሩበታል ፡፡ ስያሜው የመነጨው ግን በአካባቢው የአቡነ አረጋዊ / ገብረ ክርስቶስ / ቤተክርስትያን ከመገኘቱ አንጻር ነው ፡፡

በዚህ አካባቢ የሚኖሩ በሽተኞች ከሁሉም የሀገሪቱ ጥግ ለህክምና ሲሉ የሚፈልሱ ናቸው ፡፡ ብዙዎቹ ታክመው ወደ ትውልድ ሀገራቸው ከመመለስ ይልቅ እዚሁ መቅረትን የሚመርጡ ናቸው ፡፡ የዚህም አካባቢ ሰዎች ልክ እንደ አምቦ ሰዎች በሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ይታወቃሉ ፡፡ አንደኛው ከበሽታቸው ከተፈወሱ የማንንም ድጋፍ ሳይጠብቁ ራሳቸውን ለመቻል የሚያደርጉት ያላሰለሰ ጥረት ነው ፡፡ እንዳቅማቸው ቤት ተከራይተው ሽንኩርትና ጎመን ለመቸርቸር ወይም ጠላና አረቄ ለመሸጥ የማይቦዝኑ መሆናቸው ልዩ ያደርጋቸዋል ፡፡ በሽታቸው ጎድቷቸው አካላቸው መድከም ከጀመረ ደግሞ የገበያ ጥናት በማጥናት በልመና ስራ ይሰማራሉ ፡፡ እነሱን ጠጋ ብላችሁ ብትጠይቁ ልመናን አስጸያፊ ሳይሆን ራስን ለመቻል የሚደረግ መፍጨርጨር በማለት ነው ብይን የሚሰጡት ፡፡ ሁለተኛው ልዩ ባህሪያቸው በህክምናና ጤና ዙሪያ ለሚነገሩና ለሚሰሩ ጉዳዮች የተለየ ትኩረት ሰጪ የመሆናቸው ጉዳይ ነው ፡፡ ምናልባትም ስጋ ደዌ የፈጠረባቸው ተጽዕኖ ወይም በሌላ መልኩ ያስገኝላቸው የአዳማጭነት ጸጋ ሊሆን ይችላል ፡፡

በቅርቡ ወደ አረብ ሀገር የሚጓዘውን ባልደረባዬ ቤተሰብ ‹‹ እንዴት ይዟችኃል ? ›› ለማለት በአካባቢው ተገኝቼ ነበር ፡፡ በርካታ ሴቶች ተሰብስበው  ዳቦ ቆሎ ፣ ኩኪስ ፣ ቋንጣ ፣ የመሳሰለውን ቀለብ በመስራት ስራ ላይ ተጠምደዋል ፡፡ የኢትዮጽያ ቴሌቪዥን የሰባት ሰዓት ዜና እወጃ ላይ ስለ ሶስተኛው የአፍሪካ ክትባት ሳምንት በስፋት ሲያወራ የሴቶቹ ጫጫታ ቀነሰ ፡፡ የዘንደሮው ክትባት ‹‹ ህይወት እናድን ፣ አካል ጉዳተኝነትን እንከላከል ፣ እንከተብ ›› በሚል ጭብጥ ላይ ይተኮረ ነበር ፡፡ ከዜናው በኃላ የሴቶቹ አብይ መወያያ ጉዳይ ክትባት ሆነ ፡፡

አንዳንዶች በክትባት በርካታ ህጻናት ከሞት እየተረፉ መሆኑን በመጥቀስ መንግስትን ማወደስ ጀመሩ ፡፡ አንድ እናት ‹‹ ልጄ የደነቆረው በመከተቡ ነው ! ›› በማለታቸው ቤቱ በድጋፍና ተቃውሞ ተጋጋለ ፡፡ ‹‹ ከክትባት በኃላ የአእምሮ በሽተኛ የሆነ ልጅ አውቃለሁ ›› የምትል ወጣት ሴት ብቅ አለች ፡፡ ሌላ ወጣት ‹‹ እንዴት ፊደል ቆጥረሽ እንዳልተማረ ሰው በግምት አስተያየት ትሰጫለሽ ! ›› በማለት በግልምጫም በማሽሟጠጥም አፈረጠቻት ፡፡ ሴቶቹ ቀስ በቀስ መደማመጥ ወደማይቻልበት ደረጃ ተሸጋገሩ ፡፡ ይባስ ብሎ ‹‹ ምን ይሄ ይገርማችኃል ! የኛ ሀገር ክትባት በሉት መርፌ ሰው እየገደለ እኮ ነው ›› የሚሉ ሴት ከወደ ጓዳ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ብቅ አሉ ፡፡

አሁን ቤቱ በአንድ እግሩ ቆመ ፡፡

እነዚህ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክንፍ ወደ ከተማ የመጡ ሴቶች አስተያየት የህብረተሰባችንን የንቃተ ህሊና የሚያንጸባርቅ ወይም የሚመረምር ቴርሞ ሜትር ነው ማለት ይቻላል ፡፡ ስለ ክትባት ፣ ኩፍኝም ሆነ ሀኪሞች ብዙ የሰሙ እና ብዙ የተመለከቱ በመሆናቸው ስጋታቸው ከጠርዝ የወጣ ነው ነው ማለት አያስችልም ፡፡ ምክንያቱም በሀገራችን ህጻናትና እናቶች ከመጠን በላይ መድሃኒት ተሰጥቷቸው መሞታቸው አዲስ አይደለም ፡፡ ምክንያቱም በስህተት የማይገባ መርፌ ተወግተው ያለጥፋታቸው የሚያሸልቡ ጥቂቶች አይደሉም ፡፡ ምክንያቱም በኛ ሀገር ቀኝ እግራቸው ታሞ በእንዝላልነት ግራ እግራቸውን ለመጋዝ የሰጡ ምስኪን በሽተኞች መኖራቸውን አሳምረን እናውቃለን ፡፡ ምክንያቱም የሀገራችን ሀኪሞች ድራማን ለማየት በማስቀደም የነፍሰ ጡር እናት ብርቅ እስትንፋስን ከድራማው ፍጻሜ ጋር እንዲደመደም እንደሚያደርጉ እናውቃለን ፡፡ ስራ በዝቶባቸው ብቻ ሳይሆን ትኩረት ባለመስጠት የቀደዱት ሆድ ውስጥ መቀስና ፋሻ የሚረሱ ሀኪሞች መኖራቸውንም እናውቃለን ፡፡

መንግስትና የሚወዳቸው ቁጥሮቹ

መንግስት ከላይ የተገለጸውን አይነት አስተሳሰብ ፣ እምነትና አሰራሮች ትኩረት ሰጥቶ ከመመርመር ይልቅ በዘመቻ የሚገኙ ቁጥሮችን ማጉላት የመረጠ መስሏል ፡፡ የአሁኑ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር የቀድሞው ስመ ጥሩው የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ክትባቱ በተጀመረበት ወቅት ያጎሉትም ይሄንኑ ሃሳብ ነው ፡፡ ‹‹ በኢትዮጽያ የልጆች የጤና ክትባት ሽፋን 95 ከመቶ ደርሷል ›› በማለት ፡፡ ይህ አኀዝ በገለልተኛ ወገን ያልተረጋገጠና ፍጹም የተጋነነ በመሆኑ አሳሳች መስመር እንዳይዝ ያሰጋል ፡፡

በኢትዮጽያ እድሜና ደመወዝ እንጂ ሪፖርቶችን ከፍ አድርጎና አጋኖ ማቅረብ ከቀበሌ እስከ ቤተ መንግስት ድረስ የተለመደ አሰራር ነው ፡፡ ያጋነነው አካል ‹ ውሸታም ! › ተብሎ አይፋጠጥም ፤ ሳይጨምር ሳይቀንስ የቀረበው ግን ‹ እንዴት ይህን ብቻ ሰራህ ? › ተብሎ በግምገማ ዱላ ሊወገር ይችላል ፡፡ በዚህም ምክንያት የትኛውም መንግስታዊ መ/ቤት ብትሄዱ የምታነቡትና የምትሰሙት የሚያስጎመዡ ቁጥሮችን ነው ፡፡ በሀገራችን እየቀረበ ያለው የኩፍኝ ክትባት አኀዝም በተለመደው ምቹ የቻይና አስፋልት ሮጦ የመጣ እንጂ ዘወትር ከሚቆፋፈረውና እግርና ጎማ ከሚለምጠው የአውራጎዳና ባለስልጣን ኮሮኮንቻማ መንገድ ጋር የሚተዋወቅ አይደለም ፡፡

አንድ ነርስ ለ 2 ሺ 500 ሰዎች በሚደርስበት ሀገር ኩፍኝን ለማጥፋት ጥቂት ሽርፍራፊ አሃዝ ነው የቀረን ማለት ለጤና ጣቢያ እጅግ ርቀው የሚገኙ የህብረሰብ ክፍሎችን ፣ ባህላዊ እምነትና የልምድ አዋቂዎችን እንደ ካስማ ይዞ የቆየን ማህበረሰብ ስነ ልቦና ዘልቆ ያለመረዳት ዉጤትን ያንጸባርቃል ፡፡

በርግጥ በጤና መስኩ አበረታች ውጤት አልታየም ለማለት አይደለም ፡፡ የአሁኑ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ከሰተ ብርሃን አድማሱ በቅርቡ ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከሰባት ዓመት በፊት 600 የነበሩት ጤና ጣቢያዎች ዛሬ 3 ሺህ መድረሳቸውን ፣ 34 ሺህ የሚደርሱ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞችም መቀጠራቸውን ነግረውናል ፡፡ ይህ ቁጥር በተደራሽነት ላይ የነበረውን ሰፊ ክፍተት በጥቂትም ቢሆን እንደሚያጠብ ይጠበቃል ፡፡ ይህ ማለት ግን በክትባት እጦትና ባለመከተብ ፍላጎት የሚደርሰውን የህጻናትና እናቶች አስከፊ ሞት እንደሚነገረው የሚታደግ አይደለም ፡፡

ርግጥ ነው የዓለም ጤና ድርጅት የቅርብ መረጃ እንዳረጋገጠው በዓለም አቀፍ ደረጃ በኩፍኝ በሽታ የሚሞተው ህጻናት ቁጥር 71 ከመቶ ቀንሷል ፡፡ ይህ የሆነውም ከ2000 እስከ 2011 ባሉት ሰፊ ግዜያት ነው ፡፡ በሌላ በኩል በዓለም አቀፍ ደረጃ 20 ሚሊየን የሚደርሱ ህጻናት የመጀመሪያ ደረጃ ክትባት እንኳ ያልወሰዱ ናቸው ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሚገኙት በአምስት ሀገሮች ነው ፡፡ በኮንጎ ፣ ህንድ ፣ ናይጄሪያ ፣ ፓኪስታንና ኢትዮጽያ ፡፡ ይህም መንግስት ሰፊ የቤት ስራ እንደሚጠብቀው በአግባቡ ያመላክተዋል ፡፡

መንግስት ሊጠቀምበት የሚገባው ሌላኛው የማንቂያ ደውል ወይም የስጋት ቴርሞሜትር በሀገራችን የኩፍኝ ወረርሽኝ በየአመቱ እንደተለመደው ድርቃችን ተከሳች ጉዳይ የመሆኑን ምስጢር ነው ፡፡ የቅርብ ግዜያትን መረጃዎች ብቻ ብንወስድ እኤአ በ2009 – 1519 ፣ በ2010 – 2401 እንዲሁም በ2011 – 3255 የኩፍኝ ምልክቶች በተለያዩ ክልሎች ተመዝግበዋል ፡፡ በ2011 ከተጠቁ ሰዎች መካከል ደግሞ 114 ህጻናት መሞታቸው በይፋ ታውቋል ፡፡

ያልታረቁ የህክምና መንገዶች

በአንድ በኩል መንግስት ኩፍኝ በህክምና  የሚድን ቀላል በሽታ ነው ይላል ፡፡ በሌላ በኩል ህብረተሰቡ ኩፍኝ በቀላሉ የምትድን በሽታ በመሆኑ ከቤቴ አላሳልፋትም ባይ ነው ፡፡ መንግስት ክትባት ተጠቃሚው መቶ ከመቶ ሊሆን አንድ እፍኝ ቀርቶናል ይላል ፡፡ ክትባት የማያውቀውና ለባህላዊው መንገድ እጁን የሰጠው ደግሞ ብዙ እፍኝ ሆኖ ይታያል ፡፡ ይህም የጤና ጣቢያ ችግር ከሌለበት አዲስ አበባ እስከ አንድ ሺህ ኪ.ሜ ርቀት የሚገኙትን አርሶአደርና አርብቶአደር ነዋሪዎችን ያካትታል ፡፡ መንግስት የክትባት ሽፋኑ ከ 90 ከመቶ በላይ ደረሰ የሚል ከሆነ የህብረተሰቡ የመረዳት አቅምና ግንዛቤ አድጓል ማለቱ ነው ፡፡ ይሁን እንጂ የኩፍኝ ክትባት ኦቲዝም ያስከትላል ፣ የኩፍኝ ክትባት መውለድ ላይ ችግር ይፈጥራል ፣ ለአካል ጉዳተኝነትና የአእምሮ ችግር ይዳርጋል የሚል መረጃ የታጠቀው የሀገራችን ህዝብ ቁጥር ደግሞ የትየለሌ ነው ፡፡

እናም በሚጋጭ እውነታ ውስጥ እየተደነቃቀፉ መጓዝ ዋጋ ያስከፍላል ፡፡ በመሆኑም እየኖርን ያለበትንና መኖር የምንፈልግበትን ስርዓት በአግባቡ መገንዘብ ብሎም አብሮ እየተጓዙ ማጣጣም በመጨረሻም ሳይንሳዊውን የብረት ቆብ ኬሻና ገመድ የለመደው ጭንቅላት ላይ የማኖር ብሂልን መላበስ ግድ ይላል ፡፡

መሬት የሚቆነጥጥ ስልት

የኢትዮጽያ የክትባት ፕሮግራም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተያዙትን የፖሊዮ በሽታ የማጥፋት ፣ የመንጋጋ ቆልፍ የመቆጣጠርና የመቀነስ ፣ የኩፍኝ በሽታን የማስወገድ ስራዎችን ይዞ ይንቀሳቀሳል ፡፡ በከተሞች አካባቢ የተሻለ የክትባት ሽፋን ቢኖርም አብዛኛው ህዝብ የሚኖርበት ገጠሩ ክፍል በተለያዩ ምክንያቶች ተደራሽ አለመሆኑን ከመቀበል መነሳት ይኖርበታል - ስልቱ ፡፡
ኩፍኝ በረቂቅ ቫይረስ አማካኝነት የሚመጣና በትንፋሽ የሚተላለፍ በሽታ አንጂ የፈጣሪ ቁጣ ፣ የተፈጥሮ ሂደት ውጤትና የሌሎች እምነትና ባህል መገለጫ አለመሆኑን በአንድ ሰሞን ዘመቻ ሳይሆን በዝርዝር መንገድ ለማስተማር ኃላፊነትን መቀበል ግድ ይላል ፡፡ ኩፍኝ ድህነት ፣ ተፋፍጎ የመኖር ችግርና ያልተከተቡ ህጻናት ባሉበት ቦታ የሚስፋፋና በከፍተኛ ደረጃ የሚገድል በሽታ መሆኑን የትምህርቱ አቢይ ምዕራፍ ማድረግ ያስፈልጋል ፡፡ ምክንያቱም የምንኖረው በወራዳ የድህነት ቀለበት ውስጥ ነው ፤ የአኗኗር ስልታችንም ከተነጠላዊ ይልቅ እንደ ዳመራ የተጃመለና የተደጋገፈ ነው ፡፡ ይህም አብሮ ለመስራትና ጠላትን ለማባረር አስፈላጊ ቢሆንም ቫይረስና ባክቴሪያ እንደ ጣሊያን መላልሰው ሲወሩን ግን በቀላሉ ለመጨፍጨፍ ያመቻልና ፡፡

ኩፍኝ ርጉዝ በሆነች ሴት ላይ ከተከሰተ ልታስወርድ እንደምትችል ፣ ህጻኑ ሊደነቁር ፣ ሊታወር እንዲሁም የአእምሮ ጉዳተኛ ሁሉ ሊሆን ይችላል ፡፡ አብዛኛው ህብረተሰባችን የሚያስበው ግን በሽታው የህጻናት ብቻ መሆኑን ነው ፡፡ ለዚህም ነው የቆሼ ሰፈር ሴቶች የኩፍኝ ክትባትን መጠቀም ህጻናትን ለሞትና ለአካል ጉዳተኝነት ይዳርጋል በማለት በግልባጩ የሚያስቡት ፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች የሚያገለግሉት የአካባቢያቸውን ህብረተሰብ በመሆኑ ግንዛቤ ለመፍጠርና ልማዳዊ ልምዶችን ለመሰባበር ምርጥ ስትራቴጂ መሆኑን በልበ ሙሉነት ይናገራሉ ፡፡ ይህን አስተሳሰብ የመጨረሻ አድርጎ መቀበል ግን የክትባት ሽፉኑ 95 ከመቶ ደርሷል ብሎ በድፍረት የመናገር ያህል የሚያስቆጥር ነው ፡፡ 
ምክንያቱም በየትኛውም የገጠሪቱ ክፍል የሚገኙ ዜጎች ከአንድ ጤና ባለሙያ ይልቅ የጎሳ መሪዎችን ፣ ታዋቂ ሽማግሌዎችን ፣ የእምነት አባቶችንና አዋቂዎችን ነው የሚያከብሩት … የሚፈሩትና ትዕዛዛቸውንም የሚፈጽሙት ፡፡ በመሆኑም ይህን ጠቃሚ ስልትም በአግባቡ ፈትሾ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ፡;

ከ 80 በላይ ብሄር ብሄረሰቦች በሚገኙባት ሀገር ለኩፍኝ ያለው አመለካከትም ሆነ ባህላዊና እምነታዊ የመከላከል ስትራቴጂው 80 ዓይነት የበዛ ነው ፡፡ አንዱ በጢሳጢስ ፣ ሌላው በዝማሬ ፣ አንዱ ወንዝ በማሻገር ፣ ሌላው ስራ ስር በመቀመም ሊጠቀም ይችላል ፡፡ ምክንያቱም የነወ/ሮ መገርቱን ባህላዊ እምነት የሚከተሉ ሰዎች ዛሬም በየትኛውም ጥግ ይገኛሉ ፡፡ የእነ አቶ ጥጋቡ መግልና ዝንብ የቀላቀለ ባህላዊ የህክምና መስጫ ተቋማት የቀራቸው ከመንግስት ህጋዊ የንግድ ፍቃድ ማውጣት እንጂ በዘልማድ የሚሰሩበትና የሚያምኑት የገጠር ወገኖቻችን ዛሬም በርካታ ናቸው ፡፡ ክትባት በራሱ ለመሃንነትና ለሌሎች ተዛማጅ ችግሮች ይዳረጋል የሚል የእምነት ጋቢ የደረበው የህብረተሰብ ክፍልም ቁጥሩ ጥቂት አይደለም ፡፡

 መንግስት የያዘው አኀዝና ህብረተሰቡ ጋ ያለው ተጨባጭ እውነት የተጣረሰ በመሆኑ የማስተካከያ ስራ ሊሰራ ይገባል ፡፡ የገነገነውን ባህላዊ ልምድንና እያቆጠቆጠ የሚገኘውን ዘመናዊ አሰራር ማጣጣምና ማስታረቅ ግድ ይላል ፡፡ በአጠቃላይ ኩፍኝንና ወረርሽኙን ለመከላከል ፤

እውነትን - ማካፈል
ግነትን - መቀነስ
ክትባትን - መደመር
ግንዛቤን - ማብዛት
የተሰኘ ቀላል ነገር ግን ጠቃሚ ሂሳባዊ ቀመርን መከተል ያስፈልጋል ፡፡
            

Monday, May 6, 2013

‎የአንድ ጎልማሳ ገንዳ ወግ‎




‹‹  እረ ለአንተው ቱ ! ባለጌ ! መተፋት ያለበት ለአንተው ዓይነት ነበር ፡፡ . . .  እረ እባክህ አፍንጫህንም መያዝ ትችላለህ እንዴ ? አሁን እንዲህ ለብሰህ ላየህ አዋቂና ጨዋ ትመስላለህ ፤ ይሄኔ ስለ ቆሻሻ ጎጂነት የምታስተምር የሳይንስ መምህር ትሆን ይሆናል . . . ነጭ ጋዋን ለብሰህ ምድረ በሽተኛን የምታመናጭቅ ድሬሰር ወይም ነርስ የማትሆንበትም ምክንያት አይኖርም ፡፡ የዚችን ከተማ ቆሻሻ ነቃቅለን እናጠፋለን ከሚሉ ዲስኩረኛ ፖለቲከኞች ተርታም የምትሰለፍ ቢሆንስ ምን ይገርማል ፡፡ እረ ማዘጋጃ ቤት የጽዳት ፣ ውበትና መናፈሻ ስራ ሂደት መሪም ብትሆን ማን ያውቃል ?

‹‹ እኔ ግን በዚች ሰፈር ካወቅኩህ ስንት ዘመን ተቆጠረ ? ቀን ቀን ‹ ይሄ ገንዳ ሸተተ ! › እያልክ ምራቅህን ትተፋብኛለህ ፤ ገልምጠኀኝ ትሄዳለህ ! አንዳንዴ ደግሞ እንደ ማስቲሽ ንፍጥህ ተጣብቆ አልከፈት በሚለው የተዥጎረጎረ መሀረብህ አፍና አፍንጫህን ለመደበቅ ትጣጣራለህ ፡፡ በል ሲልህ ደግሞ ‹ ቅርናታም ገንዳ ! › እያልክ በብልግና መፈክር ትለማመዳለህ ፡፡ ማታ ማታ ግን ከእኔ በላይ በመጠጥ ቀርንተህ በሁለት እጆችህ ጥርቅም አድርገህ ይዘኀኝ ገላዬ ላይ ስትሸና አንዳችም ነገር አይከረፋህም ፡፡ አስመሳይ  - ሰው መሳይ በሸንጎ ! እንዳንተ ዓይነቱን ስንት የሰው ገንዳ ታዝቤያለሁ መሰለህ ?! ይሄኔ የቆለጥህ ማስቀመጫ ጨርቅና ካልሲህን በተናጥልም ሆነ በጥምረት የሚያሸታቸው ቢኖር  ‹ እረ ተመስገን ! › የሚባልልኝ እኔ ነበርኩ ፡፡ እውነት እልሃለሁ አንድዬ ለአፍታም ቢሆን እጅ ቢያውሰኝ እንዲህ በነጋ በጠባ ቁጥር ቆሽቴን አታሳርረውም ነበር ፡፡ በሚያምረው ከረባትህ ጎትቼ አስጠጋህና እንደ አርጋው በዳሶ በጭንቅላትህ እቀብርህ ነበር ፡፡ ይሄ የሰው አህያ ! እንደ ወሎ ፈረስ መልክህን ብቻ ከማሳመር ቀፎ ጭንቅላትህ ውስጥ ንቦች ምግብ እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታ ብትፈጥርላቸው አይሻላልም ?

‹‹ ጆኒ ቀዌ መጣች ፡፡ ዛሬ ደግሞ እነዚህ የጎዳና ልጆች እያዋከቡት ነው ፡፡ እንደው እኔም ርስት ሆኜ የሰው ዘር በይገባኛል ሲጣላብኝ ያመኛል ፡፡ ይህን ያወኩት እዛ ቆሼ የተባለ ሰፈር ነው ፡፡ ቢያንስ በዓመት ሶስትና አራቴ ቆሼ እንድሄድ ይፈቀድልኛል ፡፡ ለነገሩማ በየሁለት ቀናትና በሳምንት ሂሳብ ነበር ቆሻሻዬ ሊራገፍ የሚገባው ፡፡ አልፎ አልፎ ስሄድ ታዲያ የሰው ልጅ የገንዳ ቆሻሻን የቦሌ - የጉለሌ ፤ የሸራተን - የሂልተን … በሚል ስያሜ ለፍቶ እንዳገኘው ርስት ሲራኮትበት ፤ ጦር ሲማዘዝበት እመለከታለሁ ፡፡ በእውነት ይሄ የዘርና የጎሳ  አስተሳሰብ ቆሻሻ ድረስ መዘርጋቱ ያሰቅቃል ፡፡ ማቲው ብቻ ሳይሆን ነፍስ ያወቀው ሁሉ ‹ ምርጥ ምግብና ምርጥ ዕቃ › ለመሰብሰብ ዘወትር ቡጢውን ሌላው ላይ መወርወር ግዴታው ሆኗል ፡፡ አንዱ አገልግሎቱ ስላበቃ ወይም ስለቆሸሸ ብሎ የጣለውን ሌላው እንደ ብርቅ ማዕድን ቆፍሮ ለማውጣት መታከቱ ያስቆዝማል ፡፡

‹‹ ታዲያ ጆኒ የሚገርመኝ የሚፈልገው የብዕር ቀፎና ማስመሪያ መሆኑ ብቻ ነው ፡፡ እነዚህ ኩይሳዎች እንኳ ላዬ ላይ ወጥተው የሚቦጠቡጡት የተራረፈ ምግብ ፍለጋ ነው ፡፡ ታዲያ ለማይገናኘው ፍላጎታቸው ለምን አጉል ይናከሳሉ ? እውነት ይሁን ውሸት ያበደውም ከቆሻሻ ጋር በተያያዘ ምክንያት ነው ይባላል ፡፡ ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ እንደተመረቀ የከተማው ቆሻሻ እንደ ችግር ሳይሆን እንደ ድሃ አጋር ሊታይ የሚችልበትን ‹ አንድ - በአራት › የተባለ ልዩ የፈጠራ ፕሮጄክት አቅርቦ ነበር ፡፡ ከቆሻሻ አግሮ ስቶን ፣ ነጭ ከሰል ፣ ባዮ ጋዝ እና የካኪ ፌስታል ለመስራት ፡፡ ጉዳዩን ያዳመጡት የሚመለከታቸው ወገኖች ‹ ፕሮጄክትህ ግማሽ እውነት - ግማሽ እብደት የተቀላቀለበት ነው › በማለት አጣጣሉበት ፡፡ እየቆየ ሲሄድ ግን አንዳንድ የፈጠራ ሰዎችና ባለሀብቶች ከጥቅሉ ፕሮጄክት አንድ አንዱን እየመዘዙ ጥቅም አነደዱበት ፡፡ ቀስ በቀስ ደግሞ ‹ ለምን ? እንዴት ? ፍትህ የለም ! › ማለት ያበዛው የጆኒ ጭንቅላት ነደደ አሉ ፡፡ ጆኒ ግን ያሳዝነኛል ፡፡ የጸዳ ነጭ ወረቀት ማለት ነው - ተንኮል ፣ ጥላቻም ሆነ እብሪት አይንጸባረቅበትም ፡፡ በዚህ ለጋ እድሜውም ማበድ አልነበረበትም ፡፡ በርግጥ በሽተኛን ደጋግሞ በማመናጨቅ የሚታወቁት ሀኪሞች በትኩረት ደጋግመው ቢያክሙት ይድናል ፡፡ ጆኒን በትኩረት ቢያጤኑት ሊማሩበትም ይችላሉ ፡፡ ምነው ብትሉ አንድም ቀን ተሳስቶ በአካባቢዬ ሽንቱን ሸንቶ አያውቅም ፡፡

‹‹ ምስኪን ! ከእነዚህ እርጉሞች ጋር ላለመጣላት ነው መሰለኝ አቅጣጫውን ቀየረ ፡፡ መጡ እነዚህ ከፈሳቸው ጋር የተጣሉ ! ዘለው አናቴ ላይ ወጡ ! መነቀሩኝ ! አቤት አስፋልቱ በአንድ አፍታ ቄጤማ ተጎዘጎዘበት ፡፡ ፈንዲሻ ተረጨበት . . . ዕጣን ተለኮሰበት . . . ደስ ይላቸዋል ልበል ?! አልናገርም ፣ አልሰማም ፣ አላይም በሚል ፍልስፍናው የሚታወቀው የአዲስ አበባ ነዋሪም ይፈራቸዋል መሰለኝ አይገስጻቸውም ፡፡

‹‹ ታዲያ ምነው ሮጡ ? . . , አሃ ! ድንጋይ ወርዋሪዋን ወይዘሮ  ተካበች አይተው ነው ፡፡ የእኚህ ሴትዮ ልብና በሁለት ገጹ የሚለበስ ጃኬት አንድ ናቸው ፡፡ ሴትየዋ ቀን ቀን ሰው እንዲያያቸው ይህን የመሰለ ልማታዊ ተውኔት ይሰራሉ ፡፡ ሰው አይደለም ውሾች ቆሻሻውን ሲመነቅሩ ዝም አይሉም ፡፡ በጩኀትም ሆነ በፉጨት በል ሲላቸውም ድንጋይ በመወርወር ያካልቧቸዋል ፡፡ ይህ ተግባራቸው ግን አንዳንዴ የከፋ ጉዳት ይዞ ሊመጣ ይችላል ፡፡ አንድ ግዜ የሆነውን ማንሳት ጥሩ ነው ፡፡ የተራቡ ይሁኑ ስሪያ የጨረሱ በርካታ ውሾች ገንዳውን ሲሞነጭሩ በመድረሳቸው ድንጋይ ማዝነብ ጀመሩ ፡፡ ኤፍ ኤም 97.1 ጠዋት ጠዋት ከሳጅን መዝገቡ ጋር አዘውትሮ የሚያሰማውን  የትራፊክ ዘገባ  ማዳመጥ ከማይመቻቸው ውሾች መካከል  ሶስቱ በደመነፍስ ሲካለቡ የትልቅ መኪና ጎማ ደፈጠጣቸው ፡፡ አንድ ቀን ሙሉ ከአስፋልት ማንም ሳያነሳቸው ከተዘረሩ በኃላ መሽተት ሲጀምሩ  ወይዘሮ ተካበች የጎዳና ተዳዳሪዎችን አሰባስበው እኔ ጀርባ ላይ እንዲወረወር አደረጉ ፡፡ አቤት ለአንድ ሳምንት የነበረው  የአካባቢ ቅርናት ! አቤት ጭንቅላቴን የወረረው የግማት ጥቃት ! ያኔ ጋዜጠኞችን ጠርቼ ጥልቀት ያለው መግለጫ ብሰጥ እደሰት ነበር ፡፡ እረ የሬዲዮ የአየር ሰዓት ገዝቶ የመዘባረቅ ሀሳብ ሁሉ የመጣብኝ ያኔ ነው ፡፡

‹‹ ታዲያ እኚህ ተዋናይ ሴትዮ ዱሪዬዎችንም ሆነ ውሻዎችን ካባረሩ በኃላ ወጪ ወራጁ እንዲሰማቸው የፈጸሙትን ገድል ለደቂቃዎች ይተርካሉ ፡፡ የንግግራቸው ቃናም ሆነ የአካላቸው እንቅስቃሴ ግዜያዊ መድረክ ላይ ያለ አይመስልም ፡፡ በጣም የሚገርመው መነባንቡን የትና መቼ እንደሚያጠኑት ነው ፡፡ ማታ ማታ ሌላ ናቸው ፡፡ የራሳቸውን የጠላ ድፍድፍ ፣ ለሌሎች ተቀጥረው ደግሞ የአትክትልና ፍራፍሬ ልጣጭና ብስባሽ በኔ ዙሪያ ይቆልላሉ ፡፡ ጠዋት ሲነጋ ከሁሉ ቀድመው ‹ አበስኩ ገበርኩ › ን የሚያዜሙት እሳቸው ናቸው ፡፡

‹‹ እኔ የምለው ይህ የከተማ ህዝብ እስከመቼ ነው የምናገባኝ ፖሊሲውን የሚያራምደው ? አንድ ሰሞን በጉንፋንና ኮሌራ ፣ በትውከትና ተቅማጥ ልጆቻችንና እኛ ማለቅ የለብንም በየአካባቢያችንም በቂ ገንዳ ሊቀመጥ ይገባል በማለት ጩኀቱን አቀለጠ ፡፡ ፊደል የቆጠሩትም ለከተማ እድገት የጽዳት አጠባበቅ አስፈላጊ መሆኑን የሌሎች ሀገሮችን ልምድ በመጠቃቀስ መንግስት ከእንቅልፉ እንዲነቃ ጎተጎቱ ፡፡ የሁሉም ሀሳብ ትክክል ስለነበር  እኔና ጓደኞቼ ሰፈር ከተማውን አጥለቀለቅነው ፡፡ ምን ዋጋ አለው ታዲያ ? ጩኀቱ ቆሻሻውን ለመድፋት ብቻ ሆነ ፡፡ ገንዳው ሲሞላ እንዲነሳ ማን ይጩህ ? በግምና ክርፋት አየር ውስጥ ያለመኖር መብታችን ይከበር ! ማን ይበል ?

‹‹ አስተዳዳሪዎቹ በምርጫ ሰሞን ‹ መልካም አስተዳደር እናሰፍናለን ! ህዳሴውን እናረጋግጣለን › ሲሉት ለምን በተጨባጩ ቆሻሻ አያፋጥጣቸውም ፡፡ ሚዛን አትደፋም ተብላ በማትጠቀሰው ቆሻሻ ተግባራዊ ማንነትን መለካት ይቻላል ፡፡ ለምሳሌ አስተዳደሩ የከተማውን ጉድፍ አይደለም በማዘጋጃ ዙሪያ የሚታየውን ሽንትና አይነምድር ማጽዳት አልቻለም ፡፡ የአውሮፓዎችን መንግስታዊ አስተዳደር ቀምሮ ቢያስፋፋ ኖሮ ስንት ግዜ ስልጣኑን በፈቃዱ በለቀቀ ነበር ፡፡

 
‹‹ በርግጥ አስተዳደሩ ከተማዋ ለአፍሪካ ህብረት መቀመጫነት አትመጥንም የሚል የሰላ ትችት በውጭ ሰዎች ድንገት ሲቀርብ የሆነ ነገር ለመስራት ተፍ ተፍ ይላል ፡፡ ለልምድና ተሞክሮ ልውውጥ የጽዳት ሰራዊቱን በምድረ አፍሪካ ይበትናል ፡፡ አንድ ሰሞን ኪጋሊ ደርሶ የመጣው ልዑክ ጆሮአችንን አደንቁሮት ነበር ፡፡ ‹ እውነት ሰው በላዋ የሩዋንዳ ከተማ እንደዚህ ውብ ናት ? › የሚለው ግርምት ከልክ በላይ ተጭኖብን ነበር ፡፡ ሰው በጦርነት ሲበላ የከረመ ከተማ የኃላ ኃላ በውበት የሚልቅ እስኪመስል ድረስ ፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ አዲስ አበባ የኪጋሊ አቻ ለመሆን የቀረበች ናት ፡፡ የቀይና ነጭ ሽብር ባለታሪክ ናትና ፡፡

‹‹ የጽዳት ሰራዊቱ ግብም በአንድ ተጨባጭ ለውጥ እንደሚደመደም ተገምቶ ነበር ፡፡ ግን የዚህን ሀገር ተግባር አውሎ ንፋስና ማዕበል ሳይሆን ወሬ ነው የሚበላው ፡፡ ይባስ ብሎ በቅርቡ ደግሞ በጥናት ሳይሆን በአውሎ ንፋስ የመጣ የሚመስል ዜና የከተማዋን ኃላፊዎች አሙቋቸዋል ፡፡ ሎንሊ ፕላኔት የተባለ ዓለማቀፍ የጉዞና አስጉበኚ መጽሀፍ ካምፓኒ አ/አ በ2013 ሊጎበኙ ከሚገባቸው አስር የዓለማችን ከተሞች አንደኛዋ ናት በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል ፡፡ ይሄን ያልኩትም ከተማዋ ፈጣን እድገት እያሳየች በመሆኑ ነው ብሏል ፡፡ መቼም ይህ ድርጅት የሀገር ውስጥ ጋዜጣ ቢሆን ኖሮ ሚዛን ያልጠበቀ ዜና በማሰራጨቱ ፍ/ቤት ሊቆም አሊያም ሊታገድ በቻለ ነበር ፡፡ ደግነቱ ስምን መልዓክ ያወጣዋል የሚል አባባል መኖሩ ፡፡ ሎንሊ ወይም ብቸኛው ድርጅት ያወጣውን ዘገባ ሌሎች አልደገፉትም ፡፡ ‹ ብቻህን ተወጣው ! › የተባለ ይመስላል ፡፡ እረ ‹ ፈረንጁ ዋልታ ማዕከል ! › ያሉትም ሳይኖሩ አይቀርም ፡፡ ብቻ ብዙ የሚጋጩ ነገሮች ስላሉ ከእንቅፋቱም ከነገሩም ላለመላተም ግራና ቀኝ እያስተዋሉ መጓዝ ይበጃል ፡፡ ለምሳሌ ባለስልጣኖች የሚፈሩት ፎርበስ / Forbes / አዲስ አበባ የዓለማችን ስድስተኛዋ ቆሻሻ ከተማ መሆኗን ነው በቅደም ተከተሉ የሚያሳየው ፡፡ ይህ አይነቱ መረጃ ከሎንሊ አይደለም ከሞተው ብሩስሊ ጋር ካራቴ አያማዝዝም ?

‹‹  አዲስ አበባ ትንሳኤ ማግኘቷን ታረጋግጥ የነበረው ያ ማነው ; . . . ጉዳዬ ሳይሞላ እያለ ያዜመው . . .  እንዳጀማመሩ ቢዘልቅበት ነበር ፡፡ ልብ በሉ ! አበራ ሞላ ሲያንጽ የነበረው ጽዳት ብቻ አልነበረም ፡፡ የአስተሳሰብ ለውጥና ውበትንም ጭምር እንጂ ፡፡ በከተማችን ስንት ሞተው ኀውልት የቆመላቸውን ቦታዎች አይደለ አንዴ እንደ ፈጣሪ . . . ‹ እፍ ተነሱ ብርሃን አግኝታችኃል › እያለ ያነቃቸው ፡፡ ካድሬዎች ግን በግምገማቸው አበራ ሞላ በከተማዋ ያበዛው ማሰሮና መፈክር ነው ማለታቸው ተሰምቷል ፡፡ እረ በሀገራችን ታሪክ መፈክር አብዝቶ የማያውቅ መንግስት ነበር እንዴ ?

‹‹ የከተማው አስተዳደር መቋቋምና ማሸነፍ ካልቻለባቸው ጉዳዮች አንዱ ጽዳት መሆኑ ይታወቃል ፡፡ ብሎ ብሎ ሲያቅተው ደጋግሞ የሚያነሳት ምክንያት ‹ ህዝቡ የአስተሳሰብ ለውጥ ሊያመጣ አልቻለም ! › የምትል ናት ፡፡ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዴት ሊመጣ እንደሚችል ግን የጠለቀ ግንዛቤ ያለው መሆኑ ያጠራጥራል ፡፡ ገንዳዎች በየአደባባዩ ከተቀመጡ ሰዎች በአካባቢው ይሸናሉ በሚል ወደ መንደር ማራቅ ተጀምሮ ነበር ፡፡ ግን ገንዳዎች ባይኖሩም የከተማችን ግንቦች ዛሬም በቀንም ሆነ ማታ እንደጉድ ይሸናባቸዋል ፡፡ ይህን ችግር ጠልቆ ያለመረዳት ነው ስንኩልና ፡፡ እንኳን ሽንት ቤት መኖሪያ ቤት የሌለው የከተማ ህዝብ ጭንቀቱን የት ይክፈል ? አስተዳደሩ በየቀበሌውና በየሰፈሩ ደረጃቸውን የጠበቁ መጸዳጃ ቤቶችን መገንባት ቢኖርበትም አላደረገውም ፡፡ ጥቃቅንና አነስተኛ ሱቆችን በየቦታው እንደ አሸን ሲያፈላ ለሽንት ቤት ግን ቦታ የለኝም ይላል ፡፡ ያሉትን ክፍት ቦታዎች በሙሉ በሰብዓዊነት ሳይሆን በገንዘብ ጭንቅላት እያሰበ ግንባታ እንዲጥለቀለቅባቸው ያደርጋል ፡፡ ለልማት ግንባታ የማይደረግ ነገር የለም በሚል ለመንገድ ግንባታ ቤቶችን ያፈርሳል ፡፡ ሽንት ቤት ለመገንባት ለምን ቤቶች እንዲፈርሱ አይደረግም ? 
‹‹ ለማንኛውም ገንዳን ለማጽዳት ፍትሃዊ ፣ ግልጽና  የጸዳ አስተሳሰብ ያስፈልጋል ፡፡ ይህን ሃሳብ በተጠማዘዘ መንገድ ላስረዳ ፡፡ አስተዳደሩ በስሪቱ ውስጥ የወይዘሮ ተካበች አይነቶችን በብዛት ከመቆለልና ከመካብ ፤ የጆኒ ቀዌ አይነቱን እያከመ ፣ እየደገፈና የስራ ነጻነታቸውን እያረጋገጠ ቢቀጥል ያዋጣዋል ››

ማስታወሻ፡- ይህ ፅሑፍ በቁም ነገር መፅሔት ቅፅ 12 ቁጥር 151 ላይ የወጣ ፅሑፍ ነው፡፡ ፅሑፉን በሌላ ሚዲያ ላይ የምትጠቀሙ ከሆነ ምንጩን እንድትጠቅሱ ትለመናላችሁ፡፡

Sunday, April 21, 2013

‎‹‹ በዓሉ ግርማ በባህርዳር ››‎




ሰሞኑን ለስራ ወደ ሰሜን ስጓዝ በውስጤ ግዘፍ ነስቶ የቆየው የበዓሉ ግርማ ጉዳይ ነበር ፡፡ በቂ ግዜ ካገኘሁ ‹ የፌስ ቡክ ሰራዊት › ሲወያይበትና ሲከራከርበት ለከረመው አጀንዳ ቢቻል የተጠጋጋ ካልሆነም እንደነገሩ የቆመ መረጃ አሰባስቤ እመለሳለሁ ስል አሰብኩ ፡፡

የዜናው መነሻ ፤

‹‹ ከወደ ባህር ዳር አካባቢ የተሰማው ወሬ በርካቶችን እያስገረመና እያስደነገጠ ይገኛል … ደራሲ በዓሉ ግርማ በዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም ውስጥ አለም በቃኝ ብሎ ሞንኩሶ እግዚአብሄርን እያገለገለ መሆኑ ታውቋል … በይስማዕከ ወርቁ ደራሲነት የምናውቃቸው ዴርቶጋዳ ፣ ራማቶሃራ ፣ ዣንዣራ እና ተልሚድ የተሰኙ ስራዎች የደራሲ በዓሉ መሆናቸው ተረጋግጧል … ይህ ወሬ ከተሰማ በኃላ በርካታ የባህር ዳር ነዋሪዎች የዳጋ ደሴትን ያጨናነቁ ሲሆን የአዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች ነዋሪዎችም በአስገራሚ መልኩ ወደ ስፍራው እየተመሙ ናቸው … ››

ይህን ዜና ያለማመንታት ‹‹ የማይታመን ›› ያሉ የመኖራቸውን ያህል ‹‹ ትክክለኛ ነው ›› እንዲሁም ‹‹ ትክክል ሊሆን ይችላል ›› የሚሉ ግምቶችን ያስቀመጡ ጥቂቶች አልነበሩም ፡፡ እኔም ‹‹ የደራሲዎች እየሱስ ! ›› የምለውን የበዓሉን ብዕር ከአድማስ ባሻገር እስከ ኦሮማይ እንደ ማስቲካ እያላመጥኩ ፣ ድዴ ሲደክም ደግሞ ወሬውን ለስራ ባልደረቦቼ በማካፈል መቋጫ የሌላው ክርክር እንዲነሳ ማድረጌ አልቀረም ፡፡

ከዚህ ቀደም ባለው አነጋገር ለመሞቱ ፣ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ደግሞ ለመጥፋቱ ምክንያት የሆነው ኦሮማይ የተባለውን መጽሀፍ … የማላቀውን የዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም … እንደ አብርሃም ቤት የለኝ እንደ ሙሴ መቃብሬ አይታወቅ የሚለውን የደራሲው ገጸ ባህሪ… ጽሁፍ ህይወት ነው ከዚያ ውጪ ሌላ የህይወት ምኞት የለኝም የሚለውን በዓሉንና በሰበቡ የተነሱትን እነ ዴርቶጋዳ …  ወደ ገዳም ለመጓዝ ሁከትና ጉጉት የሚታይበትን የባህርዳር ህዝብ… ተራ በተራ እየሳልኩ ነበር ባህርዳር የደረስኩት ፡፡

የማጣሪያ ወሬ ፤

በበዓሉ ግርማ ዙሪያ የተነሳውን ዜና ወይም ወሬ ለማጣራትና ወደ አንድ አቅጣጫ ለማምጣት በጉዳዩ ዙሪያ የሚወዳደሩ ክፍሎችን ወይም የሊግ አባላትን ማብዛት ያስፈልጋል ፡፡ ጋዜጠኛም ጸሀፊም በመሆኔ ነው መሰል አስቀድሜ የጨዋታውን ንድፍና ህግጋት / sketch / ለመሳል ያልቦዘንኩት ፡፡ በዚህ ፍትጊያ መሃል ነው ለእውነት የተጠጋ መረጃ ሊገኝ የሚችለው ወይም የተሰወረ መንገድን ማወቅ የሚቻለው ፡፡

እናም የባህርዳር ነዋሪዎች ፣ የተለያዩ የመንግስት መዋቅሮች / ፖሊስ ፣ ባህልና ቱሪዝም ፣ ጋዜጠኞች / ፣ ቀሳውስት ፣ መጽሀፍት ሻጮች ፣ አንባቢዎች ፣ የጀልባ አከራዮችና የዳጋ እስጢፋኖስ አስተዳደሮች በማጣሪያው እንዲሰለፉ አቀድኩ ፡፡ የትኛው ቡድን ወይም የትኛውም መንገድ ለፍጻሜ እንደሚደርስ ለመተንበይ ግን አልሞከርኩም  ፡፡

በጉዳዩ በጣም ተጨናንቋል የተባለውን የባህር ዳር ነዋሪ እኔ ያገኘሁት በሁለት መልኩ ነው ፡፡ አንደኛውና በጣም የሚበዛው ጭራሽ ስለ ርዕሰ ጉዳዩ ያልሰማና ምንም መረጃ የሌለው ነው ፡፡ ሁለተኛው ክፍል ስለ ጉዳዩ የሚያውቅ ነገር ግን የተለያዩ መላምቶችን ደርዝ በሌለው መልኩ ያዘለ ነው ፡፡ አንዳንዶች ‹‹ እስካሁን ይወራል እንጂ የታመነ ዜና አልተገኘም ›› ይላሉ ፡፡ ሌሎች ‹‹ ተጨባጭ መረጃ ባይገኝም በዓሉ ግርማ ገዳሙ ውስጥ ሊኖር እንደሚችል ይሰማናል ›› ብለዋል ፡፡ ወሬው ሀሰት ነው ከሚሉት ውስጥ ዜናው ተቀነባብሮ የተፈጠረው በጀልባ አከራዮች ነው ያሉት ጥቂቶች አይደሉም ፡፡ ለምን ለተባለው ጥያቄ ደግሞ ‹‹ ገበያ ለመፍጠር ›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ደራሲው ገዳም ውስጥ ሊኖር ይችላል የሚሉ ወገኖች ዋነኛ መከራከሪያ ደግሞ በዓሉ በደርግ ተይዞ ተሰወረ ተባለ እንጂ ስለመሞቱ ማረጋገጫ ያለመገኘቱን ጉዳይ ነው ፡፡

በርግጥ የበዓሉ ግርማ ወሬ በፌስ ቡክ ከተለቀቀ በኃላ በባህርዳር የሚገኙ የመንግስት አካላት ጉጉትና ውጥረት ገኖ ቆይቷል ፡፡ አንድ ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ የመንግስት ሰራተኛ የተለያዩ ከፍተኛ ኃላፊዎች ወሬው እውነት ይሁን ሀሰት እንዲጣራ በተለያዩ መንገዶች በገዳሙ ውስጥ ፍለጋ እንዲከናወን አድርገዋል ፡፡ ይህም ጥረት የገዳሙን ነዋሪ ከማጨናነቅ የዘለለ ተጨባጭ ፋይዳ ያስገኘ አልነበረም ፡፡ አንዳንድ የፖሊስ ሰራዊት አባላትም ወሬውን ሊያረጋግጥ የሚችል መረጃ ባለመገኘቱ እውነት ነው የሚል እምነት የለንም ብለዋል ፡፡

ርዕሰ ጉዳዩ ጋዜጠኞችም ሰፈር ደርሷል ፡፡ ጋዜጠኞችም ወሬው ህብረተሰቡ ምርጫውን በአግባቡ እንዳያከናውን ለማደናቀፍ ወይም ለማዘናጋት የሚደረግ ጥረት እንደሆነ ገለጻ ተደርጎላቸዋል ፡፡

በባህርዳር ከተማ ጥቂት የማይባሉ መጽሀፍት መሸጫ መደብሮች ይገኛሉ ፡፡ በዚህ ወሬ ምክንያት የበዓሉ ግርማ መጽሀፍት ከወትሮው በተለየ መልኩ ሊሸጡ እንደሚችሉ ገምቼ ነበር ፡፡ ይህን ግምት ይዤ አራት ከሚደርሱ ነጋዴዎች ጋር ተወያየሁ ፡፡ ሁሉም ስለ ወቅታዊው ወሬ ከበቂ በላይ መረጃ ቢኖራቸውም በዚሁ ሰበብ የበዓሉ ግርማ መጽሀፍት እንዳልተሸጡ ተናግረዋል ፡፡ ሁለቱ ሚያዚያ ውስጥ የተሰማው ወሬ ‹ የአፕሪል ዘ ፉል › ውጤት መሆኑን ሲናገሩ ሁለቱ ደግሞ ማንኛውም ወሬ ውስጥ ጥቂት የእውነት ፍሬ ሊገኝ እንደሚችል ጠቋቁመዋል፡፡ በየግዜው ለገዳሙ በርካታ መጽሀፍት እየተገዙ መግባታቸው የትላልቅ ሰዎች መናኀሪያ መሆኑን ለማስረዳት በመሞከር ፡፡

ሰው በሰው ያገኘኃቸው ቀሳውስት ወሬው ከተማው ውስጥ እንጂ በገዳሙ እንደማይሰማ ተናግረዋል ፡፡ ለብዙ ዓመታት በገዳም ውስጥ ህይወታቸውን ያቆዩ አባቶችን የትናንት ማንነት ለማወቅ ከባድ መሆኑን ብቻ ሳይሆን ብዙም ጠቃሚ እንዳልሆነም አስረድተዋል ፡፡ አለም በቃኝ ብሎ ከፈጣሪ ጋር ለመገኛኘት የሚተጋ ህብረተሰብ የቀደመውን ማንነት ማስታወስ ምን ይረባዋል በማለትም ጫጫታውን ለማርገብ የሞከሩም ይመስላሉ ፡፡

ይህ የጥቂት ቀናት አሰሳ ከጥሩ አንባቢያን ጋርም አገናኝቶኛል ፡፡ በተለይ አንድ አንባቢ ‹ ጥሩ ቀልድ ናት › ነው ያለኝ ፡፡ ይህ ሰው ወሬው ሆን ተብሎ ተቀነባብሮ የተፈበረከው የመቀበል ጸጋ በተሳናቸው ጠማማ ሰዎች ምክንያት እንደሆነ ነው የሚያምነው ፡፡ እሱ ጠማማ ሰዎች የሚላቸው የይስማዕከ ወርቁን ችሎታ ለመቀበል የተናነቃቸውን ነው ፡፡ ወጣቱ ደራሲ ያልተጠበቁ ስራዎች መስራቱ የቅናትና የመበለጥ ስሜታቸው እንዲቆጣ ምክንያት ፈጥሯል ፡፡ እናም ህያው ውብ እጅን ከማድነቅ ይልቅ ለሰበብነት የሞተ ማንነትን እንደ ምክንያት መጠቀም ተመርጧል ፡፡

ወሬውን መንግስት ራሱ ሆን ብሎ ያሰራጨው  መሆኑን በልበ ሙሉነት የሚናገሩም አጋጥመውኛል ፡፡ ይህ ዓይነት አከራካሪና በቀላሉ እልባት ሊያገኝ የማይችል መረጃ የሚለቀቀው ወቅታዊ ጉዳዮችን ወይም ውጥረቶችን ለማርገብ ሲፈለግ ነው ፡፡ መንግስት ከሙስሊሙ ህብረተሰብ ጋር መጋጨቱ ፣ ከተለያዩ ክልሎች የተፈናቀለው የአማራ ብሄረሰብ ጉዳይ መነጋገሪያ መሆኑን እንደ ምክንያት ያነሳሉ ፡፡ በተቃራኒው የበዓሉ ግርማ በዳጋ እስጢፋኖስ የመታየት ጉዳይ ለገዢው ክፍል የሚመች ዜና ያለመሆኑን ያስረዱ አሉ ፡፡ እንዴት ሲባሉ የበዓሉ በህይወት መገኘት የደርግን ገዳይነትና ጨካኝነት እንዲለዝብ ስለሚያደርግ በኢህአዴግ አይን መታየት ያለበት ጉዳይ አያደርገውም ፡፡ በመሆኑም ለገዳሙም ሆነ ለደራሲው ቀጣይ ስጋት እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል ፡፡

መንገዶች ሁሉ ወደ ጣና ይወስዳሉ ፤

ከሰማኃቸው መረጃዎች መካከል ዳጋ እስጢፋኖስ የዶክተሮች ፣ የምሁራኖችና በንባብ የመጠቁ በርካታ ሰዎች ስብስብ ገዳም ነው የሚለው አስተያየት ከፍ ብሎ ይሰማኛል ፡፡ በገዳሙ ለሚገኙ ሰዎች አንዳንድ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት በጎ አድራጊዎች መጽሀፍና ቁሳቁስ የሚረዷቸው ከምን አንጻር ነው ? የሚለውም ጥያቄ የጥርጣሬ ሚዛን ወደታች ዝቅ ብሎ እንዲመዝን የሆነ አስተዎጽኦ ሊያደርግ ይችላል ፡፡ በርግጥ ዳጋ እስጢፋኖስ ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሸፈነና ከሌሎቹ ገዳማትም ልዩ ገጽታ እንዳለው ይታወቃል ፡፡ የገዳሙ ህንጻ የጀልባ ቅርጽ ያለው ሲሆን የዚህ ተምሳሌትም የኖህ ጀልባ የሰው ዘርን ከጎርፍ ጥቃት የማዳኑን ምስጢር ይጠቁማል ፡፡

በዓሉ ግርማ በዚህ ደንና ዋሻ ውስጥ ተደብቆ ይሆን ? ‹ ተፈጸመ › ን ለንባብ አበርክቶ የፍጻሜው ማረፊያ ትሆን ዘንድ በኖህ ጀልባ ተሳፍሮ ይሆን ? ሽቅርቅሩና ታጋዩ ደራሲ በርግጥ ጭምተኛና ገዳማዊ መሆንን መርጧል ? ከሆነ እንዴት ከባድ ምርጫ ነው ፡፡ ምክንያቱም አንድ ገዳማዊ ጤዛ ልሶ ፣ ድንጋይ ተንተርሶ ፤ ድምጸ አራዊትን ግርማ ሌሊትን ታግሶ ነው የሚኖረው ፡፡ አንድ ገዳማዊ ከዓለማዊ ኑሮ ርቆ ፣ ራሱን በራሱ እየረዳ ዘወትር በጾምና ጸሎት ፣ በገድልና ትሩፋት ተጠምዶ የሚኖር የእግዚአብሄር ሰው ነውና ፡፡

እንደ ጣና ማዕበል ግራና ቀኝ የሚላተመውን ሀሳብ ይዤ ወደ ጣና ኃይቅ የግል ጀልባ ማህበር አመራሁ ፡፡ እዚህ ወደ ዳጋ እስጢፋኖስ የሚቀዝፉ ጀልባዎች ይገኛሉ ፡፡ እዚህ ወደተለያዩ ገዳማት የሚጓዙ ሰዎችን ሀሳብና ፍላጎት እንዳልሰሙ ሆነው የሚሰሙ የጀልባው ካፕቴኖች ይገኛሉ ፡፡ እዚህ ስለገዳማቱ የቀረበ መረጃ ያላቸው ሰዎች አይጠፉም ፡፡ እዚህ የሀሰት ፈጠራ ሊፈበረኩ ይችላሉ ተብለው የሚታሙ ሰራተኞችም አሉ ፡፡

ሰላምታ ሰጥቼ ወደቢሮው ከዘለቅኩ በኃላ ስለ ስራ ጉዳይ ማውራት ጀመርኩ ፡፡ የማህበሩ ኃላፊ የሞቀ አቀባበል አደረገልኝ ፡፡ ሞተሬን ካሞቅኩ በኃላ ስለ ርዕሰ ጉዳዩ መጠየቅ ጀመርኩ ፡፡

‹‹ በዓሉ ግርማ በዳጋ እስጢፋኖስ ሊኖርም ላይኖርም ይችላል ›› በማለት ማጋደል ያቃተው ምላሽ ወረወረልኝ
‹‹ እንዴት ነው ሊኖር የሚችለው ? ››
‹‹ ገዳሙ የምሁራን አምባ ስለሆነ ››
‹‹ እንዴት ነው የማይኖረውስ ? ››
‹‹ ምክንያቱም እስካሁን እኔ አይቸዋለሁ የሚል ሰው ስላልተገኘ ››
‹‹ ወሬው ከተሰማ በኃላ ወደ ዳጋ የሚሄደው ጎብኚ ቁጥር በዝቷል ? ››
‹‹ እንግዶች ይሄዳሉ ፡፡ ግን ደራሲውን ፍለጋ ነው ብለው አይናገሩም ››
‹‹ ይህ ወሬ ታዲያ ከየት መጣ ? ››
‹‹ ከፌስ ቡክ ነው ! ››
‹‹ ከእናንተ ነው የሚሉም አሉ ፡፡ ማለትም ገበያ ለመፍጠር ››
‹‹ ዉሸት ነው ! እኛ ያልተረጋገጠ ወሬ ለደንበኞች አንናገርም ፡፡ ይኀው እንዳንተ በርካታ ሰዎች እየመጡ በዓሉ ካለ ልሄድ ነው መረጃ ንገረኝ ይሉኛል ፡፡ እኔ ገንዘብ ብፈልግ አደርገዋለሁ ፡፡ በግልጽ የምነግራቸው ምንም መረጃ እንደሌለኝ ነው ፡፡ የምመክራቸውም መሄድ ያለባቸው ገዳሙን የመጎብኘት ፍላጎት ካላቸው ብቻ መሆኑን ነው ››
‹‹ እውነት ስለ በዓሉ ምንም አላውቅም ነው የምትለኝ ? ››

ኃላፊው የሚያውቀውን በትክክል እንደገለጸልኝ ደጋግሞ ነገረኝ ፡፡ ትንሽ ቆይቶ ግን የአንድ ሰው ስም ጠራና የተሻለ መረጃ ሊገኝ እንደሚችል ጠቆመኝ ፡፡ ወጣቱ የሚሰራው በዳጋ እስጢፋኖስ ጀልባ ላይ ነው ፡፡ ጀልባዋ ሁለት ጥቅም ትሰጣለች ፡፡ አንደኛው የገዳሙን አባላት ካሉበት ወደ ከተማ ፣ ከከተማ ወደ ገዳም ማመላለስ ሲሆን ሁለተኛው ጎን ለጎን ወደ ገዳሙ የሚጓዙ ሰዎችን በተለመደው ታሪፍ ታጓጉዛለች ፡፡ የጀልባዋ ካፕቴን አንተሁን ጥበቡ በገዳሙ የሚኖር ሲሆን የማስጎብኘትም አገልግሎት ይሰጣል ፡፡

ቀጠሮ ለመያዝ ስደውልለት ወደ ክብራን ገብርኤል እንግዶችን ይዞ እንደሄደ ገለጸልኝ ፡፡ ሌላ እድል ስላልነበር የስልክ ቃለ መጠይቁን ማድረግ አንደሚገባኝ ወዲያው ወሰንኩ ፡፡ ዳጋ ውስጥ ከመቶ በላይ መነኮሳት እንደሚገኙ የገለጸው አንተሁን ወደ ገዳሙ የገባ ሰው ራሱን ደብቆ የሚኖር በመሆኑ ተፈላጊውን ለይቶ ለማወቅ ያስቸግራል ባይ ነው ፡፡ በዓሉ ግርማን በፎቶ እንኳ እንደማያውቀው ፣ በቦታው ኖሮ ቢያየው እንኳ ትርጉም እንደሌለው አስረድቷል ፡፡ ብዙዎቹ የበሰሉና ምሁራን ሆነውም ራሳቸውን ምንም እንደማያውቅ መሃይም አድርገው ለመኖር የሚያደርጉት ጥረት ምስጢራዊው ህይወት ምን ያህል ከባድ መሆኑን የሚያስረዳ ነው ፡፡ በዚህም ምክንያት እስካሁን ለጠየቁኝ ሰዎች የሰጠሁት ምላሽ አላውቅም የሚል ነው ብሏል ፡፡ ደራሲውን በአካል የሚያውቀው ሰው ለአዳር መጥቶ መፈለግ እንደሚኖርበትም ሃሳብ ሰጥቷል ፡፡

የገዳሙን ሰው አመስግኜ ወደ ጣና ዳር ተጠጋሁ ፡፡ አያሌ ጀልባዎች ወታደራዊ ሰልፍ ይዘው እንግዶቻቸውን ይጠባበቃሉ ፡፡ ጀልባዎቹ ከተደገፉበት ግንብ አናት ላይ ጉዞን የተመለከተ መረጃ የሚሰጥ ታፔላ ቆሟል ፡፡ የአጭርና ረጅም ጉዞ ታሪፍ ነው ፡፡ ዳጋ እስጢፋኖስ የአጭር ጉዞ ዝርዝር ውስጥ የለም ፡፡ በረጅሙ ጉዞ ውስጥ በሁለተኛ ረድፍ ላይ ግን ጎልቶ ይታያል ፡፡ በብረት ጀልባ ለመሄድ 1700 ብር ፣ በፋይበር ጀልባ ከሆነ ደግሞ 2200 ብር ያስጠይቃል ይላል መልዕክቱ ፡፡



ካፒቴኑ እንደነገረኝ ዳጋ ለመድረስ አራት ሰዓት ይፈጃል ፡፡ ማደር ካለ ደግሞ ክፍያው ከፍ ይላል ፡፡ የቀረኝ እንጥፍጣፊ መረጃ ቢኖር ገዳሙ ራሱ የሚነግረኝ ነው ፡፡ በሁለት ምክንያት ግን ወደ ምሁራኑ አምባ ለማቅናት አልችልም ፡፡ የመጀመሪያው ወደ ደባርቅና ሁመራ ቀሪ መንገድ ስለሚጠብቀኝ የሚያወላዳ ግዜ የሌለኝ መሆኑ ነው  ፡፡ ሁለተኛው ገንዘብ ነው ፡፡ ግዜን ከመንግስት ስራ ቀነጫጭቤ ማትረፍ ብችል እንኳ ገንዘብን ከራሴ ኪስ ለመስረቅ አልቸልም - ከባዶ ኪስ ፡፡

ባዶነት ተሰማኝ ፡፡ ውጤቱ ምንም ሆነ ምን ገዳም ላይ የሚደረገውን የመጨረሻ ፍለጋዊ ውድድር መመልከት ነበረብኝ ፡፡ እንደ ሀገሬ ብሄራዊ ቡድን እያለቃቀስኩም ሆነ እየዘፋፈንኩ ስፖንሰር ለመጠየቅ ዕድል አልነበረኝም ፡፡ ለብሄር ብሄረሰቦች በዓል የተገዛችውን ህብር የተባለች የክት መሳይ ጀልባ እየቃኘሁ ሀይቅ ላይ ወደቆመው ጣይቱ መዝናኛ በዝግታ አመራሁ ፡፡ የኔ አሰሳ በዚሁ ተፈጸመ ፡፡ ‹ ተፈጸመ › የሚባለው የበዓሉ ግርማ ጀግና ወይም ‹ ጦሰኛ › መጽሀፍ ግን እንዲህ ይላል ‹‹ ህይወት አንድ ቦታ ላይ አትቆምም … ትቀጥላለች ያንዱን ህይወት ከሌላው ጋር ድርና ማግ እያደረገች …  ››

ኦሮማይ !!!

Friday, April 19, 2013

‎በመተካካት የተጎዳው ጢስ አባይ ! ‎




የአማራ ባህል፣ ቱሪዝምና ፓርክ ልማት ቢሮ ለቱሪስቶች በሚያሰራጨው ብሮሸር ላይ ስለ ጢስ አባይ ፏፏቴ ግሩም ጽሁፍ አስፍሯል ፡፡ በየቀኑ ጢስ አባይን ለመመልከት የሚሄደው ደቀመዛምርም መምህሩ የጻፈውን ቅኔ በልቡ እያጠና ወደ ቦታው ይጓዛል ፡፡ በነገራችን ላይ ወደ ፏፏቴው ለመሄድ ሁለት አማራጮች አሉ ፡፡ አንደኛው የአባይን ወንዝ በጀልባ ተሻግሮ 15 ደቂቃ የእግር መንገድ መጓዝ ነው ፡፡ በጎዞዬ ላይ ምን አያለሁ ካሉ በመስኖ የሚበቅሉ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ፣ ጋሽዬ ልከተሎት ላስጎበኝዎትም ካሜራ ካልያዙ እንኳ በፌስ ቡክ ላይ የሚለቁትን ምርጥ ፎቶ በሞባይልዎ ላነሳዎት እችላለሁ የሚሉ በርካታ ማቲዎችን ፣ ሻርፕና ጌጣጌጦችን ካልገዙኝ በማለት እስከመዳረሻዎ ሳይታክቱ የሚሸኝዎትን ሰዎች እንዲሁም ‹  የሰው ነገር › የሚል ስም የተሰጠውን ቅጠል ይመለከታሉ ፡፡ ይህ ቅጠል በእጅ ሲነካ ሽምቅቅ ብሎ መጠኑን ይቀንሳል ፡፡ በሌላ አነጋገር የቅጠል ኤሊ መሆኑ ነው ፡፡ ድንጋይ ውስጥ ባይሆንም ሁለመናውን ግንዱ ላይ ይለጥፋል - ከሶስት ደቂቃ ቆይታ በኃላ ደግሞ ወደቀድሞው ይዞታው ይለጠጣል ፡፡

 ሁለተኛው መንገድ መኪናዋን እስከተወሰነ ርቀት ከነዱ በኃላ ከ 30 እስከ 40 ደቂቃ በእግር ሊጓዙ ግድ የሚልዋት ነው ፡፡ ይህኛውን በዳገት የታጀበ አድካሚ መንገድ ቱሪስቶች ይመርጡታል ፡፡ ምክንያቱም አካባቢውን በአግባቡ ለመቃኘት ፣ በ 17ኛው ክፍለ ዘመን የተሰራውን ጥንታዊ የአላታ ድልድይና ሸለቆ ለመመልከት ስለሚረዳ ነው ፡፡ እኔ ሁለተኛውን አማራጭ ስለማውቀው አንደኛውን ምርጫ በመጠቀም ቦታው ተገኝቻለሁ ፡፡ እናም የብሮሸሩ ምንባብ ከጉብኝት በኃላ የሆነ አጭር መልመጃ ቢኖር እንኳ በአግባቡ አስታውሶ ለመመለስ ስለሚረዳ ጎብኚው ደጋግሞ ከኪሱ እያወጣ ያያታል ፡፡ እንዲህ ትላላች ፡፡

The Falls are found at 30 km to south of Bahir Dar near Tis Abay town. Here there is a spectacular basalt cliff Where the Nile form an incredible falls of 45 meters high, known as the Blue Nile Falls. The noise, the force and the smoke created by this fall is really worth discovering. The Blue Nile Falls is locally called the Tis Isat , meant water that smokes .

ቱሪስቱ ከጉብኝት በኃላ ወደ መረጃ ክፍል ተመልሶ ቢገባ ግን መምህሩ ሊፈትነው አይሞክርም ፤ ምናልባትም ትምህርትም ሆነ መረጃ ሰጪዎችን ላያገኝ ይችላል ፡፡ ግን በትምህርቱና በብሮሸሩ ንባብ መሰረት ራሱን መፈተኑ ይጠበቃል - እንዲህ እያለ ፡፡ ‹ በንባቡ መሰረት ትክክለኛ የሆነውንና ያልሆነውን ለይተህ አውጣ ! ትክክለኛ ባልሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ አብሮህ ከጎበኘው ሰው ጋር በድፍረት ተወያይበት ፡፡ የመፍትሄ ሀሳቦችህንም ሀሳብ መስጫ ሳጥን ውስጥ ጨምር ! ›

ሀ . ትክክለኛ የሆነው ፤

1 . ጢስ አባይ ከባህር ዳር 30 ኪሜ ርቀት ላይ ይገኛል
2 . 45 ሜትር ቁልቁል ይወረወራል

ለ . ትክክለኛ ያልሆነው ፤

1 . የሚገርም ፏፏቴ ሊባል አይችልም
2 . ድምጹና ሁካታው እንደተባለው የተጋነነ አይደለም
3 . ታች ሲወርድ የሚፈጠር ልዩ ጢስ የለም
4 . የሚፈጠር ቀስተ ዳመና የለም
5 . ግርማ ሞገሳም ሳይሆን ቆሌ የራቀው መሆኑ ይታያል ፡፡

የመፍትሄ ሀሳብ ፤

. የሰው ነገር የተባለው ቅጠል አባባል አሁን ገና በአግባቡ ገብቶናል

በርግጥም ቱሪስቶች ብዙ ተወርቶላቸው ግዜ ፣ ገንዘብ እና ጉልበታቸውን መስዋዕት አድርገው ጢስ አባይ ዳገት ላይ ሲደርሱ ‹‹ እንግዲህ ጢስ አባይ ፏፏቴ ማለት ይህ ነው ! ›› ይላቸዋል ወጣት አስጎብኚው

‹‹ የቱ ? ››
‹‹ ይኀው ፊት ለፊት የምታዩት ! ››
‹‹ መቼም እየቀለድክ አይደለም ! ››
‹‹ እረ በስራ አንቀልድም ››
‹‹ ካልቀለድክ ታዲያ የታለ  የፏፏቴው ግዝፍና ? የቱ ነው ግርማ ሞገሱ ? የታለ ዳገት ላይ የሚደርሰው የውሃ ፍንጥቅጣቂ ? ቀስተ ዳመና የተባለውስ ? የታለ አስደማሚው ጢሱ ? ››

አስጎብኚው ያለው ብቸኛ እድል የሰው ነገር እንደተባለቸው ቅጠል ቀስ እያለ መሸማቀቅ ብቻ ነው ፡፡ ሳር እንዳጣ ከብት እንዲህ የገረጣውን ጢስ አባይ ለሃይል ማመንጫ ስለተገደበ ወዘተ … እያለ ማሳበቡ ለቱሪስቱ በቂ ምላሽ እንደማይፈጥርለት እሙን ነው ፡፡ ምክንያቱም የኃይል ጥያቄ ለሀገሬው እንጂ ለቱሪስቱ ጉዳዩ አይደለምና ፡፡ የእሱ መሰረታዊ ጉዳይ ብዙ ያወጣበትና የለፋበትን መስህብ አይቶ መርካት ነው ፤ እርካታው ከሞላ ደግሞ ወደ ሀገሩ ሲሄድ ያየውን በማውራት እግረ መንገዱን ማስታወቂያ መስራት ነው ፡፡ ዛሬ ግን አያሌ አስጎብኚዎች እንግዳቸውን ለማሳመን ሳይችሉ በርካታ ጎብኚዎች በሚሰጣቸው ምክንያት ሳይረኩ እየተበሳጩ መመለስ ግዴታቸው ሆኗል ፡፡

የፏፏቴው ጉዳይ አሳሳቢ ነው ፡፡ 75 ከመቶ ያህሉ ለሃይል ጥቅም ስለተገደበ ወደ ፏፏቴው የሚወርደው የውሃ መጠን የወፍራም ሰው ሽንት አክሏል ፡፡ ይህን ኢምንት ውሃ ደግሞ በሌላ ቦታ ማየት ይቻላል ፡፡ ወይ ያለቅጥ የሚሰማውን የተንዠረገገ ማስታወቂያ እንደ ጎጃም ልጅ ቁንጮ አስቀርቶ መከርከም አሊያም በድንጋይ ፋንታ ሙሉ ዉሃ የሚታይበትን ፕሮግራም ነድፎ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ፡፡ ለምሳሌ ያህል ቅዳሜና እሁድ በርከት ያለ የውሃ መጠን ከግድቡ ቢለቀቅ ጎብኚው ሳምንቱን እየጠበቀ እየረካ ሊመለስ ይችላል ፡፡ የማይቻል ከሆነ ግን በቴሌቪዥን የሚታየውና በቃል የሚነገርለትን ጢስ አባይ ለሁለት ከፍሎ ማየት ሊገባ ነው ፡፡ የሚያስጎመጀውን ‹ የቀድሞው ጢስ አባይ › በማለት የአሁኗን ‹ በመተካካት የተገኘች › ማለት ይሻላል ፡፡ 
ምክንያቱም ዉሸት ስለሚያሳፍር ፡፡ ባይሆን እቺ የተተካቸው ‹ አቅም እየፈጠረች ስትሄድ መፈርጠሟና ማስደመሟ አይቀርም › እያሉ መስበክ ይሻላል ፡፡ የቱሪዝሙም ገቢ አይቅርብኝ ፣ የሃይል ጉዳይም የግድ ነው ብሎ ውሃ ውሃ የሚል ወጥ መስራት ግን መጨረሻው የበሰለውን ማበላሸት ይሆናል ፡፡ 

Tuesday, April 9, 2013

‎ሰላማዊ ሰልፍ በየዓይነቱ !‎


mexico
.


ሰላማዊ ሰልፍ ዴሞክራሲ ከወለዳቸው የነጻነት ልጆች አንደኛው ነው ፡፡ በርግጥ እንደ ልጅና እንጀራ ልጅ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰልፎች መኖራቸው ይታወቃል ፡፡ እንደ ልጅ የሚቆጠረው የደገፈውም ሆነ የተቃወመው ሰልፋዊ ጥያቄ ይፈታለታል ወይም ባይፈታለት እንኳ በጥሞና ይደመጥለታል ፡፡ የእንጀራ ልጅ ዓይነቱ ግን ሶስት ዓይነት መንገድ የሚከተል ይመስላል ፡፡

. ትንሽ በሚራራ ወላጅ ያለው - ያለ ምንም አዳማጭ አደባባይ ተንጫጭቶ እንዲመጣ ይፈቀድለታል ፡፡
. በተረገመ ወላጅ ስር ያለው - ሰላማዊ ሰልፍ የሚሰማ እንጂ የሚነካ አይደለም እየተባለ ያድጋል ፡፡
. በብልጣ ብልጥ ወላጅ መዳፍ ስር ያለው - አባቱ ሲፈቅድና ደስ ሲለው ብቻ ለድጋፍ የሚወጣበት ምርጥ መሳሪያ መሆኑን ጸጉሩ እየተደባበሰ በተመስጦ ይነገረዋል ፣ ይማራል ፡፡

በዚህና በመሳሰሉ ስሌቶች የዓለማችን ህዝቦች ሰላማዊ ሰልፍ አከናውነዋል ፤ እያከናወኑም ይገኛሉ ፡፡ የሰልፎቹ መነሻም ሆነ የሚንጸባረቁበት መንገድ ጠንካራ ፣ ረጅም ግዜ የሚቆይ ፣ ልዩና ገራሚ እንዲሁም ለውጥ አምጪ ሊሆን ይችላል ፡፡ በዚህ ረገድ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአንዳንድ ሀገሮች የሚታየውን ተጠቃሽ ሰላማዊ ሰልፍ ገጽታ በስሱ እንቃኝ ፡፡

. ደቡብ አፍሪካ  - ከአፓርታይድ ትግል ወዲህ በዚች ሀገር የጠንካራ ሰላማዊ ሰልፍ ምንጮች የማዕድን ሰራተኞች ናቸው ፡፡ ጉልበታችን አላግባብ እየተበዘበዘ ስለሆነ የላባችን ውጤት ይከፈል በማለት ሞትን ያስከተለና መንግስትን ያጨናነቀ ሰልፍ አድርገዋል ፡፡

. ቻይና  - ገባ ወጣ ቢሆንም በዚች አፋኝ ሀገር የሰላማዊ ሰልፉ መሰረታዊ ጥያቄ ቅድመ ምርመራና አፈናን መቃወም ነው ፡፡

. ሶሪያ ፣ ቱኒዝያ ፣ ግብጽ ፣ ሊቢያ፣  አልጀሪያ ፣ ሞሮኮ ፣ የመን ፣ ባህሪን  - መንግስትና የሚከተለው ፓለቲካዊ ስርዓት ቤተሰባዊ እንጂ ህዝባዊ ጥቅም የሌለው በመሆኑ መንግስትም አሰራሩ ይቀየርልን በሚል በብዙ ሰልፍና ተቃውሞ ደክመዋል ፡፡ የተሳካላቸው እንዳሉ ሁሉ ገና በመንገድ ላይም ያሉ ብዙ ናቸው ፡፡

. አሜሪካ  - በተለይም ዋል ስትሬት በተባለው ተቃውሞ እኛ 90 ከመቶ ነን ያሉ ሰልፈኞች የድሃውን እኩል አኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ይረጋገጥ በሚል ሰፊ ድምጽ አሰምተዋል ፡፡

. ፍልስጤም  - አሷፊዎች ለተቃውሞና ሰልፍ የተፈጠሩ ይሏቸዋል - ተገራሚዎች የመብትና የነጻነት ታጋዮች ይሏቸዋል ፡፡ ሰው በጥይት ሲሞት ይሰለፋሉ፣ ሞት ለእስራኤልና አሜሪካ በማለት ባንዲራ ለማቃጠል ይሰባሰባሉ ፣ ለመሬትና ድንበር ጥያቄ ያልተሰለፉበትና ያልተጋጩበት ቀን ኢምንት ነው ፡፡

. ቤልጂየም  - የወተት ሽያጭ ዋጋ አሽቆለቀለ በማለት የአውሮፓን ገበሬዎች በሙሉ አስተባብረው የተቃውሞ ሰልፍ ያከናውናሉ ፡፡ በሰልፉ ላይ አንድ ሺህ የሚደርስ ትራክተር ሊያሰልፉ ይችላሉ ፡፡

. ስፔን  - ሀገሪቱ ከቅርብ ግዜ ወዲህ የገጠማትን የኢኮኖሚ መላሸቅ ተከትሎ በርካታ እንጀራ ነክ ኡኡታዎችን ብታስተናግድም እቺ ሀገር ለየት ባለ ሰልፍም ትታወቃለች ፡፡ ይኅውም እጅግ ተስፋፍቶ የሚታየውን የ ‹ ቡል ፋይት › ከእንስሳት መብት አንጻር በመቃወም ሴቶች ራቁታቸውን አስፓልት ላይ የመተኛታቸው ጉዳይ ነው ፡፡

. ህንድ  - በሀገሪቱ ፍጹም እየተስፋፋ የሚገኘው የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ይቁም ! አጥፊዎች አስተማሪ ቅጣት ይሰጣቸው  ! በሚል በየግዜው ታላላቅ ሰልፎች ይደረጋሉ ፡፡

ሩሲያ  - የሩሲያ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ትልቁ ጥያቄ ልክ እንደ ጣሊያናዊው ቤርለስኮኒ / Basta Berlusconi እንደተባሉት / የፑቲንም ስርዓት ማብቂያ ይበጅለት ፣ የመንግስት ስርዓት እንደፈለጉ የሚገቡበትና የሚወጡበት የግል ቤት አያድርጉት ! ፍትህ ይስፈን ! የሚል ነው ፡፡ የፑሲ ተቃውሞ / pussy Riot / በሚል አዲስና ልዩ ስልት ሴቶች ብልታቸውን በዘግናናኝ መልኩ ቆልፈው በየአደባባዩና ቤተ እምነት ሳይቀር የተቃወሙበት ሂደት ነው ፡፡

. ቺሊ - ልጆቻችን ጥራት ያለው ትምህርት እያገኙ አይደለም በሚል ጥንዶች ተቃውሞያዊ ሰልፋቸውን ያቀርባሉ ፡፡ በምን መንገድ ከተባለ ግን በመሳሳም ይሆናል ምላሹ ፡፡

. ኢትዮጽያ  - ኢትዮጽያኖች ሁልግዜም ጠዋትና ማታ ትላልቅና በሰው የተጨናነቀ ሰላማዊ ሰልፍ ያደርጋሉ ፡፡ ሰልፋቸው መስቀል አደባባይን ንቆ በየሰፈሩ ሆኗል ፡፡ የሰላማዊ ሰልፉ ምክንያት ታክሲ አጣን ፣ በትራንሰፖርት እጦትና ኢ ፍትሃዊ ታሪፍ ተንገላተን  በማለት አይደለም - በቃ ታክሲ ጥበቃ ነው ፡፡

Sunday, April 7, 2013

‎የወላጅ አልባ አንበሶች ያልተነገረ ታሪክ‎


ስለ ወላጅ አልባ ህጻናት እንጂ ስለ ወላጅ አልባ እንስሳት ብዙዎች ብዙ እንዳልሰሙ ግልጽ ነው ፡፡ ብይኑ እነዚህን እንስሳት ወላጅ የሌላቸው እንስሳት ሆነው ራሳቸውን ማስተዳደር የማይችሉ ይላቸዋል ፡፡ ለሀገራችን ወላጅ አልባ ህጻናት መፈረጃ ትልቁ ምክንያት ድህነትና ኤችአይቪውን ጥቂት ከጎናቸው በማራቅ በምትኩ በሽታን ይወስዳሉ ፡፡ በመኪናና በተፈጥሮ አደጋ በተለይም ደግሞ በአዳኞች ርጉም ጥይት መሞት አብይ መንስኤያቸው ሆኗል ፡፡

ትልቅ ሆነው ፍርሃት ከሚያነግሱ እንስሳት አንበሳን በዋናነት መጥቀስ እንችላለን ፡፡ ይህ የስልጣን ፣ የኃይል ፣ የድፍረትና የዝና ምልክት የሆነው እንስሳም ክፉ ቀን ከመጣበት ወላጅ አልባ መጠለያ ውስጥ ፊቱን ጥሎ ሊታይ ይችላል ፡፡ መቼም እነ ጎሽ ፣ የሜዳ አህያ ፣ ሚዳቆ ፣ አጋዘን የመሳሰሉት በአጋጣሚ በሽቦ አጥር የተከለለ መጠለያ ውስጥ ቢያዩት መቶ ፐርሰንት ተስማምቶም ሆነ ተገዶ እዚህ መገኘቱን አያምኑም ፡፡

‹ ወይ ጋሽ አንበሶ ? እንዲህ ዓይነት ማዘናጊያ ጀመረ ደግሞ ! › ልትል ትችላለች ሚዳቆ
‹ ቆይ ግን ምን ለማለት ነው ? በመላመድ ከሌሎች ጋ በሰላም መኖርም እችላለሁ እያለን ነው ? › አጋዘን እየበሸቀ መናገሩ ይጠበቃል ፡፡
‹ ሌባ በለው አጭበርባሪ ! › ከጎሽ ኃይለ ቃል አይጠፋም ፡፡

ሌሎቹም ቢሆኑ በጣም እየፈሩና እይተጠነቀቁም ቢሆን የበዛ ስልቂያ እንደሚያሰሙ አያጠራጥርም ፡፡ ምክንያቱም የደኑ ንጉስ ከፈለገ አጥሩን በጣጥሶ አሊያም ብዙም ሳይንደረደር ከለላውን እንደሚዘላት ይገባቸዋልና ፡፡ እንኳን እነሱ ‹ ከኔ በላይ ላሳር › የሚለው የሰው ልጅ ከእሱ በላይ መኖሩን የሚያስመሰክር ዘፈን ዘወትር እንደሚከተለው እንደሚያሰማ የወሬ ወሬ ሰምተዋል ፡፡

          ‹‹ አንበሳው አንበሳው አንበሳው ልጅሽ
                              ይኅው መጣልሽ !!! ››

ይህን የሚዘምረው በጣባብ የጎል ልዩነት ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈ ብሄራዊ ቡድን ብቻ አይደለም ፡፡ ይህን የሚዘምረው ወገቡ በዝናር ጥይትና በእጅ ቦንብ ፤ እጁ አውቶማቲክ ጠመንጃና ጸረ ታንክ የተሸከመ ስልጡን ወታደር ጭምር እንጂ ፡፡ ዓለምን የሚያደባይ መሳሪያ የጨበጠ ሰው እንኳ ከመሳሪያው ይልቅ ለአንበሳ ትልቅ ክብር እንደሚሰጥ ይረዳሉ ፡፡
ታዲያ የነጎሽና አጋዘን መላምት እንዴት ትክክል ላይሆን ይችላል ? እረ ለቁጥር የሚታክቱ ማሳያዋችና ማስረጃዋችንም አንድ ሁለት እያሉ መዘርዘር አይከብድም ፡፡ ምን ዘፈን ፣ ሙገሳና ቀረርቶ ብቻ ?

ማነው የአንበሳው ክፍለጦር እያለ ስያሜ የሚሰጠው ?
አንበሳ ግቢ ?
አንበሳ አውቶብስ ?
አንበሳ ጫማ ?
አንበሳ ባንክ ?
አንበሳ ኢንሹራንስ ?
ጥቁር አንበሳ ?
አቶ አንበሴ ?

የአውጉስታ ሸሚዝ ፋብሪካ ምልክት የሆነው የሜዳ አህያም ሆነ የፈጣንና ዘመናዊ መኪናዋች ምስል የሆነው አቦሸማኔ አንበሳ በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጽያ የብዙ ነገሮች ምልክት መሆኑን የሚያውቁት ገና ጥርስ ከማውጣታቸው በፊት ነው ፡፡
አንበሳ በቀድሞዎቹ የኢትዮጽያ ባንዲራ ላይ
በአሁኑ ፍራንክ ላይ
በቀድሞ ጽሁፎች ላይ
በኢትዮጽያ ንግድ መርከብ
በቀድሞው አየር መንገድ
በኢትዮጽያ መንገዶች ባለስልጣን
በቴሌኮሙኒኬሽን

ባልጠቀስናቸው መ/ቤቶች እንደ ሎጎ አገልግሏል ፤ ዛሬም በገሃድ እያገለገለ ይገኛል ፡፡ በሚንሊክ ዘመነ መንግስት መስቀል በእግሩ የያዘና ዘውድ የደፋ አንበሳ ባንዲራ ላይ ይታይ ነበር ፡፡ ይህ ምልክት በንጉስ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስትም ሰርቷል ፡፡ የይሁዳ አንበሳ ይሉታል ፡፡ ደርግ ስልጣን ሲይዝ አናቱ ላይ የደፋውን ዘውድ በሞርታር ጥይት አሽቀንጥሮ በዚያው ይቀጥላል ቢባልም አንበሳው የያዘው መስቀልና እሱ የሚከተለው ርዕዮት ሊዛመድለት አልቻለም ፡፡ በአጠቃላይ ‹ አንበሳ አያስፈልገኝም › በማለት ገፈተረው ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ግን አንበሳው ክፍለጦርን አቋቁሞ አንበሳውን ደጋግሞ ማሞገስ ተያያዘ ፡፡

አንበሳ ከዚህም በላይ ሊወራለት እንደሚችል ይታወቃል ፡፡ ከዚህ አንጻር አንበሳ በወላጅ አልባ እንስሳት ስም መጠለያ ገባ የሚለው ዜና የማይመስል ሊመስል ቢችል አያስገርምም ፡፡ ወይም የማይታወቅ ፡፡

ከአዲስ አበባ በ25 ኪሎ ሜትር ርቀት ማለትም ሆለታ አካባቢ የሚገኘው የእንስሳት መጠለያ ግን የስድስት አንበሶች ልዩ ታሪክ ይዟል ፡፡ ቦርን ፍሪ በሰዎች ተይዘው የሚሰቃዩ እንስሳትን ተግባር በማስቀደም ከችግር የሚላቀቁበትንና እንክብካቤ የሚያገኙበትን ሁኔታ የሚያመቻች አለማቀፍ ድርጅት ነው ፡፡ የዚህ ድርጅት የኢትዮጽያ ተጠሪ ሆለታ አካባቢ የሚገኘውን መጠለያ ‹‹ የእንስሳት ኮቴ ›› የሚል ስያሜ በመስጠት በሀገራችን የመጀመሪያውን የዱር እንስሳት ጥበቃ ፣ ልማትና ትምህርት ማዕከል በመሆን እየሰራ ይገኛል ፡፡

ግቢው 77 ሄክታር መሬት የሚያካልል ሲሆን በደን የተሸፈነ ነው ፡፡ በቀጣዮቹ አንቀጾች ከምንገልጻቸው ጥንድ - ጥንድ አንበሶች በተጨማሪ አቦሸማኔ ፣ ጉጉት ፣ ጦጣ ፣ ኤሊ ፣ ተራውና በሀገራችን ብቻ የሚገኘው ዝንጀሮዋችም ይገኙበታል ፡፡

ዶሎና ሶፍያ

ዶሎና ሶፍያ

ዶሎ የተባለው አንበሳ አንድ ሜትር ርዝመት ባለው ሰንሰለት በደቡብ ኢትዮጽያ በሶማሌ ድንበር አካባቢ በአንድ ሰው እጅ ነበር ፡፡ ይህ ሰው ለአራት ዓመታት ያህል በፍልጥ እንጨት በተሰራ ጠባብ ክፍል ውስጥ እንዲኖር አስገድዶታል ፡፡ የአካባቢው ሰዎች እንዳስረዱት አንበሳው ብቸኛ በመሆኑና አያያዙም ጥሩ ስላልነበር ዘወትር ጠዋት የሚያሰማው የሰቆቃ ጩኀት በከተማው ሙሉ  ይሰማ ነበር፡፡

ሰቆቃወ ወ ዶሎ ከአዛማጅ ትርጉም አንጻር እንደሚከተለው የሚገለጽ መስሎኛል . . .

‹ እረ የአንበሳ ያለህ ?! እረ የእንስሳት ያለህ ?! ዛሬስ ጠረናችሁ ናፈቀኝ !! ›
‹ አይ እናቴ ! ነጻ በሆነው ጫካ ተወልደሃል የምትይው መዝሙር እንዴት ተቀይሮ ከባርነት ጫማ ስር ተገኘሁ ?! ›
‹ እረ የነጻነት ያለህ ?! እረ የፍትህ ያለህ ?! በምን ጥፋቴ ነው ሰንሰለት የሚበላኝ ?! በምን ተፈጥሮ ነው በሰው ልጅ የምዳኝ ?! ›
ይህ ሁኔታ ብዙዎችን ስላሳሰበ ጉዳዩን ለሚመለከተው ክፍል አሳወቁ ፡፡

ዶሎ በዱር እንስሳትና በቦርን ፍሪ ትብብር መጀመሪያ የተወሰደው ወደ አዋሽ ብሄራዊ ፓርክ ነበር ፡፡ እዚያ የተሻለ እንክብካቤ አግኝቷል ፡፡ አንበሳ ያልነበረው የእንስሳት ኮቴ ዶሎን የመጀመሪያ እንግዳ አድርጎ ለመቀበል ብዙ ጥረት አድርጓል ፡፡ ደረጃውን የጠበቀ ግቢ ለመስራት ፣ የተሻለ ምግብ በቀጣይነት ለማቅረብና  ህክምናውን ለመከታተል የሚያስችሉ ዝግጅቶች ከተከናወኑ በኃላ ጉዞ ወደ ሆለታ ሆነ ፡፡ ዶሎን ለማጓጓዝ ሰባት ሰዓታትን ማሳለፍም ግድ ብሏል ፡፡

ዶሎ አሳድገዋለሁ ባለው ሰው እጅ እያለ ምን እንደሆነ ባይታወቅም አይኖቹ ተጎድተዋል ፡፡ ሩቅ የማየት ችግር እንዳለበትም ተረጋግጧል ፡፡ ሀኪሞች በልጅነቱ በምግብ እጥረት በመጎዳቱ ለአይን በሽታ ሳይጋለጥ አይቀርም የሚል ሀሳብ አላቸው ፡፡ በሰንሰለቱ ምክንያትም ግርማ ሞገስ ሊፈጥርለት የሚገባው የጋማው ጸጉር ሊረግፍ ችሏል ፡፡

ዶሎ በሰፊው ግቢ፣ በምግቡና በተፈጠረለት አንጻራዊ ነጻነት ቢረካም ‹  አንድ ውሃ አጣጪ ባገኝ ምን አለበት ? › እያለ እንደሚያስብ ይገመታል ፡፡ የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖ ኡደት በተባለ ቦታ የሚገኙ ልጆች ሴት አንበሳ ይዘው በአነስተኛ እንጨት ውስጥ መቀመጧ ሪፓርት ይደረጋል ፡፡ አንበሳዋ ስትገኝ እድሜዋ ገና ሰባት ወር ብቻ ነበር ፡፡ እናትየው ልጆቿ ወንዶች ከሆኑ ትልቁ አንበሳ በመቅናትና የነገ ባላንጣዬ ነው በማለት እንደሚገድላቸው ስለምታውቅ ከአጠገቧ እንዲርቁ አታደርግም ፡፡ አንበሶች ልጃቸውን ለመንከባከብ ግድ የማይኖራቸው የምግብ ችግር ባለበት ግዜ ነው ፡፡ ምናልባትም በኃላ ላይ ‹‹ ሶፍያ ›› የሚል ስም የተሰጣት አንበሳ በህጻናቱ እጅ የወደቀችው ይህን በመሰለ ችግር ሊሆን ይችላል ፡፡

ዞሮ ዞሮ ዶሎ ከሶፍያ ጋር መጣመር መቻሉን እንደ ሁለተኛ ዕድልም ድልም ነው የሚመለከተው ፡፡ የመጀመሪያው ሰንሰለቱን የማስቆረጡ ተግባር ነው ፡፡ ሰንሰለት በውሻ እንጂ በአንበሳ አንገት ላይ ቦታው አይደለምና ፡፡ ሁለተኛው ዕድል / ድል በረዶ የሰራበትን ብቸኝነት ብቻ ሳይሆን እንደ አለት የጠጠረውን የፍቅር ጥያቄ ቀስ በቀስ እያቀለጠች ምላሽ ልትሰጥ የምትችል ተቃራኒ ጾታ የማግኘቱ ሚስጢር ነው ፡፡ በርግጥ ጾታዊ ግንኙነቱ ‹ ብዙ ተባዙ ! › እስከማለት የሚያደርስ አይደለም ፡፡ ምክንያቱም የግቢው ህግ የተጎዱ እንስሳትን ለመንከባከብ እንጂ ለማራባት የሚፈቅድ አይደለምና ፡፡ ለምን ከተባለ የዱር እንስሳትን በተወሰነ አጥር ውስጥ ከልሎ ማራባት ከተፈጥሯዊ የኑሮ ዘይቤያቸው አንጻር ስለማይቻል ፡፡ አደኑ ፣ መሯሯጡ ፣ ምግብ ፍለጋው ፣ መደበቂያው ፣ መራቢያው እና ሌላውንም ጉዳይ የሽቦው ቤታቸው አይመልስምና ፡፡ በዚያ ላይ የተራቡትን ሁሉ ለማሳደግ የኢኮኖሚ አቅም አይፈቅድም ፡፡ ይህን ሳይንሳዊ የተባለ የሰው ልጅ ምክንያት እነ አንበሶ አይቀበሉትም ፡፡ አንዳንዶች ስለ ሙሉ ነጻነት ነው የሚያስቡት ፤ ሰዎች ደግሞ እነዚህ አንበሶች ወደ ጫካው ቢለቀቁ የመገለልና የመጠቃት ዕጣ ስለሚያጋጥማቸው ጉዳቱ ይብስባቸዋል ነው የሚሉት ፡፡ አንበሶቹ ግን የፈለገ ቢሆን ማን እንደ ቤት … ማን እንደ ዘር ባይ ናቸው ፡፡ አንዳንዶቹ ተቃውሟቸውን በጩኃት ይገልጻሉ ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ የማንዴላን መጽሀፍ ያነበቡ ይመስል ‹‹ LONG ROAR TO FREEDOM ›› የሚል ድርሰት ለመጻፍ በዝምታ ያደፈጡ ይመስላል ፡፡

ሜጀርና ጄኔራል


ሜጀርና ጄኔራል

በወታደራዊ አጠራር ሜጀር ጄኔራል ትልቅ ስልጣን ነው ፡፡ በሀረር የሚገኝ አንድ የጦር ካምፕ ለ13 አመታት ሲያሳድጋቸው ለቆየው ሁለት አንበሶች ወታደራዊ መጠሪያ ለመስጠት ባያመነታም ትልቁን ወታደራዊ ማዕረግ ለሁለት መሰንጠቁ ግን ግራ አጋቢ መስሏል ፡፡ አንዱን ሜጀር ሌላውን ጄኔራል በማለት ፡፡

እነዚህን ጀርባ ጥቁር አንበሶች የተመለከተ በግርማ ሞገሳቸው ይማረካል ፡፡ ከነዶሎና ሶፍያ ግቢ በተወሰነ ርቀት ላይ በሌላ የሽቦ አፓርታማ ውስጥ ነው የሚኖሩት ፡፡ በርግጥም እንደ ወንድማማችነታቸው ተሳስበው በሰላም የሚኖሩ ይመስላሉ ፡፡ አልፎ አልፎ ግን ከአንዱ ጥግ ወደ ሌላው እየተንጎማለሉ የሚያሰሙት ልዩና አሳዛኝ ድምጽ አላቸው ፡፡ ባለሙያዎቹ የተለመደና ተፈጥሯዊ ጉዳይ ነው ቢሉም እኔ ግን ምናልባትም ስለ ሶፍያ የሚያሰሙት የፍቅር መወድስ ሊሆን ይችላል ባይ ነኝ ፡፡ የአንበሳ የፍቅር ዘለቄታነት እስከመጨረሻው ቢሆንም ሴት እጅግ ብርቅ በሆነበት በዚህ ጫካ መንግስት እንደሚለው ወጪን ብቻ ሳይሆን ሁሉን ነገር ተጋርቶ መኖር እንደ ስርዓት አልበኝነት አያስቆጥርም ፡፡ እናም ዶሎ ቢከፋው እንኳ … ሜጀርና ጄኔራል እንደሚከተለው  እያሉ መስሎኛል …

                  ኦ ! ሶፍያ . . .
                  መች ይሆን የፍቅርሽ ገበያ
                  የሚውለው ከጠረንሽ አልፎ
                  ልፍያና ጉንተላን አሰልፎ
                  ከኛም ግቢ … ከኛ መንደር
                  የሚወደስ  … የሚከበር
                  ኦ ! ሶፍያ . . .
                  ከለለን አጥሩ
                  አነቀን ድንበሩ
                  እንዲህ ነበር እንዴ ወጉ ?!
                  የባህል ልምዳችን ማእረጉ
                  ታዲያ መች ይጸድቃል ቀኑ ?
                  ‹ ፓሪ › መጨፈሪያችን ‹ ዩኒየኑ ›
                   ኦ ! ሶፍያ . . .                           

የዛሬን አያድርገው እንጂ ወንድማማቾቹ የተፈጠሩት ሶስት ሆነው ነበር ፡፡ በአንድ ክፉ ቀን ሶስት የአንበሳ ግልገሎች በባሌ አካባቢ በወታደሮች ተገኙ ፡፡ ወይም በወታደራዊ ቋንቋ ተማረኩ ፡፡ የግልገሎቹ ወላጆች የት ጥለዋቸው እንደሄዱ ፣ ወይም ምን እንደሆኑ አይታወቅም ፡፡ አንደኛዋ ግልገል ሴት ነበረች ፡፡ ይሁን እንጂ ማራኪዎቹ ወደ ካምፓቸው ባደረጉት ጉዞ ሴቷ በፋቲክ ለባሾች እጅ ከመውደቅ በሚል ነው መሰለኝ ከመኪና በመዝለሏ ወዲያው ሞተች ፡፡ ሁለቱ ወንድማማቾች ከመሞት መሰንበትን መርጠው ካምፕ ውስጥ በአነስተኛ መጠለያ ለመቀመጥ በቁ ፡፡

ግልገሎቹ እያደጉ ሲመጡ ማራኪዋቻቸው የየዕለት ተግባራቸውን መቆጣጠር አልቻሉም ፡፡ በመሆኑም የዱር እንስሳት ባለስልጣን እንዲታደጋቸው ጥሪ አቀረቡ ፡፡  ቦርን ፍሪ በበኩሉ የአንበሶቹን መኖሪያ በመገንባት የሶስት ወራት ግዜ ወሰደ ፡፡ ትላልቆችን አንበሶች በትልቅ የጭነት መኪና የእንስሳት ኮቴ ግቢ ለማድረስ 16 ሰዓታት መንዳት አስፈልጓል ፡፡ ዛሬ የሜጀርና ጄኔራልነት ተክለ ሰውነት ብቻ ሳይሆን ስለ ፍቅር ፣ ወንድማማችነትና ስለ ህይወት የሚያቀነቅኑትን ፉከራዎችንና አርምሞዎችን መስማት የሆነ ስሜት ይፈጥራል ፡፡

አንድሪያና ጃኑ


አንድሪያና ጃኑ

ስማቸው እንደሚጠቁመው እነዚህ ሁለት አንበሶች ዜግነታቸው ከጣሊያን ነው ፡፡ አስተዳደጋቸው ደግሞ ኢትዮጽያ ፡፡ አንበሶቹ በሆነ ወቅት አነጋጋሪ ጉዳይ መፍጠር ችለው ነበር ፡፡

ነገሩ እንዲህ ነው ፡፡

እአአ በ2006 ሁለቱ ቤተሰብ አልባ ግልገል አንበሶች ጣሊያን ኤምባሲ ውስጥ ተገኙ ፡፡ የመጡት የአንድ ልዑክ ቡድን ምክትል ኃላፊ በሆኑ ሰውና ሚስታቸው አማካኝነት ነበር ፡፡

ሁለቱ ወንድማማች አንበሶች እያደጉ ሲመጡ ጣሊያኖቹ አንበሶቹ ማግኘት ስለሚገባቸው ትክክለኛ ቤትና የወደፊት ዕጣ ፈንታ በተመለከተ ቦርን ፍሪን ማነጋገር ጀመሩ ፡፡ አንደኛው ሀሳብ አንበሶቹ ወደተወለዱበት ጣሊያን መመለስ ይኖርባቸዋል የሚል ነበር ፡፡ጣሊያን መቼም የራሷን ንብረት አይደለም የወረረችውንም ሀገር ሃውልት ሳይቀር ተሸክማ ሄዳለች ፡፡ በነገራችን ላይ ወራሪዎች የከበሩ ማዕድናትንና ውድ ቅርሶችን በመዝረፍ አልሆን ካላቸውም አውድመው በመሄድ ይታወቃሉ ፡፡ ጣሊያን ግን ያን ትልቅ ሃውልት ስንት ባህር አቋርጣ ተሸክማ መሄድዋ ይገርመኛል ፡፡ እንደውም አንዳንዴ እኛ በተረት የምናውቀው አህያ ተሸክሞ የሚሄደውን ማሞ ቂሎ ሁሉ የሆነች ይመስለኛል ፡፡ እያደር ግን ድንጋይና ኃውልት ላይ ሃይለኛ ፍቅር እንዳላቸው ተገንዝቤያለሁ ፡፡

መቼም ፍትሃዊ ህዝብና መንግስት ሀገር ላወገዘው ወንጀለኛ / ግራዚያኒ / የጀግና ሃውልት ያቆማል ተብሎ አይታሰብም - ልክ ብልጥ መንግስት የሰማይ ስባሪ የሚያህል ሃውልት ተሸክሞ እንደማይሄደው ሁሉ ፡፡ ጣሊያን ግን ከነዚህ እውነት ጀርባ በኩራት ቆማለች ፡፡ እናም አንበሶቻችን ይመለሱ ብለው መጠየቃቸው የኃላ ታሪካቸውን ለሚያውቅ አያስገርምም ፡፡

የኢትዮጽያ መንግስት ግን ከብዙ ሁኔታዎች አንጻር ይህን ሀሳብ ለመቀበል ተቸገረ ፡፡ ይሄኔ ቦርን ፍሪ ከፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ መነጋገር ጀመረ ፡፡ ይህ ውይይትም ትውልደ ጣሊያን አንበሶቹ ለግዜው በፕሬዝዳንቱ ቤ/መንግስት ይቀመጡ የሚል ውሳኔ ሀሳብ እንዲመነጭ አስቻለ ፡፡

ቤተ መንግስቱ ግን የተሻለና የመጨረሻ አማራጭ ባለመሆኑ ዘለቄታዊ ማረፊያ ወደሆነው የእንስሳት ኮቴ በህዳር 2011 እንዲጓዙ ተደረገ ፡፡

አንድርያና ጃኑ እንደ ሜጀርና ጄኔራል የመቅበጥበጥም ሆነ እረ ጎራው የማለት ባህሪ አይታይባቸውም ፡፡ ምናልባት እንደ ጌቶቻቸው አድፋጭነት ተጋብቶባቸው ይሆናል ፡፡ ምናልባት ጸብ አጫሪነት ፋይዳ ቢስ መሆኑን በመረዳት በነጭ ባንዲራ ስር ለመኖር ቆርጠው ይሆናል ፡፡ ምናልባትም መወለድ ቋንቋ ነው እንዲሉ ላደጉበት ሀገር ሰላምና ፍቅር በመመኘት ቋሚ ‹ አርምሞ › ውስጥ ገብተው ይሆናል ፡፡ ምናልባትም በቅርቡ  ይፋ የሆነውን ሰበር ዜና አስቀድመው ስለሚያውቁት በራስ የመተማመን ስሜታቸው ተሰብሮ ይሆናል ፡፡

የቅርቡ ዜና  የኢትዮጽያ አንበሶች ዝርያ ከመላው አፍሪካ አንበሶች ይለያል የሚል ነው ፡፡ ከ 20 አንበሶች ውስጥ የዲ ኤን ኤ ምርመራ የተደረገላቸው 15ቱ ልዩነት ማሳየታቸው ታውቋል ፡፡ ይህ ማለት እንግዲህ አንበሳ ‹ አንበሳ › ከሚለው አስፈሪና ሞገሳም ዝናው በተጨማሪ ‹‹ በኢትዮጽያ ብቻ የሚገኝ ! ›› የሚለው ማዕረግ በሰዎች ክብር ሊጨመርለት ነው ማለት ነው ፡፡ ለነገሩ ነገሩ ቀድሞ የተገለጠላቸው የሚመስሉት አንዳንድ የሀገራችን መሪዎች ለአንበሳ የሚገርም ፍቅርና አክብሮት ነበራቸው ፡፡ አጼ ቴዎድሮስ መቅደላ ተራራ ላይ በአንበሳ ተከበው ይውሉ ነበር ፡፡ ንጉስ ሃይለስላሴ አንበሳ እያረቡ መሳጭ ወዳጅነት መፍጠር ችለዋል ፡፡ የሀገራችን አርበኞች በህቡዕ ሲደራጁ ስማቸውን  ‹ የጥቁር አንበሳ አርበኞች እንቅስቃሴ › ማለት ነው የወደዱት ፡፡ አንበሳ ብቻ አይደለም - ጥቁር አንበሳ ፡፡  አንበሳ ወደ ዳለቻና ቡኒ ቀለም መጠጋቱ እየታወቀ በሀገራችን ብዙ ነገሮች ‹ ጥቁር አንበሳ › የሚል ስያሜ እንዴት ሊያገኙ ቻሉ ? የሚሉትን ጥያቄዎች ጆሮውን መጠምዘዝ ከተፈቀደ ቀደም ያሉትን አባቶቻችንን ምናባዊ ዕውቀት ልናድቅ ግድ ይለናል ፡፡ የመገለጥ ብቃት ፡፡

ርዕሰ ዜናውን አንድ ግዜ ላስታውስና ልቀጥል ፡፡ ይህ ማለት እንግዲህ አንበሳ ‹ አንበሳ › ከሚለው አስፈሪና ሞገሳም ዝናው በተጨማሪ ‹‹ በኢትዮጽያ ብቻ የሚገኝ ! ›› የሚለው ማዕረግ በሰዎች ክብር ሊጨመርለት ነው ማለት ነው ፡፡ በሌላ አነጋገር ዶሎ ፣ ሶፍያ ፣ ሜጀርና ጄኔራል እንደ ሳሞራ የኑስ ብቸኛውን ማዕረግ ትከሻቸው ላይ ሊጭኑ ነው  - ሙሉ ጄኔራል ወይም ልዩና ብርቅዬ አንበሳ ፡፡ አንድርያና ጃኑ ደግሞ ባለ ሌላ ማዕረግተኛ  - ወይም ተራው አንበሳ ፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጽያዊ ደም ስለሌላቸው ሳይንሳዊው እርከን አይመለከታቸውም ፡፡ ይህ ኮምፕሌክስ በጫካው ሰፈር አይኖርም ለማለት ማረጋገጫ አይኖርም ፡፡ 
ተመራማሪዋቹ በነካ እጃቸው ይህ ኮምፕሌክስ እየቆየ ሲሄድ ‹ አንበሳዊ ፍርሃት › ይፈጥራል የሚል ጥናት ያሰሙን ይሆናል ፡፡

ለማንኛውም  ተሷሚዎቹንም ሆነ ባለ ሌላ ማዕረግተኞቹን  ወላጅ አልባ አንበሶች በእንሰሳት ኮቴ ተገኝቶ መጎብኘት ስለሚቻል አንድ እሁድ ጎራ ብለው ይዝናኑ ፡፡

ማስታወሻ፡ይህ ፅሑፍ በቁም ነገር መፅሔት ቅፅ 12 ቁጥር 149 ላይ የወጣ ፅሑፍ ነው፡፡ ፅሑፉን በሌላ ሚዲያ ላይ የምትጠቀሙ ከሆነ ምንጩን እንድትጠቅሱ ትለመናላችሁ፡፡