አንድ ድረ ገጽ ውስጥ ገብተን ስለ
ኢትዮጽያ መረጃ ብንጠይቅ ቢያንስ የህዝብ ብዛት ፣ መልከዓምድር ፣ ቋንቋ ፣ ባህል ፣ ሃይማኖት ፣ የመንግስት ስሪትና ገጽታውን
የተመለከቱ ምላሾች ልናገኝ እንችላለን ፡፡ አንድ ኢትዮጽያዊ ምን ይመስላል ? ተክለቁመናው… እምነቱ… ፍልስፍናው…
ሀገራዊ ስሜቱ … እውቀቱ … የሚጠላውና የሚደሰትበት ? እነዚህን ለመሳሰሉት ጥያቄዎች ግን የተዘረዘረ መልስ የሚሰጠን
ድረ ገጽም ሆነ ተቋም አናገኝም ፡፡
በአስር ዓመት ቆጠራ የሚያካሄደው
የማዕከላዊ ስታቲክስ ኤጀንሲም ዝርዝር ኪስ ይቀዳል በሚል እሳቤ ነው መሰለኝ መረጃውን እስከታች ተንትኖ ማስቀመጥ አለመደበትም
ይህ ጥያቄ ባደጉትም ሆነ እያደጉ
በሚገኙት ሀገሮች በቂ ምላሽ እያገኘ መጥቷል ፡፡ ለአብነት ‹ አሜሪካኖች ምን ይመስላሉ ? › ብሎ የሚጠይቅ
ግለሰብም ሆነ ሀገር የተጃመለ ሳይሆን የተዘረዘረ መረጃ በቀላሉ ያገኛል ‹‹ የአሜሪካ ወንድ ቁመቱ በአማካኝ
አምስት ጫማ ከዘጠኝ ኢንች ሲሆን 180 ፓውንድ ይመዝናል ፡፡ ደረቱ 41 ኢንች ፣ ወገቡ 35 ዳሌው 40.5 ኢንች ይደርሳል
፡፡ 90 ከመቶው ያህል ያጨሳል ፡፡ አብዛኛው መልበስ የሚወደው ጂንስ ሱሪና ቲሸርት ነው ፡፡ ብልቱ ሲቆም ስድስት ኢንች
ይደርሳል ፡፡ ወጪ የማይጠየቅ ከሆነና ተግባሩ የማይጎዳው ከሆነ ከአምስቱ ሶስት ያህሉ ብልታቸውንን ማስረዘም ይፈልጋሉ ፡፡ 78
ከመቶ ያህሉ ብልቱን የተገረዘ ሲሆን ዕድሜው 78 ይጠጋል ፡፡ በአናቱ ላይ መቶ ሺህ የሚደርሱ ጸጉሮች ሲኖሩት ከዚህ ውስጥ
በቀን ከሃያ እስከ መቶ ያህሉን ያጣል ›› ወዘተ እያለ ይተነትናል መረጃው ፡፡
ለመሆኑ የጋብቻና ፍቺው ቀመር
ጤነኛ ነው ? ሳቅና ለቅሶው ? ሀገራዊ ስሜቱ የተለየ ነው ? መጠጥ ላይ እዛው ያነጋል ? ከፈጣሪ ጋር ይገናኝ ይሆን ?
እነዚህና መሰል ስብዕና ተኮር ጥያቄዎች ብትወረውሩ አታፍሩም ፡፡ በጉዳዩ ላይ ድረ ገጾቹ የሚሉት እንደተጠበቀ ሆኖ ለማጣቀሻ
የሚበቁ መጻህፍትም ይገኛሉ ፡፡ በዚህ ረገድ የደራሲ በርኒስ ካነር ‹‹ When it comes to guys what is
normal ? ›› የሚለው መጽሀፍ አንጀት ያርሳል ፡፡
የእውነት አሜሪካዊያን ምን
ይመስላሉ ? ለየት ያሉ ገጽታቸውን ከመረጃው እየቆነጠርኩ ‹ እነዚሁ › እላለሁ ፤ የኛ ማንነት በዚህ ረገድ
የማይታወቅ ቢሆንም ለተሳትፎ ያህል ሸራፋ መረጃንና ያማረ ግምትን በማደባለቅ ‹ እንዲህ ነን › እያልኩ እገልጻለሁ ፡፡ ፎርፌ
ጥሩ ስላልሆነ ።
ሳቅና ለቅሶ ፤
/ አሜሪካ / የአሜሪካ ሰው በቀን 15 ግዜ ሲስቅ በወር
የሚያለቅሰው ለአንድ ወይም ሁለት ግዜ ነው ፡፡
/ኢትዮጽያ/ ኢትዮጽያዊው
ሰው በቀን አንድ ግዜ እንደምንም ሲስቅ አስር ግዜ ፊቱ ይለዋወጣል ፡፡ ከዚህ ውስጥ ሁለት ግዜ በተለያዩ አናዳጅ ነገሮች
ደምስሮቹ ይቆማሉ ፡፡ ሁለት ግዜ በማያውቀው ምክንያት ለንቦጩ ተዘርግፎ ከአንዳንድ ሰብዓዊነት ከሚሰማቸው ግለሰቦች ወይም
ድርጅቶች ‹ እባክህ ሰብስበው ! › የሚል ቀና ምክር ይለገሰዋል ፡፡ ሁለት ግዜ መጣሁ ቀረሁ በሚል የእንባ ዝናብ
ፊቱ ይዳምናል ፡፡ ሁለት ግዜ በጣም የሚወደውን ‹ እንኳን እናቴ ሞታ እንደውም አልቅስ አልቅስ ይለኛል › የተባለውን ጥቅስ
እየተደገፈ እዬዬውን ያስነካዋል ፤ ሰበበ ምክንያቱ ሲፈተሸ ለቅሶ ሲሰማ … ሰው በግፍ ሲታሰር … የእህል ዋጋና የቤት
ኪራይ ሲጨምር … አለኝ የሚለው ወዳጅና ዘመድ ሲከዳው … ሆኖ ይገኛል ፡፡ ቀሪዋን ሁለት በቁጠባ የሚይዛት ይመስላል ፡፡
ጠላትን ለምን ደስ ይበለው እያለ እንደምንም ጨክኖ እንባውን አደባባይ ሳያወጣ ወደ ውስጥ ያለቅሳል ፡፡
ወሲብ ፤
/አሜሪካ / 14.3
የሚደርሰው የወሲብ ተጋሪ አያጣም ፡፡ ድንግልናቸውን የሚያስረክቡት በ16 ዓመታቸው ነው ፡፡ ከሌላ ሰው ጋር ያላቸውን ውጫዊ
ግንኙነት በፍጹም አያምኑም ፡፡ በዓመት ለ135 ግዜ ወሲብ የሚፈጽም ሲሆን ከ 120 እስከ 600 ሚሊዮን የሚደርሱ ስፐርሞች
ይረጫሉ ፡፡ ከነዚህ ውስጥ 400 ያህሉ ብቻ ናቸው እንቁላሉን የሚያገኙት ፡፡ 54 ከመቶ ያህሉ በቀን አንድ ግዜ ስለ ወሲብ
ያስባሉ ፡፡ ቢጠቀሙም ባይጠቀሙም ከሶስቱ ሰዋች ሁለቱ ኮንዶሞችን አልጋቸው ስር ማስቀመጥ አይረሱም ፡፡
·
/ኢትዮጽያ/ 40 ከመቶ
የሚደርሰው የወሲብ ተጣማሪ አለው ፡፡ 20 ከመቶው ጥሮ ግሮ የገነባው ሲሆን ቀሪው 20 ከመቶ የወንዱን እግር መራቅ ተከትሎ
የሚያንጎዳጉድ ነው ፡፡ ሴቶቹ ድንግላቸውን በ 10 ዓመት ሲነጠቁ ፤ ወንዶቹ በ 15 ዓመታቸው ድንግልና ፍለጋ ይራወጣሉ ፡፡
በዓመት ለ 265 ግዜ ወሲብ የሚፈጽም ሲሆን ድርጊቱ ሲከፋፈል 35 ከመቶ በሃሳብና ወጪ ወራጁን በማየት ፣ 35 ከመቶ እጆቹ
ብልቱ ላይ እንዲያንኮራፉ በማድረግ 35 በመቶ ደግሞ በተግባር ነው ፡፡ ከ 10 እስከ 20 ሚሊዮን የሚደርሱ ስፐርሞች ይረጫሉ
፡፡ ተግባሩ በዝቶ ፈሳሹ ያነሰው ከምግብ እጥረትና ከድርቀት መከሰት ነው ፡፡ እንደዛም ሆኖ 90 ከመቶ ያህሉ እንቁላሉን
አግኝተው ልጅ መፍጠር ይችላሉ ፡፡ ልጆቹ ግን ሶስት ወር ሳይሞላቸው ተጨናግፈው በየገንዳው ይጣላሉ ፡፡ 70 ከመቶ ያህሉ በቀን
ሶስት ግዜ ስለ ወሲብ ያስባሉ ፡፡ ከቁርስ ፣ ምሳና ራት በኃላ ማለት ነው ፡፡ 5 ከመቶው አራት ግዜ ያደርሱታል ፡፡ ይህ
የሆነውም መክሰስ ስለሚጠቀሙ ነው ፡፡
ሞትና መንስኤው ፤
/አሜሪካ /
ከ45 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዋች ከዘጠኝ አንዱ በሳምባ ካንሰር ይሞታል ፡፡ 5.6 ከመቶ ያህሉ በስትሮክ ፣ 3.7 ያህሉ
በኒሞኒያ ፣ 2 .8 ያህሉ በዲያቤት ይጠቃል ፡፡ ወንዶቹ ብዙውን ግዜ የሚሞቱት ራስን በማጥፋት ፣ በጉበት ፣ በአደጋ ፣
በወንጀል ድርጊቶች ነው ፡፡
·
/ኢትዮጽያ/ አብዛኛው
ህዝብ የሚያልቀው ንዳድ እያለ በሚጠራው ወባ ነው ፡፡ አሳምሮ መዳን ይቻላል በሚባልለት ቲቢም አስጠሊታ ሆኖ ማለፍ ተለምዷል
፡፡ የውሃ ሃብታም ቢሆንም ውሃ ጠላት እንጂ ወዳጅ ሆኖት አያውቅም ፡፡ በአጠቃቀም ጉድለት በውሃ ወለድ በሽታ ይወድቃል
… በአጠቃቀም ፍርሃት በሃይጂን ጦስ ይቀሰፋል … በአስጠቃሚ ማጣት በረሃብ ይረግፋል … ሲንቀዠቀዥ መኪና ይበላዋል ፤
ባይንቀዠቀዥም መኪና ቤቱ ድረስ መጥቶ ይገድለዋል ፡፡
ሀገራዊ ስሜት ፤
/አሜሪካ / አብዛኛዋቹ
በአርበኝነት ስሜታቸው ይኮራሉ ፡፡ 90 ከመቶ ያህሉ ሀገሩ ትክክል ሰራችም አልሰራችም በክፉ ግዜ ከመደገፍ ወደ ኃላ አይልም
፡፡ 72 ከመቶው የአሜሪካ ባንዲራ መኪናቸው ላይ እንዲውለበለብ ይፈልጋሉ ፡፡ ከመከላከያ ሰራዊት ይልቅ ለአየር ኃይልና ባህር
ኃይል የተለየ ግምት አላቸው ፡፡
·
/ኢትዮጽያ/ አብዛኛዋቹ በአሁኑ ሳይሆን ባለፈው የሀገሪቱ ታሪክ የበለጠ ይኮራሉ ፡፡ 80 ከመቶ
ያህሉ ሀገራቸውን በክፉ ቀን ለመርዳት የሚፈልጉት ዘመቻው ወደ ሰሜን ከሆነ ብቻ ነው ፡፡ 40 ከመቶ የሚደርሰው የሀገሪቱ
ባንዲራ እንዲውለበለብ የሚፈልገው ያለምንም ቅጥያ ነው ፡፡ 40 ከመቶው መሃሉ ውስጥ ኮኮብ እንዲኖር ሲፈልግ 20 ከመቶው
ከአንበሳው ጋር ቢያየው ይፈልጋል ፡፡ ከቤተ መንግስት መኪናዎች ውጪ ባለመኪናውም ሆነ ሹፌሩ ባንዲራውን መኪናው ላይ ማውለብለብ
የሚፈልገው በዓመት አንድ ግዜ በባንዲራ ቀን ብቻ ነው ፤ በአራት አመት አንድ ግዜ ደግሞ የኦሎምፒክ ጀግኖችን
ለመቀበል ፡፡ አብዛኛው ሰው ጦሩ ሲታስብ ለጠፋው ባህር ኃይል ከፍተኛ ግምት አለው ፡፡ አንዳንዶች እንደውም
‹‹ የባህር ኃይላችን መልህቅ
የጣለበት
የጠቅል አሽከሮች በፓሪስ
በኒውዮርክ የተሟገቱለት
የአሉላ ፈረሶች ውሃ የጠጡበት
የት አለ ባህሩ የተማማንልበት ››
በማለት ያስቡታል - ታዲያ በሆዳቸው ነው ፡፡
ችግር በመጣ ቁጥር ያለምንም ርህራሄ በሚደበድበው ፣ ያለ ጥያቄ በሚያፍሰውና በሚያስረው ፌዴራል ምክንያት
ብዙዎቹ ለፓሊስ ያላቸው እምነት የጎመዘዘ ነው ፡፡ በምርጫ ማግስት በተፈጠረ ብጥብጥ የአንዳንዶችን ግንባር የኢላማ ተኩስ ሰሌዳ
ባደረገው የአጋዚ ጦር ሰበብ ለምድር ኃይሉ ያለው አመለካከትም የጠራ አይደለም ፡፡ በንጽጽር በርካታ ሰዋች ለአየር ኃይሉ
የተሻለ ድጋፍ ያላቸው ይመስላል ፡፡
በስራ ላይ ፤
/አሜሪካ / ከአምስት
ሰዋች አንዱ ስራ እየሰራ ያፏጫል ፣ ይዘፍናል ፣ ያንጎራጉራል ፡፡
·
/ኢትዮጽያ/ ከ30 ሰዋች
አንዱ ስራ እየሰራ ያፏጫል ፡፡ ከአስር ሰዋች አራቱ ከመዝፈን ይልቅ ያንጎራጉራሉ ፡፡ የእንጉርጉሮው አውድ ግን እንደቦታውና
ሁኔታው የተለያየ ነው ፡፡ የፍቅር ቁስል ወይም እንከን ያለበት የትዝታ ዘሮችን በመሳብ ለምሳሌ የጸጋዬ እሸቱን
‹ የትዝታን ዜማ እንዴት
ላንጎራጉረው
እምባ እየቀደመኝ ገና
ስጀምረው
ወይ አንጎራጉሬው ዘፍኜ አይወጣልኝ
ስምሽ ነው አፌ ላይ ቀድሞ
የሚመጣልኝ › ማለት ይመርጣል ፡፡
ጸጸት ሸንቆጥ ያደረገው የመንግስት ሰራተኛ ደግሞ
‹ እደግ እደግ ብለን ያሳደግነው
ቀጋ
ይላል ጎንበስ ቀና እኛኑ ሊወጋ !
› በማለት ትዝብቱን ለኮስ ያደርጋል ፡፡ የሙስናው ፣ የወንጀሉ ፣ ጤና ያጣው የፓለቲካ ሹክቻ ያስፈራው ቀና ሰው ደግሞ
‹ እባክህ አምላኬ ንፋሱን መልሰው
ወንድሙን ወንድሙ ሸጦ ሳይጨርሰው
› እያለ ነው ፡፡
መጠጥ ፤
/አሜሪካ / 2.3 ከመቶ የሚደርሰው ህዝብ በየቀኑ ቢራ ይጠጣል ፡፡ 18
ከመቶው በየቀኑ የሚጠጣው አልኮል ሲሆን 45 ከመቶው ምርጫው ወይን ነው ፡፡ 14 ከመቶው መጠጥ ሲቀማምስ ከአቅሙ በላይ
እንደሆነ ያምናል ፡፡ 31 ከመቶው ህዝብ መጠጥ ለቤተሰብ ብጥብጥና መፍረስ ትልቅ ምክንያት እንደሆነ ያምናል ፡፡
·
/ኢትዮጽያ/ 40 ከመቶ የሚደርሰው በየቀኑ ጠላ ፣ ጠጅና ካቲካላ ይጠጣል ፡፡ ከዚህ ውስጥ 30
ከመቶው ያህል መጠጡ አንድም የኑሮን ሸክም እንደሚያረሳሳ በሌላ በኩል ወይ ፈንካች አሊያም ተፈንካች እንደሚያደርጋቸው ያውቃሉ
፡፡ 10 ከመቶው ድራፍትና ቢራ በጣም አልፎ አልፎ ከጥሬ ስጋ የሚቀማምስ ሲሆን 4 ከመቶ የሚደርሱት ሀብታሞችና የሀገር ሌቦች
ካለ ውስኪ አንነካም የሚሉ ናቸው ፡፡
ብቸኝነት ፤
/አሜሪካ / 13 ከመቶ ያህሉ ብቻውን የሚኖረው የኑሮ ተጋሪውን ሞት ነጥቆበት ሲሆን 38 ከመቶ
የሚደርሰው ብቸኛ ግን ምክንያቱ ፍቺ ነው ፡፡ ብቻቸውን ከሚኖሩት ውስጥ 46 ከመቶ ያህሉ በድጋሚ አላገቡም ፡፡
/ኢትዮጽያ/ 40 ከመቶ የሚደርሰው ጎረምሳና ጎልማሳ ብቻውን የሚኖረው በስጋትና በፍርሃት
ምክንያት ነው ፡፡ የድህነቱን ቋጥኝ መሸከም ስለማይችል የሚፈልገውን ትዳር መመስረት አይፈልግም ፡፡ ወልዶ መሳም የተፈጥሮ
መፈክር ቢሆንም የልጅ ፍላጎቱን የሚወጣው የልጆች ፕሮግራምን ደጋግሞ በማየት ነው ፡፡ 20 ከመቶ ያህሉ ተበድሮ ካስጨፈረው
ሰርግ ማግስት የኑሮ ውሉን የቀደደው በጭቅጭቅ ነው ፡፡
ጸሎት ፤
/አሜሪካ / 59 ከመቶ የሚደርሰው ወንድ በየግዜው ይጸልያል ፡፡ ከዚህ ውስጥ
62 ከመቶው የጸሎቱ ምክንያታቸው ድጋፍና ርዳታ ለማግኘት ነው ፡፡ 54 ከመቶው ፈጣሪን ለማመስገን ፣ 47 ከመቶው ይቅርታ
ለመጠየቅ ይጠቀማሉ ፡፡ በጣም የሚገርመው ሃይማኖት የሌላቸው 14 ከመቶ የሚደርሱ ሰዋች በየቀኑ የመጸለያቸው ጉዳይ ነው ፡፡
·
/ኢትዮጽያ/ 60 ከመቶ የሚደርሰው ህዝብ እንደየሃይማኖቱ ይጸልያል ፡፡ ከዚህ ውስጥ
አንድ ሶስተኛው በልቡ ትልቅ የማመልከቻ ዶሴ ይዞ ይጓዛል ፡፡ የተወሰነው የተቀናቃኙ እግር ቄጤማ ፣ አይኑ ደግሞ ጨለማ
እንዲሆን ፈላጊ ነው ፡፡ ለዚህም ስራ ማሰፈጸሚያ ይሁን መደለያ የማይሳለውና ቃል የማይገባው ነገር የለም ፡፡ ሌላው የሰማውን
ሂስና ግለሂስ እንዳለ ኮፒ በማድረግ ለመተግበር ወደ ኃላ የማይለው ነው ‹‹ እስኪ እንጠያየቅ አሁን አታዳለም ?!
... እውነት ፍትህ ትሰጣለህ ? አንዱ ቂጣ እያረረበት ሌላው በውስኪ እንዲታጠብ ታደርጋለህ … አንዱን ኗሪ ሌላውን
አኗኗሪ የምታደርገው በምን ሂሳብ ይሆን ? ቤት አጥቶ በየሜዳው የሚተኛው በፓሊስ እየተባረረ ቪላ አማራጩ ደግሞ
በፓሊስ ይጠበቃል ? እውነት የአንተ ‹ ላለው ይጨመራል › ብሂል መነሻው ምንድነው ? ›› ይለዋል አምላኩን
፡፡ መቼም ፈጣሪ ወፈ ሰማይ ‹ ካድሬዋች › ቢኖሩት ኖሮ ደፍሮ ላይናገር ይችላል ፡፡ ቀሪው አንድ ሶስተኛ ስቅስቅ ብሎ
የሚያለቅሰው ‹ ምነው የእለት እንጀራ ነፈከኝ … ምነው የሰው እጅ አሳየኀኝ … ምነው የውሃ አጣጭዮን እንደ ቶምቦላ እጣ ብርቅ
አደረከው ? › እያለ ሳይሆን አይቀርም ፡፡
የእረፍት ግዜ ፤
/አሜሪካ / የአብዛኛው ወንድ እረፍት ግዜ አምስት ሰዓት አካባቢ ሲሆን ከዚህ
ወስጥ ግማሽ ያህሉን ቴሌቪዥን በማየት ፣ ሃያ ደቂቃ ራሱን ለማዝናናትና ለማሰብ ፣ 50 ደቂቃውን ከቤተሰቡ ጋር ለማሳለፍ
ያውለዋል ፡፡ 19 ከመቶ የሚደርሱት ብቻ የቤት ውስጥ ልዩ ልዩ ስራዋች የሚሰሩ ሲሆን 34 ከመቶ ያህሉ ደግሞ ምግብ ለማብሰልና
በጽዳት ላይ እንደሚሳተፉ ይናገራሉ ፡፡
·
/ኢትዮጽያ/ የመንግስት ሰራተኛ እረፍት ዘጠኝ ሰዓታት ያህል ነው ፡፡ ቢሮ
ከሚያሳልፈው ስምንት ሰዓታት ውስጥ አምስቱን የሚያሳልፈው ጓደኛውን ፣ አለቃውንና ስርዓቱን በመቦጨቅ… ቻት በማድረግና የስራ
ማስታወቂያ በመፈለግ … እንደ ሀገር ውስጥ ቱሪስት የተለያዩ መምሪያ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን በመጎብኘትና በማድነቅ … በትልቅ
በትንሹ የሚታደምባቸውን አራት ነጥብ ፈሪ ስብሰባዎች በአክዋ አዲስና ማኪያቶ እየተጉመጠመጠ በመዋጥ ነው ፡፡ ከስራ በኃላ
ቅዳሜና እሁድ የሚገኙ እረፍቶች ነጻነት የበዛባቸው በመሆኑ ቄንጠኛ እረፍቶች ናቸው ማለት ይቻላል ፡፡ እጆቹ ለስላሳ የሴት
ገላም ሆነ ሰፊ የወንድ ደረት ፣ የጫት እንጨትም ይሁን የድራፍት ብርጭቆዎችን ባማለለ መልኩ መጨበጥ ይችሉበታል ፡፡ እነዚህን
የቀመሱ አፎች ደግሞ በተዓምር ለዝምታ እጅ አይሰጡም ፡፡ እግር ኳሱ … የአረብ አብዮቱ … የሴት ውበቱ … የወንድ ልጅ ሀሞቱ
… የምርጫችን ትርዒቱና ትዕቢቱ … እንደየአመጣጡ ይሸነሸናል ፡፡ ከዚያ አየር ላይ ክብ እየሰሩ የሚታዩ ገጣጣ ፣ ጠፍጣፋና
ወልጋዳ ሳቆች እኢዲሁም ቁጭቶች ይከተላሉ ፡፡
ትምህርት፤
/አሜሪካ / 84 ከመቶ የሚደርሰው ዜገኛ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የጨረሰ ሲሆን የኮሌጅ ዲግሪ
ያለው 28 ከመቶው ነው ፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው በዓመት የ66ሺህ 810 ዶላር ተከፋይ ሲሆን ባለዲፕሎማው 30 ሺህ 414
ዶላር ያገኛል ፡፡
·
/ኢትዮጽያ/ 43 ከመቶ የሚደርሰው ህዝብ የማንበብና መጻፍ ችግር የለበትም ፡፡ ከኮሌጅ
በዲፕሎማ የተመረቀ ሰው ደመወዙ መጠነኛ ቤት ለመከራየት ትንሽ ይጎድለዋል ፡፡ በዲግሪ የተመረቀ ሰው ደመወዙ ለክፉ የማይሰጥ
ቤት ሊያከራየው ይችላል ፡፡ በፈለገው ተዓምራዊ የሂሳብ ቀመር ከሽርፍራፊ እህል አልፎ ወደ ስራ ለሚመላለስበት መጓጓዣ
ስለማይተርፈው ቆራጥ እግረኛ መሆን ይጠበቅበታል ፡፡ በሌሊት እየተነሳ ‹ ልወዝወዘው በእግሬ › የሚለውን ዜማ እንዲያቀነቅን
ተፈርዶበታል ፡፡ በማስትሬት የተመረቀ ሰው ባለ ሰፊ ምኞት ቢሆንም የምኞቱን ለሃጭ ከማንጠባጠብ ማገድ አይችልም ፡፡ ለምሳሌ
ከክብሩ አንጻር ቢያንስ ቢያንስ ጥሬ ስጋንና ቢራን መጎንጨት ይኖርበታል ፡፡ ግና ልቡ እንጂ ኪሱ ባዶ በመሆኑ በስጋ ቤት ደጃፍ
የሚያልፈው ሶስቱን የ ‹‹ ማ ›› ህጎች በመዘመር ነው ፡፡ ማየት… ማድነቅ… ማለፍ…