Tuesday, April 1, 2014

ግብረሶዶማዊነት በሁለቱ ታዋቂ ጻጻሳት ልቦና


የተመሳሳይ  ታ ጋብቻ ህጋዊ የሆነበትን ቀን ተንተርሶ እንግሊዝ ሰሞኑን በግብረሰዶማዊያን ሰርግ ፈንጠዚያ ላይ ነበረች ። በስነስርዓቱ ላይ የተገኙት ዴቪድ ካሜሮን ጥምረቱን « ታሪካዊ » ሲሉ አወድሰውታል ። በምድረ እንግሊዝ ይህን መሰሉ ጥምረት በ2004 የተጀመረ ቢሆንም ወደ ህጋዊ ጋብቻነት የተቀየረው አሁን ነው ።
ይህ ጋብቻ እውን የሆነው የካቶሊኩ ሊቀጻጻስ ፍራንሲስ ታዋቂ አምስት ቃላቶች « ውዳሴ » ገና ባልከሰመበት ወቅት ነው « WHO AM I TO JUDGE » ይላሉ ጆርጅ ማሪዮ በርጎሊዬ - ለመፍረድ እኔ ማነኝ ? እንደማለት ።
ከዛሬ 24 ዓመታት በፊት ናዚር ጋይድ ሩፋኤል በበኩላቸው በእንግሊዝ ተገኝተው የግብረሶዶማዊነትን ኀጢያታዊ ተግባርና የወደፊት አደገኛነት ለታዋቂ ሰዎችና ምዕመናን ትምህርት እየሰጡ ነበር « HOMOSEXUALITY IS AGAINST NATURE » በማለት - ግብረሶዶማዊነት ተፈጥሮን ይቃረናል እንደማለት ። ይህን አባባል ግን ጋዜጠኞች ታዋቂው ባለአራት ቃላቶች በማለት አላወደሱትም ። ደግነቱ ሊቀጻጻስ ሺኖዳ ዛሬ በህይወት ስለሌሉ በዚህ ዜና አያዝኑም ።
እነዚህ ሁለት ጻጻሳት በትህትናቸውና አንቱ በሚያሰኝ ስራዎቻቸው ይመሳሰላሉ ።
ጻጻስ ፍራንሲስ የአርጀንቲና ሊቀ ጻጻስ በነበሩት ግዜ የተለየ ጥቅማጥቅም አያስፈልገኝም በማለት ተራ አፓርታማ ላይ ክፍሎች ተከራይተው ምግባቸውን ራሳቸው እያበሰሉ ፣ ህዝብን መስለው በአውቶብስ እየተጋፉ ነበር የሚጔጔዙት ። የካቶሊክ ሊቀጻጻስ ሆነው ሲሾሙም ቤተመንግስት ከመግባት ይልቅ የቫቲካን ሰራተኞች በሚኖሩበት ህንጻ ላይ መኖርን መርጠዋል ። ለሳቸው ይወጣ የነበረውን የትየለሌ ገንዘብ ለሰብዓዊ ርዳታ እያዋሉ ይገኛሉ ።
ጻጻስ ሽኖዳ የግብጽን በረሃ በመምረጥ የምንኩስና ህይወትን ለብዙ አመታት አጣጥመዋል ። ከግብጽ ውጭ ገዳማትንና መንፈሳዊ ኮሌጆችን በማሰፋፋት መንፈሳዊ እውቀት እንዲጎለበትና ቁጥሩ እንዲጨምር ልዩ ሚና ተጫውተዋል ። ኢል ከራዛ የተባለ ሃይማኖታዊ መጽሄት በማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን ከሰፊው ዕውቀታቸው በመጨለፍ 101 የሚደርሱ መጽሃፍትን ለንባብ አብቅተዋል ። ስራዎቹም በልዩ ልዩ ቌንቌዎች ተተርጉመዋል ።
እነዚህ ሁለት ጻጻሳት ከክርስትና ባህር የተቀዱ ቢሆንም ዛሬ አለምን በስፋት እያነጋገረ በሚገኘው ግብረሶዶማዊነት ዙሪያ ያላቸው አመለካከት በፍጹም አይገናኝም ።
ለምን ?
አይታወቅም ።
አንድ መሆን ይጠበቅበት ነበር ?
ቢያንስ በጣም መራራቃቸው እንዴት ? የሚል ጥያቄ እንዲወለድ ምክንያት ይሆናል ።
የአሌክሳንደሪያው ጻጻስ ሽኖዳ ግብረሶዶማዊነት ከተፈጥሮና ከመጽሀፍ ቅዱስ ቃል የሚቃረን በመሆኑ ሃጢያት መሆኑንና አባላቱ መንግስተ ሰማያት እንደማይገቡ ያስረዳሉ ። የካቶሊኩ ጻጻስ ፍራንሲስ የቤተክርስቲያኒቱን መመሪያ በመንተራስ ግብረሶዶማዊነትን በሁለት ከፍለው ነው ሀሳብ የሚሰጡት ። የግብረሶዶማዊነት ዝንባሌ ያለው እንደሃጢያተኛ አይቆጠርም ። ግብረሶዶማዊ ተግባርን የሚፈጽም ግን ሃጢያተኛ ነው ። < ዝንባሌ > የሚለው ቃል እንዴት ሊፈጠር ቻለ ? በግርድፉም ደጋፊነትንና አድናቂነትን ይገልጻል ። የድጋፉ መነሻስ ከምንም ተነስቶ ነው ማለት ይቻላል ? ምናልባት ይህ ደጋፊ ነገ ተጨዋች ለመሆን በእጅጉ የቀረበ ይመስላል ። መገመት የማይቻለው አሰላለፉን ነው - ተመላላሽ አጥቂ ነው ወይስ ቌሚ ተከላካይ ? ወይም እንደ ሚስት ነው የሚተውን እንደ ባል እንደማለት ።
ቅጣቱን በተመለከተም የጻጻሳቱ አመለካከት እንደሰሜንና ደቡብ ዋልታ ጫፎች የተራራቀ ነው ። ሺኖዳ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን የተወገዘና ክፉ ውጤት የሚያስከትል መሆኑን ያስረዳሉ ። በኦሪት ዘሌላዊያን ምዕራፍ 20 ፡ 13 « አንድ ወንድ ከሌላው ወንድ ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት ቢፈጽም ሁለቱም አስከፊ ነገር ስላደረጉ በሞት ይቀጡ ። ስለመሞታቸውም ኃላፊነታቸው የራሳቸው ይሆናል » የሚለውን ለአብነት ጠቅሰዋል ።
የአዲስ ኪዳኖቹ
ወደ ሮም ሰዎች 1 ፡ 27
ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 6 ፡ 9
የይሁዳ መልዕክት 7 የግብረሶዶማዊነትን ቅጣትና የእግዚአብሄርን መንግስት አለመውረስ የሚያስረዱ ናቸው ።
ፍራንሲስ እነዚህን ጥቅሶች በመተው የተለየ ምላሽ መስጠትን መርጠዋል ። ታዋቂ የተባለውን who am i to judge ? በርግጥ እነዚህ ተሳቢ ቃላቶች ነገር ለማሳመር ተከርክመው ቀረቡ እንጂ ሪሞርኬው ከፊት አለ - እንዲህ ነው ያሉት « አንድ ግብረሶዶማዊ ፈጣሪን ከተቀበለና መልካም ስነምግባር ካለው እኔ ማነኝ እና ነው የምዳኘው ? » አንዳንዶች ይህን አባባል የተጠቀሙት ትህትናን ለማሳየት ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ ህገ መጽሀፉን ለመሸሽ ነው ብለዋቸዋል ።
እዚህ ጋ ፍጥነታችንን አቀዝቅዘን ከሀሳቦቹ  ጀርባ ሊሆን ስለሚችለው ጉዳይ የሆነ ነገር እንበል ። ሽኖዳ መጽሀፍ ቅዱስን ቃል በቃል ጠቅሰው ሞት ይገባል ነው ያሉት ። ኃላፊነቱም የሟቹ ነው ። ህግ ከውሃ የቀጠነ መሆኑ ቢታወቅም እንደዚህ አይነት ውሳኔዎች ወዳልተፈለገና የከፋ ጫፍ እንደሚያደርሱም ይታወቃል ። ምክንያቱም ስሜታዊነትን አቅፈዋልና ። ለአብነት ያህል ኡጋንዳ የጸረ ግብረሶዶማዊነት ህግን ባጸደቀች ማግስት በተነሳ አመጽ አንድ ግብረሶዶማዊ ተቃጥሎ እንዲሞት ተደርጔል ። መቼም የሶዶምና ገሞራ ሰዎችም በዚህ መልኩ ነው የተፈጁት ብለን የምንከራከር ከሆነ የጻጻስ ፍራንሲስ አምስት ቃላቶች ትክክል ናቸው ማለት ነው ። እኛ ማነንና ነው ህግን የተላለፈ ሰው በጣም በተጋነነና ለቀሪው ትምህርት ሳይሆን በሽታ ሊፈጥር በሚችል መልኩ በእሳት የምናቃጥለው ? ህግ በቀለኛ መሆኑ ይታወቃል ። የበቀሉን ጉማሬ ከኃላ ኪሱ የሚያወጣው ግን መጀመሪያ ገስጾና አስተምሮ ነው ። ሰው ሲሞት እንኴን አስከሬኑን የማቃጠል ባህል መቅረት አለበት በሚባልበት ዘመን ህይወት ያለውን ሰው እንደዳመራ በመለኮስ ሰብሰብ ብሎ ወደ ሰሜን ይወድቃል ወይስ ወደ ምዕራብ እያሉ መወራረድ እንዴት ያስደስታል ? ያሰቅቃል እንጂ ።

በሌላ በኩል ጻጻስ ፍራንሲስ እንደቀድሞው ጻጻስ ተጽዕኖው በዝቶባቸዋል አሊያም የሳይንሱን እውነታ እየሸራረፉም ቢሆን መቀበል ጀምረዋል ። እንደሚታወቀው ግብረሶዶማዊነት የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ሆኖ የመፈጠር ነው የሚሉ አንዳንድ ሳይንቲስቶች ጣጣውን የጄኔቲክና ሆርሞን ውጤት አድርገውታል ። ለዚህም ማሳያ ይሆን ዘንድ በክሮሞዞምስ ፣ አእምሮና ሆርሞኖች ላይ ጥናቶች አከናውነዋል ። ለአብነት ያህል 400 የሚደርሱ መንታ ልጆች ላይ የተደረገ ጥናት Xq28 የተባለውን ክሮሞዞም እንደሚጋሩት ያሳያል ። ይህን ክሮሞዞምስ ጥንድ ያልሆኑ ወንድሞች አይጋሩትም ወይም በጥቂቱ ነው የታየው ። በዚህም መሰረት አንዱ ልጅ ግብረሶዶማዊ ከሆነ ሌላኛው ጥንድ የመሆን እድሉ 50 ከመቶ ይደርሳል ። እነዚህና የመሳሰሉት ጥናቶች እውነት ይኖራቸው እንዴ የሚያሰኝ ጥያቄ እየፈጠረባቸው ይመስላል ።
ዛሬ አለምን ጉድ እያሰኘ የሚገኘው ግብረሶዶማዊነት ሳይሆን የግብረሶዶማዊያን የጋብቻ ጥያቄ ነው ። ምክንያቱም ጋብቻ የተባለውን አንጋፋና ህጋዊ ተቌም እየተጋፋ በመሆኑ ። አለም ተቀብሎት የኖረው የጋብቻ ብይን እድሜያቸው ለአቅመ አዳም / ሄዋን በደረሰና በፍቅር በተግባቡ አንድ ወንድና ሴት መካከል የሚደረገው ማህበራዊ ጥምረት ነው ። እነዚህ ጥምሮች ውለዱ ክበዱ የሚለውን የሰርግ ላይ ምርቃት ከአመት በኃላ ተግባራዊ ያደርጋሉ ። ፍሬና ፍቅር ማየት የሰው ልጆች ሁሉ ጸጋ ነውና ።
ዛሬ አንድ ተማሪ « ጋብቻ የሁለት ጺማም ሰዎች ቁርኝት ነው ፣ በፍቅር ለመደንገጥና ለመሳሳብም አጔጊ ዳሌ ፣ እንቡጥ ከንፈር ፣ የተቀሰሩ ጡቶች ፣ ገዳይ አይን ፣ አመለሸጋነትም ሆነ የጎን አካልነት ምክንያት ሊሆኑ አይችሉም ። በግብረስጋ ለመርካት የግድ ወርቃማ ምንተሃፍረቶች አያስፈልጉንም - ማንኛውም ቀዳዳ እንጂ » የሚል መመረቂያ ጽሁፍ ቢሰራ ማነው ትክክል አይደለም የሚለው ? ጋብቻ በትርጉም ብቻ ሳይሆን ቀጥሎ በሚመጣው ቤተሰባዊ ተቌምነቱም እየተኮማተረ ነው ። ህንጻው ውስጥ ከወጉ ፣ ከእምነትና ስርዓቱ ፣ ከባህሉና ከአኗኗር ዘይቤው ጋር የማይመሳሰል ምናልባትም የሚቃረን ደባል ሰተት ብሎ ገብቷል ። ትግሉ ከቀዝቃዛው ጦርነት በላይ የጦዘውም ለዚህ ነው ።
ውጣልኝ !  - አልወጣም !
በህግ አምላክ  ?! - በህግማ ነው የመጣሁት !
እረ የሀገር ያለህ ? የመንግስት ያለህ ? - ነባሩ ትዳር በስቃይ ተተብትቦ ነጋ ጠባ ሊጮህ ነው ። ቆይቶ የሚያገኘው ፖለቲካዊ ምላሽ « ተቻችላችሁ ኑሩ  - ተከባበሩ » የሚል መሆኑ አያጠራጥርም ።
እዚህ ላይ ጻጻስ ፍራንሲስ ጋብቻን በተመለከተ አስገራሚ ለውጥ ማድረጋቸውን ማስታወስ ያስፈልጋል ። የአርጀንቲና ጻጻስ በነበሩበት ግዜ « ይህ የፈጣሪን እቅድ የማጥፋት ዘመቻ ነው » በማለት ነው ተቃውሟቸውን በግልጽ አሰምተዋል ። የካቶሊክ ሊቀ ጻጻስ ሆነው ከኢጣሊያኑ ኮሬ ዴላ ሴራ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ « ጋብቻ በአንድ ወንድና ሴት የተወሰነ ነው ፣ ነገር ግን ቤተክርስቲያናችን የተመሳሳይ ጾታን ጥምረት በተለይም ከህክምና አገልግሎትና ከንብረት ባለቤትነት አንጻር መደገፍ አለባት » በማለት ልዩ ጉዳዮች በልዩነት የሚመዘኑበት ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል ።
ሺኖዳ ፍቅር መንፈሳዊና ንጽህ ከመሆኑ አንጻር በሁለት ተመሳሳይ ጾታ መካከል የሚደረግ ጥምረትን የሚበይኑት ዝሙት በማለት ነው < ግብረሰዶማዊነት ተፈጥሯዊ እኮ ነው ? > የሚል ጥያቄም ቀርቦላቸው ነበር ። አንድ ሰው በዚያ መልኩ ከተፈጠረ መጸለይ ፣ መፈወስ በህክናም ማስተካከል ይቻላል ባይ ናቸው ። ይሁን እንጂ ቤተክርስቲያን ሰዎች በዚህ መልክ ይፈጠራሉ ብላ እንደማታምን ይልቁንም ዝሙት መሆኑን በምሳሌ ማስረዳት መርጠዋል ። ቅዱስ አውግስቶ እና ቅዱስ ፓለጊያ ዝሙት ፈጻሚዎች ነበሩ ። ኃላ ቅዱስ እስከመባል የደረሱት በመጥፎ ተግባራቸው ተጸጸተው ራሳቸውን በማስተካከላቸው ነው ።
የግብረሶዶማዊያን ነገር « ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡ ? ውሃ ቢያንቅ በምን ይውጡ ? » አይነት ደረጃ የደረሰ ይመስላል ። ምክንያቱም የተቀጣጠለውን እሳት በማጥፋት ረገድ የእሳት አደጋ ተከላካይ ባልደረባ በመሆን ትልቅ ሚና ይጫወታሉ ተብለው የሚገመቱት ቄሶች ራሳቸው የእሳት ራት በመሆናቸው ።
ልክ እንደ ሺኖዳ ሁሉ የቀድሞው ጻጻስ ቤንዲክት XVI የግብረሶዶማዊነት ጥልቅ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ቄሶች ሊሆኑ አይችሉም ብለው ፈርመው ነበር ። ጻጻስ ፍራንሴስ ግን ግብረሶዶማዊያን ቄሶች ይቅርታ ያገኛሉ የሚል አስተያየት ሰጥተዋል ። ጻጻሱ እንዲህ የተናገሩት ተቸግረው ይመስላል ። ምክንያቱም በሮማን ካቶሊክ የግብረሶዶማዊያን ቄሶችን ቁጥር በትክክል ማወቅ አስቸጋሪ ቢሆንም በርካታ መሆናቸው ብዙዎችን ያስማማልና ። ሌላው ቀርቶ በአሜሪካ ከ1970 እስከ 80ዎቹ በነበሩት ግዜያት በሎስ አንጀለስ ታይምስ በተደረገ ጥናት 1854 ቄሶች ራሳቸውን ግልጽ አድርገዋል ። ይህም በአሜሪካ ብቻ 33 ከመቶ የሚደርሱ ቄሶች ግብረሶዶማዊያን መሆናቸውን ያመለክታል ። ይህን አሃዝ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ተከታዮችን በምትመራው ካቶሊክ መካከል መመዘን የአደጋውን ስፋት በግልጽ ሊያመላክት ይችላል ።
በርግጥ የሁለቱ ጻጻሳት የተለያየ ምስጢር ምንድነው ?
አንዱ ለዘብተኛ ሌላው አክራሪ ስለሆነ ?
አንዱ የምዕራቡ ዓለም የስልጣኔ ውጤት ሌላው የአፍሪካ ኃላቀር ባንዲራ አራጋቢ ስለሆነ ?
አንዱ የተጽዕኖ ውጤት ሌላኛው በራሱ የቆመ ስለሆነ ?
ከእነሱ እምነትና አስተሳሰብ በመነሳት የነገዋን አፍሪካ መገመት ይቻላል ?
አይታወቅም ።


No comments:

Post a Comment