Friday, February 28, 2014

የባለገሩ ስነቃልና የ « አቶ አለምነው ቤት »


ንደማንኛውም መጽሀፍ በትኩረት ላንብበው ብዬ አይደለም የገለጽኩት ። < እስኪ ትንሽ በአነጋገራችን ልዝናና > በማለት እንጂ ። ድንገት ከመሃሉ ገለጥ ሳደርገው < ስራ ያጣ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ ይሰፋል > ከሚለው ንባብ ጋር ግጥምጥም አልኩ ። < ጎሽ ይዞልሃል > አልኩት በፈገግታ - የምሳሌያዊ አነጋገር መጽሀፉን ።
እናም ከ ሀ እስከ ታች የተዘረዘሩትን አነጋገሮች እንደ ፎቶ አልበም እያገላበጥኩ መጫወት ቀጠልኩ ። የገረሙኝን መቼ ይሆን የተነሱት ይቅርታ መቼ ይሆን የተነገሩት ፣ በየትኛው አካባቢ በማለት caption ብጤ እፈላልግ ነበር ። አንዳንዶቹ ሳይታዘዙ የሰው ብብትን ኮርኩረው በግድ ሳቅ መፍጠር የሚችሉ ናቸው ። ለምሳሌ ያህል ፣
< ለሰበበኛ ቂጥ መረቅ አታብዛበት ! >
< ቢያንጋልሏት ጡት የላት ፣ ቢደፏት ቂጥ የላት ! >
< ምንም ብትሞቺ ፣ እንዴት አደርሽ አንቺ ?! >
< እግዜር ሲቆጣ በዝናብ አር ያመጣ >
< ተደብቃ ትጸንሳለች ፣ ሰው ሰብስባ ትወልዳለች ! >
< አባቴ ትንሽ ነው ፣ ብልቴ ትልቅ ነው የሚል የለም ! >
< ልጅ አባቱን ገደለ ቢለው እረ የኔ ልጅ እንዳይሰማ አለው >
የሚሉት ጋ ስደርስ ከትከት ብያለሁ ።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አንዳንዶቹ አባባሎች ጥያቄ የሚያስነሱ ... እንደ መጽሀፍ ቅዱስ ቃል አስረጅ የሚፈልጉ ወይም ደግሞ ሃይለኛ ማስተካከያ የሚፈልጉ ሆነው ነው ያገኘኃቸው ።
ለአብነት ያህል < ነገሩ ነው እንጂ ጩቤ ሰው አይጎዳም ! > የሚለው አባባል ድሮ ጩቤ ከጎማ ወይም ከቆዳ የሚሰራ መሆኑን ነው የሚያመለክተው ። ካልሆነ ታዲያ በአሁኑ ግዜ እንቅፋት ፣ የበዛ ሀሳብ ፣ ድንጋጤና ትንታ እንኴን ሰው ለመግደል ፍቃድ አውጥተው እንዴት ሆኖ የሾለ ብረት ሰው ለመግደል የሚያንሰው ?
< ማን ይሙት ጠላት ፣ ማን ይኑር አባት ! >
የሚለው ስነቃል የተደረሰው የእንጀራ እናት ባሳደገችው ባላገር እንደሆነ ግምት አለኝ ። አሊያማ ከአባት በላቀ መልኩ እናቱንና ሀገሩን « እምዬ » የሚለው ኢትዮጽያዊ ተቆጥረው የማያልቁ የእናት ክብር መግለጫ ግጥሞችን እንደ ዝናር ታጥቆ አይደለም እንዴ የሚዞረው ? ድንገትም
< እናቱን ለናቀ ክብሯን ላዋረደው >
መሬት ትዙርበት ጸሃይ አትሙቀው » ብሎ ሊቆጣ እንደሚችል ሁሉ መች አጣችሁት ?
< ለሰው ሞት አነሰው ! >
የሚለው አባባልስ በምንድነው የተሰራው ? በዝሆን ሀሞት መሆን አለበት ። በዚህ ሀሞት እንጀራ ፈርፍረው በግድ ያጎረሱት አንድ ሰው ክፋትንና ጭካኔን ለመግለጽ  አክ - እንትፍ ያለው ሀረግ ይመስላል ። መቼም ሞት አነሰው የሚለን እድሜ ልክ በእስር ይበስብስ ለማለት አይደለም ። ምናልባት የሚረካው ከጀግናውና ሀገር ወዳዱ አጼ ቴዎድሮስ አንድ የጭካኔ ሰበዝ መዞ ሲተገብረው ሊሆን ይችላል ። አጼ ቴዎድሮስ በደግነትና ጭካኔ ተደባልቀው የተሰሩ ንጉስ ነበሩ ። ቁጣ የንዴታቸውን ጣሪያ በሚያግለው ግዜ የሚያቀዘቅዙት የሰው እጅና እግርን አስቆርጠው ነበር - ከዛ ቁራጭህን ይዘህ ሀገር ግባ ነው ። እግር እንደ ዛፍ የሚመለመልበት ዘመን ። ለነገሩ ይህ ዘመን አልፏል ። ዛሬም ግን ሰዎች በድንጋይ ተወግረው ይሞታሉ ፣ አንገታቸው በሻሞላ ይቀላል ፣ ሰውነታቸው ተቀብሮም ከብቶች በላያቸው ላይ ይነዳል ። እዛ ያሉት አጼ ልክም ነው ህግም ነው ይሉሃል - እኛ የምንለው ያዝልን መጀን ! ነው ።
 < ሙቅ ውሃና የሰው ገንዘብ አይጠቅምም  ! >
በመርህ ደረጃ ልክ ነው ። ዳሩ ግን ጂ+1 ውስጥ እየኖሩ ጂ+6 የሚያስገነቡት ፣ ሚሊየን በሚደፍር መኪና የሚንፈላሰሱት ፣ ለልደታቸው ወይ ዱባይ አሊያም አካፑልኮ ደርሰው የሚመጡት ፣ ይህ ካልተመቸ ከፓሪስ ኬክ የሚያሰጋግሩት ልማታዊ ሀብታሞች በኑሮ ሰረገላ ከአያት ተራራ እስከ እስከ ካራማራ የሚንፈላሰሱት ስፍር ቁጥር የሌለውን የሰው ገንዘብ በጥቂት ማግኔታዊ ላባቸው በመሰብሰብ አይደለም እንዴ ? መሰለኝ እንግዲህ !
< ልጅ ቢያስብ ምሳውን ፣ አዝማሪ ቢያስብ ጠላውን ! >
ይህች አባባል ገና ድሮ ጡረታ መውጣት ሲገባት ለሰዎች በተጨመረው የስራ ዘመን ፍዳዋን ትቆጥራለች ። ለማንኛውም የዛሬ ልጅ ከአባቱ የተረፈውን ሳይሆን ከአባቱ ጸሎት በፊት አስቀድሞ የሚጎርስ ፣ እንግዳ አክብሮ ጔዳ የሚሸሸግ ሳይሆን ልክ እንደ ርዕሰ ብሄር እንግዳውን በራሱ ክፍል ውስጥ ተቀብሎ የሚያነጋግር ፣ አንዲት ምሳውን ሳይሆን ለትምህርት ቤት ከሰኞ እስከ አርብ በሁለት ሳህን ስለሚያስቌጥራቸው የምግብ አይነቶች ከፈለገ ከአረብ ቻናል ፣ እንዳማራጭም ኢቢኤስን ቁጭ ብሎ በመቃኘት  መርሃ ግብር የሚነድፍ ነው ። ስለፍቅር ፣ ስለኑሮ ውድነት ፣ ነገር ስላሰከራቸው ጎረቤቶች ፣ ስለተሸራረፉ መብቶች ፣ ስለቀበሌም ሆነ ገዢው ፓርቲ አያውቅም ብለው ፊቱ ካወራችሁ ተሳስታችኃል - ምክንያቱም በሌላ ቀን እርስዎን እንደ ዋቢ ምንጭ በመጥቀስ ለጔደኛው ወይም ለጥቁሩ እንግዳ ገለጻ ሲያደርግ ሊሰሙ ይችላሉና ።
ስለሴትነት ብዙ ተብሏል ። ጥቂቱን ብቻ እንምዘዝ ።
< ሴትና አህያ በዱላ ! >
የወረደ ነው ወይስ የተጋነነ ንጽጽር የሚባለው ?
 < ሴት የወደደ ገሃነም እሳት ወረደ ! >
የመላከ ጊዮርጊስ ?! እናቴን ? እህቴን ? ልጄን ? ሚስቴን ? ያለው ማን ነበር ?
< ሴት ካልወለደች ቌንጣ አትጠብስም ! >
በጉዴ መጣ አሉ እትዬ ዘነቡ - ባለስልጣኗን አይደለም
< ሴት በማጀት ወንድ በችሎት ! >
ወቸው ጉድ ?! ይህን የማህበራዊና ባህላዊ ልምድ ጣጣ ነው ብሎ ማለፍ እንዴት ይቻላል ? ጠንካራ ፖለቲካም ጭምር እንጂ ። ቆይ ግን የወ/ሮ ዘነቡ መ/ቤት በተለይም ሴቶችን በተመለከተው ርዕሰ ጉዳይ ምን እያሰበ ነው ? ለነገሩ እሳቸው ሰሞኑን የግበረ ሶዶማዊያን አጀንዳ ላይ ናቸው ። ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ ጻጻስ ፍራንሲስ ስለ ጌይ ምን ይላሉ ሲባሉ « እኔ ማነኝ እና ነው ይህን የምዳኘው ? » የተመድ ዋና ጸሃፊ ባንኪሙን በበኩላቸው « ግብረ ሶዶማዊያን እንደ ሁለተኛ ዜጋ ብቻ ሳይሆን እንደ ወንጀለኛም እየተቆጠሩ ነው » በማለት ኡኡ ብለው ያውቃሉ  ። ፕሬዝዳንት ሮበርቱ ሙጋቤ በአንድ ወቅት “ ግብረሰዶማዊያን ከአሳማና ከውሾች የከፉ ናቸው » ማለታቸው አይዘነጋም  ። ሚኒስትር ዘነቡ ማን ከማን ያንሳል ብለው ምን ነበር አሉ የተባሉት ? መቼም ይሄ ሁሉ የስነቃል የቤት ስራ እያለባቸው እዛ ውስጥ ከገቡ የጉድ ነው ።
< በሽተኛ ያድርቅህ መጋኛ  ! >
አሁን ነው መሸሽ ። በደጉ ዘመን በነገር ወይም በቦክስ ገጭቶት አሁን ብድሩን የሚመልስ ሰው ይሆን ? ነው ህመምተኛው ሲያቃስት ከእንቅልፉ እየተቀሰቀሰ በቃሬዛ ጤና ኬላ ማመላለስ የሰለቸው አባወራ ? ለነገሩ የአቶ ቦጋለ መብራቱ እና የወ/ሮ ውድነሽ በጣሙ ዘመድም ሊሆን ይችላል ። አቶ ቦጋለ ወጥሮ የያዛቸው የተስቦ በሽታ ለሌላውም እንዳይተርፍ ለመጋኛ ስለት የሚያቀርብ ምስኪን ገበሬ ። ወይ አጨካከን ?! በሽተኛን ፈጣሪ ይዳብስህ በማለት ያጽናኑታል እንጂ እንዴት ይለጥፉበታል ። ግድየለም እንዲህ የሚናገሩት የሰው ልጆች ሳይሆኑ የሰው ገዢዎች መሆን አለባቸው ።
እነዚህን የመሳሰሉ አነጋጋሪ ፣ ተሻሻይ ወይም ተሰራዥ አባባሎች ጥቂት አለመሆናቸውን መገንዘብ ይቻላል ። ለዚህ ለዚህ የቀድሞው ባህል ሚኒስቴር ከተፎ ስራ ይሰራ ነበር ። የአሁኖቹ እንኴ በፍላጎትና በሞያ ሳይሆን በሹመትና ሽረት ብሎም በአንሚ ደረጃ የተወከሉ ናቸው ስለሚባል  ደረትን ለመንፋት የሚያስችል መሰረት መኖሩ ያጠራጥራል ። ለማንኛውም ግልባጩ ይድረሳቸው ።
ትልቁ እውነት ግን አብዛኛው አባባል ወይም ስነቃል ዘመን ተሻጋሪ መሆኑ ነው ። በነዚህ በርካታ ስነቃል ውስጥ ያልተዳሰሰ ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ሃይማኖታዊ ፣ ባህላዊ ጉዳዮች አለ ለማለት ያስቸግራል ። ከማጣት እስከ ማግኘት ፣ ከስንፍና እስከ እውቀት ፣ ከጅልነት እስከ ብልሃት ፣ ከፍቅር እስከ ጥላቻ ፣ ከጉንዳን እስከ ዝሆን ፣ ከሸፍጥ እስከ ታማኝነት ፣ ከክብር እስከ ውርደት ፣ ከረሃብ እስከ ጥጋብ ፣ ከልጅ እስከ አባት ፣ ከልደት እስከ ሞት ፣ ከዲያቢሎስ እስከ ክርስቶስ ፣ ከሴት እስከ አማት ፣ ከሹመት እስከ ሽረት ፣ ከፍርሃት እስከ ጀግንነት ፣ ከነጻነት እስከ አምባገነንነት .... ምናለፋችሁ ጥላሁን ገሰሰ ያልዘፈነበት ባላገሩ ያልተቃኘበት ፍልስፍና የለም ብሎ እውቅና መስጠት እንደማጋነን የሚያስቆጥር አይመስለኝም ። እያንዳንዱን ርዕሰ ጉዳይ የሚመለከቱትን ስንኞች እዚህ ገጽ ላይ ፈሰስ ባደርጋቸው እደሰት ነበር ። ብዛታቸው ግን አስፈራኝ ። ማንን መርጦስ ማንን መተው ይቻላል ።
እውነት ይህን ሁሉ የደረሰው ብዙዎቻችን ቀለም አልዘለቀውም የምንለው ባላገር ከሆነ የ < ቀለም >ጉዳይ ማጠያየቁ አይቀርም ። እውነት ይህን ሁሉ ነባራዊ እውነት በቃላት ሸብልሎ ያጎረሰን ባላገር ከሆነ < ባገረስኩ ተነከስኩ > ቢል አይፈረድበትም ።
ማነው ነካሽ ?
አሁን በቅርቡ የሚያስተዳድሩትን ባላገር ያበሻቀጡትና ያዋረዱት የአማራው ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አለምነው እውነት ባላገሩን ያውቁታል ?  ካወቁትስ እንዴት ነው የመዘኑት ? ለማለት ስለምንገደድ ነው ። ለምሳሌ ያህል ሹሙ የእውቀትና የልምድ ሀብት የሚለካው ጫማ በማድረግና ባለማድረግ ነው ብለው የተነሱ አስመስሎባቸዋል ። ከዛው ክልል የተገኙት አጼ ቴዎድሮስ ሀብት ሳያንሳቸው ጫማና ኮፍያ ማድረግ አይወዱም ነበር ። ጀግንነትና የሀገር ፍቅር ከባዶ እግር ጋር አይያያዝም ። አበበ ቢቂላ በሮም የኦሎምፒክ ውድድር ያሸነፈው 11 ቁጥር ማሊያና ቁምጣ አድርጎ እንጂ ጫማ ተጫምቶ አልነበረም ። ማራቶን ከጽናትና ጥበብ ጋር እንጂ ከባዶ እግር ጋር ግንኙነት እንደሌለው ሌላ ማሳያ ሊሆን ይችላል ። ርግጥ መንገዱ በማይመችበት ቦታ ተጽዕኖ ሊፈጥር እንደሚችልም ግምት ውስጥ በማስገባት ።
እናም  < ባላገሩ ባዶ እግሩን እየሄደ የሚናገረው ግን መርዝ ነው  > ማለት አንድም ጭንቅላታቸው ውስጥ የሚውለበለብ የንቀት ባንዲራ መኖሩን በሌላ በኩል ደግሞ ያላዋቂነት መነሻ ይሆናል ። ይኀው መነሻ መድረሻ ይኖረው ዘንድ ደግሞ  < ትምህክተኛ ነው ፣ ለሃጫም ነው > እያሉ ልጥፉን ማወፈር በርግጥም ባዶ እግርን ሳይሆን የጎደለ ወይም በዘይት እጦት የሚንጣጣ ጭንቅላትን ወገግ አድርጎ የሚያሳይ ነው ።
በሀገራችን ታሪክ ትላልቅ ስራ የሰሩ በርካታ የሀገራችን ጀግኖች እንደተግባራቸው ስማቸው በክብር እንዲታወስ ተደርጔል ማለት አይቻልም ። ይሁን እንጂ የታደሉት ደግሞ ስንት የጀግንነት ተግባር ፈጽመው በስማቸው እውቅና አግኝተዋል ። ለምሳሌ ያህል አትሌት ኃይሌ  « ሃይሌ ገብረስላሴ ጎዳና »ን በስሙ ማግኘቱ ያንስበታል ።  አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ሆስፒታል አይደለም  ሰሞኑን ለደነገጠው አየር መንገድ ማስታወቂያ ብትሆን መሳ ለመሳ ናት ። ያም ማርሽ ይቀይራል - እሷም ዙሩ ሲሳሳ አዲስ አቦሸማኔ  ትሆናለች ። ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን የራሱን የአገጣጠም ስልት በመፍጠሩ « የጸጋዬ ቤት » የተባለ ስያሜ ተበርክቶለታል ። በዚሁ መሰረት በባዶ ጭንቅላት የሚመረቱ መረን የወጡ ስድቦችን « የአቶ አለምነው ቤት » ብሎ መጥራት  ተገቢ ይሆናል ።
ስራ ለሰሪው እሾህ ላጣሪው እንዲል ባላገሩ ።

Tuesday, February 11, 2014

የኢህአዴግ « እብዶች »






ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ
አክቲቪስት የኔ ሰው ገብሬ
ጋዜጠኛ አበበ ገላው


ፊልድ ማርሻል  ኦማር ሀሰን አልበሽር በታሪከኛው ባድመ የተቃቃሩትን ሁለት ሀገሮች ለማስታረቅ ደፋ ቀና እያሉ ነው ። በቅርቡም ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝንና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ካርቱም ጠርቼ እንዲነጋገሩ አደርጋለሁ ማለታቸው ተሰምቷል ።
ይህን ዜና ሳነብ ትዝ ያለኝ በጦርነቱ ዋዜማና ማግስት በኢህአዴጎች የተጻፈው የቃል መጽሀፍ ነብር ። ርዕሱ « ትዕቢተ ኢሳያስ » የሚል ሲሆን ዋናው ገጸባህሪ ከጥንቱ ኢያጎ ፣ ከዘመናዊው አሰናቀ / በኢቴቪ በመታየት ላይ ያለው የሰው ለሰው ድራማ ተዋናይ /
 በላቀ መልኩ እኩይነትን አሽሞንሙኖ ያሳየ ነበር ። ኢህአዴግ ጨካኝ ቢሆንም በፖለቲካው ሂሳብ አልተዋጣለትም ነው የሚለው ። በደራሲው አስገዳጅነት ማፊያ ፣ ወሮበላ፣ ጋጠወጥ፣ አምባገነን እና እብድ የተሰኙ ባህሪያትን በተናጠልም ሆነ በጋራ እንዲሸከማቸው ተደርጔል ።
በተለይ « እብዱ » የተሰኘው ስያሜ ፈገግ ማድረጉ ግድ ነበር ። ደግሞ በእብድና በአህያ ፈስ ይሳቃል እንዴ ? ካላችሁ « እብድና ብርድ ያስቃል በግድ » የሚባል ስነቃል እንዳለን ማስታወስ ግድ ይሆንብኛል ።
ዞሮ ዞሮ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ የኢህአዴግ አንደኛው እብድ ነበሩ ። አቶ ሃይለማርያም በነገሱ በሶስተኛው ወራቸው በአልጀዚራ የቴሌቪዠን አድራሻ ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የእንነጋገር ጥያቄ አቅርበው « አይቻልም » የተባሉትም « እብድ » ስለሆኑ ይሆናል ። ምክንያቱም « እብድና ዘመናይ የልቡን ይናገራል »
እነሆ ዛሬ ግን ከ « እብድ » ጋር ቁጭ ብሎ መወያየት ግድ ብሏል ። « እብድ ከወፈፍተኛ ቤት ያድራል » ይልሃል ነገረኛው ስነቃል ። በድርጅቱ የቃል መጽሀፍ ውስጥ « እብድ ቢጨምት እስከ አኩለ ቀን ነው » የሚል ምዕራፍ ባይኖርም የኢህአዴግ ሰዎች እቺን ካርድ መዘዝ ከማድረግ አይቆጠቡም ።
ሁለተኛው እብድ ነፍሱን ይማረውና የኔ ሰው ገብሬ ነው ። እንደ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ዘገባ የ 29 አመቱ መምህር በዳውሮ ዞን ጣርቻ ከተማ ራሱን አቃጥሎ መስዋዕት የሆነው የፍትህና የነጻነት ጥያቄ በማንሳት ነው ።
ህብረተሰቡና ባለስልጣናት በተሰበሰቡበት አዳራሽ ያለጥፋታቸው ብቻ ሳይሆን ያለፍርድ የታሰሩት ወጣቶች ጉዳይ እንዲታይ እንዲሁም እንዲፈቱ ጠይቌል ነው የሚባለው ። በቂ ምላሽ ያላገኘው ወጣት ራሱ ላይ ቤንዚን አርከፍክፎ በብዙዎች ፊት ሲቃጠል ሶስት መሰረታዊ ጥያቄዎችን በጩኀት እያሰማ ነበር
ፍትህ
ነጻነት
ዴሞክራሲ
ቱኒዚያው መስዋዕት መሀመድ ቡአዚ ተግባር በየት መጣ ያለው ኢህአዴግ አሁን « ሳይቃጠል በቅጠል » የሚለው ጥቅስ ተመራጭ ሆኖ አገኘው ። የዳውሮ ዞንም ሆነ ሌላው ማህበረሰብ የኔ ሰውን « የኛ ሰው » ከማድረጉ በፊት ማንነቱን  እንዲያውቅ አደረገ ።
መንግስት በቴሌቪዥኑ  የኔ ሰው የአእምሮ ችግር ያለበት እንደነበር በእህቱና በአባቱ እንዲገለጽ አስደረገ  ። ምክንያቱም ስም ይወጣል ከቤት ይከተላል ጎረቤት ተፈጻሚ ይሆን ዘንድ ። በአናቱ ላይ ደግሞ « እብድ የያዘው መልክ አይበረክትም » ሲል ከንፈሩን እየመጠጠ አስተያየቱን በአየር ውስጥ ናኘው ።
እብድን ግን እንደ ሀገር ባህል ሰብሰብ ብላችሁ አትቅበሩ የሚል ህግም ሆነ ጥቅስ አለ እንዴ ? መስዋእቱ vs እብዱ የኔሰው በጥቂት ሹማምንቶች ብቻ ታጅቦ ነው አሉ የተቀበረው ። መቼም ሳይንስ እብደት የማይተላለፍ በሽታ መሆኑን ነው የሚመሰክረው ። ታዲያ ድርጅቱ ምን ነክቶት ነው የህብረተሰቡን የቀብር ባህል የተጋፋው ?  መቼም የሞተ ሰው አያስፈራም - የሟቹ እውነተኛ መንፈስ እንጂ ። 
« ስመሰክርልህ ስመሰክርልህ ዋልኩ ቢለው ስታዘብህ ስታዘብህ ዋልኩ አለ » ደገኛ
ሶስተኛው እብድ ጋዜጠኛ አበበ ገላው ነው ። አቶ መለስ በካምፕ ዴቪድ በተጋበዙበት የጂ - 8 ስብሰባ ላይ ተሞክሯቸውን በማቅረብ እሞገሳለሁ ብለው እንጂ እሰደባለሁ ብለው እንዴት ይጠብቃሉ ? « Meles Zenawi is dictator .... Don’t talk about food without  freedom » የሚል ወፍራም ቁጠኛ ድምጽ የአዳራሹን አየር ቀየረው ።
አበበ ገላው የሙንታዳር አልዛይድ ጔደኛ ነበር እንዴ ያሰኛል ። ሙንታዳር ትዝ አላችሁ ? ፕሬዝዳንት ቡሽ ባግዳድ ውስጥ ፕሬስ ኮንፈረንስ ሲያካሂዱ ጫማውን ወርውሮ ያስደነገጣቸው የአረብ ጋዜጠኛ ። በርግጥ ሙንታዳር ጫማ በመወርወሩ የመጀመሪያ አልሆነም ። ይህን የመሰለ ድርጊት በህንድ፣ አየርላንድ ፣ አውስትራሊያ ፣ ታይዋን ፣ ሆንግ ኮንግና ፓኪስታን ተደርጔልና ። እንዲህ ያደረገ ኢትዮጽያዊ ጋዜጠኛ ባለመኖሩ ግን አበበ የመጀመሪያ ድርጊቱ ደግሞ አስገራሚና አነጋጋሪ ሊሆን በቅቷል ። ጥቂት ቆይቶም አቶ መለስ በመሞታቸው
« አበበ ገላው መለስን በላው » የሚል ግጥም ተደረሰ ። ኢህአዴግና ደጋፊዎቹ « አበበ ገላው የአእምሮ በሽታ ያለበት ንክ ሰው ነው » በማለት ጉዳዩን ተራ ለማድረግ የመልስ ምት ሰጥተዋል ።
« አበበ ገላው በነካ እጅህ እገሌ የተባለውን ሚኒስትር አስደንግጥልን » የሚለው የፌስ ቡክ ጥያቄ ቀላል አልነበረም ። ኢህአዴግ ግን ለመጀመሪያ ግዜ እብድን ንቆ ወይም ስቆ ለመተው ተቸገረ ። የኢህአዴግ ሰዎች « እንኴን ለገንፎ ለሙቅም አልደነግጥ » የሚል ጥቅስ መኖሩን ዘንግተው ይሆን ?
የጋዜጠኛውን መንገድ የሚከታተሉ ፣ ንግግሩን የሚቀርጹ ፣ ቆይ ጠብቅ አሳይሃለሁ ወይም እገድልሃለሁ የሚሉ ማስፈራሪያዎች ግን እንደ እድገታችን በሁለት አሃዝ እያደጉ ነው ።
ተንጋለው ቢተፉ ተመልሶ ባፉ እንዲሉ አበው ።

Saturday, January 18, 2014

የቴዲ አፍሮ አዝመራ ...

 


ለእኔ ቴዲ አፍሮ የቲፎዞ ግፊያ ወይም የአጋጣሚ አውሎ ንፋስ ድንገት እሽኮኮ አድርጎት ከፍ ካለው ማማ ላይ ከሰቀለው በኃላ ሳያጣራ ለማድነቅ ወይም ለመውቀስ በሚቸኩለው የትየለሌ አበሻ ዘንድ እልልታን በወደቀ ዋጋ የሸመተ ሰው አይደለም ። ቴዲ አይን ፣ ህሊናና ልቦና ተነጣጥለው ሳይሆን ተዛምደው በሚያዩትና በሚሰማቸው ጥልቅ ትዕይንት የሚመሰጡበትና የሚደነቁበት የጥበብ ማሳ ነው ።
ማሳው ቸልተኛና ቀሽም አርሶአደር ባወጣው ያውጣው ብሎ እንደሰራው ጎስቌላ መሬት የተመሰቃቀለ ምስል የሚታይበት አይደለም ። ማሳው ሰልፍ ማሳመር እንደሚችሉት የሩቅ ምስራቅ ወታደሮች ህብርና ከቃላት በላይ መግለጫ የሚፈልግ ውበት ተሰናስሎ የሚታይበት ክቡር ኪናዊ መድረክ ነው ። ማሳው ጥልቀት ባላቸው የግጥም ሀሳቦችና ሸናጭ ዜማዎች ውህደት ምናብ ሰራቂ እንቅስቃሴዎች የሚታይበት መስክ ነው ።
አዝመራው በስልጡኑ ገበሬ ቴዲ ሲፈልግ ለሙዚቃ የሚሆን ገብስ ፣ ሲፈልግ ለመጽሀፍ መድብል የሚያገለግሉ ስንኞች ተዘርቶ የበቀለበት ነው ። ይህ አዝመራ እንደሌሎች የኪነት ገበሬዎች ገጣሚ ተፈልጎ ስንኝ እስኪመተርና የዜማ አድባር እስኪለመንበት ድረስ በአረም የሚሞላና በከብቶች ኮቴ የሚደፈር አይደለም ። ይህ አዝመራ እንደ ብዙዎቹ የሀገራችን ምስኪን የኪነት ገበሬዎች የሰማይን ዝናብ ጠብቆ በአመት አንዴ ብቻ የሚዘራበት አለመሆኑ ሌላኛው መገለጫው ነው ። የቴዲ አዝመራ ወቅታዊና አስቸኴይ ጉዳዮች ሲፈጠሩ በተሰጥኦ ቅመም የተሰራውን የምርጥ ግጥምና ዜማ እንክብል ውጦ የፌሽታ ፈንዲሻን እነሆ በረከት የሚል ነው ።
ሁሌም ባለመስመር ፣ ሁሌም በንፋስ ኮርኴሪነት ደፋ ቀና እያለ የሚያባብል ፣ ውርጭና ዶፍ  ቢያስቸግረው እንኴን እንደ ሱፍ አበባ ብርሃንና ፍቅርን የሚከተል ነው ።
ይህ ማሳ በመስመር እንደተዘራበት ሰብል ደስ ይላል የሚባልበት ብቻ አይደለም ። ማሳው ላይ የሰርከስ ኦርኬስትራ ልዩ ልዩ ብልሃቶችንና ጥበቦችን የሚያንጸባርቁበትም እንጂ ። ለቢራ የደረሰው የገብስ አዝመራ አስካሪነቱን ብቻ ሳይሆን አዝናኝነቱንም ለምግብነት ከበቀለው ገብስ ጋር ተወያይቶ የሚግባበት የፍቅርና የመቻቻል ገመድ አለው ። ለብዙ ጥቅም የሚውለው የስንዴ አዝመራ በልምድ አናሳ ግምት የተሰጠውን የጔያ ሰብል የሚያገልበት ወይም የባቄላውን አዝመራ « ፈሳም » እያለ የሚያሸማቅቅበት ምዕራፍ የለውም ።
ነጭ ጤፍን የሀብታም ወይም የባለግዜ ቦለቄውን የድሃ ወይም የተጨቌኝ ተወካይ በማለት እያላገጠ የሚያሽካካበት ግዜም ያጥረዋል ። የአዝመራው መስመር በነጠላ መስመር ብቻ ያልተዘረጋውም አንድም ከዚህ አኴያ ነው ። የሰብሎችን ህብርና ስብጥር በልዩ ልዩ ቅርጾች እየወከለ፣ እየገለጠ የሚታይ የኦርኬስትራው ወይም የሰርከሱ መሪ መድብል ነው ።
የቴዲ አዝመራ ደርሶ ሲበላ የመጨረሻ ግቡ በ « ጥጋብ » ደስታን መፍጠር አይደለም ። ፈጣን ምናብ ያለው ገና እህሉን እያላመጠ ፣ ቆይቶ የሚገባውደግሞ በስተመጨረሻም ቢሆን ይሄ ምግብ ከምን ተሰርቶ እንዴት ሊጣፍጥ ቻለ ? እንዴት አንጀትን ያርሳል ? እያለ እንዲያንሰላስልና ብዙ እንዲጠይቅ ማድረጉ ነው ። አዝመራው ፍቅርና ሰላምን ፣ መቻቻልና ብሄራዊ እርቅን ፣ የሃይማኖትና ፖለቲካ እኩልነትን ፣ ፍትሃዊነትንና ሰብዓዊነትን ፣ ቅንነትንና ጀግንነትን በጣም በተኴለና ወጣ ባለ መንገድ ለምናብ አድራሽ ነው ።
ስር በሰደደ ሙያዊ እውቀትና ፍቅር የተያዘው የቴዲ አዝመራ ከአመት አመት የሚሰጠው ምርት እያደገ የመምጣቱን ያህል አፈንጋጭነቱና ልዩ አተያዩ አለርጂ የፈጠረባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች በሚገኘው ጠባብ የስህተትም ሆነ የመዘናጊያ ቀዳዳ ሾልኮ በመግባት አንካሴያቸውን ከመወርወር ተቆጥበው አያውቁም  ። እናም አሁንም ለብዙ ግዜኛ መሆኑ ነው ሰብሉ ላይ ልክ እንደ ነጭ ርግብ የተምች ፣ ነቀዝና ፌንጣ ሰራዊት አንገታቸው እየተሳሙ ተለቀዋል ።
በርግጥ መቼ ይሆን በፍቅር አረዳድ ራሳችንን የምንችለው ?
አዝመራው ግን ውርጭና ዶፍ ቢያስቸግረውም እንደ ሱፍ አበባ ብርሃንና ፍቅርን የሚከተል ነው ...


 

Thursday, January 9, 2014

« ግልጽነት የሚሻው ግልጽ ደብዳቤ »


አቶ ግርማ ካሳ ሰሞኑን በዘ ሀበሻ ድረ ገጽ ላይ  « ግልጽ ደብዳቤ ለፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም » የሚል ጦማር ጽፈው አንብበናል ። የደብዳቤው ዋና አላማ በ 2007 ዓ.ም ለሚደረገው ብሄራዊ ምርጫ አንድነት የተባለው ድርጅት በተለይም ከመድረክ ፣ መኢአድ ፣ አረና ፣ ኢዴፓና ሰማያዊ ፓርቲዎች ጋር ውህደት ፈጥሮ ስልጣን በቃኝ የማያውቀውን ድርጅት መታገልን ይመለከታል ።

በርግጥ ግልጹ ደብዳቤ ያስፈለገው የተቃዋሚዎችን ዳግማዊ የአንድነት ትንሳኤ አስረግጦ ለማሳየት ነው ወይስ ለምልጃነት የሚል ገራገር ጥያቄ በእግረ መንገድ ካነሳን ምላሹ የኃለኛው ሃሳብ ሆኖ እናገኘዋለን ። እዚህ ላይ ነው እንግዲህ « ግልጽነት የሚሻው ግልጽ ደብዳቤ » የሚል የመጻፊያ ርእስ ድንገት ብቅ የሚለው ። ፕሮፌሰር መስፍን በኢህአዴግ ዘንድ እጅግ የሚፈራውና የተገለለውን የይቅርታ መንፈስ በሀገሪቱ ዳመና ላይ ለማርበብ ወይም በፖለቲካው አጠራር የብሄራዊ እርቅን አጀንዳ ደጋግሞ ርእሰ ጉዳይ በማድረግ ወደ ተጨባጭ ምዕራፍ ለመለወጥ የተጉ ምሁር መሆናቸው ይታወቃል ። ይህንንም በሚያደርጉት ንግግር ብቻ ሳይሆን ያሳተሟቸውን በርካታ መጽሀፍት በማንበብም መረዳት ቀላል ነው ።

አጠያያቂው ጥያቄ ፣ አቶ ግርማም እንደነገሩን ፣ ፕሮፌሰር መስፍን ሰማያዊ ፓርቲን ከመሰረቱት አንደኛው በመሆናቸውና የመጀመሪያውም መሪ ስለነበሩ « ግልጹ ደብዳቤ » ሌላው ቢቀር ያለ ግልባጭ ቀጥታ ለእሳቸው የመጻፉ ነገር ነው ። በአሁኑ ወቅት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት መሆናቸው ይታወቃል ። ይህ ደብዳቤ መጻፍ የነበረበት ቀጥታ ለወቅታዊው የፓርቲው አመራር ወይስ ወደጎን ለቀድሞው ቁልፍ ሰው ?

ይህም ጥያቄ ሌላ ጥያቄ ይወልዳል ። አቶ ግርማ ፓርቲውን አነጋግረው ጥሩ ምላሽ አላገኙም ማለት ነው ? ከሆነ የጻፉት ግልጽ ደብዳቤ እስከሆነ ድረስ ለአንባቢው ይኀው የኃላ ታሪክ መገለጽ ነበረበት ። ርግጥ ነው አቶ ግርማ ውስጥ ያለውን ነገር ሊነግሩን ባይፈልጉም የግልጹ ደብዳቤ አንዳንድ ሀረጎች በራሳቸው ችግር መኖሩን እየጮሑ የሚያሳብቁ ናቸው ።

አቶ ግርማ ፈገግ ብለው አሉ ።

1 . « የሰማያዊውን ነገር በርስዎ ጥዬዋለሁ ። ያሳምኗቸውና ያግባቧቸው ዘንድ እጠይቃለሁ »

አቶ ግርማ ኮስተር ብለው አሉ ።

2 . « ምክርዎትን አልሰማ ብለው የተናጥል ጉዞ ከቀጠሉ ምርጫው የእነርሱ ይሆናል »  ጥርሳጨውን እያንቀጫቀጩና ሳይታወቃቸው ጠረጤዛ እየደለቁ ... « ጉዳዩ የፌዝና የቀልድ ወይንም የግለሰቦች ተክለሰውነት የመገንባት ሳይሆን የአገር ህልውናና ደህንነት ነው ... »  በማለት ቀጠሉ ።

ልብ በሉ አምስት ሳንቲም አላጋነንኩም ። ያደረኩት የአቶ ግርማ ቃላቶች ደምና ስጋ እንዲለብሱ ማድረግ ነው ወይም ቃላቶቹ የሚወክሉትን አካላዊ እንቅስቃሴ አስደግፎ ማቅረብ ብቻ ነው ። ታዲያ እንዴት ነው ጎበዝ ማነው እያፌዘና እየቀለደ ያለው ? እረ ማነው ፖለቲካን ለተክለ ሰውነት መገንቢያ ጥቅም እያዋለ የሚገኘው ? የሚሉ ጥያቄዎች ውስጣችን እየተንጫጫ እንዴት ነው ሆዳችንን የማይቆርጠን ... ለዚህም ነው ግልጹ ደብዳቤ ሊነግረን ያልፈለገው ወይም የደበቀን ነገር በመኖሩ የግልጽነቱን አላማ ስቷል የሚያስብለው ።

 አንባቢ « ነገርን ከስሩ ውሃን ከጥሩ » ብሎ ይመረምርና ይታዘብ ዘንድ በቂ የመረጃ ትጥቅ ሊኖረው ይገባል ። አቶ ግርማ እንዳሉት የማስታረቅና የመሸምገል ልምድ ያላቸው ፕሮፌሰር መስፍን በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ያለውን ጠባብም ሆነ ቦርቃቃ ልዩነት ከምን ተነስተው ምን ደረጃ ላይ አደረሱት ? የሚል ምናባዊ ቢጋር አዘጋጅቶ እንዲንቀሳቀስም ይረዳው ነበር - አንባቢው ። ግና ቢጋሩ እንዳይነደፍ ግልጹ ደብዳቤ ውስጥ unግልጽ የሆኑ እንክርዳዶች መንገድ ዘግተዋል ።

ነገር ሰነጠቅክ አትበሉኝ እንጂ ደብዳቤው ውስጥ የኢህአዴግን የመሰለ « ረጅም ሪሞት ኮንትሮል » የተመለከትኩ መስሎኛል ። በመጀመሪያ ለዚህ ጽሁፍ ዓላማ የተዘጋጀውን « ሪሞት ኮንትሮል » ብያኔ እንስጠው ።

ሀ . የተለየ ትርጉም ካልተሰጠው በስተቀር በዚህ ጽሁፍ ውስጥ « ሪሞት ኮንትሮል » ማለት ገባ ወጣ የማይል የህንድ ፊልም አክተር ማለት ነው ። የህንድ ዋና አክተር በገጀራ አንገቱ ቢከተከት ፣ በላውንቸር ጥይት ደረቱ ቢቦደስ ለግዜው ቢደማ ፣ ለግዜው ቢሰቃይ እንጂ በፍጹም አይሞትም ። የህንድ አክተር እንደ ፈጣሪ በሶስተኛው ቀን ባይሆንም እንደ እባብ ከሞተ በኃላ አፈር ልሶ በመነሳት ተመልካቹን ጉድ የማሰኘት አቅም አለው ።

የኢህአዴግ ህንዳዊ አክተር የሆነት አቶ መለስ ይኀው ሞተውም ቢሆን ሀገር እየገዙ ፣ ሰራዊት እያዘዙ ፣ ቦንዳዊ መልዕክታቸውን ከሚያማምሩ ጥቅሶች ጋር እያስተላለፉና « ሌጋሲ » የተባለ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማቸውን እያዘጋጁና እየተወኑ ናቸው ። በሪሞት ኮንትሮል ። ብዙ ግዜ ታዲያ የህንድ ፊልም ተመልካች የአክተሩን ልዩ ተግባር እያደነቀ መመሰጥና ማጨብጨብ እንጂ ለምንና እንዴት በሚሉ ገሪባ ጥያቄዎች መጨናነቅ አይፈልግም ። እናም ኢህአዴግ ማለት በአራት ጎሳዎች ውህደት የተሰራ ድርጅት ነው የሚለው ትምህርት እንዴት እንደተደለዘ ሳይታወቅ ኢህአዴግ ማለት መለስ መሆኑ ከተረጋገጠ ቆየ ።

ታዲያ በአቶ ግርማ ደብዳቤ ውስጥ የታየው ሪሞት ኮንትሮል ምንድነው ? ከተባለ ነገሩን ከኢዴፓ ለመጀመር ይቻላል ። ኢዴፓን ለረጅም ግዜ የመሩት አቶ ልደቱ አያሌው ፖለቲካ ርስት አይደለም በማለት ከሳርና ስፖንጅ የተሰራውን ወንበራቸውን ለምክትላቸው ለአቶ ሙሼ ሰሙ ማስተላለፋቸው ይታወሳል ። በሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ሳይሆን በሶስተኛ የፍልስፍና መንገድ የሚታወቁት አቶ ልደቱ ከፖለቲካ ርቀው በቅርቡ ወደ መዶለቻው ሰፈር /ፖለቲካ / መቀላቀላቸውን በዜና ሰምተናል ። አቶ ግርማ ለግልጽ ደብዳቤያቸው ማጠናከሪያ ይሆን ዘንድ « አቶ ልደቱ አያሌው ለአድማስ ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት ኢዴፓ ከአንድነት ጋር አብሮ ለመሆን የመፈለግ አዝማሚያ ሳይኖረው እንደማይቀር አስባለሁ » ብለው ጽፈዋል ። ልብ አድርጉ ባለሙሉ ስልጣኑን አቶ ሙሼን አይደለም የገለጹት - ከጨዋታው የራቁ የመሰሉትን አምባሰደር ልደቱን እንጂ። እዚህ ሀሳብ ውስጥ የህንድ አክተርም በሉት ሪሞት ኮንትሮልን እንደ ቀጭኔ አንገቱን አስግጎ አልታያችሁም ?

ሁለተኛው ሪሞት ኮንትሮል ራሱ ሰማያዊ ፓርቲ አካባቢ የሚሸት ነው ። አቶ ግርማ « የርስዋ ድርጅት ሰማያዊ ፓርቲ ሀገር ቤት ጥሩ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ ድርጅቶች ከጥቂቶቹ መካከል አንዱ ሆኗል » በማለት ነበር ለፕሮፌሰሩ የሚገልጹት ።

ኃይለ ቃል ፣ የርስዎ ድርጅት

ምዕራፍ አንድ ፣ አሁን የአመራር አባል ላልሆነ ሰው እንዲህ እንዲገለጽ የቌንቌ / ሰዋሰው /  ስርዓታችን ይፈቅዳል ?

መካከለኛ ምዕራፍ ፣ የርስዎ ደርጅት የሚለው አነጋገር በጣም ለማጠጋጋት እንደሚያስቸግር ቁጥር ከመሃል ዝቅ ብሎ የወረደ ቢሆንም ድሮ የመሰረቱት ለማለት ተፈልጎ ነው ብለን ብናፏቅቀው ምን ያህል ያስኬደናል ?

መደምደሚያ ፣ የርስዋ ድርጅት ማለት ሳናጠጋጋው እረ እንደውም ከሩቅ በሪሞት ኮንትሮል ብንነካካው ትርጉሙ አሁንም ከጀርባ ሆነው የሚመሩት ማለት ይሆን ?


የገምጋሚው ማስታወሻ ፣ ግልጽነት ሳይቀድም ይቅር ለእግዚአብሄር መባባል ትርጉም ያጣል ። የግልጽነትን ድልድይ ሳይረግጡ ከአንድነት ቅጥር ግቢ መድረስ ያስቸግራል ። ደብዳቤውም ግልጽነት ያንሰዋል ። በደብዳቤው እንድንግባባ ተጨማሪ የማፍታታት ስራ እንዲሰሩ ይነገራቸው ። በቂ ነው ብለው ካሰቡ ግን ላጺስ ከኢህአዴግ ተውሰው ርዕሱን በአስቸኴይ ይደልዙት ። ለባለይዞታው ይመለስ ብለናል ።

Wednesday, December 18, 2013

ሊቨርፑል በገና ዋዜማ





ሰማዩ እጅግ ከፍቶታል ...

እንዲህ መሆን ከጀመረ ቆየ ።

አምቆ የያዘውን ጥቁር እባጭ የመሰለ ነገር ዘርግፎ ቢጨርሰው ሰላም ባገኘ ነበር ። ግና ቁጣ እንዳስበረገገው የአበሻ ህጻን ቆይቶ - ቆይቶ ነው ጠብ የሚያደርገው - ርግጥ ነው እንደ ህጻን ችክ ያለ ማላዘን አይታይበትም ።

ተጠሪነቱ ለደመናው ይሁን ለምድሪቱ ያልታወቀው ብርድ ግን የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ እየተወጣ ይገኛል ። አንዳንዴ በግልጽ እንደ ውሻ ይናከሳል ... አንዳንዴ እንደ ስለታማ ቢላ አካልን ይሰነጥቃል ። በግላጭ በሚያገኛቸው ጆሮ ፣ አፍንጫና የእጅ ጣቶች ላይ ደግሞ ጥቃቱ ለጉድ ነው ። እንደ ንብ ነድፎ - ነድፎ በረዶ ቤት የተቀመጡ ዕቃዎች ያደርጋቸዋል ።

ምድሪቱ ጉንጭ ላይ ስስ ፈገግታ ይታያል ...

ዓላማና ግቧ ግን ሙሉ ፊቷ ላይ ሳቅ እንደፈንዲሻ እንዲተራመስ ማስቻል ነው ። እናም ግብግብ ላይ ናት ። በረዶው ፣ ንፋሱ ፣ ብርዱ ፣ ዝናብና ጭጋጉ የቱንም ያህል ጥቃት ቢያደርስብን የገና በዓላችንን ከማድመቅ አይገድብንም የሚሉት ሊቨርፑዲያንስ ሙሉ ከተማውን ሞልተው ይሮጣሉ ። ሩጫቸውን ከንግድ ቤቶች የሚወጣው የገና ሙዚቃ ያግዛቸዋል ። ታላቅ ቅናሽ እያሉ በማይክራፎን የሚያላዝኑት ሱቆችም በረከቱ እንዳያመልጣቸው አጥብቀው ይወተውታሉ ። እዚህ እንደ እኛ ሀገር ዶሮና በግ ጥጋቸውን ይዘው አይጮሁም ። ሳርና ችቦ የሚቸረችሩ ወቅታዊ ነጋዴዎች ማየት አይቻልም ፤ አየሩ በተነጠረ ቅቤ ፣ በኮባና ኩበት ጢሳጢስ የተሞላ አይደለም ።

በርግጥም አየሩን የተቆጣጠሩት አብረቅራቂ መብራቶችና ሙዚቃዎች ናቸው ። መኖሪያ ቤቶች ፣ ህንጻዋችና « ሲቲ ሴንተር » የተባለው የገበያ ቦታ ለአይን በሚማርኩ የመብራት ውጤቶች ተንቆጥቁጧል ። ከሱቆቹ በተጨማሪ እዚህም እዚያም የተለያዩ የሙዚቃ ስራዋችን የሚያሳዩ ግለሰቦች እንደ አሸን ፈልተዋል ። ትላልቅ ሴቶች ሳይቀር አኮርዲዮን እጥፍ ዘርጋ እያደረጉ ሳንቲም ይሰበስባሉ ። ሁለት ሶስት ሆነው ቆርቆሮን እንደ ከበሮ በመጠቀም የመንግስት ማርሽ ባንድን የሚያስንቁ ሰዋችም ይታያሉ ። በአርሞኒካ ብቻ የብዙዋቹን ትዝታ የሚያማልል ፣ እንዲሁም ከውሻው ጋር ቁጭ ብሎ የሚመስጥ መሳሪያ የሚጫወት ሌላ ሰው በሌላ ክንፍ አይታጡም ።

በስነስርዓት ማይክራፎንና ኪቦርድ አዘጋጅቶ የፈረንጆቹን ሙዚቃ የሚጫወት አንድ አፍሪካዊ ግን ብዙ ግዜ የብዙዋችን ትኩረት ሲስብ ተመልክቼያለሁ ። ተመልካቹ ክብ ሰርቶ አፉን ከፍቶ ፣ አንገቱን ግራና ቀኝ እየናጠ ይመለከተዋል ። አንዳንዶቹ ደግሞ መሃል ገብተው ይወዛወዛሉ ። ይህን ሰው X – Factor አያውቀውም ወይስ X – Factor / የእንግሊዞች ታዋቂ አይዶል ሾው / አንጋሎ የተፋው ነው ? ድምጹ ብርዱንና ውሽንፍሩን በታትኖ ከጆሮ የሚደርሰው ሳይደናቀፍ ነው - አይጎረብጥም ። የዳጎሰ ልምድ ያለው መሆኑ ለተራ ሰውም ግልጽ ነው  - አንዳንዶች ሊወኒልን ሪቼ እያሉ ይጠሩታል ። በርግጥም የታዋቂውን አቀንቃኝ አንድ ሙዚቃ ሲያቀነቅን ነበር ፣

Good bye  ይለዋል ታዳሚውን እንደሚሰናበት ሁሉ  

I wanted you for life
You and me
In the wind
I never thought there come a time
That our story would end
It’s hard to understand
But I guess I’ll have to try
It’s not easy
To say good bye ... good bye ... good bye ..


ሙዚቃውን ሲጨርስ ታዲያ የሚሰሙት ጭብጨባ አንድ ትልቅ ቲያትር ቤት የታደሙ ያህል ነው ። ከዚያም ፊት ለፊት ባስቀመጠው ሻንጣ ውስጥ የእንግሊዝ ነጭና ቀይ ሳንቲሞች ሲንቦጫረቁ ይሰማል ።

አፍሪካዊው አቀንቃኝ

ሙዚቃ ወዳዱ የሊቨርፑል ነዋሪ ሲጋራውን እያቦነነ ፣ ሀምበርገሩን እየገመጠ ፣ የሚጠጣውንም እየተጎነጨ ያዳምጣል ። የዚህ ከተማ ሃምሳ የሚደርሱ አቀንቃኞች በምድረ እንግሊዝ ብቻ ሳይሆን በዓለማቀፍ ደረጃም ትልቅ ስም ያላቸው ናቸው ። ሙዚቃዋቹ ለጆሮ በደረሱበት ዘመን በሽያጭ ረገድ ቁጥር አንድ በመባላቸው ከተማዋ በጊነስ ቡክ ላይ የሙዚቀኞች ሀገር ለመባል አስችሏታል። በ1960 የተመሰረተውን The Beatles ብቻ ለአብነት ማንሳት ይቻላል ። አራቱ የቡድኑ አባላት ጆን ሊኖን ፣ ፓውል ማካትኒ ፣ ጆርጅ ሀሪሰን እና ሪጎን ስታር በ1962 « Love Me Do » የሚለውን አልበም እንደለቀቁ ነበር ታዋቂነትን የተጎናጸፉት ። ሮሊንግ ስቶን ሙዚቀኞቹን የምንግዜም ትልቅ አርቲስቶች ብሏቸዋል ። ታይም መጽሄት በበኩሉ የሃያኛው መቶ ክፍለዘመን መቶ ተጽዕኖ ፈጣሪ ብሎ ከዘረዘራቸው ግለሰቦች መካከል አስፍሯቸዋል ። የፈረደበት ጊነስ ቡክ ወርልድ የሙዚቀኞቹን « Yesterday » የተባለው ሙዚቃ ከሶስት ሺህ አርቲስቶች በላይ ከእንደገና ተጫውተውታል ይለናል ። አስደናቂው ነገር እንዲህ ተደጋግሞ የተዘፈነበት ሌላ ሙዚቃ አለመኖሩ ነው ።

በከተማው መሃል ለገና እየቀረበ ያለው ሌላው ስጦታ የግለሰቦች « ምትሃታዊ » ስራ ነው ። ለነገሩ አስማት ይባል ሌላ ጥበብ በድፍረት መናገር ቸግሮኛል ። እስኪ አንድ አጭር « ሾው » በጽሁፍ እንከታተል ፤

 አንድ ሰው ሻንጣ ይዞ መጣ ።
ከሻንጣው ውስጥ የሚያብረቀርቅ ልብስ አውጥቶ ለበሰ ።
 አናቱ ላይ  ቀንድ ያለው ማክስ አጠለቀ ።
ፊቱንም ልብሱን የመሰለ ነገር ተቀብቶታል ።
የልብሱን ቀለም የመሰለች ብትር አወጣ ።
ዙሪያ ገባውን ማትሮ በፈገግታ እጁን አወዛወዘ ።
በአካባቢው መንኮራኮር የለም እንጂ ወደ ላይ ለመምጠቅ የመጨረሻ ሰላምታ የሚሰጥ ነበር የሚመስለው ።
 መሬቱ ላይ ጥቁር ጨርቅ አነጠፈ ።

የፈራነው ደረሰ ?

እንዴ ? ... ዱላውን ተሞርኩዞ በአየር ላይ ቁጭ አለ ። በቃ ! ... ይወርዳል ብለን ብንጠብቅ - ብንጠብቅ ቁጭ እንዳለ ቀረ ። መቼም ይህ ሰው ሊንሳፈፍ የቻለው ጭንቅላቱን « ጨረቃ ላይ ነህ » ብሎ በማሳመኑ ሊሆን አይችልም ። ብዙዋቹ በጥበቡ በመገረም ሳይሆን በፍርሃትና በጥራጣሬ ነበር የሚመለከቱት ። እንዴት ሊሆን ቻለ ? ሰውነቱ ውስጥ የቀበረው ነገር ይኖር ይሆን ? በዜና ያልሰማነው ምን የሚያንሳፍፍ መሳሪያ ተገኘ ? መልስ አልነበረም ። ሳንቲም ወርወር ሲያደርጉለት ብቻ እጁን በአፉ እየሳመ ፈገግ ይላል ። ከዚያ ውጪ ኮስተር ስላለ ጥሩ ቀራጺ የሰራው ሃውልት ነው የሚመስለው ።

ተንሳፋፊው ሰው

 « ይገርማል » እያልኩ ሌላውን የገበያ አቅጣጫ መከተል ጀመርኩ ። የማስበው ስለ ምትሃት ነበር ። አስማት ጥበብ ነው ፣ ሳይንስ ነው ፣ ፈጣን የጭንቅላት ጨዋታ ነው ፣ በባዕድ አምልኮ ጋር የተገናኘ መንፈሳዊ ስራ ነው ... ብዙ ብዙ ይባላል ። ድንገት አባባ ተስፋዬ ሳህሉ በአእምሮዬ ጔዳ ብቅ አሉ ። በቴሌቪዥን መስኮት የምትሃት ጥበብ እያሉ ገመድ ሲቌጥሩና ሲፈቱ ፣ ጨርቅ ሲያሳዩና ሲሰውሩ  ብዙዎቻችን ተመልክተናቸዋል ። ምናልባትም ለአስማትና ምትሃት ያለን የእውቀት ጥግ ያንን ያህል በመሆኑ ሊሆን ይችላል አድናቆታችን አለቅጥ የሚረዝመው ።

ስለ አስማት የሚያውጠነጥነው አእምሮዬ ተጨማሪ ነገር የፈለገ ይመስል ከሌላ ምትሃተኛ ጋር ተገጣጠምኩ ። ይሄኛው ደግሞ በሙሉ ልብስ ዝንጥ ያለ ነው ። የያዛትን ዣንጥላ አንዴ ይደገፋታል ፣ ሌላ ግዜ ይዘረጋታል ። እየሰራ ያለውን ነገር በግልጽ እንድትረዱት ለማድረግ የግድ ስዕላዊ ገለጻ መጠቀም አለብኝ ። ለምሳሌ ያህል መደገፊያው ራቅ ያለ ምርጥ ሶፋ ላይ እግራችሁን አንፈራጣችሁ ቁጭ ብላችኃል እንበል ። ቀስ ተብሎ ሶፋው ከስራችሁ ሸርተት ቢደረግ ቁጭ እንዳላችሁ ትቀራላጭሁ ወይስ ሚዛን ስለማይኖራችሁ ትወድቃላችሁ ? መልሱ ግልጽ ነው ። እንግዲህ ይህ ምትሃተኛ አየር ላይ የተቀመጠው ሶፋው ከተነሳበት በኃላ መሆኑ ነው ። ሙሉ ሚዛኑን እየተቆጣጠረ ያለው በሁለት እግሩ ነው ። እስኪ ሞክሩት ።
ወገብዋ እንክትክት ቢል ግን የለሁበትም ።

አየርን ተደግፎ መቀመጥ

ከገበያው ግርግር ወጥቼ አስገራሚ ስነጥበብ ያረፈባቸውን ህንጻዋች ፣ ሙዚየሞችና የስዕል ጋለሪዋች እየተመለከትኩ ስጔዝ እግሬን አልበርት ወደብ አካባቢ አገኘሁት ። እየቸኮልኩ ነበር ። ምክንያቱም እዚህ ሀገር የሚጨልመው ከቀኑ አራት ሰዓት / በእኛ 10 /  ጀምሮ በመሆኑ ብርሃንን መሻመት አለብኝ ። ጠዋት አንድ ሰዓት ሆኖም ጨለማው እንደተዘፈዘፈ ነው ። ካላወቁ ጠዋት ቀጠሮ ይዘው እንኴ « እረ አልነጋም » ብለው ይተኛሉ ። አስራ ሁለት ሰዓት ሲሆን የምሽት ስንብትንና የመንጋት መምጣትን ወፎች በጨኀት አያበስሩም ። ለነገሩ የቤት ርግብ እንጂ ወፍ ይኑር አይኑር ርግጠኛ መሆን አልቻልኩም ። ውስን ወፎች ቢኖሩ እንኴ እንቅልፋሙን ሰው የመቀስቀስ ግዴታ የሌለባቸው ይሆናል ። ምክንያቱም ይህ ዴሞክራሲ የበዛበት እንግሊዝ ነውና ። ስለዚህ ጠዋት ስራ ገቢ ከሆኑ ሰዓት ሞልተው ጆሮዎ ስር አላርሙን በወፍ ዜማ ማስጮህ ይኖርቦታል ።

ይሄ የመምሸት ነገር ግን እንደሚመስለኝ ቀን ያለ ሰዓቱ ወደ ምድር የሚወረወረው ተፈጥሯዊ ሬንጅ በማግስቱም ከመሬት ለመላቀቅ የሚገጥመው ፍትጊያ ቀላል አይደለም ። እጅ ላይ የፈሰሰ የበረሃ ሙጫ በሉት ። « ወግድልኝ » ብትሉትም ሙጭጭ ብሎ እየተሳበ የሚልመጠመጥ ። እናም እስከ የካቲት ድረስ ጸሃይ ብቻ ሳትሆን ቀንም ራሱ ብርቅ ይሆናል ነው የሚባለው ።

በስመዓም ... አልበርት ወደብ በጣም ይጎበኛል ። ከጥንታዊነቱም ከዘርፈ ብዙ አገልግሎት ሰጪነቱ አኴያ ሊሆን ይችላል ። በ1846 ነው የተገነባው ። ይሁን እንጂ ቡና ቤቶች ፣ ሱቆች ፣ ሆቴሎች ፣ የባህር ትራንዚትና የአለማቀፍ ባርነት ሙዚየሞች እንዲሁም የ ዘ ቢትልሶችን ታሪክ አቅፎ ይዟል ። በግዜውም በያዘው ሰፊ ቦታና ተግባር ከዓለማችን ቁጥር አንድ ነበር ።

የከተማው አዛውንቶች ታዲያ ዉሻ እያስከተሉ ነው ወደቡን የሚጎበኙት - በልብስ ያጌጡ ውሾች ። ውሾቹ ግን የሌላ ሀገር ምርጥ ተሞክሮ እጥረት ያለባቸው ነው የሚመስሉት ። ምክንያቱም መናከስ፣ ማስደንገጥ ቢያንስ መጮህ የተባለውን የዘመዶቻቸውን ቌንቌ የት እንዳደረሱት አይታወቅም ። ማንም ቢያባብላቸውና ቢደባብሳቸው ግድ የላቸውም ። የሚታያቸው ቶሎ ብሎ የውስጥ ገላቸውን ፈርከስከስ አድርጎ ማቅረቡ ነው ። ዉሻ ካልጮኀ ደግሞ በግ ሊመስል ይችላል ። የሀገሬ ሰው ግድጔድ ቆፍሮ ቀብሮ ፣ ቢቻል ተርብ እያበላ አሳድጎ ዉሻው ጸጉረ ልውጥ ሰው ጅርባ ላይ ፊጥ ሲልማ መመልከት ይፈልጋል ። አለዚያማ እንደ አውደልዳይ ዉሻ መንገድ ላይ ይጣላል ። የዚህ ሀገር ዉሾች ውሎአቸው መኪናና ቡናቤት አዳራቸው ደግሞ ሳሎን ነው ። ውሻ የሚያሳድጉበት ዋና አላማም ሰውንም ሆነ ሌባ ማስደንገጥ አይመስልም ። ታዲያ ምንድነው ከተባለ የእንስሳት ፍቅር ወይም ሆቢ ብሎ ማለፍ ይቻላል ።

         እንዳልኴችሁ የሊቨርፑል ወደብ ከተማዋ እንድታድግ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጔል ። ይህን ወደብ ጨምሮ ስድስት የሚደርሱ አካባቢዋችም በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ መዝገብ ውስጥ የሰፈሩ ናቸው ። ታዋቂው ብዕረኛ ቻርልስ ዲከንስም  ወደቡን « ሃብታሙና ማራኪው » በማለት ነበር የገለጸው ።

አልበርት ዶክ 

በነገራችን ላይ ዳንኤል ዴፎ ፣ ዋሽንግተን ኢርቪንግ ፣ ቻርልስ ዲከንስና ሌሎች ታዋቂ የጥበብ ሰዋች ሊቨርፑልን ጎብኝተዋል ። ደጋግሞ በመጎብኘት ምናልባትም አስራ ሁለት ግዜ ዲከንስን የሚያህል የለም ። ደራሲው ደጋግሞ የሚመጣው መጽሀፎቹን ለመጻፍ ይረዳው ዘንድ አንዳንድ ነገሮችን ለመመርመር ፣ መድረክ ላይ ተጋብዞ ለመናገርና የራሱን ስራዎች ለማንበብ ነው ። እንደሚታወቀው ሃያ የሚደርሱ መጽሀፍትን ለአንባቢያንን አበርክቶ ነው ያለፈው ። ስነጽሁፍ በኮሌጅ የተማረም Great expectation , Oliver twist , A tale of two cities , Hard times እና The pick wick papers የተባሉ ስራዎቹን አይረሳም ። እኔ በወቅቱ ዲክንስ ከአደፍርሱ ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ ጋር ይመሳሰልብኝ ነበር ። ሁለቱም ቃላትን አጥብቀው የሚወዱ ፣ በቃላት መራቀቅ የሚፈልጉ « Wordy » የሚባሉ አይነቶች ናቸው ። ጹሁፉን በአግባቡ ተረድተን የቤት ስራችንን ለመስራት በጣም እንቸገር ነበር ። አደፍርስንስ ስንት ግዜ ነው እየጀመርኩ የተውኩት ? የቁጠኛውን ዳኛቸውን ባላውቅም ዲክነስ ፍጹም የመድረክ ተናጋሪና ተከራካሪ እንደነበር መዛግብት ያስረዳሉ ። ዲክነስ እንደ ንግግሩ ሁሉ ጹሁፎቹ ለጥቅስ የሚበቁ ናቸው ። ለዛሬ ግን የሚከተለውን ላስታውስለት ፣

« No one is useless in this world who lightens the burden of another . »

ከአልበርት ወደብ አካባቢ ሆኖ ጀምስ መንገድ ላይ የሚገኘው የአልቢዎን ሀውስ ይታያል ። ይህ ህንጻ ሲነሳ ደግሞ ሊቨርፑልና ታይታኒክ የተባለችው ታሪካዊ መርከብ የነበራቸውን ጥብቅ ቁርኝት መረዳት ያስችላል ። እንደሚታወቀው ከመርከቧ የፈት ገጽ ላይ ታይታኒክ ከሚለው ጽሁፍ በታች Liver Pool የሚል ጽሁፍ ይታያል ። ይህ የሆነው የካምፓኒው ጽ/ቤት / አልቢዎን  ሀውስ / እዚህ በመገኘቱ መርከቧ የተመዘገበችው በከተማው ስም ስለሆነ ነው ።

የታይታኒክ ማዋለጃ ቤት

ታይታኒክ የተጸነሰችውም ሆነ የመጨረሻውን ዲዛይን የያዘችው በሊቨርፑል ይሁን እንጂ ነፍስ ዘርታ መንቀሳቀስ በጀመረችበት ወቅት ሊቨርፑልን ማየት አልቻለችም ። ሌላው ቁርኝት ከመርከቧ ሰራተኞች 90 ያህሉ በተለይም ታይታኒክ ከበረዶ ጋር ስትጋጭ የተመለከቱትን ሁለት ሰዋች ጨምሮ የተቀጠሩት ከሊቨርፑል መሆኑ ነው ። ፊልሙን ባየነው መሰረት የሰውየው አጯጯህ  እንዴት ነበር ? « የበረዶ ቌጥኝ ይታየኛል ! ... የበረዶ ቌጥኝ ይታየኛል ! ... » ምን ዋጋ አለው አንዳንዶች ዘግይቶ ሪፖርት አድርጔል በማለት ከርፋፋ ሲሉት ሌሎች ደግሞ ስራውን በአግባቡ የተወጣ ጀግና ያደርጉታል ። መርከቧ ስትሰምጥ ምንም ሳያቌርጡ ሲዘፍኑ የነበሩ ሙዚቀኞችን እንዲሳፈሩ ያደረጋቸው ወኪል የሚገኘውም በሊቨርፑል ነው ። ባይሆን የሙዚቀኞቹ ነገር እጅግ ይገርማል ። ሰው ህይወቱን ለማትረፍ ላይ ታች ሲራኮት የእነሱ ነፍስ ግን በሙዚቃው ሃይል ውስጥ ተውጦ ነበር ። ሊቨርፑልና የሙዚቃ ፍቅርን በማያያዝ እነዚህ ሰዎች ሊቨርፑዲያን ነበሩ ማለት አይቻል ይሆን ? አላውቅም ። የመርከቧ የሞተር ክፍል / Engine / የተሰራውም ሊቨርፑል በሚገኝ ድርጅት ነው ። ለታይታኒክ ሞተር ክፍል ሰራተኞች መታሰቢያ ይሆን ዘንድ በዋተር ፍሮንት ሃውልት ቆሟል ።

ይህ ታሪካዊ ህንጻ በአሁኑ ወቅት ምን እየተሰራበት እንደሆነ ባላውቅም / ምናልባትም ለሽያጭ ቀርቦ ይሆናል / እንደ ታሪካዊነቱ በአግባቡ የተያዘ አይመስልም ። ሶስቱ በግማሽ ጨረቃ ቅርጽ የተሰሩት የፊት ለፊት በሮቹ ተዘግተዋል ። በጎን በኩል የሚገኘውም እንደዚሁ የታሸገ ነው - የዚህኛው ልዩነቱ ከበሩ ጀርባ የቆሻሻ ክምር መታየቱ ነው ። ምናልባትም የታይታኒክ ቅርጽ ይኖረው ይሆን በሚል ጥርጣሬ ራቅ ብዬ አጠናሁት ። ባለ ሶስቱ ፎቅ ህንጻ በምንም ተዓምር መርከቢቷን አይመስልም ። እረ ታይታኒክ ቅንጡ ህንጻ ነበረች ። ለነገሩ ለግንባታዋ የፈሰሰው ዶላር ቀላል አይደለም -  7.5 ሚሊየን ። 3547 ሰዎችን አሳፍራ በኩራት ነበር ባህሩን የምትሰነጥቀው ። አጠቃላይ ቁመቷም ቢሆን 11 ፎቅ ርዝመት ካለው ህንጻ ጋር የሚተካከል ነው ። ውስጧስ ቢሆን ዘመናዊ ሆስፒታልን ጨምሮ ምን የሌላት ነገር አለ ?

ህንጻውን እየራቅኩት ስሄድ በሆነ ነገር ላመሳስለው እየፈለኩ ነበር ። በል ቻዎ ስለው የታይታኒክ ማጀቢያ የሆነው የሴሊንዲዮን my heart will go on የሚለው ዜማ ከየት አባቱ እንደመጣ አላውቅም ። ውስጤ ለአፍታ ያህል የተንጫጫ መሰለኝ ፣

Every night in my dream
I see you , I feel you
That is how I know you go on
Far across the distance
And spaces between us
You have come to show you go on
Near , far , wherever you are
I belive that the heart does go on
Once more you open the door
And you’re here in my heart
And my heart will go on and on


እቺ ከአየርላንዱ ደብሊን እና ከጀርመኗ ኮሎኝ መሃል የምትገኝ መካከለኛ ከተማ የፊልም አምራች ድርጅቶችንም ቀልብ መግዛት የቻለች ናት ። captain America , In the name of the father , Sherlock holmes , Fast and furious 6 , Harry potter and the dealthy hallows የተባሉ ትላልቅ ስራዋችን ጨምሮ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ፊልሞች ተቀርጾባታል ።

ዛሬ እነዚህ ታሪካዊ ቦታዋች በሙሉ ዋና ትኩረታቸው የፊልም ኢንዱስትሪውንና ጊነስ ቡክን መሳብ ሳይሆን በቅርቡ የሚከበረውን የገና በዓል ደማቅ ማድረግ ይመስላል ። Remember , if Christmas isn’t found in your heart , you won’t find it under a tree . የሚለው አባባልም ለበዓሉ የሚሰጠውን ግዙፍ ክብር አመልካች ነው ። ለማንኛውም መልካም ገና ይሁንላቸው ማለት ይገባል ።

ግልባጭ ፣
ጥቂት ቆይቶ ብቅ ለሚለው አትዮጽያዊው ገና ።

Wednesday, December 11, 2013

አሳዛኙ የመንግስት ሰራተኛ




የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚጠቁመው ኢትዮጽያ ውስጥ ከአንድ ሚሊየን በላይ የመንግስት ሰራተኞች ይገኛሉ ፡፡ እነዚህ ሰራተኞች አባቴ ለሚሉት መንግስት አቋርጠው የማያውቁት ጥያቄ ‹ ኑሮ ስለከበደኝ ደመወዝ ጨምርልኝ ! › የሚል ነው ፡፡ በቀደመው አሰራር ሰራተኞች በየሁለት አመቱ ጥቂትም ብትሆን የእርከን ጭማሪ ያገኙ ነበር ፡፡ ይህም ሁልግዜ ከፊታቸው የተንጠለጠለ የተስፋ ዳቦ እንዳለ ስለሚጠቁማቸው ለመጨበጥ ይተጉ ነበር ፡፡  / ርግጥ ነው በአንድ ወቅት 320 ብር የነበረውን ደመወዝ 420 ፤ 3152 የነበረውን የመምሪያ ኃላፊ ደመወዝ 4343  ያስገባ ጭማሪ ተከናውኗል  ፤ ያው በወሩ ጭማሪው ሻጭና አከራይ እጅ ተገኘ እንጂ /

‹‹ በመርህ ደረጃ ኑሮ እየከበደ እንደሚሄድ እገነዘባለሁ ፤ ግና በተወሰነ ርቀት ብር መጨመሩ ሳይንሳዊና አዋጪ አይደለም ! ›› የሚለው ኢህአዴግ ሰራተኛው ማደግ የሚገባው የሚታይና የሚቆጠር ሀገራዊ እድገት ሲያበረክት ነው በሚል የቆየው አሰራር ላይ ‹ ታሽጓል › የሚል ወረቀት ለጥፎ ነበር - በአራት ነጥብና በቃል አጋኖ በመታገዝ  ፡፡
‹‹ ታዲያ እስከዛስ ችግሩን እንዴት እንቋቋም ? ›› አባቴ የሚሉት ሰራተኞች ባገኙት የስብሰባ አጋጣሚ ሁሉ ጥያቄያቸውን ወረወሩ ፡፡

‹‹ በረሃብና በስቃይ ቀቀለን እኮ ?! ›› በየኮሪደሩና በየመሸታው ቤት ይህን ስሜት የተነፈሱት ደግሞ ኢህአዴግን የእንጀራ አባት ብለው የደመደሙት ናቸው ፡፡

የደመወዝ ጥያቄ ከለውጥ መሳሪያዎች አንጻር

መንግስት ለሁሉም ወገኞች በቂ ምላሽ መስጠት የሚቻለው ሳይንሳዊ አሰራርን በመዘርጋት ነው በሚል የጥናት ቁፈሮ ጀመረ ፡፡ ማዕድንን ፈልጎ ለማውጣት አታካች አመታትን አሳልፏል ፡፡ በመጨረሻም ቢፒአር / Business Process Reengineering / የተባለ የከበረ ድንጋይ መገኘቱ ይፋ ሆነ ፡፡ ከወጪ ፣ ግዜ ፣ ጥራትና ደረጃ መመዘኛዎች አንጻር አሰራሩ ቀልጣፋ ፣ ፍትሃዊና አንጀት አርስ መሆኑ ተነገረለት ፡፡ ሰራተኞች የፍልስፍናውን ሀሁ በየተቋማቸው በሶስት ቀን ጥልቅ ጥናት ከአኩዋ አዲስ ጋር አጣጣሙት ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ብዙዋቹ ቀድመው መማር የፈለጉት ስለ ደመወዝ የሚያትተውን ምዕራፍ ነበር ፡፡ ይህ ምዕራፍ ግን እዚህ ጥራዝ ውስጥ አልነበረም ፡፡ እንደውም ትንሽ ቆይቶ ሀሴትን ሳይሆን መርዶን ማዘሉንም አበሰረ ፡፡ ጥቂት የማይባሉትን ከእኔ አሰራር ጋር መጓዝ አትችሉም ፣ የትምህርት ዝግጅታችሁ በቂ አይደለም ፣ አመለካከት ሲቀነስ የተንጠለጠለ ብቃት እኩል ነው  C  ማይነስ በሚል ከስራ ዉጪ አድርጓቸዋልና ፡፡ በአንዳንድ መ/ቤትማ ብቀላና ፖለቲካ ስራቸውን ሰርተዋል ፡፡

ከአውሎ ንፋሱ የተረፉት ጥናቱን ተግባራዊ ለማድረግ ማበረታቻና የደመወዝ ጭማሪ የግድ ያስፈልጋል የሚል ዳግማዊ ጥያቄ ከማንሳት አልተቆጠቡም ፡፡ መንግስትም የሰራን ለመሸለምና ለማሳደግ የሚቻለው የዚህን ተከታይ ሳይንስ እውን በማድረግ ነው በሚል ሌላ ቁፋሮ ውስጥ ገባ ፡፡ ከአመታት በኃላም ሚዛናዊ የውጤት ተኮር / Balanced Score Card / ስርዓትን አስተዋወቀ ፡፡ በዘጠኝ ደረጃዎች የተዋቀረው ውጤት ተኮር ከስትራቴጂ ግንባታ ጀምሮ እስከ ክትትልና ግምገማ ድረስ የሚዘረዘር ነው ፡፡ ጥናቱ እንደ አሹ ቤት ስጋ የሚያስጎመዥ ነው ፡፡ በደረጃ ሰባት ላይ የሚገኘው ‹‹ አውቶሜሽን ›› የእያንዳንዱን ፈጻሚ ስራ መመዝገብና መተንተን የሚችል በመሆኑ ሰራተኛውን ከለጋሚው ለመለየት የሚያስችል ነው ተብሏል ፡፡ በሌላ አነጋገር አጭበርባሪው ፊርማ ፈርሞ ሹልክ ማለት ወይም መድረክ ላይ በሚያቀርበው አስመሳይ ተውኔት ብቻ ተላላ ሃላፊዎችን መሸወድ አይቸልም ፡፡ ፋብሪካና ኢንድስትሪ ውስጥ ባይሆንም ከቢሮ የሚታደለውን ስራ ቆጥሮ ይረከባል በኃላ ደግሞ ቆጥሮ ያስረክባል -  ይህ ማለት ግን የሚሰራው ንብረት ክፍል ውስጥ ነው ወይም ከጥበቃ ስራ ጋር በስተደቡብ ይዋሰናል ማለት አይደለም ፡፡ በፍጹም ፡፡ ርግጥ ነው ሳይንሱ አንድ ኃላፊ እንደ ጥበቃም እንደ ንብረት ክፍል ኤክስፐርትም ሁለገብ እንዲሆን ያበረታታል ፡፡ እንግዲህ በዚህ ምክንያት ነው ሳይንሱ ስራና ሰራተኛን ያገናኛል የተባለለት ፡፡

በመሆኑም ምርጥ ፈጻሚዎች ተገቢውን ሽልማትና የደመወዝ እድገት ለማግኘት እንዲችሉ በመነገሩ ስራው ተጧጧፈ ፡፡ በአንዳንድ ተቋማት የምርጥ ፈጻሚዎችና ምርጥ አመራሮች ፎቶግራፍ ሳይቀር መለጠፍ ጀመረ ፡፡ አመቱ መጨረሻ ላይ ሽልማትና ዕድገት የሚጠበቅ ቢሆንም መንግስት እፍርታም ሆነ ፡፡ ለምርጦች እውቅና ከመስጠት ይልቅ በርካታ ምክንያቶችን መደርደርን ‹‹ ደረጃ አስር ›› አደረገው ፡፡ ግምገማው ትክክል አይደለም ፣ በተቋሙ መሰረታዊ ለውጥ ካልመጣ ሰራተኞችም የተለየ አፈጻጸም ሊኖራቸው አይችልም … የሚሉትን እንደ ዋና ዋና ማሳያነት ማነሳሳት እንችላለን ፡፡

ዛሬ አገር ጥለው የሄዱት የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር አቶ ጁነዲን ሳዶ በአንድ ወቅት የመንግስት መ/ቤቶች ቢፒአርን እንዴት እንደሚጠቀሙበት በቂ ትኩረትና ዝግጅት ሳያደርጉበት ወደ እንቅስቃሴ በመግባታቸው መፍትሄ ሊያመጣ አልቻለም በማለት መግለጫ ሰጡ ፡፡ ለነገሩ ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው እንዲሉ ሆኖ እንጂ ቢፒአርና ቢኤስሲ ስልጠና ሲሰጥ ብዙ ቸግሮች መኖራቸውን መስማት ነበረባቸው ፡፡ አንደኛው ችግር በስልጠናው ወቅት ከሰራተኛው የተነሱ መሰረታዊ ጥያቄዎችን አሰልጣኞች በበቂ ሁኔታ መመለስ አለመቻላቸው ነው ፡፡ እናም አሰልጣኞች ወዴት እየሄዳችሁ ነው ? ሲባሉ ‹‹ ያልገባኝን ነገር ላልገባቸው ሰዎች ልነግርን ነው ›› አሉ ተብሎ እስካሁንም ይቀለዳል ፡፡

የመንግስት ሰራተኛው ሁለቱን የለውጥ መሳሪያዋች ለማስፈጸም ዛሬም እየተንገታገተ ቢሆንም ቃል በተገባለት የደመወዝ ጭማሪና በሳይንሳዊ አሰራሮቹ መካከል ያለው ተጨባጭ ቁርኝት ሊገለጽለት አልቻለም ፡፡ ብዙ ተቋማት ውስጥም የለውጡ ስራ መሬት የወረደ ፣ የሚታይና የሚቆጠር ከመሆን ይልቅ አንዳንዶች ‹ ኮስሞቲክ › እያሉ እንደሚጠሩት ሳምንታዊ ቅጽ መሙላት ፣ ደረት ላይ ባጅ ማድረግ ፣ ጠረጼዛ ላይ ስምና የስራ ድርሻን ማስተዋወቅ እየሆነ መጥቷል ፡፡ የአዲሱ አሰራር ግብ ይህ አይደለም ፤ ሰራተኛው አዲሱ አሰራር / ሳይንስ / ህይወቴን ለመቀየር የሚያስችል መሰረት የለውም የሚል ድምዳሜና የጥርጣሬ ዳርቻ ላይ አዳርሶታል ፡፡ የዚህ ውጤት ደግሞ መርፌ ከለገመ ቅቤ መብሳት አይችልም የሚባለውን ብሂል ይኮረኩራል ፡፡

አድጎ ያላደገው የውሎ አበል

ሌላው የመንግስት ሰራተኞች መሰረታዊ ጥያቄ የውሎ አበል ጉዳይ ነው ፡፡ እንደሚታወቀው ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ ሲሰራበት የቆየው የውሎ አበል ክፍያ ዝቅተኛው 35 ከፍተኛው ደግሞ 70 ብር ነበር ፡፡ ይህ ክፍያ በተለይም ከ 2000 ዓም በኃላ አስቂኝ ገጽታ ይዞ ነበር ፡፡ ሰራተኛው እንደነገሩ የቆመ አልቤርጎን በ70 ብር ተከራይቶ ምግብ ሳይበላ ነበር በፈጣሪ ቸርነት ስራውን ሲሰራ የቆየው ፡፡ ይህ ችግር የመስክ ሰራተኞች መኪና ውስጥ እንዲያድሩ ፣ በየሄዱበት ዘመድ ብቻ ሳይሆን ዘመዳቸው ድንገት የተዋወቃቸውን ሰዎች እንዲፈልጉ ፣ አንድ አልጋ ለሁለትና ሶስት ሆነው እንዲከራዩ አድርጓቸዋል ፡፡

ከስንት አቤቱታ በኃላ አዲሱ የውሎ አበል ታህሳስ 27 ቀን 2004 ዓም በሚኒስትሮች ም/ቤት ቀርቦ ጸደቀ ፡፡ በዚህ ግዜ አልጋ ብቻ ሳይሆን ኑሮ ጣራ ያለፈበት በመሆኑ አበሉ ከፍተኛ እንደሚሆን ተጋኖ ተወርቶለት ነበር ፡፡ መንግስትም ለማስተካከያ 465 ሚሊየን 838 ሺህ ብር ተጨማሪ ማድረጉን ገለጸ ፡፡ ይህ ትልቅ የሚመስል ገንዘብ ሲተነተን ግን የብዙዎቹን አንገት አስደፋ ፡፡ አበሉ ወረዳን ፣ ዞንና ዋና ከተሞችን ብቻ ሳይሆን የደመወዝ እርከንንም ከፋፍሎ የሰራ ሆነ ፡፡ ለምሳሌ ያህል እስከ 2248 ብር ደመወዝ የሚከፈላቸው ሰራተኞች ሃዋሳ ከሄዱ 182 ብር ፣ ከ2249 እስከ 3816 ብር ደመወዝ የሚያገኙ 192 ብር ፣ ከ3817 ብር በላይ ደመወዝ ተከፋዮች ደግሞ 201 ብር ያገኛሉ ፡፡ ይህ በዋና ከተማ ደረጃ በመሆኑ ትልቁ ክፍያ ነው ፡፡ ሰመራ ፣ ባህርዳር ፣ ድሬደዋ ወዘተ ሲጓዙ ደግሞ የገንዘቡ መጠን እየቀነሰ ይመጣል ፡፡ ትንሹ የአበል ክፍያ እንደቅድም ተከተሉ 83 ፣ 92 እና 101 ብር ነው ፡፡

ብዙ የተወራለት የአበል ጭማሪ የወቅቱን የሆቴሎች የአገልግሎት ዋጋ ፍጹም ያላገናዘበ ነው ፡፡ አንድ ተራ አልጋ 90 እና 100 ብር በሚጠራበት በአሁኑ ወቅት 111 ብር ይዞ ከቤተሰብ መራቅን የመሰለ መሳቀቅና ቅጣት ከየት ይገኛል ? ይህ መስተካከልን የሚጠይቅ አንደኛው ችግር ሲሆን ሁለተኛው  ለመስክ የሚወጣን ሰራተኛ በአበል ማበላለጡ ተገቢ ያለመሆኑ ጉዳይ ነው ፡፡ አልጋውና ምግቡ እንደሆነ ለሁሉም እኩል ነው ፤ ታዲያ - የቢሮ ቢሮክራሲ ጫካና በረሃ ድረስ አብሮ እንዲጓዝ መፍቀድን ምን አመጣው ? በስራው ውጤት ከመጠበቅና ከፍትሃዊነት አንጻርም  ፍጹም የማይጠቅምና ትክክል ያልሆነ  አሰራር ነው ፡፡

የተጋነነ የታክስ መጠን

የኑሮ ውድነቱ ጫና በደመወዝ ጭማሪም ሆነ በውሎ አበል ማካካስና ማስተካከል ያልቻለው የመንግስት ሰራተኛ በመንግስት አይን እንቁላል የሚጥል ዶሮ ነው ወይም ሳያንገራግር የሚታለብ ላም ፡፡

የመንግስት ሰራተኛ እንደሌሎች ነጋዴዎች ወይም ባለሀብቶች የስራ ግብርን ለማስቀረት ፣ ለማስቀነስ ፣ ለማጭበርበር የሚያስችል መሰረት የለውም ፡፡ ምክንያቱም ግብሩ የሚቆረጥበት ገና ደመወዙን ከመቁጠሩ በፊት ነውና ፡፡ ዜጎች ግብር የመክፈል ግዴታ ያለባቸው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሁሉም  ዜጋ ግብርን መክፈል ያለበት ፍትሃዊና እኩል በሆነ አግባብ መሆኑ አያጠያይቅም ፡፡ ይሁን እንጂ ትንሹ ደመወዝተኛ ትልቅ ግብር እንዲከፍል መደረጉ ያሳምማል ፡፡ በአመት ብዙ መቶ ሺህና ሚሊየን ብር የሚያስገቡት ነጋዴዎች ግብር በዛብን ብለው በመደራደርና በማስቀነስ ከገቢያቸው ጋር የማይመጣጠን ገንዘብ እየከፈሉ ጉልበት በሌለውና መድረሻ ቢስ በሆነ  ዜጋ ላይ መጨከን አግባብ አይደለም ፡፡

አንድ ምሳሌ እንውሰድ ፡፡ በህጉ ቀመር መሰረት ከታክስ ነጻ የሚሆኑት እስከ 150 ብር ገቢ ያላቸው ዜጎች ናቸው ፡፡ ከ 151 እስከ 650 ብር የሚያገኝ ሰው 10 ከመቶ ፣ ከ651 እስከ 1400 ብር የሚያገኘው 15 ከመቶ ፣ ከ1401 እስከ 2350 ብር የሚያገኙ 20 ከመቶ ፣ ከ2351 እስከ 3550 ብር የሚያገኙ 25 ከመቶ ፣ ከ3551 እስከ 5000 ብር የሚያገኙ 30 ከመቶ ፣ ከ5000 ብር በላይ የሚያገኙ ደግሞ 35 ከመቶ ይቆረጥባቸዋል ፡፡ ርግጥ ነው በሁሉም ስሌት ላይ ተቀናሽ የሚሆኑ ጥቂት ገንዘቦች አሉ ፡፡

በወር 3817 ብር ደመወዝ የሚያገኙት አቶ ፍርድ ያጣው 30 ከመቶ የግብር እዳ ሲከፍሉ  አንድ ሺህ 145 . 10 ያጣሉ ፡፡ በቀመሩ መሰረት 412 .50 ሳንቲም ሲቀነስላቸው 732 .60 በየወሩ ግብር ይከፍላሉ ማለት ነው ፡፡ ከዚህ ላይ ሰባት ከመቶ የጡረታው ሲወራረድ  267 .19 ይቀነስባቸዋል ፡፡ በአጠቃላይ ግብርና ጡረታው 999 .79 ስለሚያሳጣቸው ለግዜው ኪሳቸው የሚገባው ገንዘብ 2818 ብቻ ነው ፡፡ ለግዜው ያልኩት ድምር ውስጥ ያልገቡ መዋጮችን በማስቀረቴ ነው ፡፡

እዚህ ላይ ሶስተኛው የፖለቲካ አማራጭ ይሁን መንገድ እከተላለሁ የሚሉትን የአቶ ልደቱ አያሌውን ሀሳብ ማድነቅ ግድ ሊል ነው ፡፡ እኚህ ፖለቲከኛ በአንድ ወቅት ለመንግስት ሰራተኛ ደመወዝ ከመጨመር ይልቅ የተጋነነውን ታክስ መቀነስ ይጠቅማል ብለው ነበር ፡፡ እሳቸው ያነሱት ከኢንፍሌሽንና ከነጋዴው ነጣቂ እጆች ለማስቀረት በሚል ቢሆንም እኔ ደግሞ ከፍትሃዊነት አንጻር ጭምር የሚለውን እጨምርበታለሁ ፡፡ አህያውን ፈርቶ ዳውላውን ለመንግስት ሰራተኛው መስራት አይኖርበትም ….

የአቶ ፍርድ ያጣው የበዙ ቃል ኪዳኖች

በ80 ቢሊየን ብር ወጪ 5250 ሜጋዋት እንዲያመነጭ እየተገነባ ያለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ የገንዘብ መሰረቱን ሀገር ቤት ነው ያደረገው ፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ የስራው 24 ከመቶ ተጠናቋል ፡፡ ለግንባታው ቃል ከተገባው 10 .2 ቢሊየን ብር ሊሰበሰብ የቻለው ግን 5.2 ቢሊየን ብር ብቻ ነው ፡፡

ቃል የገቡ ሰዋችና ድርጅቶች ሀሳባቸውን ለምን አጠፉ ? ወይም ለመክፈል ለምን መዘግየት ፈለጉ ? ብዙ የመላ ምት ምክንያቶችን መደርደር ይቻላል ፡፡ በጣም የሚያስገርመው ግን የመንግስት ሰራተኛ እንደሌሎቹ ቃሌን አጥፋለሁ ወይም ‹ ይብራብኝ › ቢል እንኳን አለመቻሉ ነው ፡፡ ምክንያቱም አንድ ሰራተኛ ሙሉ ደመወዙን በአመት ለመክፈል ቃል ከገባ ልክ እንደ ግብሩ ደመወዙን ከመጨበጡ በፊት በሂሳብ ክፍል ተቆርጦ ስለሚወሰድበት ፡፡ ስለዚህ አሁንም የመንግስትን ሰራተኛ ታማኝ ፣ ማምለጫ የሌለው ፣ ሳያንገራግር የሚታለብ ወዘተ ልንለው እንችላለን ፡፡ የህዳሴ ግድብ ግንባታ 76 ከመቶ ገና የሚቀር በመሆኑ ለቀጣይ አራትና አምስት አመታት አሁንም እንደ መርግ ከተጫነው ኑሮ ጋር የተለመደውን ክፍያ ቃል እየገባ ወይም ቃል እየተገባለት እንደሚከፍል ሳይታለም የተፈታ ነው ፡፡

አሁንም የ3817 ብር ደመወዝተኛውን አቶ ፍርድ ያጣውን እናምጣቸው ፡፡ የወር ደመወዛቸውን በአመት ለመክፈል ቃል ከገቡ በየወሩ የሚያስቆርጡት 318 ብር ይሆናል ፡፡ በግብርና ጡረታ 999 ብር ያጡት እኚህ ሰው ከግድቡ መዋጮ ጋር ሲደመርላቸው 1317 ብር ያስከረክማሉ ፡፡ በኪሳቸው የሚገኘው የተጣራ ገንዘብ ደግሞ ወደ 2500 ያሽቆለቁላል ፡፡

እንደሚታወቀው የሚኒስትሮች ም/ቤት የጤና መድህን ኤጀንሲ ማቋቋሚያ አዋጅን በ2003 አጽድቋል ፡፡ የኤጀንሲው አላማ በየተቋማቱ የጤና መድህን የሚስፋፋበትን መንገድ ማመቻቸት ነው ፡፡ ለዚህ ደግሞ የመንግስት ሰራተኞች ከደመወዛቸው ላይ 3 ከመቶ መዋጮ ያደርጋሉ ፡፡ ይህም ስርዓት በቅርቡ እንደሚጀመር በየተቋሙ ኦሪየንቴሽን ተሰጥቷል ፡፡ በመሆኑም የደመወዛቸው ሶስት ከመቶኛ ሲሰላ 114 ብር ነው ፡፡ ከደመዛቸው ላይ የሚያስቆርጡት ገንዘብ 1431 ሲመጣ ኪሳቸው የሚቀረው የተጣራ ብር ደግሞ 2386 ይደርሳል ፡፡ አቶ ፍርድ ያጣው አንገታቸውን አቀርቅረው ስለሚኖሩ ቤት አከራያቸው ለረጅም ግዜ ታሪፍ አልጨመሩባቸውም - በመሆኑም ለሁለት ክፍል ቤት በየወሩ 1200 ብር ይወረውራሉ ፤ ይህም የተጣራ ደመወዛቸውን 1186 ያደርሰዋል ፡፡ ከቤት ኪራይ ጫና ብቻ ሳይሆን ከአንዳንድ አከራዮች ግፍ ለመገላገል ኮንዶሚኒየም የተመዘገቡ ቢሆንም እድላቸውም እንደ ኪሳቸው ‹ ድሃ › ሆኖ አስካሁን ስማቸውን አዲስ ልሳን ጋዜጣ ላይ ሊመለከቱት አልቻሉም ፡፡

በቅርቡ የአዲስ አበባ መንግስት አዲስ ደንብ በማውጣቱ ለሁለት መኝታ ቤት በየወሩ 561 ብር ባንክ ማስቀመጥ ግዴታ ሆኖባቸዋል - በዚህም ምክንያት የተጣራ ደመወዛቸው 625 ብር ብቻ ነው ፡፡ ‹ ዘመድ አዝማድ  ለ4 ሺህ ጥቂት የጎደለው ብር  ይገሸልጣል እያለ ቢያማኝም እኔን ማቆሚያ የሌለው መዋጮ ደህና አድርጎ እየገሸለጠኝ ነው › የሚሉት  አቶ ፍርድ ያጣው በየቀኑ ለሚጨምረው ወርሃዊ አስቤዛ ፣ ለልጆች ት/ቤት  ፣ ለልብስና ጫማ ፣ ለትራንስፖርት ፣ ለእድር ፣ ለህክምና ፣  የመሳሰሉትን ክፍያዎችን እንዴት እንደሚሸፍኑ ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው ፡፡ እንግዲህ ምርኮኛው ፣ የሚታለበውና ምስኪኑ የመንግስት ሰራተኛ በአስማት ነው የሚኖረው የሚባለው ለዚህ ነው ፡፡

ተረት ተረት  ?

መንግስት የመንግስት ሰራተኛውን ድካምና ጥረት ብቻ ሳይሆን የኑሮ ውድነቱንም ጫና ግንዛቤ ወስጥ በማስገባት ሰበቦቹን ከርክሞ በቂ የሚባል የደመወዝ ጭማሪ ማድረግ ይጠበቅበታል ፡፡ ሁለት ዲጂት እያደግን ባለንበት ወቅት ይህ አይቻልም የሚባል ከሆነ ደግሞ አንድ ዲጂትን በተግባር ማዋል ያቃተውን ሰራተኛ ለዚህና ለዚያ አዋጣ የሚለውን ልመናና ግዴታ መገደብ ይኖርበታል ፡፡ ቢያንስ ጥያቄውን ‹ አዋጅ › ከማድረጉ በፊት ገቢና ወጪውን ለአፍታ ያህል ማመዛዘንና ማስላት ይጠበቅበታል ፡፡

የላም በረት ? !



Tuesday, October 8, 2013

የመቻቻልን ሂሳብ ማን ይክፈል ?




መንገድ ሁሉ ስለተቦዳደሰ መንገድ የለም ፡፡ ታክሲ ሁላ ቀዳዳ መንገድ በመሸሹ ታክሲ የለም ፡፡ ይህን ችግር ያሰሉ ጥቂቶች ሲመጡ የሰው ንብ ይወራቸዋል  ‹‹ እስኪ አትራኮቱ አጭር መንገድ ነው የምንጭነው ! ›› ይላሉ ኢትዮጽያዊ የማይመስሉት ሾፌርና ወያላ ቀብረር ብለው ፡፡ ባቡሩ ይሰራልሃል የተባለው ከተሜ መስዋዕትነቱ ስለበዛበት እህህእያለ ለአጭሩ መንገድ ሁለት እጥፍ ይከፍላል ፡፡ ሁለት እጥፍ ከፍሎ እንኳ አንድ ወንበር ላይ ለሁለት መቀመጥ ከናፈቀው ቆየ ‹‹ የታክሲና የሰው ትርፍ የለውም  ! ›› የሚል አዲስ ሌክቸር በወያላው ይሰጠውና ትርፉን እንዲያቅፍ ወይም እንዲያዝል ይገደዳል ፡፡

ይህ በባቡሩ ዘመን አይደለም ቀድሞም ተለምዷል ፡፡ አንድ ቀን ግን እንዲህ ሆነ ፡፡
 
የትራፊክ ፖሊሶችን መጥፋት ወይም ቢኖሩም ከቁብ ባለመቁጠር የታክሲ ሾፌሮችና ወያላዋች መንገደኛውን ላይ በላይ ይጭናሉ ፡፡ ተሳፋሪው ምንም ሳያማርጥ መሬት ላይ ሁሉ ይቀመጣል ፡፡ ሁለት የተለዩ መንገደኞች ግን  በሁለት ተቃራኒ ሀሳቦች የጦፈ ጭቅጭቅ ጀመሩ ፡፡ ወንበር የያዘው ሰው እጥፍ ከፍዬ ሶስተኛ ሰው አላስቀመጥም ሲል የሌላኛው መከራከሪያ ለአስር ደቂቃ መንገድ ምቾት ብታጣ ምንም አይደለም የሚል ነበር ፡፡ በርግጥም ሁሉም ወንበሮች ሰዋችን ደርበዋል ፡፡ ቀስ በቀስ የክርክሩ አቅጣጫ ተለውጦ እንካ ሰላንቲያ ጀመሩ ፡፡

እንካሰላንቲያ
በሜንታ

አልተባባሉም እንጂ የጅራፉን ሰላምታ ማስጮህ ቀጥለዋል ፡፡
‹‹ ክብርና ምቾት ከፈለግህ ለምን መኪና አትገዛም ? ›› ይለዋል አትቀመጥም የተባለው በስጨት ብሎ
‹‹ ይኑረኝ አይኑረኝ በምን ታውቃለህ ?! ›› ባለ ወንበሩ ይመልሳል
‹‹ መኪና አይደለም መኪና ሰፊ የምታውቅ አትመስልም ! ››
‹‹ መኪና እንኳ እንደማይሰፋ የማታውቅ ልቅ አፍ ነገር ነህ ! ››
‹‹ እረ አንዳች ይልቀቅብህ ! ››
‹‹ ግፊያና ስድብ ከተማርክበት አውቶብስ ወደዚህ መምጣት አልነበረበረህም !  ››
ጥቂት የእንካ ሰላንቲያ ሸርተቴዎችን እየተጫወቱ ወደታች ቢወርዱ ኖሮ መናተራቸው አይቀሬ ነበር ፡፡ ሰውን እንደ ጆንያ ሲጠቀጥቅ የነበረው ሾፌር ዲፕሎማት ሆኖ ጣልቃ ገባ ‹‹ ለምን አትቻቻሉም ! አሁን አይደል ጥላችሁት የምትወርዱት ? ››

በርግጥ መቻቻል  እንዴት ?  ለምንና መቼ ነው የሚያስፈልገን  ?  በኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ የጥልና ግጭት ምርት በከፍተኛ ደረጃ ከሚመረትባቸው መስኮች መካከል  ትራንስፖርት ማጓጓዣ እንዲሁም ሰልፎች ዋነኞቹ ሳይሆኑ አይቀሩም  ፡፡ ሰልፉ የዳቦ የመብራት ክፍያ ፣ የስራ ምዝገባ የሆስፒታል የስታዲየም ወዘተ ሊሆን ይችላል ፡፡
በሆነው ባልሆነው ህግና መመሪያ ማውጣት የሚወደው መንግስት ወደ ሰሚትና አያት በሚያቀኑ አውቶብሶች ላይ ያለውን ሁኔታ ቢመለከት አንድ ስራ ሊያገኝ በቻለ ነበር ፡፡ በነዚህ መስመሮች የሚጠቀሙ ሰዋች ሙዚቃም ሆነ ሬዲዮ መስማት የሚፈልጉት ከአውቶብሱ ሳይሆን ሞባይላቸውን አምቦርቅቀው በመክፈት ነው ፡፡ ምን አይነት ልምድ እንደሆነ አልተገለጸለኝም ፡፡ ለምን የጆሮ ገመድ መጠቀም እንደማይፈልጉ አልገባኝም ፡፡ ሙዚቃው ኤፍኤም ሬዲዮው ከሬዲዮው ጋር አብሮ የመዝፈን ጣጣምናለፋችሁ አንዳንዴ የሆነ የእግር ኳስ ቡድን አሸንፎ ከደጋፊዎቹ ጋር የምትጓዙ ሁሉ ሊመስላችሁ ይችላል ፡፡

ሞባይልዎ  ቢጠራ ለማነጋገር የትኛውን ሰው ‹ እባክህ ቀንስው ወይም ዝጋው ? › እንደሚሉ አይታወቅም ፡፡ ካሉም ምናገባህ !  › ወይምስትፈልግ ጆሮህን መዘጋት ትችላለህ ! › መባል ይመጣል - ይህም ነው እንግዲህ ያልተፈለገ ግርግር ውሰጥ የሚከተው ፡፡ የሆነ ፈላስፋ ወይም ደራሲ በኢትዮጽያ አውቶብሶች ውስጥ ሲጓዙ ፕራይቬሲም ሆነ ከራስ ጋር ማውራት አይቻልም የሚል ታላቅ ሀረግ  እንዴት እስካሁን ጣል አላደረገም ?  ደፋሮቹ የማስታወቂያ ሰራተኞቻችን ግን በሆነ ባስ ሲሄዱ ቀና ነው መንገዱ  ያሉ ይመስለኛል ፡፡  

ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ አንበሳ ያሰራቸውን ሽንጠ ረጃጅም አውቶብሶች ሀገሬው ‹‹ አኮርዲዮን ›› እንደሚላቸው ይታወቃል ፡፡ ይህን ስያሜ አንድ ቦታ ‹‹ አባጨጓሬ ›› ሲባል ሰምቻለሁ ፡፡ በቅርቡ ደግሞ ሰሚት አካባቢ  ‹‹ ትግሬና ኦሮሞ ›› ከሚል መጠሪያቸው ጋር ስተዋወቅ ሳቅ አምልጦኛል - አይ ሰው በማለት ፡፡ ትግሬው ኦሮሞውን ይጎትተዋል የሚል ነው ፖለቲካዊ አንድምታው ፡፡ ብቸኛው አዲሱ አውቶብስ ደግሞ ‹‹ አማራ ›› ተብሏል ፡፡ እንዴት ?  የሚል ጥያቄ ለሚያነሳ ‹‹ አማራ ቀብራራ ስለሆነ ›› የሚል ምላሽ ያገኛል ፡፡

ዞሮ ዞሮ ትግሬና ኦሮሞ በሚለው ስያሜ ምክንያት ወጣቶች እስከመደባደብ ደርሰዋል ነው የሚባለው ፡፡ እኛ አቃፊ እንጂ ተጎታች አይደለንም በሚል ፡፡ እኛ የሀገር አስኳል እንጂ ቅርፊት አይደለንም በሚል ፡፡ በሀገራችን ብብሄር ብሄረሰቦች ባህል ፣ ወግና ቋንቋ መቀላለድ አዲስ ባይሆንም አንዳንዴ ስቆ ለማለፍ ወይም መቻቻል ከሰማይ ሲርቅ ይታያል ፡፡

መቻቻልን ማወቅ ወይም ለመቻቻል መስዋዕትነትን መክፈል የሚያስገኘው ጠቀሜታ ላቅ ያለ ነው ፡፡ ታክሲ ውስጥ ወያላው አስር ሳንቲም መልስ አልሰጠኝም ብሎ መሰዳደብ ወይም መቧቀስ በሂሳብ ቢተመን የሚያዋጣ አይደለም ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ጓደኛዬን ወይም ሚስቴን አፍጥጠህ ተመልክትሃል በማለት ከማያውቁት ሰው ጋር ይጣላሉ ፡፡ ጉረቤታሞች በዶሮ በህጻናትና በአንድ ስንዝር መሬት ጦርነት ያወጃሉ ፡፡ ቼልሲ ከአርሴናል የጠነከረ አቋም አለው ብሎ አስተያየት የሚሰጥ ወጣት በፍጥነት ሊኮረኮም አሊያም ከድራፍት ቆይታ በኃላ  በጩቤ ሊወጋ ይችላል ፡፡

መቻቻልን ባለመቻል ክቡር ህይወት ሊጠፋና ሊጎድል ፍትህ ሊጠፋና ጭቆና ሊያቆጠቁጥ ይችላል ፡፡ ሚስቴን ሳያባልግ አይቀርም በሚል ጥርጣሬ የሰው እግር በገጀራ መቁረጥ እንደ ዛፍ መገንደስ ቀላል አይደለም ፡፡ ጓደኛዬ ጣል ጣል አደረገችኝ በማለት የሀገር ድንበር በሚጠበቅበት መሳሪያ በንጹሃን የቤት ድንበር ውስጥ እየገቡ ደም ማፍሰስ ሀገራችን ውስጥ ወጥቶ እያጨቃጨቀ ከሚገኘው የሽብርተኛ ህግ አቅም በላይ ነው ፡፡ ስቸገር አረዳኝም ብሎ መከታ የሆነውን ወንድም ጋሻ የሆነውን አባት ወይም መኩሪያ የሆነን የቅርብ ዘመድ እስትንፋስ ማቋረጥ የሰይጣን እንጂ የሰው ልጅ ተልዕኮና ግብ አይደለም ፡፡ በአንድ ወቅት የተማረኩበትን አይን በተልካሻ ምክንያት ጎልጉሎ ማውጣት በአንድ ወቅት ለማየት ይጓጉበት የነበረ ፊት ላይ አሲድ ደፍቶ ማፈራረስ የስግብግበነት እንጂ የፍቅር ቴርሞሜትርን አያሳይም ፡፡

መቻቻል አስፈላጊ ነው የሚባለው በመቻቻል እጦት ከፍተኛ አደጋ ሊደርስ ስለሚችል ነው ፡፡ መንግስታት የሃይማኖት አባቶች የህግና ስነልቦና ምሁራን ስለ መቻቻል የሚሰብኩት መቻቻል ከህግ በላይ ሆኖ አይደለም ፡፡ መቻቻል ሞራላዊ ግዴታ በመሆኑ እንጂ ፡፡ በተለይ የፖለቲካ መቻቻል በስም እንጂ በተግባር ባለመታየቱ ግጭቶችና ቀውሶች ከተሰቀሉበት የክፋት ጫፍ ባንዲራቸውን እያውለበለቡ ይገኛሉ ፡፡

መንግስት ሀገርን በህብረት ለማሳደግ የሚያስፈልገው ‹‹ ብሄራዊ መግባባት ›› ነው ሲል ተቃዋሚዎች የሀገራችን መሰረታዊ ችግር ‹‹ ብሄራዊ እርቅ ›› ቦታ ባለመስጠታችን ነው ይላሉ ፡፡መግባባትእናእርቅበቀናዎች አይን ሲታዩ ሊጠጋጉ የሚችሉ ሃሳቦች ቢሆኑም በፖለቲካው ብይን ግን እሳትና ጭድ ሆነዋል ፡፡ እርቅ የሚጠየቀው ማን ከማን ተጣልቶ ነው የምታረቀው ባይ ነው ፡፡ መግባባት ፈላጊው ማንነትን በጎሳ ከመቸርቸር ይልቅ ህዝባዊ አንድነት እንዲፈጠር የሚያስችሉ ስራዎችን አስቀድም ይባላል ፡፡ ለነገሩ የሀገራችን ፖለቲካ እናሸንፋለንእና እናቸንፋለንአቅም እንኳ ልዩነቱን የሲኦልና የገነት ያህል በማስፋት ስንት እልቂትና ጥፋት እንዲፈጠር ቀለሃ ያቀበለ ነው ፡፡

የሀገራችን ፖለቲካ ከስርዓቶች ውድቀት ከመማር ይልቅ የስርዓቶችን የሃጢያት መዝገበ ቃላት ማዘጋጀት የሚያስደስተው ነው ፡፡ በመዝገበ ቃላቱ ብይን መሰረት አንዱ ህግ አስከባሪ ሌላው አሸባሪ ነው ፡፡ አንዱ መብት ጠያቂ ሌላው መብት ነፋጊ ነው ፡፡ አንዱ የነጻነት ብርሃን ሌላው የተገኘውን ብርሃን አድናቂ ነው ፡፡ አንዱ ሰጪም ነሺ ሌላው ትርፍራፊ አንሺ ነው ፡፡ አንዱ ሁሉን አዋቂ ሌላው የጭብጨባ አርቃቂ ነው ፡፡ አንዱ ለብዙሃኑ ዋስትና ሌላው የፍርሃት ፈተና ነው ፡፡ አንዱ የልማት ጓድ ሌላው የጥፋት ጉድጓድ ነው ፡፡ አንዱ ለሀገር ተቆርቋሪ ሌላው ነገር ቆርቋሪ ነው ፡፡ አንዱ የሀገር አባት ሌላው የሀገር እበት ነው ፡፡

ሃይማኖት የግል ሀገር የጋራ የሚባለውን አንድምታ ባለመቀበልም ግጭቶች ይከሰታሉ ፡፡ ባል እሳት ሲሆን ሚስት ውሃ እንድትሆን የሚመከረው ኪሳራ እንዳለው ሳይታወቅ ቀርቶ አይደለም ፡፡ ኪሳራው ፍቺ ከሚያስከትለው ቀውስ ስለማይበልጥ እንጂ ፡፡ በየሰፈራችን ሰውን የሚያስታርቁ ሽማግሌዎች ‹‹ ይቅር መባባል ይበልጣል ›› በማለት ተልዕኳቸውን የሚፈጽሙት በዳይና ተበዳይን አብጠርጠረው ሳያውቁ ቀርተው አይደለም ፡፡ ይበልጥ መቻቻል ያስፈልጋል ከሚል እምነት እንጂ ፡፡ በቅናት፣ በትንሽ ገንዘብና በመሳሰሉት ጉዳዮች የሰው ህይወት አጥፍተው ማረሚያ ቤት የሚወርዱ ሰዎች ቆይተው የሚጸጸቱት አስቀድመው ‹‹ መቻቻል ›› ባለማገናዘባቸው ነው ፡፡

ተወደደም ተጠላ መቻቻል ውስጥ ‹‹ ሂሳብ ›› አለ ፡፡ ሂሳቡ ሁልግዜ ለሁለቱም ወገን ሃምሳ ሃምሳ ለማካፈል አይችልም ፡፡ አንዱ ለግዜው በስሱ መጉዳት ይኖርበታል ፡፡

 ማስታወሻ፡ይህ ፅሑፍ በቁም ነገር መፅሔት ላይ የወጣ ነው፡፡ ፅሑፉን በሌላ ሚዲያ ላይ የምትጠቀሙ ከሆነ ምንጩን እንድትጠቅሱ ትለመናላችሁ፡፡