Wednesday, July 26, 2017

የጣና ነጋሪት መቼ ይጎሰማል ?


የህገ መንግስቱ አንቀጽ 93 የውጭ ወረራ ሲያጋጥም  ፣ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰት ፣ የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የህዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት የሚኒስትሮች ምክር ቤት እና የክልል መስተዳድሮች የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ሊያውጁ እንደሚችሉ ይደነግጋል ።

ከላይ በተገለጸው አንቀጽ ውስጥ አራት መሰረታዊ ሀረጎች ጎልተው ይታያሉ ። የውጭ ወረራ ፣ የስርአት አደጋ ፣ የተፈጥሮ አደጋ እና የጤንነት አደጋ ።

መንግስት እስካሁን የተመቸው ሀረግ የ ‹ ስርአት አደጋ › ነው ። በዚህ ለመጣበት አይደራደርም ። በዚህ የመጣበትን በብዙ ጆሮዎች የመስማትና በብዙ አይኖች የመመልከት ችሎታ አለው ። ይህን አደጋ በወንበር የመማለል አደጋ ይለዋል ። እረ ጥሩ ጥሩ ዘይቤያዊ አነጋገሮችንም ይጠቀማል ። መንግስት እንደ ኢያሪኮ ግንብ በጩኅት አይፈርስም የሚላት ነገር አንደኛዋ ናት ... መንግስት እንደ ሾላ ፍሬ በድንጋይ አይወርድምም ይልሃል ... ሌላም ሌላ ጥብቅ ማሳሰቢያዎች አሉት ። የስርዓቱን አደጋ ለማነቃነቅና ለመጣል የተሞከረን ሀገራዊ ‹ ብጥብጥና ሁከት › ጸጥ ለማድረግ ይቻል ዘንድ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ከታወጀ አያሌ ወራት ተቆጥረዋል ። ይህም የጥብቅ ማሳሰቢያው የመጨረሻ ደረጃ ነው ። ከዛሬ ነገ አዋጁ ይነሳል ሲባል የሰርዓቱ አደጋዎች ቅርጽ እና ይዘታቸውን እየቀየየሩ መፈልፈላቸው አሳሳቢ ነው ። አንዱ በአንዱ ቀለበት ውስጥ እየገባ ዛሬ የግብር አደጋ ተረኛ ጥያቄ ፈጣሪ ሆኗል ። እናም የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ታፍሮና ተፈርቶ ለማይታወቅ ዘመናት ሊውለበለብ ይችላል ።

የአዋጅ ነገር ከተነሳ በተፈጥሮ አደጋም ተጨማሪ ክተት ያስፈልገን ነበር ። መንግስት የሚመቸውን ብቻ አዳማጭ ስለሆነ እንጂ የጣና በእምቦጭ አረም የመወረር አደጋ ምታ ነጋሪት ክተት ሰራዊት የሚታዘዝበት ነበር ።

የመንግስትን ዳተኝነት የገነቡት ብዙ ምከንያቶች ሊሆኑ ቢችሉም ሁለቱን የጎሉ አስተሳሰቦች እንመልከት ። አንደኛው ችግሩን መፍታት ያለበት የክልሉ መንግስት ሲሆን ጉዳዩም ከክልሉ አቅም በላይ የሚዘል አይደለም የሚል ነው ። የክልሉ መንግስት ለበርካታ አመታት ሳይንሳዊ ውጤት ለማምጣት ባዝኗል ። ችግሩን መፍታት ቢኖርበት ይህን ሁሉ አመታት ያለ ተጨባጭ ነገር መራወጥ ባልተገባው ነበር ። እውነታው ግን የምርምርም ሆነ የገንዘብ አቅሙ ተፈላጊውን መፍትሄ ያስገኘለት አለመሆኑ ነው ።

ሁለተኛው መንግስታዊ አመለካከት የጣና ሃይቅ በአረም መወረር በውጭ ወራሪ መወረር አይደለም ወይም የተፈጥሮ አደጋ ነው ብሎ ለመቀበል የሚያስችል መደላድል የለም ከሚል ይመነጫል ። ሲጀመር ህገ መንግስቱ የተፈጥሮ አደጋ ምን ማለት እንደሆነ በግልጽ አላሰፈረም ። ሌላው ቀሮቶ ‹ የህዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት › የሚለው ሀረግ አሻሚና ግልጽነት የሌለው ነው ። በሽታ የሚለው ተላላፊዎችን ነው ... በሽታ የሚለው ግዜ የማይሰጡትን ነው ... በሽታው ኮሌራ ነው ? ኢቦላ ነው ? ማጅራት ገትር ነው ? ... አይታወቅም

በመሆኑም የ « ተፈጥሮ አደጋዋችም » ሆኑ « ጤንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ በሽታዋች» ን እውነተኛ ብይን መረዳት ያስፈልጋል ። የተፈጥሮ አደጋዋች ሰፊ ናቸው ። በአጭሩ ግን ስነ ምድራዊ ፣ ሰነ ውሃዊ ፣ ስነ አየራዊ ፣ ሰደድ እሳት እና የህዋ ጥፋት ብሎ ማሰቀመጥ ይቻላል ። ለአብነት መሬት መንቀጥቀጥን፣ የበረዶ ናዳ እና እሳተ ጎመራን ስነ ምድራዊ ውስጥ እናገኛቸዋለን ። ድርቅና የተለያዩ የአውሎ ንፋስ አደጋዋችን ሰነ አየራዊ ውስጥ ይመደባሉ ። በዚህ ሳይንሳዊ አካሄድ መሰረት የጣና ሃይቅ ችግር ስነ ውሃዊ / Hydrological Disasters / ውስጥ የሚገኝ ይሆናል ።

ሳይንቲስቶች ስነ ውሃዊ አደጋን A Violent , Sudden and destructive change either in the quality of earth’s Water or in the distribution or movement of water on land below the surface or in the atmosphere በማለት ይበይኑታል ።

ህገ መንግስቱ ዝርዝር መግለጫ ስለሌለው ከዚህ በመነሳት ሀሳብ መስጠት ግድ ይላል ። በመሆኑም በጣና ሃይቅ የደረሰው አደጋ የውሃውን መጠን ፣ ጥራትና ፍሰት የሚጎዳ ነው ። በውሃውና በአካባቢው የሚገኙ ስነህይወታዊ ስርአትን ያፋልሳል ። ከሃይቁ ቀጥተኛ የህልውና ትርጉምን እውን በሚያደርገው ማህበረሰብ ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና ይፈጥራል ።

ከዚህ ሁሉ በላይ ጣና የኢትዮጽያ ታላቅ ቅርስ ነው - በባህላዊ ፣ ታሪካዊ ፣ ሰነውበታዊ እና ስነ ምድራዊ ሃብቶች የበለጸገ ። በእኛም ብቻ ሳይሆን በዩኔስኮ ዳኝነት የተመሰከረለት ። እንግዲህ ይህ የሀገርና የአለም ሀብት ነው አደጋ ውስጥ ስለሆነ ምታ ነጋሪት ክተት ሰራዊት ያስፈልገዋል እየተባለ የሚገኘው ።

በቅርቡም ባለሙያዋች እንደገለጹት ሃይቁን ተረባርቦ ማከም ካልተቻለ በአደገኛው አረም ሊጠፋ ይችላል ። ከዚህ የላቀ ምስክርነት ታዲያ ከየት ሊመጣ ይችላል? ይህን አደጋ የተፈጥሮ አደጋ አይደለም ማለት ፣ ይህ አደጋ በህዝብ ሃብትና ማንነት ላይ የተጋረጠ ቀውስ አይደለም ማለት ራስን ከማታለል የሚቆጠር ነው ። እናም አደጋውን ለመቀልበስ በሚደረገው ጥረት መንግስት የዋና ገጸባህሪ ብቻ ሳይሆን የአዘጋጅነቱንም ሚና መጫወት ይኖርበታል ። መንግስት ልግመኛ ካልሆነ በስተቀር ‹ ኩራትም እራትም › ነው የሚለውን በርካታ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በቦታው ቢያሰማራ የማይናቅ ለውጥ ሊመጣ ይችላል ። በነገራችን ላይ መከላከያ ሰራዊት ህዝባዊነቱን እያሳየ ነው  ተብሎ ብዙ ግዜ አረም ሲነቅልና እህል ሲያጭድ በቲቪ ተመልክተናል እኮ ? ታዲያ ምነው እንቦጭን ለመንቀል አልከሰት አለ ?

መንግስት ጣና የሀገር ጉዳይ ነው ብሎ ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት ከሰራ ሀገራዊ መፍትሄ የሚጠፋ አይመስለኝም ። ከአቅም በላይ ከሆነም ወደ ውጭ ለማየት አሁንም የመንግስት አይን ጥቅም አለው ።  ቢያንስ A+ ባለው የእርዳታ ክህሎቱ ‹ ጎበዝ ተባበሩኝ ›  ቢል አውሮፓዋቹ የሚጨክኑ አይመስለኝም - ሌላው ቢቀር ቻይናዊ መፍትሄ አይጠፋም ። ለስርአት አደጋ ብቻ ሳይሆን ቀስ እያለ በተፈጥሮ ሊደርስ የሚችል ጥፋትን ለመከላከል ሳይቃጠል በቅጠል የተሰኘ ፖሊሲ መከተል ብልህነት ነው ።

ጣና የሁላችንም ጉዳይ ነው !

ቢረፍድ እንኳን ለጣና ምታ ነጋሪት ክተት ሰራዊት ያስፈልጋል !

Saturday, July 15, 2017

የአማረ አረጋዊ ልዩ ዋንጫ


አቶ አማረ አረጋዊ የኢትዮጽያ ፕሬስ ባለውለታ መሆናቸውን በማገናዘብ ሰሞኑን የእውቅና ሽልማት አግኝተዋል ። አንዳንዶች አቶ አማረ ከኢትዮጽያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ሽልማት ማግኘታቸውን አልወደዱትም ። ለምን ሲባሉ ሁለት ምክንያቶችን ያቀርባሉ ። የመጀመሪያው ምከር ቤቱ የማይገባውን ስራ በመስራቱ የሚል ነው ። የምክር ቤቱ ቀዳሚ ስራ የፕሬስ ነጻነት እንዲረጋግጥ ብሎም በስርጭት ወቅት ክህዝብ የሚቀርብ አቤቱታ ካጋጠመ እንዲታረም ማድረግ ነው  ። ከዚህ አንጻር አባላትን ለመሸለም የሚያስችል ህጋዊ ማእቀፍ እንደሌለው ይገልጻሉ ።

ሁለተኛው ምክንያት የአመራር አባል የሆነን ግለሰብ መሸለም በሽልማቱ አካሄድ ላይ ተጽእኖ እንዲፈጠር እድሉን ያሰፋል የሚል ነው ። የአቶ አማረ አመራር አባልነት በሽልማቱ አካሄድ ላይ ችግር ይፈጥራል የሚለው ህሳብ እንኳን በቀላሉ ቅቡልና የሚያገኝ አይመስለኝም ። ምክንያቱም የምክር ቤቱ አባላት በበርካታ እውቀት ጠገብ ድርጅቶች የታቀፈ ነው ።  ፎርቹን ፣ አዲስ አድማስ ፣ ሸገር ፣ ኢቢሲ ፣ ዛሚ ፣ ካፒታል ፣ ኢትዮጽያ ፕሬስ ኤጀንሲ ፣ ኢጋማ ፣ ኢትዮ ቻናል ፣ ቁም ነገር እና ሌሎች ማህበራት ይገኙበታል ። ሲጀመር እነዚህ ቡድኖች ጥራት ያለው ማንዋል አይኖራቸውም ማለት ይከብዳል ። ሲለጥቅ በግልጽ ፣ በማያሻማና ዴሞክራት በሆነ መልኩ የፈልጉትን የሚመርጡበት ስነ ሰርዓት ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል ።

የሆኖ ሆኖ አቶ አማረና ድርጅታቸው ከዚህ በፊትም አንድ ሀገራዊ ምርጫ አሸንፈው መጭበርበራቸውን ለሚያውቅ ለእኔ አይነቱ ሰው የአሁኑ ምርጫ አሸናፊነት ብዙም ላያስገርመው ይችላል ።

እንዴት ተጭበረበሩ ?

የቀዳማዊ ሃይለስላሴ የሽልማት ድርጅት ከተረሳ በርካታ አመታት በኋላ በሀገራችን አንድ የሽልማት ድርጅት ተቋቁሞ ነበር ። የኢትዮጽያ ስነጥበባትና መገናኛ ብዙሃን ድርጅት የሚባል ። ይህ ድርጅት በ 1994 ዓም ላካሄደው የሽልማት ተግባር አስቀድሞ ነበር በየዘርፉ ሊዳኙ ይችላሉ ብሎ ያመነባቸውን ግለሰቦች የመረጠው ። እናም የመጀመሪያው ትውውቅ ቀን በስብሰባ ማዕከል ተጠርተን በአቶ እቁባይ በርሄ የአሰራር መግለጫና ወፍራም አደራ ተሰጥቶን በየቡድናችን ስራውን ማሳለጥ ጀመርን ።

ጋዜጠኞችን ለመምረጥ ታሪካዊውን እድል ያገኘነው አምስት አባላት ነበርን ። ስብጥሩ ደግሞ ሁለት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አንጋፋ መምህራን ፣ አንድ የኢቲቪ አንጋፋ ጋዜጠኛ / ከእንግሊዘኛው ክፍል / ፣ አንድ የአትዮጽያ ሬዲዮ አንጋፋ ጋዜጠኛ እና እኔ ነበርን ።

ቢሮአችን ዩኒቨርስቲ ውስጥ ሆኖ ደከመን ሰለቸን ሳንል ተጋን ። ሊቀ መንበራችን ልምድ ያለው ሰው በመሆኑ እንዴት መሄድ እንዳለብንና ምን የተሻለ ስራ ማከናወን እንደሚኖርብን መንገድ አመላካች ነበር ማለት ይቻላል ። መጠይቆች ተሰርተው በመንግስትና በግልሚዲያ ተቋማት ተበተኑ ። የዚህ መጠይቅ ውጤት ተሰብስቦ እስኪቀመር ድረስ ደግሞ በየዘርፉ ያሉ ጋዜጠኞችን መዘርዘር ጀመርን ። የዳኞች ስብጥር ሁሉንም አካባቢ የሚወክል በመሆኑ ብዙም አልተቸገርንም ነበር ። ከዚያም በእያንዳንዱ ጋዜጠኛ ላይ ውይይትና ክርክር ይደረጋል ። ብዙ መቶዎችን ወደ መቶ ፣ መቶዎቹን ወደ ሃምሳ ፣ ሃምሳውን ወደ ቀጣዩ ግማሽ በመውሰድ ለፍጻሜ መድረስ ቻልን ። በመሃሉ ግን ‹ የስነጥበብ ዘርፍ ዳኞች እየጨረሱ ናቸው እናንተ ምን እያደርጋችሁ ነው ? › የሚለው የነ አቶ እቁባይ ጭቅጭቅ እረፍት ነሺ ሆነብን ። የኛ ጥያቄ ታዲያ ‹ በአጭር ግዜ የሚጨርሱት ምን አይነት ስልት ቢከተሉ ነው ? › የሚል ነበር ። በጥራት እሰራለሁ ብሎ ለሚነሳ ቡድን እያንዳንዱን እጩ በተጨባጭ አቅሙን መፈተሽ ግድ ይለዋል ። የራሱን ግምት ብቻ ሳይሆን የባለሙያውን አስተያየት ምርኩዝ ማድረግ ይኖርበታል ። ይህ ደግሞ ግዜ ይፈልጋል ።

በእውነት ከባድና አታካች ስራ ነበር ። ብዙ ግዜም የተሻሉትን ለመምረጥና ለማበላለጥ ስንቸገር ድምጽ መስጠቱ ነበር የሚገላግለን ። እናም በርካታ ወራት ከደከምን በኋላ የተሸላሚዎችን ስም ዝርዝር ከነ ምክንያቱና ማብራሪያው ጽፈን አስረከብን ።

ተጠባቂው ቀን ደረሰ ።

ሸራተን ሆቴል ልዩው ስነ ስርአት ሲካሄድ የመረጥናቸው ሁለት ሰዋች ተሰርዘው የማናውቃቸው ሁለት ጋዜጠኞች ክብሩንና 20ሺ ብሩን በእጃቸው ወሰዱት ፣ በአንገታቸው አጠለቁት ። የእኛ እንገት ግን በሃፍረት፣ በቁጭትና በህዘን አቀረቀረ ። ሁለት ዳኞችን አግኝቼ ስለ ሁኒታው አነጋገርኳቸው - እንደኔ ድንጋጤ አስክሯቸው ነበር ። ያ ሁሉ ልፋታችን ገደል ገባ ። « የዳኞች የመጨረሻ ውሳኔ የመጨረሻ ነው » በተባልነው ዲስኩር ላይ ለማላጋጥ ሞከርኩ - ይህን ማድረግ ግን አልቻልኩም ፤ ምክንያቱም በግልጽ ያላገጠብኝ እሱ መሆኑን ሰለተረዳሁ ።

ለዳኞች የተሳትፎ ወረቀት በሚሰጥበት ቀንም በነበረው አሰራር ላይ ውይይት ስለነበር በአጭበርባሪው ምርጫ ላይ የማላገጥ እድል አገኘሁ ። የተሰማኝን ሁሉ ተነፈስኩ ። ነገር ግን በእኔ ሀሳብ ላይ ምላሽ ወይም አስተያየት የሰጠ አልነበርም ። አንዱ በአንዱ ሲስቅ... እንደማለት ።

በእነ እቁባይ በርሄ ከተሰረዙት ተሸላሚዎች መካከል ብዙ ወንድማገኝ እና ሪፖርተር ጋዜጣ ይገኙበታል ። የተተኩት ደግሞ በኢትዮጽያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ የነበሩት ሳሙኤል ፍቅሬ እና የሃይለራጉኤል ታደሰ ባለቤት የሆነችው ሂሩት ናቸው ።

ያኔ ታዲያ ሪፖርተርን እንደ ጋዜጣ እንዲሸለም ያጨነው ህትመት ላይ ካሉ ጋዜጦች ጋር በማወዳደር ነበር ። ለማወዳደሪያነትም ተነባቢ ፣ አሳታፊ ፣ ወቅታዊ ፣ ተጽእኖ ፈጣሪ የሚሉና ሌሎች የጋዜጠኝነት መርህና መመሪያዎችን መሰረት እድርገናል ። ይህ ማለት የስታፉ ሁለገብ ተሳትፎን ጨምሮ የዋና አዘጋጁ አማረ አረጋዊ ሚና ትልቅ እንደነበር የሚያመላክት ነው ። አቶ አማረ ከ 97 በፊትና በኋላ አንድ አይደለም የሚሉ ሰፊ ሃሳቦች ቢኖሩም ፈተና ለበዛበት የሀገራችን ፕሬስ ያደረገው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ። ትናንት ያጣውን ሽልማት አሁን ማግኝቱ ማስደሰቱ ብቻ ሳይሆን እንደ ልዩ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ።

Tuesday, July 11, 2017

የዘመኑ ሥነ-ግጥም ያነሳውና የጣለው



የፌስ ቡክ ግድግዳ ከሚነግረን አንደኛው ጉዳይ በርካታ ገጣሚያን እያፈራን መሆኑን ነው ። ሰነጽሁፍ በማይበረታታበት ሀገር ወፈ - ሰማይ ስንኝ መታሪያዎች እንደምን ፈለቁ የሚለውን ጥያቄ በቀላሉ ማንሳት ቢቻልም ጥናት ላይ ሳይመሰረቱ ቀላልና የዋዛ ምላሽ ማግኘት አይቻልም ።

ግን ደግሞ ለጸሀፊዎች ወይም ለመስኩ ባለሙያዎች ትልቅ ርዕሰ ጉዳይ የተገኝ ይመስለኛል ። የወጣ መጽሀፍን እያደንኩ በማነብበት ዘመን አታሚዎችም ሆነ አከፋፋዮች ሥነ- ግጥምን ምናምን እንደነካው እቃ አፍንጫቸውን ይዘው ሲያርቁት አውቃለሁ ። ያኔ ብዙዎች እንደ ቀንድ አውጣ ኩምሽሽ ብለው ራሳቸውን ምሽግ ውሰጥ ይከቱ ነበር ።

ዛሬ ተመስገን ነው ። ቀንድ አውጣዎቹ አንገታችውን ስበው እየዳኹ ብቻ ሳይሆን ቢያንስ በፌስ ቡክ ግድግዳ ላይ ክንፍ አውጥተው እየበረሩ ናቸው ። በህትመት ደረጃ የሚታየውን የብዛት መሰላል ግራፍ ለማድረግ የቅርብ አስተውሎት / በርቀት ምክንያት / ባይኖረኝም አሁንም የፌስ ቡክ ግድግዳ የሚነግረኝ ዜና አለ ። ግጥም ጥቂት በማይባል መልኩ እየተመረቀ መሆኑን ።
ታዲያ እነዚህ የግጥም ስራዎች የሚያበስሩን ብዛታቸውን ብቻ ሳይሆን ያነሱትንም የጣሉትንም ጉዳይ ጭምር ነው ። በርግጥ ምን የተለየ ነገር እያነሱ ናቸው ?

1 . የዘመኑ ግጥሞች በሚያነሱት ሀሳብ በእጅጉ የበለጸጉ ናቸው ። ያልታሰቡና ያልተገመቱ ርዕሰ ጉዳዮችን ፈልፍለው በማውጣት በደማቅ ሲጽፏቸው እንመለከታለን ። ይህ የሚያሳየው ገጣሚው የመጻፊያ ርዕስ ችግር የሌለበት መሆኑን ነው ። ርዕስ ለመምረጥ አምስቱንም የስሜት ህዋሳቶች በደንብ ይጠቀማሉ ።

ከወደቀ ግዙፍ ግንድ ላይ የሚያማመሩ ጉማጆችን ለማውጣት በጭፍኑ አይደለም መጥረቢያቸውን የሚወረውሩት ። በስልትና በተገራ መልኩ ነው ጎኑን የሚኮረኩሩት ። ያኔ ተንሳጣጭ ሳይሆን የሚያስቅ ድምጽ ፈጥረው እኛንም የሳቅ ተጋሪ ያደርጉናል ።

2 . ጥበባዊ አጨራረስ የዘመኑ ግጥም ደማቅ ባህሪ እየሆነም ይመስላል ። ከተነሳው ሀሳብ በተጨማሪ የግጥሙ መዝጊያ አንዳንዴም የግጥሙ አንኳር መልዕክት አንባቢው ከሚጠብቀው በተቃራኒ ሁኔታ ሲያልቅ እንመለከታለን ። በስልቱም እንዝናናለን ። እንስቃለን - በሥስ ፈገግታ ሳይሆን ጮክ ብሎ ባመለጠን ሳቅ ። እንገረማለን - በአርምሞ ብቻ ሳይሆን ነገርና ጥያቄ በሚያመነጭ ትዝብት ። ይህ አይነቱ የፈጠራ አካሄድ ቀደም ባሉት የግጥም ስራዎች ጎልቶ የወጣ ነው ማለት አይቻልም ።

3 . ምጸታዊ ቅርጽም / Satirical poetry / ሌላኛው መለያ እየሆነ መጥቷል ። በዚህ ስልት ትልቅ ልምድ ያላቸው ሮማንስ ናቸው ። ስልቱ በተለይም ነባራዊውን የፖለቲካ መስመር ለመሸንቆጥና ለመተቸት ፣ በገሃድ የሚታየው ፍትህና ሞራል ላይ ለማላገጥ አመቺ  ስልት ነው ።

የዘመኑ ገጣሚ የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቦበት በየቤቱ እኽኽ ... የሚለውን ዜጋ ትንፋሽ በቅብብሎሽ አደባባይ ላይ እያሰጣው ይመስላል ። በፖለቲካው ምክንያት በየቤቱ የተወከለው የበገና ድምጽ ነው ። ለስለስ ያለና አንዳች ተአምር የሚለማምን ድምጽ ። ገጣሚዎቹ ይህን በገና አንዴ ትራምፔት ሌላ ግዜ ማሲንቆና ከበሮ እያደረጉት ነው - በደማቁ ።

ከላይ የተገለጹት  የፈጠራ አካሄዶችና ስልቶች ቀደም ባሉት የግጥም ስራዎች ጎልተው የወጡ አልነበሩም ። በሌላ በኩል የዘመኑ ገጣሚ እንዳነሳው ሁሉ ምን አይነት ስልቶችን እየጣለ መጥቷል የሚለውን ጥያቄ መቃኘት መልካም ነው ።

1 . የምሰላ / Imagery / መኮሰስን እንደ አንደኛው ችግር ማንሳት ይቻላል ። ገጣሚ በአንባቢ ጭንቅላት ውስጥ ምስልና ስሜትን መፍጠር ይኖርበታል ። ምሰላ ስንል የፎቶ ጉዳይ ብቻ አይደለም ። ምሰላ የሰእል ፣ የድምጽ ፣ የማሽተት ፣ የመቅመስና የመዳሰስ ህብረ ውጤት ነው ።

ከዚህ አንጻር የዘመኑ ግጥሞችን በአምስቱ ህዋሳታችን ለመረዳት እያስቸገረን ነው ። ለዚህ ትልቁ መንስኤ ደግሞ አንድ አይነትን ይተበሃል መከተላቸው ነው ። አብዛኛው ገጣሚ ግጥም በአራት፣ በስድስት እና ስምንት መስመር የሚያልቅ ጥበብ እንደሆነ የበየነ ይመሰላል ። እናም ጉዳዩን እንደጀመረ ጉዳዩን አሳጥሮ ይጨርሳል ። የግጥም መንገድ አጭርና የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው ነው ባይ መስሏል ። አንዳንዴ ግጥም ማንበብ ጀምራችሁ ማለቁን በግድ ታምናላችሁ ። በቃው ... ይሄው ነው ? ... ምን ለማለት ፈልጎ ነው የሚሉ ጥያቄዎች በምናባችሁ ይዥጎደጎዳል ። ያ ማለት ግጥሙ ወይም መልእክቱ አላሳመናችሁም ማለት ነው ። ግጥም እንደ አንባቢው መረዳት ነው ብሎ የቤት ስራውን ለእናንተ የሚቆልል ስንኝ ቋጣሪ ሳይውል ሳያድር ስራውን መፈተሽ ይኖርበታል ።

ውጤቱን በምሳሌ ላስረዳ -  በቡና መታደም ስርአት ። የበፊት ገጣሚዎች ስኒውን ፣ ቡና ቁርሱን ፣ የካዳሚዋን እንቅስቃሴ ኪናዊ በሆን መንገድ ሊያቀርቡት ይችላሉ ። ቡናው ከጀበናው ማማ ቁልቁል ስኒው ላይ እንደ ፏፏቴ ከመፈጥፈጡ በፊት ጢሱን ሊያሳዩንና እንድናሸተው ሊጋብዙን ይችላሉ ። በጢሱ ጠመዝማዛ ሰረገላ አሳፍረው የነገውን መጻኢ ማንነት ሊያመላክቱን ሁሉ ይችላሉ ። የአሁኑ ገጣሚ ዙሪያ ጥምጥሙን በመግደፍ በሞቀ ውሃ ውስጥ ዱቄት ጨምሮ እንደሚጠጣ እያሳየ ነው ።

ለአሁኑ ገጣሚ የሰርገኛ መኪና አደባባዩን ደጋግሞ መዞሩና አናስገባም ሰርገኛ እያሉ መገፋፋት ብዙም ጠቃሚ የሆነ አይመስልም ። ለመጋባት ከማዘጋጃ ፍቃድ ማግኘት ካልሆንም ያለምንም ግርግር ጠልፎ ጉዳዩን መጨረስ በቂ እንደሆነ እያሳየ ይመስላል ። ይህነኑ ብይንና እምነት ሰእላዊ በሆነ መንገድ ማቅረብ ቢቻልም አንድ ጥሩ መንገድ በሆነ ነበር - ሆኖም ቶሎ ወደ ጉዳዩ የመንደርደር ስልት ግን ምሰላን እያዳከመው ነው ። የዘመኑ ገጣሚ የግድ እንደ ሆሜር ኦሊያድ እና ኦዲሴ ረጅም ተራኪ ስታይል ይጠቀም ለማለት ሳይሆን ቢያንስ ስብጥራዊ መንገዶች ይኑሩት ነው ። ረጅም ሆኖ የሚመስጥ ግጥም መስራት እንደሚቻልም የከበደች ተክለአብ ፣ አበራ ለማ ፣ ክፍሌ አቦቸር እና የመሳሰሉ ስራዎችንም ያገላብጥ ነው ።

በቅርጽ አወራረድም የመመሳሰል በሽታ ይታያል ። ብዙ ግጥሞች እንደ ፋብሪካ ምርቶች ተመሳሳይ ፍሰት ፣ ዜማና ምት የሚጋሩ መስሎ ይሰማናል ። በጣም የወጡ ገጣሚዎች በሌሎች ላይ እያሳደሩ የመጡት ተጽእኖ ቀላል አለመሆኑ እስኪታወቅ ደረስ ። ገጣሚው ለምሳሌ እንደ በእውቀቱ እንጂ እንደ ጸጋዬ ፣ ሰይፉ መታፈሪያ ፣ ከበደ ሚካኤል ፣ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ወዘተ የራሱን መስመር ማስመር እንዳለበት አላመነም ።

2 . የቋንቋ ችግር ። የዘመኑ ገጣሚ ግጥም የሚጻፈው በቀላል ቋንቋ ነው የሚባለውን መረዳት በመያዝ ይመስላል የተለየ ትኩረት ሲሰጥ የማይታየው ። የግጥም ቋንቋ ከተራውና ከተለመደው መግባቢያ የላቀ ውበትና ዜማ የተጎናጸፈ ነው ።  የግጥም ቋንቋ የሚፈጥረው ውስጣዊ ወይም ሌላኛው ትርጉምም ማለታችን ነው ። የግጥም ቋንቋ ከሰዋሰውና ከቀበሌኛ ዘዬም በላይ ነው ።
ጠንካራና ውብ ቋንቋ ለመፍጠር ሰርካዝም የሚባሉትን ምጸት ፣ ሽሙጥና ውስጠ ወይራዎችን ማወቅና መጠቀም ይጠቅማል ። ሜታፎር የሚባሉትን ዘይቤያዊ አነጋገር ፣ አሊጎሪና ምሳሌዎችን ማወቅና መጠቀም ግድ ይላል ። ግጥም እነዚህን ዘይቤዎች አይነኬ የሚያደርጋቸው ከሆነ ተራ መደዴ ነው የሚሆነው ። ውበትና ልቀትን ነው የሚያደበዝዘው ።


እናም የሚነሳውን እያጠናከሩ የሚጣለውን ደጋግሞ እየመረመሩ መሄድ የሚያዋጣ ይመስለኛል ።

Tuesday, July 4, 2017

እየመጣ ያለው አስቀያሚ ስያሜ



ፊንፊኔ ስላሽ አዲስ አበባ
አዲስ አበባ ወይም ፊንፊኔ
ፊንፊኔ እና አዲስ አበባ 
አዲ ሃይፈን ፊን
ፊን ነጥብ አዲ
አ ወይም ፊ

የቱ ነው እየመጣ ያለው የከተማችን መጠሪያ ? የቱ ነው እውነቱ ? የሚያስከትለው ውጤትስ ? ታዋቂው አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ራልፍ ኤድዋርድ Truth and Consequences እንዲል ። ይህን Truth and Consequences የተባለውን የNBC ቴሌቪዥን ፕሮግራም የመመልከት እድል ያጋጠመው ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮችን ይገነዘባል ። እውነትን ማወቅ ስጋት ማራገፊያ መሆኑንና እውነታን መሳት ካልታሰበ ችግር ጋ የሚያላትም መሆኑን ።

የፕሮግራሙ ፈጣሪ ራልፍ ኤድዋርድ ከተመልካች ውስጥ የተወሰኑትን መድረክ ላይ በማቅረብ ነው ጥያቄውን የሚያቀርበው ። የጥያቄውን ምላሽ ያገኘ ነጻ ይወጣል ። እውነታውን የሳተ ግን በቀጣይ የሚቀርብለትን አስደናቂ ወይም አስቸጋሪ ወይም አሳፋሪ ትርዒት የማቅረብ ግዴታ አለበት ። ትርዒቱ ከአቅሙ በላይ ሊሆንይችላል ፣ ቢሆንም ከድርጊቱ ጋር መጋፈጥ አለበት ። ለምሳሌ ያህል አንድ ወቅት ያየሁት ተጠያቂው ባለ አንድ ጎማ ብስክሊት እንዲያሽከረክር ታዞ ነበር ። ሰውየውን እንደምንም ብለው የሳይክሉ ረጅም ወንበር ላይ ሰቀሉት ። ታዲያ ምን ያደርጋል ላይ ተንጠልጥሎ ራሱን ባላንስ ማድረግ አልቻለም ። እናም ፔዳሉን ወደፊትና ወደኋላ ከማባበል ይልቅ በሃይልና በድንጋጤ ሲንጠው ቀጥታ ወደ ተመልካቹ ተፈተለከ - ህዝቡ መሃል እንደ ቲማቲም ፈርጦ ክፉ የሽብር ተግባር ይፈጽማል ብዬ ስጠብቅ አምላክ ረድቶት አንድ ጥግ ምናምን ይዞ ዳነ ።  በሰውየው ድንጋጤና ያልተገራ ጥበብ ብዙ ሰአት እንደሳቅኩ አስታውሳለሁ ።

የዚህ ፕሮግራም አዘጋጅ ከመድረክ ኩምኩና በተጨማሪም ለአለማችን አስቂኝ የከተማ ስም በመፍጠርም ይታወቃል ። ነገሩ እንዲህ ነው ። በ1940 የተጀመረውን Truth and Consequences አስረኛ አመት ለማክበር በአዘጋጁ በኩል አንድ ጥሪ ይተላለፋል ። የከተማውን ስያሜ በፕሮግራሙ መጠሪያ ለሚቀይር ዝግጅቱ በቀጥታ ከከተማው እንዲተላለፍ ይደረጋል የሚል ። ይሄኔ የ < Hot Spring > ነዋሪዎች ፍቃደኝነታቸውን ይገልጻሉ ። ከተማዋ የበርካታ የተፈጥሮ ሙቅ ውሃ ባለቤት ናት ። እናም በመጋቢት 1 ቀን 1950 ዓም ህዝበ ውሳኔ ያከናውናሉ ።  295 ሰዎች ይህን እብደት አንደማይቀበሉ ሲገልጹ  1294 ያህሉ ግን ስማችን እንዲቀየር እንፈልጋለን አሉ ። በቀጣዩ ቀን ማለትም ሚያዚያ 1 1950 ፕሮግራሙ ከከተማዋ ተላለፈ - የከተማዋ አዲሱ መጠሪያም Truth or Consequences ሆነ ።

ይህ ስም በአለማችን ካሉት ረጅም እና ቀፋፊ ስሞች መካከል እንደ አንደኛው ሊቆጠር  የሚችል ነው ። የTruth or Consequences ከተማ ነዋሪዎች ይህ ቀፋፊ ስም እንዴት ከእናንተ ተግባር ጋር ይገናኛል ሲባሉ የሚከተለውን ሽፍንፍን ያለ ምላሽ ይሰጣሉ  « እውነታው / Truth /  በከተማችን ጤና ሰጪ ፍልውሃዎች ያለን መሆኑ ነው ፣ ይህ ያስከተለው ውጤት/ Consequences /  ከተባለ ደግሞ ሰዎች ተጠቃሚ መሆናቸው ነው » የሚል ነዋሪዎቹ ዛሬ ዛሬ በረጅሙ ስያሜ በመዳከማቸው  ቲ ኦር ሲ ወደሚል ምህፃረ ቃል ወርደዋል ።

ምናልባትም ሁለተኛው ረጅም እና ቀፋፊ ስም የአዲስ አበባው ፊንፊኔ ጥምረት ሊሆን ይችላል ። በህግ ፊት እኩል የመቆም መብት የተሰጣቸው አዲስ አበባና ፊንፊኔ በሚያስከትለው ውጤት / Consequences / ብዙ ሊፋተጉ ይችላሉ ተብሎ የተሰላ ይመስላል ። አዲስ አበባ ይቅደም ፊንፊኔ ? አቀማመጡ እና ጥምረቱስ ? በወይም ይቆለፍ ወይስ በ እና ሰረገላ ? በስላሽ ድንበር ያብጁ ወይስ  የዶት ታኮ ይሰራላቸው ?

ምፀታዊ ዋጋው የአዲስ አበባ ህዝብ መሰረታዊ ለውጥ በሚያመጣው በዚሁ ጉዳይ ሀሳብህ ምንድነው ተብሎ አለመጠየቁ ነው ። ስሙን በማስረዘሙ ልዩ ጥቅም ያገኛል ? የውሃ ፣ መብራት ፣ ስልክ ፣ ስራ እና የዋጋ ንረት ሰቆቃው በፊንፊኔ ስላሽ አዲስ አበባ ገመድ ይጠፈነጋል ? ከአንድ ወደ ሁለት ቃላት ያደረገውን ድንገተኛ ሽግግር ተመችቶት ይቀበለዋል ፣ ህጋዊና ስነልቦናዊ ግዴታስ አለበት ? ነው መንግስት ካለ አለ ነው- ተከተል አለቃህን አክብር አርማህን እንዲሉ ። ከቅርብ ግዜያት የፖለቲካ ተሞክሯችን ስንነሳ ግን በንግግርና መግባባት ላይ ያልተመሰረተ ውሳኔ ያልታሰበ ውጤት ለማስከተል ምንም የሚያግደው ነገር የለም ። በመሆኑም  የኦሮሞ ተወላጆች ፊንፊኔ ሲሉ የተቀሩት ደግሞ በአዲስ አበባ እንዲፀኑ መንገድ ይከፍታል  ። በአንድ ከተማ ሶስት ስያሜ መሆኑ ነው ።

ይህም ወደ ሌላ አላስፈላጊ ውጤት ይመራል ። ወደ ይዞታ ጉዳይ ። ከተማዋ ለእኛ ነው የምትገባው ወደሚለው  የኦሮሞ - አማራ ጭቅጭቅ ። በርግጥ ማነው ቀደምቱ ? ከአዲስ አበባ በፊት ፊንፊኔ ነበር ... ስለዚህ ከተማዋ የኛ ናት ፣ እናንተ እንግዶቹ በኛ ስር ልታድሩ ግድ ነው ይልሃል አንደኛው ጠርዝ ... ከፊንፊኔ በፊትስ እነማን በምን ስም ነበሩ ?... ኦሮሞዎቹስ ከየትና እንዴት መጥተው በሀገሪቱ ተስፋፉ ይልሃል ሌላኛው ጠርዝ   ። ጭቅጭቁና እንካሰላንቲያው በተዋረድ በሰፈርና አደባባይ ስሞች ግዘፍ ነስቶ ይመጣል ። ለመንገድ ስያሜ ከተሜው ግድ ላይኖረው ይችላል ። ግድ የሚሰጠው ግን እንደ ማተቡ ውስጡ የቆየውን የሰፈር ስያሜ ቀይር አትቀይር የሚል ሙግት ከተከተለ ነው ። መንግስት በቀጭን ትዕዛዝ አስራለሁ ቢል እንኳን ጥቁር ገበያው አይሎ ኢ- መደበኛው ኮሙኑኬሽን እንደሚልቅ አያጠራጠም ።

የአዲስ አበባን ደም መርምሮ ሁነኛ ብይን ማግኘት አይቻልም ። የደም ምርመራው ኦ ኔጌቲቭ ፣ ኦ ፖዘቲቭ ፣ ኤ ኔጌቲቭ ፣ ኤ ፖዘቲቭ ፣ ቢ ኔጌቲቭ ፣ ቢ ፖዘቲቭ ፣ ኤቢ ኔጌቲቭ እና ኤቢ ፖዘቲቭ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም ። ይህ የሚያሳየው ደግሞ አዲስ አበባ ከኦሮሞም ከአማራም በላይ መሆኗ ነው ። ከተማዋ የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ሃብት ናት ። የኢትዮጽያዊነት አሻራ ወይም ቅጂ ናት ። የአፍሪካዊነት መሰረት የዝማሬያቸውም  ሰንደቅ ናት ።

ከመቶ አመታት በላይ የዘመናዊ  አስተዳደር ጽንሰ ሃሳብን ስትገነባ የመጣችን ከተማ በምን ተአምር የብሄር ካፖርት ማልበስ ይቻላል ? የዘመናዊነት ትርፉ እኮ ትላልቅ ፎቆችንና ዘመናዊ ባቡሮችን ማስገኘት ብቻ አይደለም ። ዘመናዊነት ከሁሉም በላይ አስተሳሰባዊ ዝመናን ይመለከታል ። የከተማው ህዝብ ኑሮ አጉብጦት ይሆናል እንጂ በአስተሳሰቡ ሸንቃጣ ነው ። ብዙ ትርፍና ተቀማጭም ሀብት አለው - የገንዝብ ሳይሆን  የማመዛዘን ፣ የመቻቻልና የፈሪሃ እግዚአብሄርነት ። በዚህ መሰል ችግር ወቅት እየመነዘረ የሚያካፍለው ። የማይናድ ልዩ ጥቅም አለው ከተባለ ይኸው  ነው ።

 ግራም ነፈስ ቀኝ የአዲስ አበባን እውነታ አብጠርጥሮ ማወቅ ካልተቻለ የሚያስከትለው ውጤት ከባድ ሊሆን ይችላል ።


Tuesday, June 27, 2017

ባልና ሚስት ደራሲዎች


ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል ባልና ሚስት ደራሲዎች ያውቃሉ ? አብረው በስነጽሁፍ ንባብ የሚመሰጡ ? በስነጽሁፍ ቋንቋ የሚወያዩ ? በስነጽሁፍ ለዛ ፍቅርና ውብትን ሚዘምሩ ? በስነጽሁፍ ድባብ መከራና ሀሴትን እንዳመጣጡ የሚያስተናግዱ ? በስነጽሁፍ መዋቅር ላይ ታች የሚናጡ ? አለባዊያንን አምጠው መድብል የሚገላገሉ ?

እውነት ምን ያህል ጣምራ ደራሲዎች / በተለይ ለመጽሀፍ/ አሉን ? ብዙ ባስብም ማወቅ የቻልኩት አንድ ያህል ብቻ ነው ። « የተሸጠው ሰይጣን » ትዝ አላችሁ ? « ያልተመቻት ችግኝ » ስ ? እነዚህን መጽሀፍት የደረሱት ጣምራዎቹ ጀማል ሱሌይማንና የዝና ወርቁ ነበሩ ።  አያያዛቸውን ይበል ያለው አንባቢ ከደራሲዎቹ ብዙ ይጠብቅ ስነበር በግዜው ብዙ ብሎላቸዋል ። ከአይን እንዲያወጣችው - ብዙ የፈጠራ ልጆችን እንዲያፈሩና ወልደው እንዲከብዱ ። ጥምረታቸው ግን ከዚህ በላይ መዝለቅ ስላልቻለ ተለያይተው በየግላቸው መጓዝ መርጠዋል ።

ብዙዎች ድርሰት በግል ከራስ ነፍስ ጋር የሚንጎረጎር ዜማ እንደሆነ ነው የሚሰማቸው ። ለዚያም ሊሆን ይችላል የሃገራችን ደራሲዎች ትዳርን ከተመሳሳይ ሙያ ጋር አቆራኝተው ለመሄድ የማይፈልጉት ። ብዙ ስመጥር ደራሲዎችን በቃለ መጠይቅ ወቅት እንደሰማናቸው ከሆነ ተጣማሪያቸው ከድርሰት ዓለም በብዙ መቶ ሺህ ማይል ርቀው የሚገኙ ናቸው ። ርግጥ ነው ጽሁፍ በማንበብ ፣ በመተየብና ሙድ ውስጥ የገባው አባወራ ተጋግሎ እንዲቀጥል ትኩስ ነገር በማቅረብ የድጋፍ እጃቸውን ይዘረጋሉ ። ይህም ወሮታ መጽሀፉ የታተመ ግዜ በእጥፍ ይመለስላቸዋል - ከፊተኞቹ ገጾች በአንደኛው ስማቸው አብረቅርቆ እንዲታይ በማድረግ ።

መሰረታዊው ጥያቄ ይህ የምስጋና ስም ለምን ከዚህ አጥር መውጣት አልቻለም የሚለው ነው ። የውጪው አለም ነባራዊ ምስል ግን ከዚህ ይለይል ። ደራሲዎች በጣም ይቀራረባሉ ። ይደናነቃሉ ። ተመሳሳይ ቋንቋቸውን ለእድገትም ለፍቅርም ያውሉታል ። በመጨረሻም በትዳር ይጣመራሉ ። የዚህ ወግ ባለቤት የሆኑ ደራሲዎች ቁጥር በርካታ ነው ። ርግጥ ነው እንደ ጀማል ሱሌይማንና የዝና ወርቁ ተጣምረው የጋራ ድርሰት መስራት የቻሉት ጥቂቶች ናችው ። ለምሳሌ ያህል House of Secrets , Tuesday’s Gone እና The Wolves of st. Peter የተባሉ ስራዎችን የደረሱትን ባልና ሚስቶች ማንሳት ይቻላል ።

አብዛኛዎቹ ባልና ሚስት ደራሲዎች ግን ያገናኛቸው የድርሰቱ ጉልበት ቢሆንም እየተነጋገሩና እየተራረሙ መጻፍ የሚፈልጉት በየግላቸው ነው ። አንዱ በሌላው ስራ ውስጥ ሀሳብ የመስጠት እንጂ የማንሳትና የመጣል እንዲሁም የመወሰን መብት የለውም ። ወይም ግዙፉን ወሳኔ የመሸከም ፈላጎቱ ግድብ ነው ።

ቨርጂንያ ውልፍ እና ሊዮናርድ ውልፍን ፣ ኸርነስት ሄሚንግዌይንና ማርታ ጊሎርን ፣ ጆርጅ ኢሊየትንና ጆርጅ ሄንሪ ሊዊሲን እንዲሁም ሌሎች በርካታ ጣምራ ደራሲዎችን መጥቀስ ይቻላል ። ሽማግሌውና ባህሩ ፣ ፀሃይዋም ትወጣለች እና በርካታ ድርሰቶችን ያቀረበልን ኤርነስት ሄምንግዌይ በሚስቱ ማርታ ብዕርም / The Face of War , Travels With Myself and Another / ተደማሚ ነው ።

ከላይ ከገለፅኳቸው ሁለት አይነት ደራሲዎች የተለዩ አይነቶችም መኖራቸው ነው እኔን ያስደመመኝ ። አላን እና ባርባራ ፒስ ይባላሉ ። እንደ ብዙ ጣምራ ደራሲዎች ትዳራቸውን በአጭር ግዜ የበተኑ አይደሉም ። 24 አመታት አብረው ቆይተዋል ። ስድስት ልጆችና ስምንት የልጅ ልጅ አይተዋል ።

ምንም እንኳ ስራዎቻቸው ኢ - ልቦለድ ቢሆንም 18 የሚደርሱ መጻህፍትን በጋራ ፅፈው ማሳተም ችለዋል ። መጻህፍቱ በመላው አለም በእጅጉ የተነበቡ ናቸው ። 27 ሚልዮን ኮፒ ተሸጠዋል ። ምን ይህ ብቻ በ 55 ቋንቋዎች ተተርጉመዋል ። ጥንዶቹ ፒስ ኢንተርናሽናል የተባለ ድርጅት በማቋቋም ኮሙኒኬሽን ፣ የሰውነት ቋንቋ ፣ የሽያጭ ድርድር ቴክኒክ ለመንግስት እና ለንግዱ ማህበረሰብ በመስጠትም ይታወቃሉ ። በዚሁ ረገድ እስካሁን በ 40 ሀገራት ተዘዋውረው ስልጠናና ጥናት አከናውነዋል ።

የመጻህፍቱ ጭብጥ የተመሰረተው በስነ ልቦና እና ተቃራኒ ፆታ ግንኙነት ላይ በመሆኑ የብዙዎችን ትኩረት ለመያዝ የቻለ ይመስለኛል ። ከየመጻህፍቱ ርዕስ ስንነሳም ደራሲዎቹ የአጻጻፍ ይትበሃላቸውን ብልህ በሆነ መንገድ የዘወሩት ይመስላል ። ለምሳሌ ያህል Why Men Lie and Women Cry በሚለው ስራ ሁለቱ ፆታዎች የጉዳዩ ምሶሶ በመሆናቸው ተከፋፍለው ለመስራት ይመቻቸዋል ። የሴት እና የወንድ ነገር አባት ሆነው በጥልቀት ያነባሉ ፣ ጥናት ያደርጋሉ ፣ በመጨረሻም ውጤቱን ይቀምራሉ ። የአንዱን ምዕራፍ ሌላኛው እንዲያነበው በማድረግ ከስር ከስሩ አረም እንዲነቀል ብሎም ምርጥ ማዳበሪያ እንዲጨመር እድል ይፈጥራል ። ይህም ስራው የተዋጣ እንዲሆን መንገድ ከፋች ነው ። እናም በ < Why > የሚጀምሩ በርካታ ርዕሶች የስራ ክፍፍልን ለመፍጠር ሳያመቻቸው አይቀርም ። የደራሲዎቹ ስራዎች የሰው ልጅን ውስብስብ ባህሪና ፍላጎት ለመረዳት ከፍተኛ እገዛ የሚያደርጉ በመሆናቸው ሊነበቡና ሊተረጎሙ የሚገቡ ናቸው ።

እነሆ የስኬታሞቹ ባልና ሚስት ገሚስ ስራዎች፣
. Why Men Don’t Listen and Women can’t Read Maps
. Why Men Can Only Do One thing at a time Women Never Stop Talking
. Why Men Don’t Have a clue and Women Always Need More Shoes
. Why Men Lie and Women Cry
. Why He’s so Last minute and She’s Got it all Wrapped up
. Why Men Want Sex and Women Need Love
. How Compatible are You ?
. You Can  People Skills for Life
. Write Language
. Talk Language : How to Use Convesation for Profit and Pleasure
. The Definitive Book of The Body Language
. The Body Language of Love
. Body Language in the Work place


Thursday, June 8, 2017

በስም እንደራጅ


መንግሥት ሰማንያ ሚሊየኑ ሕዝብ በተበታተነና በተበጣጠሰ መልኩ ለሚያነሳው ችግርና ጥያቄ እልባት ለመስጠት አይቻለኝም ብሏል መብትን ለማስከበር ፣ ብጣቂ  የምታህለውን ብድር ለማግኘት ሥራ ለመስራት ቦታ ለማግኘት ብቻ ለሁሉም ነገር መደራጀት ግድ ብሏል

ግዴታውን ለመወጣት ሕዝቡ በጾታ ተደራጅቷል፤የሴት ሊግ የሴቶች ማኅበር እያለ ። በሙያ ተደራጅቷል - የመምህራን የሕግ የፋርማሲ የስታቲክስ ወዘተ እያለ በዕድሜ ተደራጅቷል - የወጣቶች የአዛውንቶች እያለ በቋንቋ ተደራጅቷልአማራ ትግሬ ኦሮሞ እያለ በብሔር ተደራጅቷል-ትግሬ ወርጂ፣ ወለኔ ጠምባሮ ደንጣ  ዱባሞ  ከችንችላ እያለ  በአምራችነት ተደራጅቷል - የጨው፣ የአሳ፣ የቡና፣ የማር፣ የኦፓል ወዘተ እያለ በጉዳት ተደራጅተል - አካል ጉዳተኛ ማየት የተሳነው መስማት የተሳነው እያለ በቀለብ ተደራጅተል ስኳር ጨው ዘይት፣ ጤፍ ሸማች እያለ በንብረቱ ተደራጅቷል - የታክሲ የአውቶብስ፣ የገልባጭ የቦቲ  እያለ በኪነጥበብ ተደራጅቷል-ሙዘቀኛ፣ ሠዓሊ ፣ ደራሲ ፣ ፊልም ሰሪ ፣ ቀራጺ፣ ቴአትረኛ እያለ ።  አንበሳ አጋዘን ጎሽ ሳላ ለማስገደል ተደራጅቷል - አሳዳኝ እያለ   ሌላው ቢቀር አንድ ለአምስት ብሎ በቁጥር ተደራጅቷል በዚህም ምክንያት የመደራጃ ርእስ ተሟጦ አልቋል።

እናም አንድ ቀን እስካሁን ክፍት በሆነው በተመሳሳይ ስም ተደራጁ መባሉ አይቀርም ያኔ ሎዳሞ  ከሎዳሞዎች ቶሎሳ ከቶሎሳዎች ደም መላሽ ከደመላሾች ጀርባ ይሰለፋሉ በርግጥ የስማችን ድግግሞሽ በርካታ በመሆኑ ሰልፉን በሥርዓት ለመምራት አስቸጋሪ መሆኑ አይጠረጠርም መቼም ሰልፉን ነገር እንደማይገባው ፓርላማ መበተን የዋህነት ስለሚሆን በስም ብቻ ሳይሆን እስከነአባታቸው ተመሳሳይ የሆኑት ተሰባስበው መላ የሚፈልጉበት ዘዴ ይፈጠራል  ። ርግጥ ነው አሁንም ክፍተቱ ሊደፈን አይችልም ተመሳሳይ ወፎች እንጂ ተመሳሳይ ስሞች አንድ ላይ ላይበሩ ይችላሉ አንደኛው በቀለ ጎሰኝነትን እንዋጋ ሲል ሌላኛው በቀለ የሙሰኛ አመራር ጉዳይ እንቅልፍ ይነሳው ይሆናል ለአንደኛዋ ትዕግስት የደረጃ እድገትና ሹመት ላይ የሚሰራ ግፍ የሚያንገበግባት ሲሆን ሌላኛዋ ትዕግስት የዲግሪና ዲፕሎማዎች ሳጥኗ ውስጥ መሻገት ነው የሚያስጨንቃት ።

ምናልባት ስምና ፍላጎትን ማቆራኘት የተሻለ ሊሆን ይችላል የእናንተን አላውቅም ፣ እኔ ግን ከሞክሼዎቼ ጋር መደራጀት የሚያስችለኝ የማርያም መንገድ ይታየኛል ለአብነት፣
አለማየሁ ገላጋይ
አለማየሁ ታዬ
አለማየሁ /ህይወት
አለማየሁ ማሞ
አለማየሁ ዲባባ
አለማየሁ ታደሰ
የሚባሉ ኪነጥበብ የጠራቻቸው ሰዎችን አውቃለሁ ሌሎችም በሂደት ይቀላቀላሉ የክበቡ ወይም የማህበሩ ወይም የሊጉ አላማ ምን ይሆናል? ይሄ የምልአተ ጉባኤው የቤት ሥራ ቢሆንም ብዙ መነሻ ሀሳቦችን መደርደር ይቻላል በትርጉም የሚቀራረቡ ስሞችን ለምሳሌ ያህል ውባየሁ ፣ ድንቃየሁ እጅጋየሁ ወዘተ በማሰባሰብ በተለጣፊነት ሳይሆን አጋር ማኅበራት የሚሆኑበትን ስልት ይነድፋል በሂደት በፌዴሬሽንም ሆነ ኮንፌዴሬሽን ውህደቱ እውን እንዲሆን በትጋት ይሠራል በሌላ በኩል ብዙአየሁ ስንታየሁ የመሳሰሉ መጠሪያዎች ያዩት ነገር ደስታ ይሁን ሀዘን ግልጽ ስላልሆነ እግረ መንገድ መልስ የሚሰጥ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራውን ያቀላጥፋልይህም በኋላ ሊመጣ የሚችለውን የአባልነት ጥያቄ ከወዲሁ ግልጽ ለማድረግ ያስችላል።

በብዙ አካባቢዎች አለማየሁ የሚለው መጠሪያ የወንድ ነው አልፎ አልፎ ግን አለማየሁ የሚባሉ ሴቶችም እንዳሉ ተደርሶበታል ሴቶች ይህን ስም ለምን ሊጠቀሙበት ፈለጉ? ማኅበሩ የውህዳኑን መብት እንዴት ሊያስተናግደው ይችላል? የሚሉ ጥያቄዎችንም ማጥናት የኮሚቴው ሌላኛው ተግባር ይሆናል

አለማየሁ በሚል መጠሪያ የግጥም የአጭር ልቦለድ የወግና የስላቅ ወድድር በማዘጋጀት አለማየዎች እንዲወዳደሩ ይደረጋል። አለማየሁ የተባሉ ባለሃብቶችን ገንዘብ በመለመን አሸናፊዎች ዓለሙን አይቶ የተዳከመ መኪና ይሸለማሉ ባገለገለው መኪና ዓለምን ባይሆንም የክልል ከተሞችን ይጎበኙበታል ዞሮ ዞሮ አሸናፊው በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ዓለሙን እንዲቀጭ እናደርገዋለን።

ከእንግሊዝ ኤምባሲ ጋር ቅርበት በመፍጠር የልዑል አለማየሁን መካነ መቃብር ለመጎብኘት ጥረት ይደረጋል የሀሳቡ መነሻ ጉብኝት ይሁን እንጂ ዋነኛው ተግባር ብዙ ስላልተባለለት ተጠባባቂ ንጉሥ ብዙ አጥንቶ ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ማሳተም ነው ይህ  መጽሐፍ ሀገራዊ ቅርስ ነው ተብሎ ቢታመንም መንግሥት ለምንጠይቀው የማሳተሚያ ገንዘብ ጥያቄ በጎ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ አይጠበቅም በመሆኑም በአለማየሁ እሸቴ የሚመራ ለስላሳ ጥዑም ዜማ በአንድ መድረክ በአለማየሁ ፈንታ የሚመራ የሽለላና ፉከራ ጥበብ በሌላ መድረክ ተዘጋጅቶ ገቢ ለማሰባሰብ ጥረት ይደረጋል  

በሂደት የሬዲዮ አየር ሰዓት በመግዛት የአለማየሁ ድምጽ የሚል ፕሮግራም ይጀመራል ፕሮግራሙ ከማዝናናት በተጨማሪ አለማየዎች እንዲነቃቁ በየክልሉ ተሰባስበው እንዲደራጁ ያበረታታል አለማየሁ ምንድነው ? እንደምንስ ተፈጠረ ? አለም ያየው ባለስሙ ነው ወይስ ልጅ ፈጣሪው? በስሙና በሰውየው መካከል ያለው ዝምድና ምንድነው? ዝምድና ከሌለ ደስታ አየሁ፣ ፍቅር አየሁ፣ በጎነት አየሁ የሚለውን ትርጉም እውነት ለማድረግ የሚያስችል አማራጭ አለ? ምን ያህሉ ነው ስሙን የሚታዘበው? ስሙ ከብዶት የቀየረ ወይም አለምና አሌክስ በማለት ስጋቸውን የቀነሰ አለ? በእነዚህና በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ክርክር ወይም ምርምር ሊያደርግ ይችላል

አለምነሽ እና አለሚቱ ከመሳሰሉ ተቀራራቢ ሴት አቻ ማኅበራት ጋር ግንኙነት በመፍጠርዓለምበተሰኘው የጋራ ነጥብ ላይ ሃሳባቸው እንዲፋጭና እንዲጋጭ ይደረጋል ብልጭታው ፍቅርና ትዳርን ሊመሠርት ይችላል ብልጭታው አለም የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት እንዲፈጠር  ምክንያት ሊሆን ይችላል ብልጭታው አለም የተሰኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም አክስዮን እንዲወለድ መንገድ ይከፍት ይሆናል ብልጭታው ምን የማይፈጥረው ነገር አለ ? …

መደራጀት እንግዲህ ጥቅሙ ብዙ ነው አለምበቃኝ መዉረድም እንደተጠበቀ ሆኖ