Tuesday, July 3, 2012

እየተወገዘ የሚለመልም …




‹‹ የት ተፈጠረ ? ›› የሚለው ጥያቄ ሲነሳ ብዙዋች ይጣሉበታል፡፡ ገሚሱ ትውልድ ሃገሩ ኢትዮጽያ ነው ሲል ሌላው የመን መሆኑን ያስረዳል፡፡ ኢትዮጽያ እና የመን ‹‹ የኔ ነው ›› እያሉ የሚከራከሩበት በስንት ነገር ነው ጃል ?! ላለፉት 3ሺ ዓመታት በታላቋ ንግስት ሳባ የታሪክ ጉተታ ውስጥ ገብተው የሃሳብ ልብሳቸውን ሲቦጫጭቁ ነበር፡፡ በርግጥ ትግሉ በአዳፍኔና በጨበጣ መጠዛጠዝን ያለመ አልነበረም፡፡ ስልቱ ዞር ያለ ነበር፡፡ ለምሳሌ ያህል

የደረጀ ጥናታዊ ጽሁፍን - እንደ ጦር ማምረቻ ሰፈር
የቁፋሮ ምርምርን - እንደ ፈንጂ
ነባራዊ ማስረጃ የሆኑትን ማለትም ቤተ መንግስትን - እንደ ዘመቻ መምሪያ
መዋኛ ገንዳን - እንደ  መርከብ
ሳባዊ ጽሁፍን - እንደ ፕሮፓጋንዳ ክፍል
የሚነገሩ ትውፊቶችን - እንደ ሚዲያ ተቋም ሳይጠቀሙ አይቀርም፡፡ ደግነቱ ሁለቱም ወገኖች ወደ ዓለማቀፉ ፍርድ ቤት ሳይሄዱ ወይም የመሄድ ፍላጎት ሳያሳዩ ሳይንቲስቶች የአሸናፊነቱን ካባ ለኢትዮጽያ አልብሰዋል፡፡ አሁንም በነካ እጃቸው የዚህን ተክል መፈጠሪያ ቢወስኑ ጥሩ ነው፡፡ ለነገሩ የመጀመሪያ መባል ታሪካዊ ትርፍ ካለው እንጂ ይሄኛው ተክልስ አጨቃጫቂ ባህሪ አለው፡፡

ይህ ተክል የት ተፈጠረ ብቻ ሳይሆን መቼ ተገኘ ? የሚለውም ሀሳብ ላይ ስምምነት አልተገኘም፡፡ ገሚሱ በ13ኛው ሌላው በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሚል ሀሳብ አለውና፡፡ ተክሉ ኢትዮጽያም ይፈጠር የመን ከዚያ ወዴት አቀና ለሚለው ጥያቄ ግን ተመራማሪዋቹ ተመሳሳይ ምላሽ አላቸው፡፡ ወደ ሶማሊያ፣ ማላዊ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ አረብ፣ ኮንጎ፣ ዚምባብዌ፣ ዛምቢያና ደቡብ አፍሪካ የሚል፡፡

ለረጅም ዓመታት የሳይንቲስቶችን ቀልብ የገዛው ተክል መጠን ሰፊ ጥናት ሲደረገረበት ቆይቷል፡፡ አንዳንዶቹ አደገኛ ሌሎች ለስላሳ ወይም የማይጎዳ የሚል ፍረጃ ቢሰጡትም የአፍቃሪዋቹ ቁጥር በእጅጉ ከመበራከት ያገዳቸው ሁኔታ የለም፡፡ መልከ መልካሙ  ቅጠል በየሀገሩ የተለያየ ስያሜ ቢሰጠውም ከቤት መድፊያ አንጻር ተመሳስሎ ይንጸባረቅበታል፡፡ በኢትዮጽያ ጫት፣ በአረብ ጃት፣ በየመን ካት ወይም ጋት፣  በሶማሊያ ጃድ፣ በኬንያና ታንዛንያ ሚራ ይባላል፡፡ ለመጀመሪያ ግዜ በኢትዮጽያ ወይም በየመን በቀለ የሚባልለት ‹ ካት . በብዙ ሀገሮች ዘንድ እንደ እርኩስ መንፈስ ተቆጥሮ / በርግጥ ቀደም ባሉት ግብጻዊያን የሰማይ ቤት ምግብ እንደሆነ እምነት አላቸው / የህግ አጥር ቢበጅለትም እንደ ጀት በፈጠነ ሩጫው ገብኝቱን ከማጠናከር ወደ ኃላ አላለም፡፡  የቅርብ ግዜ መረጃዋች እንደጠቆሙት ከሆነ ‹ ጃድ › በእንግሊዝ፣ ጣሊያን፣ አምስተርዳም፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ ኒውዚላንድና አሜሪካ ታይቷል፡፡

ጫት እንደ ክፉው ሰይጣን በቀን ሺህ ግዜ ይወገዛል ፡፡ አደንዛዥነቱ፣ የሱስ ተገዢ ማድረጉና የስራ ባህልን መጉዳቱ፣ ከጥርስ ጀምሮ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ ጉዳት ማስከተሉ፣ አልፎ አልፎም የአእምሮ ስርዓትን በማፋለስ ለቀውስነት እንደሚዳርግ ሳይንሳዊ እውነታዋችን ዋቢ በማድረግ የማስጠንቀቂያ አታሞ ይደለቅለታል፡፡ በተቃራኒው ጎን ደግሞ ሺ ግዜ ይሞገሳል ፣ ይገጠምለታል ፣ ይጠቀስለታል ‹ የቃመ ተጠቀመ ፣ ያልቃመ ተለቀመ › ዓይነት ...

ዛሬ የከተማን ህጻን ጅብ ይበላሃል ብለው ቢያስፈራሩት ባማረ መልኩ ይስቅቦታል፡፡ ምክንያቱም ከተሞች ጅብን የሚያሳድር ጫካቸውን በሚያስፈራሩ ሰዋች መነጠቃቸውን ያውቃልና፡፡ እንደ ህጻናቱ ሁሉ ወጣቱም ሆነ አዛውንት የቂማ ስራዊት በጫት ላይ የተመሰረቱ አስጊ ዜናዋችን የሚያዳምጠው ጫት እየቃመ ነው፡፡ ከመደንገጥ ይልቅ ፈገግ ይላል፡፡ ፈገግታው መቼም ለምጸት እንጂ ለኮረኮረው እውነታ ቅርብ ሆኖ አይመስልም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ምጸቶች ደግሞ ኅልቆ መሳፍርት የሆነ ፍቺ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ እንደው ሲያቀብጠኝ እንደሚከተለው እያሰበ ይሆን እላለሁ ?

እሳቤ አንድ፣

ደራሲው በመጣጥፉም ሆነ በግጥሙ ጫት እንዴት ትውልድን እያደነዘዘና እየገዘገዘ መሆኑን በሚያስጨበጭብ መልኩ ይገልጸዋል፡፡ የተጨበጨበለትን ስነጽሁፍ የደረሰው ግን ኮባውን ትራስ፣ እንጨቱን መፋቂያ፣ ቅጠሉን መስተፋቅር አድርጎ ነው፡፡

እሳቤ ሁለት፣

ጋዜጠኞች በአንደኛው መታወቂያቸው ሀሳቡን ደጋግመው ወቅጠውታል፡፡ ምናልባት የቀራቸው ‹‹ በርጫ ›› የሚል ቋሚ አምድ ወይም ፕሮግራም ማስጀመር አለመቻላቸው ነው፡፡ በሁለተኛው መታወቂያቸው ላይ ‹‹ ለዚች ዓለም ዱካክና ድብርት ሳትበገር ሀቃራህን ፍታ ! ›› የሚል ጽሁፍ በትልቁ ይታያል፡፡ ይህ ጽሁፍ የሚገኘው ‹ ብሄር › የሚለው ሰረዝ ላይ ነው፡፡

እሳቤ ሶስት፣

ሙዚቀኛው ምርጥ ግጥምና ዜማን ለማፍለቅም ሆነ ለመምረጥ ተመስጦ ፍቱን መሳሪያ መሆኑን ያምናል፡፡ ተመስጦውን ተግባራዊ ለማድረግ ግን ዮጋን ሳይሆን በለጬን አስበልጧል ፡፡ በህንድ የተመሰረተው ዮጋ ሂንዱዚም፣ ቡዲሂዝም፣ ጄይኒዝም፣ ሲኪዝም በተባሉ የእምነት እቅፍ ውስጥ ያደገ ነው፡፡ ታዲያ በዮጋ ለሰዓታት ተቆራምዶ የማይታወቅ የ< ኢዝም > ባህር ውስጥ ሰምጦ ማን ይንቦጫረቃል ? ከማያውቁት መልዓክ የሚያውቁት ሰይጣን እንዲሉ ይልቅ ሳቅ፣ ደመቅና ቦርቀቅን አስቀድሞ ጨመቅና ደንዘዝን ለሚያስከትለው ቅጠል የአውሊያን መንገድ ማሳየት ይበልጣል ፡፡

እሳቤ አራት፣

መንግስት በአደባባይ ያወግዘዋል ፤ ከበስተኃላ በጫት የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ እንዴት የሆነ እጥፍ መጨመር እንደሚገባው ከብጤዋቹ ጋር እየገመገመ አቅጣጫ ያስቀምጣል፡፡

አስደሳች ማስተካከያ ፤ ደራሲ፣ ጋዜጠኛና ሙዚቀኛ የሚለው ሀሳብ ፊት ‹‹ አንዳንድ ›› የምትል ሚዛናዊ ማድረጊያ ቃል እንዳለች በውስጠ ዘ ይታወቅልኝ !!

ታዲያ እንዲህ እየተወገዘ የሚለመልም ተክል እንዴት የአጋሮቹ ቁጥር ሊቀንስ ይችላል ?  ‹ ሚራ ›  የሚያስገኘው ጥቅም ከፍተኛ ከመሆኑ አንጻርም በእርሻ ክፍለ ዘርፍ ውስጥ ግዛቱ ሰፊ እየሆነ ነው ፡፡ ለምሳሌ በየመን 40 ከመቶ የሚሆነው የውሃ አቅርቦት በመስኖ የሚጓዘው የጫት ተክልን ሊያለማ ነው፡፡ በ2001 በተደረገ ጥናት የየመን አርሶአደር ከአንድ ሄክታር ፍራፍሬ 0.57 ሚሊዮን ሪያል ሲያገኝ የጫቱ ገቢ ግን 2.5 ሚሊዮን ሪያል ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ጫት የሚበቅልበት 8ሺህ ሄክታር በ2000 ዓ.ም 103 ሺህ ሄክታር ደርሷል፡፡ ኢትዮጽያ በምትልከው ጫት በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ እያገኘች በመሆኑ እንደ ቃሚው ሁሉ የእርሻ መሬቱም ግዛቱን እያሰፋ መጥቷል፡፡
 

የጫት አርሶ አደሮቹም በየግዜው ቃለ መጠይቅ ሲደረግላቸው ፤ ከፍተኛ ገቢ አግኝተንበታል … አነስተኛ ውሃ ነው የሚፈልገው… የማይበጠስ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ቁርኝት አለው / በሰርግ፣ በለቅሶ፣ በጸሎት ወዘተ ወቅት ይቃማል / … እንደ ሌሎች ሰብሎች ጉልበታችንን አይበላም… እንደ ምግብም ያገለግላል… ወዘተን የሚገልጹት በታላቅ መተማመን ነው ፡፡ 
ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ  አንድ ተጠቃሽ ቀልድ ትዝ አለኝ ፡፡ አንዳንዶች እውነት ነው ቢሉትም እኔ አስተማማኝ መረጃ ባለማግኘቴ ጉዳዩን ብቻ አነሰዋለሁ ፡፡ ሀረር ውስጥ በቀረበ አንድ የ ‹ ልጅ ቀለብ ይቆረጥልኝ › ክስ ፍርድ ቤቱ የተከሳሹን ወርሃዊ የደመወዝ ገቢ መሰረት በማድረግ ቀለብ እንዲቆረጥ ውሳኔ ይሰጣል ፡፡ ሆኖም ተከሳሽ በፍርድ ቤት የተቆረጠበት የገንዘብ መጠን ፈጽሞ አልዋጽልህ ይለዋል ፡፡ ስለሆነም የይግባኝ አቤቱታ ለይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ያቀርባል ፡፡ ተከሳሹ በይግባኝ አቤቱታው ላይ ቅሬታውን ሲያሰማ ‹‹ የተከበረው ፍርድ ቤት በዚህ የኑሮ ውድነት ደመወዝ ከምግብና ከበርጫ እንደማታልፍ እየታወቀ …. ›› ብሎ በመናገሩ ፍርድ ቤቱ  የቀለብ መጠኑን ሲወስን  ‹‹ በርጫን ›› ግምት ውስጥ ማስገባት እንደነበረበት በአጽንኦት ተከራክሯል ፡፡  
ታዲያ ጫትንና እንደ አንዳንዶች አገላለጽ ‹  ጫታም ትውልድን › እንዴት ነው ማረቅ  የሚቻለው ?  ሲሰድቡትም ደስ የሚል ፣ ሲቅሙትም ደስ የሚል ነገር እንደምን ማጥፋት ይቻላል ? ለምሳሌ ጫትን ሳንቲም አድርገን ብንወስደው በሁለቱም ፊቱ አንድ አይነት ምስል ነው ያለው ፡፡ ወይ ጎፈር ወይ ዘውድ፡፡ ሁለቱንም ምስሎች በግድ እንኳን ብናጠፋ ሳንቲሙ ሳንቲም የመባሉ ጉዳይ ያበቃለታል፡፡  ጫት የማይነገር ከፍተኛ ክብር እንዳለውም ማወቅ ይገባል፡፡ የውጭ ምንዛሪ በማምጣት የቡና ተከታይ በመሆኑ እስካሁንም የብር ሜዳሊያ አጥላቂነቱን የነጠቀው ምርት የለም፡፡ ወደፊት የኢኮኖሚ ዋልታ በርጫ በርጫ… ተብሎ አይዘፈንለትም ብሎ መከራከር ጠባብ ዕድል እንደመያዝ ያስቆጥራል፡፡

‹ ለሁሉም ግዜ አለው ! › የተሰኘውን የጠቢቡ ሰለሞንን ምሳሌ የተዋሰው የሚመስለው ‹ ጫት › በኢትዮጽያ ሌላ ታሪክ መፍጠር ችሎ እንደነበር ስንቶቻችን እናውቃለን ?  ነገርን ከስሩ ውሃን ከጥሩ ነውና አጭር ትረካ ላስከትል …

 በአንድ ወቅት ዶ/ር እያሱ ኃ/ስላሴን ለማነጋገር ካሳንችስ ወደሚገኘው ክሊኒካቸው አምርቼ ነበር ፡፡ ሀኪሙ በመደበኛ ከሚሰጡት የህክምና አገልግሎት ውጪ በስነ ተዋልዶና በኤችአይቪ ዙሪያ ምሽት አካባቢ ለህብረተሰቡ ትምህርት ይሰጣሉ፡፡ በተጨማሪም የምርምር ስራዋችን ያከናውናሉ፡፡ በወቅቱ እኔን የሳበኝ በጫት ቅጠል ላይ ያደረጉት ምርምር ነበር ፡፡ መጀመሪያ በኢትዮጽያ ጫት በሚበቅልባቸው አካባቢዋች በመዘዋወር የጫትን አጠቃላይ ባህሪ አጠኑ፡፡ በተለይም የአደንዛዥነቱና የምርቃና ደረጃው ምን ያህል ነው ?  አንዱ ከሌላው እንዴት ይለያል ?  የሚለውን ማለት ነው፡፡ እሳቸው እንደነገሩኝ ጫት ከተቆረጠ ከ48 ሰዓታት በኃላ የማነቃቃት ኃይሉን ያጣል ፡፡ ከዚህ አንጻር ጫት ከነማሪዋናና ኮኬይን ጋር ተጨፍልቆ የሚሰደበውና የሚወገዘው አለኃጢያቱ ነው እንዴ ?  የሚል ጥያቄ ማንሳት ነውር የለውም ፡፡

እናም በአንጻራዊነት ለስላሳ ከሚባለው ዕጽ የምርምር ውጤታቸውን ይፋ አደረጉ ፡፡ የጫት ቪኖ ተሰራ !! የቪኖው የአልኮልነት መጠን ከአስካሪ መጠጦች ደረጃ ጋር ሲነጻጸር ዝቅ ያለ ነበር ፡፡ ይህንንም ደረጃ መዳቢዋች በመሄድ እንዲረጋገጥ አድርገዋል፡፡ እኔም ታሽገው ከተቀመጡት ቪኖዋች ለሙከራ ስለተሰጠኝ ማጣጣም ችያለሁ ፡፡ ወደ ጫት የተጠጋው መዓዛ በስሱ ነው የሚታይበት ፡፡ እንደ መደበኛው ቪኖ ጉሮሮ ላይ የሚያግደው ነገር ሳይኖር ቁልቁል ከብለል ይላል ፡፡ የዶክተሩ እቅድ ሰፊ ነበር ፡፡ ምርቱን በስፋት ወደ ውጭ በመላክ ለራሳቸውም ሆነ ለሀገር የገቢ ምንጭነት ማሳደግ ፡፡ ሆኖም ከመድሃኒትና ቁጥጥር መ/ቤት ጋር በግዜው መግባባት ላይ መድረስ አልቻሉም ፡፡ ዛሬ ባለሙያው ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ አላውቅም ፡፡ በመሆኑም በኢትዮጽያ የተፈጠረው የጫት ቪኖ እውቅና ሳያገኝ ተድበስብሶ ቀርቷል ፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ እነ የመን ኮፒ ፔስት ከተጠቀሙ ሌላ የጭቅጭቅ ምዕራፍ ሊከፈት አይደል ? ይልቅ ዛሬ- ዛሬ በጣም የምታስፈራው ቻይና ናት ፡፡  ሀገራችን ብቅ ጥልቅ የሚሉት ዜጎቿ አሳምረው መቃምና መጨበስ ጀምረዋል ፡፡ ታዲያ ተከታዩ ጉዳይ ቪኖ አይደለም የድሃ ውስኪ መስራት ላይ አያነጣጥርም ማለት አይቻልም ፡፡ 

ዞሮ ዞሮ የቪኖው ሀሳብ  በራሱ ገራሚ ነው ፡፡ ምነው ቢሉ ቪኖው በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ ቅቡልና ካገኘ  ‹ አደገኛ › ፣ ‹ እርኩስ › ፣ ‹ የጥፋት ቀለሃ ›  ወዘተ የሚሉ ቅጥያዋችን አራግፎ ለውዳሴ ይበቃል ፡፡ ቪኖው አሪፍ ጣዕም ስላለው እንደ ‹ ወይን ሃረጊቱ › እና የ ‹ ሾላ ፍሬነሽ › ሊገጠምለት ወይም ሊዘፈንለት ላለመቻሉስ ርግጠኛ የሚሆን ማን አለ ?

የጫት ብይን ምን ይሁን ታዲያ ?
.  እየተወገዘ የሚለመልም
.  እየተነቀፈ አጋር ያደመቀው
.  ሳይዋጋ የሚማርክ  ፡፡

No comments:

Post a Comment