Tuesday, July 16, 2013

ጥርስ የሚፍቁ መስሪያ ቤቶች



1 . ‹‹ እንደ ተቋም ጥፋት ስላጠፋን ይቅርታ እንጠይቃለን ›› የሚለው መግለጫ የሚጠበቅ ስለነበር የሚያስገርም አልሆነም ፡፡ አስገራሚ የሆነው የሚጠበቀው መፍትሄ ሊፈታ ያልቻለ እንቆቅልሽ መሆኑ ነው ፡፡ የተጎዳውን ህዝባዊ ስሜት ለመጠበቅ ከሞራልና ህግ አንጻርም ሊሰራበት ያልተቻለን ስልጣንን ለሚሰራ አካል ማስረከብ ግድ ነውና አመራሩ ለራሱ ቀይ ካርድ እንደሚያሳይ ተጠብቋል ፡፡
ግን አልሆነም ፡፡

‹‹ ሁለት ቢጫ ማየት በምንያህል ተሾመ ይብቃ ! ›› ሲል የአቋም መግለጫውን አሰማ ፡፡ ይህ መግለጫ ደረቅ አይሆን ዘንድም ጥቂት የእግር ኳሱና የአመራሩ አባላት በጥፋተኝነት ቅባት እንዲዋዙ ተደረገ ፡፡ የፌዴሬሽኑ አመራር አካላት በህዝብ ለቀረበላቸው የልቀቁ ጥያቄ ‹‹ በክረምት ቤት አይገኝም ! ›› በሚል ሰበብ ለራሳቸው የወራት እድሜን ጨምረዋል ፡፡ በውስጣቸው  ግን  ‹ ይህ ስልጣን በመልቀቅ ሀብታም የሆነው የአውሮፓ ፌዴሬሽን አይደለም ! › ማለታቸው ይገመታል ፡፡

መቼም ይህ ፌዴሬሽን እንደ ሁላችንም ጨዋታ ተመልካች እንጂ መንገድ አመላካች አልሆነም ፡፡ ምንም ስራ እንደሌለበት ፊውዳል ክቡር ትሪቡን ላይ ቁጭ ብሎ ጥርሱን እየፋቀ ይባስ ብሎ ግራና ቀኝ ሰው መኖሩን በመዘንጋት የቆሸሸ ምራቁን ጢቅጢቅ .. በማድረጉ ስንቱን የዋህ ህዝብ ለማዲያትና ለጨጓራ በሽታ ዳረገ ?

2 . አንድ ሰሞን ከነዳጅ መውጣትና መውረድ ጋር ተያይዞ የትራንስፖርት ታሪፍን ለህዝቡ ይገልጽ ነበር ፡፡ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን ድሃዋ አዲስ አበባ በሚያስገርም ሁኔታ ሀብታም ፎቆችን ሳይቀር ማፈራረስ ይዛለችእግረ ጠባቦቹም ሆኑ ሰፋፊዎቹ መንገዶቿ አዲሱን ሰርገኛ ለማስተናገድ በመፈራረስ ሽርጉድ አብዝተዋል ፡፡

ይህ ያልተጠበቀ ግርግር የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮን ያደናገረው ይመስላል ፡፡ አምስትና አስር ሳንቲም መጨመር የሚቻለው በእኔ እውቅና ነው ይል የነበረው ይኀው ተቋም ዛሬ ታክሲዎች 1 . 35 መንገድን 2 . 70 2 .70 መንገድን 3 . 70 በገዛ ፍቃዳቸው ሲያስገቡ ስልጣኑን ማስጠበቅ አልቻለም ፡፡ ለአብነት ያህል ከጦር ኃይሎች /ፍርድ ቤት በልደታ አድርጎ ሜክሲኮ በመድረሱ ብቻ ዋጋው መቶ ፐርሰንት መድረሱ በእጅጉ የሚያስገርም ሆኗል ፡፡

በዚህ ሁሉ የህግ ጥሰትና ዘረፋ መካከል ቢሮው ጋቢ ደርቦ ቁጭ ብሏል ፡፡ ከሶማሌ ባስመጣው ረጅም መፋቂያ ጥርሱን ደጋግሞ እየፈተገ ከራሱ ጋር እሰጥ አገባ ይዟል  ‹‹ ምን ይደረግ ታዲያ ! የልማት ጉዳይ ነው ፡፡ መንገድ በሌለበትስ ታሪፍን እንዴት ከፍና ዝቅ ማድረግ እችላለሁ ? ››
ከደረበው ጋቢ ይሁን ከግድየለሽነቱ ከመብራት ኃይል ቀጥሎ የላቀ የቸልተኝነት ኃይል እያመነጨ ይገኛል ፡፡ ይኀው ቸልታው ግን  ‹ እንኳን እናቴ ሞታ ድሮም አልቅስ አልቅስ ይለኛልየሚለውን የከተማ ነዋሪ ለጉዳት እየዳረገው ነው ፡፡ አዲሱ ሰርገኛ የሚመጣው ከሁለትና ሶስት ዓመታት በኃላ በመሆኑ ይህ ቢሮም እስከዛ ድረስ የአፉን መደገፊያ ላይጥል ነው ማለት ነው :: እስከዛ ድረስ ለሚደርሰው ብዝበዛ ማን እንደሚጠየቅ ለጸረ ሙስና ወይም ለእንባ ጠባቂ ግልባጭ ማድረግ ሳያስፈልግ አይቀርም ፡፡

3 .ገንዘብ በመቆጠባችሁ ብቻ እሸልማለሁ ማለት ከጀመረ አመታት አሳለፈ ፡፡ ስልቱም የልማት አጋር ብቻ ሳይሆን የአዲስ አሰራር መንገድ መሆኑን
ነግሮናል ፡፡

ኬር ! ብለናል ፡፡

አዲስና ዘመናዊ መንገድ ብሎ ካስተዋወቀን አሰራር ውስጥ ኤቲኤም ይገኝበታል ፡፡ ይህ ካርድ የተሰጠን ግዜ ላላፊው አግዳሚው ብቻ ሳይሆን ለራሳችንም አስር ግዜ ከኪሳችን መዥለጥ እያደረግን አስኮምኩመነው ነበር ፡፡

መሰለፍ ድሮ ቀረ ብለናል ፡፡
ብር እንደ አበሻ ጎመን ከቅርባችን ሊቀነጠስ ነው ብለናል ፡፡

ይሁን እንጂ እነዚህ ማሽኖች በአጭር ግዜ ውስጥ በበሽታ ማስነጠስ ጀመሩ ፡፡ ቀስ በቀስም የሚከበሩ ዋንጫዎች ሳይሆኑ ባዶ ቆርቆሮ መሆናቸውን አስመሰከሩ ፡፡ እንደ ወንድማቸው የመንገድ ስልክ የነሱንም ወገብ በፍልጥ የሚነርት በዛ ፡፡ የአራዳ ልጆች አናታቸውን ከፈት አድርገው ቆሻሻ ይጥሉበት ነበር ፡፡ ይህ ከመሆን ለጥቂት የተረፈው ቆርቆሮዎቹ የቆሙት ጥበቃ ያለበት አካባቢ መሆኑ ነው ፡፡ አልፎ አልፎ የሚሰሩት ደግሞ ሰው ብር በሚፈልግበት ቅዳሜና እሁድ ለጥቂቶች አገልግለው ጎተራቸው ባዶ መሆኑን ያውጃሉ ፡፡
የታመመውን ዘመናዊነት መታደግ የደከመው የኢትዮጽያ ንግድ ባንክ ነው እንግዲህ በአናቱ ላይ ስለ ቁጠባ ሳያሰልስ የሚጨቀጭቀን ፡፡ አንዳንዶች ዘወትር ለስራ የሚጠቀሙትን አንዳንዶች ወር ጠብቀው የሚያገኙትን ደመወዝ ለመቀበል ሲሄዱ ‹‹ እንኳን ደህና መጣችሁ ! ›› የሚለው ትሁት ቃል አይጠብቃቸውም ፡፡ ደንበኛን የማያስቀይመው ንግድ ባንክ ግን ተመሳሳይ ቃል አመንጭንቷል ፡፡

‹‹ ኮንኬሽን የለም ! ›› የሚል
‹‹ ዛሬም ?! ››
‹‹ ምን እናድርግ ? ቴሌ እኮ ነው ?! እጀ ሰባራ አደረገን ! ››
‹‹ ታዲያ ሌላ አማራጭ የለም ? ››
‹‹ ምን ይምጣ ? የለም ! ››
‹‹ ወይ ጌታዬ ምን ይሻል ይሆን ? ››
‹‹ ሌላ ቀን ብቅ ማለት ወይ እስኪመጣ መጠበቅ ነዋ ! ››
‹‹ መቼ ይመጣ ይሆን ? ››
‹‹ እንጃ ! ቴሌም አያውቀው ! ››

ስለ ዘመናዊነት የሚያወራው ባንክ ስራውን ከቴሌ ጋር በጋራ ተስማምቶና ተነጋግሮ እንደጀመረ ይገመታል ፡፡ ግን ጉልቤው በየቀኑ ሲቆነጥጠውና ሲያሸው ሊታገለው ሊቃወመው ሊገስጸው አልደፈረም ፡፡ ስለዚህ ብር አስቀማጩ ባንክ አስር አለቃ የአየሩ አክሮባቲክስ ቴሌ ኮሎኔል መሆናቸውን ለመገመት እንገደዳለን ፡፡ ጂኔራሎቹን ያው መገመት ይቻላል ፡፡
በዚህም ምክንያት አዳራሽ የሞሉት ባለከራባት ሰራተኞች ወንበር ላይ ተለጥጠው ጣራ የነካ ብር ተደግፈው ጥርሳቸውን መፋቅ ይጀምራሉ ፡፡ ትዕግስተኛው ህዝባችን ደግሞ ከመስታውቱ ጀርባ እጅብ ብሎ አፋፋቃቸውን በጥብቅ ይመለከታል ፡፡

‹‹ አለ መፋቂያ ! መፋቂያ  ! … የክትክታየቀረሮየዋንዛ
  የሚያሳምር  … የሚያወዛ ››

የሚል ድምጽ ስማ ስማ አለው ጆሮዬን ::

Monday, July 15, 2013

‎መቼ ነው የሀገራችን መንጃ ፍቃድ የሞት ፍቃድ የማይሆነው ?‎



ሞጆ ---- ሰኔ 2005 . ፡፡

የምሽት ጉዞ ክልከላን የናቀ ወይም ያልተቀበለ ሾፌር እንደሚግ እየተወረወረ መንገድ ላይ ከቆመ ትልቅ መኪና ጋር ተላተመ ፡፡ በተአምርና በተለየ ብልጠት ካልሆነ በስተቀር አንድ ሚዳቆ ዝሆንን ገፍታ ከቦታው ታርቃለች ማለት ይከብዳል ፡፡

የሆነው ግን ይኀው ነው ፡፡

ከዝዋይ ወደ አዲስ አበባ የሚፈተለከው ዶልፊን ሚኒባስ ተበላሽቶ የቆመውን ትልቁን ማርቼድስ ከነበረበት 50 ሜትር ርቀት አፈናጠረው ፡፡ ወደ ገደላማ ቦታም ሰደደው ፡፡ ሀገር ሰላም ብለው መኪና ውስጥ የተኙ ሰዎች ከለሊቱ አስር ሰዓት መኪናው ሲንቀሳቀስ በእንቅልፍ ልባቸው ወደ አንድ ጋራዥ እየተጓዙ ቢመስላቸው አያስገርምም ፡፡ ነቅተው ያሉበትን ሲረዱ ግን በታላቅ ድንጋጤና ሽብር ተርበተበቱ ፡፡ ከአደጋው መትረፋቸውን ሲያረጋግጡም ስሜታቸው ተዘበራረቀ - ደስታና ፍርሃት ፡፡

ወዲህ  22 ሰዎችን የጫነው ሚኒባስ አንድ ከዝሆን የተሰራ ሰው እንደ 4 ጨምድዶ ወደ ቅርጫት የወረወረው ወረቀት መስሏል ፡፡ ጭምድዱ በቁርጥራጭ የሰው ልጆች ስጋና አጥንት የተሞላ ቢሆንም መጠኑን አላሳደገውም ፡፡ ያለቅጥ ተደራርበው ከተጫኑት 22 ተሳፋሪዎች መካከል ሹፌሩን ጨምሮ 16 ንጹሃን ነፍስ በምሽቱ ተቀጠፈ ፡፡ የሀገራችን መኪና አደጋ ከዚህም በላይ ቁጥር በማስመዝገብ የሚታወቅ ቢሆንም የአሟሟቱ ሰቅጣጭነት ግን ከእስከዛሬው ሁሉ ይጎፈንናል ፡፡ የሰው ልጅ አንገት እዚህና እዚያ እንደ ጎልፍ ኳስ በሯል ፡፡ አካል ከዶሮ በቀጠነ መልኩ በግድ ተበልቷል ብቻ ሳይሆን ለመልቀም በሚያስቸግር መልኩ ተጨፈላልቋል ፡፡ ‹‹ የዉሃ ያለህ ! ›› በሚባልበት ሀገር ደም ያለ ቆጣሪ ፈሷል ፡፡

አለልቱ --- 1999 ፡፡

ከወደ ላይ የጣለው ዝናብ ጎርፍ ወልዶ የመኪና መንገድ ላይ ይደነፋል ፡፡ አንድ የቀይ መስቀል አምቡላንስ ለስራ ተጣድፎ ሳይሆን አይቀርም ጎርፉን ገፍቶ ለማለፍ ሲሞክር ወደ ወንዙ ይወድቃል ፡፡ ይህ ሲሆን በርካታ ሰዎችን የጫነ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ከኃላ ይመለከታል ፡፡ ሞተሩን በደንብ ኮርኩሮ ወደፊት ተንቀሳቀሰ ፡፡ ‹‹ እባክህ አትዳፈር ! ጥቂት ትዕግስት ይኑርህ ! ›› የሚሉ ድምጾችን ለማስተናገድ ፈቃደኛ አልሆነም ፡፡ ጎርፉን በጭንቅላቱ ሳይሆን በመኪናው ትልቅነት የመዘነው ሾፌር በማታውቁት ጥልቅ አትበሉ / በሆዱ ነው / በሚል እሳቤ ከባላጋራው ጋር ግብግብ ገጠመ ፡፡ ጥሶት ሊወጣ ተንፈራገጠበንዴት ጓጎረጎርፉ ግን እያስጮኀውም እያሳሳቀውም ገለበጠው ፡፡ የበርካታ ንጽሀን ነፍስም ለሰሚ በሚከብድ መልኩ በጎርፉ ተቀረጠፈ ፡፡

በጣም ትዝ ይለኛል ትራፊክ ፖሊስ ‹‹ ቸልተኛና ሃላፊነት የማይሰማው ! ›› በማለት ነበር ሾፌሩን ያወገዘው ፡፡ ይህ አይነቱ ወቀሳና ስያሜ በሀገራችን ዕድሜ ጠገብ ቢሆንም ዛሬም ሰንሰለቱ መጠናከሩን እንጂ ያለመበጠሱን የሞጆና አለልቱ ታሪኮች ያመላክታሉ ፡፡ የሞጆው አደጋ በተከሰተ በሶስተኛው ቀን በሱሉልታ ሚኒባስ 13 ሰዎችን ጨርሷል ፡፡ ጊዮርጊስ ከሀዋሳ ከነማ ለነበረበት ጨዋታ ወደ ሀዋሳ ሲጓዙ መቂ ከተማ ላይ መኪናው በመገልበጡ ሁለት ደጋፊዎች ሲሞቱ ሁለቱ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል ፡፡ በአዲስ አበባ በየቀኑ የትራፊክ አደጋ ከነሞቱ ፣ጉዳቱ እና የንብረት ውድመቱ ተመዝግቦ ለጆሮአችን እንደ ቁርስ ይቀርባል ፡፡ በቅርቡ ወደ ጎንደር ሁመራ ቋራና ጅጅጋ ለስራ አቅንቼ ነበር ፡፡ በሁሉም መስመሮች በጣም በተቀራረበ ርቀት በሚያሳዝንና በሚሰቀጥጥ መልኩ ከቤት መኪና እስከ ተሳቢዎች በየመንገዱ ተጨማደውና እግራቸውን ሽቅብ ሰቅለው በየገደሉ ‹ ዳይቭ › ጠልቀው ተመልክቼያለሁ ፡፡ ብዙዎቹ ሞተዋል፣ ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል ሀብት ወድሟል ፡፡

ያስደነግጣል ፡፡

ወዴት እየሄድን እንደሆነ በቅጡ አልተፈተሸም ፡፡ ከጠጡ አይንዱ ፣ ከነዱ አይጠጡ የሚለው የዘወትር ምክር ከመልዕክቱ ይልቅ ጥቅስነቱ ያሸበረቀ መስሏል ፡፡ አደጋውን የሚያስገነዝቡ የነሞገስ ተካና መሰል ድምጻዊያን ዘፈን ከእንጉርጉሮነት ለምን አላለፉም ? ከፕሮግራም ማዳመቂያነት ወይም የአየር ሰዓት መሙያነት ለምን አልተሻገረም ? … በጫት ምርቃና ፣ እጅን ከመሪና ማርሽ ይልቅ ለሞባይል በማዋል ፣ በአጉል ጀብደኝነት ፣ ያለ በቂ ችሎታ በማሽከርከር ፣ አይን የመንገድ እንቅስቃሴን ከመቆጣጠር ይልቅ የሴት ዳሌ ላይ እንዲያሸልብ በመፍቀድ ፣ ከፍጥነት በላይ በመሮጥ ፣ ተሸከርካሪን መንጃ ፍቃድ ለሌለው ሰው አሳልፎ በመስጠት ወዘተ … የሚሉ ምክንያቶች የሞታችን መንስኤ ከመሆን መቼ ያቆማሉ ?

እኛና ወዘተ የተባለው ነገር የተጋመድንበት ሰንሰለት ያስገርማል ፡፡

ማለት ፈረንጅ ሲባል ሁልግዜ መኪና ይፈበርካል ፤ አበሻ ሲሆን ሁልግዜ በመኪና ሰውና እንስሳትን ይገድላል ሊሆን ነው ፡፡ ለነገሩ ወደ ሀገራችን  ብቅ የሚለው የውጭ ዜጋ ልክ እንደ ቪዛው ‹‹ ኢትዮጽያ  ውስጥ አትንዳ ! የግድ ሲሆን እንጂ ከመሳፈር ይልቅ እግርህን እመን ! መስቀለኛ መንገድ ላይ ስትሻገር እንኳ የቆሙ መኪናዎችን ተገላመጥ ! ›› የሚል የቃል ይለፍ መቀበሉም ይረጋገጣል ይባላል ፡፡ ይህን ምጸት ተራ የሀገሬ ሰውም ገና ድሮ ‹‹ መንጃ ፍቃድ የሞት ፍቃድ ! ›› በማለት አጠናክሮት እንደነበር አይዘነጋም ፡፡ የተማረውና ምርምር አድርጌበታለሁ የሚለው ከረቫት ለባሽ ደግሞ ‹‹ በተሸከርካሪ አደጋ ሶስተኛ ደረጃ ላይ እንገኛለን ›› በማለት በየስብሰባው ከጣፋጭ ኩኪስ ጋር እንድናወራርደው ያደርጋል ፡፡

እነዚህ ሁሉ ምጸቶች ምን ያሳዩናል ? የሚከተሉትን ምርጫዎች በጥሞና በማንበብ ትክክለኛውን ምላሽ ለአፍታ ያንሰላስሉ ?

ሀ . ትላልቅ መኪናዎች ትላልቅ እቃዎች ለማጓጓዝ በእጅጉ ጠቃሚ የመሆናቸውን ያህል ትላልቅ በሬዎችንና ግመሎችን መጨፍለቃቸው የሚጠበቅ ነው ፡፡
ለ . ትንሽ በማይባሉ ትራፊክ ፖሊሶች ባሉበት ሀገር በጠራራ ጸሃይ ህጻናትን እንደ ሰርዲን አጭቀው የሚሮጡ ታክሲዎች ሲፈልጉ እንዲሞቱ ይፈርዱባቸዋል ፡፡
ሐ . ሾፌሮች ፍሬን አልታዘዝ ሲላቸው  ከስልክ እንጨት ፣ ከድንጋይ አጥር ወዘተ ጋር ከማጋጨት ይልቅ ቤት ደርምሰው የሚገቡት ‹‹ ዞሮ ዞሮ ከቤት ኖሮ ኖሮ ከመሬት ›› ለሚለው ጥቅስ ከፍተኛ አክብሮት ስላላቸው ነው ፡፡
መ . ቶራ ቦራ ተራራን የሚወደው አልቃይዳ እና አይሱዙዎች የሚያመሳስላቸው ራሳቸውንም ሌሎችንም ለማጥፋት ወደ ኃላ የማይሉ በመሆናቸው ነው ፡፡

ምርጫዎቹ በመኪናዎቹ አይነቶች ላይ ያነጣጠሩ ይምሰል እንጂ በውስጡ ተአምረኛው ወይም ምንተስኖት ሊባል የሚችለው ‹‹ አበሻ ›› መኖሩ ይታወቃል ፡፡ ‹‹ ምንተስኖት ›› በሞት ፍቃዱ አሰጣጥ ላይ ሳይታወቀው ድጋፍ የሚሰጥበት ሁኔታም ይታያል ፡፡

አይሱዙን እናንሳ ፡፡

የእነዚህን መኪናዎች ስያሜ ‹‹ አልቃይዳ ›› በማለት ዳቦ ቆርሷል ፡፡ መኪናዎቹ ለመገልበጥ ሾፌሮቹ ደግሞ ለመጋጨት ቅርብና ዝግጁ በመሆናቸው ነው ስያሜውን ያወጣው ፡፡ ህብረተሰቡ ሌላው ቢቀር መንጃ ፍቃድና የእቁብ ገንዘብ ለመጠየቅ ወደ ኃላ የማይለው ትራፊክ ፖሊስ እውቅና የሰጠውን ይህን ስያሜ እነሱም በደስታ መቀበላቸው ማስገረሙ አይቀርም ፡፡ የማይቃወመው ፣ የሚያጨበጭበውና አንዳንዴም የሚያሸልበው  የሀገራችን ፓርላማ  ‹‹ አሸባሪ ›› ብሎ ስማቸውን በአዋጅ ካሰፈረው ድርጅቶች መካከል ‹‹ አልቃይዳ ›› አንዱ መሆኑን ቢሰሙ እንኳ ደንታ የላቸውም ፡፡

 
ዛሬም በከተማም ሆነ በገጠር  እንደ ጄት ሲሮጡ ፖሊሱ ፣ መንገደኛውም ሆነ መኪናው ዳር ይዞ ያሳልፋቸዋል ፡፡ እኛ ለእኩይ ተግባራቸው የእውቅና ዲፕሎማ መስጠታችን እነሱ ደግሞ ይሄንኑ ሆይ ሆይታና ሳያገናዝቡ በአስፈሪ ተግባራቸው መቀጠላቸውን ቆም ብሎ ለመረመረ ገረሜታን ሳይጭር አይቀርም ፡፡ ለመሆኑ በሀገራችን መኪና የሚነዳው ለምን ዓላማ ነው ? አሽከርካሪና ተሸከርካሪ ማለትስ ? … ልብ ብላችሁ ካሰባችሁ መኪናው ያለተግባሩ የ ‹‹ ጥይት ›› ን ቦታ ተክቶ እየሰራ ነው ፡፡ አሽከርካሪው ደግሞ ቃታ ሳቢ ወታደር … እና ነገሩ እንደዚህ የሚታሰብ ከሆነ ሰላማዊ ሰዎች ከተባራሪ ወይም ደግሞ ከአባራሪ ጥይት ራሳቸውን ለማዳን በየትኛው መንገድ ይሂዱ ? ..

ለነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት ትልቁን ድርሻ የሚወስደው መንግስት መሆኑ አያጠያይቅም ፡፡ መንግስት አደጋውን ለመቀነስ ለሾፌሮች ሰፊ የቀለምና የተግባር ትምህርት እሰጣለሁ በማለት አሰራሩን ከዘረጋ ቆየ ፡፡ አሰራሩ ስልጡን መሆኑን ለመግለጽ ‹‹ ሁለተኛ መንጃ ፍቃድ ያለው ስልጠናውን እስከወሰደ ድረስ በአንድ ዝላይ ባለአምስተኛ ከመሆን የሚያግደው የለም ! ›› በማለት በመግለጫ ተቀናጣ ፡፡ ይህ አሰራር ግን በየቦታው በስፋት እየታጨደ ያለውን ሞት ለማስቆምና ለህይወት ሁነኛ ዋስትና ለመስጠት ቃል አልገባም ፡፡ ይህ አሰራር እንደምንጠብቀው ምጡቅ ሾፌሮችን ለማምረቱ ልበ ሙሉ መስካሪዎች አላደረገንም ፡፡ ይህ አሰራር ዛሬም መንጃ ፍቃድ ቤት ድረስ በአፋጣኝ መልዕክት ከመድረሱ እንዲቆጠብ ዘብ አልቆመም ፡፡ በዚህ ሳይንሳዊ አሰራር መሰረት የኢትዮጽያ በመኪና የመሞት ሰቆቃ ቢያንስ እንደ እግር ኳሱ ጥቂት ደረጃዎችን ማሻሻል አልቻለም ፡፡ 
ምናልባትም ብሶበታል ፡፡

ታዲያ ምንድነው ዲስኩሩ ?
 ምንድነው ጥሩንባው ?
በየመንገዱ የሚወድቀውን ንጽሃን ቅበሩ ነው ?
መቼስ ነው የሀገራችን መንጃ ፍቃድ የሞት ፍቃድ ላለመሆኑ የተኛው ፓርላማ በነጋሪት ላይ የሚነግረን ?
‹‹ የአመለካከት ችግር ሲቀየር ነው  ›› --- እኮ የማ ?



Tuesday, June 11, 2013

No Dam , No Victory !‎




‹‹ No Money , No Funny ! ››  ሲሉ ነበር ፈረንጆቹን የምናውቃቸው ፡፡ የሙርሲ ሀገር ሰዎች ደግሞ ‹‹ No Nile , No Egypt ! ›› የሚል መዝሙር  ማቀንቀን  ጀምረዋል ፡፡ ይህን ፈሊጣዊ አባባል በጓድ መንግስቱ ዘመን ብንቃኘው ‹‹ እናት ሀገር ወይም ሞት ! ›› ወይም ‹‹ ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር ! ›› የሚል አቻ ምንዛሪ እናገኝበታለን ፡፡

በውስጥ ችግሮች የተጠላለፉት የግብጹ መሪ መሀመድ ሙርሲ በሙሉ አፋቸው ‹‹ አንዲት ጠብታ ውሃ እንኳ አንፈቅድላቸውም ! ›› ብለዋል ፡፡ በጣም የሚገርመው የማይፈቀድልን ውሃ የራሳችን ንብረት መሆኑ ነው ፡፡ ነው ‹ አንዲት ጠብታ አፈር እንኳን ወደ ዉጭ እንዲወጣ አልፈቅድም › በማለት ጫማ አስወልቀው ያስጠረጉ የሀገራችንን መሪ ታሪክ ለመድገም አስበው ነው ? ይህ የተደረገው ደግሞ በሰው ሳይሆን በራስ ኀብት ነው ፡፡ የቀድሞው ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊም በአንድ ወቅት ‹‹ የአባይ ግንባታ ለአንዲትም ደቂቃ ቢሆን አይቋረጥም ! ›› ብለው ነበር ፡፡

አንዲት ጠብታ !
አንዲት ደቂቃ !

ግብግቡን አያችሁት - ማለቴ የውጥረቱን ስስነት ፡፡ መቼም በ ‹ አንፈቅድላቸውም ! › እና በ ‹ አይቋረጥም ! › መካከል እንደ አባይ ወንዝ የረዘመ የእልህ ክፍተት አለ ፡፡ እነዚህ የተንቦረቀቁ ሀሳቦች እንደምን ሊቀራረቡ እንደሚችሉ ማሰብ ለግዜው ግርታ ይፈጥራል ፡፡ እውነቱ ግን የተራራቀው አባባሉና መፈክሩ እንጂ መሬት ላይ ሊለካ የሚችለው ተጨባጭ ተግባሩ አይመስለኝም ፡፡ ምክንያቱም እንደ ግብጾች ቁጣ ከሆነ እኛ ‹ የሬሳ ማጠቢያ የሆነውን ውሃ ለለመነ አይከለከልም › የምንለውን ቅዱስ ብሂል ባለመረዳት አንዲት ኩባያ እንኳ ለጥማታችን ሊሰጡን አልፈቀዱም ፡፡ እንደ ስነ ጽሁፍ ተማሪነት ሰሙን ወደ ጎን ትተን ወርቁን የምንፈልግ ከሆነ ግን የሚሊኒየሙ ግድብ 21 ከመቶ ያህል ተከናውኗል … ተደፈርን በሚል ስሜት ደማቸውን ያንተከተከው የቅልበሳ ስራም ተከናውኗል ፡፡ አንድ አምስተኛ የተከናወነው ስራ ቀስ በቀስ አንድ አራተኛ … አንድ ሶስተኛ … የሚባለውን ስሌት ተከትሎ የግድቡ ገላ እየፈረጠመ መሄዱ አይቀርም ፡፡

ይህም ሲሆን ፉከራው ፣ ቀረርቶው ፣ ዛቻውና ውጥረቱ እየጮኀ - በዝምታ / contradictory / ይቀጥላል ባይ ነኝ ፡፡ ምክንያቱም የሚጮህ ውሻ ሁሉ ፈሪ ቢሮጥለት እንጂ እንደማይናከስ ከልምድ ይታወቃልና ፡፡ በርግጥ የግብጽ ጋዜጦች ‹ ዉሾቹ ይጮሃሉ ፣ ግመሎቹ ጉዟቸውን ቀጥለዋል › የሚል አናዳጅና ነገር አቀጣጣይ ዘገባዎችን ማፋፋማቸው ይጠበቃል ፡፡

‹ እውን ደርግ አለ ? › የሚለውን ታሪካዊና ወጥ አባባል እያስታወስን ‹ እውን ግብጾች አይናከሱም ? › የሚል በአሽሙር የተንጋደደ ጥያቄ ወርወር እናድርግ ፡፡ ርግጥ ነው ድንገት ከኃላ ተደብቆ እግር ስር የሚጮህ ዉሻ እንኳ ቀልብ ይገፋል ፡፡ በዚህም ምክንያት ከቆመ ስልክ እንጨት ጋር ሊያጋጭ ወይም በኮብልስቶን ካልተቀየረ ሹል የወንዝ ድንጋይ ላይ በደረት ሊደፋ ይችላል ፡፡ በተቃራኒው ግብጽ በቀጣይ ልታደርሰው የምትችለው ጉዳት እንደ ሶርያ ከተማ ያፈራርሰናል ብሎ ማሰብ ግን አጓጉል ስጋት ነው የሚሆነው ፡፡

እኮ ለምን ?
ከ 500 በላይ የሚደርሱት ተዋጊ አውሮፕላኖቻቸው በሶ ጨብጠዋል ?
ከ 1 ሺህ በላይ የሚቆጠሩት ተወንጫፊ ሚሳይሎቻቸው በቀፎን ተጨባብጠዋል ?
እነ ኤፍ 16 ፣ ሚግ 17 ፣ ሚግ 21 ፣ አልፋ ጄት ፣ ሚራዥ ፣  የኬሚካል ጦር መሳሪያዎቻቸው ምን ይጠብቃሉ ? መባሉ ግድ ነው ፡፡ እኮ ታዲያስ ?

1 . ለነገርም ሆነ ለአውሮፕላን መንደርደሪያነት እጠቀምባታለሁ የምትላት ሱዳን ግድቡ ጠቃሚ መሆኑን በመረዳት ለሀገራችን ድጋፏን ሰጥታለች ፡፡ ይህ ማለት ደግሞ አንዴ በሞሉት ነዳጅ ከ 1 እስከ 3 ሺህ ኪ.ሜ የሚጓዙት ተዋጊ ጀቶች ግድቡ ጋ መድረስ ቢችሉ እንኳን ሀገራቸው ለመመለስ አይችሉም ፡፡ ርግጥ ነው እንደ አልቃይዳ እዛው እየፈነዳን እናልቃለን ካሉ ምርጫቸው ነው ፡፡ ይህን ምርጫ ለመጠቀም ካሰቡ የኛ የቤት ስራ ገና ድንበራችን እንዳለፉ በመቃወሚያ መልቀም ነው ፡፡ የጋሽ አልበሽር ሀሳብ ነገ ሊቀየር ከቻለስ ? የሚል ስጋት ሚዛን ከደፋም መፍትሄ አይጠፋም ፡፡ ሰውየው በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት በወንጀል ስለሚፈለጉ አንጠልጥለን እንደምንሰጣቸው አስረግጠን ማስረዳት ነው ፡፡

2 . የግብጽ መንግስት ስር ነቀል ለውጥ የሚፈልገውን ህዝብና ወግ አጥባቂዎችን አስተባብሮ ለጥፋት ዓላማ ለመሰማራት ይከብደዋል ፡፡ ምንም እንኳ ህዝቡ አንድ ሆኖ በአባይ ጉዳይ እንዲያተኩር እየቀሰቀሰ ቢሆንም ፡፡

3 . ግብጽ የራሷን የችግር ቁልል ወይም ተሰርቶ የማያልቅ የቤት ስራ ገና አጽድታ አልጨረሰችም ፡፡ ግድቡን አፈራርሳለሁ የሚለው የግብጽ መንግስት በህዝባዊ ተቃውሞ ወይም ባደፈጠው ጦር ሰራዊት ሊፈራርስ አይችልም ማለት አያዋጣም ፡፡

4 . ግድቡ የግብጽንና ሱዳንን ጥቅሞች በከፋ መልኩ የማይጎዳ መሆኑን ሀገራቱን ያካተተውና የገለልተኞች ስብስብ የሆነው አጥኚ ቡድን አረጋግጧል ፡፡ ይህ ውሳኔ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ እንደ ቋሚ ህግ ወይም መመሪያ ሊያገለግል የሚችል ነው ፡፡ ህግን ጥሶ ወደ ጦርነት መግባት ደግሞ ዓለማቀፍ ውግዘትን እንጂ ድጋፍን አያስገኝም ፡፡

5 . ቢያዋጡንም ባያዋጡንም እነ ቻይና ፣ እስራኤልና አሜሪካ የኛ አጋር እንደሆኑ የመገመት ወይም የመፈረጅ አባዜ በምድረ ግብጽ እየተስፋፋ ነው ፡፡ ይህ ጉዳይ ለእኛ መልካም አጋጣሚ ለሚያስፈራሩት ደግሞ ስጋት ይፈጥራል ፡፡ በዚህ ግዜ የሚገኘውን ‹ ቲፕ › መቀበል ይጠቅማል ፡፡

6 . በታሪክ አይን ኢትዮጽያን መተናኮስ ወይም በሃይል ማስገበር ብዙ መስዋዕትነት ሊያስከፍል እንደሚችል ይታወቃል ፡፡ ስለዚህ ግብጾች ክተት ከማወጃቸው አስቀድሞ የጦርነቱን የመጨረሻ ውጤት ከወዲሁ አስልተው መነሳት ይኖርባቸዋል ፡፡

7 . በአፍሪካ ህብረት የላቀ ክብር ያገኘውን የኢትዮጽያ ጦር ሰራዊት ፣ በተመድ ዶላር ብቻ ሳይሆን ኒሻን የተከፈለውን ጦር ሰራዊት አቅም አሳንሶ ማየት የሚቻልበት አግባብ የለም ፡፡ ግዜውም አይፈቅድም ፡፡


እነዚህን የመሳሰሉ ተጨማሪ ምክንያቶችን መዘርዘር ይቻላል ፡፡ ይሁን እንጂ ግብጽ ውክልናንም ሆነ ሰላማዊ የክርክር መድረክን በመጠቀም ልትናከስ የምትችልባቸው አግባቦች አይኖሩም ማለት አይቻልም ፡፡ አንደኛው ራሳቸው እንደተናገሩት በራሳቸውም ሆነ በሌሎች የውጭ ሃይሎች የሽብር ተግባር መፈጸም ነው ፡፡ እንደውም አስፈሪውና ለእውነት የቀረበው ይኀኛው መንገድ ነው 

፡፡ ሁለተኛው ኢትዮጽያ ከአበዳሪ ድርጅቶች ጋር በቂ ገንዘብ እንዳታገኝ የማግባባትና የማሳመን ስራ ማከናወን ይሆናል ፡፡ ይህም በጣም ሊተገበር ይችላል ፡፡ እንዴት ከተባለ ሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የዲፕሎማሲና የነገር ልምድ አካብታለች ፡፡ በሌላ አነጋገር ያደፈ ቢሆንም እጇ ረጅም ነው ፡፡ ግድቡ ጉዳት የለውም የሚለው የኛ መፈክርና እንዴት እንደፈራለን የሚለው የእነሱ ‹ ባላባታዊ ቁጣ › ደግሞ በቀላሉ እንዳንግባባ ያደርገናል ፡፡ ተከብሮ የኖረውን የሳዳትና የናስር መርህ እናስጠብቃለን ሲሉ እኛ ደግሞ የአጼ ቴዎድሮስንና የሚኒልክን ሀገራዊ ተጋድሎና ዝና እንደግማለን እንላለን ፡፡ ይህ ክፍተት በራሱ ለጋሽ ሀገሮችና አበዳሪ ድርጅቶች ወደ አንዱ ወገን እንዳያጋድሉ ያስፈራቸዋል ፡፡ ጭቅጭቁ የሰላም ማረጋገጫ ወይም ዋስትና አልሰጠንም እንዲሉ በር ይከፍትላቸዋል ፡፡ በሌላ አነጋገር ለኛ የተቆለፈው እጃቸው ነገም እንደተከረቸመ ይቀጥላል ማለት ነው ፡፡

አሁን ‹ No Money , No Funny › ወይም ‹ No Money , No Dam ›  የእውነት በኛ ላይ እንዳይሰራ ወይም በብሂሉ ተጠልፈን እንዳንቆም መስጋት አግባብ ይሆናል ፡፡ በርግጥ መሃንዲሱም እኛ ፣ የገንዘብ ምንጩም እኛ መሆናችን ቀደም ብሎ የተገለጸ ነው ፡፡ የግብጾች ትንኮሳ ፣ እብሪትና ማን አለብኝነትም የህዝቡን ቁጭት ለማቀጣጠል የሚያስችል ክብሪት እንደሚፈጥርም ይገመታል ፡፡ መንግስት አሪፍ ከሆነ አጀንዳውን ለሀገራዊ መግባባት ሊጠቀምበት ይችላል ፡፡

እንደዛም ሆኖ ግን ‹ ተራራው የግድብ ብር ›  ላይ ለመድረስ ምስኪኗ የወር ደመወዛችንና የአንዳንድ ባለሃብቶች ለቀቅ ያለ ልግስና ብቻ የትም አያደርሰንም ፡፡ በመሆኑም ያልታዩ አዳዲስ ስልቶች ያስፈልጉናል ፡፡ ለዚህም ስልት መሳካት ቆራጥ ርምጃዎችና ‹ እናት ሀገር ወይም ሞት ! › የሚሉ አመራሮች ያስፈልጋሉ ፡፡

እኮ ለምን ? ምን ሊያደርጉ ?

ብዙ ብዙ ነገሮችን ለማድረግ መጠበብ ያስፈልጋል ፡፡ ቢያንስ ሁለት ክፉ ምሳሌዎችን እንደ ማሳያ ልወርውር ፡፡

. አንደኛ ትንሽ ትልቁ በሙስና እየበላ የሚገኘውን ገንዘብ ጠንክሮ በማስመለስ ለግድቡ እንዲውል ማድረግ ፡፡ ሁለት መቶ ደርሷል የተባለውን ተጠርጣሪ እንደ ትራንስፎርሜሽኑ የተለጠጠ ዕቅድ በመቶ እጥፍ በማሳደግ ካቴና የሚያጠልቀውን የሌባ ቁጥር ከፍ ማድረግ ፡፡

. ሃብታም ባለስልጣናት ለፖለቲካው ልዕልና ሲባል ዘብጥያ የማይወርዱ ከሆነ እንኳ ቢያንስ በአንድ ነገር መደራደር ፡፡ ሰርቀው ካጠራቀሙት በርካታ ገንዘብ በርካታ እጁን እንዲያዋጡ ማድረግ ፡፡ ይህ ጥያቄ ጋሼ ትልቁና እትዬ ትልቋንም ይመለከታል ፡፡ እነሱም ከኛ እኩል የወር ደመወዛችንን ለገስን ሲሉ ‹ Shame › አይዛቸውም እንዴ ?  Really , It is not a joke !

No Dam , No Joke !
No Dam , No Justice !
No Dam , No Victory !
One  Nile  , More Togetherness !



Monday, May 27, 2013

‹‹ ጉድ በል ቢሊየን ዶላር !! ››




አቶ መለስ ዜናዊ በፔሮል የሚከፈላቸው ብቸኛ የአለማችን መሪ መሆናቸውና ክፍያቸውም ከ 4 እስከ 6 ሺህ እንደማይበልጥ በባለቤታው በወ/ሮ አዜብ መስፍን ተነግሮን ነበር ፡፡

በዚሁ መሰረት የወ/ሮ አዜብ ጡረታ ቢያንስ በግማሽ ካነሰ በቀጣዩ ህይወታቸው ላይ እክል እንዳያጋጥም እየሰጋን ነበር ፡፡ ለነገሩ መንግስት ያደረጉትን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ግምት ውስጥ በማስገባት ሙሉ ደመወዛቸው ሳይሸራረፍ እንደሚሰጣቸው የብዙዎቻችን እምነት ነው ፡፡ ቀጣዩን ኑሮ ለመደጎም ከታሰበ ብዙ አማራጮችን መጠቀምም ይቻላል ፡፡ ለምሳሌ ያህል በተለያዩ ቦታዎች የቦርድ ሰብሳቢ ማድረግ ፣ ከቅርብ ሰዎችና ከልማታዊ ባለሀብቶች ሚኒ ቴሌ ቶን ማሰባሰብ ወዘተ ይቻላል ፡፡

በዚህ ስጋት ውስጥ እያለን The Richest የተባለ ዌብ ሳይት / www.the richest. org / የዓለማችን ሀብታም ጠ/ሚኒስትሮች በሚል ለእኛ አስገራሚ ለቤተሰቦቸቸው ደግሞ አስደሳች ዜና ለቀቀ ፡፡ አቶ መለስ ዜናዊን ከሀብታሞቹ ጎራ አሰልፏቸው የተጣራ 3 ቢሊየን ዶላር በዉጭ ሀገር እንዳላቸው ነገረን ፡፡

‹ ጉድ በል ጎንደር! ›  አለ የጎንደር ሰው የአማርኛ መምህር ከደቡብ ክልል መጥቶልሃል ሲባል ፡፡ እኛ ስንት እየተጨነቅን …  እረ ይህን ሁሉ ሃብት ከወዴት አመጡት ? አቶ መለስ ቀደም ሲል ደጋግመው ስለ ቁጠባ ባህል ጠቃሚነት ብዙ ይነግሩን የነበረው ከራሳው ተሞክሮ ተነስተው ነበር ማለት ነው ? ይህ ወሬ እውነት ከሆነ ‹‹ ጉድ በል የሀገሬ ፓርላማ  የድሮውን የሀገሪቷን ዓመታዊ በጀት አንድ ሰው ላይ ስታገኝ ! ›› መባሉ ነው ።

እኔማ ቢቸግረኝ … የገንዘባውን አመጣጥ ለማወቅ የማያልቅና የማይደረስበት የሂሳብ ስሌት ውስጥ ገባሁ ። እስኪ ሳይቆራረጥ 6 ሺ ብራቸውን በፔሮል ይወሰዱ እንበል ፡፡ ለ 21 ዓመታት በዚሁ ብር አገለገሉ እንበል ፡፡ በ21 ዓመታት ውስጥ 252 ወሮች አሉ፡፡ ለ ጠ/ሚ/ር ጻጉሜም ሊከፈለው ይችል ይሆን በሚል እሳቤ 21 ዓመቱን በ13 ወራት አባዛሁት - 273 ወራቶች መጡልኝ ፡፡ እነዚህን ወራቶች በ 6 ሺህ ደመወዝ አባዛዋቸው ፡፡ ቁልጭ ያለ 1 ሚሊየን 638 ሺህ የኢትዮጽያ ብር ሰጡኝ ፡፡ መቼም የሀገር መሪ ከፍተኛ ኃይልም ክብርም አለውና ለቤት ኪራይ ፣ ለምግብ ፣ ለትራንስፖርት፣ ለሻይ ቡና ፣ ለውስኪ ፣ ለልጆች የትምህርት ወጪ ፣ ለእሱና ለቤተሰቦቹ አልባሳት ፣ ደስ ላለው ቁሳቁስ ወዘተ እንደማይከፍል ገመትኩ ፡፡ ስለዚህ 6 ሺውን ብር ሳይሸራርፉ እንዳለ መቆጠብ ችለዋል  ፡፡ ብሩ ግን ሁለት ሚሊየን እንኳን መሙላት አልቻለም ፡፡

ታዲያ ከየት አመጡት ? ሌላ የገቢ ምንጭ ማፈላለግ ያዝኩ ፡፡ እ… አበል ተገኘ ፡፡ አበል ለአንዳንድ ኃላፊዎች ወር ማዳረሻ ሳይሆን ራሱን የቻለ ደመወዝ መሆኑ ትዝ አለኝ ፡፡ ስለዚህ አቶ መለስ ለሀገራዊ ጉዳይ በዓመት 12 / አይበዛም ? / ግዜ ወደ ዉጭ ቢመላለሱ በ21 ዓመታት ውስጥ 252 ግዜ ወጥተዋል ማለት ነው ፡፡ ለአንድ ግዜ ጉዞ በሀብታም ሀገር እይታ 3 ሺህ ዶላር ቢከፈላቸው ለ252 ግዜ 756 ሺህ ዶላር አግኝተዋል ፡፡ ይህን ዶላር ለመዘርዘር በአማካኝ በ 17 ብር ሳባዛው / ጥቁር ገበያን መቼም አይሞክሩትም በሚል ነው / 12 ሚሊየን 852 ሺህ ብር መቆጠብ ችለዋል ማለት ነው ፡፡ አሁን የብራቸው መጠን 14 ሚሊየን 490 ሺህ ደረሰ ፡፡ ቢሆንም ገና ብዙ ይቀራል ። እስካሁን እየቆጠቡ እንጂ ብር እያወጡ አለመሆኑንም ልብ በሉ ፡፡

ሌላ የገቢ ምንጭ ትዝ አለኝ ፡፡ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑ ባለስልጣናት ከደመወዛቸው በላይ ከፍተኛ ጥቅማጥቅም ያገኛሉ ይባላል ፡፡ አቶ መለስ ምንም እንኳ በስራ የተጨናነቁ መሪ ቢሆኑም ከእንቅልፋቸው ሰዓት ቀንሰው  40 የሚደርሱ  ቁልፍ መ/ቤቶችንና ድርጅቶችን በቦርድ ሰብሳቢነት ያገለግላሉ እንበል ፡፡ ከአንዱ መ/ቤት በዓመት 20 ሺህ ብር ብር ያገኛሉ ቢባል ከአርባው 8 መቶ ሺህ ብር አላቸው ማለት ነው ፡፡ ይህን ብር ላገለገሉበት 21 ዓመታት ስናባዛው 16 ሚሊየን 8 መቶ ሺህ ብር ይሆናል ፡፡ አሁን ደግሞ አጠቃላይ ገንዘባቸው 31 ሚሊየን 290 ሺህ ብር ደርሷል ፡፡

በተለያዩ ግዜያት ከሚያገኙት የእውቅና ክብር ጋር የ 100 ሚሊየን ብር ስጦታም አግኝተዋል ቢባል / የተወሰነ ብር ለሆነ ደርጅት የለገሱ ቢሆንም / የብሩ መጠን 131 ሚሊየን 290 ሺህ ብር ነው ፡፡ ሌላ ገንዘብ የሚያገኙበት ምን ምንጭ አለ ?

አንዳንድ መ/ቤቶች በተለይ አትራፊ ድርጅቶች ዓመቱ መጨረሻ ላይ ለሰራተኛ ቦነስ ይሰጣሉ ፡፡ ታዲያ አትራፊ ያልሆነው ቤ/መንግስት ለሚያፈሰው የቤቱ ጣሪያ እንኴን ማደሻ ጥሪት አልነበረውም ፡፡ ‹ ቦነስ በቤተመንግስት › እያልን ብናወራ አሪፍ የሲኒማ ርዕስ ካልሆነ በስተቀር እንዴት ይታመናል ?  ለነገሩ ስፖንሰር በመጠየቅም የአትራፊነት የበጀት ርዕስ መትከል ይቻላል ፡፡ በቃ ! እንዲህ ሊሆን ይችላል ብለን ኦዲታችንን እንቀጥል ፡፡ ቦነስ ያው ደመወዝን ስለሚያክል 273 ወራቶችን በ6 ሺህ ብር ማባዛት ይጠበቃል ፡፡ 1 ሚሊየን 638 ሺህ ብር መጣ ፡፡ አጠቃላይ ሃብታቸው ስንት ሆነ መሰላችሁ 132 ሚሊየን 928 ሺህ ብር ፡፡

ታዲያ The Richest የተባለው ዌብ ሳይት ምንድነው የሚነግረን ? የሳቸውን ገንዘብ በጣም አብዝተነው እንኴ በዶላር ቢታሰብ ከ 8 ሚሊየን አይዘልም ፡፡ አላቸው የሚለው ግን 3 በሊየን ዶላር ነው ፡፡ ወይ አቶ መለስ ጨዋ ናቸው እያልን እንደ አፍሪካ መሪዎ ድርሻውን ወስደዋል ማለት ነው ? አያደርጉትም  ይህን ሂሳብ ለማምጣት ርግጠኛ ነኝ 24 ሰዓት ብደምርና ባካፍል አላገኘውም ፡፡ ታዲያ ማነው የዋሸን ? ዌብ ሳይቱ ወይስ ወ/ሮ አዜብ ፡፡ በርግጥ በሁለቱም በኩል አነጋጋሪ ክፍተቶች አሉ ፡፡ ዌብ ሳይቱ መረጃውን ያገኘበት ምንጭ አልጠቀሰም  ፡፡ ወ/ሮ አዜብም ምንም እንደሌላቸው ሲነግሩን ግድ የለም እንመናው በማለት እንጂ ያጡ የነጡ ለመሆናቸው ምን መረጃ ያቀርባሉ ? ታዲያ የወሬው አመጣጥ የአቶ መለስን ስም ለማጥፋት ነው ወይስ እሳውንም  እንደሌሎ ባለስልጣናት በሙስና ተጠያቂ ለማድረግ ? ያም ሆነ ይህ ወደፊት የሚታይ ይሆናል ። 

ደግሞ እኮ አሳምሮ ነው ያስቀመጠው ፤

የተጣራ ገቢ - 3 ቢሊየን ዶላር
የሀብት ምንጭ - ፖለቲካ
የመለስ ዜናዊ ዕድሜ - 58
የመለስ ዜናዊ የትውልድ ቦታ - አድዋ
የጋብቻ ሁኔታ - ያገባ / አዜብ መስፍን/ ን ይላል ፡፡

‹‹ ጉድ በል ቢሊየን ዶላር !! ›› አለ የሀገሬ ሰው ፡፡

Wednesday, May 8, 2013

የተሰቀለው ሪፖርትና የተደፈጠጠው እውነት

[ ICFJ ከጤና ጥበቃ ሚ/ር ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የክትባት ውድድር ላይ ያሸነፈ ጽሁፍ ]



አምቦ

ከአዲስ አበባ በ 95 ኪሜ በቅርብ ርቀት የምትገኝ የደስ ደስ ያላት ከተማ ናት ፡፡ አንድ ሰው ከተማዋ በጣም ጎልታ የምትታወቅበትን ጉዳዮች ቢያስስ ቢያንስ ሁለት ነገሮችን ጎልተው ያገኛቸዋል ፡፡

አንደኛው በርካታ ኢትዮጽያዊያን ስብሰባ ውለው ምሳ ከተጋበዙ በኃላ ለመጠጥነት በአንድ ድምጽ የሚመርጡት አምቦ ውሃ መሆኑን ነው ፡፡ በተለምዶ ምግብ ያንሸራሽራል ፣ ያስገሳል ፣ የውሃ ጥምን ይቆርጣል የሚባለው ይህ አንጋፋ መጠጥ የሚመረተው በዚህ ከተማ ነውና ፡፡ ሁለተኛው ሀገሪቱን ለ 22 ዓመታት እያስተዳደራት ከሚገኘው የኢህአዴግ መንግስት ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው ፡፡ የዛሬው ኢህአዴግ የትላንትናው ወያኔ በመጨረሻው ሰዓት ደርግን በየከተማው እየጣለ የመጣው ፈጣን ማርሽ በመጠቀም ነበር ፡፡ እዚች ትንሽ ከተማ ሲደርስ ግን ሩጫውን አቁሞ በአንደኛ ማርሽ ‹ ባላንስ › ለመስራት ተገደደ ፡፡ ህዝቡ ሀገር ሻጭና ከፋፋይ ፖለቲካን የሚያራምድ አማጺ ወደ መሃል ሀገር አናስገባም በማለት በጦርነት ገትሮት ያዘው ፡፡ ሀገሬው በውጊያው ብዙ እንደጣለ ሁሉ ከእሱም ወገኞች ብዙውን አጣ ፡፡ እናም በአምቦ ከተማ ይህን ግብግብ የሚያሳይ ህዝባዊ ኀውልት መታየት ባይችልም በህዝቡ ልቦና ግን በማይታይ ማህተም የተቀረጸ ልዩ ታሪክ አለ ፡፡

ወ/ሮ መገርቱ በዚች የውሃና ደም ታሪክ ባላት ከተማ መኖር ከጀመሩ 38 ዓመታትን አስቆጥረዋል ፡፡ የሁለት ሴትና አንድ ወንድ ልጅ እናት ናቸው ፡፡ የሶስት ዓመት ዕድሜ ያለው የመጨረሻ ልጃቸው በኩፍኝ በሽታ መያዙን ቢያወቁም ወደ ጤና ጣቢያ ማምራት አልፈለጉም ፡፡ ህጻኑ ላይ የሚታየው የሳል ፣ ንፍጥ ፣ ትኩሳትና ሽፍታ ህመሞች ያን ያህል አላስጨነቃቸውም ፡፡ የከተማው ህዝብ ያለው የጀግንነት ስሜት ተጋብቶባቸው አይደለም - የቆየ የህክምና ልምዳቸው እንጂ ፡፡ ኩፍኝ ለሳቸውም ሆነ ለቀድሞ ቤተሰቦቻቸው ተራና የማይቀር የልጅ በሽታ በመሆኑ እንዴት ማጥፋት እንደሚቻልም በአግባቡ ያውቃሉ ፡፡
እናም የእናት - አባታቸውን ከራማ እያስታወሱ ትርክክ ባለው የከሰል ፍም ላይ ደግመው ደጋግመው የተለያዩ ጢሳ ጢሶችን ያጉራሉ ፡፡ ትንሷ የጭቃ ቤት ከአቅሟ በላይ የሆነ የጢስ ምርት ማምረት ጀመረች ፡፡ ሁለቱ ኩፍኝን በግዜያቸው ያሸነፉ ሴት ልጆቻቸው በስራ ተጠምደዋል ፡፡ አንዷ ቡና ትቆላለች ፣ ሌላዋ ገና ያልበረደው ትኩስ ቂጣ ላይ በዘይት የተለወሰ በርበሬና ኑግ ትለቀልቃለች ፡፡ ጎረቤቶችና የቅርብ ዘመዶችም የውጭ በር ላይ ተኮልኩለው ፈጣሪ ለህጻኑ ፈጣን ምህረት እንዲልክለት ይለማምናሉ ፡፡

የቡናው ስነ ስርዓት ከተፈጸመ በኃላ ቆሎ ፣ ቂጣ ፣ ኑግ ፣ ለምለም ሳር የያዙ ሴቶች ምህረት እየለመኑ አቅራቢያቸው ወደሚገኝ ወንዝ አመሩ ፡፡ ወንዙን ከተሻገሩም በኃላ የያዙትን ወደ ወንዙ ዳር ወርውረው ተመለሱ ፡፡ በቃ ! በእምነቱ አስተሳሰብ መሰረት በኩፍኝ የተያዘው ልጅ በቅርብ ቀን ይፈወሳል ፡፡ ምክንያቱም የህጻኑ ገላ በሳሩም በቂጣውም በአሪቲውም ተሻሽቶ የተወረወረ በመሆኑ ጦስ ጥንቡሳሱም እዛው ተጣብቆ ይቀራል ፡፡

ፀለምት

የአማራ ክልል አንድ አካል የሆነች ከአዲስ አበባ በ 800 ኪ.ሜ ርቀት አካባቢ ላይ የምትገኝ ቆዛሚ ምስኪን ከተማ ናት ፡፡ አቶ ጥጋቡ በዚችው ከተማ ተወልደው ያደጉ የመንግስት ሰራተኛ ናቸው ፡፡ ዛሬ አድራሻቸው ጎንደር ቢሆንም ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅ በየግዜው ወደ ከተማዋ ይመላለሳሉ ፡፡

የአቶ ጥጋቡ ሀገር ሰው ከወ/ሮ መገርቱ ሀገር ሰው የሚመሳሰልበትም የሚለያይበትም መንገዶች አሉት ፡፡ ፀለምቶች ኩፍኝን ‹ ፎረፎር › እያሉ ሲጠሯት ብዙዎቹ ሀኪም ቤት መሄድ ሳያስፈልግ ልትድን የምትችል ሞኛ ሞኝ በሽታ መሆኗን ይስማማሉ ፡፡ ከወ/ሮ መገርቱ ሀገር ህዝብ ግን የሚለዩት በሰፈሩ አንድ ህጻን በፎረፎር ታመመ ከተባለ አስገራሚ የመከላከል ስራ መስራት መቻላቸው ነው ፡፡ ከነ ስያሜው መድሃኒቱን ‹‹ ክትባት ›› ነው የሚሉት ፡፡

በፍጥነት ወደታመሙት ልጆች በመሄድ ከሽፍታው ላይ መግል እያፈረጡ ይወስዳሉ ፡፡ ከዚያም ያልታመሙ ልጆች የግራ እጅ በምላጭ ይቀደድና መግሉ ከዝንብ ጋር ተጨፍልቆ በጨርቅ እንዲታሰር ይደረጋል ፡፡ አቶ ጥጋቡ  50ኛ የዕድሜ ሻማቸውን ቢለኩሱም ዛሬም ይህ የክትባት ስርዓት በአካባቢው እንደሚከናወን ይገልጻሉ ፡፡ ግራ እጃቸውን አንስተው አሳዩኝ ፡፡ ለባህላዊው የኩፍኝ ክትባት የተቀደዱት ጠባሳ አሁንም የታሪክ አሻራውን ይዞ ግዜ ሳያደበዝዘው  ይታያል ፡፡

‹‹ የአካባቢውን ተወላጆች እጅ እያነሳህ ብታይ ይህን ምልክት ታያለህ ›› በማለት በፈገግታ መለሱልኝ ፡፡
‹‹ የሆነውስ ይሁን ?! የዝንቧ ምስጢር አልገባኝምና ጠቀሜታው ምንድነው ? ›› ስል ጠየቅኳቸው
‹‹ ልጅ እያለሁ አይገባኝም ነበር ፡፡ አሁን የሚመስለኝ ግን ዝንብ በሽተኛዎች ደጃፍ መድረሷ ስለማይቀር የበሽታው ፈሳሽ አለባት በሚል ነው ›› አሉና ቅዝዝ ብለው ወደ ኃላ በሃሳብ ተመነጠቁ ፡፡ ከአፍታ በኃላም የሚያወሩልኝ እንባ በሚተናነቅ የሳቅ ድምጽ ነበር ፡፡ ‹‹ በጣም ይገርመኛል ፤ መድሃኒቱ እጅ ላይ ሊታሰር ሲል ዝንብ አድኑ ! የሚባሉት ህጻናት ናቸው ፡፡ ግማሹ የሚበር ዝንብ በትንሽ እጁ ለመጨበጥ ሲታገል ፣ ሌላው ዝንብ ያዝኩ ብሎ ዕቃ ሲሰብር ፣ ግማሹ ፊቱ ላይ ዝንብ ለመደፍጠጥ ፊቱን ሲጠፈጥፍ ይውላል … ››

ሳይንስ እንደሚለው ከሆነ የኩፍኝ ክትባት የሚሰራው ከተዳከመ የ ‹‹ ሚዝልስ ቫይረስ ›› ነው ፡፡ የአቶ ጥጋቡ ሀገር ህዝብም ባህላዊውን መንገድ ይከተል እንጂ መድሃኒቱ ያለው በሽታው ላይ መሆኑን አውቋል ፡፡ ሌላው ባህላዊው ስርዓት በኩፍኝ የተያዙ ልጆችን ለመጠየቅ የሚጣለው ገደብ ነው ፡፡ በነአቶ ጥጋቡ ሀገር መሰረት የግብረ ስጋ ግንኙነት ያደረጉ ሰዎች ታማሚዎችን ወደ ቤት ሄደው መጠየቅ አይችሉም ፡፡ ምክንያቱም ይህን ሁሉ ልፋት ያረክሳሉና ፡፡ በነወ/ሮ መገርቱ አካባቢ ኩፍኝ አንዴ ወንዝ በመሻገሩ ተመልሶ ስለማይመጣ ማንኘውም ሰው ቤት ገብቶ ቢጠይቅ ችግር የለውም ፡፡ ኩፍኝን ‹‹ አለሜ ›› እያሉ በሚጠሯት ‹‹ አለሜ በዓለም ያውጣሽ ! ›› እያሉ በሚለማምኗት የአዲስ ዘመን አካባቢ ነዋሪዎች ደግሞ በሽተኞች በር ላይ የሆነ ቅጠላ ቅጠል ነገር ይሰቀላል ፡፡ ይህን ምልክት የሚያይ እንግዳም ወደ ውስጥ ከመግባት ይታቀብና ደጅ ሆኖ ምህረት ይጠይቃል ፤ ከፈለገ ደግሞ ስለ ቀሪው ቤተሰብ ፣ ስለ እርሻና የዝናብ መጥፋት፣ ስለ እነ ላሜቦራ ጤንነት ሁሉ ድምጹን ከፍ አድርጎ መወያያት ይችላል ፡፡

አዲስ አበባ
ቆሼ ፡፡

ይህን የከተማውን ቆሻሻ በሙሉ ሰብስቦ ለመያዝ የተስማማውን ሰፈር ‹‹ ገብረ ክርስቶስ ›› ማለት የሚቀናቸውም አሉ ፡፡ በአካባቢው የስጋ ደዌ ህክምና መስጫ ሆስፒታል ከመኖሩ ጋር ተደራርቦ በርካታ በስጋ ደዌ በሽታ የተጠቁ ሰዎች ይኖሩበታል ፡፡ ስያሜው የመነጨው ግን በአካባቢው የአቡነ አረጋዊ / ገብረ ክርስቶስ / ቤተክርስትያን ከመገኘቱ አንጻር ነው ፡፡

በዚህ አካባቢ የሚኖሩ በሽተኞች ከሁሉም የሀገሪቱ ጥግ ለህክምና ሲሉ የሚፈልሱ ናቸው ፡፡ ብዙዎቹ ታክመው ወደ ትውልድ ሀገራቸው ከመመለስ ይልቅ እዚሁ መቅረትን የሚመርጡ ናቸው ፡፡ የዚህም አካባቢ ሰዎች ልክ እንደ አምቦ ሰዎች በሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ይታወቃሉ ፡፡ አንደኛው ከበሽታቸው ከተፈወሱ የማንንም ድጋፍ ሳይጠብቁ ራሳቸውን ለመቻል የሚያደርጉት ያላሰለሰ ጥረት ነው ፡፡ እንዳቅማቸው ቤት ተከራይተው ሽንኩርትና ጎመን ለመቸርቸር ወይም ጠላና አረቄ ለመሸጥ የማይቦዝኑ መሆናቸው ልዩ ያደርጋቸዋል ፡፡ በሽታቸው ጎድቷቸው አካላቸው መድከም ከጀመረ ደግሞ የገበያ ጥናት በማጥናት በልመና ስራ ይሰማራሉ ፡፡ እነሱን ጠጋ ብላችሁ ብትጠይቁ ልመናን አስጸያፊ ሳይሆን ራስን ለመቻል የሚደረግ መፍጨርጨር በማለት ነው ብይን የሚሰጡት ፡፡ ሁለተኛው ልዩ ባህሪያቸው በህክምናና ጤና ዙሪያ ለሚነገሩና ለሚሰሩ ጉዳዮች የተለየ ትኩረት ሰጪ የመሆናቸው ጉዳይ ነው ፡፡ ምናልባትም ስጋ ደዌ የፈጠረባቸው ተጽዕኖ ወይም በሌላ መልኩ ያስገኝላቸው የአዳማጭነት ጸጋ ሊሆን ይችላል ፡፡

በቅርቡ ወደ አረብ ሀገር የሚጓዘውን ባልደረባዬ ቤተሰብ ‹‹ እንዴት ይዟችኃል ? ›› ለማለት በአካባቢው ተገኝቼ ነበር ፡፡ በርካታ ሴቶች ተሰብስበው  ዳቦ ቆሎ ፣ ኩኪስ ፣ ቋንጣ ፣ የመሳሰለውን ቀለብ በመስራት ስራ ላይ ተጠምደዋል ፡፡ የኢትዮጽያ ቴሌቪዥን የሰባት ሰዓት ዜና እወጃ ላይ ስለ ሶስተኛው የአፍሪካ ክትባት ሳምንት በስፋት ሲያወራ የሴቶቹ ጫጫታ ቀነሰ ፡፡ የዘንደሮው ክትባት ‹‹ ህይወት እናድን ፣ አካል ጉዳተኝነትን እንከላከል ፣ እንከተብ ›› በሚል ጭብጥ ላይ ይተኮረ ነበር ፡፡ ከዜናው በኃላ የሴቶቹ አብይ መወያያ ጉዳይ ክትባት ሆነ ፡፡

አንዳንዶች በክትባት በርካታ ህጻናት ከሞት እየተረፉ መሆኑን በመጥቀስ መንግስትን ማወደስ ጀመሩ ፡፡ አንድ እናት ‹‹ ልጄ የደነቆረው በመከተቡ ነው ! ›› በማለታቸው ቤቱ በድጋፍና ተቃውሞ ተጋጋለ ፡፡ ‹‹ ከክትባት በኃላ የአእምሮ በሽተኛ የሆነ ልጅ አውቃለሁ ›› የምትል ወጣት ሴት ብቅ አለች ፡፡ ሌላ ወጣት ‹‹ እንዴት ፊደል ቆጥረሽ እንዳልተማረ ሰው በግምት አስተያየት ትሰጫለሽ ! ›› በማለት በግልምጫም በማሽሟጠጥም አፈረጠቻት ፡፡ ሴቶቹ ቀስ በቀስ መደማመጥ ወደማይቻልበት ደረጃ ተሸጋገሩ ፡፡ ይባስ ብሎ ‹‹ ምን ይሄ ይገርማችኃል ! የኛ ሀገር ክትባት በሉት መርፌ ሰው እየገደለ እኮ ነው ›› የሚሉ ሴት ከወደ ጓዳ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ብቅ አሉ ፡፡

አሁን ቤቱ በአንድ እግሩ ቆመ ፡፡

እነዚህ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክንፍ ወደ ከተማ የመጡ ሴቶች አስተያየት የህብረተሰባችንን የንቃተ ህሊና የሚያንጸባርቅ ወይም የሚመረምር ቴርሞ ሜትር ነው ማለት ይቻላል ፡፡ ስለ ክትባት ፣ ኩፍኝም ሆነ ሀኪሞች ብዙ የሰሙ እና ብዙ የተመለከቱ በመሆናቸው ስጋታቸው ከጠርዝ የወጣ ነው ነው ማለት አያስችልም ፡፡ ምክንያቱም በሀገራችን ህጻናትና እናቶች ከመጠን በላይ መድሃኒት ተሰጥቷቸው መሞታቸው አዲስ አይደለም ፡፡ ምክንያቱም በስህተት የማይገባ መርፌ ተወግተው ያለጥፋታቸው የሚያሸልቡ ጥቂቶች አይደሉም ፡፡ ምክንያቱም በኛ ሀገር ቀኝ እግራቸው ታሞ በእንዝላልነት ግራ እግራቸውን ለመጋዝ የሰጡ ምስኪን በሽተኞች መኖራቸውን አሳምረን እናውቃለን ፡፡ ምክንያቱም የሀገራችን ሀኪሞች ድራማን ለማየት በማስቀደም የነፍሰ ጡር እናት ብርቅ እስትንፋስን ከድራማው ፍጻሜ ጋር እንዲደመደም እንደሚያደርጉ እናውቃለን ፡፡ ስራ በዝቶባቸው ብቻ ሳይሆን ትኩረት ባለመስጠት የቀደዱት ሆድ ውስጥ መቀስና ፋሻ የሚረሱ ሀኪሞች መኖራቸውንም እናውቃለን ፡፡

መንግስትና የሚወዳቸው ቁጥሮቹ

መንግስት ከላይ የተገለጸውን አይነት አስተሳሰብ ፣ እምነትና አሰራሮች ትኩረት ሰጥቶ ከመመርመር ይልቅ በዘመቻ የሚገኙ ቁጥሮችን ማጉላት የመረጠ መስሏል ፡፡ የአሁኑ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር የቀድሞው ስመ ጥሩው የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ክትባቱ በተጀመረበት ወቅት ያጎሉትም ይሄንኑ ሃሳብ ነው ፡፡ ‹‹ በኢትዮጽያ የልጆች የጤና ክትባት ሽፋን 95 ከመቶ ደርሷል ›› በማለት ፡፡ ይህ አኀዝ በገለልተኛ ወገን ያልተረጋገጠና ፍጹም የተጋነነ በመሆኑ አሳሳች መስመር እንዳይዝ ያሰጋል ፡፡

በኢትዮጽያ እድሜና ደመወዝ እንጂ ሪፖርቶችን ከፍ አድርጎና አጋኖ ማቅረብ ከቀበሌ እስከ ቤተ መንግስት ድረስ የተለመደ አሰራር ነው ፡፡ ያጋነነው አካል ‹ ውሸታም ! › ተብሎ አይፋጠጥም ፤ ሳይጨምር ሳይቀንስ የቀረበው ግን ‹ እንዴት ይህን ብቻ ሰራህ ? › ተብሎ በግምገማ ዱላ ሊወገር ይችላል ፡፡ በዚህም ምክንያት የትኛውም መንግስታዊ መ/ቤት ብትሄዱ የምታነቡትና የምትሰሙት የሚያስጎመዡ ቁጥሮችን ነው ፡፡ በሀገራችን እየቀረበ ያለው የኩፍኝ ክትባት አኀዝም በተለመደው ምቹ የቻይና አስፋልት ሮጦ የመጣ እንጂ ዘወትር ከሚቆፋፈረውና እግርና ጎማ ከሚለምጠው የአውራጎዳና ባለስልጣን ኮሮኮንቻማ መንገድ ጋር የሚተዋወቅ አይደለም ፡፡

አንድ ነርስ ለ 2 ሺ 500 ሰዎች በሚደርስበት ሀገር ኩፍኝን ለማጥፋት ጥቂት ሽርፍራፊ አሃዝ ነው የቀረን ማለት ለጤና ጣቢያ እጅግ ርቀው የሚገኙ የህብረሰብ ክፍሎችን ፣ ባህላዊ እምነትና የልምድ አዋቂዎችን እንደ ካስማ ይዞ የቆየን ማህበረሰብ ስነ ልቦና ዘልቆ ያለመረዳት ዉጤትን ያንጸባርቃል ፡፡

በርግጥ በጤና መስኩ አበረታች ውጤት አልታየም ለማለት አይደለም ፡፡ የአሁኑ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ከሰተ ብርሃን አድማሱ በቅርቡ ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከሰባት ዓመት በፊት 600 የነበሩት ጤና ጣቢያዎች ዛሬ 3 ሺህ መድረሳቸውን ፣ 34 ሺህ የሚደርሱ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞችም መቀጠራቸውን ነግረውናል ፡፡ ይህ ቁጥር በተደራሽነት ላይ የነበረውን ሰፊ ክፍተት በጥቂትም ቢሆን እንደሚያጠብ ይጠበቃል ፡፡ ይህ ማለት ግን በክትባት እጦትና ባለመከተብ ፍላጎት የሚደርሰውን የህጻናትና እናቶች አስከፊ ሞት እንደሚነገረው የሚታደግ አይደለም ፡፡

ርግጥ ነው የዓለም ጤና ድርጅት የቅርብ መረጃ እንዳረጋገጠው በዓለም አቀፍ ደረጃ በኩፍኝ በሽታ የሚሞተው ህጻናት ቁጥር 71 ከመቶ ቀንሷል ፡፡ ይህ የሆነውም ከ2000 እስከ 2011 ባሉት ሰፊ ግዜያት ነው ፡፡ በሌላ በኩል በዓለም አቀፍ ደረጃ 20 ሚሊየን የሚደርሱ ህጻናት የመጀመሪያ ደረጃ ክትባት እንኳ ያልወሰዱ ናቸው ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሚገኙት በአምስት ሀገሮች ነው ፡፡ በኮንጎ ፣ ህንድ ፣ ናይጄሪያ ፣ ፓኪስታንና ኢትዮጽያ ፡፡ ይህም መንግስት ሰፊ የቤት ስራ እንደሚጠብቀው በአግባቡ ያመላክተዋል ፡፡

መንግስት ሊጠቀምበት የሚገባው ሌላኛው የማንቂያ ደውል ወይም የስጋት ቴርሞሜትር በሀገራችን የኩፍኝ ወረርሽኝ በየአመቱ እንደተለመደው ድርቃችን ተከሳች ጉዳይ የመሆኑን ምስጢር ነው ፡፡ የቅርብ ግዜያትን መረጃዎች ብቻ ብንወስድ እኤአ በ2009 – 1519 ፣ በ2010 – 2401 እንዲሁም በ2011 – 3255 የኩፍኝ ምልክቶች በተለያዩ ክልሎች ተመዝግበዋል ፡፡ በ2011 ከተጠቁ ሰዎች መካከል ደግሞ 114 ህጻናት መሞታቸው በይፋ ታውቋል ፡፡

ያልታረቁ የህክምና መንገዶች

በአንድ በኩል መንግስት ኩፍኝ በህክምና  የሚድን ቀላል በሽታ ነው ይላል ፡፡ በሌላ በኩል ህብረተሰቡ ኩፍኝ በቀላሉ የምትድን በሽታ በመሆኑ ከቤቴ አላሳልፋትም ባይ ነው ፡፡ መንግስት ክትባት ተጠቃሚው መቶ ከመቶ ሊሆን አንድ እፍኝ ቀርቶናል ይላል ፡፡ ክትባት የማያውቀውና ለባህላዊው መንገድ እጁን የሰጠው ደግሞ ብዙ እፍኝ ሆኖ ይታያል ፡፡ ይህም የጤና ጣቢያ ችግር ከሌለበት አዲስ አበባ እስከ አንድ ሺህ ኪ.ሜ ርቀት የሚገኙትን አርሶአደርና አርብቶአደር ነዋሪዎችን ያካትታል ፡፡ መንግስት የክትባት ሽፋኑ ከ 90 ከመቶ በላይ ደረሰ የሚል ከሆነ የህብረተሰቡ የመረዳት አቅምና ግንዛቤ አድጓል ማለቱ ነው ፡፡ ይሁን እንጂ የኩፍኝ ክትባት ኦቲዝም ያስከትላል ፣ የኩፍኝ ክትባት መውለድ ላይ ችግር ይፈጥራል ፣ ለአካል ጉዳተኝነትና የአእምሮ ችግር ይዳርጋል የሚል መረጃ የታጠቀው የሀገራችን ህዝብ ቁጥር ደግሞ የትየለሌ ነው ፡፡

እናም በሚጋጭ እውነታ ውስጥ እየተደነቃቀፉ መጓዝ ዋጋ ያስከፍላል ፡፡ በመሆኑም እየኖርን ያለበትንና መኖር የምንፈልግበትን ስርዓት በአግባቡ መገንዘብ ብሎም አብሮ እየተጓዙ ማጣጣም በመጨረሻም ሳይንሳዊውን የብረት ቆብ ኬሻና ገመድ የለመደው ጭንቅላት ላይ የማኖር ብሂልን መላበስ ግድ ይላል ፡፡

መሬት የሚቆነጥጥ ስልት

የኢትዮጽያ የክትባት ፕሮግራም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተያዙትን የፖሊዮ በሽታ የማጥፋት ፣ የመንጋጋ ቆልፍ የመቆጣጠርና የመቀነስ ፣ የኩፍኝ በሽታን የማስወገድ ስራዎችን ይዞ ይንቀሳቀሳል ፡፡ በከተሞች አካባቢ የተሻለ የክትባት ሽፋን ቢኖርም አብዛኛው ህዝብ የሚኖርበት ገጠሩ ክፍል በተለያዩ ምክንያቶች ተደራሽ አለመሆኑን ከመቀበል መነሳት ይኖርበታል - ስልቱ ፡፡
ኩፍኝ በረቂቅ ቫይረስ አማካኝነት የሚመጣና በትንፋሽ የሚተላለፍ በሽታ አንጂ የፈጣሪ ቁጣ ፣ የተፈጥሮ ሂደት ውጤትና የሌሎች እምነትና ባህል መገለጫ አለመሆኑን በአንድ ሰሞን ዘመቻ ሳይሆን በዝርዝር መንገድ ለማስተማር ኃላፊነትን መቀበል ግድ ይላል ፡፡ ኩፍኝ ድህነት ፣ ተፋፍጎ የመኖር ችግርና ያልተከተቡ ህጻናት ባሉበት ቦታ የሚስፋፋና በከፍተኛ ደረጃ የሚገድል በሽታ መሆኑን የትምህርቱ አቢይ ምዕራፍ ማድረግ ያስፈልጋል ፡፡ ምክንያቱም የምንኖረው በወራዳ የድህነት ቀለበት ውስጥ ነው ፤ የአኗኗር ስልታችንም ከተነጠላዊ ይልቅ እንደ ዳመራ የተጃመለና የተደጋገፈ ነው ፡፡ ይህም አብሮ ለመስራትና ጠላትን ለማባረር አስፈላጊ ቢሆንም ቫይረስና ባክቴሪያ እንደ ጣሊያን መላልሰው ሲወሩን ግን በቀላሉ ለመጨፍጨፍ ያመቻልና ፡፡

ኩፍኝ ርጉዝ በሆነች ሴት ላይ ከተከሰተ ልታስወርድ እንደምትችል ፣ ህጻኑ ሊደነቁር ፣ ሊታወር እንዲሁም የአእምሮ ጉዳተኛ ሁሉ ሊሆን ይችላል ፡፡ አብዛኛው ህብረተሰባችን የሚያስበው ግን በሽታው የህጻናት ብቻ መሆኑን ነው ፡፡ ለዚህም ነው የቆሼ ሰፈር ሴቶች የኩፍኝ ክትባትን መጠቀም ህጻናትን ለሞትና ለአካል ጉዳተኝነት ይዳርጋል በማለት በግልባጩ የሚያስቡት ፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች የሚያገለግሉት የአካባቢያቸውን ህብረተሰብ በመሆኑ ግንዛቤ ለመፍጠርና ልማዳዊ ልምዶችን ለመሰባበር ምርጥ ስትራቴጂ መሆኑን በልበ ሙሉነት ይናገራሉ ፡፡ ይህን አስተሳሰብ የመጨረሻ አድርጎ መቀበል ግን የክትባት ሽፉኑ 95 ከመቶ ደርሷል ብሎ በድፍረት የመናገር ያህል የሚያስቆጥር ነው ፡፡ 
ምክንያቱም በየትኛውም የገጠሪቱ ክፍል የሚገኙ ዜጎች ከአንድ ጤና ባለሙያ ይልቅ የጎሳ መሪዎችን ፣ ታዋቂ ሽማግሌዎችን ፣ የእምነት አባቶችንና አዋቂዎችን ነው የሚያከብሩት … የሚፈሩትና ትዕዛዛቸውንም የሚፈጽሙት ፡፡ በመሆኑም ይህን ጠቃሚ ስልትም በአግባቡ ፈትሾ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ፡;

ከ 80 በላይ ብሄር ብሄረሰቦች በሚገኙባት ሀገር ለኩፍኝ ያለው አመለካከትም ሆነ ባህላዊና እምነታዊ የመከላከል ስትራቴጂው 80 ዓይነት የበዛ ነው ፡፡ አንዱ በጢሳጢስ ፣ ሌላው በዝማሬ ፣ አንዱ ወንዝ በማሻገር ፣ ሌላው ስራ ስር በመቀመም ሊጠቀም ይችላል ፡፡ ምክንያቱም የነወ/ሮ መገርቱን ባህላዊ እምነት የሚከተሉ ሰዎች ዛሬም በየትኛውም ጥግ ይገኛሉ ፡፡ የእነ አቶ ጥጋቡ መግልና ዝንብ የቀላቀለ ባህላዊ የህክምና መስጫ ተቋማት የቀራቸው ከመንግስት ህጋዊ የንግድ ፍቃድ ማውጣት እንጂ በዘልማድ የሚሰሩበትና የሚያምኑት የገጠር ወገኖቻችን ዛሬም በርካታ ናቸው ፡፡ ክትባት በራሱ ለመሃንነትና ለሌሎች ተዛማጅ ችግሮች ይዳረጋል የሚል የእምነት ጋቢ የደረበው የህብረተሰብ ክፍልም ቁጥሩ ጥቂት አይደለም ፡፡

 መንግስት የያዘው አኀዝና ህብረተሰቡ ጋ ያለው ተጨባጭ እውነት የተጣረሰ በመሆኑ የማስተካከያ ስራ ሊሰራ ይገባል ፡፡ የገነገነውን ባህላዊ ልምድንና እያቆጠቆጠ የሚገኘውን ዘመናዊ አሰራር ማጣጣምና ማስታረቅ ግድ ይላል ፡፡ በአጠቃላይ ኩፍኝንና ወረርሽኙን ለመከላከል ፤

እውነትን - ማካፈል
ግነትን - መቀነስ
ክትባትን - መደመር
ግንዛቤን - ማብዛት
የተሰኘ ቀላል ነገር ግን ጠቃሚ ሂሳባዊ ቀመርን መከተል ያስፈልጋል ፡፡
            

Monday, May 6, 2013

‎የአንድ ጎልማሳ ገንዳ ወግ‎




‹‹  እረ ለአንተው ቱ ! ባለጌ ! መተፋት ያለበት ለአንተው ዓይነት ነበር ፡፡ . . .  እረ እባክህ አፍንጫህንም መያዝ ትችላለህ እንዴ ? አሁን እንዲህ ለብሰህ ላየህ አዋቂና ጨዋ ትመስላለህ ፤ ይሄኔ ስለ ቆሻሻ ጎጂነት የምታስተምር የሳይንስ መምህር ትሆን ይሆናል . . . ነጭ ጋዋን ለብሰህ ምድረ በሽተኛን የምታመናጭቅ ድሬሰር ወይም ነርስ የማትሆንበትም ምክንያት አይኖርም ፡፡ የዚችን ከተማ ቆሻሻ ነቃቅለን እናጠፋለን ከሚሉ ዲስኩረኛ ፖለቲከኞች ተርታም የምትሰለፍ ቢሆንስ ምን ይገርማል ፡፡ እረ ማዘጋጃ ቤት የጽዳት ፣ ውበትና መናፈሻ ስራ ሂደት መሪም ብትሆን ማን ያውቃል ?

‹‹ እኔ ግን በዚች ሰፈር ካወቅኩህ ስንት ዘመን ተቆጠረ ? ቀን ቀን ‹ ይሄ ገንዳ ሸተተ ! › እያልክ ምራቅህን ትተፋብኛለህ ፤ ገልምጠኀኝ ትሄዳለህ ! አንዳንዴ ደግሞ እንደ ማስቲሽ ንፍጥህ ተጣብቆ አልከፈት በሚለው የተዥጎረጎረ መሀረብህ አፍና አፍንጫህን ለመደበቅ ትጣጣራለህ ፡፡ በል ሲልህ ደግሞ ‹ ቅርናታም ገንዳ ! › እያልክ በብልግና መፈክር ትለማመዳለህ ፡፡ ማታ ማታ ግን ከእኔ በላይ በመጠጥ ቀርንተህ በሁለት እጆችህ ጥርቅም አድርገህ ይዘኀኝ ገላዬ ላይ ስትሸና አንዳችም ነገር አይከረፋህም ፡፡ አስመሳይ  - ሰው መሳይ በሸንጎ ! እንዳንተ ዓይነቱን ስንት የሰው ገንዳ ታዝቤያለሁ መሰለህ ?! ይሄኔ የቆለጥህ ማስቀመጫ ጨርቅና ካልሲህን በተናጥልም ሆነ በጥምረት የሚያሸታቸው ቢኖር  ‹ እረ ተመስገን ! › የሚባልልኝ እኔ ነበርኩ ፡፡ እውነት እልሃለሁ አንድዬ ለአፍታም ቢሆን እጅ ቢያውሰኝ እንዲህ በነጋ በጠባ ቁጥር ቆሽቴን አታሳርረውም ነበር ፡፡ በሚያምረው ከረባትህ ጎትቼ አስጠጋህና እንደ አርጋው በዳሶ በጭንቅላትህ እቀብርህ ነበር ፡፡ ይሄ የሰው አህያ ! እንደ ወሎ ፈረስ መልክህን ብቻ ከማሳመር ቀፎ ጭንቅላትህ ውስጥ ንቦች ምግብ እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታ ብትፈጥርላቸው አይሻላልም ?

‹‹ ጆኒ ቀዌ መጣች ፡፡ ዛሬ ደግሞ እነዚህ የጎዳና ልጆች እያዋከቡት ነው ፡፡ እንደው እኔም ርስት ሆኜ የሰው ዘር በይገባኛል ሲጣላብኝ ያመኛል ፡፡ ይህን ያወኩት እዛ ቆሼ የተባለ ሰፈር ነው ፡፡ ቢያንስ በዓመት ሶስትና አራቴ ቆሼ እንድሄድ ይፈቀድልኛል ፡፡ ለነገሩማ በየሁለት ቀናትና በሳምንት ሂሳብ ነበር ቆሻሻዬ ሊራገፍ የሚገባው ፡፡ አልፎ አልፎ ስሄድ ታዲያ የሰው ልጅ የገንዳ ቆሻሻን የቦሌ - የጉለሌ ፤ የሸራተን - የሂልተን … በሚል ስያሜ ለፍቶ እንዳገኘው ርስት ሲራኮትበት ፤ ጦር ሲማዘዝበት እመለከታለሁ ፡፡ በእውነት ይሄ የዘርና የጎሳ  አስተሳሰብ ቆሻሻ ድረስ መዘርጋቱ ያሰቅቃል ፡፡ ማቲው ብቻ ሳይሆን ነፍስ ያወቀው ሁሉ ‹ ምርጥ ምግብና ምርጥ ዕቃ › ለመሰብሰብ ዘወትር ቡጢውን ሌላው ላይ መወርወር ግዴታው ሆኗል ፡፡ አንዱ አገልግሎቱ ስላበቃ ወይም ስለቆሸሸ ብሎ የጣለውን ሌላው እንደ ብርቅ ማዕድን ቆፍሮ ለማውጣት መታከቱ ያስቆዝማል ፡፡

‹‹ ታዲያ ጆኒ የሚገርመኝ የሚፈልገው የብዕር ቀፎና ማስመሪያ መሆኑ ብቻ ነው ፡፡ እነዚህ ኩይሳዎች እንኳ ላዬ ላይ ወጥተው የሚቦጠቡጡት የተራረፈ ምግብ ፍለጋ ነው ፡፡ ታዲያ ለማይገናኘው ፍላጎታቸው ለምን አጉል ይናከሳሉ ? እውነት ይሁን ውሸት ያበደውም ከቆሻሻ ጋር በተያያዘ ምክንያት ነው ይባላል ፡፡ ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ እንደተመረቀ የከተማው ቆሻሻ እንደ ችግር ሳይሆን እንደ ድሃ አጋር ሊታይ የሚችልበትን ‹ አንድ - በአራት › የተባለ ልዩ የፈጠራ ፕሮጄክት አቅርቦ ነበር ፡፡ ከቆሻሻ አግሮ ስቶን ፣ ነጭ ከሰል ፣ ባዮ ጋዝ እና የካኪ ፌስታል ለመስራት ፡፡ ጉዳዩን ያዳመጡት የሚመለከታቸው ወገኖች ‹ ፕሮጄክትህ ግማሽ እውነት - ግማሽ እብደት የተቀላቀለበት ነው › በማለት አጣጣሉበት ፡፡ እየቆየ ሲሄድ ግን አንዳንድ የፈጠራ ሰዎችና ባለሀብቶች ከጥቅሉ ፕሮጄክት አንድ አንዱን እየመዘዙ ጥቅም አነደዱበት ፡፡ ቀስ በቀስ ደግሞ ‹ ለምን ? እንዴት ? ፍትህ የለም ! › ማለት ያበዛው የጆኒ ጭንቅላት ነደደ አሉ ፡፡ ጆኒ ግን ያሳዝነኛል ፡፡ የጸዳ ነጭ ወረቀት ማለት ነው - ተንኮል ፣ ጥላቻም ሆነ እብሪት አይንጸባረቅበትም ፡፡ በዚህ ለጋ እድሜውም ማበድ አልነበረበትም ፡፡ በርግጥ በሽተኛን ደጋግሞ በማመናጨቅ የሚታወቁት ሀኪሞች በትኩረት ደጋግመው ቢያክሙት ይድናል ፡፡ ጆኒን በትኩረት ቢያጤኑት ሊማሩበትም ይችላሉ ፡፡ ምነው ብትሉ አንድም ቀን ተሳስቶ በአካባቢዬ ሽንቱን ሸንቶ አያውቅም ፡፡

‹‹ ምስኪን ! ከእነዚህ እርጉሞች ጋር ላለመጣላት ነው መሰለኝ አቅጣጫውን ቀየረ ፡፡ መጡ እነዚህ ከፈሳቸው ጋር የተጣሉ ! ዘለው አናቴ ላይ ወጡ ! መነቀሩኝ ! አቤት አስፋልቱ በአንድ አፍታ ቄጤማ ተጎዘጎዘበት ፡፡ ፈንዲሻ ተረጨበት . . . ዕጣን ተለኮሰበት . . . ደስ ይላቸዋል ልበል ?! አልናገርም ፣ አልሰማም ፣ አላይም በሚል ፍልስፍናው የሚታወቀው የአዲስ አበባ ነዋሪም ይፈራቸዋል መሰለኝ አይገስጻቸውም ፡፡

‹‹ ታዲያ ምነው ሮጡ ? . . , አሃ ! ድንጋይ ወርዋሪዋን ወይዘሮ  ተካበች አይተው ነው ፡፡ የእኚህ ሴትዮ ልብና በሁለት ገጹ የሚለበስ ጃኬት አንድ ናቸው ፡፡ ሴትየዋ ቀን ቀን ሰው እንዲያያቸው ይህን የመሰለ ልማታዊ ተውኔት ይሰራሉ ፡፡ ሰው አይደለም ውሾች ቆሻሻውን ሲመነቅሩ ዝም አይሉም ፡፡ በጩኀትም ሆነ በፉጨት በል ሲላቸውም ድንጋይ በመወርወር ያካልቧቸዋል ፡፡ ይህ ተግባራቸው ግን አንዳንዴ የከፋ ጉዳት ይዞ ሊመጣ ይችላል ፡፡ አንድ ግዜ የሆነውን ማንሳት ጥሩ ነው ፡፡ የተራቡ ይሁኑ ስሪያ የጨረሱ በርካታ ውሾች ገንዳውን ሲሞነጭሩ በመድረሳቸው ድንጋይ ማዝነብ ጀመሩ ፡፡ ኤፍ ኤም 97.1 ጠዋት ጠዋት ከሳጅን መዝገቡ ጋር አዘውትሮ የሚያሰማውን  የትራፊክ ዘገባ  ማዳመጥ ከማይመቻቸው ውሾች መካከል  ሶስቱ በደመነፍስ ሲካለቡ የትልቅ መኪና ጎማ ደፈጠጣቸው ፡፡ አንድ ቀን ሙሉ ከአስፋልት ማንም ሳያነሳቸው ከተዘረሩ በኃላ መሽተት ሲጀምሩ  ወይዘሮ ተካበች የጎዳና ተዳዳሪዎችን አሰባስበው እኔ ጀርባ ላይ እንዲወረወር አደረጉ ፡፡ አቤት ለአንድ ሳምንት የነበረው  የአካባቢ ቅርናት ! አቤት ጭንቅላቴን የወረረው የግማት ጥቃት ! ያኔ ጋዜጠኞችን ጠርቼ ጥልቀት ያለው መግለጫ ብሰጥ እደሰት ነበር ፡፡ እረ የሬዲዮ የአየር ሰዓት ገዝቶ የመዘባረቅ ሀሳብ ሁሉ የመጣብኝ ያኔ ነው ፡፡

‹‹ ታዲያ እኚህ ተዋናይ ሴትዮ ዱሪዬዎችንም ሆነ ውሻዎችን ካባረሩ በኃላ ወጪ ወራጁ እንዲሰማቸው የፈጸሙትን ገድል ለደቂቃዎች ይተርካሉ ፡፡ የንግግራቸው ቃናም ሆነ የአካላቸው እንቅስቃሴ ግዜያዊ መድረክ ላይ ያለ አይመስልም ፡፡ በጣም የሚገርመው መነባንቡን የትና መቼ እንደሚያጠኑት ነው ፡፡ ማታ ማታ ሌላ ናቸው ፡፡ የራሳቸውን የጠላ ድፍድፍ ፣ ለሌሎች ተቀጥረው ደግሞ የአትክትልና ፍራፍሬ ልጣጭና ብስባሽ በኔ ዙሪያ ይቆልላሉ ፡፡ ጠዋት ሲነጋ ከሁሉ ቀድመው ‹ አበስኩ ገበርኩ › ን የሚያዜሙት እሳቸው ናቸው ፡፡

‹‹ እኔ የምለው ይህ የከተማ ህዝብ እስከመቼ ነው የምናገባኝ ፖሊሲውን የሚያራምደው ? አንድ ሰሞን በጉንፋንና ኮሌራ ፣ በትውከትና ተቅማጥ ልጆቻችንና እኛ ማለቅ የለብንም በየአካባቢያችንም በቂ ገንዳ ሊቀመጥ ይገባል በማለት ጩኀቱን አቀለጠ ፡፡ ፊደል የቆጠሩትም ለከተማ እድገት የጽዳት አጠባበቅ አስፈላጊ መሆኑን የሌሎች ሀገሮችን ልምድ በመጠቃቀስ መንግስት ከእንቅልፉ እንዲነቃ ጎተጎቱ ፡፡ የሁሉም ሀሳብ ትክክል ስለነበር  እኔና ጓደኞቼ ሰፈር ከተማውን አጥለቀለቅነው ፡፡ ምን ዋጋ አለው ታዲያ ? ጩኀቱ ቆሻሻውን ለመድፋት ብቻ ሆነ ፡፡ ገንዳው ሲሞላ እንዲነሳ ማን ይጩህ ? በግምና ክርፋት አየር ውስጥ ያለመኖር መብታችን ይከበር ! ማን ይበል ?

‹‹ አስተዳዳሪዎቹ በምርጫ ሰሞን ‹ መልካም አስተዳደር እናሰፍናለን ! ህዳሴውን እናረጋግጣለን › ሲሉት ለምን በተጨባጩ ቆሻሻ አያፋጥጣቸውም ፡፡ ሚዛን አትደፋም ተብላ በማትጠቀሰው ቆሻሻ ተግባራዊ ማንነትን መለካት ይቻላል ፡፡ ለምሳሌ አስተዳደሩ የከተማውን ጉድፍ አይደለም በማዘጋጃ ዙሪያ የሚታየውን ሽንትና አይነምድር ማጽዳት አልቻለም ፡፡ የአውሮፓዎችን መንግስታዊ አስተዳደር ቀምሮ ቢያስፋፋ ኖሮ ስንት ግዜ ስልጣኑን በፈቃዱ በለቀቀ ነበር ፡፡

 
‹‹ በርግጥ አስተዳደሩ ከተማዋ ለአፍሪካ ህብረት መቀመጫነት አትመጥንም የሚል የሰላ ትችት በውጭ ሰዎች ድንገት ሲቀርብ የሆነ ነገር ለመስራት ተፍ ተፍ ይላል ፡፡ ለልምድና ተሞክሮ ልውውጥ የጽዳት ሰራዊቱን በምድረ አፍሪካ ይበትናል ፡፡ አንድ ሰሞን ኪጋሊ ደርሶ የመጣው ልዑክ ጆሮአችንን አደንቁሮት ነበር ፡፡ ‹ እውነት ሰው በላዋ የሩዋንዳ ከተማ እንደዚህ ውብ ናት ? › የሚለው ግርምት ከልክ በላይ ተጭኖብን ነበር ፡፡ ሰው በጦርነት ሲበላ የከረመ ከተማ የኃላ ኃላ በውበት የሚልቅ እስኪመስል ድረስ ፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ አዲስ አበባ የኪጋሊ አቻ ለመሆን የቀረበች ናት ፡፡ የቀይና ነጭ ሽብር ባለታሪክ ናትና ፡፡

‹‹ የጽዳት ሰራዊቱ ግብም በአንድ ተጨባጭ ለውጥ እንደሚደመደም ተገምቶ ነበር ፡፡ ግን የዚህን ሀገር ተግባር አውሎ ንፋስና ማዕበል ሳይሆን ወሬ ነው የሚበላው ፡፡ ይባስ ብሎ በቅርቡ ደግሞ በጥናት ሳይሆን በአውሎ ንፋስ የመጣ የሚመስል ዜና የከተማዋን ኃላፊዎች አሙቋቸዋል ፡፡ ሎንሊ ፕላኔት የተባለ ዓለማቀፍ የጉዞና አስጉበኚ መጽሀፍ ካምፓኒ አ/አ በ2013 ሊጎበኙ ከሚገባቸው አስር የዓለማችን ከተሞች አንደኛዋ ናት በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል ፡፡ ይሄን ያልኩትም ከተማዋ ፈጣን እድገት እያሳየች በመሆኑ ነው ብሏል ፡፡ መቼም ይህ ድርጅት የሀገር ውስጥ ጋዜጣ ቢሆን ኖሮ ሚዛን ያልጠበቀ ዜና በማሰራጨቱ ፍ/ቤት ሊቆም አሊያም ሊታገድ በቻለ ነበር ፡፡ ደግነቱ ስምን መልዓክ ያወጣዋል የሚል አባባል መኖሩ ፡፡ ሎንሊ ወይም ብቸኛው ድርጅት ያወጣውን ዘገባ ሌሎች አልደገፉትም ፡፡ ‹ ብቻህን ተወጣው ! › የተባለ ይመስላል ፡፡ እረ ‹ ፈረንጁ ዋልታ ማዕከል ! › ያሉትም ሳይኖሩ አይቀርም ፡፡ ብቻ ብዙ የሚጋጩ ነገሮች ስላሉ ከእንቅፋቱም ከነገሩም ላለመላተም ግራና ቀኝ እያስተዋሉ መጓዝ ይበጃል ፡፡ ለምሳሌ ባለስልጣኖች የሚፈሩት ፎርበስ / Forbes / አዲስ አበባ የዓለማችን ስድስተኛዋ ቆሻሻ ከተማ መሆኗን ነው በቅደም ተከተሉ የሚያሳየው ፡፡ ይህ አይነቱ መረጃ ከሎንሊ አይደለም ከሞተው ብሩስሊ ጋር ካራቴ አያማዝዝም ?

‹‹  አዲስ አበባ ትንሳኤ ማግኘቷን ታረጋግጥ የነበረው ያ ማነው ; . . . ጉዳዬ ሳይሞላ እያለ ያዜመው . . .  እንዳጀማመሩ ቢዘልቅበት ነበር ፡፡ ልብ በሉ ! አበራ ሞላ ሲያንጽ የነበረው ጽዳት ብቻ አልነበረም ፡፡ የአስተሳሰብ ለውጥና ውበትንም ጭምር እንጂ ፡፡ በከተማችን ስንት ሞተው ኀውልት የቆመላቸውን ቦታዎች አይደለ አንዴ እንደ ፈጣሪ . . . ‹ እፍ ተነሱ ብርሃን አግኝታችኃል › እያለ ያነቃቸው ፡፡ ካድሬዎች ግን በግምገማቸው አበራ ሞላ በከተማዋ ያበዛው ማሰሮና መፈክር ነው ማለታቸው ተሰምቷል ፡፡ እረ በሀገራችን ታሪክ መፈክር አብዝቶ የማያውቅ መንግስት ነበር እንዴ ?

‹‹ የከተማው አስተዳደር መቋቋምና ማሸነፍ ካልቻለባቸው ጉዳዮች አንዱ ጽዳት መሆኑ ይታወቃል ፡፡ ብሎ ብሎ ሲያቅተው ደጋግሞ የሚያነሳት ምክንያት ‹ ህዝቡ የአስተሳሰብ ለውጥ ሊያመጣ አልቻለም ! › የምትል ናት ፡፡ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዴት ሊመጣ እንደሚችል ግን የጠለቀ ግንዛቤ ያለው መሆኑ ያጠራጥራል ፡፡ ገንዳዎች በየአደባባዩ ከተቀመጡ ሰዎች በአካባቢው ይሸናሉ በሚል ወደ መንደር ማራቅ ተጀምሮ ነበር ፡፡ ግን ገንዳዎች ባይኖሩም የከተማችን ግንቦች ዛሬም በቀንም ሆነ ማታ እንደጉድ ይሸናባቸዋል ፡፡ ይህን ችግር ጠልቆ ያለመረዳት ነው ስንኩልና ፡፡ እንኳን ሽንት ቤት መኖሪያ ቤት የሌለው የከተማ ህዝብ ጭንቀቱን የት ይክፈል ? አስተዳደሩ በየቀበሌውና በየሰፈሩ ደረጃቸውን የጠበቁ መጸዳጃ ቤቶችን መገንባት ቢኖርበትም አላደረገውም ፡፡ ጥቃቅንና አነስተኛ ሱቆችን በየቦታው እንደ አሸን ሲያፈላ ለሽንት ቤት ግን ቦታ የለኝም ይላል ፡፡ ያሉትን ክፍት ቦታዎች በሙሉ በሰብዓዊነት ሳይሆን በገንዘብ ጭንቅላት እያሰበ ግንባታ እንዲጥለቀለቅባቸው ያደርጋል ፡፡ ለልማት ግንባታ የማይደረግ ነገር የለም በሚል ለመንገድ ግንባታ ቤቶችን ያፈርሳል ፡፡ ሽንት ቤት ለመገንባት ለምን ቤቶች እንዲፈርሱ አይደረግም ? 
‹‹ ለማንኛውም ገንዳን ለማጽዳት ፍትሃዊ ፣ ግልጽና  የጸዳ አስተሳሰብ ያስፈልጋል ፡፡ ይህን ሃሳብ በተጠማዘዘ መንገድ ላስረዳ ፡፡ አስተዳደሩ በስሪቱ ውስጥ የወይዘሮ ተካበች አይነቶችን በብዛት ከመቆለልና ከመካብ ፤ የጆኒ ቀዌ አይነቱን እያከመ ፣ እየደገፈና የስራ ነጻነታቸውን እያረጋገጠ ቢቀጥል ያዋጣዋል ››

ማስታወሻ፡- ይህ ፅሑፍ በቁም ነገር መፅሔት ቅፅ 12 ቁጥር 151 ላይ የወጣ ፅሑፍ ነው፡፡ ፅሑፉን በሌላ ሚዲያ ላይ የምትጠቀሙ ከሆነ ምንጩን እንድትጠቅሱ ትለመናላችሁ፡፡