ኢትዮጽያ አይኗን በጨው ካጠበችው ግብፅና አይኗን በአግባቡ መታጠብ ካቃታት ሱዳን ጋር እሰጥ አገባ ከገባች
አመታትን አስቆጠረች ። ድርድሩ የፓለቲካውና ዲፕሎማሲውን መንገድ ይከተል በሚል እንጂ በጉንጭ አልፋው ንግግር ውጤት ይገኛል ተብሎ አይጠበቅም ።
ፈጣጣዋ ግብፅ የቅኝ ግዛቶችን ውል ከትከሻዋ ላይ ማውረድ አትፈልግም ። ከግፈኛዋ
እንግሊዝ የተቀበለችውን የውሃ ድርሻ እንደ ጄነራል ክፍ አድርጎታል ። ይህን ማእረግ ወደ ሻምበልነት የሚያወርድ ተጋፊ ሃይልን አትቀበልም
። እናም በእሷ ቀመር የውሃው ባለቤትነት የሚመዘነው ከሚመነጭበት ቦታ ሳይሆን በተፈጥሮ ቀድሞ በያዘ ነው - ላለው ይጨመርለታል
የሚባለውን የወንጌል ጥቅስ እንድናስታውስ በማድረግ ።
ሱዳን ከቅኝ ገዢዋ መሃንዲስ የሚበቃትን ያህል ድርሻ ተቀብላለች ። የአባይ
ወንዝና የግድቡ ወሬ ሲነሳ የምታዳምጠው አይናር የማይጠፋውን አይኗን እየሞዥቀች ነው ። አይናሩ ሲለቃት ግድቡ ይጠቅመኛል ከኢትዮጽያ
ጎን ነኝ ትላለች ። አይናሩ አንቆ ሲይዛት የግብጽ ማስፈራሪያ ነው ቀድሞ የሚሰማት ። ያኔ ግብፅን በአረብኛ ማናገር ትጀምራለች
- አቋም እንዲኖራት አትፈልግም ።
እነዚህ ሀገሮች ከያዙት ሀገወጥ ጥቅምም ሆነ ከሚያስተሳስረቸው ፖለቲካዊ ውግንና
አንጻር ወደ መሃል ተስበው የሚመጡ አይደሉም ። ወደታች ወርደው የእውነት ባልጩት ላይ ከቆሙ ድንጋዩ ያበቀለው አልጌ አዳልጦ እንደሚጥላቸው
ይረዳሉ ። የሚደራደሩት አዲሱን እውነት ለመቀበልና የቆየውን ክብር ለማጣት አይደለም ።
ለዚያም ነው በተለይ ግብፅ ከድርድር ይልቅ አደራዳሪን ምርኩዝ ማድረግ የምትመርጠው
። ለቡራኬ ሰጪዎች ትልቅ ቦታ አላት ። ድሮ ለዚህ ያበቃቻት እንግሊዝ ዛሬ ባትጠቅማትም አሜሪካንን መተካት አላቃታትም ። ትላልቆቹ
በስሟ እንዲያስፈራሩላትና የረባሽ ሀገራትን ጆሮ እንዲቆነጥጡላት ትፈልጋለች ። የያዘችው እውነት ለዛሬው አለም ባይሰራም አይኗን
አፍጣ አለም መንግስታት ፊት ስሞታ ታቀርባለች ። ጩኸቷን እንዲጮሁላት አጥብቃ ነው የምትሰራው ። አልፋም ትሄዳለች - ሁሉንም አማራጮች
እጠቀማለሁ የሚል ማስፈራሪያ በመልቀቅ ።
እንደሚታወቀው የውሃው መነሻም ሆነ የግድቡ መድረሻ ከኢትዮጽያ ነው ወይም
ኢትዪጽያ ናት ። በውሃ የመጠቀም አለማቀፋዊ መብቷ ጥያቄ ውስጥ ባይገባም የምትደራደረው ግን በድርድር ተጎጂልን ከሚሏት ፈጣጣ ሀገራት
ጋ ነው ። ድርድሩን አለም ይውቅልኝ ፣ ፍትሃዊነቱንም ይገንዘብልኝ የምትለው የሌሎችም አጋር መሆናን ለማሳየት ነው ። ሀገሬ ግን
ነገ ጠባ እየከሰሷት ፣ አለፍ ሲልም እያስፈራሯት ፍትሃዊ አካሄዴ ይታወቅልኝ በሚል ባዘነች ።
እንደ እውነቱ ከሆነ ግድቡን ለመስራትም ሆነ ውሃውን ለመሙላት የማንንም ፍቃድ
መጠየቅ አያስፈልግም ። መጠንቀቅ ያለብን ሌሎችን በጭፍን ጥላቻ ላለመጉዳታችን ብቻ ነው ። ከዚያ ውጪ ወንዙም ግድቡም የኛ ነው ። በያዝነው ነገር ላይ መያዛችንን
ከማይቀበል ቡድን ጋር ለምን ሃይላችንን እናጠፋለን ? ብለህ ብለህ አልቀበል ካለህ የያዝከውን አስተማማኝ የፍትህ መዶሻ በራስህ
ጠረጼዛ ላይ መምታት ተገቢ ነው ። ከዚያ ለፍርድ አፈጻጸም ወደሚመለከተው አካል በየአድራሻው መላክ - ይኅው ነው ። ውሃውን መሙላት
ስትጀምር ትላንት አልቀበል ያለህ ሁሉ ሰልፉን ካንተ ጋ ያሳምራል ፤ ቋንቋውንም ይለውጣል ። ዋ ! የሚልህን ረስቶ ‹ እባክህ
› ማለት ይጀምራል ። አለም የምታሳየን እውነት ይሄንን ነው ። ከወሬው ቀንሰን ይህን ለማድረግ እንፍጠን ። ያኔ የመታኸው መዶሻ
ጠብቆ መግባቱን ቢያንስ ቢያንስ ደግሞ ትክክል መሆኑን ትገነዘባለህ ።
በርግጥ ሌሎችን ተደግፎም ሆነ በራሱ የሚያስፈራራው ቡድን ምንም አያመጣም
ብሎ መዘናጋት ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል ። ግልጽ ጦርነት ባይከፍትብህ እንኳ ሌሎችን በገንዝብ በመግዛት ጥቅምህን ለመናድ ሌት ተቀን
ይሰራል ። ሱዳን እና የኛ ሀገር ባንዳዋችን በዋናነት እንደሚጠቀም መጠራጠር አይኖርብንም ። ግድቡ ድንበር ላይ እንዲሰራ መደረጉ
ምናልባት የሚጎዳንም በዚህ መሰሉ አጣብቂኝ ግዜ ነው ። እናም በአንድ በኩል ግድቡን ለመጨረስ እየተጉ በሌላ በኩል ግድቡንና አካባቢውን
በአስተማማኝ መከላከያ ማጠር ያስፈልጋል ። የሀገር ቤቶችን ባንዳዎች እግር በእግር ተከታትሎ ግባቸውን ለማጨናገፍ ፣ የጆሮ ጠቢውን
መስሪያ ቤት ሚና ከመቼውም ግዜ በላቀ መልኩ ማሳደግ ተመራጭ ይሆናል ።
No comments:
Post a Comment