Saturday, August 18, 2018

በግማሽ ሜዳ መጫወት ...



ሶሎ ጎል ይሉታል ፈረንጆቹ ፡፡ አንድ ተጫዋች በርካታ ባላጋራዎቹን አልፎ ጎል ሲያስቆጥር ፡፡ በጥበብ ፣ አካላዊ ብቃት ፣ ብልጠትና ድፍረት መሞላትን ስለሚጠይቅ ሁሉም ተጫዎቾች ሊያከናውኑት አይችሉም ፡፡ እናም ለግብ አግቢው ከወንበር ተነስቶ የረዘመ ጭብጨባና ክብር መስጠት ግድ ይላል ፡፡

ልክ እንደ ሶሎ < ዋው > የሚያስብል ሌላ ጥበብም እለ በእግር ኳሱ ዘንድ ፡፡ ከግማሽ ሜዳ ኳስን በትክክል መትሮ ጎል ማስቆጠር ፡፡ ይህንም ሲያደርጉ ያየናቸው ጥቂት የዓለማችን ተጫዋቾች ናቸው ፡፡ ጁዋን ካርሎስ ፣ ናቢ ፍቅርና ዋይኒ ሩኒን እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል ፡፡ ኤቨርተንና ዌስትሃም ሲጫወቱ ዋይኒ ሩኒ ያደረገው ምንድነው ? ከክልሉ ወጥቶ ኳሷን ወደ መሃል ያወጣትን በረኛ ሁኔታ በመገንዘቡ ኳሷ ስትደርሰው ቀጥታ ወደፊት አጎናት ፡፡ ዳኛው የተለጋውን ኳስ እንዳይነካ አፈገፈገ ... ሁለት ተጫዋቾች ባለ በሌለ ሃይላቸው ወደላይ ለቴስታ ዘለሉ ... የመጨረሻው ተከላካይ ከሩቅ የተለጋ ኳስ ከሚቆጠርብን በእጄ ለኤሪጎሬ ባስቀራት ይሻላል ብሎ ወደ ላይ ዘለለ – አላገኛትም ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግብ ጠባቂው ወደጎል ሮጦ በማያውቀው ፍጥነት እየተፈተለከ ነበር ፡፡ ልብ አንጠልጣይ ድራማ ካየን በኋላ ኳሷ ከመረቡ ጋ ተሳሳመች ፡፡

ዶ/ር አብይ በእነዚህ አብዶኛ ተጫዎቾች ይመሰላሉ ፡፡ ከግማሽ ሜዳ የጠለዟቸው የፖለቲካ ኳሶች ጅቡቲ ፣ ሱዳን ፣ ግብፅ ፣ ሳዑዲ ፣ ኡጋንዳና ኤርትራ አርፈው ድል አስቆጥረዋል ፡፡ በአንድ በኩል የዲፕሎማሲውን ግንኙነት ሲያጠናክሩ በሌላ በኩል ማንም ሀሳብ ውስጥ ያልነበሩ ዜጎችን ከእስር አስፈትተዋል ፡፡ ወደክልሎች በመጓዝ ጥበብ ፣ ብልጠትና ድፍረት የተሞላበት ሃገራዊ ምክክር አድርገዋል ፡፡ በጎሳና ዘረኝነት ክፋት ተሰነጣጥቆ ሊበተን የነበረውን ኢትዮጵያዊ ትሪ ጠግነዋል ፡፡ የተራራቁ ሰዋች በአንድነት ተሰባስበው ባዛው ትሪ ላይ ማዕድ እንዲቀርቡ ፣ የጋራ ፀሎታቸውም ፍቅር ፣ ሰላምና ኢትዮጵያዊ ድማሬ እንዲሆን መንገድ አሳይተዋል ፡፡ ርቆ የተቀበረው ኢትዮጵያዊነት ክብሩ ተመልሶ ከባንዲራ በላይ እንዲውለበለብ አድርገዋል ፡፡

ዶ/ር አብይ በአጭር ግዜ ውስጥ ያስመዘገቧቸው ድሎች አመርቂና ተስፋ ሰጪ ቢሆኑም እየተጫወቱ የሚገኙት በግማሽ ሜዳ ነው ፡፡ ከትልቁ ጥያቄ አንደኛው ስንቱን ህዝባዊ ጥያቄ ከግማሽ ሜዳ እየመተሩ ማስገባት ይችላሉ ? የሚለው ነው ፡፡ ከትልቁ ጥያቄ ሁለተኛው ስንቱን እግር ሰባሪ ተከላካይ በአብዶ እየሸወዱ ውጤት ያስመዘግባሉ የሚለው ነው ፡፡

ዶ/ር አብይ ብዙ ተከላካዮችን አብዶ ሰርተው አልፈው ጎል የሚያስቆጥሩት ኢትዮጵያዊነትን ከዳር እስከ ዳር ለማሳደግ ነው ፡፡ ይሁንና ጥቂትም ሳይቆይ ሲዳማው ፣ አገው ፣ ጉራጌው በኔ ልክ የተሰፋ ክልል ይገባኛል ብሎ ጥብቆ ሲናፍቅ ታገኘዋለህ ፡፡ ዶ/ር አብይ ብዙ ተከላካዮችን አብዶ ሰርተው አልፈው ጎል የሚያስቆጥሩት  እንደ < ገነት > የምንናፍቀውን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እናይ ዘንድ ጥርጊያ መንገዱን ለመገንባት ነው ፡፡ ይሁን እንጂ ለድሃ ዳቦ እንጂ ነፃ ስርዓት አያስፈልገውም የሚሉ አምባገነኖች በተሰነጣጠቀው መንገዳችን ላይ የሚፈነዳዳ ፈንጂ ከመቅበር ሊቆጠቡ አልቻሉም ፡፡ ዶ/ር አብይ ከመሃል ሜዳ ለግተው ጎል የሚያስቆጥሩት የማሸነፍ ረሃብን ለማስታገስና ሮል ሞዴሎችን ለመቅረፅ ነው ፡፡ ይሁን እንጂ ማጥቃትንም ሆነ መከላከል እርግፍ አድርገው ትተው ጨዋታ የሚያቆሙ ብዙሃንን ታያለህ ፡፡ በሌላ አነጋገር ጨዋታውን አቋርጠው በፎርፌ ማሸነፋችን ይታወጅልን የሚሉ ፡፡ እነዚህ ወገኖች በጥቂት ወይም ሚዛን በማያነሳ ምክንያት ዱላ ፣ ገጀራና ክብሪት አንስተው ቀጣዩን ጥፋት ለማከናወን የማያመነቱ ሆነዋል ፡፡ ነገር ቆስቋሾች ፣ ገዳዳ አክቲቪስቶች ፣ በቀልተኛ ፖለቲከኞች ጃስ ባሏቸው ቁጥር ለምን ? እና እንዴትን ? ሳያነሱ ዘለው ንጹሃንን የሚናከሱ ወገኖቻችን እየበዙ መጥተዋል ፡፡ እነዚህን ሁሉ መግራት ከባድ ነው ፡፡ በአንድ ቀን ምክክርና የእርቅ ጉባኤም አጀንዳውን መዝጋት አይቻልም ፡፡

ጠ/ሚ/ሩ በየክልሉ በዘር ፣ ቋንቋና ሃይማኖት የሚለኮሱ ግጭቶችን ለማብረድና ለማስታረቅ የሚሯሯጡ ከሆነ ሌላውን አንገብጋቢ ስራ መስራት አይችሉም ፡፡ የፖለቲካ መዋቅሩም ሆነ ህዝቡ ጥሩ ጎል አግቢ ስለሆኑ እሳቸውን ብቻ የሚጠብቅ ከሆነ ሽምግልና እንጂ መንግስታዊ አሰራር ውሃ ይበላዋል ፡፡ ለዚያም ነው ጠ/ሚ/ሩ በግማሽ ሳይሆን በሙሉ ሜዳ መጫወት የሚችሉበት ቋሚ አሰራር መፈጠር አለበት የሚባለው ፡፡ ለዚያም ነው ከቅርብም ሆነ ከሩቅ ለግተው ግብ የሚያስቆጥሩ ኮኮቦችን ማፍራት ይገባቸዋል የምለው ፡፡

ርግጥ ነው በሀገራችን ያንዣበበውን ስጋት ለመቅረፍ ክፋትንና ድህነትን ተጭኖና አጥቅቶ በመጫወት ተደጋጋሚ ግቦችን ማስቆጠር ያስፈልጋል ፡፡ አለበለዚያ አቻ መውጣትና መሸነፍም ያጋጥማል ፡፡ አቻ መውጣት ክፋትንና ድህነትን አቅፎ መኖር ነው ፡፡ ወንድም ጋሼ ... ጌታ መሳይ... እያልከው ፡፡ ከተሸነፍክ ያለውድ በግድ < ጅቦች ለዘላለም ይኑሩ ! > የሚል መፈክር ተሸክመህ ትዘልቃለህ ፡፡ እነሱ የሚጥሉትን ቅንጥብጣቢ አያሳጣኝ እያልክ ፡፡ የሰላምና የፍቅርን ኳስ በማራኪ አጨዋወት እስከተቃራኒው ክልል ደርሶ ያማረ ጎል ማስገባት ያስፈልጋል ፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ለዋናው አጥቂ ኳስ አመቻችተው የሚሰጡ ደጀኖች ፣ አጥቂው ሲደክም ጎል ማስቆጠር የሚችሉ ቁርጠኛና ጥበበኛ ተጫዋቾች መሰለፋቸው መረጋገጥ ይኖርበታል ፡፡

በየክልሉ የሚለኮሱ ጎሳዊ ግጭቶችን ለመቀነስና ለመከላከል የተጠናከረ ትምህርትና ስልጠና ግድ ነው ፡፡ ለ27 ዓመታት የዘውጌ ስርዓት በማበቡና ብሄርተኝነት የተሻለ አማራጭ ተደርጎ በመሰበኩ ኢትዮጵያዊነትን በቀላሉ ማስረፅ ሳይከብድ አይቀርም ፡፡ ይህን ስራ የሚሰሩ የሲቪክ ተቋማትን ማስፋፋት ይጠይቅ ይሆናል ፡፡ ተመሳሳይ የፖለቲካ መስመር የሚከተሉ ድርጅቶችንና ቲንክታንኮችን Add እና Tag ማድረግ ግድ ይመስላል ። በውስጥ አሰራር ደግሞ ለንቋሳ አመራሮችን እየሻሩ ፣ ጠንካሮቹ ንቃተ ህሊናን ለማዳበር የሚያስችሉ የምክክር መድረኮችን ረጅም የስራ አካልና ግብ አድርገው እንዲተጉ ማሳሳብ ይጠበቃል ፡፡

ዘረኝነትና ጎሰኝነት አይደለም በአፍሪካ በአውሮፓ መሞት አልቻለም ፡፡ ጉዳት እንዳያደርስ ሸብቦ የያዘው ግን ጠንካራ ህጋቸው ነው ፡፡ ዶ/ር አብይ የፍቅርና ይቅርባይነትን ሎጎ ከፍ በማድረግ አስተዳደራቸው እንዳይንገጫገጭ ማድረግ ቢችሉ ሸጋ ነበር – ድብቁና ውስብስቡ ፖለቲካ ግን በዚህ ቀመር የሚሰራበት አግባብ በእጅጉ የሰለሰለ ነው ፡፡ አሸባሪ ፖለቲከኞችን ፣ የዘረኝነት ፈንጂ ቀማሚዋችን ፣ ብሄርን ከብሄር ለማጋጨት ሃሳብ ፣ ክብሪትና ጥይት የሚያቀብሉ የደም ነጋዴዋችን በአጠቃላይ ህገወጦችን መስመር የሚያሲዙበት ህጋዊ ማእቀፍ ያስፈልጋቸዋል ፡፡

No comments:

Post a Comment