Monday, September 25, 2017

ደራሲው ጋዳፊ ለምን ሀሳቡን አልሆነም ?




የሊቢያው መሪ ሙአመር ጋዳፊ ፖለቲከኛ ፣ ሃሳብ አመንጪ እና ደራሲ ነው ። በረጅም የስልጣን ዘመን ቆይታው Escape to hell and others , My vision እና The Green Book የተሰኙ ሶስት ተጠቃሽ መጻህፍትን ለዓለም አበርክቷል ።

አዲስ የፖለቲካ ፍልስፍናውን በመጽሐፍ መልክ ማሳተም የጀመረው በ1975 ነበር ። የዴሞክራሲ ችግር መፍትሄ ፣ የኢኮኖሚ ችግር መፍትሄ እና የሶስተኛው ዓለማቀፍ ቲዎሪ ማህበራዊ መሰረቶች የሚሉ ሶስት ጥራዞችን በተለያዩ ግዜ ጽፏል ። ኋላ ላይ እነዚህን ጥራዞች አንድ ላይ በመሰብሰብ አረንጓዴው መጽሐፍ በሚል ለንባብ አብቅቷቸዋል ።

አረንጓዴው መጽሐፍ ዓለምን ብዙ ያነጋገረና ያከራከረ ስራ ነው ። ይህን መጽሐፍ የተማሩበት የሊቢያ ወጣቶች ብቻ አልነበሩም ። በፈረንሳይ ፣ ምስራቅ አውሮፓ፣ ኮሎምቢያ እና ቬንዚውላ ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች ተወያይተውበታል ፤ አውደጥናት ተካፍለውበታል ።

ጋዳፊ የፍልስፍና ውሃ ልኩን በአረንጓዴው መጽሐፍ ለማሳየት ሞክሯል ። በተለይ የምእራቡ ዓለም የዴሞክራሲ፣ ኢኮኖሚና ፖለቲካዊ አስተምህሮ ጠማማ መሆኑን መነሻ በማድረግ የችግሮቹን መፍትሄ በአማራጭ አተያይ / ሶስተኛው አለማቀፍ ቲዎሪ / ለመተንተን ሞክሯል ።

ጋዳፊ በዚህ ጥራዝ ብዙ ርእሰ ጉዳዮችን ነው የመዘዘው ። በመጀመሪያ ክፍል ምርጫን ፣ የተወካዮች ም/ቤትንና ህዝበ ውሳኔን በእጅጉ ይኮንናል ። እንደርሱ እምነት ዴሞክራሲ የህዝቦች ስልጣን እንጂ የጥቂት እንደራሴዎች ሃብት አይደለም ። ህዝብን እንወክላለን ብለው በፓርላማ በሚሰበሰቡ አባላት ዴሞክራሲ እውን ሊሆን አይችልም ምክንያቱም እነሱ ከተመረጡ በኋላ ለራሳቸው ጥቅም ነው የሚንቀሳቀሱት ። በተለይ ፓርላማው በአንድ ፓርቲ የተዋቀረ ከሆነ የአሸናፊ ፓርቲ ፓርላማ እንጂ የህዝብ ፓርላማ መባሉ አግባብ አይደለም ። ጋዳፊ የወቅቱን የእኛ ሀገርን ፓርላማ ቀድሞ ነው የተቸው ማለት ነው ። እውነተኛው ዴሞክራሲ የሚገኘው በቀጥተኛው የህብረተሰብ ተሳትፎ ነው ። እውነተኛ ዴሞክራሲ ተግባራዊ የሚሆነው ብዙሃኑ በህብረት ወጥቶ ህዝባዊ ኮሚቴ እና ታላቅ የመማክርት ጉባኤ ሲዋቀሩ ነው ። ህዝበ ውሳኔም ቢሆን / Referendum / ዴሞክራሲን የማጭበርበሪያ ዘዴ እንደሆነ ጽፎታል ። ‹ አዎ › ወይም ‹ አይ › ብለው እንዲመርጡ የሚገደዱ ዜጎች ነጻ ሃሳባቸውን እንዲገልጹ አይደረግም ። በመሆኑም ይህ አይነቱ አሰራር ጨቋኝና አምባገነናዊ ነው ሊባል የሚገባው ።

ፕሬስንና ሃሳብን በነጻነት መግለጽን አስመልክቶም የግለሰቦችና የቡድኖች ያልተገደበ መብት እንደሆነ ይዘረዝራል « ፕሬስ ማለት ማንኛውም ሰው ራሱንና አስተሳሰቡን የሚገልጽበት ነው ፣ ሌላው ቀርቶ እብደቱን ጭምር ። የዚህ ሰውየ እብደት የሌላ ሰው ወይም ሰዎች እብደት ነው ተብሎ መቆጠር የለበትም ። በመሆኑም በጋዜጦች የሚወጡ አስተያየቶችን የህዝብን ሃሳብ አደርጎ ጥያቄ ማንሳት መሰረተ ቢስ ነው ፣ ምክንያቱም ጋዜጦች ያተሙት የዚያን ሰውየ አስተያየት ነውና »

በሁለተኛው ክፍል ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተዳሰዋል ። እንደ ጋዳፊ ሃሳብ ደመወዝተኞች ለቀጠራቸው ግለሰብ ግዜያዊ ባሪያዎች ናቸው ። መሰረታዊ ፍላጎቶች/ ቤት ፣ ትራንስፖርት ወዘተ / በግለሰቦች ቁጥጥር ስር መዋል የለባቸውም ምክንያቱም ብዝበዛንና ባርነትን ያመጣሉና ። በሶሻሊስት ማህበረሰብ ውስጥ ሰዎች የሚሰሩት በሽርካነት እንጂ ለደመወዝ ብለው አይደለም ። በሌላ ሠው ቤት የሚኖሩ ሰዎች ማለትም ኪራይ የሚከፍሉም ሆነ የማይከፍሉት ነጻነት አላቸው ማለት አይቻልም ። መሬት የማንም ሃብት አይደለም ነገር ግን ማንኛውም ሰው በመሬት ላይ ማንንም ሳይቀጥር የተለያዩ ስራዎችን ማከናወን ይችላል ። የቤት ሰራተኝነት የዘመናዊው ዓለም ባርነት ነው ። እናም የቤት ስራ መከናወን ያለበት በነዋሪዎቹ ነው ።

ሶስተኛው ክፍል ማለትም የሶስተኛው ዓለማቀፍ ቲዎሪ ቤተሰብን ፣ ጎሳን ፣ ብሄርን ፣ ሃገርን ፣ አናሳ ብሄርን ፣ ሙዚቃን ፣ ስፖርትና ሴቶችን ይዳስሣል ። ሌላው ቀርቶ ጥቁር ህዝቦች ወደፊት አለምን / ቀደም ብሎ ቢጫዎች ፣ አሁን ደግሞ ነጮቹ እየገዙ ነው / ይመራሉ ይላል ። ስፖርት ልክ እንደ ጸሎት ግላዊ ጉዳይ መሆኑን ይገነዘባል ። ቦክስ እና ነጻ ትግል ግን የሰው ልጅ ገና ከአረመኔነቱ አለመላቀቁን የሚያሳዩ ድርጊቶች ናቸው ።

ጋዳፊ ቤተሰብ ከመንግስት የበለጠ አስፈላጊ ተቋም እንደሆነ በሚከተለው መልኩ ያምናል  « ቤተሰብ እንደ እጽዋት ነው ። ቅርንጫፍ ፣ ግንድ ፣ ፍሬና ቅጠል ያለው ። እጽዋት የመነቀል ፣ የመድረቅ እና የእሳት አደጋ እንደሚያጋጥማቸው ሁሉ ቤተሰብም ህልውናው በብዙ ነገሮች ይፈተናል ። ያበበ ማህበረሰብ ማለት ግለሰቦች በቤተሰብ ውስጥ ቤተሰቦች ደግሞ በማህበረሰብ ውስጥ ማደግ ሲችሉ ነው ። ቅጠል ለቅርንጫፍ ፣ ቅርንጫፍ ለዛፍ እንዲሉ ግለሰብም በቤተሰብ ውስጥ የጠነከረ ትስሥር አለው ። ግለሰብ ያለ ቤተሰብ ትርጉም የለውም ። የሰው ልጅ እንደዚህ አይነቱን ትስስር ከጣለ ስር የሌለው ሰው ሰራሽ አበባ ነው የሚሆነው »

ጋዳፊ ለጎሳ መራሹ የአፍሪካ ህዝብም ጠቃሚ ስንቅ ያቀበለ ይመስላል ። ማህበራዊ ትስስር ፣ አንድነት ፣ ቅርበትና ፍቅር ከጎሳ ይልቅ በቤተሰብ ይጠነክራል ፤ ከሀገር ይልቅ በጎሳ ይጠነክራል ። ከዓለማቀፍነት ይልቅ በሀገር ይጠነክራል ። ጎሳ ትልቅ ቤተሰብ ነው ... ለጎሳ ትልቁ መሰረት ደም ነው ... ጎሳ አባላቱን የሚከላከለው በመበቀል ነው ። ጎሰኝነት ናሽናሊዝምን ያጠፋል ፤ ምክንያቱም የጎሳ ታማኝነት ከሀገር ታማኝነት የላቀ ነው ። በሀገር ውሰጥ የሚገኙ ጎሳዎች የሚጋጩ ከሆነ ሀገር ችግር ውሰጥ ይወድቃል ። ብሄርተኞች ፍላጎታቸውን በሃይል የሚገልጹ ከሆነና የራሳቸውን ፍላጎት የሚያሰቀድሙ ከሆነ ሰብዓዊነት ላይ አደጋ ይፈጠራል በማለት ስጋቱን ክፍላጎቱ ጋር አዛምዶ መርሁ ላይ አስፍሮታል ።

የአንድ ሀገር ህዝቦች የሚበየኑት በቦታው ላይ በመፈጠራቸው ብቻ አይደለም ። ይህ መሰረታዊ ነገር ሊሆን ይችላል ። ከዚህ በተጨማሪ ግን ለረጅም ግዜ በአንድ ላይ በመኖር የጋራ ታሪክ ፣ ቅርስ እና ተመሳሳይ እጣ ፈንታ ሲኖራቸው ነው ። ህዝቦች ከደም ትስስር ይልቅ ሀገራዊ አንድነትና የኔነትን በጋራ ይዛመዳሉ ።

ሴቶች ከወንዶች እኩል አይደሉም በሚባለው ብሂል ጋዳፊ አይስማማም ። ሴቶች እኩል መስለው የማይታዩበትንም ሳይንሳዊ ምክንያት በዝርዝር አስቀምጧል ። ሴቶች አንስታይ ወንዶች ተባእታይ ናቸው ። ባለሙያዎች እንዳረጋገጡት ሴቶች በየወሩ ደም ሲያዩ ወንዶች አይኖራቸውም ። ሴት ደም ካላየች ነፍሰጡር ናት ። ነፍሰ ጡር ስትሆን ለአመት ያህል ንቁ ተሳታፊ አትሆንም ። ልጅ ስትወልድ ወይም ሲያስወርዳት ደግሞ በ ፒዩፐሪየም / Puerperium / ትሰቃያለች ። ወንድ ይህ ሁሉ ስቃይ አይደርስበትም ። ከወለደችም በኋላ ለሁለት አመታት ታጠባለች ። ጡት ማጥባት ማለት ሴት ከልጅዋ የማትለያይበት በመሆኑ አሁንም ሌሎች እንቅስቃሴዎቿ ይቀንሳል ። በመሆኑም ሌላን ሰው ለመርዳት ቀጥተኛ ሃላፊነት መውሰድ በእሷ ላይ ይወድቃል። ያለ እርሷ ብርቱ ድጋፍ ያ ፍጡር ይሞታል ። ወንድ በሌላ በኩል አያረግዝም ፣ አያጠባም ::

ጋዳፊ በአረንጓዴው መጽሐፍ ታላላቅ ሀሳቦችን አንስቷል ። በክፍል አንድ ስልጣን የህዝብ መሆኑን እንመለከታለን ። ግለሰቦች ሊያብዱ ይችላሉ ይህ ማለት ግን ማህበረሰቡ አብዷል ማለት አይደለም በሚለው ነጥብ ዙሪያ ፕሬስ ሃሳብን መግለጫ ነጻ መሳሪያ መሆኑ ተሰምሮበታል ። በሁለተኛው ክፍል ለኢኮኖሚው ችግር መፍትሄው ሶሻሊዝም መሆኑ ተቀምጧል - በእያንዳንዱ ቤት ወስጥ የሚኖር ዜጋ የቤቱ ባለቤት እንጂ ጭሰኛ መሆን የለበትም የሚል የሚደላ አቋም ይታያል ። የአስቂኝም አስደናቂም ስብስብ በሆነው ሶስተኛ ክፍልም ሴት ከወንድ ታንሳለች ማለት የተፈጥሮ ህግን መካድ ነው የሚል ጠንካራ አቋም ይገኛል ።

ደራሲው ጋዳፊ ከፖለቲከኛው ጋዳፊ ጋር ተጣጥሞ ቢዘልቅ መልካም ነበር ። በተለይ በዙሪያህ የተኮለኮሉ ሰዎች / የተለያዩ ፍላጎት ያላቸው / የስብእና አምልኮ እየገነቡልህ ሲሄዱ ዝም ካልክ መቀበሪያህ እየተማሰ መሆኑ ማወቅ ይገባል ። ። ጋዳፊ መርሁ እንዲዘመር እንጂ እንዲሰራበት ለማድረግ ያልቻለበት አንደኛው ምክንያትም ይሄው ነው ። ጹሑፍህን ደጋግመህ በፍቅር ታነበዋለህ እንጂ ደፍረህ አርትኦት አታደርገውም ። በዚያ ላይ ፍልስፍናን ለማሰብና ለመራቀቅ እንጂ ሆኖ ለመኖር ይከብዳል ።




No comments:

Post a Comment