Saturday, September 8, 2018

አርበኞች ግንቦት 7 እንኳን ደህና መጣህ




ወያኔ በግዳጅ በጫነው ፖለቲካዊ አደረጃጀት ሳቢያ ህዝባቸውን ለመታደግ ሲሉ ብሄር ተኮር አደረጃጀት ፈጥረው የተንቀሳቀሱ ድርጅቶችን ማክበር ተገቢ ነው ፣ በተለይም የእውነት ለታደጉትና እየታደጉ ለሚገኙት ፡፡ ሁሉን በአንዲት ታላቅ ሀገር ስም ፣ ሁሉን በኢትዮጵያዊነት ጥላ ደምረን እንሰራለን የሚሉ ድርጅቶች ሲገኙ ደግሞ ክብራችን ሌላ ጋት ይጨምራል ፡፡

አስጊ ጫፍ ላይ የተንጠለጠለችውን ኢትዮጵያ ወደ መሃል ስቦ ሚዛኗንና ሚዛናዊነትን ለማስጠበቅ እሰራለሁ የሚለውን አርበኞች ግንቦት 7ን ማበረታታትና መደገፍ የውዴታ ግዴታ ሆኗል ፡፡ ለምን ? ነባራዊው የፖለቲካ ሁኔታ የሚነግረን ጥቂት የአንድነት ወይም ኢትዮጵያዊያን ሃይሎች በየትየለሌ ብሄር ዘመም ድርጅቶች ተውጠው መገኘታቸውን ነው ፡፡ ብሄር ተኮር ድርጅቶች እድል አግኝተው ምርጫ ቢያሸንፉ እንኳ በኢትዮጵያ ላይ የሚኖራቸው የመጨረሻ ግብ ግልፅ አይደለም ፡፡ ኢትዮጵያ እንዳትፈራርስ ዋስትና የሚሰጥ ጠንካራ የፖለቲካ ፕሮግራምም የላቸውም ፡፡

ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያዊነትን እያዜመ የሚገኘው < አዲሱ ኢህአዴግ > እንኳ የአቅጣጫና የርዕዮት መስመሩን አላሻሻለም ፡፡ አራቱ እህት ድርጅቶች ሜጀር ተግባራቸውም ሆነ ቀጣይ ግባቸው ብሄር ተኮር ድልድይ መገንባት ይሆናል ፡፡ ኢትዮጵያዊነትን የሚጠቃቅሱት በማይነር አስተምህሮት ነው ፡፡ በዚህ ስሌት ኢትዮጵያነት እንደምን ገዝፎና አሸንፎ ሊወጣ እንደሚችል ግልፅ አይደለም ፡፡ ከአቅጣጭ አንፃርም ኢህአዴግ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መንገዱን እንደማይለቅ ዶ/ር አብይ በቅርቡ መናገራቸው ይታወሳል ፡፡ በልምድ እንዳየነው ደግሞ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ዘብነት ወይም ጥብቅና ለብሄሮች እንጂ ለኢትዮጵያዊ ዜግነት አይደለም ፡፡

በብሄር ብቻ ሳይሆን በሃሳብ እና በአመክንዮ የሚወዳደሩ ጠንካራና ብስል ድርጅቶች ያስፈልጉናል ፡፡ በብሄርም ሆነ በዜግነት ማሰብ የወገንተኝነት መዳረሻ አለው ይባላል ፤ ትክክል ነው ፡፡ ፍትሃዊ ትክክለኝነት የሚመነጨው ግን የአግላይነት ድንበር ሲነሳ ነው ፡፡ የብሄር እሳቤ ትልቁ በሽታ ቀስ በቀስ ደራሲ ጆርጅ ኦርዌል ወደፈጠረው የአሳማዋች ፍልስፍና የማዳረሱ ክፋት ነው ፡፡ እንደሚታወቀው በአኒማል ፋርም አብዮት ያነሱት አሳማዋች የመጀመሪያ መፈክራቸው ውብ ነበር ፡፡ < ሁሉም እንስሣት እኩል ናቸው > እያሉ ነበር የሚዘምሩት ፣ ለውጡን በሙሉ ልብ ለመደገፍ የቆሙት ፡፡ እየዋለ እያደር ግን ብሄራዊ መፈክራቸው ወይም ህገ መንግስታቸው  < እኛ የተሻልን ነን > በሚሉ አሳማዋች ተቀይሮ ALL ANIMALS ARE EQUAL BUT SOME ANIMALS ARE MORE EQUAL THAN OTHERS የሚለውን ዘረኛ አንቀፅ ተሸካሚ ሆነዋል ፡፡ ሃሳቡን የማይደግፉ ሁሉ ትምክህተኛ እየተባሉ ተዘልፈዋል ፣ እንዲሸማቀቁ ተደርጓል ፣ ከመኖሪያ ቀያቸውም ተፈናቅለዋል ፡፡ የብሄር እሳቤ ትልቁ በሽታ < እኔ ከሌሎች የተሻልኩ ነኝ > የሚል ስስታም ተቀጥላ ስለሚያመነጭ ለዘወትር ብጥብጥና ግጭት መንሳኤ መሆኑ ነው ፡፡

ይህን በመሰሉ 40 እና 50 ድርጅቶች ተውጦ ፖለቲካን መስራት ደግሞ ያሰጋል ፡፡ መቼም ቢሆን ስነልቦናዊ መረጋጋትን ፈጥሮ በኢኮኖሚውም ሆነ ማህበራዊ ሰልፍ ወስጥ ራስን ለማስገባት ያስቸግራል ፡፡ የዳር ተመልካቹን ፣ የምናገባኝ አቀንቃኙን ፣ ባለግዜዎቹ  ይዘውሩት ባዩን ያበራክታል ፡፡ ሀገር ሰልላ እንድትሞትም አሉታዊ ሚና ይጫወታል ፡፡ ለዚህም ነው ፖለቲካው በቋንቋና ብሄር ብቻ ሳይሆን በሃሳብ ይሞገት የሚባለው ፡፡ ሃገር የሚያሳድገውና የሚያስከብረው ለሁሉም የሚጠቅም የዳበረ ሃገራዊ ሃሳብ ሲመነጭ ነው ፡፡ ሃሳብ ሳይገደብ ሊፈስና ሊመነጭ የሚችለው ደግሞ አጥር ሲፈራርስ ነው ፡፡ ከጠባብና የሚያፍን ክፍል ወጥቶ ማለቂያ በሌለው መስክ ላይ እንደልብ መሯሯጥ ሲቻል ፡፡

ህዝቡ በቅርቡ የተገኘውን ለውጥ የደገፈው ኢትዮጵያዊነት ከፍ ብሎ ስለተዘመረለት ነው ፡፡ በኢትዮጵያዊነት ውስጥ አንድነት ፣ ሰላምና ፍቅርን አበለፅጋለሁ ብሎ ስላሰበ ነው ፡፡ ይህ ከፍታ ደረጃውን ጠብቆ ይጓዝ ዘንድ እንደምሶሶ ጠልቀው የተቸነከሩ ድርጅቶች እዚህና እዚያ መታየት ይኖርባቸዋል ፡፡

ተወደደም ተጠላ ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ናት ፡፡ የሚመጥናት ትልቅነቷን ጠብቆ ከተቻለም አልቆ የሚጓዝ ድርጅት ነው ፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ዳግም ለማንገስ ተስፋ ከተጣለባቸው ድርጅቶች አንዱ አርበኞች ግንቦት 7 ነው ፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ስለ ኢትዮጵያዊነት ሆ ! ብለው ቢዘምሩ ሳያፍርና ሳይሸማቀቅ የግጥምና ዜማ ድርሰት ለማበርከት መዘጋጀት ስለሚችል ነው ፡፡ ሌላ ጠንካራ ህብረ ብሄራዊ ድርጅት እንደ አማራጭ እስኪወጣ ድረስም ግንቦት 7 እንዳይደናቀፍ አጥርና ጋሻ ሆኖ መመከት ያስፈልጋል ፡፡ ይህ ድርጅት በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወስኖ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ትልቅ ትርጉም አለው ፡፡ ከመሰል ድርጅቶች ጋር ህብረት ፈጥሮ ስለሚንቀሳቀስም የተፈጠረው ኢትዮጵያዊነት እሳቤ እንዲቀጣጠልም ይረዳል ፡፡ ቢያንስ በዘውገኞች የተከበቡ ዜጎች ተስፋ እንዳይቆርጡ ተስፋ እና ዋስትና ይፈጥራል ፡፡ አርበኞች ግንቦት 7 በትክክለኛው ግዜና ቦታ የተገኘ ድርጅት ስለሆነ እንኳን ደህና መጣህ ሊባል ይገባል ፡፡

Saturday, August 18, 2018

በግማሽ ሜዳ መጫወት ...



ሶሎ ጎል ይሉታል ፈረንጆቹ ፡፡ አንድ ተጫዋች በርካታ ባላጋራዎቹን አልፎ ጎል ሲያስቆጥር ፡፡ በጥበብ ፣ አካላዊ ብቃት ፣ ብልጠትና ድፍረት መሞላትን ስለሚጠይቅ ሁሉም ተጫዎቾች ሊያከናውኑት አይችሉም ፡፡ እናም ለግብ አግቢው ከወንበር ተነስቶ የረዘመ ጭብጨባና ክብር መስጠት ግድ ይላል ፡፡

ልክ እንደ ሶሎ < ዋው > የሚያስብል ሌላ ጥበብም እለ በእግር ኳሱ ዘንድ ፡፡ ከግማሽ ሜዳ ኳስን በትክክል መትሮ ጎል ማስቆጠር ፡፡ ይህንም ሲያደርጉ ያየናቸው ጥቂት የዓለማችን ተጫዋቾች ናቸው ፡፡ ጁዋን ካርሎስ ፣ ናቢ ፍቅርና ዋይኒ ሩኒን እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል ፡፡ ኤቨርተንና ዌስትሃም ሲጫወቱ ዋይኒ ሩኒ ያደረገው ምንድነው ? ከክልሉ ወጥቶ ኳሷን ወደ መሃል ያወጣትን በረኛ ሁኔታ በመገንዘቡ ኳሷ ስትደርሰው ቀጥታ ወደፊት አጎናት ፡፡ ዳኛው የተለጋውን ኳስ እንዳይነካ አፈገፈገ ... ሁለት ተጫዋቾች ባለ በሌለ ሃይላቸው ወደላይ ለቴስታ ዘለሉ ... የመጨረሻው ተከላካይ ከሩቅ የተለጋ ኳስ ከሚቆጠርብን በእጄ ለኤሪጎሬ ባስቀራት ይሻላል ብሎ ወደ ላይ ዘለለ – አላገኛትም ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግብ ጠባቂው ወደጎል ሮጦ በማያውቀው ፍጥነት እየተፈተለከ ነበር ፡፡ ልብ አንጠልጣይ ድራማ ካየን በኋላ ኳሷ ከመረቡ ጋ ተሳሳመች ፡፡

ዶ/ር አብይ በእነዚህ አብዶኛ ተጫዎቾች ይመሰላሉ ፡፡ ከግማሽ ሜዳ የጠለዟቸው የፖለቲካ ኳሶች ጅቡቲ ፣ ሱዳን ፣ ግብፅ ፣ ሳዑዲ ፣ ኡጋንዳና ኤርትራ አርፈው ድል አስቆጥረዋል ፡፡ በአንድ በኩል የዲፕሎማሲውን ግንኙነት ሲያጠናክሩ በሌላ በኩል ማንም ሀሳብ ውስጥ ያልነበሩ ዜጎችን ከእስር አስፈትተዋል ፡፡ ወደክልሎች በመጓዝ ጥበብ ፣ ብልጠትና ድፍረት የተሞላበት ሃገራዊ ምክክር አድርገዋል ፡፡ በጎሳና ዘረኝነት ክፋት ተሰነጣጥቆ ሊበተን የነበረውን ኢትዮጵያዊ ትሪ ጠግነዋል ፡፡ የተራራቁ ሰዋች በአንድነት ተሰባስበው ባዛው ትሪ ላይ ማዕድ እንዲቀርቡ ፣ የጋራ ፀሎታቸውም ፍቅር ፣ ሰላምና ኢትዮጵያዊ ድማሬ እንዲሆን መንገድ አሳይተዋል ፡፡ ርቆ የተቀበረው ኢትዮጵያዊነት ክብሩ ተመልሶ ከባንዲራ በላይ እንዲውለበለብ አድርገዋል ፡፡

ዶ/ር አብይ በአጭር ግዜ ውስጥ ያስመዘገቧቸው ድሎች አመርቂና ተስፋ ሰጪ ቢሆኑም እየተጫወቱ የሚገኙት በግማሽ ሜዳ ነው ፡፡ ከትልቁ ጥያቄ አንደኛው ስንቱን ህዝባዊ ጥያቄ ከግማሽ ሜዳ እየመተሩ ማስገባት ይችላሉ ? የሚለው ነው ፡፡ ከትልቁ ጥያቄ ሁለተኛው ስንቱን እግር ሰባሪ ተከላካይ በአብዶ እየሸወዱ ውጤት ያስመዘግባሉ የሚለው ነው ፡፡

ዶ/ር አብይ ብዙ ተከላካዮችን አብዶ ሰርተው አልፈው ጎል የሚያስቆጥሩት ኢትዮጵያዊነትን ከዳር እስከ ዳር ለማሳደግ ነው ፡፡ ይሁንና ጥቂትም ሳይቆይ ሲዳማው ፣ አገው ፣ ጉራጌው በኔ ልክ የተሰፋ ክልል ይገባኛል ብሎ ጥብቆ ሲናፍቅ ታገኘዋለህ ፡፡ ዶ/ር አብይ ብዙ ተከላካዮችን አብዶ ሰርተው አልፈው ጎል የሚያስቆጥሩት  እንደ < ገነት > የምንናፍቀውን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እናይ ዘንድ ጥርጊያ መንገዱን ለመገንባት ነው ፡፡ ይሁን እንጂ ለድሃ ዳቦ እንጂ ነፃ ስርዓት አያስፈልገውም የሚሉ አምባገነኖች በተሰነጣጠቀው መንገዳችን ላይ የሚፈነዳዳ ፈንጂ ከመቅበር ሊቆጠቡ አልቻሉም ፡፡ ዶ/ር አብይ ከመሃል ሜዳ ለግተው ጎል የሚያስቆጥሩት የማሸነፍ ረሃብን ለማስታገስና ሮል ሞዴሎችን ለመቅረፅ ነው ፡፡ ይሁን እንጂ ማጥቃትንም ሆነ መከላከል እርግፍ አድርገው ትተው ጨዋታ የሚያቆሙ ብዙሃንን ታያለህ ፡፡ በሌላ አነጋገር ጨዋታውን አቋርጠው በፎርፌ ማሸነፋችን ይታወጅልን የሚሉ ፡፡ እነዚህ ወገኖች በጥቂት ወይም ሚዛን በማያነሳ ምክንያት ዱላ ፣ ገጀራና ክብሪት አንስተው ቀጣዩን ጥፋት ለማከናወን የማያመነቱ ሆነዋል ፡፡ ነገር ቆስቋሾች ፣ ገዳዳ አክቲቪስቶች ፣ በቀልተኛ ፖለቲከኞች ጃስ ባሏቸው ቁጥር ለምን ? እና እንዴትን ? ሳያነሱ ዘለው ንጹሃንን የሚናከሱ ወገኖቻችን እየበዙ መጥተዋል ፡፡ እነዚህን ሁሉ መግራት ከባድ ነው ፡፡ በአንድ ቀን ምክክርና የእርቅ ጉባኤም አጀንዳውን መዝጋት አይቻልም ፡፡

ጠ/ሚ/ሩ በየክልሉ በዘር ፣ ቋንቋና ሃይማኖት የሚለኮሱ ግጭቶችን ለማብረድና ለማስታረቅ የሚሯሯጡ ከሆነ ሌላውን አንገብጋቢ ስራ መስራት አይችሉም ፡፡ የፖለቲካ መዋቅሩም ሆነ ህዝቡ ጥሩ ጎል አግቢ ስለሆኑ እሳቸውን ብቻ የሚጠብቅ ከሆነ ሽምግልና እንጂ መንግስታዊ አሰራር ውሃ ይበላዋል ፡፡ ለዚያም ነው ጠ/ሚ/ሩ በግማሽ ሳይሆን በሙሉ ሜዳ መጫወት የሚችሉበት ቋሚ አሰራር መፈጠር አለበት የሚባለው ፡፡ ለዚያም ነው ከቅርብም ሆነ ከሩቅ ለግተው ግብ የሚያስቆጥሩ ኮኮቦችን ማፍራት ይገባቸዋል የምለው ፡፡

ርግጥ ነው በሀገራችን ያንዣበበውን ስጋት ለመቅረፍ ክፋትንና ድህነትን ተጭኖና አጥቅቶ በመጫወት ተደጋጋሚ ግቦችን ማስቆጠር ያስፈልጋል ፡፡ አለበለዚያ አቻ መውጣትና መሸነፍም ያጋጥማል ፡፡ አቻ መውጣት ክፋትንና ድህነትን አቅፎ መኖር ነው ፡፡ ወንድም ጋሼ ... ጌታ መሳይ... እያልከው ፡፡ ከተሸነፍክ ያለውድ በግድ < ጅቦች ለዘላለም ይኑሩ ! > የሚል መፈክር ተሸክመህ ትዘልቃለህ ፡፡ እነሱ የሚጥሉትን ቅንጥብጣቢ አያሳጣኝ እያልክ ፡፡ የሰላምና የፍቅርን ኳስ በማራኪ አጨዋወት እስከተቃራኒው ክልል ደርሶ ያማረ ጎል ማስገባት ያስፈልጋል ፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ለዋናው አጥቂ ኳስ አመቻችተው የሚሰጡ ደጀኖች ፣ አጥቂው ሲደክም ጎል ማስቆጠር የሚችሉ ቁርጠኛና ጥበበኛ ተጫዋቾች መሰለፋቸው መረጋገጥ ይኖርበታል ፡፡

በየክልሉ የሚለኮሱ ጎሳዊ ግጭቶችን ለመቀነስና ለመከላከል የተጠናከረ ትምህርትና ስልጠና ግድ ነው ፡፡ ለ27 ዓመታት የዘውጌ ስርዓት በማበቡና ብሄርተኝነት የተሻለ አማራጭ ተደርጎ በመሰበኩ ኢትዮጵያዊነትን በቀላሉ ማስረፅ ሳይከብድ አይቀርም ፡፡ ይህን ስራ የሚሰሩ የሲቪክ ተቋማትን ማስፋፋት ይጠይቅ ይሆናል ፡፡ ተመሳሳይ የፖለቲካ መስመር የሚከተሉ ድርጅቶችንና ቲንክታንኮችን Add እና Tag ማድረግ ግድ ይመስላል ። በውስጥ አሰራር ደግሞ ለንቋሳ አመራሮችን እየሻሩ ፣ ጠንካሮቹ ንቃተ ህሊናን ለማዳበር የሚያስችሉ የምክክር መድረኮችን ረጅም የስራ አካልና ግብ አድርገው እንዲተጉ ማሳሳብ ይጠበቃል ፡፡

ዘረኝነትና ጎሰኝነት አይደለም በአፍሪካ በአውሮፓ መሞት አልቻለም ፡፡ ጉዳት እንዳያደርስ ሸብቦ የያዘው ግን ጠንካራ ህጋቸው ነው ፡፡ ዶ/ር አብይ የፍቅርና ይቅርባይነትን ሎጎ ከፍ በማድረግ አስተዳደራቸው እንዳይንገጫገጭ ማድረግ ቢችሉ ሸጋ ነበር – ድብቁና ውስብስቡ ፖለቲካ ግን በዚህ ቀመር የሚሰራበት አግባብ በእጅጉ የሰለሰለ ነው ፡፡ አሸባሪ ፖለቲከኞችን ፣ የዘረኝነት ፈንጂ ቀማሚዋችን ፣ ብሄርን ከብሄር ለማጋጨት ሃሳብ ፣ ክብሪትና ጥይት የሚያቀብሉ የደም ነጋዴዋችን በአጠቃላይ ህገወጦችን መስመር የሚያሲዙበት ህጋዊ ማእቀፍ ያስፈልጋቸዋል ፡፡

Thursday, August 9, 2018

የኦሕዴድ የነገ ፈተና ...




ስልጣኑ ያለው ኦህዴድ ውስጥ ነው ፤ ኦሮሚያ ልብ ውስጥ ግን ኦነግ ከፍ ብሏል ፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ለዶ/ር አብይ አህመድ ፣ ለአቶ ለማ መገርሳና ለቲም ለማ ከፍተኛ ፍቅርና አክብሮት አለው ፡፡ ማሳያዎቹ ብዙ ናቸው ፡፡ ለምሳሌ በርካታ የሜኔሶታ ነዋሪ የሆኑ ኦሮሞዋች ሁለቱን መሪዎች በላቀ ደስታና የጀግንነት ስሜት ነው የተቀበሏቸው ፡፡ ነዋሪው የወደደው ግን ግለሰቦቹን ወይም የቲም ለማ ቡድንን እንጂ ባልሰልጣናቱ የቆሙበትን ድርጅት ጭምር አይደለም ፡፡ ድርጅታቸው የሰራውን ተግባር ዋጋ ለመስጠት አልፈለገም ፡፡ የዚህ አይነተኛ መገለጫ ደግሞ ከኢህዴድ ባንዲራ ይልቅ የኦነግ መለያ አዳራሹን ማጥለቅለቁ ነው ፡፡

በወቅቱ ባለስልጣናቱ ምን ያህል እንደተገረሙ ወይም ምን እያሰቡ እንደሆነ ማወቅ ቢቻል እንዴት መልካም ነበር ብዬ አስቤ ነበር ፡፡ ግን ስሜታቸውን ደብቀው ወይም ተቆጣጥረው መውጣት ችለዋል ፡፡ አንዳንዶች ይህ ጉዳይ ሜኔሶታ የተፈጸመው ኦነግ ለበርካታ አመታት የፓለቲካ ድልድዩን በእያንዳንዱ ሰው አካል ላይ መገንባት ስለቻለ ነው ይሉ ይሆናል ፡፡ አሁን በቅርቡ እንኳ ኦ ኤም ኤን አዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ባዘጋጀው ዝግጅትም ላይም የኦነግ ባንዲራ ግዘፍ ነስቶ ታይቷል ፡፡ አዲስ አበባና አካባቢዋ ደግሞ ኦህዴድ እንጂ ኦነግ የፖለቲካ ድልድይ ለመገንባት እድል አልነበረውም ፡፡ ከለውጡ በፊትና በኋላም ቢሆን በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች በተካሄዱ ሰልፎች ላይ የኦነግ ምልክት በዋዛ የሚታይ አልነበረም ፡፡ ታሪካዊና ገራሚ አባባሎችን እንዲሁም ሳቅ ጫሪ መፈክሮችን ሲያውለበልብ ያየነው ህዝብ < ኦህዴድ ደማሪ ድርጅታችን ነው > ለማለት ባይደፍር እንኳ < እናመሰግለን > የሚል ባነር ከፍ ለማድረግ እጁን ምን እንደያዘው አጠያያቂ ነው ፡፡

ነገሩ ፓራዶክስ ይመስላል ፡፡ ቄሮና የፖለቲካ ድርጅቶች ከመላው ህዝብ ጋር በመተባበር ለውጡን አፋጥነውት ይሆናል ፡፡ የትግሉ መስመር በተለይ በኢትዮጵያዊነት ሃዲድ ላይ ዳግም እንዲጓዝ ያደረጉት ግን አብይና ለማ ናቸው ፡፡ የአነዚህን ሰዎች የላቀ ጥረት ዋጋ ሳይሰጡ መጓዝ ይከብዳል _ ኢትዮጵያዊነትን ቸለል ካላሉት በስተቀር ፡፡ የአንደበት ወዳጁ ህልቆ መሳፍርት የለውም ፣ በተግባር ልብ ውስጥ ያለው ማህተም ግን ንባቡ ሌላ እየመሰለ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንደዋዛ እንድንጠይቅ እያደረገ ነው ፡፡ ህዝቡ የምንወዳችሁ እኛ የያዝነውንም ስትወዱልን ነው እያለ ነው ? የድልድይ ሚናነት ስለተጫወታችሁ እናመሰግናለን እኛ ግን ከዚህኛው ወገን ነን እያለ ነው ? ወይስ የቲም ለማ ቡድን ነገ ከኦነግ ጋር እንዲቀላቀል በንግር / Foreshadowing / ቴክኒከ እያመላከተ ይሆን ?

ዶ/ር አብይ ዋና አላማዬ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ነው ብለዋል ፡፡ መሬት ላይ የሚታየውን እውነት ተከትለን እንበይን ወይም እንገምት ካልን ማለትም ሁኔታዎች በዚሁ መልክ ከተጓዙ በኦሮሚያ የቀጣዩ ምርጫ አሸናፊ ኦህዴድ መሆኑ ያጠራጥራል / ምንም እንኳ የቲም ለማ ቡድን አባላት ወንበር ማግኘት ባይከብዳቸውም / ፡፡ ታዲያ የቡድኑ ልፋትና ጥረት ምንድነው ? ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ? ጥሩ ነው ፡፡ ግን ሽግግሩ ከኢትዮጵያዊነት ቆዳ የተሰራ ጠንካራ ኦህዴድን ለመገንባት የሚያስችል ነው ? ያጠራጥራል ፡፡ ነው ወይስ አንዳንዶች በግልፅ እንደሚሰጉት ኦህዴድ ቀስ በቀስ በህዝባዊ ማእበል እየተሸረሸረና እየተገፋ በኦነግ ሼል ውስጥ ይዋጣል ?

አንድን ሰው ከወደድክ ከነምናምኑ ነው ይባላል ፡፡ በተራ የሎጂክ ትንታኔ መሰረት ፣ ለለውጡ ትልቅ ሚና የተጫወተው ኦህዴድ እውቅና ተነፍጎት የተወሰኑ መሪዎቹ ብቻ የሚወደሱ ከሆነ ድርጅቱ የአደጋ ቀጠና ውስጥ ይገኛል ማለት ነው ፡፡ የድርጅቱ አደጋ ውስጥ መውደቅ ደግሞ የራሱ ጉዳይ ተብሎ የሚታለፍ አይሆንም ፡፡ ምክንያቱም ይህ ድርጅት ለግዜውም ቢሆን አትዮጵያዊነትን በውክልና የተሸከመ ነውና ፡፡ በተራ የሎጂክ ትንታኔ እሳቤ ኦህዴድ < ባለ ተራው > መንግስትም ጭምር ነው ፡፡ እና እንዴትስ ቢያደርጉ ነው ግለሰባዊ ዝናን ተሻግረው ፖለቲካዊ / ድርጅታዊ አሸናፊነትን የሚቀዳጁት ? ነገሩ ቀላል ይምሰል እንጂ የመሆን _ አለመሆን ጥያቄ አለበት ፡፡ የቀድሞው መሪ እንዳሉት ኦህዴድ ሲፋቅ ኦነግ ይሆናል ወይስ ኦህዴድ ሲፋቅ ለመላው ህዝብ አንድነት ይበጃል ?

የኦህዴድ የነገ ፈተና በፍጹም ቀላል አይሆንም ፡፡ ሳይንሳዊ ድጋፍም የሚፈልግ ጭምር ፡፡


Friday, March 30, 2018

የደበበ ሰይፉ የ ‹ ብርሃን ፍቅር › ምስጢር ምንድነው ?



የታላቁ ገጣሚ ደበበ ሰይፉ የግጥም መጽሐፍ ‹ የብርሃን ፍቅር › ይሰኛል ። በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት አማካኝነት በ1980 ዓ.ም ለህትመት የበቃ ቢሆንም ዛሬም እንደ አዲስ ቢነበብ የማይጎረብጥ ይልቁንም በተክለቁመናው የሚመስጥ ስራ ነው ። ማለትም የዜማው ፣ የቃላት አጠቃቀሙ ፣ መልእክቱ ፣ የቤት አመታቱ እና የስንኝ አወራረዱ የአንባቢን ቀልብ ይስባል ።

አንባቢያንና የዘርፉ ባለሙያዎችም ተክለቁመናውን መሰረት በማድረግ ያሳደረባቸውን ስሜት በአስተያየትና በሂስ መልክ ሲጽፉ ኖረዋል ። የማያረጅ ወይም ዘመን ተሻጋሪ ስራ ነውና ነገም ብዙ እንደሚባልለት አያጠራጥርም ።

ደበበ የመጽሐፉን ስያሜ ለምን « የብርሃን ፍቅር » እንዳለው ግን ምንም የተባለ ነገር የለም ። ምንም ያልተባለው ሚዛን የሚደፋ ቁም ነገር ስለጠፋ አይደለም ። እንደሚመስለኝ ትችቶቹ ከተክለቁመናው ባሻገር ያለውን ገጽታ ማየት ባለመቻላቸው ነው ። ደበበ እንደ ብዙ ገጣሚዎች አንደኛውን ትልቅ ወይም ገዢ ሃሳብ ያለው ግጥም አንስቶ ለመጽሐፍ ርዕስነት አላደረገም ፤ በውስጡ ‹ የብርሃን ፍቅር › የሚል ግጥም የለምና ። የመጽሐፉን አጠቃላይ አንድምታ በመለካትም መዞ ያወጣው ነው ለማለት በቂ አይደለም ። ይልቁንም ብርሃናዊ ሚስጢራትን በመስቀለኛ ሃሳቦች እንድንመረምራቸው የፈለገ ነው የሚመስለው ፤ ማለትም ርዕሰ ጉዳዩን ከቀጥታ እይታ ፣ ከተምሳሌት ፣ ከአሊጎሪ አውድና ከመሳሰሉት ፈትሸን እንድናይ ከተቻለም የተገለጸውን ብርሃን እንድንሞቅ ።

ደበበ በስሜት ብቻ ሳይሆን በእውቀትም የሚጽፍ ባለቅኔ በመሆኑ ይህንን አያስብም ብሎ መከራከር አይቻልም ። ጸሐፊ ተውኔትነቱና ተመራማሪነቱም ይህን ሃሳብ ለመደገፍ እገዛ ያደርጋሉ ። ለምሳሌ ያህል ገጸባህሪ ፣ ሴራ ፣ መቼት እና ቃለ - ተውኔት የተባሉ ስነጽሑፋዊ ቃላትን በመፍጠር ሙያዊ እገዛ አድርጓል ።

አጋጣሚ ሆኖ እነዚህ የአማርኛ ፍቺ ያገኙ ሙያዊ ቃላት ይጠቀሱለታል እንጂ በግጥሞቹ ውስጥም በርካታ ያልተባለላቸው ስልቶች የሚገኙ ይመስለኛል ። አንደኛው ቃላትን በሚያዝናና መልኩ ደቅሎ መልእክትን የማስተላለፍ ጥበቡ ነው ።

ለምሳሌ ያህል ‹ ልጀቱ የዘመነችቱ › በተሰኘው ግጥሙ ውስጥ ዘማኒዋ ሱሪዋን - ሱርት ፣ ጫማዋን - ጭምት ፣ ቀበቶዋን - ቅብትት ፣ ጃኬቷን - ጅክት ነው የምታደርገው ። እነዚህ ከስም ውስጥ የተደቀሉ መገለጫዋች የገጣሚውን ምናበ ሰፊነት ያስረዳሉ - አንድም ቋንቋን ከመፍጠር አንድም ምስል አከሳሰትን ከማጉላት ።

እንደ እኔ እምነት የደበበ ሰይፉን ስራዎች በጥልቀት የመረመረ ባለሙያ አንድ ተጨማሪ የግጥም አይነት መታዘቡ አይቀርም ። ከወል ፣ ሰንጎ መገን ፣ ቡሄ በሉ ፣ ሆያሆዬ እና ከመሳሰሉት ውጪ ማለቴ ነው ። ደበበ ልክ እንደ ፀጋዬ ገ/መድህን የራሱ ቀለማት ፣ አወቃቀርና ምት የሚጠቀም ባለቅኔ ይመስለኛል ። በተለይ ከግጥም አወራረዱ አንጻር የአንድ ቃል ዜማ / ሽግግር / ወይም የአንድ ቃል መድፊያን በሚጥም መልኩ በብቸኝነት ተጠቃሚ ነው ።

ሰማይና ምድር ፣ ልጅነት ፣ በትን ያሻራህን ዘር ፣ ያቺን ሟች ቀን የተሰኙ ግጥሞች የዚህ አባባል ማሳያ ናቸው ። በ ‹ ሰማይና ምድር › ውስጥ

በጀርባዪ ተንጋልዬ
አውዬ
በቅጽበት የፈተልኩትን ለብሼ
ሞቆኝ
በእኔው አለም ነግሼ
ደልቶኝ
ከፅድቁ ገበታ ቀምሼ
ጣፍጦኝ
እያለ ይወርዳል ።
አውዬ
ሞቆኝ
ደልቶኝ
ጣፍጦኝ ... የሚሉ ነጠላ ቃላት ያነከሱ ይመስላሉ እንጂ ያለክራንች ነው የቆሙት - ለዛውም ጠብቀው ። በ ‹ ያቺን ሟች ቀን › ውስጥም እንዲሁ ብቻቸውን ቁጭ ያሉት ትብነን ! ... ትምከን ! ... የሚሉ ቃላት ርግማናዊ ግዝፈታቸው ከምላሰ ጥቁር የሰፈር ሽማግሌዎች ወይም መጋረጃ ካገዘፋቸው ታዋቂ ጠንቋዮች የላቀ ነው ።

ይህ ሃይለኛ የአወራረድ ስልት በ ‹ ደበበ ቤት › ተይዞ መጠናት ያለበት ይመስለኛል ። ደበበ እንግዲህ እንዲህ ከምናውቀው በላይ ብዙ ነው ። የብርሃን ፍቅር ሚስጢርነትም ሰፊ ፍቺ የሰነቀ ነው ። በመድብሉ ውስጥ 49 ግጥሞች ተካተዋል ። ከእነዚህ ውስጥ 24 ግጥሞች ብርሃንን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያነሳሉ ። 15 የሚደርሱ ግጥሞቹ ብርሃንን የሚያወሱት ፀሃይንና ጨረቃን መሳሪያ በማድረግ ነው ። ማለትም ፀሃይና ጨረቃ በተፈላጊው ቦታና አውድ በግልጽ ተጠቅሰዋል ። ዳኢቴ ፣ አዴላንቃሞ ፣ እቴቴ ፣ ዛሬ እንኳን ፣ ብቻ መገኘትሽ ፣ ሀዘንሽ አመመኝ ፣ ይርጋለም እና የመሳሰሉትን ለአብነት መጠቃቀስ ይቻላል ።

ዘጠኝ በሚደርሱ ግጥሞች ደግሞ ‹ ብርሃን › የተወከለው ራሱን ችሎ ወይም ተምሳሌታዊ ሻማ በማብራት ነው ። ሰማይና ምድር ፣ ያቺ ቆንጂት ፣ ወለምታ ፣ ስንብት ፣ መንታ ነው ፍጥረትሽ እና የመሳሰሉት እዚህ ምድብ ወስጥ የሚወድቁ ናቸው ። ለአብነት ያህል ‹ ያቺ ቆንጂት › በሚለው ግጥም

ጋሼ ላጫውትህ ትለኛለች
ያይኔን ብርሃን እየሞቀች  › የሚል ተደጋጋሚ ስንኝ አለ ። እዚህ ላይ ብርሃን የተወከለው ፍቅርና መልካምነትን ለመግለጽ ነው ።
በግጥም መድብሎች ላይ በተለይም አንድን ጉዳይ በስፋትና በጥልቀት መወቀር የተለመደ አይደለም ። ምክንያቱ የተለያየ ቢሆንም በዋናነት ግን ገጣሚው ራሱ ሊያመነጫቸው በሚችለው ውስን ሀሳቦች ባለመርካቱ ሲሆን አልፎም ተርፎም አንባቢን አሰለቻለው ብሎ መፍራቱ ነው ።

የብርሃን ፍቅር ብርሃናዊ ጨረሮቹን በተለያየ መልክ ሳይሰስት ነው የሚያደርሰን ። በርግጥ ለደበበ ሰይፉ ብርሃን ምንድነው ? ብርሃንን የሚያስረዳን የጨለማ ተቃርኗዊ ውጤት መሆኑን ነው ? ወይስ ከሳይንሳዊ ፣ አፈታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ዳራዎች ጋር የተያያዙ ሃሳቦች አሉት ?

በ ‹ እሱ ነው - እሱ › ግጥሙ ላይ
እሱ ነው - እሱ
አይን ሳይኖረው
      ለምን ብርሃን ኖረ የሚለው
እግር ሳይኖረው
      ለምን መንገድ ኖረ የሚለው
እሱ ነው - እሱ
ከቀናቴ
      ፀሃይቱን የሰረቀ
በመንገዴ
      አሜከላ ያፀደቀ
እያለ የሚበሳጨው ለምንድነው ? ይህ ግጥም የምናወራበትን የ ‹ ብርሃን › ጉዳይ በሚገባ የሚገልጽ ነው ። ምክንያቱም የገጣሚውን ያገባኛል ባይነት ደምቆ እንመለከታለን ። በተጠየቅ የሚሞግትባቸው ቃላዊ - ሃሳቦች ብርሃን ፣ መንገድ እና ፀሃይ ናቸው ። ሃሳቦቹን በቤተዘመድ ጉባኤ አይን ካየናቸው አንድም ሶስትም ናቸው ። ገጣሚው በእውቀት ፣ እድገት እና እውነት ላይ የማይደራደር መሆኑ ይሰማናል ።

የደበበ ሰይፉ የብርሃን ትኩረት አንደኛው ምንጭነት ከህይወት ተምሳሌትነት የመቀዳቱ ጉዳይ ይመስላል ። ፈጣሪ በመጀመሪያ ሰማይና ምድርን ከፈጠረ በኋላ የምድር ጨለማ የተሸነፈው በብርሃን ውልደት አማካኝነት ነው ። ፈጣሪ ብርሃንን የፈጠረው ለድምቀት ብቻ አይደለም ። በብርሃን አማካኝነት ሃይል ተሞልቶ ለፕላኔታችን መቀጠል ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል ። የመሬት ሰርዓተ ምህዳር የተመሰረተው በፀሃይ ከሚገኘው ብርሃን ነው ። ምክንያቱም አጽዋት የፀሃይ ብርሃንን ምግባቸውን ለማዘጋጀት ይጠቀሙበታል ። በሌላ በኩል ሰውና እንስሣት ምግባቸውን ከእጽዋት ስለሚያገኙ ሰንሰለቱ የጠነከረ ነው ።

ደበበ ሰይፉ የብርሃን ሰረገላ የማይታየውን ወይም የማይደፈረውን ነገር ሁሉ እውነት ለማድረግ የሚያስችል መሳሪያ መሆኑን የመረዳቱ ጉዳይም ርዕሰ ጉዳዩን አጥብቆ እንዲይዝ አግዞታል ።

ምነዋ ባየሁኝ › በሚለው ግጥም
ምነው ባየሁኝ
መሬቷን ሰቅስቄ
ዛፉን ተራራውን ቤቷን ሰዋን ሁሉ
አንድ ላይ ጠቅልዬ
በብርሃን ፍጥነት በሚምዘገዘግ ዘንግ
ወዲያ አንጠልጥዬ
እያለ ቀስተ ዳመናንና ጨረቃን ሁሉ ቀላል መጫወቻ እንዲሆኑለት ይመኛል ። ይህ ምኞት መለኮታዊ መሻትም ጭምር ነው ። ምክንያቱም መላዕክት የሚታዩት ብርሃን ባለበት ነው ። ብርሃንን ከመሬት ወደ ሰማይ ለመጓጓዝ እንደ ኤሌክትሮማግኔቲክ ሃይል ይጠቀሙበታል ። ሰዋች ጸሎትና ምሰጣ ሲያከናውኑ እንደ ሻማ አይነት ብርሃናዊ ነገሮችን የሚጠቀሙትም መለኮታዊ ግንኙነት ለመፍጠር በማሰብ ነው ።

ሌላው የደበበ ግጥሞች መሰረታዊ መለያ ፀሃይንና ጨረቃን የብርሃን ምሶሶ ወይም ኪናዊ ምርኩዝ የማድረጋቸው ጉዳይ ነው ። ከላይ እንደገለጽኩት 15 የሚደርሱ ግጥሞች ላይ ምርኩዝ ሆነው ቆመዋል ። አንባቢም በገባው መልኩ በዛቢያቸው እንዲሽከረከሩ ያደርጋቸዋል ። ገጣሚውም አልፎ አልፎ ለብቻ አንዳንዴ ደግሞ አንድ ላይ ያቀርባቸዋል ።

የጥንት ሰዋች የሁለቱን አብሮነት Duality በማለት ይገልጹታል ። ምክንያቱም እንደ ብዙ ሀገሮች አፈታሪክ ከሆነ ፀሃይና ጨረቃ ባልና ሚስት ፣ ወንድምና እህት ወይም ወንድማማቾች ሆነው ይወከላሉ ። የስው ልጅ ሲፈጠር ጀምሮ የሁለትዮሽ ውጤት ነው ። ሁለት እጅ ፣ ሁለት እግር ፣ ሁለት አይን ፣ ሁለት ጆሮ ወዘተ ያለው ። ይህ ጥምረት የፀሃይን ግማሽ እና የጨረቃ ግማሽ ውህደትንም ይወስዳል ። ፀሃይ የቀኝ ጎን ስትሆን ጨረቃ የግራ ናት ፤ የቀኝ ጎን ወንድ የግራ ደግሞ ሴትነትን ወካይ ነው ይላሉ ።

ደበበ ‹ አዴ ላንቃሞ › በተሰኘው ግጥም / አንድ የሲዳሞ ወንድ ነው / ተጠቃሹ ሰው ባሉት ሶስት ሚስቶችና ወንድ ሆኖ በመፈጠሩ ሲደሰት እናያለን ። በደማቅ የጨረቃ ብርሃን ታጅቦ ለሶስቱም ሚስቶች ለአዳር እንደሚመጣ ትእዛዝ ሰጥቶ እንዴት ሽር ጉድ እንደሚሉ በማሰብ ነው የሚስቀው ። ሊያድር የሚችለው ግን አንዷ ጋ ብቻ ነው ።

ብርማይቱ ጨረቃ
የብርሃን ጠበል አፍልቃ
ተፈጥሮን ስታጠምቃት
እንደገና ስትወልዳት
እያለ ነው ግጥሙ የሚዘልቀው ። እንደ ጨረቃዋ ልዩ ድምቀት ሶስቱ ሚስቶቹ ጋ በነበረው ሃያል ሙቀት እየረካ ነበር ። ምክንያቱም ሶስቱም ‹ እኔ ጋ ነው የሚያደረው › በሚል ያሻቀበ ጉጉት ጎጆውን በፍላጎት ፍላት እንደሚያነዱት ስለማይጠረጠር ። ጨረቃዋና ሴቶቹ በፈጠሩት ግለትም ሆነ ጾታዊ አንድነት የተመሳሰሉ ይመስላል ። በግጥሙ መሰረትም አዴ ላንቃሞ የወንድነቱን ፅድቅ አድናቂ ነውና ከጨረቃ በትይዩ የቆመ የፀሃይ ወገን ሊሆን ይችላል ።

ደበበ በተለይም ‹ ገና በልጅነት › እና ‹ ዛሬ እንኳን › በተሰኙ ግጥሞቹ ውስጥ ፀሃይና ጨረቃን በጋራ እየገለጸ ተጠቅሞባቸዋል ። ፀሃይን ሲያነሳ ሃይልን ፣ ህይወትን ፣ ጤናን ፣ ጥልቅ የፍቅር ስሜት መገለጫነትን በመወከል ሲሆን ጨረቃን ሲገልጻት ሚስጢርን ፣ ብቸኝነትን ፣ ውበትን የመሳሰሉትን እንድናስብ በማመላከት ነው ። የደበበ ሰይፉ የብርሃን ፍቅር ብርሃን አስሶ ፣ በብርሃን ተማርኮ ብርሃን የሚሰብክ ኪናዊ ዳመራ ነው ። ‹ የብርሃን ፍቅር › አንድ አይኑን ፀሃይ ሌላውን ጨረቃ አድርጎ ብርሃናማ መሃልየ የሚሰብክ ኪናዊ ካህን ነው ።

Wednesday, December 20, 2017

« አብዮት የራት ፓርቲ አይደለም ! » . ቀይዋ መጽሐፍ



በዓለማችን በብዛት እየተነበቡና እየተሸጡ ያሉ መጻህፍት ልቦለዶች አይደሉም ። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የመጀመሪያ ደረጃን በመያዝ የወርቅ ሃብል እንዳጠለቀ የሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ ነው ። እንደ ጊነስ ወርልድ ሪከርድ መረጃ ከሆነ የሁልግዜ አንደኛ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ህትመት ከ 5 ቢሊየን በላይ ይሆናል ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ተከታታይ ተሸላሚነት ላይገርም ይችላል ፣ ምክንያቱም ለአይሁድና ክርስትና እምነት የእምነት መሰረት የሆኑ ሃሳቦችን የያዘ ግሩም መድብል በመሆኑ ። ይልቅ የሚገርመው ስለሃይማኖት የማይሰብከው መጽሀፍ የዓለማችን ሁለተኛ መጽሐፍ ሆኖ የብር ሃብል ማጥለቁ ነው ። ርግጥ ነው የመደብ ተጻራሪ የሆኑት ምዕራባዊያን ፓለቲከኞች የ « ማኦ መጽሐፍ ቅዱስ » እያሉ ነው የሚጠሩት ። እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ተከታይ በማፍራቱ ።

ይህ መጽሐፍ ከቢሊየን ኮፒ በላይ ታትሞ ተነቧል ። ሪከርድ ያሰጠው መጠሪያ « የሊቀ መንበር ማኦ ጥቅሶች » የሚል ቢሆንም ብዙዎቹ እያንቆለጻጸሱ የሚጠሩት « ትንሿ ቀይዋ መጽሐፍ » በማለት ነው ።

ይቺ ትንሽ መጽሐፍ በጥቅስና አባባሎች የተከበበች ትምሰል እንጂ መልዕክቷና ዓላማዋ ከቻይና አልፎ የዓለማቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት መሳብ ችሏል ። አያሌ ምሁራን የቻይናው ህዝባዊ ሪፐፕሊክ መስራች የሆነውን ማኦ « የማይጠግብ አንባቢ » ይሉታል ። ማኦ እንደ ሆዳም አንባቢነቱ ሆዳም ፀሀፊ ነበር ። ጥሩ ፖለቲከኛ ብቻ ሳይሆን ጥሩ የፖለቲካ ጸህፊ ለመሆኑ On New Democracy እና On Coalition Government የተሰኙ ስራዎቹን መጥቀስ ይቻላል ። ጥሩ አሳቢ ብቻ ሳይሆን ጥሩ የፍልስፍና ጸሀፊ ለመሆኑ Four essays on Philosophy የተባለውን ስራ ማገላበጥ ይጠቅማል ። ጥሩ ወታደራዊ መሪ ብቻ ሳይሆን ጥሩ የወታደራዊ ሳይንስ ጥበብ ጸሀፊ መሆኑን The art of war እና On Guerrilla warfare የተሰኙ ስራዎቹን ማንበብ ይቻላል ። ማኦ ከ 30 በላይ ስራዎች ሲያበረክት አንደኛዋ ግጥም ነበረች ። ከአብዮቱ በፊት እና ከአብዮቱ በኋላ በሚል ንኡስ ርዕስ የተከፋፈሉ 36 ግጥሞችን የያዘች መድብል ።

ከሁሉም ታዲያ በአጋጣሚ ገና የወጣችው ቀይዋ መጽሐፍ ናት ። ዋነኛ ምክንያቱም ቻይና ባከናወነችው የባህል አብዮት / 1966- 1976 / ለህዝቡ በተለይም ለቀዩ ዘብ መሰረታዊ መመሪያና ምክር በመሰነቋ ነው ። በነገራችን ላይ ማኦ ያከናወናቸው ሁለት ታላላቅ ጉዳዮች Great Leap forward እና Cultural revolution ባስከተሉት የረሃብና የግጭት ቀውስ ለበርካታ ሚሊየን ዜጎች መጥፋትም ምክንያት ሆነዋል ።

በባህል አብዮት ዘመን በተለይ ከመስመር የወጡ ተማሪዎች ‹ አራቱን አሮጌዎች አስወግድ ! › በሚል መርህ አሮጌ ባህል ፣ አሮጌ ልማድ ፣ አሮጌ ወግ እና አሮጌ አስተሳሰቦችን እናስተካክላለን በማለት በከተሞች ላይ ትልቅ ጥፋት አድርሰዋል ። በሌላ በኩል የማኦ ቀይ መጽሀፍ ያፈነገጡትን በመመለስ ፣ መስመር ውስጥ ያሉትንም ስራቸውን በምን መልኩ አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው ታድጋለች ። ምክንያቱም አብዮት ሲባል የቀድሞውን እያጠፉ ብቻ ንፋስ ወደነፈሰብት መረማመድ አይደለም ። ለዚህም ነው ቀይዋ መጽሀፍ ጠቃሚ ርዕሰ ጉዳዮችን እያነሳች መንገዱን ያሳየችው ። ኮሙኒስት ፓርቲ ፣ የመደብ ትግል ፣ ጦርነትና ሰላም ፣ ዲስፕሊን ፣ አንድነት ፣ የህዝብና የመከላከያ ሰራዊት ግንኙነት ፣ ካድሬ ፣ የመሳሰሉ ርዕሰ ጉዳዮችን በማንሳት ነገረ አንድምታቸውን ታወጋለች ።

እንዲህ በማለት ።

የመደብ ትግል በሚለው ሃሳብ ስር አብዮትን በሚከተለው ንፅፅር ፍርጥ አደርጎ ነው ያስቀመጠው « አብዮት የራት ፓርቲ አይደለም ፣ አብዮት ወግ መቸክቸክ ፣ ሰዕል መጫጫር ወይም ጥልፍ መስራት አይደለም ። አብዮት አንዱ መደብ ሌላውን ለመገልበጥ የሚያነሳው ሁከት ወይም ብጥብጥ ነው »

ማኦ አሜሪካ የምትኩራራበትን የአቶሚክ ቦንብ የወረቀት ላይ ነብር ነው በማለት ሀገሬው ስጋት ላይ እንዳይወድቅ ያበረታታል ። የጦርነት ውጤት የሚወሰነው በህዝቦች እንጂ በአንድ ወይም በሁለት አይነት መሳሪያ አለመሆኑን በማስገንዘብ ። ብዙሃንን መጨፍጨፊያ መሳሪያ ቢሆንም እንደ ቻይና የህዝብ ብዛት ያላቸውን ሀገራት ማሸነፍ እንደማይቻል ነው የሚያስገነዝበው ።

ሰላምና ጦርነት በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ስርም ዓለም ስለሚሰጋበት የሶስተኛው ዓለም ጦርነት አንስቷል ። ሶስተኛው የዓለም ጦርነት የሚነሳ ከሆነ ለኢምፔሪያሊስቶች የሚሆን ቦታ እንደማይኖር በስሌት በማስቀመጥ ። በአንደኛው ዓለም ጦርነት 200 ሚሊየን ስዎች ሶቪየት ህብረትን ተከትለዋል ። በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወደ ሶሻሊስት ካምፕ የተቀላቀለው 900 ሚሊየን ህዝብ ነው ። ሶስተኛው ዓለም ጦርነት ከመጣ ግን አለም ለኢምፔሪያሊስቶች የሚሆን ቦታ እንደሌላት ምስክር ይሆናል ።

አለም በሁለት ርዕዮት በመከፈሏ የተፈጠረውን ብሽሽቅ የሚያጠናክሩ አባባሎችም በስፋት ይታያሉ ። በአለም ላይ ካሉ ቀላል ነገሮች አይዲያሊዝም እና ሜታፊዚክስ ይገኙበታል የሚለው ማኦ ለዚህ የሚሰጠው ምክንያት ደግሞ ያለምንም ተጨባጭ ግብ ጠቃሚ ያልሆኑ ዝባዝኬዎችን ማውራታቸው ነው ። ተጨባጩን አለም መሰረት ያደረጉ ሁለት ፍልስፍናዎች ደግሞ ማቴሪያሊዝምና ዴያሌክትስ ናቸው ። ማኦ ተራማጅና ምክንያታዊ አስተሳሰብ አላቸው የሚላቸውን ሶሻሊዝምና ኮሙኒዝም ከፍ ከፍ በማድረግ ፣ የፊውዳሊዝም እና ካፒታሊዝም ብቸኛው ቦታዎች ሙዚየሞች መሆናቸውን ይገልጻል ።

ጥሩ ፒያኖ ለመጫወት ሁሉንም ጣቶች በአንድ ግዜ ማንቀሳቀስ አይመከርም ፤ እንደዛ ከሆነ ዜማ ስለማይኖር ። አስሩም ጣቶች በየተራ በጥሩ ምት እና ቅንብር መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል ። የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትም ችግሮችን ለመፍታት የግድ ፒያኖ መማር እንዳለባቸው ዘይቤያዊ በሆነ መልኩ አሳስቧል ። ለማኦ ጥሩ መሪነት ከፒያኖ ጨዋታ ጋር ይመሳሰላል ።

ወታደሩና መኮንኑ ፣ ጦር ሰራዊቱና ሲቪሉ ማህበረሰብ ለሀገሩ በፍቅርና በአንድነት ሊቆም የሚችለው የመተሳሰቢያ ድልድዮች ሲኖሩት ነው ። እነዚህ የመተሳሰቢያ ድልድዮች ደግሞ በዋነነት መዋቀር ያለባቸው በጦር ሰራዊቱ ትከሻ ላይ ነው ። በመሆኑም ጦር ሰራዊቱ ሶስቱን ደንቦችና ስምንቱን ነጥቦች ተግባራዊ ማድረግ ይጠብቅበታል ይላል ማኦ ።

ሶስቱ ደንቦች የትኞቹ ናቸው ?
1.      ሁሉንም ትዕዛዞች በስርዓት ተቀበል
2.     ከብዙሃኑ ሰባራ መርፌ ወይም ብጣሽ ክር እንዳትወስድ
3.     የማረከውን ሁሉ አስረክብ

 ስምንቱ ትኩረት የሚሰጣቸውስ ?
      1. በትህትና ተናገር        
      2. ለምትገዛው ሁሉ አግባብ ያለው ክፍያ ክፈል
      3. የተዋስከውን ሁሉ መልስ
      4. ለምታጠፋው ሁሉ ክፈል
      5. ህዝብ ፊት አትማል
      6. ስብል አታበላሽ
      7. ከሴት ጋር አትባልግ
      8. ምርኮኛ ላይ የጭካኔ ተግባር አትፈጽም ።

ከማኦ እምነት እና ደንብ የምንማረው ጦር ሰራዊቱ የሃይል አበጋዝ ቢሆንም በጉልበቱ ተማምኖ ዋልጌነትና ሙስና መስክ ላይ እንዳይጨፍር ዛብ የሚያስፈልገው መሆኑን ነው ። የትህትና እና የፍቅር ተምሳሌት ከሆነ የእውነተኛ ህዝባዊነትን ማዕረግ ከእያንዳንዱ ቤት በሶጦታ ያገኛል ።

እንደሚታወቀው ማኦ ሀገሪቱን በእንዱስትሪ የቀደመች ለማድረግ The Great Leap Forward መርሃ ግብር ክተት ካለ በኋላ እቅዱ ሀገሪቱ ባጋጠማት አደገኛ ድርቅ ሊከሽፍ ችሏል ። ይህ ውድቀትም ማኦ ስልጣኑን እንዲያጣ አድርጎታል ። ሆኖም የሀገሪቱ ወጣቶች እሱን በመደገፋቸው እንደገና መነሳት ችሏል ። ወጣቱ የንባብ ማእከላትን አጠናክሮ በማጥናትና በመከራከር ሌላው ቀርቶ ማንበብ የማይችለው ህብረተሰብ ጋር ተደራሽ በመሆን ትልቅ ሚና ተጫውቷል ። ቀይዋ መጽሐፍ በህዝብ አውቶብስ ውስጥ ሌላው ቢቀር በሰማይ ላይ ሁሉ ይጠና ነበር -  የቻይና ሆስቴሶች የማኦን የጥበብ ቃላት ለተሳፋሪያቸው ይሰብኩ ነበር ። ማኦና ወጣቱ እንደ ጣትና ቀለበት ስምሙ መሆኑ የቻሉት ቀይዋ መጽሐፍ ወጣቱን የሚያቀልጥ ሃሳብ በመያዟ ይመስለኛል ።

እንዲህ በማለት ።

« አለም የናንተ ናት ፣ የኛም ጭምር ። እንደ መጨረሻ ትንታኔ ከሆነ ግን የናንተ ናት ። እናንተ ወጣቶች እንደምታብብ ህይወት ... ልክ ሁለት እና ሶስት ሰዓት እንደምትወጣው የጠዋት ፀሃይ ብርታትና ጥንካሬ የተሞላችሁ ናችሁ ... »

ማኦ በቀይዋ መጽሐፍ ላይ « የማርክስ ፣ ኤንግልስ ፣ ሌኒንና ስታሊን ቲዎሪ አለማቀፍ ተቀባይነት ያገኘ ነው ። እኛ የምንቀበለው እንደ ቀኖና ሳይሆን እንደ መንገድ መሪ ነው » ይላል ። በርግጥ ማኦ በመሰረተ ሃሳብ ደረጃ ማርክሲስቶችን ቢያከብርም የራሱን ቲዎሪ  የገነባ ብሎም ተጽእኖ የፈጠረ ሰው ነው

ስሙን መሰረት ያደረገው « ማኦኢዝም » የኢንዱስትሪ መስፋፋት ከበርቴው ይበልጥ ህዝቡን እንዲበዘብዝ መንገድ ይፈጥራል ባይ ነው ። በዚሁ ፍልስፍናው የፋብሪካው ሰራተኛ ሳይሆን ገበሬው የኮሙኒስት አብዮትን መምራት አለበት ብሎ ያምናል ። ከማርክሲዝም ርዕዮት ጋር ልዩ የሚያደርጋቸውም ሀሳብ ይኸው ነው ። ማርክሲስቶች የከተማው ሰራተኛ ላይ ትኩረት ሲያደርጉ ማኦ ኢዝም ለገበሬው ይወግናል ።

ምዕራባዊያን ማኦ የበርካታ አስገራሚ ጥቅሶች ፈጣሪ እንደሆነ ይቀበላሉ ። ከአስገራሚው አንዱም « ብዙ መጽሐፍ ያነበበ አደገኛ ነው » ያለው እንደሚገኝበት ጽፈዋል ። የአንባቢ ወታደሮችን መጽሐፍ ሰብስቦ ያቃጥል ነበር የሚሉትም አሉ ። ነገሩ ተረት ይመስላል ። ቀይዋ መጽሐፍ አንባቢነትን አትቃረንም - ይልቅ ስለ ትምህርትና ስልጠና አስፈላጊነት ነው የምትሰብከው ። እንግሊዞች ማኦን እንደሚተርቡት ሁሉ አድንቀው ፓርላማ ውስጥ ጥቅሱን ለንግግራቸው ማዳመቂያነት የሚያውሉም አሉ ።በቀይዋ መጽሐፍ የተሰባሰቡት ጥቅሶችና አባባሎች የማኦን ፍልስፍናና እምነት ያንጸባርቃሉ ::

እንዲህ በማለት ።

መጥረጊያህ ቆሻሻው ጋ ካልደረሰ ቆሻሻው በራሱ ግዜ አይጠፋም ።
ጦር ሰራዊታችን ለጠላት ጨካኝ ለወገን ደግሞ ደግ መሆን አለበት ።
የጓዶቻችን ጭንቅላት ምናልባት አቧራ ይሰበስብ ይሆናል ፣ በመሆኑም በግምገማና ግለ ሂስ መጠረግና መታጠብ ይፈልጋል ።
ማኦ በዛሬይቷ ቻይና ብቻ ሳይሆን በዛሬዋ አለማችን ዙሪያ አንድ መሰረታዊ ተጽዕኖ ፈጥሮ ማለፍ ችሏል

እንዲህ በማለት ።

« የፖለቲካ ስልጣን የሚመጣው ከጠመንጃ አፈሙዝ ነው ! » ለዚያም ነው በርካታ የዓለማችን መሪዎች ማቆሚያ የሌለው የጦር መሳሪያ እሽቅድድም እና ግንባታ ውስጥ የገቡት ።


Sunday, October 29, 2017

« አውሮራ » - የጦርነት አረር ፣ የፍቅር ቀለሃ


ሪኩ የተገነባው ዙዎቻችን በምናውቀው እውነት ላይ ነው ። ጠላትህ ጠላቴ ነው ተባብለው የተማማሉ ሁለት ብሄርተኛ ቡድኖች ለረጅም አመታት ታግለው እንደ ሀገር የሚያስበውን ቡድን አሸንፈው ስልጣን ያዙ ።

በስልጣን ማግስት ሀገር የፈለገውን ይበል ብለው መስመር ባለፈ ፍቅር ከነፉ ። እንደ ደራሲ ከበደ ሚካኤል ግጥም ‹ ሁለት አፍ ያለው ወፍ › ሆኑ ። በፍቅር ተጎራረሱ ። ተቃቅፈው በረሩ ፣ አለም ጠበባቸው ... ተጣብቀው ዘመሩ ‹ አይበላንዶ  ...  › እያሉ ።ተያይዘው ፈከሩ ! ‹ ነፍጠኛ ሰመጠ ፣ ተራራ ተንቀጠቀጠ › በማለት ... አብረው ተዛበቱ ‹ ትግል ያጣመረውን ህዝብ አይለየውም › በሚል ስልቂያ ... ኪስህ ኪሴ ነው ፤ ሚስትህ ሚስቴ ናት ፤ ግዛትህ ግዛቴ ... ምን ያልተባባሉት አለ ?

 ከአይን ያውጣችሁ ያላቸው ግን አልነበረም ።

እየቆየ አይንና ናጫ ሆኑ ... በአጎራረስህ እየተጎዳው ነው በሚል አንደኛው አፍ የጫካ ውንድሙን ካደ ። የእህል ምርቱንም ሆነ የሚያጌጥበትን ማእድን ደበቀ ። የብር ኖቶችን ቀየረ ፣ የድንበር ንግድ ግብይት በዶላር እንዲሆን ድንገተኛ ህግ አረቀቀ ። ይህ ተግባር ለሁለተኛው አፍ የማይታመን ክህደት ነበር ። ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ አለ ። ጠፍጥፎ በሰራው ልጅ ተናቀ ... ሹካ አያያዝ አስተምሬው ? በኔ ደም ለወንበር በቅቶ እንዴት ክብሬን ያራክሳል በማለት ለጦርነት ተዘጋጀ ።

‹ አውሮራ › ይህን የምናውቀውን ታሪክ ይዞ ነው መዋቅሩን የገነባው ። የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት እንዴት ተጀምሮ እንደምን እንዳለቀ እናውቃለን ፣ ምን እንዳስከተለም የብዙ ወገኖች መረጃ አለን ። የመንግስት ሚዲያዎችን ጨምሮ የድርጅቶቹ ልሳኖች የአውደ ውጊያውን ታሪክና የታሪክ ሰሪ ሰዎችን ህይወት በመዳሰስ አታካች በሆነ መልኩ በተከታታይ አቅርበውልናል ። ታዲያ አውሮራ ምን የተለየ ነገር ሊነግረን ታሪክ ቀመስ ልቦለድ ሆነ ? ቢባል ትክክል ነው ።

ደራሲው ሀብታሙ አለባቸው ግን ብልህ ነው ፣ ገና በጠዋቱ ፣ ሁለተኛው ምዕራፍ ላይ ያስተዋወቀንን የታሪክ በከራ እንዴት ሳይሰለች እያጠነጠነ እስከ ምዕራፍ 43 መዝለቅ እንዳለበት በሚገባ ተረድቷል ። ስለተረዳም ሳቢና ተነባቢ አደረገው ።

ይህን ለማከናወን ከረዳው ስልት አንደኛው የትረካውን ኳስ ለመለጋት በመረጠው የመቼት አንግል የተወሰነ ይመስለኛል ። ደራሲው 80 ከመቶ የሚሆነውን ታሪክ የሚያቀብለን ከኤርትራ አንጻር ሆኖ ነው ። በትረካው የአስመራን ውበት ፣ የወታደራዊ ካምፖችን ሚስጢር ፣ የደህንነት ተቋማት ፕሮፓጋንዳ ፣ ሳዋ ስለተባለው የሰው ቄራ ፣ የፕሬዝዳንቱን ጽ/ቤት ከነተግባርና ግዴታቸው እንመለከታለን ። የህዝቡን አበሻዊ ጥላቻ ፣ ፖለቲካዊ ሹክሹክታ እና ስነልቦና እንመረምራለን ። የባለስልጣናቱን በተለይም የፕሬዝዳንቱን እምነት ፣ አስተሳሰብ እና ፍላጎት እንታዘባለን ። በአጠቃላይ ከአስመራ የምናገኘው አዲስ መረጃ ታሪኩ ሰቃይና አጓጊ እንዲሆን ትልቅ ሚና ተጫውቷል ። የታሪኩ ልጊያ ከአስመራ እየተነሳ ወደ ኢትዮጽያ ፣ ጅቡቲና ሌሎች አካባቢዎች ሲያመራ ደግሞ ተዝናኖት ብቻ ሳይሆን አማራጭ እሳቤ ይፈጥርልናል ። በመሆኑም የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት አዲስ ሆኖ እንዲሰማን አድርጓል ።
ሌላም አለ ። ታሪኩን የሚደግፉት የሴራ ቅንብሮች ባለሁለት አፍ ወፎቹ ይፋ በሆነ መልኩ በመድፍ እንዲቆራቆሱ ብቻ አይደለም የሚያደርገው - ወፎቹ በየሰፈራቸው በተዳፈነው ረመጥ እንዲለበለቡም ጭምር እንጂ ።

የአስመራው ወፍ / ኢሳያስ / ክብሩንና ጥቅሙን ለማስጠበቅ መጠነ ሰፊ ፣ የተደራጀና ህቡዕ ተኮር እንቅስቃሴ ያደርጋል ። ኢትዮጽያዊው ወፍ / መለስ / አንድም አናት አናቱን ከሚጠቀጥቁት ወንድም ግንደ ቆርቁሮች በሌላ በኩል ከሩቅ አጎቱ የሚወረወርበትን ሞርታር ለመከላከል መከራውን ሲበላ እንመለከታለን ።

በነገራችን ላይ ከአስመራ ወደ ኢትዮጽያ የሚጋልበው የታሪክ ጅረት ሁለት መቆጣጠሪያ ቤተመንግስቶች አሉት ። የአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ እና የአቶ ሃይላይ ሃለፎም ። በፍትህ ሚ/ሩ አቶ ሃይላይ ቤት አራት የታሪኩ ቁልፍ ሰዎች ይገኛሉ ። ቤተሰቦች ናቸው ። ሳህል በረሃ የተወለደችው ፍልይቲ ፣ ወንድሟ ሰለሞን እና ባለስልጣን እናታቸው አኅበረት ። ሃይላይ በርግጥም ለሰላምና ፍትህ የቆመ ብቸኛ ሚኒስትር ነው ። ከኢትዮጽያ ጋር የሚደረገው ጦርነት መሰረት የሌለው የዜሮ ድምር ፖለቲካ በመሆኑ መቆም አለበት በሚለው አቋሙ ከዋናው ቤተመንግስት ሰውዪ ጋር ይጋጫል ።

በሌላ በኩል ኢሳያስ የሃይላን ልጅ ፍልይቲን እንደ ጆከር ሲጠቀምባት እናያለን ። ኢ/ያ ውስጥ የሚከናወነውን የዶላር ዘረፋ ፣ የስለላ ስራና ህቡዕ ግድያ ትመራለች ። በጅቡቲ ወደብ ወደ ኢ/ያ የሚገባውን ስትራቴጂካዊ ንብረት ለማውደም ተመራጭዋ ሰው እሷ ናት ። ባድመ በመዝመት ለሌሎች ያስቸገሩ የመረጃና የተመሰጠሩ መልእክቶችን የመፍታት ስራ ትሰራለች ። ፍልይቲ የፕሬዝዳንቱ ቀኝ እጅ ፣ ብሩህ አእምሮ ያላት ፣ ደፋር ፣ አፍቃሪ እና ጨካኝ ገጸባህሪ ናት ።

ከኤርትራ ህዝብ አንጻር / አማራ ጠላት ነው የሚል ቆሻሻ ሀሳብ / ግን አንድ ይቅር የማይባል ክህደት ትፈጽማለች ። ክህደቱ ለኤርትራ የቴሌ እና ኤሌክትሮኒክስ ግንባታ ትልቅ ድርሻ ያከናወነውን ኢትዮጽያዊ ሰው በማፍቀሯ ነው ። አስራደ ሙሉጌታ ይባላል ። ሻእቢያ ጉልበቱንና እውቀቱን እንደ ሽንኮራ ከመጠጠው በኋላ ሊያስወግደው ቀነ ቀጠሮ ይዞለታል ። ለአስመራ ፖለቲካ ትልቅ አይን የሆነችው ፍልይቲ ከመንግስታዊው ተልዕኮ ጎን ለጎን ፍቅረኛዋን ለማዳን ህቡዕ ትግል ስታከናውን እንመለከታለን ። የሃይላይ ወንድ ልጅ ሰለሞን ‹ ናጽነት › በሚለው ነጠላ ዜማው በከተማው የታወቀ ዘፋኝ ሆኗል ። ሙዚቃው ማዝናኛ ብቻ ሳይሆን የዘመቻ መቀስቀሻም ነው ። ናጽነት ብሎ የዘፈነው ግን በኢሳያስና በአባቱ ለተመራው ትግል ማስታወሻ ለመስራት ብቻ አይደለም ። እንደውም በዋናነት የዘፈነው ነጻነት የተባለች ቆንጆ ወጣት በማፍቀሩ ነው ። ነጻነት ለኤርትራ ወጣት የእግር እሳት ወደሆነበት ሳዋ ስትገባ እሱም እንዳላጣት ብሎ ፈለግዋን ይከተላል ። እሷን ፍለጋ ላይ ታች ሲል ነጻነት በሁለት የባደመ ጦር ጄነራሎች አይን ውስጥ ትወድቃለች ። ልክ እንደ ባድመ መሬት ሊቆጣጠሯት ሌት ተቀን ስትራቴጂክ ይነድፋሉ ።

እናም የአንደኛው ቤተመንግስት ሰውዪ ከኢ/ያ ድል ለማግኘት ሲራራጥ ፣ የሁለተኛው ቤተመንግስት አባላት ደግሞ ከራሱ ከኢሳያስ ጭቆና ለመላቀቅ እንዲሁም ፍቅረኛዎቻቸውን ለመታደግ ላይ ታች ሲሉ በታሪኩ ተወጥረን እንያዛለን ።

መጽሐፉ ጥቃቅን ቴክኒካል ችግሮች የሉበትም ማለት አይቻልም ፣ ለአቅመ ግነት የሚበቁ ስላልመሰለኝ ዘልያቸዋለሁ ። ይልቁንስ ደራሲው የራሱ እምነት የሚመስል ጉዳይ መጀመሪያ ምዕራፍ ላይ ቆስቁሶ እንዲረሳ ወይም እንዲጨነግፍ ማድረጉ የሚቆጭ ይመስለኛል ። ያነሳቸው ጥያቄዎች የአንባቢም መሰረታዊ ጥያቄዎች ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው ። የባርካ ማተሚያ ቤት ባለቤት የሆኑ ግለሰብ አቶ ሃይላይ ሊጽፉ ባሰቡት መጽሐፍ ውስጥ አራት መሰረታዊ ጥያቄዎችን አዳብረው አንዲሰሩ ሀሳብ ያቀርባሉ ። ከቀረቡት ሃሳብ ውስጥ ሁለቱ የሚከተሉት ናቸው ፣

1 . የኤርትራ ነጻነት ትግል ለምን በ 1885 ምጽዋ በኢጣሊያ መያዝን በመቃወም አልተጀመረም ?
2 . ከኤርትራ ልዩ ማንነት የተፀነሰ ትግል ከሆነ ለምን 30 አመታት ፈጀ ?

ደራሲው ስራውን ከሰሩት 285 ሺህ ናቅፋ እንደሚያገኙም ውል ታስሮ ነበር ። ሆኖም የማተሚያ ቤቱ ባለቤት ሲያዙ ፣ አቶ ሃይላይም ሲገደሉ ሃሳቡ ይመክናል ። እንደ ስነጽሁፍ ሃያሲ የሁለቱ ሰዋች መጥፋትን በአስመራ ወስጥ የመጻፍ ፣ የመናገር ፣ የማሰብ እና የዴሞክራሲ መሞትን ለመተርጎም ያስረዳን ይሆናል ። ከዚህ በላይ ግን ታሪኩ ባይጨነግፍ የበለጠ ጠቃሚ ያደርገን ነበር ብሎ መከራከር ያስኬዳል ። አቶ ሃይላይ ለእውነት የቆሙ ገጸባህሪ በመሆናቸው እየመረራቸውም ቢሆን ከኤርትራ ጀርባ የተደበቁ ጉዳዮችን ያነሱ ነበር ። ይሄን አንስተው ቢሞቱ ደግሞ ሞታቸውንም ይመጥን ነበር ። የበለጠ ጀግና መስዎዕት እናደርጋቸው ነበር ።

‹ አውሮራ › ጦርነት ላይ መሰረት አድርገው እንደተሰሩት ልቦለዶቻችን ማለትም ኦሮማይ እና ጣምራጦር የተሳካ ስራ ነው ። ድንበር ያቆራርጣል ፤ እዚህና አዚያ እንደ ቴኒስ ኳስ ሲያንቀረቅበን ጨዋታው ሰለቸኝ ብለን ከሜዳው ዞር ማለት አንችልም ። ፈጣን ነው ፤ በድርጊት የተሞላና በመረጃ የደነደነ ። መንቶ ነው ፤ ፍቅርና ጦርነትን በእኩል ጥፍጥና ከሽኖ ማቅረብ የቻለ ። ሰባኪ ነው - ፍቅር ያሸንፋል የሚል አይነት ፤ ተዛምዶ ተጋብቶ ተዋልዶ የተካደ ትውልደን የሚያባብል ። የሆነውን ብቻ ሳይሆን  የሚሆነውን ቁልጭ አድርጎ የሚናገር ። በተለይም የአንድነት አሳቢዎችን ገድለን ቀብረናል ብለው ለሚመጻደቁ ጠባቦች « ውሸት ነው ! » ብሎ ጥበባዊ ምስክርነት የሚሰጥ ።

በታሪኩ ውስጥ ማንነቱን ደብቆ ስሙን አቦይ ግርማ አስብሎ ቀን ከለሊት በባድመ የልመና ተግባር የሚያከናውነው እንኮዶ /የደርግ ኮማንዶ የነበረ / አንድ እጁ ስለተቆረጠና አይኑ ስለተጎዳ ማንም ግምት ውስጥ ያሰገባው አልነበረም ። ሆኖም መጀመሪያ የባድመን መሬት ፈልፍለው የገቡ የሻእቢያ ወታደሮችን ፣ በመጨረሻም እጁን በመጋዝ ቆርጦ የጣለውን ጄኔራል ግዜ እየጠበቀ መበቀል ችሏል « ለገንጣይና ጡት ነካሽ ዋጋው ይሄ ነው » እያለ ። ይህ ትርክት በስነጽሁፍ ቋንቋ ፎርሻዶው ወይም ንግር የሚባለው ቴክኒክ ነው - ነገ እንዲህ መሆኑ አይቀርም ለማለት ።



Sunday, October 22, 2017

በአፍሪካ ጭንቅላት ዓለምን መምራት ?


« የማይቻለውን እንደሚቻል እናረጋግጥ » በሚል መሪ መፈክር ስር ተወዳድረው የአለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጄነራልነትን ያሸነፉት አቶ ቴዎድሮስ አድሃኖም ፣ ሮበርቱ ሙጋቤን የበጎ ፍቃድ አምባሳደር አድርገው መሾማቸው አለማቀፍ ተቃውሞ አስከትሎባቸዋል ። እኔም ሰውየው የሚመለከቱበት መነጽር እንዴት ሸውራራ ሆነ ብዪ ጥያቄ አንስቼያለሁ ።

አንዳንዶች ነጮች ሙጋቤን ስለማይወዱት በተራ ጥላቻ የተደረገ ተቃውሞ እንደሆነ ያስባሉ ። እውነቱ ግን ይሄ አይደለም ። ሙጋቤ የፈለገ ያህል ለነጭ ተንበርካኪ አይሁኑ እንጂ በሀገራቸውም የሚመሰገን የፖለቲካ ስብእና የላቸውም ። ሀገሪቱን ላለፉት ሰላሳ አመታት የገዙት የተቃዋሚዎቻቸውን ድምጽ ብቻ ሳይሆን የህዝባቸውን የዴሞክራሲ ጥማት ጨፈላልቀው ነው ። ለስሙ ያህል ምርጫ ያካሄዳሉ እንጂ ‹ በህይወት እስካለሁ ድረስ ፕሬዝዳንት ነኝ › የሚሉትን መርህ አጥብቀው እየተገበሩ የሚገኙ ሰው ናቸው ። ምን ይሄ ብቻ በቅርቡም ባለቤታቸው ግሬስ ፣ ሙጋቤ ቢሞት እንኳ ሬሳው ይወዳደራል ማለታቸው የሚዘነጋ አይደለም ። የሰው ልጆች በተፈጥሮ ያገኙትን የዴሞክራሲ መብቶች የግል በማድረግ ነጻነት እንዲጠፋ ፣ ጭቆና እንዲስፋፋ የሚተጉ ባለስልጣናትን እውቅና ከሚሰጠው ጎዳና ገለል አለማለታችን ያሳዝናል ።

  ከአፍሪካ የተገኙት ቴዎድሮስ የሙጋቤ አምባገነን መሆን ጉዳያቸው ላይሆን ይችላል - ስልጣንን አለመልቀቅ የአፍሪካ ያልተጻፈ ህግ ስለሆነ ። አንድ የአፍሪካ ባለስልጣን ወደ አለማቀፉ ደረጃ ከፍ ሲል ግን በዚያው የአሰራር ስርዓት ውስጥ ሊጓዝ ግድ ይለዋል - ምክንያቱም ከአፍሪካ መጣ እንጂ አፍሪካን ብቻ ሊመራ አይደለም እዛ የተወከለውና ። እና አንድ መሪ አዎንታዊ  ቅቡልና የሚያገኘው ለሰው ልጆች ካለው ክብርም አኳያ ነው ። ሙጋቤ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ረገድ የረባ ሰእል የላቸውም ። ተመድ በግልጽ ከሚመራባቸው መርሆዎች አንዱ ደግሞ ሰብዓዊ መብትን ማክበር ነው ። ታዲያ ሙጋቤ በምን አንጀታቸው ነው ርህራሄ የሚፈልገውን የጤና ተቋማት መደገፍ የሚችሉት ?

ሙጋቤ 93ተኛ አመታቸው ላይ ይገኛሉ ። አለመታደል ሆኖ እንጂ ይህ የማረፊያና የጥሞና ግዜ ነበር ። በየግዜው እንደምናያቸውም በአካልም ሆነ በአእምሮ ደክመዋል ። መራመድ ተስኗቸዋል ፣ ስብሰባ መቀመጥ ባለመቻላቸው በየሄዱበት ያንቀላፋሉ ። አንድ ሰው ንቁ ካልሆነ እንዴት ለሌላ ስራ ይታጫል ? አቶ ቴዎድሮስ ለዚህ ጥያቄ አሳማኝ ምላሽ የሚኖራቸው አይመስለኝም - በሙጋቤ ቃል አቀባይ ፎጋሪ አስተያየት ካልተስማሙ በስተቀር ። ፎጋሪው ሰውየ ምን አለ መሰላችሁ « ሮበርቱ ሙጋቤ በየስብሰባው የምታዩዋቸው እየተኙ አይደለም - አይናቸውን ስለሚያማቸው እያረፉ እንጂ »

አቶ ቴዎድሮስ ለዙምባቤ ጤና አገልግሎት አሰጣጥ አዎንታዊ ድጋፍ እንዳላቸውም ተናገረዋል ። ይህ አስተያየታቸው ግን ከነባራዊው እውነታ ጋር የሚጣረስ ነው ። በርካታ መረጃዎች የሚያመለክቱት የዙምባቤ የጤና ስርአት እጅግ አሳዛኝና አሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑ ነው ። ሰራተኞች ያለ ደመወዝ የሚሰሩበት ግዜ ጥቂት አይደለም ፣ በመንግስት ሆስፒታሎች መድሃኒት ባለመኖሩ ሰራተኞች በቂ ህክምና ለመስጠት ተቸግረዋል ።

አቶ ቴዎድሮስ ሙጋቤ በዓለማቀፉ ጤና ድርጅት ተመርጠው መስራታቸው የሀገራቸውንም ሆነ የአፍሪካን የጤና አያያዝ ሊያሻሽሉ ይችላሉ ባይ ናቸው ። እውነቱ ግን ሙጋቤ በሀገራቸው ጤና ስርአት ላይ እምነት የሌላቸው መሆኑ ነው ። እምነት በማጣታቸውም ሲታመሙ እንኳ በሆስፒታላቸው ሊታከሙባቸው አይፈልጉም ።  አቶ ቴዎድሮስ ‹ የህክምና ቱሪስት ፕሬዝዳንቶች ›  / Medical Tourist Presidents / ስለተባሉት የአፍሪካ መሪዎች አንበው ቢሆን ኖሮ ይህን ከመሰለ ስህተት ውስጥ ባልገቡ ነበር ።

ዓለም የሚሳለቅባቸው እነዚህ የህክምና ቱሪስቶች የናይጄሪያው ሙሃመድ ቡሃሬ ፣ የአንጎላው ጆሴ ኤድዋርዶ ፣ የቤኒኑ ፓትሪስ ታሎን ፣ የአልጄሪያው አብዱላዚዝ ቡተፍሊካ እና የዙምባቤው ሮበርቱ ሙጋቤ ናቸው ። እነዚህ መሪዎች በአመት ውስጥ ደጋግመው ውጭ ሀገር ለህክምና ስለሚመላለሱ በርካታ የሀገር ሃብት ያጠፋሉ ። ሙጋቤ ባለፈው አመት ብቻ ሶስት ግዜ ወደ ሲንጋፖር ለህክምና አቅንተዋል ፣ ለዚህም 50 ሚሊየን ዶላር ወጪ ያደረጉ ሲሆን ይህ ገንዘብ የሀገሪቱን ጤና ጣቢያዎች ለማስፋፋት ከተመደበው አመታዊ በጀት በሁለት እጥፍ ይበልጣል ። ሙጋቤ ሲንጋፖር ሄደው የሚታከሙትም በጥቁር ሀኪም ነው ። ነጭ ሁሉ ጠላት ነው የሚሉት ሙጋቤ በአለም አቀፍ የህክምና መድረክ ብቅ ቢሉ እንዴት ነው በፍቅር መስራት የሚችሉት የሚለውን ጥያቄ አቶ ቴዎድሮስ መመለስ ይኖርባቸው ነበር ።

ዞሮ ዞሮ የሙጋቤ አምባሳደርነት ተፍቋል ። አቶ ቴዎድሮስ ይህን በፍጥነት ማድረጋቸው መልካም ነው ፣ ነገር ግን በብዙ መልኩ ጥያቄና ጥርጣሬ ውስጥ ወድቀዋል ። ነገሮችን የሚያዩብት መነጽር ሸውራራ እንዳይሆን ተፈርቷል ። ስለ ተመድ ያላቸው እውቀትና አረዳድ አስጊ መስሏል ። በስሜት ሳይሆን በተጨባጭ መረጃ ውሳኔ ሰጪ አይሆኑ እንዴ አሰኝቷል ። የዴሞክራሲ ማእከል ውስጥ ገብተው ዴሞክራት ላልሆኑ ሰዎች መወገናቸው አስደንግጧል ። አቶ ቴዎድሮስ ከለመዱት ‹ አብዮታዊዊ › አሰራር በፍጥነት መላቀቅ ካልቻሉ ገና ከብዙ ጉዳዮች ጋር መላተማቸው አይቀርም ። በርግጥም በኢትዮጽያና አፍሪካ ባርኔጣ ዓለምን መምራት አይቻልም - ባርኔጣው ካልተስተካከለ ::


Saturday, October 14, 2017

የ « ማዕቀብ » መሳጭ ሀሳቦች


« ማዕቀብ » ከእንዳለጌታ ከበደ ግሩም ስራዎች አንደኛው ነው ። መጽሐፉ በዋናነት ‹ ዴሞክራት ገዢዎቻችን › በድርሰት ፣ ደራሲያንና ተደራሲያን ላይ ስላስከተሉት አሉታዊ ተጽዕኖ ይተርካል ። ከዚያ በመለስ የተመረጡ ደራሲያንና መጻህፍት ሻጮችን የህይወት ውጣ ውረድ ያመላክታል ።

በመጽሐፉ ከአዳዲስ መረጃዎችና ሀሳቦች ጋር እንተዋወቃለን ፤ ከመሳጭና ሞጋች ሀሳቦች ጋር እንፋጠጣለን ። በመሳጭ ሀሳቦች እየተብሰከሰክን ከሞጋቾቹ ጋር የከረረ ምናባዊ ምልልስ እናደርጋለን ።

ከተነሱት ሞጋች ሀሳቦች አንዱ የአቶ መለስ ዜናዊ ልቦለድ ደራሲነት ጉዳይ ነው ። አቶ መለስ በብዕር ስም ‹ መንኳኳት ያልተለየው በር › እና ‹ ገነቲና › የተሰኙ ሁለት መጻህፍትን ለንባብ አብቅተዋል ። እንዳለጌታ ተማሪ በነበረበት ወቅት አንድ ተጋባዥ መምህር ስለ ትግርኛው ስነጽሁፍ የማብራራት እድል ያገኛሉ ። እኚህ ምሁር « በአማርኛው ስነጽሁፍ በቋንቋ ፣ በጭብጥ ፣ በአጻጻፍ ቴክኒክ ታዋቂ የሆነው ዳኛቸው ወርቁ እንደሆነ ሁሉ የትግርኛው ዳኛቸው ደግሞ መለስ ዜናዊ ነው » በማለት ሃሳባቸውን ያጠቃልላሉ ።

ሲጀመር በዳኛቸው ላይ የተሰጠው ዳኝነት ትክክል አይመስለኝም ። እንዳለጌታ እንደሚለው ደግሞ መለስን እንደልቦለድ ደራሲነት ማወቅ እና ማሰብ ይከብዳል ። ደራሲ የደራሲን ህይወት ያውቃል ... ይረዳል ... ባይረዳ እንኳ ያበረታታል ... ጥበብ እንዲያድግ ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል ። የነበሩ ቤተመጻህፍትን እንዲጨምሩ እንጂ እንዲጠፉ አያደርግም ። ሰውየው በስልጣን ዘመናቸው ለደራሲያን ሲቆረቆሩ አልታየም ። በአንድ ወቅት አስታዋሽ ስላጡ አንጋፋ ደራሲያን ሲጠየቁ ከአንድ አርሶአደር ለይተን አናያቸውም ነበር ያሉት - በርግጥ ከአድካሚ ስራ ጋር የሚተዋወቅ ደራሲ ደራሲነትን በዚህ መልኩ ብቻ ነው የሚረዳው ? እናም ሰውየው ስለጭብጥ እና ገጸባህሪያት ቀረጻ ይበሰለሰላሉ ብሎ ማሰብ ቁንጫ ቆሞ ሲቀድስ ፣ አህያ ሞቶ ጅብ ሲያለቅስ የመስማት ያህል ነው ይላል - እንዳለጌታ ።

በርግጥ ደራሲያን እሳቸው ‹ መንኳኳት ያልተለየው በር › እንዳሉት የድርሰት ስያሜ ሁሌም ሃሳብ እንዳንኳኳ የሚኖር ነው ። እሳቸው የቤተመንግስት በር ወለል ብሎ ከተከፈተላቸው በኋላ ሰለተዘጉ በሮች አለማሰብ ፍትሃዊ አይሆንም - በር የሚያንኳኳውን እንዳልሰማ መዘንጋት ፣ ባስ ካለም በውሻና በጥበቃ ማባርረ ከባለ ብዕረኛ አይጠበቅም ።

ሌላኛው ሞጋች ሀሳብ ሳንሱር ዛሬም ቢሆን የለም ማለት ይቻላል ወይ የሚለው ጉዳይ ነው ። ሳንሱር በአዋጅ በግልጽ ይደንገግ እንጂ በውስጥ ከሳንሱር የሚተካከሉ አሰራሮች አሉ ።

ሜጋ የመጻህፍት ማከፋፈያ ስራው መጽሐፍ በአደራ ተቀብሎ ማሰራጨት ቢሆንም ይዘታቸውን እየገመገመ የሚመልሳቸው ስራዎች አሉ ። ይህ ቁልጭ ያለ እውነት ነው ። ማተሚያ ቤቶች ህትመት ከጀመሩ በኋላ የሚቋረጡ ስራዎች አሉ ። ይህም እንዳይታተሙ የሚል ቀጭን የቃል መመሪያ ከነጌቶች ስለሚደርሳቸው ነው ። አንዳንድ ማተሚያ ቤቶች የመንግስትን ቅጣት በመፍራት ያተሙት መጽሐፍት ጀርባ ላይ ድርጅታቸውን ከመጻፍ ይቆጠባሉ ። 

ፓለቲካ ነክ ፊልሞች ከተሰሩ በኋላ እንዳይተላለፉ ታግደዋል ። የቴዲ አፍሮና የአንዳንድ ሙዚቀኞች ስራ በመገኛኛብዙሃን እንዳይተላለፉ ተደርጓል ። ዝግጅት አጠናቀው መድረክ የጀመሩ ቲአትሮች መጋረጃ ተዘግቶባቸዋል ። ጋዜጦች በጻፉት ጉዳይ መጠየቅ ሲገባቸው ገና ማተሚያ ቤት እንደደረሱ ቀኝ ኋላ ዙር ተብለዋል ።
ታዲያ ይህ ሁሉ ጉዳይ ክፍል ሁለት ሳንሱር ነው የሚባለው ወይስ የዚያኛው ሳንሱር ሁለተኛው ገጽታ ? ሀገሬው አጠናክሮ ሊወያይበት የሚገባ የቤት ስራ ይመስለኛል ።

አንዳንድ መሳጭ ሃሳቦችን ደግሞ እንመልከት ።

በርግጥ የዳኛቸው ወርቁ ‹ አደፍርስ › አከራካሪ ስራ ነው ። ለዚያም ነው አንባቢያን በብዙሃን ድምጽ ጥሩነቱን መመስከር የተሳናቸው ። ደራሲው ግን ጠመንጃ ባነገበው አንባቢ አንጻር ጦርና ጋሻ ይዞ ቆመ ። እጅና እግር ለሌለው መጽሐፍህ አምስት ብር አይገባውም እያለ በሚዘምተው ተደራሲ ፊት « ዋጋውን አስር ብር አድርጌብሃለሁ ! » ሲል የተሳለ ውሳኔውን እንደ ጦር እየነቀነቀ አሰማ ። ታዳሚውና ነጋዴው የጉድ አገር ገንፎ እያደር ይፋጃል አሉ ።

ቆይቶ ብቅ አለና ደግሞ አንባቢው ምን እንደሚል ጠየቀ ። ማንበብ ስላልቻለ ምን ሊል ይችላል ሲሉ ነጋዴዎች መለሱ ፤ ቅናሽ እንዲያደርግም ሃሳብ አቀረቡ ። ዳኛቸው ጦሩን ነቅንቆ እረ ጎራው አለ ፤ እረ ወንዱ አለ ። የጀግንነቱን ልክ ለማሳየትም ዋጋው ወደ 15 ብር ከፍ ማለቱን አበሰረ ። በአንባቢውና በደራሲው መሃል እንደ አሸማጋይ የቆሙት ነጋዴዎች ማሰራጨት አንደማይፈልጉ ነገሩት ። ዳኛቸው ከፉከራ በላይ ተቆጣ ። ጦሩን መሬት ላይ ቸንክሮ « ንሳ ! » ሲል ትዕዛዙን አሰማ « ከእንግዲህ መጽሃፍቶቼን ለማንም እንዳትሽጥ ! ያሰራጨሃቸውን በሙሉ ሰብስበህ አስረክበኝ ! »

ማንም ያልጠበቀው ሃሳብ ነበር ። የኢትዮጽያ ደራሲ ነጋዴ ዋጋ ቀንስ ሲለው የሚቀንስ ፣ ኮንሳይመንት ጨምሯል ሲሉት እሺ የሚል ፣ የወረቀት ክምርህ ስላልተሸጠ ይዘህ ጥፋ ሲባል ተሽክሞ የሚሮጥ ነው ። ይሄኛው ደራሲ ግን ነጋዴውን የሚያሽቆጠቁጥ ሆነ ፣ ይሄኛው ደራሲ አንባቢ ካልገባው መንገዱን ጨርቅ ያድርግለት የሚል ሆነ ። ይሄኛው ደራሲ ፍጹም አፈንጋጭ ነው ። ይሄኛው ደራሲ በክብሩም ሆነ በመንፈስ ልጁ ላይ የመጣን ጥቃት ለመመከት ቆርጦ የተነሳ ነው ። ይሄኛው ደራሲ የኢትዮጽያዊያንን ለንቋሳ አንባቢነት እና እውቀት የሚራገም ሆነ ። ምንም ሳይፈራና ሳይጠራጠር ቀጥታ ወደ ህዝቡ የሚተኩስ ሆነ « እኔን ለመረዳት 20 አመት ይቀርሃል ! » እያለ ። አደፍርስ የፈለገ ባይመች የዳኛቸው ልበ ሙሉነት ግን ይደላል ባይ ነኝ ።

በኢትዮጽያ ስነጽሑፍ ታሪክ ትልቅ  ቦታ ከሚሰጣቸው ደራሲያን መካከል አንዱ ብርሃኑ ዘሪሁን ነው ። ይህ ደራሲ በርካታ ስራዎችን ቢያቀርብልንም  በርካታ ስራዎች መስራት በሚችልበት እድሜው ላይ ነበር /54 / ያለፈው ።

አሁን እኔ ማውራት የፈለኩት ሰለ ብርሃኑ ሳይሆን ብርሃን ስለፈጠረችለት ሚስቱ ነው ። ስለ ብርሃኑ ምርጥ ባለቤት ስለ ወ/ሮ የሺ ። ዘወትር የብርሃኑ አምሽቶ መምጣት ያሰጋት ሚስት አንድ ነገር እንዳይሆን በመፍራት መጠጡን እንዲተው ትጨቃጨቅ ነበር ። እሱ ግን በደሙ ስለተዋሃደ ያለጂን ብእር ማንሳት አልቻለም ። አልኮል እያጣጣሙ  ከ 10 በላይ ግሩም መጻሕፍትን መድረስ በራሱ ገራሚ ነው ። ምክንያቱም ለብዙዎች አልኮል እንቅልፍ መጥሪያ እንጂ ለስነጽሑፍ ከራማ መዘየጃ ሲሆን አልታየምና ።

ግራ ቢገባት ጂን እየገዛች ቤት ውስጥ ትቀዳለት ጀመር ፤ አላስደሰተውም ። ምነው ? ብትለው ብቻዪን እንዴት እጠጣለሁ ? የመጠጥ ቤት ድባብ ያስፈልገኛል አላት ። ፈተና ሆነባት ። ጎረቤት እየጠራች ቤቷን እንደ ቡናቤት አታሟሙቀው ነገር ሃብት ይፈልጋል ። ቡቡዋ ሚስት መንገድ ወድቆ ከሚቀር በሚል ‹ እኔ አጣጣሃለሁ › አለችው ። ለእሱ ብላ የጠላችውን ወደደች ። ቀስ በቀስ ጨዋታውን ለመደች :: ምን ያደርጋል ታዲያ ታላቁ ደራሲ በዚሁ ጦስ ከሞተ ጥቂት ቆይቶ የእሷም ጉበት መበላሸቱ ተነገራት ። በአንድ በኩል የባለቤቷ ሀዘን በሌላ በኩል የራሷ ህመም ተባብረው ገደሏት ።

ለባሏ ብላ መስዋዕት ሆነች ። በኢፍትሃዊ መንገድ ተቀጣች ። የደራሲ ሚስቶች ታይፕ በመምታትና በመናበብ ፣ ቡና በማፍላትና ጋቢ በመደራረብ ሲተጉ ነው የምናውቀው ። የሺ ግን ለእነዚያ ለሚያምሩ ድርሰቶች ሻማ ሆና ቀለጠች ። የዓለም አስደናቂ ስራዎች መመዝገቢያ መጽሐፍ ያላየው ታሪክ ።

ማዕቀብ ብዙ አዲስ መሳጭ ታሪኮችን ይዛለች ። ስብሃትና ባለቤቱ ዋሴ በተባለው ህመምተኛ ልጃቸው እንዴት እንደተሸነፉ ... አዲሱን መጽሐፌን አይቼውና ዳብሼው ልሙት እያሉ በጉጉት ስላለፉት ማሞ ውድነህ እና ስለሌሎችም ተረክ አላት ። ማዕቀብ የአዝናኝ መልኮችም ባለቤት ናት ። አድሃሪያን በህይወት ብቻ ሳይሆን በልቦለዱ አለምም መኖር አይፈቀድላቸውም ተብሎ በግድ ስለተገደሉት ገጸባህሪም ትሰማላችሁ ። ሰው ሲሞት ይናዘዛል ፤ ስብሃት ከመሞቱ በፊት እንደምንም ተነስቶ የተናገረው ምን ይመስላችኋል ?

« እኔ የምለው መለስ ዜናዊና ሰይፉ ፋንታሁን አሁንም በኢትዮጽያ ህዝብ ላይ እየቀለዱበት ነው ወይስ አዲስ ነገር አለ ? »
ሃሃሃሃሃሃሃሃ .... ‹ ማዕቀብ › የሌለው ንግግር ይልሃል ይሄ ነው !



Monday, September 25, 2017

ደራሲው ጋዳፊ ለምን ሀሳቡን አልሆነም ?




የሊቢያው መሪ ሙአመር ጋዳፊ ፖለቲከኛ ፣ ሃሳብ አመንጪ እና ደራሲ ነው ። በረጅም የስልጣን ዘመን ቆይታው Escape to hell and others , My vision እና The Green Book የተሰኙ ሶስት ተጠቃሽ መጻህፍትን ለዓለም አበርክቷል ።

አዲስ የፖለቲካ ፍልስፍናውን በመጽሐፍ መልክ ማሳተም የጀመረው በ1975 ነበር ። የዴሞክራሲ ችግር መፍትሄ ፣ የኢኮኖሚ ችግር መፍትሄ እና የሶስተኛው ዓለማቀፍ ቲዎሪ ማህበራዊ መሰረቶች የሚሉ ሶስት ጥራዞችን በተለያዩ ግዜ ጽፏል ። ኋላ ላይ እነዚህን ጥራዞች አንድ ላይ በመሰብሰብ አረንጓዴው መጽሐፍ በሚል ለንባብ አብቅቷቸዋል ።

አረንጓዴው መጽሐፍ ዓለምን ብዙ ያነጋገረና ያከራከረ ስራ ነው ። ይህን መጽሐፍ የተማሩበት የሊቢያ ወጣቶች ብቻ አልነበሩም ። በፈረንሳይ ፣ ምስራቅ አውሮፓ፣ ኮሎምቢያ እና ቬንዚውላ ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች ተወያይተውበታል ፤ አውደጥናት ተካፍለውበታል ።

ጋዳፊ የፍልስፍና ውሃ ልኩን በአረንጓዴው መጽሐፍ ለማሳየት ሞክሯል ። በተለይ የምእራቡ ዓለም የዴሞክራሲ፣ ኢኮኖሚና ፖለቲካዊ አስተምህሮ ጠማማ መሆኑን መነሻ በማድረግ የችግሮቹን መፍትሄ በአማራጭ አተያይ / ሶስተኛው አለማቀፍ ቲዎሪ / ለመተንተን ሞክሯል ።

ጋዳፊ በዚህ ጥራዝ ብዙ ርእሰ ጉዳዮችን ነው የመዘዘው ። በመጀመሪያ ክፍል ምርጫን ፣ የተወካዮች ም/ቤትንና ህዝበ ውሳኔን በእጅጉ ይኮንናል ። እንደርሱ እምነት ዴሞክራሲ የህዝቦች ስልጣን እንጂ የጥቂት እንደራሴዎች ሃብት አይደለም ። ህዝብን እንወክላለን ብለው በፓርላማ በሚሰበሰቡ አባላት ዴሞክራሲ እውን ሊሆን አይችልም ምክንያቱም እነሱ ከተመረጡ በኋላ ለራሳቸው ጥቅም ነው የሚንቀሳቀሱት ። በተለይ ፓርላማው በአንድ ፓርቲ የተዋቀረ ከሆነ የአሸናፊ ፓርቲ ፓርላማ እንጂ የህዝብ ፓርላማ መባሉ አግባብ አይደለም ። ጋዳፊ የወቅቱን የእኛ ሀገርን ፓርላማ ቀድሞ ነው የተቸው ማለት ነው ። እውነተኛው ዴሞክራሲ የሚገኘው በቀጥተኛው የህብረተሰብ ተሳትፎ ነው ። እውነተኛ ዴሞክራሲ ተግባራዊ የሚሆነው ብዙሃኑ በህብረት ወጥቶ ህዝባዊ ኮሚቴ እና ታላቅ የመማክርት ጉባኤ ሲዋቀሩ ነው ። ህዝበ ውሳኔም ቢሆን / Referendum / ዴሞክራሲን የማጭበርበሪያ ዘዴ እንደሆነ ጽፎታል ። ‹ አዎ › ወይም ‹ አይ › ብለው እንዲመርጡ የሚገደዱ ዜጎች ነጻ ሃሳባቸውን እንዲገልጹ አይደረግም ። በመሆኑም ይህ አይነቱ አሰራር ጨቋኝና አምባገነናዊ ነው ሊባል የሚገባው ።

ፕሬስንና ሃሳብን በነጻነት መግለጽን አስመልክቶም የግለሰቦችና የቡድኖች ያልተገደበ መብት እንደሆነ ይዘረዝራል « ፕሬስ ማለት ማንኛውም ሰው ራሱንና አስተሳሰቡን የሚገልጽበት ነው ፣ ሌላው ቀርቶ እብደቱን ጭምር ። የዚህ ሰውየ እብደት የሌላ ሰው ወይም ሰዎች እብደት ነው ተብሎ መቆጠር የለበትም ። በመሆኑም በጋዜጦች የሚወጡ አስተያየቶችን የህዝብን ሃሳብ አደርጎ ጥያቄ ማንሳት መሰረተ ቢስ ነው ፣ ምክንያቱም ጋዜጦች ያተሙት የዚያን ሰውየ አስተያየት ነውና »

በሁለተኛው ክፍል ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተዳሰዋል ። እንደ ጋዳፊ ሃሳብ ደመወዝተኞች ለቀጠራቸው ግለሰብ ግዜያዊ ባሪያዎች ናቸው ። መሰረታዊ ፍላጎቶች/ ቤት ፣ ትራንስፖርት ወዘተ / በግለሰቦች ቁጥጥር ስር መዋል የለባቸውም ምክንያቱም ብዝበዛንና ባርነትን ያመጣሉና ። በሶሻሊስት ማህበረሰብ ውስጥ ሰዎች የሚሰሩት በሽርካነት እንጂ ለደመወዝ ብለው አይደለም ። በሌላ ሠው ቤት የሚኖሩ ሰዎች ማለትም ኪራይ የሚከፍሉም ሆነ የማይከፍሉት ነጻነት አላቸው ማለት አይቻልም ። መሬት የማንም ሃብት አይደለም ነገር ግን ማንኛውም ሰው በመሬት ላይ ማንንም ሳይቀጥር የተለያዩ ስራዎችን ማከናወን ይችላል ። የቤት ሰራተኝነት የዘመናዊው ዓለም ባርነት ነው ። እናም የቤት ስራ መከናወን ያለበት በነዋሪዎቹ ነው ።

ሶስተኛው ክፍል ማለትም የሶስተኛው ዓለማቀፍ ቲዎሪ ቤተሰብን ፣ ጎሳን ፣ ብሄርን ፣ ሃገርን ፣ አናሳ ብሄርን ፣ ሙዚቃን ፣ ስፖርትና ሴቶችን ይዳስሣል ። ሌላው ቀርቶ ጥቁር ህዝቦች ወደፊት አለምን / ቀደም ብሎ ቢጫዎች ፣ አሁን ደግሞ ነጮቹ እየገዙ ነው / ይመራሉ ይላል ። ስፖርት ልክ እንደ ጸሎት ግላዊ ጉዳይ መሆኑን ይገነዘባል ። ቦክስ እና ነጻ ትግል ግን የሰው ልጅ ገና ከአረመኔነቱ አለመላቀቁን የሚያሳዩ ድርጊቶች ናቸው ።

ጋዳፊ ቤተሰብ ከመንግስት የበለጠ አስፈላጊ ተቋም እንደሆነ በሚከተለው መልኩ ያምናል  « ቤተሰብ እንደ እጽዋት ነው ። ቅርንጫፍ ፣ ግንድ ፣ ፍሬና ቅጠል ያለው ። እጽዋት የመነቀል ፣ የመድረቅ እና የእሳት አደጋ እንደሚያጋጥማቸው ሁሉ ቤተሰብም ህልውናው በብዙ ነገሮች ይፈተናል ። ያበበ ማህበረሰብ ማለት ግለሰቦች በቤተሰብ ውስጥ ቤተሰቦች ደግሞ በማህበረሰብ ውስጥ ማደግ ሲችሉ ነው ። ቅጠል ለቅርንጫፍ ፣ ቅርንጫፍ ለዛፍ እንዲሉ ግለሰብም በቤተሰብ ውስጥ የጠነከረ ትስሥር አለው ። ግለሰብ ያለ ቤተሰብ ትርጉም የለውም ። የሰው ልጅ እንደዚህ አይነቱን ትስስር ከጣለ ስር የሌለው ሰው ሰራሽ አበባ ነው የሚሆነው »

ጋዳፊ ለጎሳ መራሹ የአፍሪካ ህዝብም ጠቃሚ ስንቅ ያቀበለ ይመስላል ። ማህበራዊ ትስስር ፣ አንድነት ፣ ቅርበትና ፍቅር ከጎሳ ይልቅ በቤተሰብ ይጠነክራል ፤ ከሀገር ይልቅ በጎሳ ይጠነክራል ። ከዓለማቀፍነት ይልቅ በሀገር ይጠነክራል ። ጎሳ ትልቅ ቤተሰብ ነው ... ለጎሳ ትልቁ መሰረት ደም ነው ... ጎሳ አባላቱን የሚከላከለው በመበቀል ነው ። ጎሰኝነት ናሽናሊዝምን ያጠፋል ፤ ምክንያቱም የጎሳ ታማኝነት ከሀገር ታማኝነት የላቀ ነው ። በሀገር ውሰጥ የሚገኙ ጎሳዎች የሚጋጩ ከሆነ ሀገር ችግር ውሰጥ ይወድቃል ። ብሄርተኞች ፍላጎታቸውን በሃይል የሚገልጹ ከሆነና የራሳቸውን ፍላጎት የሚያሰቀድሙ ከሆነ ሰብዓዊነት ላይ አደጋ ይፈጠራል በማለት ስጋቱን ክፍላጎቱ ጋር አዛምዶ መርሁ ላይ አስፍሮታል ።

የአንድ ሀገር ህዝቦች የሚበየኑት በቦታው ላይ በመፈጠራቸው ብቻ አይደለም ። ይህ መሰረታዊ ነገር ሊሆን ይችላል ። ከዚህ በተጨማሪ ግን ለረጅም ግዜ በአንድ ላይ በመኖር የጋራ ታሪክ ፣ ቅርስ እና ተመሳሳይ እጣ ፈንታ ሲኖራቸው ነው ። ህዝቦች ከደም ትስስር ይልቅ ሀገራዊ አንድነትና የኔነትን በጋራ ይዛመዳሉ ።

ሴቶች ከወንዶች እኩል አይደሉም በሚባለው ብሂል ጋዳፊ አይስማማም ። ሴቶች እኩል መስለው የማይታዩበትንም ሳይንሳዊ ምክንያት በዝርዝር አስቀምጧል ። ሴቶች አንስታይ ወንዶች ተባእታይ ናቸው ። ባለሙያዎች እንዳረጋገጡት ሴቶች በየወሩ ደም ሲያዩ ወንዶች አይኖራቸውም ። ሴት ደም ካላየች ነፍሰጡር ናት ። ነፍሰ ጡር ስትሆን ለአመት ያህል ንቁ ተሳታፊ አትሆንም ። ልጅ ስትወልድ ወይም ሲያስወርዳት ደግሞ በ ፒዩፐሪየም / Puerperium / ትሰቃያለች ። ወንድ ይህ ሁሉ ስቃይ አይደርስበትም ። ከወለደችም በኋላ ለሁለት አመታት ታጠባለች ። ጡት ማጥባት ማለት ሴት ከልጅዋ የማትለያይበት በመሆኑ አሁንም ሌሎች እንቅስቃሴዎቿ ይቀንሳል ። በመሆኑም ሌላን ሰው ለመርዳት ቀጥተኛ ሃላፊነት መውሰድ በእሷ ላይ ይወድቃል። ያለ እርሷ ብርቱ ድጋፍ ያ ፍጡር ይሞታል ። ወንድ በሌላ በኩል አያረግዝም ፣ አያጠባም ::

ጋዳፊ በአረንጓዴው መጽሐፍ ታላላቅ ሀሳቦችን አንስቷል ። በክፍል አንድ ስልጣን የህዝብ መሆኑን እንመለከታለን ። ግለሰቦች ሊያብዱ ይችላሉ ይህ ማለት ግን ማህበረሰቡ አብዷል ማለት አይደለም በሚለው ነጥብ ዙሪያ ፕሬስ ሃሳብን መግለጫ ነጻ መሳሪያ መሆኑ ተሰምሮበታል ። በሁለተኛው ክፍል ለኢኮኖሚው ችግር መፍትሄው ሶሻሊዝም መሆኑ ተቀምጧል - በእያንዳንዱ ቤት ወስጥ የሚኖር ዜጋ የቤቱ ባለቤት እንጂ ጭሰኛ መሆን የለበትም የሚል የሚደላ አቋም ይታያል ። የአስቂኝም አስደናቂም ስብስብ በሆነው ሶስተኛ ክፍልም ሴት ከወንድ ታንሳለች ማለት የተፈጥሮ ህግን መካድ ነው የሚል ጠንካራ አቋም ይገኛል ።

ደራሲው ጋዳፊ ከፖለቲከኛው ጋዳፊ ጋር ተጣጥሞ ቢዘልቅ መልካም ነበር ። በተለይ በዙሪያህ የተኮለኮሉ ሰዎች / የተለያዩ ፍላጎት ያላቸው / የስብእና አምልኮ እየገነቡልህ ሲሄዱ ዝም ካልክ መቀበሪያህ እየተማሰ መሆኑ ማወቅ ይገባል ። ። ጋዳፊ መርሁ እንዲዘመር እንጂ እንዲሰራበት ለማድረግ ያልቻለበት አንደኛው ምክንያትም ይሄው ነው ። ጹሑፍህን ደጋግመህ በፍቅር ታነበዋለህ እንጂ ደፍረህ አርትኦት አታደርገውም ። በዚያ ላይ ፍልስፍናን ለማሰብና ለመራቀቅ እንጂ ሆኖ ለመኖር ይከብዳል ።




Wednesday, September 13, 2017

« በፍቅር ሥም » ከጥቅል አደረጃጀት አንጻር



የአለማየሁ ገላጋይን « በፍቅር ስም » ለመተቸት የሚነሳ ሀያሲ በምን ርዕሰ ጉዳይ ስር ልጻፍ ብሎ የሚጨነቅ አይመስለኝም ። መጽሐፉ በዘርፈ ብዙ የሃሳብና የትርክት ሃዲዶች ላይ ስለሚጋልብ አንዱን የታሪክ ሰበዝ መዞ ምልከታንና ሙያዊ ትንተናን ማዋሃድ ይቻላል ።

እኔ እንግዳ በመሰለኝ የመዋቅር አደረጃጀት እና ፍሰት ላይ አተኩራለሁ ። ደራሲው እኔ በተሰኘው የአተራረክ ስልቱ ጽሁፉን የሚጀምረው « በሴት የመከበብን ጥቅም የምናውቀው እኔና ጠቢቡ ሰለሞን ብቻ ነን » በማለት ነው ። የታሪኩ አባት ትንሹ ‹ ታለ  › ነው ። ታለ ይህን የሚነግረን በጥቅሙ በረከት ፈግጎ ነው ። ወጣቱ ታለ በመጽሐፉ መዝጊያ ላይ በተመሳሳይ ዜማ የሚከተለውን ይናገራል « የኛ አስር ደቂቃ በእርሱ / ቹቹ / ስንት እንደሆነ የማውቀው እኔ ነኝ » ታለ ይህን የሚነግረን በህመምና ፀፀት ውስጥ ሰምጦ ነው ።

ታለ የፍቅርና ፀፀት ጥለትን እየለበሰና እያወለቀ የሚዘልቅ ገጸባህሪ ነው ። ደራሲው ይህን የታሪክ ጉዞ የሚያሳየንና የሚነግረን በተለመደው የገጸባህሪ የበቀል/አሸናፊነት ፍትጊያ አይደለም ። የታሪኩ መረማመጃዎች ጥቅል ሰብዕናዋች/ ማንነቶች ናቸው ። አንዱ ጥቅል ቢዘንና አንጓቼ / ባልና ሚስት / ናቸው ። ይህ ጥቅል አውቶብስ በመሰለው ቤተሰባዊ ጎጆ / በነገራችን ላይ የቤተሰቡ መኖሪያ በገጽ 22-23 በአስቂኝ መልኩ ተገልዿል / ውስጥ እንደ ሹፌርና አውታንቲ ሊቆጠር የሚችል ነው ። ሹፌርና ረዳት በሳንቲም መጋጨታቸው አይደንቅም ። አንድ ቤት የሚኖሩ ባልና ሚስት ግን ወንድን ልጅ / ታለን / የግላቸው ለማድረግ የማያባራ ጦርነት መከፈታቸው ያልተለመደ / bizarre / ነው ።

« እግዚአብሄር የሰጠኝን ወንድ ልጅ የገዛ ሚስቴና ልጆቼ ነጠቁኝ » ይላል አባወራው
« ከመላእክት እስከ አጋንንት ደጅ የረገጥኩበትን ልጄንማ አልተውም » ትላለች እማወራ

በዚህ መነሻነት ጥቅሉ እየተፈታ ሌላ ግዜ እየተተረተረ ታሪኩንና የታሪኩን ማህበረሰብ ያናጋዋል ። በስድብና ሽሙጥ አረር ይጠዛጠዛሉ ። የቅናትና ጥርጣሬ ዳመራ በየግዜው ይለኮሳል ። ሰባት ሴት ልጅ መውለዳቸው ያልተዋጠላቸው አባወራ ሰባት ስድቦችን ነው የወለድኩት እስከማለት ይደርሳሉ ። በመልክ ለየት ያሉ ልጆችን ሳይቀር በተጠየቅ ይሞግቷቸዋል ። ጥቁሯን አበባ « ለመሆኑ የአፍሪካ ህብረት ሲቋቋም ተረግዛለች ? » ቀይዋ ስምረትን « መልኳ ሁሉ የእንግሊዝ ነው ፣ እኔ የምለው እንግሊዝ ሲመጣ ነው የተወለደችው ? » ረቂቅን ደግሞ « ይሄ ባኒያንኮ ያልደረሰበት ቦታ የለም » በማለት የነገር ጅራፋቸውን ይተኩሳሉ ። ባልና ሚስቱ በሚታክት መልኩ ይናቆሩ እንጂ ችግር በመጣ ግዜ እንደ ማግኔት ይፈላለጋሉ ፣ ጥቅሉ ማንነት ውስጥ ለአደባባይ አይናፋር የሆነ መተሳሰብ አለ ።

ሁለተኛው ጥቅል ሰባቱ ሴቶች ልጆች ናቸው ። አውቶቡስ በመሰለው ቤት ውስጥ ተሳፋሪ ይምሰሉ እንጂ መኪናው እንዳይገለበጥ ወይም ተበላሽቶ እንዳይቆም ምሶሶ ሆነው የቆሙ ናቸው ። ለምሳሌ የአቶ ቢዘን ጡረታ ስለማያወላዳ እናታቸውን በጉሊት ስራ ይረዳሉ ። በተቃራኒው አባታቸው ጠጅ ቤት ከሰው ጋ ሲጣላ ተሰብስበው ሄደው ወግረው በድል ይመለሳሉ ። ይህም የቢዘን ፍርጎ የሚል ስያሜ ቢያሰጣቸውም አባታቸው በሰፈሩና በየካቲካላው ቤት እንዲፈራ አድርጓል - ከሴት ልጅ ባህሪ አኳያ ግን ያልተለመደ ነው ።

ይህ ጥቅል ገጸባህሪ ለየት የሚልበት ሌላም ጉዳይ አለው ። ቤተሰባቸውን ያፍቅሩ እንጂ ለሌላው እምብዛም ፍቅር የላቸውም ። በተለይ ወንድን በማባረር ተመሳሳይ አቋም ነው ያላቸው ። የርስ በርሳቸው ምክር « እንግባ ቢልሽ አትግቢ ! እንውጣ ቢልሽ አትውጪ ! » ብቻ ነው ። ፍቅር ተፈጥሯዊ ጸጋ ስለመሆኑ ፊት አይሰጡም ። ድንገት ከመካከላቸው አንዷ ፍቅር ሽው ያለባት ግዜ እንኳ መቀመጫ ሲያሳጧት ይታያል ። ወንዳወንዴዋ ቹቹ እንኳ ሰለወደዳት ልጅ እንዲወራ አትፈቅድም ። ይህ ከሴት ልጅ ስስ ልቦናና ተቃርኗዊ ትስስር አንጻር ያልተለመደ ይመስላል ።

ሶስተኛው ጥቅል አራቱ ስፖርተኞች ናቸው ። ደራሲው በዚህ ሃዲድ እንድንጓዝ የፈለገው የልጅነትን ሌላኛው ገጽታ እንድንመለከት ብቻ አይደለም ። እንደ ሽክና አይነት ቀልደኞች ቆምጫጫውን የታሪክ ጉዞ እንዲያለሳልሱት ብቻ አይደለም ። እግርህን ከፍተህ የምትሄደው ጭገርህን ስላላበጠርክ ነው እያለ በግድ መጣላት የሚፈልገውን የ ‹ ቲኔጀር › ሞት አይፈሬነት ለመጠቆም ብቻ አይደለም ። የወንድነት ክትባት የሚፈልገውን ታለን ለማከምም ጭምር ነው ። ስፖርተኞቹ ሰፈር የምታደርሰው ወንዳወንዴዋ ቹቹ መሆኗን ስናስብ ግን በቤተሰቡ ውስጥ ያለውን ሁለተኛ ‹ ቢዛሪ ›ጉዳይ እናጤናለን ።

በሌላኛው ጥቅል አደረጃጀት ውስጥ የተቀረጹት ሶስቱ ወታደሮች ናቸው ። ወታደሮቹ በአፋዊ ገጽታቸው ይለያዩ እንጂ በሀገር ፍቅር ጽናታቸው አንድ ናቸው ። ብዙ ግዜ ለመዝመትና ለመሞት የቆረጡ ናቸው ። ተሸንፈው እንኳን አንዲት ህገር በሚለው መንግስቱ ስም ለመለመን አይሳቀቁም ። መንግስቱን ሳይሆን ታሪካዊ መርሁን አሻግረው ያያሉ ።

የወታደሮቹ ሌላኛው ውክልና ሀገር የገባችበትን ውጥንቅጥ ፈተና ማሳየት ነው ። በማህበረሰቡ ውስጥ አፈሳ ያስከተለውን የፍርሃት ቆፈንና የአስተዳደር መናጋት እንመለከታለን ። ፍርሃት ምንያህል ሀገራዊ ኩይሳ እንደሰራ ለማውቅ የአእምሮ ዝግምተኛው ቹቹ እንኳ መደበቂያ ሲፈልግ መታየቱ ነው ። ሻምበል ጠናጋሻውን ስናስብ ደግሞ ደራሲው ጦር ሰራዊቱ ውስጥ ያነበቡ ፣ የተማሩና ህዝባዊ ፍቅር የተላበሱ ግለሰቦች መኖራቸውን ለመጠቆም ብቻ እንዳልቀረጸው እንረዳለን ። ሻምበሉ ለታሪኩ እንድርድሮሽ መረማመጃነት አገልጋይ ነው ። ሻምበሉ ለታለ ያበረከተው የማይታመን ነገር ግን ጠቃሚ ስጦታ ቀጣዩ ጥቅል ስብእና የደረጀ እንዲሆን አግዟል ።

በዚህ መሰረት ለጥቆ የምናገኛቸው ታለን እና ሲፈንን ነው ። ርግጥ ነው በታለ ውስጥ ቹቹ ፣ በሲፈን ውስጥም ቹቹ አለ ። ቹቹ ‹ ኮመን ዶሚነተር › ነው ። የታለና ሲፈን ፍቅር አይኑን ገልጾ ከፍተኛ ደረጃ / Climax / የደረሰው ሻምበሉ ከከፈለው ጥሎሽ በኋላ ነው ። ጥሎሹ ሲፈን እንድትዝናና ታለ በአዲሱ አለም ላይ አይኑን እንዲከፍት አስችሎታል ።

ሲፈን በርግጥም የአውሊያ ፈረስ ትመስላለች ። ጋልባ ጋልባ ስድስተኛው ጥቅል ገጸባህሪያት ሰፈር የምታደርሰው እሷ ናት ። ደራሲው ይህን በ ‹ ጃክሰኖች › መስሎታል ። አምስቱ ጃክሰኖች የተለያዩ የሙያ ባለቤት ሲሆኑ በሚገናኙበት ጫት ቤት ውስጥ የማያነሱትና የማይጥሉት ርዕሰ ጉዳይ የለም ። እውቀት ጠገብ / ለምሳሌ ከታሪኩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስላለው የአውሊያ ጉዳይ ተነስቶ አጥጋቢ ምላሽ ሲሰጡ ይታያል / ሆነው በሚፈልጉበት የስራ መስክ መሰማራት ያልቻሉትን የሀገራችንን ምሁራን ይወክላሉ ። ተጠየቃዊ ሙግቶች የክብርና የአደባባይ አጅንዳ ከመሆን ይልቅ በየስርቻው የሚጣሉ የጋን ውስጥ መብራት መሆናቸውንም ያሳያል ።

« በፍቅር ስም » በጥቅል ገጸባህሪያት አደረጃጀት ውስጥ ነው የሚያልፈው ። ጥቅሉ እየተፈታ የሚሰበሰብ ፣ እየተሰብሰብ የሚፈታ ነው ። ጥቅሉ ለታሪኩ መጓጓዣ ምንጣፍ ነው ። የጎሉ ተናጥላዊ ባህሪያት ቢኖሩ እንኳ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ጥቅል ውስጥ እንደቀንዳውጣ ወጣ ገባ ማለታቸው አይቀሬ ነው ። ደራሲው ተናጥላዊ ባህሪያትን አጉልቶ ለመለየት የማይረሳ ምልክት ለጥፎባቸዋል ። ለምሳሌ አቶ ቢዘን ባወሩ ቁጥር ‹ ጣ › ይላሉ ። ቹቹ ‹ ቲሽ ! › ማለት ይቀናታል ። የታለ እናት ‹ ኦሆሆይ › በማለት ግርምታቸውን ይተነፍሳሉ ። ሻምበል ሲጠይቅም ሲመልስም ‹ ጥሩ › ን ያስቀድማል ።

እንደ ጥቅልም እንደተናጠልም የሚታየው ታለ ማነው ? ምን ይፈልጋል ? ስንል ወደ ጭብጡ መንደር እንደርሳለን ። በዚህም ረገድ ጥቅል ጉዳዮች ይገኛሉ ። ወንዳወንድነትን ማግኘት በዋናነት ደግሞ አውሊያና ጥንቆላን መዋጋት ። ታለ ህብረተሰቡ « ሴታሴት » ነህ ብሎ ስለፈረደበት ከዚህ የጅምላ ንቀትና ተጽእኖ ለመላቀቅ ያላሰለሰ ትግል ያከናውናል ። ህበረተሰቡ ተፈጥሮውን ተቀብሎ እንኳ እንዲኖር አልፈቀደለትም ። ወንዳወንድ እንዲሆን የተመረጡ ወንዶች ጋር ይውላል ። ወታደር በመሆንና በመሞት ወንድነት የሚገኝ ከሆነ እዘምታለሁ እስከማለት የደረሰ ነው ። የህብረተሰቡን ጥያቄ የተቀበለው ግን ራሱ ህብረተሰቡን በመንቀፍ ነው ። ነቀፌታው ገደብ የለውም እናቱን ፣ አባቱን ፣ ጃክሰኖችን ፣ ሲፈንን ፣ እህቶቹን ፣ ቹቹን ሳይቀር ይተቻል - ያሽሟጥጣል ። ድንኳን መትከልና መንቀል የወንድ ንፍሮ መቀቅልን የሴት ስራ ያደረገው ማነው ? ይላል ። የእንስሣት ሴታ ሴት ይኖር ይሆን እያለ ደግሞ ፈጣሪውን ይሞግታል ።

በሌላ ፊቱ በጥንቆላና ድግምት የእኔን በሽታ ወደ ቹቹ አዙራ ለጥፋተኝነትና ለጸጸት የዳረገችኝ እናቴ ናት በማለት ከእናቱ ጋር የስነልቦና ጦርነት ያካሄዳል ። ሲፈንም ፍቅረኛዬ ሳትሆን በእናቴ እኔን ታገልግል ዘንድ የተመረጠች አውሊያ ናት ብሎ ያምናል ። ሻምበል ይህን ቤተሰባዊ እምነት በማስቀየር የቹቹ በሽታ የአእምሮ ዝግመት ችግር መሆኑን ቢነግረውም አይቀበልም ። ስንት የታገለችለትን እናቱን ፊት ይነሳል ። በርግጥ አውሊያ ልክ እንደ አፈሳው ምን ያህል በሰፈርተኛው እንደሚፈራ እንገነዘባለን ።

ደራሲው በፍቅር ስም ፍቅር አልባ መሆን አለ የሚል ይመስላል ።