በዓለማችን በብዛት እየተነበቡና እየተሸጡ ያሉ መጻህፍት ልቦለዶች አይደሉም ። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የመጀመሪያ ደረጃን
በመያዝ የወርቅ ሃብል እንዳጠለቀ የሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ ነው ። እንደ ጊነስ ወርልድ ሪከርድ መረጃ ከሆነ የሁልግዜ አንደኛ የሆነው
መጽሐፍ ቅዱስ ህትመት ከ 5 ቢሊየን በላይ ይሆናል ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ተከታታይ ተሸላሚነት ላይገርም ይችላል ፣ ምክንያቱም ለአይሁድና ክርስትና እምነት የእምነት መሰረት የሆኑ
ሃሳቦችን የያዘ ግሩም መድብል በመሆኑ ። ይልቅ የሚገርመው ስለሃይማኖት የማይሰብከው መጽሀፍ የዓለማችን ሁለተኛ መጽሐፍ ሆኖ የብር
ሃብል ማጥለቁ ነው ። ርግጥ ነው የመደብ ተጻራሪ የሆኑት ምዕራባዊያን ፓለቲከኞች የ « ማኦ መጽሐፍ ቅዱስ » እያሉ ነው የሚጠሩት
። እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ተከታይ በማፍራቱ ።
ይህ መጽሐፍ ከቢሊየን ኮፒ በላይ ታትሞ ተነቧል ። ሪከርድ ያሰጠው መጠሪያ « የሊቀ መንበር ማኦ ጥቅሶች » የሚል ቢሆንም
ብዙዎቹ እያንቆለጻጸሱ የሚጠሩት « ትንሿ ቀይዋ መጽሐፍ » በማለት ነው ።
ይቺ ትንሽ መጽሐፍ በጥቅስና አባባሎች የተከበበች ትምሰል እንጂ መልዕክቷና ዓላማዋ ከቻይና አልፎ የዓለማቀፉን ማህበረሰብ
ትኩረት መሳብ ችሏል ። አያሌ ምሁራን የቻይናው ህዝባዊ ሪፐፕሊክ መስራች የሆነውን ማኦ « የማይጠግብ አንባቢ » ይሉታል ። ማኦ
እንደ ሆዳም አንባቢነቱ ሆዳም ፀሀፊ ነበር ። ጥሩ ፖለቲከኛ ብቻ ሳይሆን ጥሩ የፖለቲካ ጸህፊ ለመሆኑ On New Democracy እና On Coalition Government የተሰኙ ስራዎቹን
መጥቀስ ይቻላል ። ጥሩ አሳቢ ብቻ ሳይሆን ጥሩ የፍልስፍና ጸሀፊ ለመሆኑ Four essays on Philosophy የተባለውን ስራ ማገላበጥ ይጠቅማል ።
ጥሩ ወታደራዊ መሪ ብቻ ሳይሆን ጥሩ የወታደራዊ ሳይንስ ጥበብ ጸሀፊ መሆኑን The art of war እና On Guerrilla
warfare የተሰኙ
ስራዎቹን ማንበብ ይቻላል ። ማኦ ከ 30 በላይ ስራዎች ሲያበረክት አንደኛዋ ግጥም ነበረች ። ከአብዮቱ በፊት እና ከአብዮቱ በኋላ
በሚል ንኡስ ርዕስ የተከፋፈሉ 36 ግጥሞችን የያዘች መድብል ።
ከሁሉም ታዲያ በአጋጣሚ ገና የወጣችው ቀይዋ መጽሐፍ ናት ። ዋነኛ ምክንያቱም ቻይና ባከናወነችው የባህል አብዮት /
1966- 1976 / ለህዝቡ በተለይም ለቀዩ ዘብ መሰረታዊ መመሪያና ምክር በመሰነቋ ነው ። በነገራችን ላይ ማኦ ያከናወናቸው ሁለት
ታላላቅ ጉዳዮች Great Leap forward እና Cultural revolution ባስከተሉት የረሃብና የግጭት ቀውስ ለበርካታ ሚሊየን
ዜጎች መጥፋትም ምክንያት ሆነዋል ።
በባህል አብዮት ዘመን በተለይ ከመስመር የወጡ ተማሪዎች ‹ አራቱን አሮጌዎች አስወግድ ! › በሚል መርህ አሮጌ ባህል ፣
አሮጌ ልማድ ፣ አሮጌ ወግ እና አሮጌ አስተሳሰቦችን እናስተካክላለን በማለት በከተሞች ላይ ትልቅ ጥፋት አድርሰዋል ። በሌላ በኩል
የማኦ ቀይ መጽሀፍ ያፈነገጡትን በመመለስ ፣ መስመር ውስጥ ያሉትንም ስራቸውን በምን መልኩ አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው ታድጋለች
። ምክንያቱም አብዮት ሲባል የቀድሞውን እያጠፉ ብቻ ንፋስ ወደነፈሰብት መረማመድ አይደለም ። ለዚህም ነው ቀይዋ መጽሀፍ ጠቃሚ
ርዕሰ ጉዳዮችን እያነሳች መንገዱን ያሳየችው ። ኮሙኒስት ፓርቲ ፣ የመደብ ትግል ፣ ጦርነትና ሰላም ፣ ዲስፕሊን ፣ አንድነት ፣
የህዝብና የመከላከያ ሰራዊት ግንኙነት ፣ ካድሬ ፣ የመሳሰሉ ርዕሰ ጉዳዮችን በማንሳት ነገረ አንድምታቸውን ታወጋለች ።
እንዲህ በማለት ።
የመደብ ትግል በሚለው ሃሳብ ስር አብዮትን በሚከተለው ንፅፅር ፍርጥ አደርጎ ነው ያስቀመጠው « አብዮት የራት ፓርቲ አይደለም
፣ አብዮት ወግ መቸክቸክ ፣ ሰዕል መጫጫር ወይም ጥልፍ መስራት አይደለም ። አብዮት አንዱ መደብ ሌላውን ለመገልበጥ የሚያነሳው
ሁከት ወይም ብጥብጥ ነው »
ማኦ አሜሪካ የምትኩራራበትን የአቶሚክ ቦንብ የወረቀት ላይ ነብር ነው በማለት ሀገሬው ስጋት ላይ እንዳይወድቅ ያበረታታል
። የጦርነት ውጤት የሚወሰነው በህዝቦች እንጂ በአንድ ወይም በሁለት አይነት መሳሪያ አለመሆኑን በማስገንዘብ ። ብዙሃንን መጨፍጨፊያ
መሳሪያ ቢሆንም እንደ ቻይና የህዝብ ብዛት ያላቸውን ሀገራት ማሸነፍ እንደማይቻል ነው የሚያስገነዝበው ።
ሰላምና ጦርነት በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ስርም ዓለም ስለሚሰጋበት የሶስተኛው ዓለም ጦርነት አንስቷል ። ሶስተኛው የዓለም ጦርነት
የሚነሳ ከሆነ ለኢምፔሪያሊስቶች የሚሆን ቦታ እንደማይኖር በስሌት በማስቀመጥ ። በአንደኛው ዓለም ጦርነት 200 ሚሊየን ስዎች ሶቪየት
ህብረትን ተከትለዋል ። በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወደ ሶሻሊስት ካምፕ የተቀላቀለው 900 ሚሊየን ህዝብ ነው ። ሶስተኛው ዓለም
ጦርነት ከመጣ ግን አለም ለኢምፔሪያሊስቶች የሚሆን ቦታ እንደሌላት ምስክር ይሆናል ።
አለም በሁለት ርዕዮት በመከፈሏ የተፈጠረውን ብሽሽቅ የሚያጠናክሩ አባባሎችም በስፋት ይታያሉ ። በአለም ላይ ካሉ ቀላል
ነገሮች አይዲያሊዝም እና ሜታፊዚክስ ይገኙበታል የሚለው ማኦ ለዚህ የሚሰጠው ምክንያት ደግሞ ያለምንም ተጨባጭ ግብ ጠቃሚ ያልሆኑ
ዝባዝኬዎችን ማውራታቸው ነው ። ተጨባጩን አለም መሰረት ያደረጉ ሁለት ፍልስፍናዎች ደግሞ ማቴሪያሊዝምና ዴያሌክትስ ናቸው ። ማኦ
ተራማጅና ምክንያታዊ አስተሳሰብ አላቸው የሚላቸውን ሶሻሊዝምና ኮሙኒዝም ከፍ ከፍ በማድረግ ፣ የፊውዳሊዝም እና ካፒታሊዝም ብቸኛው
ቦታዎች ሙዚየሞች መሆናቸውን ይገልጻል ።
ጥሩ ፒያኖ ለመጫወት ሁሉንም ጣቶች በአንድ ግዜ ማንቀሳቀስ አይመከርም ፤ እንደዛ ከሆነ ዜማ ስለማይኖር ። አስሩም ጣቶች
በየተራ በጥሩ ምት እና ቅንብር መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል ። የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትም ችግሮችን ለመፍታት የግድ ፒያኖ መማር እንዳለባቸው
ዘይቤያዊ በሆነ መልኩ አሳስቧል ። ለማኦ ጥሩ መሪነት ከፒያኖ ጨዋታ ጋር ይመሳሰላል ።
ወታደሩና መኮንኑ ፣ ጦር ሰራዊቱና ሲቪሉ ማህበረሰብ ለሀገሩ በፍቅርና በአንድነት ሊቆም የሚችለው የመተሳሰቢያ ድልድዮች
ሲኖሩት ነው ። እነዚህ የመተሳሰቢያ ድልድዮች ደግሞ በዋነነት መዋቀር ያለባቸው በጦር ሰራዊቱ ትከሻ ላይ ነው ። በመሆኑም ጦር
ሰራዊቱ ሶስቱን ደንቦችና ስምንቱን ነጥቦች ተግባራዊ ማድረግ ይጠብቅበታል ይላል ማኦ ።
ሶስቱ ደንቦች የትኞቹ ናቸው ?
1. ሁሉንም ትዕዛዞች በስርዓት ተቀበል
2. ከብዙሃኑ ሰባራ መርፌ ወይም ብጣሽ ክር
እንዳትወስድ
3. የማረከውን ሁሉ አስረክብ
ስምንቱ ትኩረት የሚሰጣቸውስ ?
1. በትህትና ተናገር
2. ለምትገዛው ሁሉ አግባብ ያለው ክፍያ ክፈል
3. የተዋስከውን ሁሉ መልስ
4. ለምታጠፋው ሁሉ ክፈል
5. ህዝብ ፊት አትማል
6. ስብል አታበላሽ
7. ከሴት ጋር አትባልግ
8. ምርኮኛ ላይ የጭካኔ ተግባር አትፈጽም ።
ከማኦ እምነት እና ደንብ የምንማረው ጦር ሰራዊቱ የሃይል አበጋዝ ቢሆንም በጉልበቱ ተማምኖ ዋልጌነትና ሙስና መስክ ላይ
እንዳይጨፍር ዛብ የሚያስፈልገው መሆኑን ነው ። የትህትና እና የፍቅር ተምሳሌት ከሆነ የእውነተኛ ህዝባዊነትን ማዕረግ ከእያንዳንዱ
ቤት በሶጦታ ያገኛል ።
እንደሚታወቀው ማኦ ሀገሪቱን በእንዱስትሪ የቀደመች ለማድረግ The Great Leap Forward መርሃ ግብር ክተት ካለ በኋላ እቅዱ ሀገሪቱ ባጋጠማት አደገኛ ድርቅ ሊከሽፍ ችሏል ። ይህ
ውድቀትም ማኦ ስልጣኑን እንዲያጣ አድርጎታል ። ሆኖም የሀገሪቱ ወጣቶች እሱን በመደገፋቸው እንደገና መነሳት ችሏል ። ወጣቱ የንባብ
ማእከላትን አጠናክሮ በማጥናትና በመከራከር ሌላው ቀርቶ ማንበብ የማይችለው ህብረተሰብ ጋር ተደራሽ በመሆን ትልቅ ሚና ተጫውቷል
። ቀይዋ መጽሐፍ በህዝብ አውቶብስ ውስጥ ሌላው ቢቀር በሰማይ ላይ ሁሉ ይጠና ነበር - የቻይና ሆስቴሶች የማኦን የጥበብ ቃላት ለተሳፋሪያቸው ይሰብኩ ነበር ። ማኦና
ወጣቱ እንደ ጣትና ቀለበት ስምሙ መሆኑ የቻሉት ቀይዋ መጽሐፍ ወጣቱን የሚያቀልጥ ሃሳብ በመያዟ ይመስለኛል ።
እንዲህ በማለት ።
« አለም የናንተ ናት ፣ የኛም ጭምር ። እንደ መጨረሻ ትንታኔ ከሆነ ግን የናንተ ናት ። እናንተ ወጣቶች እንደምታብብ
ህይወት ... ልክ ሁለት እና ሶስት ሰዓት እንደምትወጣው የጠዋት ፀሃይ ብርታትና ጥንካሬ የተሞላችሁ ናችሁ ... »
ማኦ በቀይዋ መጽሐፍ ላይ « የማርክስ ፣ ኤንግልስ ፣ ሌኒንና ስታሊን ቲዎሪ አለማቀፍ ተቀባይነት ያገኘ ነው ። እኛ የምንቀበለው
እንደ ቀኖና ሳይሆን እንደ መንገድ መሪ ነው » ይላል ። በርግጥ ማኦ በመሰረተ ሃሳብ ደረጃ ማርክሲስቶችን ቢያከብርም የራሱን ቲዎሪ
የገነባ ብሎም ተጽእኖ የፈጠረ ሰው ነው
ስሙን መሰረት ያደረገው « ማኦኢዝም » የኢንዱስትሪ መስፋፋት ከበርቴው ይበልጥ ህዝቡን እንዲበዘብዝ መንገድ ይፈጥራል ባይ
ነው ። በዚሁ ፍልስፍናው የፋብሪካው ሰራተኛ ሳይሆን ገበሬው የኮሙኒስት አብዮትን መምራት አለበት ብሎ ያምናል ። ከማርክሲዝም ርዕዮት
ጋር ልዩ የሚያደርጋቸውም ሀሳብ ይኸው ነው ። ማርክሲስቶች የከተማው ሰራተኛ ላይ ትኩረት ሲያደርጉ ማኦ ኢዝም ለገበሬው ይወግናል
።
ምዕራባዊያን ማኦ የበርካታ አስገራሚ ጥቅሶች ፈጣሪ እንደሆነ ይቀበላሉ ። ከአስገራሚው አንዱም « ብዙ መጽሐፍ ያነበበ አደገኛ
ነው » ያለው እንደሚገኝበት ጽፈዋል ። የአንባቢ ወታደሮችን መጽሐፍ ሰብስቦ ያቃጥል ነበር የሚሉትም አሉ ። ነገሩ ተረት ይመስላል
። ቀይዋ መጽሐፍ አንባቢነትን አትቃረንም - ይልቅ ስለ ትምህርትና ስልጠና አስፈላጊነት ነው የምትሰብከው ። እንግሊዞች ማኦን እንደሚተርቡት
ሁሉ አድንቀው ፓርላማ ውስጥ ጥቅሱን ለንግግራቸው ማዳመቂያነት የሚያውሉም አሉ ።በቀይዋ መጽሐፍ የተሰባሰቡት ጥቅሶችና አባባሎች
የማኦን ፍልስፍናና እምነት ያንጸባርቃሉ ::
እንዲህ በማለት ።
መጥረጊያህ ቆሻሻው ጋ ካልደረሰ ቆሻሻው በራሱ ግዜ አይጠፋም ።
ጦር ሰራዊታችን ለጠላት ጨካኝ ለወገን ደግሞ ደግ መሆን አለበት ።
የጓዶቻችን ጭንቅላት ምናልባት አቧራ ይሰበስብ ይሆናል ፣ በመሆኑም በግምገማና ግለ ሂስ መጠረግና መታጠብ ይፈልጋል ።
ማኦ በዛሬይቷ ቻይና ብቻ ሳይሆን በዛሬዋ አለማችን ዙሪያ አንድ መሰረታዊ ተጽዕኖ ፈጥሮ ማለፍ ችሏል
እንዲህ በማለት ።
« የፖለቲካ ስልጣን የሚመጣው ከጠመንጃ አፈሙዝ ነው ! » ለዚያም ነው በርካታ የዓለማችን መሪዎች ማቆሚያ የሌለው የጦር
መሳሪያ እሽቅድድም እና ግንባታ ውስጥ የገቡት ።