አዶልፍ ሂትለርና ዊንስተን ቸርችል በተቃራኒው
መንገድም ቢሆን የሚመሳስል ነገር አላቸው ። ሁለቱም በውትድርና ሀገራቸውን አገልግለዋል ። ሁለቱም ሀገራቸውን መርተዋል ። ሁለቱም
ሀገራቸውን < ለማስቀደም > የአባራሪና ተባራራሪን ሚና ወክለው ተፋልመዋል - ሂትለር ድመት ቸርችል አይጥ እንዲሉ ።
ሁለቱም ሃይለኛ ተናጋሪ ናቸው ። ሁለቱም ደራሲ
ናቸው ። እንደውም ሁለቱም ታስረው በእስር ቤት ውስጥ መጽሀፍ መፍጠራቸው ገጠመኙን ጠንከር ያደርገዋል ። ቸርችል በቦየር ጦርነት
ወቅት ወደ ደቡብ አፍሪካ ባመራበት ወቅት ተይዞ እስር ቤት ውስጥ ተወርውሮ ነበር ። እዛ ግን ስራ አልፈታም ። <
London to lady smith via Pretoria > የሚል
ስራ ጨርሶ ለአንባቢያን አቅርቧል ። ሂትለር የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አድርገሃል ተብሎ ዘብጥያ በተላከ ግዜ < Mein Kampf > ወይም የኔ ትግል የሚል ጠንካራ ስራ ሰርቶ በኌላ ላይ አሳትሞታል
። ርግጥ ነው ሂትለር በስሙ አስር ስራዎች ቢታተሙለትም ሁሉም እንደ ቸርችል ጠብሰቅ ያሉና ሚዛን የሚደፉ አይደሉም ። ቸርችል
43 መጽሀፍት ለአለም አበርክቷል ። በዚህም ጥረቱ በ1953 የስነጽሁፍ ኖቤል ተሸላሚ መሆን ችሏል ። ምናልባትም በዘርፉ ትልቅ
ክብር ያገኘ ብቸኛው የአለማችን መሪ ነው ።
በስልጣናቸው ዘመን ሁለቱም የራሳቸው መለያ የሆነ
የሰላምታ አሰጣጥ ስርዓት ነበራቸው ። ቸርችል ሁለት ጣቱን በማውጣት ሰላም ይላል - እናሸንፋለን ለማለት ጭምር ። ሂትለር ቀኝ
አጁን ወደፊት በመዘርጋት ሰላምታ ይሰጥ ነበር - < Seig
Heli > - እናሸንፋለን እንደማለት ። ሁለት ጣት ሲወጣ መሳቅም መጥቀስም ይቻላል ። ቀኝ እጅ ወደፊት እንደ ቀስት ሲወረወር
ግን ምናልባት ሂትለር ! ከማለት ውጪ መፈገግ አይቻልም - ኮስተር ብሎ ሰኮንዶችን ማሳለፍ እንጂ ። የናዚ ሰላምታ በአሁኑ ወቅት
በጀርመን ፣ ኦስትሪያ ፣ ስሎቫኪያ እና ቼክ የወንጅል ድርጊት በመሆኑ እስከ ሶስት ዓመት ያስቀጣል ። የቪ ምልክት የትም ሀገር
ወንጀል ባይሆንም በአንድ ወቅት በኢትዮጽያ የብዙዎች መቀጣጫ ሆኗል ።
ሁለቱም መሪዎች ሰዓሊዎች ናቸው ። በቀውጢው ዘመን
ብሩሽና እርሳስ ጨብጠው በቀለማት ዜማ ሃሳባቸውንና ፍልስፍናቸውን ሸራ ላይ ተንፍሰዋል ። ርግጥ ነው ሂትለር በ1905 ገና በ16
ዓመቱ ዳገት የሆነበትን ትምህርት ትቶ ነበር ፕሮፌሽናል ሰዓሊ የመሆን ህልሙን ፍለጋ የጀመረው ። የቸርችል ህልም ከሰዓሊነት ይልቅ
የጦር ዘጋቢነትና ደራሲነት ነበር ማለት ወደ እውነታው መንደር ጠጋ ያደርገናል ። ለማሳያም በወቅቱ በትላልቅ ጋዜጦች ላይ ይጽፋቸው
የነበሩትን መጣጥፎችና ብርሃን ያዩ የህትመት ስራዎቹን መመልከት በቂ ነው ። ተደብቆ የቆየው የሰዓሊነት ፍላጎት ብቅ ያለው እንደ
ሂትለር በወጣትነት ዘመን አይደለም - በጉልምስና/ 40 / እንጂ
።
ቸርችል በአንድ ወቅት የፖለቲካው ህይወት ሲያስጠላው
ራሱን አግሎ ነበር ። ያኔ ራሱን ለማዝናናት ከጽሁፉ ጎን ለጎን መስመሮችን መገጣጠም ጀመረ ። አንዳንድ መረጃዎች እንደሚነግሩን
ስእሉን መማር የጀመረው ከጓደኛው ፓወል ሜዞ ነበር ። አንዳንድ መረጃዎች ደግሞ የታዋቂዎቹ ሰዓሊዎች ማለትም የክላውድ ሞንት ፣
ቪንስንት ቫ ጎህ እና ዊሊያም ተርነር ስራዎች ትልቅ ተጽዕኖ ፈጥረውበት እንደነበር ያስረዳሉ ።
ለሂትለር የስዕል መስመሮችን ለመጀመሪያ ማን እንዳሳየው
የሚገልጽ መረጃ የለም ። ይሁን እንጂ የትምህርት ቤቱ ሰርተፍኬት እንደሚያሳየው በብዙ ትምህርቶች በቂና ከበቂ በታች ውጤት አሰመዝግቦ
በስዕል ትምህርት ግን < እጅግ በጣም ጥሩ > የሚል የሞቀ መገለጫ ነው የሰፈረለት ። ይህም ገና በታዳጊነቱ ስዕል አፍቃሪ
መሆኑን ያቃጥራል ። ያም ሆነ ይህ የሂትለር ተጽዕኖ ውስጣዊ ፍላጎትና የህይወት ችግር ነበር ። አባቱ አሎያስ ሂትለርን ለሶስተኛ
ግዜ ካገባት ሚስቱ በ51 ዓመቱ ነበር የወለደው ። ሂትለር ስድስት ዓመት ሲሞላው ጡረታ በመውጣቱ የችግር ጥላ ቤቱን በወፍራም ግራጫ
ቀለም ለቅልቆት ነበር ። ሂትለር 13 ዓመት ሲሞላው ግራጫው ቀለም ወደ ጥቁርነት ተቀየረ - አሎይስ አረፈ ። እናቱ ክላራም በ1908
በጡት ካንሰር ሞተች ። እናም ራሱን ለማሸነፍ እንደ ቀስት መወርወር ነበረበት ።
በ1907 በቬና የስነጥበብ አካዳሚ ለመማር አመልክቶ
ያቀረብከው ስራ ብቁ አይደለም ተብሎ ነበር ። በ1908 ትም ወደዚሁ ማዕከል መወርወር ግድ ብሎት ነበር ። አሁንም ለመግቢያ ፈተና
ያቀረበውን ስራ የገመገሙ መምህራን ብቃት እንደሌለው በግልጽ ነገሩት ። በብቃቱ ይተማመን የነበረው ሂትለር ጠማማውን ምላሽ አምኖ
ለመቀበል አልቻለም ። ተቋሙ ሂትለር ከሰዓሊነት ይልቅ በአርክቴክቸር የበለጠ ተሰጥኦ እንዳለው ያምን ነበር ። ሂትለር በአይሁዳዊያኑ
መምህራን ላይ ቂም ቋጠረ ።
እንደ ቸርችል ከሃብታም ቤተሰብ ባለመፈጠሩ ስዕሉን
ችላ ብሎ ሌላ የህይወት ሰበዝ የመምዘዝ እድል አልነበረውም ። እናም መሳሉን ገፋበት ። በተለይም ከ1908 እስከ 1913 በቬና
ህይወቱን ለማቆየት በመቶ የሚቆጠሩ ስዕሎችንና ፖስት ካርዶችን ሰርቶ ሸጧል ።
ቸርችል በአንደኛው ዓለም ጦርነት ወቅት በጦር
ሰራዊትና ባህር ሃይል ከፍተኛ የሃላፊነት ቦታዎች ላይ አገልግሏል ። ሂትለር የአንደኛው ዓለም ጦርነት ሲጀመር በኦስትሪያ ዜግነት
በቫሪያን ጦር በፍቃደኝነት ለማገልገል ተቀላቀለ ። የስዕል ስራዎቹን ጦር ሜዳ ይዞ በመሄዱ < አርቲስቱ > እየተባለ ነበር
የሚጠራው ። ጦርነቱ ቸርችልን እስከ ሚኒስትር ደረጃ እንዳደረሰው ሁሉ ሂትለርም የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ የጀግና ሽልማቶችን ከሻምበልነት
ማዕረግ ጋር አስገኝቶለታል ። በትርፍ ሰዓቱም ለጦር ሰራዊቱ ጋዜጣ የካርቱን ስዕሎችን በመመገብ የአዝናኝነትን ሚና ከፍ አድርጓል
።
hitler 's works
የሂትለርና ቸርችል የአብዛኛዎቹ ስራዎች ጭብጥ
መልከዓምድር ፣ ተፈጥሮና የሰው ምስል መሆናቸውን ስንመለከት ብዙ ጥያቄዎች ሊፈጠሩብን ይችላሉ ። ምክንያቱም ወቅቱ የፖለቲካ ውጥረት
የበዛበት ፣ ህይወት በጥይት የሚያልፍበት ፣ አንዱ ሌላውን ለማጥቃት እንቅልፍ የሚያጣበት በመሆኑ ነባራዊውን እውነታ ማንጸባረቅ
ለምን እንዳልፈለጉ ግልጽ አይደለም ። ስራዎቻቸው ከጭብጥ አንጻር
ተቀራራቢ ቢመስልም የስዕሎቹ መኳኳያ መንገድ ግን ለየቅል ነው ። ቸርችል የዘይት ቅብን መሰረት ሲያደርግ ሂትለር የውሃ ቀለም ይመቸዋል
። የስዕልን ፍላጎት ለረጅም ግዜ ይዞ በመቆየትም ቸርችል ቅድሚያውን ይይዛል ። ለዚያም ነው አምስት መቶ የሚደርሱ ስራዎችን ያመረተው
። የእንግሊዙ ታዋቂ ሰዓሊ ሰር ኦስዋልድ በርሊ << ቸርችል ለፖለቲካው እንደሰጠው ሰፊ ግዜ ለስዕሉም ቢሰጥ ኖሮ ዓለማችን
ታላቂ ሰዓሊ ታገኝ ነበር >> ሲል ተናግሯል ። በአሁኑ ወቅትም የቸርችል ስራዎች በጨረታ እየተጫረቱ በሚሊየን ዶላር እየተሸጡ
ናቸው ። በሌላ በኩል < civil registry office and old town hall of munich > የሚል ርዕስ
የያዘው የሂትለር ስራ በ 161 ሺህ ዶላር ተሸጧል ። አጫራቹ ድርጅት ለኒዊስክ እንደገለጸው ስራው በጥሩ ሁኔታ የሚገኝ ሲሆን የሰዓሊውንም
ችሎታ ያሳየ ነው ። ምንም እንኳን ብዙዎች የዚህን ከይሲ ሰው ጥሩ ስራ መስማትም ማድነቅም ባይፈልጉም ።
ርግጥ ነው ሂትለር ለሁለተኛው ዓለም ጦርነትና
ለ 11 ሚሊየን ዜጎች እልቂት ተጠያቂ ነው ። ሂትለር እጆቹ በደም ከመጨማለቃቸው በፊት በስዕል ህብረ ቀለማት የለመለሙ ነበሩ ።
ስዕሎቹን ተራ በተራ የተመለከተ ሰው መገረሙና መመሰጡ አይቀሬ ነው ። ስሜታዊ ከሆነም የቬና የስነጥበብ አካዳሚ እውነት ምን ነክቶት
ነው ሁለት ግዜ ጠልዞ ከግቢ ያባረረው ? ሊል ይችላል ። ምናልባት ሂትለር ሰዓሊ ሆኖ ቢቀጥል የሁለተኛው አለም ጦርነት ርዕሰ ጉዳይ
ላይኖር ይችላል ። ይህ ጦርነት በመወለዱ ግን ሂትለር ጥበባዊ ልዕልናውን ሲያጣ ቸርችል የሞገስ ካባና አክሊሉን አጠልቋል ። ምክንያቱም
በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ላይ የሚያትቱ ስድስት መጽሀፍት ደርሷልና ። ሂትለር አይጥ ቸርችል ድመት እንዲሉ ።
የሂትለር ጺም ፣ የቸርችል ሲጋራ ድንገት በምናብ
ብቅ እንደሚልብን ሁሉ ፤ የሂትለርን ተሸናፊነት የቸርችልን አሸናፊነት ምሳሌ እንደምናደርገው ሁሉ ፤ ሂትለርን በጨካኝነት ቸርችልን
በደፋርነት እንደምንበይነው ሁሉ ፤ የሁለቱንም ሌሎች ተመሳሳይ እጆች
ማወቅ ይኖርብናል ። እናም እንደእኔ እምነት የስዕል ስራዎቻቸውን አሰባስቦ በአንድ ሙዚየም ውስጥ ለማሳየት የሚተጋ ግለሰብ ወይም
ተቋም ያስፈልጋል ባይ ነኝ ።