ደራሲ አማረ ማሞ ብዙ አልተባለላቸውም ። ግን ለስነጽሁፍ ብዙ ሰርተዋል ፤ በእጅጉ ደክመዋል ። እጣ ፈንታ ሊሆን ይችላል
። አንዳንድ ያደለው በአንድ ጥሩ ስራ ስማይ ላይ ሊወጣ ይችላል ። የዚህ አይነቱ እድለኛ ባለቲፎዞም ስለሚሆን ክበባቱ ፣ ሚዲያውና
ማስታወቂያው እንኮኮ ያደርገዋል ።
በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ደራሲ፣ አርታኢና ተርጓሚ አማረ ማሞ ማናቸው ተብሎ አልተመረመሩም ። እኚህ ሰው ስነጸሁፍ ፍቅራቸው
ብቻ ሳይሆን ህይወታቸው በመሆኑ ኖረውብታል ማለት ይቻላል ። የኢትዮጽያ መጻህፍት ድርጅት ስነጽሁፍንና ደራሲዎችን ለማሳደግ አይነተኛ
ሚና ተጫውቷል ። እሳቸው ደግሞ በድርጅቱ ውስጥ ም/ስራ አስኪያጅ ነበሩ ።
በድርጅቱ አሳታሚነት ለንባብ ይበቁ የነበሩ መጻህፍትን የሚያስታውስ አንባቢ የአቶ አማረን ድርሻ በአግባቡ ለመረዳት አያዳግተውም
። የነባርና እጩ ደራሲዋችን የአሳትሙልኝ ረቂቅ ጽሁፎችን በመለየት ፣ የተለየውን ደግሞ የአርትኦት ስራ በማከናወን በድርሰት ላይ
የማዋለድና ጥሩ ቁመና የመፍጠር ህክምና አበርክተዋል ።
እንዴት ላሳትም ወይም በምን መልኩ ልጻፍ ወይም የመሳሰሉ ጥያቄዋችን አንግቦ ቢሯቸው ጎራ የሚሉትን ጥበብ አፍቃሪዋች ውሃ
የሚያነሳ ምላሽ ለመስጠት አያነቅፋቸውም ። የኢትዮጽያ መጻህፍት ድርጅት ከስራ ውጪ ከሆነ በኋላ እንኳ አቶ አማረን ኪነጥበባዊ እድሞሽ
ላይ ማግኘት ቀላል ነበር ። በስነጽሁፋዊ ውይይቶችም ሆነ ህትመት ምርቃቶች ላይ ከፊት በመገኘት ልምዳቸውንና ሃሳባቸውን ሳይሰላቹ
አጋርተዋል ።
አቶ አማረ የበርካታ መጻህፍት ደራሲና ተርጓሚ ናቸው ። ዶን ኪሆቴ ፣ አሳረኛው ፣ እሪ በይ ሃገሬ ፣ የእውነት ብልጭታ
፣ የቀለም ጠብታ እና የልብ ወለድ ድርሰት አጻጻፍ የተስኙ ስራዋችን በጥቂቱ መጠቃቀስ ይቻላል ።
እውነቱን ለመናገር የልብ ወለድ ድርሰት አጻጻፍ የተሰኘው ስራቸው ብቻ ሽልማት የሚገባው ነው ። በ1960ዎቹ የታተመው ይህ
ስራ የብዙ ድርሰት አፍቃሪያንን አይኖች የገለጠ ነው ። እንደሚታወቀው ኮሌጅ/ዩኒቨስቲ የመግባት እድል ያላጋጠማቸው የሀገራችን ደራሲዎች
ጥቂቶች አይደሉም ። ብዙዎቹ ታዲያ መጽሀፉን እንደ አንድ ተቋም ክብር በመስጠት የልቦለድ ባህሪና ምንነትን እንዲሁም እንዴት መቀሸር
እንደሚገባው የተረዱት ይህን መጽሀፍ በማንበብ ነው ። ለመጽሀፉ ምስጋና ይግባውና ጠንካራ ምናብና ብእር ያላቸው ደራሲዎች መፈጠር
ችለዋል ።
ይህ መጽሀፍ ድንበር ያጠረው አልነበረም ። ሌላው ቀርቶ በኮሌጆችና/ዩኒቨስቲዎች ለስነጽሁፍ ትምህርት አጋዥ በመሆን ለመምህራኑም
ሆነ ለተማሪዎች ትልቅ ግብዓት ፈጥሯል ። በነገራችን ላይ የራሳቸውን ማንዋል አዘጋጅተው ወይም አጋዥ ስራ አሳትመው የሚያስተምሩ
ውለተኛ መምህራን ቁጥር እጅግ አነስተኛ ነው ። የቲያትር ኮርስ ሲሰጥ የፋንታሁን እንግዳ የተውኔት መጽሀፍ ነው ትልቅ ድርሻ የሚወስደው
። ተማሪ እየተናጠቀ ኮፒ ለማድረግ ይራወጣል ። በዚህ ረገድ ደበበ ሰይፉና ዘሪሁን አስፋው የሚታሙ አይመስለኝም ። ርግጥ ነው ብርሃኑ
ገበየሁም ኋላ ላይ ተቀላቅሏል ። መሰረታዊ ስነጽሁፍ ለኮሌጅ ተማሪዋች በተለይ የአፍሪካ ስነጽሁፍን አስመልክቶ ግን ብዙ ያልተዘመረለት
መምህር አለ ። መላክነህ መንግስቱ የሚባል ። ርግጠኛ ባልሆንም ከኮተቤ
ወደ ዩኒቨርስቲ የተዘዋወረ ይመስለኛል ። በርካታ ድርስት ነክ ስራዎችን በእንግሊዘኛ
ቋንቋ አሳትሟል ። ተማሪዎችም የእሱን ስራዎች መነሻ በማድረግ የአፍሪካን ስነጽሁፍን ለማወቅና ለመመርመር አግዟቸዋል ።
የአቶ አማረ ስራ ግን ኮሌጅ ለረገጠውም ላልገባውም ፣ ለጀማሪውም ለመምህራንም ፣ ለስነጽሁፍ አድናቂም ለተመራማሪውም ዛሬም
ድረስ የውለታ ሃውልት ሆኖ ቆሟል ። እንግዲህ እዚህ ሃውልት ላይ ነው ሰሞኑን የክብር ካባ እና የወርቅ ብእር የተሰቀለው ። በሸላሚው
ድርጅት ማለትም በንባብ ለህይወት የፌስ ቡክ ገፅ ላይ « አይናቸውን ያልጨፈኑ የድርሰት ሰማያችንን ያደመቁ ኮኮብ ሆነው ሆነው በመገኘታቸው
የዓመቱ የወርቅ ብዕር ተበርክቶላቸዋል » የሚል ጽሁፍ ይነበባል ።
ግሩም ምስክርነት ሆኖ ስላገኘሁት ደስ ብሎኛል ። በርግጥም የድርሰት ሰማያችንን ለማድነቅ የተጉ በርካታ ጸሐፊያን አሉን
። አቶ አማረ ግን ኮኮቦቹ ከመታየታቸውም በፊት ጧፍ ሆነው ተገኝተዋል ። ብዙዎችን አርመዋል ... ኮትኩተዋል ... በርካቶችም
የጧፉን ብርሃን ተከትለው መንገድ አግኝተዋል ።
ንባብ ለህይወት በአጭር እድሜው አምባሳደር ዘውዴ ረታ ፣ አዳም ረታንና አማረ ማሞን የወርቅ ብዕር ተሸላሚ አድርጓል ።
መልካም ጅምር ስለሆነ ለረጅምና ላልተቆራረጠ ጉዞ ብርታቱን እንዲሰጣችሁ እመኛለሁ ። ብርታቱ ግን እንደ አማረ ማሞ ብዙ ሰርተው
ያልተነገረላቸውን ብዕረኞችን ለማፈላለግ ጭምር እንዲሆን ማድረግ ይገባል
።