አዲሱን
የቴዲ አፍሮ አልበም አጣጣምኩት ። ከላይ ወደታች ፣ ከታች ወደላይ
ተመላላሰኩበት ።
ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላው ስዘል ውበቱን ፣ ስልቱን ፣ ስሜቱንና መልእክቱን ለመለካት እየሞከርኩ ነበር ። በዚህ የወዲህ - ወዲያ
ቅኝቴ የፈጠርኩት ስእል ትሪያንግል ሆነ ።
እኩል ሶስት ማእዘን ባለው ቅርጽ ላይ ሶሰት ሙዚቃዎች ከፍ ብለው ተመለከትኩ ። በአንደኛው
ጫፍ ‹ ኢትዮጽያ › ፣ በሁለቱ ጎኖች ደግሞ አጼ ቴዎድሮስ እና ማር እስከ ጧፍ ። የእነዚህ ሶስት ሙዚቃዎች ተምሳሌትነት ከፍ ያለ ነው ። የሶስቱም
ዘፈኖች ግጥማዊ ክህሎት ምጡቅ ነው ። ትሪያንግሉ በራሱ ለመቆም ምሉዕ
ቢሆንም አንዳንዴ ሀገር ከሚያምሰው የነገርና ምቀኝነት ሱናሜ ለመትረፍ የሚያስችልም ስንቅ አንግቧል ። ኢትዮጵያ ውስጥ / ሀገር/ ፣ አጼ ቴዎድሮስ  ውስጥ / ጀግንነት / 
ማር እስከ ጧፍ ውስጥ ደግሞ / ፍቅር / ተወከሎ ይገኛልና ።
                                                                                                       ኢትዮጽያ![]()  | 
| አጼ ቴዎድሮስ ማር እስከ ጧፍ | 
‹ ኢትዮጵያ › ቀደም ብሎ የተለቀቀ ነጠላ ዜማ ቢሆንም ከሙሉ አልበሙ ጋር ሳየውም መጠሪያ መሆኑ አያንስበትም ። ሙዚቃው የትልቅ አጀንዳ ባለቤት ነው ። የሞት- ሽረት ጠርዝ ላይ የሚገኘውን ኢትዮጵያነት ይሞግታል ። ኢትዮጵያነት ከዘጠና ሚሊየን ህዝቦች ውህደት በላይ መሆኑን ለማሳየት ባንዲራው ያለውን ክብርና ጸጋ ይዘክራል ።
              « እንኳን ሰማይ ላይ ባንዲራሽን አይቶ
                ኢትዮጵያ ሲባል ማን ዝም ይላል ሰምቶ »
ቴዲ የፖለቲካ
ኩርፊያና በደል ማንነትን ለመካድ መሰረት ሊሆን አይችልም ባይ ነው 
« ቢጎል እንጀራው ከመሶቡ ላይ ፣ እናት በሌላ ይቀየራል ወይ » በርግጥም ዓለም የሉሲ ልጆች ፣ የነጻነት ምሳሌዎች
እያለ የሚጠራቸው አበሾች በየአደባባዩ በርካታ ትናንሽ ባንዲራዎች ተሸክመው ሲያያቸው ያዝናል ። በትልቁ ባንዲራችን ፍቅር ወድቀው
የራሳቸውን ለመቅረጽ መነሻ ያደረጉ አፍሪካዊያንም ከንፈራቸውን መምጠጥ ከጀመሩ ቆይተዋል ። እናም የሰንደቅ እና ሀገር ጉዳይ ውሃ
ቢወቅጡት እንቦጭ እንደሆነ ቀጥሏል ።
  « ተዉኝ ይውጣልኝ ልጥራት ደጋግሜ
    ኢትዮጵያ ማለት ለኔ አይደል ወይ ስሜ » ያስብላል 
ይህ ሙዚቃ
ብቻውን የተለቀቀ ሰሞን እንካሰላንቲያ ያማዘዘውም የትሪያንግሉ አንደኛው ማእዘን ሰለሆነ ነው ። ኢትዮጵያነት ግን ያው የነብር ቆዳነት
ነው ። ብዙ ሂትለሮች በለስ ቀንቷቸው ኢትዮጵያዊያንን ማጥፋት ቢችሉ እንኳ ኢትዮጵያ የተሰራችበትን ታሪካዊ ፣ ሃይማኖታዊ እና ሳይንሳዊ
አሻራዎች መደለዝ አይችሉም ።
በርግጥ
አንዳንዶችም ሙዚቃውን አሰታከው የዋህ አስተያየት ሲሰጡ ተሰምተዋል ። አንደኛውና ዋነኛው ወቅትን እየጠበቁ እንዲሁም ሰዎችና ክስተቶች
ላይ መዝፈን የጥበብ ሰው ባህሪ አይደለም የሚል ነው ። ይህ አባባል የጥበብ ምንነትን ካለማወቅ ይነሳል ። የጥበብ ግብ የገሃዱን
ዓለም ጥሬ እውነት ጥበባዊ በሆነ ኩታ አስውቦ መገኘት ነው ። ስለዚህ ሰዎች እና ክስተቶች ከብዙ በጥቂት የሚቀዱ ምንጮች ናቸው
ማለት ነው ። 
ሌላው
የቴዲ አፍሮን የጥበብ መንገድና ስልት አለመገንዘብ ነው ። ይህ ድምጻዊ በአጭር ግዜ ውስጥ የማይታመን ተቀባይነት ያገኘው  ለምንድነው ? የሚለውን ጥያቄ ስንመልስ  መስመሩን እናገኛለን ። ቴዲ የድፍረት ፣ የፈጣንና ሰፊ ምናብ ባለቤት ነው
። ማንም አቀንቃኝ የሚፈራውን የአንድነትና የመገንጠል ጉዳይ ሲፈልግ አስውቦ ያዜማል ። በፈጣን ምናቡ ወቅታዊና ትኩስ እውነቶችን
የውበትና ተዝናኖት ክንፍ ሰርቶላቸው አድማጩ ቤት ድረስ እንዲያንዣብቡ ያደርጋቸዋል ። 
ፖለቲካ ያስፈራራቸውን ወይም ሀገር የረሳቸውን ጀግኖች በፈጠራ ሃውልት ያንጻቸዋል ። እነዚህ ሃውልቶች እንደምናውቃችው አይነቶች የተመረቁ እለት ብቻ የሚነገርላቸው አይደሉም ። ሃውልቶቹን በፍቅር ይተክላቸዋል ፤ እኔና እናንተ ደግሞ ደምና ስጋ ሞልተን ስለነፍሳቸው ዘወትር እናዜማቸዋለን ። በግጥም ዘርፍ « የጸጋዬ ቤት » እንደምንለው ሁሉ ይህን የዜማ አተያይም « የቴዲ አፍሮ ስልት » ማለት ይቻላል ። ታዲያ ይህን በእሱ ፍቃድ ብቻ የሚገኝ ሃያል ስልት እንዳይቀጥል የሚፈልግ ጅላጅል ተደራሲ ማነው ?
ፖለቲካ ያስፈራራቸውን ወይም ሀገር የረሳቸውን ጀግኖች በፈጠራ ሃውልት ያንጻቸዋል ። እነዚህ ሃውልቶች እንደምናውቃችው አይነቶች የተመረቁ እለት ብቻ የሚነገርላቸው አይደሉም ። ሃውልቶቹን በፍቅር ይተክላቸዋል ፤ እኔና እናንተ ደግሞ ደምና ስጋ ሞልተን ስለነፍሳቸው ዘወትር እናዜማቸዋለን ። በግጥም ዘርፍ « የጸጋዬ ቤት » እንደምንለው ሁሉ ይህን የዜማ አተያይም « የቴዲ አፍሮ ስልት » ማለት ይቻላል ። ታዲያ ይህን በእሱ ፍቃድ ብቻ የሚገኝ ሃያል ስልት እንዳይቀጥል የሚፈልግ ጅላጅል ተደራሲ ማነው ?
የትሪያንግሉ
ሁለተኛው ማእዘን « አጼ ቴዎድሮስ » ነው ። በዚህ ዜማ የጀግንነት ከፍታ ታይቶበታል ። የታሪኩ ባለቤት አጼ ቴዎድሮስ ለሀገራቸው ክብር በመቅደላ ተራራ ያደረጉት ተጋድሎ ተዘርዝሯል ። ቴዎድሮስ የተከፋፈለችውን ኢትዮጽያ አንድ
ለማድረግ በተደረገው ትግል የአንድነት ምልክት ናቸው ። ለዛም ነው ድምጻዊው 
 « ጎንደር ጎንደር የቴዎድሮስ ሀገር
   የአንዲት ኢትዮጽያ ዋልታና ማገር » የሚለው
ቴዎድሮስ በኢትዮጽያ የመሪዎች ታሪክ ልዩ ቦታ ያገኙትም የተከፋፈለች ወይም የተሸነፈች
ሀገርን ላለማየት መስዋዐት በመሆናቸው ነው ። ከራስ በላይ ንፋስ የሚል መሪ በችግር ግዜ እጁን ይሰጣል ወይም ይሰደዳል እንጂ ራሱን
አያጠፋም ። ድምጻዊው ይህን መስዋእትነት ያስተሳሰረው ከሰንደቅ ዓላማ እና ከቀጣይ መልዕክት ጋር ነው ።
   « ጨክኖ ካሳ ጋተና ኮሶ
     ሞተ ለአንድ ሀገር ባንዲራ ለብሶ »           
ቀጣዩ
መልዕክትም የተላለፈው
በባንዲራው ድልድይነት ነው ። ይህን ባንዲራ ማንሳት ብቻ ሳይሆን የተዳፈነውንም ጀግንነት በብዙሃኑ ላይ እንዲጋባ ይፈለጋል ። ሀገር
ለመስራት ጀግኖች ያስፈልጋሉ ። የጀግኖችን ራእይ ተግባራዊ ለማድረግ የወራሾች
ሚና ወሳኝ ይሆናል ። ወራሾች የሞተውን ጀግና በማሰብ ከማለቃቀስ ይልቅ የአሟሟቱን ሚና በመረዳት ላይ እንዲተጉ ይጠበቃል ። ይህን
ግን እውን ለማድረግ ቀላል አይደለም ። 
 « ግመሌን ላጠጣት ቀይ ባህር ተጉዤ
    አንድ ገመድ አጣው ልመልሳት ይዤ » የሚለው ስንኝ የአንድን ጠንካራ ወራሽ
ስጋትና ተስፋ መቁረጥ በምሳሌ የሚያሳይ ነው ። የአጼ ቴዎድሮስን ህልም እውን ለማድረግ ወቅታዊው የፖለቲካ ምህዳር ጠባብ ቢሆንም መልእክት አደራሹ
ከያኒ ግን የጋመ ፍላጎቱን ጾታ ሳይለይ ለማስተላለፍ ‹ ሹሩባ › የሚለው ቃል የተመቸው ይመስለኛል ። 
  « አንጡ ቆርጣችሁ ከሹሩባው ላይ
    ኪታብ እንሰር እንዳንለያይ »
የትሪያንግሉ
ሶስተኛው ማእዘን « ማር እስከ ጧፍ » ይሰኛል ። ሙዚቃው የተመሰረተው የፍቅር እስከ መቃብር ድርሰት ላይ ነው ። ይህ መጽሀፍ በእንግሊዘኛ የመተርጎም
እድል ቢያጋጥመው ኖሮ ዓለም ‹ የድርሰት ሉሲ › በኢትዮጵያ ተገኘ ማለቱ ባልቀረ ነበር ።
ቴዲ ይህን
ትልቅ መጽሀፍ እንደገዘፈ ለማቅረብ ሞክሯል ። ገጸባህሪያቱን አሳይቶናል ። በተለይ ተፈቃሪዋ ሰብለ ወንጌል መልከ ብዙ ሆና ተስላለች
- ብራና ፣ ንብ እና ማር ። ብራና ሆና የፍቅር መወድስ እናነብባታለን ። ንብ ሆና በአንድ በኩል ትጋትዋን በሌላ በኩል የጥቂት
አመታት እድሜዋን እንዲሁም ማር ሆና ጣፋጭነትዋን በተለዋጭ ዘይቤ እንመለከታለን ። ይህን ውብ ቋንቋ ቅኔያዊ በሆነ መስተጋብር እያስተሳሰረ
አቅርቦታል ።
 « ላሳደገኝ ደብር የስለት ልጅ ሆኜ
   ካህን እንዴት ይፍታኝ ያንቺ እስረኛ ሆኜ
   ማር ጧፍ ሆኖ ገባ - ከመቅደስ
   ነዶ ለኔ ጸሎት ሊያደርስ  »
ቢጫ ለብሳ ገዳም የገባችውን ሴት መንጥቆ ለማውጣት የሚደረገው  ትግል ጠንካራ ነው ። ሆኖም የቱንም ያህል አዋቂ ቢኮን ፍቅር አንበርካኪ
መሆኑን እንረዳለን ።
  « ለካ ሰው አይድንም በደገመው መጽሀፍ
    እንደ ሰም አቅልጦ
ፍቅር ካደረገው ጧፍ »          
የቴዲን ትሪያንግል እንደ ጋሪ ለመግፋት ብንፈልግ አራት ጎማዎች ያስፈልጉናል ። ሰምበሬ
፣ አና ንያቱ ፣ ያምራል እና ኦላን ይዞ በአቀራረብ ስልታቸውና ሳቢነታቸው የእኔ ምርጫዎች ናቸው ።            
 ኦላን ይዤ አላፍርም ይህን አውቃለሁ
 ወደ ፍቅር ልሂድ ምን እጠብቃለሁ
 ወደ ፍቅር ጉዞ ተያይዞ
 ቂምን ከሆድ ሽሮ
 ኦላን ይዞ …                                                                  

