Thursday, May 4, 2017

የቴዲ አፍሮ ትሪያንግል


አዲሱን የቴዲ አፍሮ አልበም አጣጣምኩት ። ከላይ ወደታች ፣ ከታች ወደላይ ተመላላሰኩበት ። ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላው ስዘል ውበቱን ፣ ስልቱን ፣ ስሜቱንና መልእክቱን ለመለካት እየሞከርኩ ነበር ። በዚህ የወዲህ - ወዲያ ቅኝቴ የፈጠርኩት ስእል ትሪያንግል ሆነ ።

እኩል ሶስት ማእዘን ባለው ቅርጽ ላይ ሶሰት ሙዚቃዎች ከፍ ብለው ተመለከትኩ ። በአንደኛው ጫፍ ‹ ኢትዮጽያ › ፣ በሁለቱ ጎኖች ደግሞ አጼ ቴዎድሮስ እና ማር እስከ ጧፍ ። የእነዚህ ሶስት ሙዚቃዎች ተምሳሌትነት ከፍ ያለ ነው ። የሶስቱም ዘፈኖች ግጥማዊ ክህሎት ምጡቅ ነው ። ትሪያንግሉ በራሱ ለመቆም ምሉዕ ቢሆንም አንዳንዴ ሀገር ከሚያምሰው የነገርና ምቀኝነት ሱናሜ ለመትረፍ የሚያስችልም ስንቅ አንግቧል ። ኢትዮጵያ ውስጥ / ሀገር/ ፣ አጼ ቴዎድሮስ  ውስጥ / ጀግንነት /  ማር እስከ ፍ ውስጥ ደግሞ / ፍቅር / ተወከሎ ይገኛልና ።
                                                                                                       ኢትዮጽያ
                  አጼ ቴዎድሮስ                                                                               ማር እስከ ጧፍ              

        
‹ ኢትዮጵያ › ቀደም ብሎ የተለቀቀ ነጠላ ዜማ ቢሆንም ከሙሉ አልበሙ ጋር ሳየውም መጠሪያ መሆኑ አያንስበትም ። ሙዚቃው የትልቅ አጀንዳ ባለቤት ነው ። የሞት- ሽረት ጠርዝ ላይ የሚገኘውን ኢትዮጵያነት ይሞግታል ። ኢትዮጵያነት ከዘጠና ሚሊየን ህዝቦች ውህደት በላይ መሆኑን ለማሳየት ባንዲራው ያለውን ክብርና ጸጋ ይዘክራል ።

              « እንኳን ሰማይ ላይ ባንዲራሽን አይቶ
                ኢትዮጵያ ሲባል ማን ዝም ይላል ሰምቶ »

ቴዲ የፖለቲካ ኩርፊያና በደል ማንነትን ለመካድ መሰረት ሊሆን አይችልም ባይ ነው  « ቢጎል እንጀራው ከመሶቡ ላይ ፣ እናት በሌላ ይቀየራል ወይ » በርግጥም ዓለም የሉሲ ልጆች ፣ የነጻነት ምሳሌዎች እያለ የሚጠራቸው አበሾች በየአደባባዩ በርካታ ትናንሽ ባንዲራዎች ተሸክመው ሲያያቸው ያዝናል ። በትልቁ ባንዲራችን ፍቅር ወድቀው የራሳቸውን ለመቅረጽ መነሻ ያደረጉ አፍሪካዊያንም ከንፈራቸውን መምጠጥ ከጀመሩ ቆይተዋል ። እናም የሰንደቅ እና ሀገር ጉዳይ ውሃ ቢወቅጡት እንቦጭ እንደሆነ ቀጥሏል ።

  « ተዉኝ ይውጣልኝ ልጥራት ደጋግሜ
    ኢትዮጵያ ማለት ለኔ አይደል ወይ ስሜ » ያስብላል

ይህ ሙዚቃ ብቻውን የተለቀቀ ሰሞን እንካሰላንቲያ ያማዘዘውም የትሪያንግሉ አንደኛው ማእዘን ሰለሆነ ነው ። ኢትዮጵያነት ግን ያው የነብር ቆዳነት ነው ። ብዙ ሂትለሮች በለስ ቀንቷቸው ኢትዮጵያዊያንን ማጥፋት ቢችሉ እንኳ ኢትዮጵያ የተሰራችበትን ታሪካዊ ፣ ሃይማኖታዊ እና ሳይንሳዊ አሻራዎች መደለዝ አይችሉም ።

በርግጥ አንዳንዶችም ሙዚቃውን አሰታከው የዋህ አስተያየት ሲሰጡ ተሰምተዋል ። አንደኛውና ዋነኛው ወቅትን እየጠበቁ እንዲሁም ሰዎችና ክስተቶች ላይ መዝፈን የጥበብ ሰው ባህሪ አይደለም የሚል ነው ። ይህ አባባል የጥበብ ምንነትን ካለማወቅ ይነሳል ። የጥበብ ግብ የገሃዱን ዓለም ጥሬ እውነት ጥበባዊ በሆነ ኩታ አስውቦ መገኘት ነው ። ስለዚህ ሰዎች እና ክስተቶች ከብዙ በጥቂት የሚቀዱ ምንጮች ናቸው ማለት ነው ።

ሌላው የቴዲ አፍሮን የጥበብ መንገድና ስልት አለመገንዘብ ነው ። ይህ ድምጻዊ በአጭር ግዜ ውስጥ የማይታመን ተቀባይነት ያገኘው  ለምንድነው ? የሚለውን ጥያቄ ስንመልስ  መስመሩን እናገኛለን ። ቴዲ የድፍረት ፣ የፈጣንና ሰፊ ምናብ ባለቤት ነው ። ማንም አቀንቃኝ የሚፈራውን የአንድነትና የመገንጠል ጉዳይ ሲፈልግ አስውቦ ያዜማል ። በፈጣን ምናቡ ወቅታዊና ትኩስ እውነቶችን የውበትና ተዝናኖት ክንፍ ሰርቶላቸው አድማጩ ቤት ድረስ እንዲያንዣብቡ ያደርጋቸዋል ። 

ፖለቲካ ያስፈራራቸውን ወይም ሀገር የረሳቸውን ጀግኖች በፈጠራ ሃውልት ያንጻቸዋል ። እነዚህ ሃውልቶች እንደምናውቃችው አይነቶች የተመረቁ እለት ብቻ የሚነገርላቸው አይደሉም ። ሃውልቶቹን በፍቅር ይተክላቸዋል ፤ እኔና እናንተ ደግሞ ደምና ስጋ ሞልተን ስለነፍሳቸው ዘወትር እናዜማቸዋለን ። በግጥም ዘርፍ « የጸጋዬ ቤት » እንደምንለው ሁሉ ይህን የዜማ አተያይም « የቴዲ አፍሮ ስልት » ማለት ይቻላል ። ታዲያ ይህን በእሱ ፍቃድ ብቻ የሚገኝ ሃያል ስልት እንዳይቀጥል የሚፈልግ ጅላጅል ተደራሲ ማነው ?

የትሪያንግሉ ሁለተኛው ማእዘን « አጼ ቴዎድሮስ » ነው ። በዚህ ዜማ የጀግንነት ከፍታ ታይቶበታል ። የታሪኩ ባለቤት አጼ ቴዎድሮስ ለሀገራቸው ክብር በመቅደላ ተራራ ያደረጉት ተጋድሎ ተዘርዝሯል ። ቴዎድሮስ የተከፋፈለችውን ኢትዮጽያ አንድ ለማድረግ በተደረገው ትግል የአንድነት ምልክት ናቸው ። ለዛም ነው ድምጻዊው
 « ጎንደር ጎንደር የቴዎድሮስ ሀገር
   የአንዲት ኢትዮጽያ ዋልታና ማገር » የሚለው

ቴዎድሮስ በኢትዮጽያ የመሪዎች ታሪክ ልዩ ቦታ ያገኙትም የተከፋፈለች ወይም የተሸነፈች ሀገርን ላለማየት መስዋዐት በመሆናቸው ነው ። ከራስ በላይ ንፋስ የሚል መሪ በችግር ግዜ እጁን ይሰጣል ወይም ይሰደዳል እንጂ ራሱን አያጠፋም ። ድምጻዊው ይህን መስዋእትነት ያስተሳሰረው ከሰንደቅ ዓላማ እና ከቀጣይ መልዕክት ጋር ነው ።
   « ጨክኖ ካሳ ጋተና ኮሶ
     ሞተ ለአንድ ሀገር ባንዲራ ለብሶ »           
      
ቀጣዩ መልዕክትም የተላለፈው በባንዲራው ድልድይነት ነው ። ይህን ባንዲራ ማንሳት ብቻ ሳይሆን የተዳፈነውንም ጀግንነት በብዙሃኑ ላይ እንዲጋባ ይፈለጋል ። ሀገር ለመስራት ጀግኖች ያስፈልጋሉ ። የግኖችን ራእይ ተግባራዊ ለማድረግ የወራሾች ሚና ወሳኝ ይሆናል ። ወራሾች የሞተውን ጀግና በማሰብ ከማለቃቀስ ይልቅ የአሟሟቱን ሚና በመረዳት ላይ እንዲተጉ ይጠበቃል ። ይህን ግን እውን ለማድረግ ቀላል አይደለም ።
 « ግመሌን ላጠጣት ቀይ ባህር ተጉዤ

    አንድ ገመድ አጣው ልመልሳት ይዤ » የሚለው ስንኝ የአንድን ጠንካራ ወራሽ ስጋትና ተስፋ መቁረጥ በምሳሌ የሚያሳይ ነው ። የአጼ ቴዎድሮስን ህልም እውን ለማድረግ ወቅታዊው የፖለቲካ ምህዳር ጠባብ ቢሆንም መልእክት አደራሹ ከያኒ ግን የጋመ ፍላጎቱን ጾታ ሳይለይ ለማስተላለፍ ‹ ሹሩባ › የሚለው ቃል የተመቸው ይመስለኛል ።
  « አንጡ ቆርጣችሁ ከሹሩባው ላይ
    ኪታብ እንሰር እንዳንለያይ »

የትሪያንግሉ ሶስተኛው ማእዘን « ማር እስከ » ይሰኛል ። ሙዚቃው የተመሰረተው የፍቅር እስከ መቃብር ድርሰት ላይ ነው ። ይህ መጽሀፍ በእንግሊዘኛ የመተርጎም እድል ቢያጋጥመው ኖሮ ዓለም ‹ የድርሰት ሉሲ › በኢትዮጵያ ተገኘ ማለቱ ባልቀረ ነበር ።
ቴዲ ይህን ትልቅ መጽሀፍ እንደገዘፈ ለማቅረብ ሞክሯል ። ገጸባህሪያቱን አሳይቶናል ። በተለይ ተፈቃሪዋ ሰብለ ወንጌል መልከ ብዙ ሆና ተስላለች - ብራና ፣ ንብ እና ማር ። ብራና ሆና የፍቅር መወድስ እናነብባታለን ። ንብ ሆና በአንድ በኩል ትጋትዋን በሌላ በኩል የጥቂት አመታት እድሜዋን እንዲሁም ማር ሆና ጣፋጭነትዋን በተለዋጭ ዘይቤ እንመለከታለን ። ይህን ውብ ቋንቋ ቅኔያዊ በሆነ መስተጋብር እያስተሳሰረ አቅርቦታል ።

 « ላሳደገኝ ደብር የስለት ልጅ ሆኜ
   ካህን እንዴት ይፍታኝ ያንቺ እስረኛ ሆኜ
   ማር ጧፍ ሆኖ ገባ - ከመቅደስ
   ነዶ ለኔ ጸሎት ሊያደርስ  »

ቢጫ ለብሳ ገዳም የገባችውን ሴት መንጥቆ ለማውጣት የሚደረገው  ትግል ጠንካራ ነው ። ሆኖም የቱንም ያህል አዋቂ ቢኮን ፍቅር አንበርካኪ መሆኑን እንረዳለን ።

  « ለካ ሰው አይድንም በደገመው መጽሀፍ
    እንደ ሰም አቅልጦ ፍቅር ካደረገው ፍ »         
የቴዲን ትሪያንግል እንደ ጋሪ ለመግፋት ብንፈልግ አራት ጎማዎች ያስፈልጉናል ። ሰምበሬ ፣ አና ንያቱ ፣ ያምራል እና ኦላን ይዞ በአቀራረብ ስልታቸውና ሳቢነታቸው የእኔ ምርጫዎች ናቸው ።           
 ኦላን ይዤ አላፍርም ይህን አውቃለሁ
 ወደ ፍቅር ልሂድ ምን እጠብቃለሁ
 ወደ ፍቅር ጉዞ ተያይዞ
 ቂምን ከሆድ ሽሮ
 ኦላን ይዞ …                                                                  

Sunday, February 26, 2017

አድዋ - ባለ ሺህ ገጽ ምርጥ መጽሀፍ



‹‹ ዳዊት እጁን ወደ ኮሮጆው አግብቶ አንድ ድንጋይ ወሰደ ፤ ወነጨፈውም ፡፡ ድንጋዩ በግዙፉ ጎልያድ ግንባር ተቀረቀረ፡፡ በወንጭፍና በድንጋይ አሸነፈው ›› 

ይህ ጥቅስ የአድዋ ድል መግለጫ ወይም Synopsis ሊሆን ይችላል ። በርግጥም ለእኔ የኢትዮጽያና የኢጣሊያ ጦርነት የዚህ ጥቅስ ሃሳብ እኩያ ነው ፡፡ ጦር ፣ ጎራዴና ውስን ቆመህ ጠብቀኝን የያዘ ህዝብ በውትድርና ጥበብ ከላቀ ፣ በትላልቅ መድፎች በታጠረ   በአጠቃላይ ዘመናዊነትን ከታጠቀ አስገባሪ ጦር ጋር ተናንቆ ድል ጨበጠ ፡፡ ጎልያድ ዳዊትን በትር ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝ ? ወደ እኔ ና ስጋህንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ ብሎት ነበር ። የኢጣሊያ ወታደሮችም ቆመህ ጠብቀኝና ጉራዴ ታጥቀው የሚያቅራሩትን ጀግኖች በንቀት እያዩ በሳቅ ይዝናኑባቸው እንደነበር ግልጽ ነው ። የተናቀ ያስረግዛል እንዲሉ የማይታመን ፣ ብዙዋችን የሚያስደምም ፣ ከአንጸባራቂ ማዕድናት የላቀ ዋጋ ያለው ክስተት በአድዋ ተራራ ተገኘ፡፡
በአድዋ ተራራ ላይ አያሌ ዳዊቶች ተፈጠሩ ።

ቅድመ ታሪክ

· 
                                   አዋጅ አዋጅ የደበሎ ቅዳጅ
የሰማህ ላልሰማ አሰማ….. 
በሚል ነጋሪት የሚኒሊክ ታማኞች ለህዝቡ ቀጭን ጥሪ ማስተላለፍ ጀመሩ ፡፡ ኢትዮጽያና ጣሊያን ውጫሌ ላይ የተፈራረሙት ስምምነት በተለይም አንቀጽ 17 ሁለት ትርጉም በመያዙ ሀገሮቹ ትታዘዘኛለህ - አልታዘዝህም በሚል ወደለየለት ግጭት ለመግባት ተገደዱ ፡፡ ንጉሱም ‹‹ ጉልበት ያለህ በጉልበት እርዳኝ ፣ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ ፣ ለምሽትህ ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በጸሎት እርዳኝ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ ፡፡ አልተውህም …. ዘመቻዬ በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እሰከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ ›› ሲሉ አዘዙ ፡፡
·                 
ወደ አድዋ የተመመው የአጼ ሚኒሊክ ጦር በ10 የጦር መሪዋች የተከፈለ ሲሆን ቁጥሩም ከ73 ሺህ በላይ ነበር ፡፡ እቴጌ ጣይቱ ፣ ራስ መኮንን ፣ ራስ መንገሻ ፣ ራስ ሚካኤል ፣ ራስ ወሌ ፣ ራስ ወ/ጊዮርጊስ ፣ አዛዥ ወ/ጻዲቅና ደጃች ተሰማ ናደው ዋናዋቹ ነበሩ ፡፡ በጣሊያን በኩል በአራት ጄኔራሎች ተዋቅሮ ቁጥሩ 22ሺህ የሚደርስ ነበር ፡፡ ባራቲየሪ ፣ አልቤርቶኒ ፣ ባልዲሴራና ዳቦርሜዳ አዛዦቹ ነበሩ ፡፡ በኢትዮጽያ በኩል የነበረው አቅም 22ሺህ ፈረሰኛ እዚህ ግባ ከማይባል የጦር መሳሪያ ፣ ጋሻና ጦር ጋር ሲሆን ጣሊያን 20ሺህ ዘመናዊ ጠመንጃዋች ከ66 መድፎች ጋር አሰልፋ ነበር፡፡

የአድዋ ጦርነት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓም በዕለተ እሁድ በጠዋቱ ተጀመረ ፡፡ በብዙ መስዋዕትነትም ምሽት ላይ በኢትዮጽያ አሸናፊነት ተደመደመ ፡፡ ድራማው አሰቃቂ ነበር ፡፡ ፊታውራሪ ገበየሁ ጉራዴ መዘው ሲገቡ በጥይት ተመቱ ፡፡ ይሄኔ የኢትየጽያ ጦር መደናገጥና መረበሽ ታየበት ፡፡ የጄኔራል አልበርቶኒ በቅሎ በጥይት ሲመታ ጄኔራሉ ወደቀ ፡፡ ወዲያው በኢትዮጽያ አርበኞች ቁጥጥር ስር ዋለ ፡፡

አሁን ደግሞ የጣሊያን ጦር ተፈታ ፡፡ እረ ጎራውና የፍየል ወጠጤው በአንድ በኩል ሲሰማ የቁስለኛው የድረሱልኝ ጩሀት በሌላ በኩል አካባቢውን ገሃነም አደረገው ፡፡ በኢትዮጽያ በኩል 4ሺህ ሰው ሲሞት 6ሺው ቆሰለ ፡፡ በጣሊያን በኩል 5179 ሲሞት 1429 ያህሉ ቆሰለ ፡፡ 1865 ያህሉ ተማረከ ፡፡ በኢትዮጽያ በኩል የደስታ ፈንጠዝያ ሲከበር ጣሊያኖች ሮምን በተቃውሞ ሰልፍ ደበላለቁት ፡፡ አጼ ሚኒልክ በሀገር በቀል ሻምፓኝ ሲታጠቡ ጠ/ሚ/ር ክሪስፒ ሽምቅቅ እንዳለ ስራውን ለቀቀ ፡፡

የድህረ ታሪክ ሽፋን

ጄኒራል ባራቲየሪ ለሮም ህዝብ ‹‹ በቅርብ ቀን ሚኒልክን በቀፎ ውስጥ አስሬ ሮማ አመጣዋለሁ !! ›› በማለት ፎክሮ ነበር ፡፡ በወቅቱ ከነበረው የሁለቱ ሀገራት ልዩነት አንጻር ለዚህ ንግግር ድጋፉን መቶ መቶ የማይሰጥ ማነው ? ጸሃይ በምስራቅ አቅጣጫ መውጣት ታቆማለች የሚል ቋሚ እውነት ለመሻር የሚከጅል እብድ ከየት ማግኝት ይቻላል ?

ግና ዕድሜ ልክ ልናከብራቸው በሚገባን የቀድሞ ትውልዶች ልዩ መስዋትነት የማይታመን ድል ተገኘ ፡፡ ይህ እንዴት ይሆናል ? ዓለም በተገቢና በጦርነት መስፈሪያ ሂደቱን ለክቶ ውጤቱን አስልቷል ፡፡ የኢትዮጽያን ሩጫ በፎርፌ ከመሸነፍ ይልቅ ተሳትፎን ለማጠናከር የሚረዳ ያህል ነበር የታመነበት ፡፡ ታዲያ ፍጥጥ ያለው ውጤት እንዴት ተቀየረ ? ዳኛው ምን ነካው ? ለድሃ ፣ ጉቦ ለማይሰጥ ፣ ዘመድ ወዳጅ ለሌለው ተከሳሽ አይደለም ትናንት ዛሬስ ቢሆን ፈርዶ ያውቃል እንዴ ? ይሄ ተጠራጣሪነትን / skepticism / የሚያጠናክር ፍልስፍና ነው ? ይሄ ልክ እንደ አሰምፕቶት / asymptote /  መስመር ላይ ለመተኛት የማይችል አልጄብራ ነው ? ይሄ በነሌኒንም ሆነ በነ ጆህን ሎኬ የፓለቲካ አስተምህሮ ውስጥ ምዕራፍ ያላገኝ አጀንዳ ነው፡፡

ለዚህም ነው ብዙ ጸሀፍት የአድዋን ድል የሚገልጹበት ቋንቋ አስገራሚ የሚሆነው ፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ታላቅ የተወላጅ ሃይል መነሳቱ ታወቀ ያለው በርክሊይ አበሾች አደገኛ ህዝቦች መሆናቸው ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ተጽፎላቸዋል በማለት የተዘነጋ እውነት እንዲዋጥ የገፋፋው ፡፡ ማርገሪ ፐርሃምም አድዋ ኢትዮጽያን የዓለም ካርታ ውስጥ አስገባት በማለት መሳጭ አስተያየት ሰጥቷል ፡፡
ይህን ታሪክ ለምን ማኮሰስ አስፈለገ ?
እስካሁን ይህን አንጸባራቂ ድል ስናከብር ያላጓደልነው ዓመታቱን መቁጠር ላይ ነው ፡፡ እያከበርን የምንገኝው አድዋ አደባባይ በመገኘት የማርሽ ባንድ ማሰማት ፣ የአርበኞችን ቀረርቶ መከታተል ፣ የአስተዳደሩ ተወካይ ያበባ ጉንጉን ሲያስቀምጡ መታዘብ ፣ ግንኙነቱ የራቀ ንግግር ማዳመጥ ነው ፡፡ የቀጣዩም ዓመት መርሃ ግብር ከዚህ አይርቅም ፡፡ እውነት ይህን ታሪክ እንዴት እያነው ነው ? እንደምን እየተረጎምነው ነው ? በምን አይነት መልኩስ እያከበርነው እንገኛለን ?

እንደ ድሉ ታላቅነት ለምን አድዋ ተራራዋች ስር አላከብርንም  ? የአባቶቻችንን ክብር የሚያጎላና የመጪውን ትውልድ መንፈስ የሚያጠናክሩ ልዩ ልዩ ኪነጥበባዊ ዝግጅቶቸን ማቅረብ እየተቻለ አልተደረገም  ፡፡ እንደ ካፓርት የሚሞቁ ታሪክ ቀመስ ጥናቶችን ማስተላለፍ እየተቻለ አልተፈለገም ፡፡ የውጪ ቱሪስቶች እንደ ጥምቀትና መስቀል እንዲጎርፉ የሚያደርግ ቋሚ ስራዋችን መስራት ቢፈለግ የሚከብድ ባልሆነ ነበር ፡፡ የአድዋን ሜዳዋች በሙዚየምና በመዝናኛ አገልግሎቶች ፣ የታሪካዊ ተራራዋቹን ግርማ ሞገስ ደግሞ እንደ ገና ዛፍ ማብረቅረቅ ወገቤን የሚያሰኝ አይደለም - ቢያንስ ለአንድ ሁለት ተሃድሶ የሚወጣውን ወጪ ቆንጠጥ አድርጎ መያዝን ነው የሚጠይቀው ፡፡ እንደ ቻይና ግንብ መወጣጫ ሰርቶም መዳረሻው ላይ የፈለገ እንደ ጀግኖቹ ዘራፍ እያለ እንዲያቅራራ ፣ ያልፈለገ ደግሞ የአባቶቻችንን የከበረ መስዋዕትነት ከልቡ ተመስጦ እንዲያስብ ማድረግ ፍጹም የሚያስደስት ነው ።

ሞኝ አሞራ ያባቱን ዋሻ ይጠየፋል አሉ ። አሞራው ዋሻው የቀፈፈው በተራ ጅልነቱ ነው ። እኛ የቀድሞ ማንነታችንን ጥቂት እንደቀረው ደናችን እየጨፈጨፍን ነገ የሚያጠፋንን በረሃ ለመፍጠር የምንተጋው ባለማወቅ ሳይሆን በተራ ጥላቻና ትዕቢተኝነት በወለደው የዘቀጠ አስተሳሰብ ነው ።

ግዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል እንዲሉ ከታላቁ የአድዋ ድል ጀርባ ታላቁ አጼ ሚኒሊክ አሉ በሚል የተጃጃለ ሃሳብ የህዝቡን መብትና ጥያቄም እየጨፈለቅን ነው ። በርግጥም አፍሪካዊ ድሉን አስተባብረው ኩራት እንዲፈጠር የአንበሳውን ድርሻ የወሰዱት አጼ ሚኒሊክ ናቸው ። ታላቅን ጀግና እንደታላቅነቱ ማክበር እንጂ በሀገር ውስጥ ጦርነት ... ቆርጧል ፣ ... ተርትሯል  እያሉ በታሪክ ውስጥ እንዳላለፈ ሁሉ ስሙን ለመደምሰስ የሚደረግ ሩጫ የትም አያደርስም ። ምክንያቱም ሰቅጣጭ የጦርነት ታሪክ ባላት ኢትዮጽያ ግዜ ሰጥቶት የነገሰው መሪ ሁሉ የራሱን ስርዓት ለማስጠበቅ ንጹሃንን ገድሏል ፣ ጨፍጭፏል … እስኪ ይህን አላደረኩም የሚል የፖለቲካ ስርዓት / ሌላው ቀርቶ ጠመንጃ የታጠቀ አማጺ ድርጅት / እጁን ያውጣ - በፍጹም አይገኝም ።
ይህ እንዲሆን ባይፈለግም ሆኗል ። ካለፈ ስህተት ተምሮ ማለፍ ይሻላል ወይስ ታሪካዊ ድሉን በመጨፍለቅ የማጣጣት ስራ መስራት ? ሚኒሊክ ሰዎችን ስለገደሉ ሃውልታቸው ይፍረስ ? የአድዋ ድል ትቢያ ይልበስ ? ጀግንነታቸውን ከርቸሌ አስረን ስማቸውን በየሚዲያውና በየስብሰባው እናጥፋ ?

ይህን ሁሉ በማድረግ በህዝቡ ውስጥ ያላቸውን ሚዛን ደፊ ፍቅርና ክብር መቀነስ አይቻልም ። ምናልባት ይበልጥ በጣም እየገነኑ ይሄዳሉ እንጂ ። ስለዚህ አስተዳደራዊ ችግራቸውን እንደመማማሪያ እያነሳን ዓለም የተቀበለውን ድልም በተገቢው መልኩ ማስተናገዱ ይበጃል ። ለፖለቲካ ፍጆታም ሆነ ከታሪክ ተጠያቂነት ለመዳን የተሻለው መንገድ ይኀው ነውና ።

የድህረ ታሪኩ አስኴል
የአድዋ ድል ውጤቱ ብዙ ነው ፡፡ ባህልን ለመውረር የተደረገ ስልትን ያኮላሸ ድርጊት ነው….. ትልቅ ስብዕናና ድፍረት ያላቸውን ህዝቦችንና የጦር መሪዋችን ለአለም አስተዋውቋል….. በጭቆና ስር ለነበሩ ጥቁር ህዝቦች በሙሉ ተስፋና መነቃቃትን ፈጥሯል….. የአውሮፓ ተስፋፊዎች በሰው ልጆች ላይ ሲፈጽሙት የነበሩትን ኢ- ሰብአዊና ኢ- ፍትሃዊ ስርዓት ቆም ብለው እንዲመረምሩ ያሰገደደ ነው ፡፡ ይህ ድል ክብርና ነጻነታቸውን የተገፈፉ የዓለም ህዝቦች በሙሉ ከጭቆና ቀንበር እንዴት መውጣት እንደሚችሉ የሚያስተምር ባለ ሺህ ገጽ ምርጥ መጽሀፍ ነው፡፡


Wednesday, September 2, 2015

ኢትዮጽያዊው < ኢንደሚክ > ጎሳ


 

                    ኢትዮጽያን በብሮሸር ፣ በበራሪ ወረቀት ፣ በቀን መቁጠሪያ ፣ በመጽሄትና ጋዜጣ የሚያስተዋውቁ ብዙዎቹ ጽሁፎቻችን እንዲህ ብለው የሚጀምሩ ናቸው
                   « ኢትዮጽያ የቱባ ባህል ፣ ወግ ፣ ትውፊት እና መልከዓምድር መገኛ ምድር ናት »
ሀገራችን በደን ሀብትዋ አርባ በመቶ ከነበረው ተራራ ቁልቁል ተምዘግዝጋ ሶስት በመቶ ላይ ተሰባብራ የተኛች ብትሆንም ፣ ያሏትን ጥቂት ዝሆኖች ጥርሳቸውን በጥይት አራግፋ በድዳቸው እንኴ እንዳይኖሩ ያልፈቀደች  ብትሆንም ፣ አውራሪስ የተባለውን እንስሳ ከምድረ ገጽ አጥፍታ « አቶ አውራሪስ » በሚባሉ ሰዎች ተጽናኑ የምትል  ብትሆንም በሁለተኛው አንቀጽ ላይ የሚከተለው እየተጻፈላት ይገኛል ።
« ኢትዮጽያ የብርቅዬ አእዋፋት ፣ ዕጽዋትና እንስሳት መናኀሪያ ሀገር ናት »
በተለይም ቁጥራቸው እየተመናመነ የሚገኙት ዋሊያ ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ ፣ የሚኒሊክ ድኩላ ፣ ቀይ ቀበሮ ፣ የስዋይን ቆርኬና የደጋ አጋዘን በሌላው ዓለም የማይገኙ ብቸኛ አንጡራ ሃብቶቻችን ቱሪስቶችን በመሳብና ከፍተኛ የገቢ ምንጭ በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ይለናል ማስታወቂያው ። 
 እኔ ደግሞ ይህ የዘወትር ጽሁፍ የዘነጋው አንድ አቢይ ነገር አለ በማለት በቀጣዩ አንቀጽ ጣልቃ መግባት ፈልጌያለሁ ። የፅሁፉ እንድርድሮሽም « ልዩ ባህልና የአኗኗር ዘይቤ እያሳዩ የሚገኙ ማህበረሰቦች < Endemic Race  > ተብለው መጠራት ይኖርባቸዋል የሚል ነው ።

‹‹ Endemic ›› ከሆኑ የሃገራችን ጎሳዎች አንደኛው ደግሞ  በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኙት ሙርሲዎች  ናቸው :: እንዴት ቢባል ከንፈሩን ተልትሎ / በአሁኑ ወቅት / ገል የሚያስቀምጥ ፣  ራቁቱን በዱላ የሚከታከት እና  ሙሉ ብሄረሰብ  ሰዓሊ የሆነበት ሀገር በየትኛውም የዓለም ጫፍ አይገኝምና  ፡፡  የሙርሲን ኢንደሚክነት እያነሳሁ መሞገት ልጀምር ።

የብርቅዬነት መገለጫ አንድ - ከንፈር
የሙግቴ ማጠንጠኛ - ያላለቀ ውበት

የሙርሲ ብሄረሰብ ልዩ ከሆነበት አንደኛው ገጽታ የሴቶች ከንፈር ጉዳይ ነው ፡፡ አብዛኛው ሴቶች ከንፈራቸውን ሲተለተሉ የታችኛዎቹን ጥርሶችም ያስወግዳሉ ፡፡ ምክንያቱም ጥርሱ ካለ ገሉን በአግባቡ ለማስቀመጥ ስለማይቻል ፡፡ አንድ ሴት ገል በሚያንጠለጥለው ከንፈር ትወደስ እንጂ ጥርሷን በመንቀሏ የምታገኘው ሞራላዊ ጥቅም የለም ፡፡ ጥርስ ለከንፈር ውበት ሲል ራሱን መስዋእት ያደረገ አካል በመሆኑ ሊታዘንለት በተገባ ነበር ፡፡

በታሪክ ሱያ የተባሉ የብራዚል ወንዶች ፣ ሳራ የተባሉ የቻድ ሴቶች ፣ ማኮንዴ የተባሉ የሞዛምቢክ ሴቶች ከንፈራቸውን ይተለተሉ ነበር ፡፡ ይህ ድርጊት ግን ዛሬ ቆሟል ፡፡ ያልቆመው በኢትዮጽያ ብቻ ነው ፡፡ በርግጥ በሀገራችን ድርጊቱ ከመጥፎ ባህላዊ ድርጊቶች ጎራ የተቀላቀለ ቢሆንም መጥፎነቱ ተጨብጭቦለት ፍጻሜ ማግኘት አልቻለም ፡፡ በቦታው ስገኝ ለምን ? የሚለውን ጥያቄ ለነዋሪዎቹ አንስቼያለሁ ።

ሙርሲዎች እኛ መጥፎ ያልነውን ድርጊት ገልብጠው አይደለም ዘቅዝቀው ለመመልከት እንኴን ፍቃደኞች  አይደሉም ፡፡ በርግጥ ማነው ዛሬ በጣም ከረፈደ ተነስቶ ሺህ ዘመናት ያሳለፈውን ‹ እውነት › - ‹ እውሸት › መሆኑ የተገለጠለት ? የዛሬ ወጣቶች በትምህርትና ባህል ፍትጊያ መሃል የሆነ አዲስ ሀሳብ ፈንጥቆ ሊታያቸው ቢችልም ማህበረሰቡን የሚመራው አዛውንት ክፍል አንድም ለቆየው ባህሉ በሌላ በኩል እያገኘ ካለው ጥቅም አኳያ ከንፈር ትልተላን የተመለከተ አዲስ አንቀጽ ለመጨመር ከልቡ ፍቃደኛ አይሆንም ፡፡ ጠንካራው እውነት ይህ ነው ። በዚያ ላይ ቱሪስቶች ብርቅዬ እንስሳቶቻችንን ከማየት በበለጠ ትኩረት የሚሰጡት የሰው ልጅ ልዩ ባህል ወይም ባህሪ ላይ ነው ። በየቀኑ እንደ አሸን እየፈሉ የሚገኙት አስጎብኚ ድርጅቶች ዓመታዊ የገቢ እቅዳቸው ግቡን የሚመታው በሰሜን ተራራዎችና ሶፉመር  ድንቅ ውበቶች ብቻ እንዳልሆነ ያውቁታል ። አቌም መያዝ ያልቻለው መንግስት ደግሞ መሃል ላይ አለላችሁ ። ከንፈር መተልተል ጎጂ ባህል ነው እያለ በስሱ ያስተምራል ፣ ታይተው የማይጠገቡትን ሙርሲዎች ሳትመለከቱ ወደ ሀገራችሁ እንዳትመለሱ እያለ ደግሞ በወፍራም ድምጽ ፈረንጅ በተገኘበት ሁላ ይሰብካል ። እነዚህ አገም ጠቀም አሰራሮች በሙሉ መሬት ላይ ያለውን ሀቅ ለመቀየር የሚያስችሉ አይሆኑም ፡፡

ግራም ነፈሰ ቀኝ የሙርሲ ሴቶች ከንፈርና ገል እንደ አክሱም ሃውልቶችና ላሊበላ ውቅሮች የገዘፈ ስም አግኝተዋል ፡፡ ይህ እስከ 16 ሴ.ሜ ሰፍቶ ገል የሚሸከመው ከንፈር በግርማ ሞገሱ ትንሽ ትልቁን ቀኑን ሙሉ እንዳስደመመ ይቀጥልና አመሻሹ ላይ ሌላ ገጽታ ይላበሳል  ፡፡ ገሉ ከመሃሉ ሲለየው ለባለጌጧ እፎይ ቀለለኝ አይነት ስሜት ሊፈጥር ይችል ይሆናል ለሌላው ተመልካች ግን አሳዛኝ ስሜት ነው የሚያሳድረው ። ቋንጣ የመሰለው ከንፈር ይሄኔ  ምቾት አይሰጥም ፡፡ ምናልባትም ውበቱ መጀመርን እንጂ ማለቅን አያሳይም ።

ከንፈራቸውን ለመተልተል ፣ የሚያጠልቁትን ገል ውበት በተላበሰ መልኩ ለመስራት የማይሰንፉት የሙርሲ ሴቶች ከንፈራቸው ደምቆ ውሎ ደምቆ እንዲያድር የሆነ መላ አለመፍጠራቸው ግን ይገርማል ፡፡ ከሰሩ ላይቀር አገጫቸውን ሰንጠቅ አድርገው የተንዘለዘለውን ስጋ ተጠቅልሎ እንዲደበቅ ቢያደርጉ ምን ነበረበት ? ለካስ ካንጋሮን አያው
ትም …

የብርቅዬነት መገለጫ ሁለት - ዶንጋ
የሙግቴ መዳረሻ - ያልተሰራበት ኢንቨስትመንት

ሙርሲዎች ጨካኝ የሆነ ባህል ተከታይ መሆናቸውን ብዙዎች ይናገራሉ ፡፡ በተለይም በረጃጅም ዱላ የሚያደርጉት ድብድብ ወይም ዶንጋ ለወንድ ልጆች የጀግንነት ክብር መግለጫ ፣ የሚስት ማግኛ ብሎም የመከራ መቁጠሪያ ምዕራፍ ነው ፡፡ ለዚህ ባህላዊ ውድድር ጎረምሶች ተደራጅተው ይቀለባሉ ፡፡ ሙገሳና ጭፈራ ያጅባቸዋል ፡፡  የሙርሲ ወንድ ቢያንስ ከአንድ ወንድ ጋር ይህን ግጥሚያ ማከናወን አለበት ፡፡ አሸናፊው በሴቶች ተከቦ ወደፊት የሚፈልጋትን ሴት እንዲመርጥ ዕድል ያገኛል ፡፡ በዚያው ልክ ተቀልበውም እስከወዲያኛው ሊያሸልቡ ይችላሉ ፡፡የሀዘን ጥላም ዘወትር  ጎናቸው ነው ፡፡  

የአማራው ብሄረሰብ ‹ በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ ! › እንደሚለው ሁሉ ሙርሲዎችም በዶንጋ ለሚሞቱ ወጣቶች ጥብቅና አይቆሙም ፡፡ መቼም ነጭ የኖራ ስዕል ብቻ በለበሰ ባዶ ገላ በቀላሉ በማይሰበር ዱላ ከመከትከት አንደኛውን የስፔን ቀውስ ሊግ ውስጥ ገብቶ በበሬ መወጋት ሳይሻል አይቀርም ፡፡

ሽማግሌዎች ዶንጋ ወጣቱ ህብረተሰብ መከራን እንዲችልና ጠላትም እንዳይፈራ ቀጥተኛ ያልሆነ አስተዎጽኦ ይፈጥራል ባይ ናቸው ፡፡ ይህ ውድድር ህይወት እስከመቅጠፍ የሚያደርስ ከሆነ ላይቀር ሙርሲንም ሆነ ሀገሪቷን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል የላቀ የኢንቨስትመንት ሀሳብ ማመንጨትይገባል ፡፡ ከዚህ አንጻር እኔ አንድ ሃሰብ አለኝ ፡፡ መጀመሪያ የዓለማችንን ምርጥ - ምርጥ ውግሪያዎች እየለቀሙ ማጥናት ፡፡ ዶንጋ ባህሉን ጠብቆ እንዴት ዓለማቀፍ ውድድር መሆን ይችላል የሚለውን ደግሞ ለጥቆ ማሰብ - መቀመር ፡፡

ለምሳሌ ያህል ብዙ ተመልካች ያለው የነጻ ትግል ስፖርት የሚከናወነው በፕሮሞተሮች ነው ፡፡ እነዚህ ፕሮሞተሮች ድርጊቱን በቴሌቪዥን ፣ በማስታወቂያ ፣ መጽሄትና ኢንተርኔት ያስተዋውቃሉ ፡፡ ታዋቂ ቡጢኞች በመዝናኛው ቻናል ብቅ እያሉ ቡራ ከረዩ እንዲሉ ያደርጋሉ ፡፡ እንግዲህ ይህ አሰራር በዚህ መልኩ ነው ቀስ በቀስ የአሜሪካ ታዋቂ ባህል እንዲሆን የተደረገው ፡፡

የታይላንድ ኪክ ቦክስንም ብንመለከት ከነጠላ መነሻነት ነው ዛሬ አድጎ ትልቅ ካፒታል መፍጠሪያ የሆነው ፡፡ የሀገሪቱ ወታደሮች ጠመንጃ በሌለበት ወቅት እንደ አጋር ተጠቅመውበታል ፡፡ ንጉሶች ለመዝናናት የጦር እስረኞች ደግሞ ለነጻነታቸው በዚህ ፍልሚያ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ቆይተዋል ፡፡ ዛሬ ስፖርቱ ኤሽያን አልፎ አውሮፓ ደርሷል ፡፡

ካራቴንም ብንመለከት ከተፈጠረ ከ 1 ሺህ ዓመት በላይ አስቆጥሯል ፡፡ ሲጀመር በገዳም ተዘውትሮ የሚሰራ ጥበብ ቢሆንም ኃላ ላይ የቻይና ገበሬዎች ከታጠቁ ሽፍቶች ጥቃት ራሳቸውን ለመከላከል ጋሻ አድርገውታል ፡፡ ቀስ በቀስ በመላው ዓለም በመዳረስ ለፊልምና ለተለያዩ ውድድሮች የማይነጥፍ ማዕድን ሆኖ እያገለገለ ይገኛል ፡፡

በመሆኑም ዶንጋን እንደ ነጻ ትግል ፣ ኪክ ቦክስና ካራቴ የላቀ ደረጃ ለማድረስ የማይቻልበት ሁኔታ ስለማይኖር ጉዳዩን በጥሞና ማሰብ ይገባል ፡፡

የብርቅዬነት መገለጫ ሶስት - የገላ ላይ ስዕል
የሙግቴ መዳረሻ - ተንቀሳቃሽ ሸራ
በአንድ ከተማ ውስጥ 10 ሺህ ህዝብ ይኖራል እንበል ፡፡ ይህ ሁሉ ህዝብ ነጋዴ ወይም መሃንዲስ ወይም አንባቢ ሊሆን አይችልም ፡፡ ገሚሱ አተረፍኩ የማይል ነጋዴ ፣ ገሚሱ ከባታ እስከ ባለእግዚአብሄር ሳያዛንፍ ቀን መቁጠር የሚችል የመንግስት ሰራተኛ ፣ ሌላው በሀገርና ህዝብ ስም የነገር ሰበዝ ሲመዝ የሚመሽለት ፖለቲከኛ  ወዘተ ነው የሚሆነው ። የሙርሲ አስር ሺህ ህዝብ በሙሉ ግን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሰዓሊ ነው ፡፡ እንዴት ከተባለ ቢያንስ በየሳምንቱ የራሱንና የሌሎች ገላ ላይ በነጭ ኖራ ቅርጻ ቅርጽ ያቀልማልና ፡፡ አንዱ የአንዱን ጀርባና ፊት በአንክሮ እየተመለከተ ቅቡን ያደንቃል ወይም እንዲህ መሆን ነበረበት እያለ ልማታዊ  አሰተያየቱን ይሰነዝራል ። አይነቱና ስልቱ ይለያይ እንጂ ሙርሲ የሰዓሊዎች ሀገር ነው ፡፡

የሀገራችን ሰዓሊዎች ስራዎቻቸውን ለተደራሲው የሚያቀርቡት ለተወሰነ ግዜ በጋለሪ ወይም በሚከራዩት ሆቴል ውስጥ ነው ፡፡ ለማየት እድል የሚያጋጥመውም በዛው መጠን በጣም ውስን ነው ፡፡ የሙርሲዎች የስዕል ሸራ ግን ሰውነታቸው በመሆኑ ጋለሪ ውስጥ የታጠረ አይደለም ፡፡ በየሜዳው ፣ በየተራራውና በየመንገዱ ይዘውት ይንቀሳቀሳሉ ፡፡ አላፊ አግዳሚውም ይመለከታቸዋል ፡፡ ሲፈልግ አብሮአቸው ፎቶ ይነሳል ፡፡ የሙርሲ ሰዓሊ ከከተማው የተማረ ሰዓሊ የሚቀርበት ጉዳይ ‹ ፈርምልኝ ? › የሚል ጥያቄ የሚያቀርብለት አለመኖሩ ነው ፡፡ ‹ ተንቀሳቃሽ ሸራ › መምሰሉን ግን ከተሜዎች በተሞክሮነት ሊያጤኗት የምትገባ ጉዳይ ናት ፡፡

ለሙርሲዎች የቀለም አባቱ ነጭ ነው ፡፡ አንዳንዶች ነጭ ቀለም ከብትን ከማርባት ጋር ይያያዛል ይላሉ ፡፡ የስዕሎቹ መሰረት ክብ ፣ መስመር ፣ ነጥብ እና ግማሽ ክብ ናቸው ፡፡ የእነዚህ መገጣጠም ፣ መለያየት ፣ መደራረብ በአጠቃላይ መወሳሰብ ነው አይን በቀላሉ የማይፈታውን አብስትራክት የሚፈጥረው ። ዞሮ ዞሮ ቅርጽና ቀለሞቹ ትርጉም ባዘለ መልኩ እንደሚቀመጡ ይገመታል ፡፡ ምክንያቱም ስዕሎቹ ውስጥ የሂሳብ ፣ አስትሮኖሚ ፣ የእንስሳት፣ የተፈጥሮና የመሳሰሉ ብልጭታዎችን መመልከት ስለሚቻል ፡፡

በርግጥ ስዕሎቹን ለማወቅ ሰዓሊዎቹን ቀድሞ መረዳት ይጠቅማል ፡፡ አስተሳሰባቸው ፣ ፍልስፍናቸው ፣ የኑሮ ዘይቤያቸውና የእምነቶቻቸው ጸጋዎችን እየገለጹ ማንበብ የማንነታቸው መዳረሻ ላይ ያደርሳል ፡፡ ስዕል የውበታቸው መገለጫ ብቻ ሳይሆን የህልውናቸው ህገ ደንብ ወይም ህገ መንግስት ሆኖ ሊገኝ ይችላል ፡፡ ይህ ካልሆነ ታዲያ እንዴት የአንድ ሀገር ሙሉ ህዝብ ሰዓሊ ሆኖ ይገኛል ? ሁሉም ለራሱ ህገ መንግስት ታማኝና ተገዢ ቢሆን እንጂ ፡፡

በመሆኑም ነው የሚመለከታቸው ክፍሎች ሙርሲን ብርቅዬ የሰው ዘር ወይም ኢንደሚክ ብለው መመዝገብ የሚኖርባቸው ።

 


Thursday, August 13, 2015

የአቶ መለስ ውዳሴና ርግማን ሲታወስ




እንዳንዶች እምነት ባለራዕዩ እንዳንዶች እምነት አምባገነኑ መለስ ያረፉት ነሀሴ 20/2012 ብራስልስ ውስጥ ነበር - እነሆ አንዳንዶች ለሶስተኛው ሙት አመት ዝክር ሻማ እያበሩ ለፈጣሪ ሊፀልዩ እነሆ አንዳንዶች ርችት እየተኮሱ ፈጣሪን ሊያመሰግኑ መንገድ ላይ ናቸው ።

አቶ መለስ ከቤተመንግስት ከተሰወሩበት - እስከተቀበሩበት እለት የነበረውን ፌስቡካዊ ልብ አንጠልጣይ ድራማ በማስታወስም መዘከር ይቻላል ይለናል - ይህ ጽሁፍ ፡፡

አቶ መለስ በጠና ታመው ለ60 ቀናት ከቤተመንግስትና ከሀገሪቱ ሚዲያ ሲጠፉ ስውር የነበሩት ሁለት ትላልቅ ጎራዎች በአካል ግዘፍ ነስተው መድረኩን ሲሞሉት ታየ ። በአዎንታዊና አሉታዊ ቃለተውኔቶች መፈነካከት - በምፀትና አሽሙር አርጩሜ መገራረፍ ደመቀ ። እልፈተ ዜናቸው ከተሰማ በኋላ 13 ቀናት ለሀዘን መግለጫነት ሲመደብ ሁለቱ ተጻራሪ ሀሳቦች በጥሩ ነው - መጥፎ ነው መልዕክት እንካሰላንቲያ ተባብለዋል ፡፡ ግብዓተ መሬቱ ከተፈጸመ በኃላም በውርሳቸው ዙሪያ /legacy/ ተቃራኒ አስተያየቶች እየተደመጡ ቀጥለዋል፡፡
                            
በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በአቶ መለስ ዜናዊ ዙሪያ ይበልጥ እየተከራከረ የመጣው መታመማቸው ከተሰማ በኋላ ነበር ፡፡ አስቀድሞ መታመማቸው አለመገለጹ ተቃራኒው ክርክር እንዲጦዝ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል ማለት ይቻላል ፡፡ በተለይም መቀመጫቸውን ውጭ ያደረጉ መገናኛ ብዙሐን የአቶ መለስን በጠና መታመም ደጋግመው ሲገልጹ በመንግስት በኩል ዝምታ ተመርጦ ነበር ፡፡ ይህ ዝምታ ከአቶ መለስ መሰወር ፣ ሊፈጠር ከሚችለው መደናገርና የፖለቲካ አለመረጋጋት ጋር የከፋ ውጤት ማስከተሉ የማይቀር መሆኑ እያፈጠጠ ሲመጣ ግን መንግስት ማስተባበያ መስጠት ጀመረ ፡፡

የአቶ መለስ ደጋፊዎች ወደ ሰማይ የሚለቋቸው ወሬ ያቋቱ ሰላማዊ ፊኛዎች ከተቃራኒው ወገን በተተኮሰ የብእር ጥይት ተሸመልምለው ቁልቁል ይወርዳሉ ፡፡ የአቶ መለስ ተቃዋሚዎች በመሪው ህይወትና ተግባር ላይ ያጠነጠኑ አደገኛ መረጃዎችን ለንባብ ሲለቁ ፣ ደጋፊዎች የማርከሻ መድሃኒቶችን ፈጥነው ያሰራጫሉ ፡፡ ሌሎች ከመረጃው በታች በሚገኝ አስተያየት ላይ ይጠዛጠዛሉ ፡፡ አንዳንዴም ከደረጃ በታችም ወርደው ይሰዳደባሉ ፡፡

“ አቶ መለስ በፍጥነት እየተሻላቸው ነው በቅርቡም ስራ ይጀምራሉ ! ” ለሚለው መልዕክት “ አቶ መለስ በጠና ታመዋል ፣ በቅርቡም ይሞታሉ ፡፡ የሚመጣው አስከሬናቸው ነው ” የሚል ተቃራኒ ምላሽ ይዘጋጃል ፡፡ እነዚህ ጥቅል ሀሳቦች በጣም እየቀጠኑ “ መለስ ከሞተ ቆይቷል ! ” “ የጠላት ወሬ ነው ! መለስ አልሞቱም ! ” እስከሚለው ደረጃ አዳርሶ ነበር ፡፡

በርግጥም “ መለስ አልሞተም ! ” ለሚለው ወገን መከራከር የሚገባው መንግስት በየቀኑ መግለጫ አልሰጥም የሚል አቋም በማራመዱ የአቶ መለስን መሞት አስቀድሞ በውስጡ የተቀበለው ህዝብ ሊበረከት ችሏል ፡፡ የሞቱ ዜናም ያልተነገረው ኢህአዴግ የተፈጠረበትን ያለመረጋጋት ችግር ለማስተንፈስና ተኪ መሪዎችን ለመምረጥ ጊዜ መግዛት በመፈለጉ እንደሆነ የራሱን ግምት እስከመዘንዘር አድርሶታል ፡፡ 

በግራና ቀኝ የሚነሱ የፌስ ቡክ አስተያየቶች እየቆዩ ደግሞ አቶ መለስ መሞት የሚገባቸው ወይም ጤና የሚያስፈልጋቸው ከምን አንጻር እንደሆነ ሁሉ መወያየት ጀምረው ነበር ፡፡ ተቃዋሚው ወገን አቶ መለስ ዜናዊ “ ዘረኛ ፣ ሀገር ሻጭ ፣ ከፋፋይ ፣ ገዳይና አምባገነን በመሆኑ ሞት ይገባዋል ” ሲል ደጋፊው ወገን “ አቶ መለስ ዴሞክራት ፣ የልማት መሀንዲስ ፣ የአፍሪካ ድምጽ ፣ ለኢትዮጽያ ጥቅም ያደሩና ባለራዕይ በመሆናቸው ረጅም ዕድሜና ጤና እንመኝላቸዋልን ” በማለት በአስተያየቱ ምላሽ ይሰጣል ፡፡

የአቶ መለስ የህመም መንስኤ በግልጽ አለመታወቁም በክርክሩ የሚወረወሩት ሻሞላዎች ይበልጥ የደመቀ የእሳት ብልጭታ እንዲፈጥሩ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ፡፡ መንግስትና ደጋፊው ወገን ቀላል ህመም ነው ለዚያውም በእረፍት መውሰድ ብቻ የሚወገድ ሲል ተቃራኒው ወገን የአቶ መለስ ህመም ካንሰርና የጭንቅላት ዕጢ በመሆኑ ይሞታሉ የምንለው ለቀልድ አይደለም በማለት ይሟገት ነበር ፡፡

ቆይቶም ቢሆን ግን የአቶ መለስ መሞት በመንግስት ሳይቀር ተረጋገጠ ፡፡ መንግስት አሁንም ባወጣው የሀዘን መግለጫ ላይ መሪው ለእልፈት ህይወት የተዳረጉት በኢንፌክሽን መሆኑን ነበር የገለጸው ፡፡ በምን አይነት ኤንፌክሽን ? - አይታወቅም ፡፡ ኢንፌክሽን በራሱ ለሞት ያበቃል ? - አይታወቅም ፡፡ ለኢንፌክሽኑ መንስኤ የሆነው በሽታ ምንድነው ? - አይታወቅም ፡፡ በዚህ ደግሞ መጠዛጠዙ ቀጠለ ፡፡

                             “ አቶ መለስ የሞቱት በማይድን ካንሰር ነው ”
                             “ ለዚህ የሚያበቃ ህመም አልነበረባቸውም ፣ የሞቱት በኢንፌክሽን ነው !”
                              “ የአቶ መለስ ጭንቅላት ፈነዳድቶ ነበር ! ”
                              “ ይህ የውሸታሞችና የጠላቶች ወሬ ነው ! ”
“ የአቶ መለስ አካል ባይበላሽ ኖሮ እንደ አቡነ ጳውሎስ መስታወት ውስጥ ሆኖ እናየው ነበር ”
                              “ ይህን ማድረግ - አለማድረግ የቤተሰብና የመንግስት ጉዳይ ነው ”

አቶ መለስ ለህክምና የቆዩባቸው 60 ቀናት ለኢትዮጵያዊን በግራም ሆነ በቀኝ አስጨናቂ ፣ አጓጊ ፣ አከራካሪና አጨቃጫቂ ምዕራፍ ነበሩ ማለት ይቻላል ፡፡ ሞታቸው ተረጋግጦ አስከሬናቸው አዲስ አበባ ከገባበት ምሽት ጀምሮ ለ13 ቀናት የቆየው የሀዘንና የማስተዛዘኛ ጊዜያት ደግሞ እንደ ሁለተኛ ምዕራፍ ሊታይ የሚችል ነው ፡፡

 በዚህ ምዕራፍ ይነሱ የነበሩ ክርክሮችና ሙግቶች ይበልጥ ጠንካራ ነበሩ ፡፡ ማህበራዊ ገጾች ያስተናግዱት የነበረው ተቃራኒ ሀሳብ በግጥም ፣ በእንጉርጉሮ ፣ በፎቶ ፣ በስዕል ፣ በጠንካራ መፈክርና አባባሎች የታጀበ ነው ፡፡ አይተናቸው የማናውቃቸውን የአቶ መለስ ዜናዊ ልዩ ልዩ ፎቶዎች (ከልጅነት እስከ እውቀት) ሁለቱም ወገኖች ለራሳቸው መልዕክት ማስተላለፊያነት ተጠቅመውበታል ፡፡ ደጋፊው ወገን የአቶ መለስን ጠንካራና ልማታዊ ንግግሮች እያጣቀሰ ሀዘኑን ገልጿል ፡፡ ተቃዋሚው ወገን በበኩሉ የአቶ መለስን መጥፎ ንግግሮች በማስረጃነት እያስደገፈ የሞቱን ተገቢነት ሲያስረዳ ቆይቷል ፡፡

የአቶ መለስን አስክሬን ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝቶ የተቀበለው በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪ ሀዘኑን በእንባ እየገለጸ መፈክር ያሰማ ነበር ፡፡ ያቺ መፈክር በእለቱ የተወለደች መስላ ለበርካታ ግዜያት በመገናኛ ብዙሐንም በፌስ ቡክም ጠንካራ ተጉዛለች ፡፡ ‹‹ መለስ አልሞተም !  ጀግና አይሞትም ! ››  የምትል ፡፡ ተቃራኒው ቡድን ለዚህ አባባል ምላሽ የሰጠው በግጥም ነበር ፡፡

                             “ በአመለካከት መታሰር ፣ በዘር መገፋት ካልቀረ
                               የአድርባይነት ቁራኛ የዘረኝነት ደዌ ካልሻረ
                               የይስሙላ ፍርድ ቤት የግብር ይውጣ ምርጫ
                               የአንድ ብሄር ፖለቲካ የአንድ ግለሰብ ብልጫ
                               ይህ ሁሉ አሳር እንደ አዲስማ ካለ
                               እውነት ብላችኋል መለስ አልሞተም አለ”

ደጋፊዎች በሀዘን ድባብ ውስጥ ቢሆኑም ውስጣቸውን በደስታ ሊያነቃቃና የአቶ መለስን የሚሊኒየም ታላቅነት ሊያበስር የሚችል መፈክር ፈጥረዋል ፡፡ “ አባይን የደፈረ ብቸኛ ጀግና መሪ ! ” የኢትዮጽያ መሪዎች ከጥንት ጀምሮ አባይን ለመገደብ የጋለ ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ከሀሳባቸው ጋር መገናኘት አልቻሉም ፡፡ ይህም ከመለስ ትልቅ ተግባራት ዋነኛው ሊሆን ግድ ብሏል ፡፡ ተቃራኒው ቡድን ለዚህ ጠንካራ እውነትም ቢሆን ምላሽ ከመስጠት አልተቆጠበም ፡፡

“ የማይደፈር ደፈረ ግን ሞተ ተቀበረ
                              21 ዓመት ሙሉ ተደነሰ ተጨፈረ
                              ዛሬ ግን ያ ቀረ ሀጢያት ተደመረ
                              ተባዛ ተከመረ በሰፈሩት መሰፈር መች ቀረ ” በማለት አቀንቅኗል ፡፡

“ አባይን ደፈረ ብለን ሳንጨርሰው
 ሞት ደፈረና ህዝቡን ጉድ አሰኘው ” የሚል ሽሙጥም በተመሳሳይ መልኩ ተነቧል ፡፡  ደጋፊው   ወገን ለአቶ መለስ ነፍስም በጎ ነገር የተመኘው በስነ ግጥም ነበር ፡፡

           “ ክቡር ይሁን ለእሱ አምላክ ይቀበለው
                                ገነት ለእሱ ትሁን አፈሩ ይቅለለው ”

ይህችን የመልካም ምኞት ደብዳቤ ፌስ ቡክ ላይ የተመለከተ ሌላ ተቃራኒ ወገን

                              “ እኔ ብቻ ልግዛ ነውና ነገሩ
                               ሰማይ ቤትም ሄደው እንዳያስቸግሩ ” በማለት ምጸታዊ መልዕክት ለማስተላለፍ ሞክሯል ፡፡
የግራው ቡድን መለስ ዜናዊን የሚገልጸው ታላቅና ጀግና መሪ በሚል ነው ፡፡ በተለይም “ ጀግና ! ”  የምትለው ቃል ለጦር ሜዳውም ለቢሮ ሥራውም ውክልናዋ ደማቅ በመሆኑ ከአፍ ላይ እንድትጠፋ አይፈልግም ፡፡ አንዱ አቀንቃኝ በስድስት ስንኞች ፣ የስንኞቹ  የመጀመሪያ ፊደላት ወደታች ሲነበብ መለስ ዜናዊ የሚል ንባብ እንዲሰጥ አድርጎ ጀግንነቱን እንደሚከተለው ገለጸው ፡፡

                              ቼም የማንረሳህ ጀግናው መሪያችን
                              መኖር ሳትጓጓ ስትሮጥ ለሀገራችን
                              ንቱን መከራ አልፈህ ስትቆም ከጎናችን
                              ናው አለያየን ተደፋ አንገታችን
                              ፍቆታችን ከስሞ ጠቆረ ፊታችን
                               ላቭ ዩ ብለን አነባን ከውስጣችን  

የቀኙ ቡድን የግጥሙን መልዕክት ካጣጠመ በኋላ አቶ መለስ በፍጹም “ ጀግና ” የሚባሉበት መንገድ ትክክል አይደለም በሚል መንፈስ ለግጥሙ ምላሽ አዘጋጀ ፡፡ እንደላይኛው ግጥም ለየት ለማድረግ ይመስላል ተራኪው ራሳቸው ‹ አቶ መለስ › እንዲሆኑ አድርጓል ፡፡

                               “ ጥይት በማይበሳው መስተዋት ተከብቤ
                                 በመድፍ ፣ በመትረየስ ፣ በስናይፐር ታጅቤ
                                 ስወጣ ስገባ የምታውቁኝ ሁሉ
                                 ፈሪ ለእናቱ ነኝ እኔን ጀግና አትበሉ
                                 ጀግና ቴዎድሮስ ነው የሞተው ለቃሉ ”    

የሀዘኑ ጉዳይም በእጅጉ አነጋገሪ ሆኖ አልፏል ፡፡ ምናልባትም ለ13 ቀናት ያህል የተለቀሰለት የዓለም መሪ መኖሩ ያጠራጥራል ፡፡ ህዝቡ ቤተመንግስት ድረስ በመጓዝ አልቅሷል ፡፡ ያው ‹ ከልቡ ነው › ፣ ‹ ለይምሰል ነው › የሚሉ እሰጥ አገባዎች እንደተጠበቁ ሆነው ፡፡ ሁሉም ቀበሌዎች ድንኳን ጥለው ተቀምጠዋል ፡፡ ደጋፊዎች ጥቁር እንዲለብሱ ተደርጓል ፡፡ ደረት መምታት ፣ ፊት መንጨት ፣ ጥቁር መልበስ ፣ አርባና ሰማንያ ጎጂ ባህል ናቸው በማለት መንግስት ለእድሮች ሲያስተምር ቆይቶ ለራሱ ሲሆን ድራማውን በለቅሶ መቀጠሉ ነው ያስገረመን ብለዋል ብዙዎች ፡፡

                             “ እረ ይሄ ለቅሶ አለቅጥ ሆነ ? ይብቃ ! ” ተቃዋሚው አስተያየቱን መስጠቱን ቀጠለ
                             “ ደግሞ በዚህ ቀናችሁ ?! ለመሪያችን ሳይደክመን እናልቅሳለን ! ” ደጋፊው መለሰ
                              “ ክፉ ቁራኛ ሲሄድ አስለቅሶ ነው -  የልምዣት ” ተቃዋሚው ምጸቱን አጠናከረ

በርግጥ ደጋፊዎች ይህን አርበ ሰፊ ለቅሶ ለሀዘንም ለፖለቲካው ድጋፍ ማግኛም ተጠቅመውበታል ፡፡ የጎንደሩ ፣ የጎጃሙ ፣ የጉምዙ ፣ የወላይታው የአለቃቀስ ስርዓትን እግረ መንገድ በየቀኑ ከሚያቀርብልን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መረዳት ችለን ነበር ፡፡ ሀዘንተኞች ለሪፖርተሮች ሲሰጡ የነበሩ አስተያየቶችም አሳዛኝም አሳፋሪም ነበር ማለት ይቻላል ፡፡ አቶ መለስን ከታሪካቸው ፣ ከማንነታቸውና ከራዕያቸው አንጻር የሚገልጹበት መንገድ ያስተክዛል ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ‹ እኔ ሞቼ እሳቸው የሚነሱ ቢሆን ነፍሴን ለመስጠት አልራራም › የሚሉ ሰዎች በርክተው ነበር ፡፡ ድንገት ፈጣሪ ‹ ና በል እንግዲህ ሞት ተፈርዶብኃል ! › ብሎ ቢናገር የእነዚህ ሰዎች ሽንትና ላብ ክረምትን ባስናቀ ነበር ፡፡ ያም ሆነ ይህ ሀገር በየተራ አልቅሷል  ወይም እንዲያለቅስ የህዝብ ግንኙነት ስራ ተሰርቷል ፡፡ ይህን መሰረት በማድረግም ደጋፊው ቡድን ጎል ክልል ሃይለኛ ቅጣት ምት እንደሚከተለው ሰነዘረ

“ መለስ ጨካኝ ነው ፣ አምባገነን ነው ይሉ የነበሩ ዛሬ ሀገር ሙሉ ሲያለቅስለት ምን ያህል የሰው መውደድ ያለውና ታላቅ መሆኑን ሊገነዘቡት ይገባል ”
ተቃራኒው የመልስ ምቱን ያዘጋጀው ለሞተ ሰው ማዘንና ማልቀስ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴት ከመሆኑ አንጻር የመሆኑን ጉዳይ ነበር ፡፡ እነሆ በቴስታ የወጣው ግጥማዊው መልስ ፣
                              “ …  ክንፈር የነከሰው
                                   ከንፈር የሚመጠው
                                   የነገ ተረኛ ነፍስ ይማር የሚለው
                                   አንድም ለራሱ ነው
                                   አንድም ለሟቹ ነው ”

በርግጥ በለቅሶ ወቅት የኢትዮጵያን ህዝብ ማንነት መበየን አስቸጋሪ ሆኖ ታይቷል ፡፡ በአቶ መለስ እና በመንግስታቸው አገዛዝ ሲማረርና ሲያልቀስ የነበረው ሁሉ በሞታቸው ጥልቅ ሀዘኑን ገልጿል ፡፡ ይህ ድርጊት ደጋፊውንም ተቃዋሚውንም ግራ ያጋባ ነበር ፡፡ ሁለቱም ወገኖች እንዴት ? ብለው በግርምት ተመሳሳይ ጥያቄ አንስተዋል ፡፡ የተለያዩት ውጤቱ ላይ ነበር ፡፡ ደጋፊው “ ያስደስታል ! ›› ሲል ተቃዋሚው  “ የማይታመን ነው ” ሲል ቆይቷል ፡፡ ለዚህም ይመስላል ደጋፊው

“ እውነትም የኢትዮጵያ ህዝብ ወርቅ ህዝብ ነው ፡፡ በጠ/ሚ/ሩ ሞት ታላቅነቱን አስመስክሯል ” በማለት ፍንድቅድቅ የሚለውን ሀሳብ የወረወረው ፡፡ በዚህ ብቻ አላበቁም “ ሀገር ሙሉ ያለቀሰው ለጠ/ሚ/ር መለስ ከፍተኛ ፍቅር ስላለው ነው ” የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል ፡፡

ለነዚህ ሁለት መሰረታዊ አባባሎች ከተቃራኒው ወገን የተወረወሩ ሁለት አጸፋዎችን እንመለክት ፡፡ አንደኛው “ ሰሞኑን እያየን ያለነው አድርባይነት ፣ አስመሳይነት ፣ ከሃዲነት ፣ አሸቃባጭነት እና ውሸታምነት የመለስ ዜናዊ የ21 ዓመታት አገዛዝ ፍሬዎች ናቸው ” የሚል ነው ፡፡ ሁለተኛው ምላሽ ‹ ህዝብ ማለት › በሚል ርዕስ የተገጠመ ረጅም ግጥም ነው ፡፡ የህዝቡን አደናጋሪ መልክና በፈለገው ጊዜ የፈለገውን የመሆን ችሎታ ይገልጻል ፡፡ ጥቂቱን ቆንጥረን እናንብብ ፡፡

                              ይህ ህዝብ ማለት …
                              አንዳንዴ ግጥም ነው… አንዳንዴ ቅኔ
                              አንዳንዴ ንስር ነው… አንዳንዴ ዋኔ
                              ይህ ህዝብ ማለት መመዘኛም የለው
                               መለኪያው ግዜ ነው እርቦና መስፈሪያው
                               ሞላ ሲሉት ስፍሩ የልኩ ጢምታ
                               የለም አይገኝም በሚዛን ገበታ
                               ይሄ ህዝብ ማለት …
                               በበረደው በርዶ በሞቀበት ሞቆ
                               ሲመርም ጉፍንን ነው ልክ እንደመቅመቆ
                               ይህ ህዝብ ማለት ፍቺ የለው አቻ
                               እንዲሉ ነገር ነው ስልቻ ቀልቀሎ ፣ ቀልቀሎ ስልቻ

የሀዘኑን ስርዓት ስናነሳ በሁለቱም ወገኖች ይታይ ነበረውን ጫፍ የደረሰ አመለካከት መጥቀስ ተገቢ ይሆናል ፡፡ ደጋፊው ወገን ከመጀመሪያው ጀምሮ ሀገሪቱ ታላቅና ጀግና መሪ በማጣቷ ሀዘኑ ሳይገደብ መከናወን ይኖርበታል ይል ነበር ፡፡ ምን ያህል እንደሚሄድ ባላውቅም ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ እንደሚባለው ዓይነት ። ተቃራኒው ወገን አቶ መለስ እንደ ጀግናም ሆነ እንደ ሀገር መሪ በወግ ማዕረግ መቀበር ይኖርባቸዋል ፣ ይህንም የሚደግፍ ህጋዊ የሀዘን ስርዓት አለ ፡፡ ከዚህ ውጪ መሄዱ ግን ከባህል ፣ ሃይማኖት ፣ ኢኮኖሚና ፖለቲካ አንጻር ትክክል አይደለም ባይ ነበር ፡፡ ይህን ሀሳብም ሲወረወሩ ከነበሩ አስተያየቶች መረዳት ይቻላል ፡፡

 ደጋፊው ፤
                             “ ዝቅ ይበል ባንዲራው ከክብሩ ይወርዳል
                               ሀገር የሚመራ ታላቅ ጀግና ወድቋል
                               ይታወጃል ሀዘን ጥቁር ይለበሳል
                               መራር ሀዘን ገዝፎ አርምም ይሆናል ”

በተግባር ተተርጉሞ የታየው የሀዘን ስርዓትም ከግጥም በላይ ነበር ፡፡ ይህ የፈጠው ብሽቀትም ይመስላል የመረረ አጸፋ የፈጠረው ፡፡

                             “ ከኛ ገለል በሉ አትተራመሱ
                               ጥቁር ማቃችሁን ዘላለም ልበሱ
                               ድንኳን ውስጥ ሆናችሁ ሙት አመት ደግሱ
                                ነገም አተራማሽ መርጣችሁ አንግሱ … ››
        
በማንኛችንም ህይወት ውስጥ የተለዩ አጋጣሚዎችና ግጥምጥሞሽ ይፈጠራሉ ፡፡ እነዚህ ግጥምጥሞሽ ደግሞ ተቀባይነት ይኑራቸውም አይኑራቸው የራሳቸው የሆነ የተጽእኖ አሻራ ይፈጥራሉ ፡፡ ከአቶ መለስ የመጨረሻ የህይወት ጠርዝ ላይ ድንገት ጎልቶ የወጣው አበበ ገላው የተባለው ጋዜጠኛ ድርጊት ነበር ፡፡ በትልቅ ስብሰባ ላይ “ Meles Zenawi is dictator ! Free Eskinder Nega and all political prisoners . You are commiting crimes against humanity ! Don’t talk about food with out freedom… ” በማለት  ተቃውሞውን በሚያስፈራ ድምጽ ገለጸ ፡፡

የጋዜጠኛው ድርጊት ትክክል ነው - አይደለም የሚሉ ሀሳቦች በወቅቱ በስፋት ተንሸራሽረዋል ፡፡ ከዚህ አጋጣሚ ጥቂት ቆይቶ የአቶ መለስ መታመም ተሰማ ፡፡ ተቃራኒው ወገን ህመሙን ከአበበ ተቃውሞ ጋር አገናኘው ፡፡ “ አቶ መለስ የታመሙት በደረሰባቸው ድንጋጤና ሀፍረት ነው ” ተባለ ፡፡ ሌላኛው ወገን  “ ስንት መከራና ችግር ያሳለፈ መሪ በአንድ ምንነቱ በማይታወቅ ሰው ልፍለፋ የሚታመምበት ምክንያት ቀልድ ነው ” በማለት ትችቱን አጣጣለ ፡፡

ተቃዋሚዎቹ ግን ይህን አጋጣሚ በቀላሉ ማሳለፍ አልፈለጉም ፡፡ አቶ መለስ በዓለም ፊት መሰደባቸውን እንደ ትልቅ ድል ተመለከቱት ፡፡ ጋዜጠኛውንም እንደ ጀግና መቁጠር ጀመሩ ፡፡ በነካ እጅህ ሚኒስትር እከሌን ስደብልን ፣ ቀንደኛውን እንቶኔ አሸማቅልን እስከ ማለት ተደረሰ ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ አቶ መለስ መሞታቸው ደግሞ ጉዳዩን አጦዘው፡፡

“አበበ ገላው መለስን በላው ! ” የሚል ግጥምም ተደረሰ

ደጋፊው ወገን አቶ መለስ የሞቱት በህመምና በእረፍት ማጣት እንጂ በአበበ ገላው ድንገተኛ ድርጊት አለመሆኑን ይረዳል ፡፡ በርግጥ አንድ የተከበረ መሪ በአንድ ጋዜጠኛ መሰደቡ አብሽቋቸዋል ፡፡ ለዚህም ይመስላል

“ አበበ ገላው ማለት የአእምሮ በሽታ ያለበት ንክ ሰው ነው ! ” በማለት የጉዳዩን ደረጃ በማጣጣያ ምላሽ የሰጡት ፡፡ ተቃዋሚው ወገን ለአበበ ምስጋና ለደጋፊው ወገን ደግሞ ምጸታዊ አጸፋውን ማሰማቱን ቀጠለ

“ አበበ ገላው እግዚአብሔር ይስጥህ አንተ ለኛ ጎልያድን እንደጣላው እንደ ዳዊት ነህ ! ” መቼም ይህ አባባል ስሜታዊ እና የተጋነነ መሆኑ ግልጽ ነው ፡፡ ይሁን እንጂ ድክመቱ ላይ ተንተርሶ እንኳ የመልስ ምት አልተሰጠም - ከደጋፊው ወገን ፡፡

በርግጥ ደጋፊው ወገን አልፎ አልፎ በቸልታ ወይም በንቀት እያየ ያለ መልስ የሚያልፋቸው ጉዳዮች ነበሩ ፡፡ ይህም “ ለሁሉም መልስ መስጠት አንችልም ከሚለው ድርጅታዊ መርህ ተቆርሶ የተወሰደ ሊሆን ይችላል ፡፡ አንዳንዴ ግን ይህ ነገር መልስ ቢኖረው እንዴት ጥሩ ነበር ? እንዴትስ መልስ ሊሰጠው ይችላል ? ” የሚል ጥያቄ ያጭራል ፡፡

አንድ አብነት ብቻ ላንሳ ፡፡ ተቃዋሚው ወገን ያዘጋጀው ቅጽ ነው ፡፡ ርዕሱ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የአለቃቀስ ግምገማ ይላል ፡፡ ወረድ ብሎ

                              የአልቃሹ ስም ------
                              ቀበሌ  ------
                              ያለቀሰበት ቋንቋ ------
                              እንባው የመጣበት ሰዓት ----
                              የእንባው መጠን ፤ ጎርፍ -- ካፊያ --- ደረቅ
                              የለበሰው ልብስ ቀለም ፤ ጥቁር --ነጭ -- ሌላ ቀለም
                              በደቂቃ ምን ያህል አለቀሰ -- የሚሉ መጠይቆችን ይዟል ፡፡
ከነዚህ መረጃዎች ወረድ ብሎ “ ለቢሮ ስራ ብቻ ” በሚል ንዑስ ርዕስ ግለሰቡ በአጠቃላይ     የሚፈረጅበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡ በገምጋሚው ይሞላ ዘንድም አራት አማራጮች ተቀምጠዋል፡፡
                               ግለሰቡ ፤
                              አስመሳይ ? ከልቡ ነው ? ያጠራጥራል ? ጭራሽ አላለቀሰም ? የሚሉ ።

ይህ ቅጽ የቢሮ አካሄድን ተከትሎ ተሰራ እንጂ ተራ ቅጽ አይደለም ፡፡ ምጸታዊ ነው ፡፡ ህዝቡ እያለቀሰ ያለው በማይታዩ ደንቦች እንጂ በውዴታ አይደለም የሚል ፡፡ ፈጠራውም የሚናቅ አይደለም ፡፡ ይህ ደግሞ ሀገሬው በሙሉ ማልቀሱ መለስን የመውደዱ ማሳያ ነው ከሚሉት ደጋፊዎች ሀሳብ ጋር የሚቃረን ነው ፡፡ ታዲያ ምላሽ ለምን ተነፈገው ? ስዕላዊ በሆነ መልኩ ምላሽ ሊያገኝ ቢችልስ ምን ያህል እንደመም ነበር ? እንደ እኔ እንደ እኔ በጦፈ ክርክር ውስጥ ምላሽ ማጣት ያስቆጫል ፡፡

በሀዘኑ ወቅት ሀገሬውና ማህበራዊ ገጾች ለምን የተለያየ ገጽታ ተላበሱ የሚለውን ጥያቄ በግሌ ጠይቄያለሁ ፡፡ ህዝቡ ጸሃይና ዝናብ ሳይበግረው በረጅም ሰልፍ ውስጥ አልፎ ለቅሶ ደርሷል ፡፡ በየቀበሌው ድንኳን እየተገኘ አንብቷል ፡፡ በመገናኛ ብዙሐን የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጿል ፡፡ የመለስን ራዕይ ለማስቀጠል ቃል ገብቷል ፣ በስሜት ገስሏል፡፡ ፎክሯል ፡፡

በማህበራዊ ገጾች መስኮት ብቅ ሲል ግን ሁለት መልክ ይዞ ነው ፡፡ ያ የመረረ ሀዘኑ ይለዝባል ፡፡ የሚወክለው ሀዘንና ውዳሴ ብቻ ነው ብለው ሲያስቡ የተደሰተ ፊትና  በትችት የተሰላ ምላስ አብቅሎ ይታያል ፡፡

“ የምስራች ! መለስ ሞተ ! ”
“ የወርቅ ጥላ ለማን ታቦት ላግባ ! ”
“ የኢትዮጵያን ህዝብ እንጂ ፈጣሪን ማታለል አይቻልም ! ”

እጅግ የከረሩ ሀሳቦች ይወረወራሉ ፡፡ ከመቼው ተቀያየረ ? ነው የኢትዮጵያ ህዝብ “ ነገርን ” በፈረቃ ነው የሚሰራው ? በገሃዱ ሀገራችን የታየው የሀዘን ድባብ ለምን በፌስ ቡክም ዓለም ተጽእኖ መፍጠር አልቻለም ?  ብሎ መጠየቅ ግድ ያስብላል  - ጥናት ይፈልጋል ።

ቀጥሎ የትችቱንና የመጠዛጠዙን ትልቅ ደረጃ ሊያሳዩ የሚችሉ ክርክሮችን እንመልከት ፡፡ ደጋፊው ወገን የበዛውን ወቀሳ ለማስታመም የሚከተለውን ጽፏል ፡፡

“ በህይወት የሌለን ሰው መውቀስ ወይም በህይወት የሌለ ሰው ላይ በደስታ መፎከር ጀንግንነት         አይደለም ፤ ሙት አይወቀሰም ፡፡ እንደ ወግ ባህላችን የጠቅላሚኒስትሩን እና የጳጳሱን ነፍስ ይማር እንበል ”

ከተቃዋሚው ወገን እንደተለመደው ምላሹ የተላከው በስነ ግጥም ነበር

                              “ አባ ታጠቅ ካሳን ስትረግሙ ከርማችሁ
                                እምዬ ሚኒሊክን ስትወቅሱ ኖራችሁ
                                ተፈሪ መኮንን ጨቋኝ ነው ብላችሁ
                                ዛሬ ቀኑ ደርሶ ዕጣ ሲደርሳችሁ
                                ሙት አይወቀስም አትበሉን እባካችሁ ”

ደጋፊው ወገን አቶ መለስን በክፋት የሚመነዝረው ፣ ታላቅነታቸውን የሚያጣጥለው ፣ በጥልቅ የሀዘን ወጀብ መመታት ሲገባው የደስታና የፌሽታ ሻምፓኝ እየከፈተ የሚገኘው ከሀገር ውጭ የሚገኘው ኢትዮጽያዊ ነው ብሎ ያምናል ፡፡ የኢትዮጵያን ዕድገትና ልማት የማይመኘው ይህ ቡድን የደርግ ኢሰፓ ርዝራዥ ወይም ስልጣንን በአቋራጭ ለማግኘት የሚቋምጥ ፊውዳል ሊሆን ይችላል ፡፡ እናም አቶ መለስና ስርዓቱን ሊያጥላሉ የሚችሉ ነገሮችን ሁሉ መረን በወጣ መንገድ ይለጥፋል ባይ ነው ፡፡

ለምሳሌ ያህል ፤

“ መለስ ዜናዊ ታላቅ ጀግና መሪ ነው ! ” የሚለውን ቅቡልና ያገኘ አባባል ጠምዝዞ “ መለስ ዜናዊ የራሱን ሀገር ህዝብ ስለገደለ ብቻ ጀግና ከተባለ እኔ አዶልፍ ሂትለርን ምን ልትሉኝ ነው ! ” የሚል ምጸት ያቀርባል ፡፡ አቶ መለስ ለአፍሪካ ህዝቦች ታላቅ ተግባር ማከናወናቸውን ዓለም መስክሯል ፡፡ ከዚህ በመነሳትም  “ መለስ የአፍሪካ መሪ ነበር ! ” ለተባለው ታላቅ አባባል “ መለስን የአፍሪካ አባት ያላችሁ አሳፋሪ ካድሬዎች ማንዴላ ሰምቶ እንዳይስቅባችሁ ” የሚል ማጣጣያ ሲያቀርብ ቆይቷል ፡፡

እንደ ብዙ ደጋፊዎች እምነት ሀገር ውስጥ ያለው ዜጋ ተመሳሳይ ስሜቱንና ቁጭቱን ሀዘን በተላበሰ መልኩ ገልጿል ፡፡ በመሆኑም በማህበራዊ ገጾች ለተከፈተው ጥቃት ዋነኛ ተዋናይ ሊሆን አይችልም ፡፡ ምናልባት አስተዋጽኦው እንዴት ይመዘናል ? ከተባለ አለ ተባለውን ከማራገብና ከሟሟቅ የሚዘል አይሆንም ፡፡ ለዚህም ይመስላል ከደጋፊው ቡድን  “ ይድረስ በየሀገሩ ለተበተኑ ኢትዮጵያዊያን ” በሚል ርዕስ ጠንከር ያለ ደብዳቤ የተሰራጨው ፡፡ እንመልክተው ፡፡

“ ጠ/ሚኒስትሩ ቢሞቱብን ስብዓዊም ኢትዮጵያዊም ሀዘን አዘንን ፡፡ በውጭ ያላችሁ የስጋችን ቁራጭ ፣ የአጥንታችን ፍላጭ የሆናችሁ አንዳንድ ወገኖቻችን ‹ የፈንጠዝያ ቀን ይሁንላችሁ ! › ብላችሁ መከራችሁን ፡፡ እኛ  እኮ ባህል ፣ ወግ ፣ ኃይማኖትና ስነ ምግባር ያለን ህዝቦች ነን ፡፡ መቼ መሳቅ ፣ መቼ ማልቀስ እንዳለብን እናውቃለን ፡፡

ዴሞክራሲ ማለት መሪን መስደብና ማጓጠጥ ፣ ዴሞክራሲ ማለት ሁልጊዜም ተቃዋሚ መሆን ፣ ዴሞክራሲ ማለት ሀገርን የወከለን መሪ በሌሎች ሀገሮች ፊት ማዋረድ መሆኑን ያስተማራችሁትን ትምህርት የገባን ዕለት ፡፡ ያኔ እንስቃለን ፡፡

ኢትዮጵያዊያን ማለት እኮ ዜግነት ለመቀየር እየተጣባበቅን ያለን አይደለንም ፡፡ ኢትዮጵያዊያን ማለት በሆስፒታል እጦት በየጫካው የምንወለድ ፣ ሰው በአየር ሲጓዝ እኛ በመንገድ እጦት ጋራ ሸንተረሩን ስንቧጥጥ የምንኖር ፣ ሀመሮች ፣ ቡርጂዎች ፣ ኮንሶዎች ፣ ደራሼዎች ፣ ሱርማዎች ፣ ቤንሻንጉሎች ፣ አፋሮች … ስሙን እንኳ ሰምታችሁት በማታውቁት ገጠራማ አካባቢ የምንኖር ብሄረሰቦች ነን ፡፡

አንደብቃችሁም ፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን ሰው ሲሞት ስቀን የምናውቀው ቴአትር ቤት ውስጥ ብቻ ነው ፡፡ መለስ የሞተ ዕለት ፈንጥዙ አላችሁን ? የቱ መለስ ? እሱ እኮ በአግባቡ ሳናነበው የተዘጋ መጽሀፍ ፣ ብዙ ነገሮች ከልለውን በቅጡ ሳናየው ያመለጠን ድንቅ ክስተት ነው…. ”

በአጠቃላይ በአቶ መለስ ስብዓዊም ሆነ ፖለቲካዊ ሰውነት ዙሪያ ያልተነሳ ጉዳይ አልነበረም ፡፡ አንዱ አምባገነን ሲል ሌላው ዲሞክራት… እብሪተኛ ለሚላቸው የድሃ አባት … አገር ሻጭ ለሚላቸው ባለራዕይ … ዘረኛ ለሚላቸው የአፍሪካ ልጅ የሚሉ ማስተባበያዎች ተከትሏቸዋል ፡፡

በርግጥም  የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልክ ሁለት እንደነበር የሚያሳዩ ማስረጃዎች በርካታ ናቸው ፡፡ ከታዋቂዎቹ  መገናኛ ብዙሐን መካከል የቢቢሲ እና አልጀዚራን አስተያየት እንደ አብነት ማንሳት ይቻላል ፡፡

“ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በማሳደግ ረገድ የሰሩ ፤ በሰብዓዊ መብት አያያዝ በኩል ክፉ ወቀሳ የሚሰነዘርባቸው ናቸው ” ያለው ቢቢሲ ሲሆን “ በኢኮኖሚው ረገድ ጥሩ ውጤት በማስመዝገባቸው የሚወደሱ ፤ በጸረ ሽብር ህግ ሽፋን የተቃውም ድምጾችን በመጨፍለቃቸው የሚወገዙ ” ሲል የገለጻቸው ደግሞ አልጀዚራ ነው ፡፡