Sunday, August 25, 2013

የእምብርት ዘመን ሲሄድ የቂጥ ዘመን መጣ








‹‹ ምን ዓይነት ዘመን ነው  ዘመነ ዲሪቶ
አባቱን ያዘዋል  ልጁ ተጎልቶ ››

እያለ አቀንቅኗል ድምጻዊ ተሾመ ደምሴ ፡፡ ተሾመ ልማዳዊው ህግ ወይም ስርዓት ተጣርሷል የሚል ጭብጥ ለማስተላለፍ የሞከረ ይመስላል ፡፡ ዜማውን በምሳሌያዊ አነጋገር ለውጡ ብንባል

‹‹ዘመነ ግልንቢጥ
ውሻ ወደ ሰርዶ
አህያ ወደ ሊጥ ›› የሚባለውን ብሂል መጥቀሳችን አይቀሬ ነው ፡፡

በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ምን ዓይነት ዘመን መጣ ያሰኘው የሴቶቻችን አፈንጋጭ አለባበስ ነበር ፡፡ ዘንድሮ ዘመነ ግልንቢጥ የተባለው ደግሞ በወንዶች ጉዳይ ሆኗል ፡፡ ለመሆኑ እንዴት ነው አህያ ወደ ሊጥ የሄደው ? የሚለውን ጥያቄ ከመፈተሻችን በፊት ትንሽ ስለቀደመው እናውራ ፡፡

ስለሴቶቹ ...
መቼም ዘመኑን ሆን ብሎ የሚያጠና ሰው ቢኖር ስለ እያንዳንዱ ግዜና መጠሪያ ስለሚሆነው ጉዳይ ስያሜ አያጣለትም ፡፡ ለአብነት ያህል በ1997 አካባቢ ሴቶቻችን በታይት ተወረው ነበር ፡፡ ይህን ግዜ ‹‹ የታይት ዘመን ›› ብሎ መጥራት ይቻላል ፡፡ የዛኔ የዘፈን ውድድር አለመፈጠሩ እንጂ ለታይት ለባሾቻችን ‹‹ ቀይ ›› ፣ ‹‹ ቢጫ በቀይ ›› ‹‹ ሙሉ አረንጓዴ ›› እያልን ጥሩ ማነጻጸሪያ መስጠት በተቻለ ነበር ፡፡ ታይት የሰውነት ቅርጽንና ውበትን አጋልጦ የማሳየት ኃይሉ ከፍተኛ ስለነበር ራሳቸውን ‹‹ ለቁምነገር የሸጡ ›› ወጣቶችም ጥቂቶች አልነበሩም ፡፡

አንዳንድ ሴቶች ደግሞ ታይትን ያለ ግልገል ሱሪ በማጥለቅ በየጎዳናው የሚያለከልኩ ወንዶች እንዲበዙ አድርገዋል ፡፡ የነዚህኞቹ ግብ በወንዶች ላይ ‹ ሙድ › ይዞ መዝናናት ይሁን ወይም የግብዣ ማስታወቂያ መስራት በውል የሚታወቅ አልነበረም ፡፡ ለሚነሳባቸው የተጃመለ ትችትም ‹‹ መብታችን ነው ! ›› በማለት የተንዥረገገ ነገር ግን የማይበላ የወይን ፍሬ ነው የሚባልለትን ህገመንግስት ተደግፈው የሚያወሩ ሴቶች ጥቂቶች እንዳልነበሩ እናስታውሳለን ፡፡ ህገመንግስቱ እንኳን የማስልበስን ራሱ የመገንጠልን ካባ በመከናነቡ አያስገርመንም የሚሉ አሽሟጣጮች በበኩላቸው የትራክተር ጎማ የሚያህል መቀመጫ ያላት ሴት በታይት ተወጣጥራ ስትንከባለል እያየን ላለማሳፈር መጣር ከጨዋነት አያስቆጥርም ይሉ ነበር ፡፡ ድርጊቱ የሳቅ ቧንቧን ቷ ! አድርጎ በመክፈቱ በየቦታው አይንና አፍን በመሸፈን የሚንፈቀፈቁ ሰዎች እንዲበራከቱ መንገድ ከፍቷልና ፡፡

ከዚህ ዘመን በኃላ ደግሞ አጭር ቀሚስ የፋሽን መገለጫ ሆኖ መጣ ፡፡ በርግጥ አጭር ቀሚስ ከማለት ይልቅ መሃሉ የተከፈተ ቁምጣ ማለት እውነቱን ቀረብ ያደርገዋል ፡፡ ሴቶቹ ቁጭ ሲሉ ገላቸውን ላለማሳየት ያቺን ምላስ የምታህል ጨርቅ በግድ ሊያረዝሟት ሲታገሉ ማየት ያስቃል ፡፡ ‹ ለምን ለበሱት - ለምን ይጨነቃሉ ? › የሚል ገረሜታ አእምሮን ይወራል ፡፡ የሴቶችን ፍላጎት ጠንቅቀን እናውቃለን የሚሉ ሴት አውሎች ግን በለበሱት ለመጨናነቅ ፣ ለማፈር ፣ የይቅርታ ፊት ለማሳየት መሞከር ሁሉ ድምር ውጤቱ ‹ ሆን ተብሎ የሚተወን የትኩረት መሳቢያ ድራማ  › ነው ባይ ናቸው ፡፡ በርግጥ አጭር ቀሚስ ወዲህ ወዲያ ሲሄዱበት የሚያምር ከሆነ በመቀመጥ ግዜ ገላን ላለማጋለጥ ነጠላ ወይም ሻርብ ነገር እግር ላይ ጣል ማድረግ በተቻለ ፡፡ ይህን የሚያደርጉት ግን ከስንት አንድ ናቸው ፡፡ ስለዚህ የአጭር ቀሚስ አላማ ከፋሽንነትም በላይ የሚሻገር ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎችን ሀሳብ መናቅ የትም አያደርስም ፡፡  ዘንድሮ ይህ ድርጊት ተገልብጦ በመምጣቱ የጭን መጋለጥ ሴቶችን ‹ አያሰጋም › ፡፡ ሱሪያቸው ግን ከኃላ ሆን ተብሎ ያጠረ በመሆኑ ለምሳሌ ያህል ከታክሲ የሚወርዱ ሴቶች መቀመጫቸውን ላለማሳየት ከላይ የለበሱትን ልብስ እስኪቀደድ ድረስ ወደታች ይጎትቱታል ፡፡ እኛም ልብስ መቀየሪያ ክፍል የገባን ያህል ላለማሳፈር ይሁን ላለመሳቀቅ ፊታችንን እናዞራለን - በጨዋ ደንብ ፡፡ ከወረዱ በኃላ ደግሞ  ‹ ምን ያለበሰቸውን ሱሪ ለመልበስ ትታገላለች ! ›  በማለት እናብጠለጥላታለን - በሀሜት ደንብ ፡፡

ታይትንና አጭር ቀሚስን ተሻግሮ በአደባባይ ብቅ ያለው ሱሪም ቀሚስም አይደለም - እምብርት እንጂ ፡፡ እንኳን ከዘመነ ጭን ወደ ዘመነ እምብርት አሸጋገራችሁ - አልናቸው እህቶቻችንን ፡፡  እምብርትን አጋልጦ ለማሳየት መደበኛ ሱሪም ሆነ ታይት መጠቀም ይቻላል ፤ ከላይ ደግሞ አጭር አላባሽ ፡፡ እድሜያቸው 14 እና 15 ያልሞላቸው ህጻናት ፣ የደረሱ ወጣቶች ፣ ብዙ ልጆች ያፈሩ እናቶች ሳይቀሩ እምብርታቸውን በየአደባባዩ አሰጡት ፡፡ ለብዙ ወንዶች ትርጉሙ ግልጽ አልነበረም ፡፡

ሴቶቹ በደፈናው ‹‹ ፋራ አትሁኑ ! ፋሽን ነው ›› አሉ ፡፡ መነሻው ህንድ ይሁን ሱርማ ፤ ጥቅሙ ሀሴት ያምጣ ግርማ ልብ ያለ ግን አልነበረም ፡፡ ወንዶቹ ‹‹ ከፋሽኑ ጀርባ ምን አለ ? ›› በማለት ጠየቁ ፡፡ ይህ ጥያቄያቸው በተለይ ከውበት ጋ የተያያዘ ነበር ፡፡ ምክንያቱም ወንዶች ጸጉር ፣ አይን ፣ አንገት ፣ ጡት ፣ ዳሌ ፣ ሽንጥና ባት እያሉ ሊያዜሙ ፣ ሃሳባቸውን ሊገልጹ ወይም ሊጽፉ ይችላሉ ፡፡ እስካሁን ግን ‹‹ እምብርትሽ ›› ብሎ ያቀነቀነ ዘፋኝ ወይም የጻፈ ደራሲ ወይም ያደነቀ አፍቃሪ አልተሰማም ፡፡ ታዲያ የእምብርት ፋይዳ ምን ይሆን ? መባሉ ግድ ነው ፡፡ አንዳንድ ሴቶች እምብርታቸው ላይ ጉትቻ እስከማንጠልጠል በመድረሳቸው ወንዶቹ እንደሚከተለው አሾፉ ‹‹ እምብርት ምድር ቤት የሚገኝ ጆሮ ነው  እንዴ ? ›› ወይም ‹‹ ከላይኛው የጆሮ ገጽ የዞረ መሆኑ ነው ? ››
ስለ ወንዶቹ …

እነሆ ዘመኑ ተገልብጦ ሴቶች በወንዶች ድርጊት እያዘኑ አልፎ አልፎም እያስካኩም ይመስላል ፡፡ የሴቶቹ እምብርት ተረት ሆኖ የወንዶቹ ቂጥ ወቅታዊ ማፍጠጫ ጉዳይ ስለሆነ ፡፡ ምናለፋችሁ በከተማችን ‹‹ የሚዝረከረኩ ወንዶች ›› ተበትነዋል ፡፡  ‹ እረ ወንድ ልጅ ሴታ ሴት ሲሆን ያስጠላል ! › የሚሉ ቆነጃጅትና እማወራዎች በዝተዋል ፡፡ ‹ ልጆቻችን ምን እስኪሆኑ ነው የምንጠብቀው ? › በማለት በሴት እድሮችና ማህበሮች ላይ ጉዳዩ የመወያያ አጀንዳ እንዲሆን የጣሩ ሴቶች ሞልተዋል ፡፡ ‹ ግብረ ሶዶማዊያን በዛ እያሉ እግዚኦ የሚሉ የሃይማኖት ተቋማትና ጋዜጠኞች የወንዶችን ልብስ መጣል እንዴት ዝም ብለው ያያሉ ? › የሚሉ ተቆርቋሪ እህቶች ሰሚ ያጡ ይመስላሉ ፡፡

የሀገራችን ሴቶች ወንዶች ቀበቷቸውን እንዲያላሉ በህጋዊ መንገድ የሚጠይቁት በአንድ መንገድ ብቻ ነው  ፤ በምጥ ወቅት ፡፡ በርግጥ  በፍቅር ጨዋታ ወቅት የሚኖረውን ውልቂያ የትኛው ክፍል እንደምንመድብ ሳያስቸግርን አይቀርም ፡፡ ታዲያ ዛሬ በህገወጥ መንገድ ቀበቶ አላልቶ ፤ ሱሪውን ከወገቡ ቁልቁል አርቆ ፤ የውስጥ ሱሪውንና የቂጡን ቀዳዳዎች እያስጎበኘ ላይ ታች በሀገራዊ ኩራት የሚጓዘው ‹ ትንሽ - ትልቅ › አበዛዙ ቀላል አልሆነም ፡፡

ወደው አይስቁ አሁን ይመጣል ፡፡ አንዳንድ የውስጥ ሱሪዎች የተቀደዱና ውሃ ካያቸው ዘመናት ያስቆጠሩ ሊሆኑ ይችላሉ  ፡፡ አንዳንድ የውስጥ ሱሪዎች ደግሞ ገመዳቸው ላልቶ ነው መሰለኝ ወደ ውስጥ የሰመጡ ናቸው ፡፡ በተለያየ ምክንያት የሚጎነበሱ ፋሽነኞች ታዲያ የሚያስጎበኙት የተራቆተ መቀመጫ በንጽህ ወንድ / አፍቃሪ ግብረሶዶም እና እንስት ባልሆነ / ከታየ ለአይን የሚቆረቁር ፣ የመንፈስ ልዕልናና ክብርን ዝቅ የሚያደርግ ነው ፡፡ ምክንያቱም  የአንዳንድ ሰው ቂጥ በጎርፍ የተቆረሰ ደለል ይመስላል … የአንዳንድ ሰው ቂጥ በላብና እድፍ ተቦክቶ ልስን የሚጠብቅ ግድግዳ ይመስላል … የአንዳንድ ሰው ቂጥ ወፍጮ ቤት ከዋለ ፊት ጋር  አንድ ነው ፡፡

አሁን ደግሞ የማይገባዎትን ጥያቄ ይወረውራሉ ፡፡ ፋሽኑ ሱሪው ነው ? የላላው ቀበቶ ነው ? ፓንቱ ነው ? የፓንቱና ሱሪው ደረጃ ሰርቶ መታየቱ ነው ? ወይስ የሰውየው ቂጥ ? ከግርምት ፣ ትዝብትና ሳቅ በኃላ ለመሆኑ ምንድነው ዓላማው ? ወይም ፋሽን ተከታዮቹን ምን ያህል ያስደስታል ? ለማለት ይገደዳሉ ፡፡ አብዛኛው ፋሽን ተከታይ በጆሮ ፣ ጸጉር ፣ ጃኬት ፣ ቲሸርት ፣ ጫማ ወዘተ ላይ ሲታይ እንደቆየው የዘመናዊነት መገለጫ ሳያካብዱ መመልከት እንደሚገባ የሚያስገነዝቡ ናቸው ፡፡ ፋሽን ይመጣል ፋሽን ይሄዳል እንዲሉ … ለምን ይቅርብኝ  ወይም ከማን አንሳለሁ በሚል ድሃ መነሻ የማያምርባቸውን ብቻ ሳይሆን የማያውቁትን ነገር የሚከውኑ ወንዶችም ሴቶችም የሚታዘንላቸው ናቸው ፡፡ እነዚህ ምስኪኖች ከሚሆኑትና ከሚለብሱት ዉጪ ስለ ጉዳዩ  አነሳስና ከጀርባው ስለሚጠረጠረው ጉዳይ ለማሰብ ግዜ የሚወስዱ አይደሉም ፡፡ 
 አነሳሱ  ...
ሱሪን ከቂጥ በታች አውርዶ መልበስ የተጀመረው በአሜሪካ እስር ቤቶች ውስጥ ነው ፡፡ Sagging Pants ይሉታል ፡፡ እስረኞች ቀበቷቸውን ራሳቸውን ለመግደልና በሌሎች ላይ ወንጀል መስሪያ መሳሪያ ማድረጋቸው ስለተደረሰበት እንዳይጠቀሙ ታገደ ፡፡ በዚህም ምክንያት ሰፊ ቱታቸውን መቆጣጠር ባለመቻላቸው ሱሪያቸው ታች መውረዱ ግድ ሆነ ፡፡

የጀርባው ንባብ  ...

ይህ ‹‹ ፋሽን ›› በጥርጣሬ ጨጎጊቶች የተከበበ ነው ፡፡ አንዳንዶች በእስር ቤት ልብስን ዝቅ አድርጎ መልበስን የሚያገናኙት ከግብረ ሶዶማዊነት ተግባር ጋ ነው ፡፡ የወሲብ ግንኑነታቸው መጠቆሚያ ስልት ነው በማለት ፡፡ አንዳንዶች የእስር ቤት አስተሳሰብ መሆኑን በመግለጽ በተለይ ጥቁሮች ‹ አሁንም እስር ላይ ነን › የሚል መልዕክት ያስተላልፉበታል ይላሉ ፡፡ አንዳንድ ጉዳዩን ያጠኑ ምሁራን ደግሞ ‹‹ በአሜሪካ የባርነት ዘመን ነጭ አለቆች የአፍሪካን ጥቁር ወንዶች አስገድደው ይደፍሯቸዋል ፡፡ ተግባሩ ከተፈጸመ በኃላ ተጠቂው ሱሪውን ዝቅ አድርጎ እንዲለብስ ይደረጋል ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አለቃው በቀጣይነትም ግንኙነት መፈጸም ሲፈልግ በቀላሉ እንዲለየው ነው ›› በማለት ቃላችን ርግጠኛ ነው ሲሉ ይደመጣሉ ፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ በ 1990ዎቹ አካባቢ የሂፕ ሆፕ አርቲስቶች ሱሪን አውርዶ መልበስን በማስፋፋት ረገድ ትልቅ ሚና መጫወታቸው ብዙዎችን ያስማማል ፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ባህልና ፋሽንን ከመግለጽ በተጨማሪ የነጻነት ማሳያም እንደሆነ ይጠቆማል ፡፡

በዚህ እሳቤ የኛዎቹ ፋሽን ተከታዮች ምን መልዕክት እያስተላለፉ መሆኑ ግራ ያጋባል ፡፡ በርግጥ በሀገራችን ግብረሰዶማዊነት እየተስፋፋ መሆኑ ይታወቃል ፡፡ የሱሪው መውረድ ሰምና ወርቅ ፋሽንና ያልተለመደ ወሲባዊ ግንኙነትን እያመላከተ ይሆን ?  ግብረ ሰዶማዊያን ለመግባቢያነት ይረዳቸው ዘንድ ጆሮአቸው ላይ ጌጥ ያደርጋሉ ፤ ሱሪ አውርደው ከሚፏልሉት ወገኖቻችን ገሚሶቹም ጆሮአቸውን ማስዋብ ይወዳሉ ፡፡ ግብረ ሰዶማዊያን  አንድ ጆሮ ላይ ጌጥ ካደረጉ ‹ አልተያዝኩም › ማለት ፈልገው ነው ፤ ሱሪ አውራጆቻችንስ ‹ አልተያዝኩም › ነው ወይስ  ‹ የማውቀው ነገር የለም ›  እያሉ  ነው የሚገኙት ፡፡ ሀገራችን እንደ ሌሎች አፍሪካዊያን ቅኝ ያልተገዛችና የባርነት ቀንበር ያልቀፈደዳት ቢሆንም ከሀገራዊ ባርነት መቼ ተላቀን እያሉበት ይሆን ? ነው አለማቀፉን ምልከታ ያልተረዳ ተራ የፋሽን ጉዳይ ?

ያን ግሩም ሙዚቀኛ ‹ ተቀበል ! › ማለት አሁን ነበር ፡፡
አቦ ተቀበል ! አፈሩ ይቅለልህና
‹ እሺ ልቀበል ! › …
‹‹ ምን ዓይነት ዘመን ነው በል ! ››
‹ ምን አይነት ዘመን ነው › …
‹‹ ምን አይነት ዘመን ነው - ዘመነ ዥንጉርጉር
 በምናገባኝ ቅኝት በኬሬዳሽ መዝሙር
 እንደሰጡት ሆኖ እንዳጣው የሚያድር
 አይገደውም ከቶ
 ‹ አይገደውም ከቶ › …
ለማያውቀው አንቀጽ ውል አጥብቆ ሲያስር
 በእውር ፈረስ ጀርባ ሽምጥ ሲኮረኩር ››
በልልኝ አቦ !!
 በእውር ፈረስ ጀርባ ሽምጥ ሲኮረኩር › …


ማስታወሻ፡- ይህ ፅሑፍ በቁም ነገር መፅሔት ቅፅ 12 ቁጥር 159 ላይ የወጣ ነው፡፡ ፅሑፉን በሌላ ሚዲያ ላይ የምትጠቀሙ ከሆነ ምንጩን እንድትጠቅሱ ትለመናላችሁ፡፡



Tuesday, August 13, 2013

የአቅጣጫ ለውጥ --- በማህበራዊ ሚዲያዎች ?




ታይም መጽሄት ፡፡

የፌስ ቡክ መስራች የሆነውን ማርክ ዙከርበርግን የ2010 የአመቱ ምርጥ ሰው በማለት ሰየመ ፡፡
የመጽሄቱ ውዳሴ ፡፡

ለፌስ ቡክ  --

‹‹ በአሁኑ ወቅት ከምድራችን ሶስተኛው ትልቅ ሀገር ነው ፡፡ በርግጠኝነትም ለዜጎቹ ከሌላው መንግስት በተሻለ መረችን ይሰጣል ››

ለማርክ ዙከርበርግ  --  


‹‹ ከሃርቫርድ ትምህርቱን ያቋረጠው ይህ ወጣት ቲሸርት የሚለብስ የሀገሪቱ ርዕሰ ብሄር ነው ››

››››                               ››››                                    ›››››                                  ››››

አንጋፋውና ታዋቂው መጽሄት ታይም ብዙዎችን ያስደመመውን ፈጠራና ፈጣሪ በዚህ መልኩ ቢያደንቀውም አትዮጽያን ጨምሮ በርካታ ሀገሮች ፌስ ቡክንና ማህበራዊ ሚዲያን የሚመለከቱት በታላቅ ጥርጣሬና ስጋት ነው ፡፡

በርግጥ ስጋቱ ከዘርፈ ብዙ አስተሳሰቦች የሚመነጭ ነው ፡፡ በዋናነት ግን የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ፣ ብሄርና ጎሳ ተኮር ግጭቶች እንዲጫሩ ፣ አክራሪ ሃይማኖታዊ አጀንዳዎች ስር እንዲሰዱ መንገድ ይከፍታል የሚሉት ሊጠቀሱ ይችላሉ ፡፡ ወረድ ሲባልም የግለሰቦች መብት ሊጣስ ፣ የስራ ባህል ሊዳከም ፣ ምርታማነት ሊያሽቆለቁል ይችላል የሚሉ መከራከሪያዎች ይቀርቡበታል ፡፡

በቴክኖሎጂው ዙሪያ የወፈረ ቅሬታ ያላቸው ሀገሮች በአብዛኛው ራሳቸውን ከሂደቱ ውስጥ ለማውጣት ግን የሚደፍሩ አይደሉም ፡፡ አካሄዳቸው አገም ጠቀም አይነት ነው ፡፡ ከቴክኖሎጂው መሸሽ እንደማይቻል ሁሉ ለዓለም ስል ትችትም ራስን አጋልጦ ላለመስጠት ሂደቱን በስሱ ወይም ለራሳቸው በሚመቻቸው መልኩ ያከናውኑታል ፡፡

እገዳ
 
‹‹ Nigeria Good People Great Nation ›› በሚል ርዕስ የሚጽፈው ብሎገር አማኑኤል አጁቡሉ የማህበራዊ ሚዲያ ቀበኛ ሀገሮችን ዘርዝሮ ጽፏል ፡፡ ፌስ ቡክ ፣ ዩቲዩብ ፣ ትዊተር እና ዊኪፒዲያን በመዝጋት ቻይናን የሚያህል የለም ሲል ያደረገቸውን ሚዛናዊነትንም ለመግለጽ በመሞከር ነው ፡፡ ቻይና ሚዲያዎቹን የዘጋችው የምዕራቡን ዓለም ተጽዕኖ ለመቋቋም ሲሆን በተነጻጻሪ የራሷን ሳይበር ኢንዱስትሪ በመፍጠር ተደራሽነቷን አረጋግጣለች ፡፡ ለአብነት ያህል Ozone የተባለው ማህበራዊ ገጽ 600 ሚሊየን አባላት አሉት ፡፡ Weibo የተባለው ሌላኛው ድረ ገጽ የቻይናን መልክ መላበሱ እንጂ ልክ እንደ ትዊተር ነው የሚሰራው ፡፡

እንደ ናይጄሪያዊው አማኑኤል ሁሉ ፍሪደም ሀውስ የተባለው ድርጅት በ 2012 ያጠናው መረጃ ኢትዮጽያን የብሎገር ፎቢያ እንዳለባት ጠቋሚ ነው ፡፡ 65 የዜናና አስተያየት፣ 14 የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ 7 የድምጽና ምስል ዌብሳይቶች፣ 37 ብሎጎችና 37 የፌስ ቡክ ገጾች ተዘግተዋልና ፡፡

ኢትዮጽያና አለምን ሲያጨቃጭቅ የነበረ ሌላ ክስተትም መጨመር ይቻላል ፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት ባጸደቀው አንድ ህግ በሀገሪቱ ውስጥ ስካይፒና ጎግል ቮይስን መጠቀም እስከ 15 ዓመታት እንደሚያሳስር ተገልጾ ነበር ፡፡ በሌላ በኩል መንግስት ስካይፒ መጠቀም ህገወጥ ድርጊት አለመሆኑን ፣ ህገወጥ የሚሆነው ህገወጥ ጥሪዎችን ማከናወን መሆኑን አስተባብሏል ፡፡ በተለይ ከዚህ አጨቃጫቂ ዜና በኃላ ሀገሪቱ ፌስ ቡክ ፣ ትዊተርና የመሳሰሉ ማህበራዊ ገጾችን ልትዘጋ እንደምትችል በስፋት ሲወራ ቆይቷል ፡፡ የኢህአዴግ አባላትም ከስብሰባ በኃላ ፌስ ቡክ ላይ የተጣዱ ሰራተኞችን በመታዘብ ‹‹ ግድየም ለጥቂት ግዜ ተመልከቱ ?! ›› በማለት ጉዳዩ እያበቃለት መሆኑን ያረዱ ነበር ፡፡

ፌስ ቡክ በተለይም ከአቶ መለስ ዜናዊ ሞት በኃላ ብዙ የድርጅቱ ደጋፊዎችን አቁስሏል ፡፡ በአቶ መለስ ሞት ህልፈት ኢትዮጽያዊ ብቻ ሳይሆን ዓለም ማዘን ይገባዋል ብለው ራሳቸውን በማሳመናቸው በሳቸው ላይ ይሰጥ የነበረውን ትችት ባለመቀበል ይህን የአሉባልታ ማናፈሻ ማሽን ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ መከርቸም እንደሚገባ በትንሹም ሆነ በትልቅ ስብሰባ ላይ አጠንክረው አስተያየት ሰጥተዋል ፡፡ በፌስቡክ ላይ የተማረሩ አንዳንድ መ/ቤቶች ሚዲያው እንዲዘጋ ያደረጉ ሲሆን በምሳ ሰዓት ብቻ መጠቀም የሚቻልበትን መንገድ ያመቻቹም ድርጅቶቸች አሉ ፡፡ የወረደ አፈጻጸም አሳይተዋል የተባሉ አንዳንድ ሰራተኞችም    ‹‹ ፌስ ቡክን በማባረር ቢሆን አንደኛ ነህ ! ›› የሚል ግምገማዊ ፌዝ ተቀብለዋል ፡፡ የኢንተርኔት መስመር ለመዘርጋት ያቀዱ አንዳንዶች ደግሞ በፌስ ቡክ ተጠቃሚዎች እንዳንወረር በሚል ስጋት እቅዳቸውን አዘግይተውታል ፡፡ በተለይም እንደ ሀገራችን በምግብ እህል ራሳቸውን ያልቻሉ ታዳጊ ሀገሮች ልማትን እንጂ ፌስ ቡክንና ግብረ አበሮቹን በፍጹም ማስቀደም እንደሌለባቸው  የሚያስረዱ ምሁራዊ ጥናቶችም እዚህና እዚያ ቀርበዋል ፡፡ በዚህና በመሳሰሉ ምክንያቶች መንግስት ፌስ ቡክን ከርችሞ ስሙን ከነፓኪስታን ፣ ኢራን ፣ ሶርያ ፣ ቱርክ ፣ ታይላንድና የመሳሰሉት ተርታ እንደሚያሰልፍ ብዙዎች እየጠበቁ ነበር ፡፡

ያልተጠበቀ ለውጥ
 
ታዲያ ምን ተፈጠረ ?
ታይም መጽሄት በ2010 ያደነቀውን ፌስ ቡክ ዛሬ የኢትዮጽያ መንግስት እንዴትና ለምን ሊቀበለው ቻለ ? ማለት እንዴት ሊሰራበት ፈለገ ?

በቅርቡ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጸ/ቤት በፌደራል ደረጃ ለሚገኙ ኮሙኒኬተሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጥቶ ነበር ፡፡ በስልጠናው በርካታ ጥናታዊ ወረቀቶች የቀረቡ ቢሆንም በውይይት ጎልቶ የወጣው ‹‹ አዲሱና ማህበራዊ ሚዲያ እንደ ተግባቦት ዘዴ ›› የሚለው ምዕራፍ ነበር ፡፡ ይህ ወረቀት በአጭሩና በጥቅሉ ሚዲያው ችግር ቢኖርበትም ጥቅሙን አጠናክሮ ለገጽታ ግንባታ መስራት የማይሸሽና የግዜው አማራጭ መሆኑን አስረድቷል ፡፡ የኮሙኒኬተር ባለሙያዎች የመ/ቤታቸውን ተግባር ብቻ ሳይሆን አጨቃጫቂውን የአባይ ግድብ የተመለከቱ መረጃዎችን ማሰራጨት እንደሚገባቸውም ተመልክቶ ነበር ፡፡
የፌስ ቡክና ማህበራዊ ሚዲያ ጉዳይም ተወካዮች ም/ቤት ደርሶ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ግንዛቤ እንዲያገኙበት ተደርጓል ፡፡ ዲፕሎማትና የአለም አቀፍ ባለሙያ የሆኑት አምባሳደር ቶፊክ አብዱላሂም በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ‹‹ የግብጽ ወጣቶች ፌስ ቡክና ትዊተር በጣም ይጠቀማሉ ፡፡ ኢትዮጽያዊያን ከግብጻዊያን ጋር እነዚህን ሚዲያዎች በመጠቀም በአባይ ወንዝ ፍትሀዊ አጠቃቀም ላይ መወያየት አለብን ፡፡ ወጣቱና የተማረው ትውልድ የግብጽ ህዝብን ለማሳመን መነሳት አለበት ›› በማለት አቅጣጫ ጠቋሚ አስተያየት ሰጥተዋል ፡፡
ግራም ነፈሰ ቀኝ የመንግስት አቋም እየተቀየረ መጥቷል ፡፡ የአቅጣጫውን ለውጥ ያመነጨው አባይ ወይስ ነባራዊው እውነት የሚል መከራከሪያ ማንሳት ግን አሁንም ይፈቀዳል ፡፡ መንግስት ከማህበራዊ ሚዲያዎች ጋር ሙሉ ለሙሉ መጋባት ባይፈልግ እንኳ ከተጨባጩ እውነት ጋ አዛምዶ ፍላጎቱን ለማሳካት እንደ አጋር ሊጠቀምበት ግድ ይለዋል ብሎ ማስቀመጥ ይቻላል ፡፡

የማይሸሸው እውነት
 
በአሁኑ ወቅት ተለምዷዊ በሚባሉት ሚዲያዎች / ጋዜጣ ፣ ሬዲዮ፣ ቴሌቭዥን / ብቻ በመታገዝ ማንነትን ለዓለም ማስተዋወቅ አይቻልም ፡፡ ማህበራዊ ሚዲያን ለመጠቀም የሚያስገድዱ በርካታ እውነቶችን ቴክኖሎጂው እያቀበለን ይገኛል ፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት 751 ሚሊየን ህዝብ ሞባይል ይጠቀማል ፡፡ በ20 ደቂቃዎች አንድ ሚሊየን መረጃዎች ሼር ይደረጋሉ ፡፡ በ20 ደቂቃዎች ሁለት ሚሊየን 176 ሺህ መልዕክት ይላካል ፡፡ በ20 ደቂቃዎች 10 . 2 ሚሊየን እስተያየቶች ይጻፋሉ ፡፡ በ20 ደቂቃዎች አንድ ሚሊየን 484 ሺህ የሁነት ማስታወቂያዎች ይለጠፋሉ ፡፡

ይህን አሐዝ ወደ አህጉራችን ጠጋ አድርገን መመልከትም ይገባል ፡፡ እንደ ‹‹ The internet coaching library ›› መረጃ መሰረት በአፍሪካ ከኢንተርኔት አልፎ የፌስ ቡክ ተጠቃሚው ቁጥር በሚያስገርም ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል ፡፡ በዚህ መሰረት ፣

ግብጽ - 12 ሚሊየን 173 ሺ 540
ናይጄሪያ - 6 ሚሊየን 630 ሺ 200
ደቡብ አፍሪካ - 6 ሚሊየን 269 ሺ 600 ፌስ ቡክ ተጠቃሚዋችን በማስመዝገብ ትልቁን ደረጃ ይዘዋል ፡፡ ሞሮኮ ፣ አልጄሪያና ቱኒዚያ በቀጣዩ ቅደም ተከተል ውስጥ የሚገኙ ሀገሮች ሲሆኑ ኢትዮጽያ በ 10 ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች ፡፡ 902 ሺ 440 በማስመዝገብ ፡፡

በአጠቃላይ ከሁለት መቶ በላይ ድረ ገጾችን ከምታስተናግደው ዓለም ርቆ ፖለቲካንም ሆነ መረጃን በሚፈለገው ልክ ማሰፋት አይሞከርም ፡፡ በተለይም 1 . 11 ቢሊየን ተጠቃሚ ካለው ፌስ ቡክ ፣ 500 ሚሊየን ተመልካች ካለው ትዊተር ፣ 225 ሚሊየን ከሚጎበኘው ሊንክደን ፣ 345 ሚሊየን ተመልካች ካለው ጎግል ፕላስ ቁርኝት አለመፍጠር የነገን መንገድ ካለማወቅ ጋር የሚገናኝ ነው ፡፡ እንግዲህ መንግስት እየቆየም ቢሆን በግድ መቆርጠም እንዳለበት የተረዳው እውነት ይህን ያህል ከድንጋይ የጠጠረ እንደሆነ መረዳት አይከብድም ፡፡

የመንግስት የቤት ስራ
 
‹ ወንድ ወደሽ ጺም ጠልተሸ አይሆንም › እንዲሉ ትግሬዎች ማህበራዊ ሚዲያዎችን ለገጽታ ግንባታ የመጠቀም ፍላጎት ካየለ ግራና ቀኙን ለመቀበል ዝግጁ መሆንን ይጠይቃል ፡፡ ቀኙ ከአዎንታዊ ውጤት ጋር የተያያዘ በመሆኑ የአደናቃፊነት ሚና ላይታይበት ይችላል ፡፡ ምናልባት የኮብል ስቶኑ መንገድ ካልተመቸ አስፋልት የማድረግ ስራ ይጠበቅ ይሆናል ፡፡ በርግጥ ማህበራዊ ሚዲያ ገጽታን ለመገንባት ፣ የገቢ ምንጭ ለማስፋት ፣ የሚዲያዎቻችንን ክፍተት ለመሙላት ፣ የዴሞክራሲና ስርዓቱን ለማጠናከር ፣ የገለሙ አሰራሮችን ለማጋለጥና ለመለወጥ ፣ የጦር ወንጀለኞችን ለማደን / ጆሴፍ ኮኒን ያስታውሷል / ፣ ምርጫን ፍትሃዊ ለማድረግም ሆነ ለማሸነፍ ፣ አምባገነኖችን ለመፈንገልና ለመሳሰሉ ጉዳዮች የላቀ ጥቅም ይሰጣል ፡፡

 ከላይ ለመጠቃቀስ እንደተሞከረው ጥቃቅኑ ችግር ገለል ሲደረግ ከስር አድፍጦ የሚገኘው ትልቁና ፖለቲካዊ ስጋቱ ወይም የግራ / ግራጋቢው / ክፍል ነው ፡፡ ማህበራዊ ሚዲያ በከፍተኛ ደረጃ የትግል መሳሪያ መሆን የጀመረው የ 26 ዓመቱ ቱኒዚያዊው ሞሀመድ ቦዋዚዝ መልካም አስተዳደር ማስፈን ያልቻለውን መንግስት ለመቃወም ራሱን በአደባባይ ካቃጠለ በኃላ ነበር ፡፡ እነዚህ ሚዲያዎች በአረብ አገራት ጭቆናና ኢ-ፍትሃዊ አሰራርን ለመዋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ የፈጠሩ ናቸው ፡፡ በግብጽ፣ ቱኒዝያና የመን በመሳሰሉ ሀገሮች በርካታ የተቃውሞና የአመጽ ጥሪዎች ተቀናብረው የተሰራጩት በፌስ ቡክና ትዊተር ነው ፡፡ አንድ የግብጽ አክቲቪስት ‹‹ ፌስ ቡክን ለተቃውሞ ፣ ትዊተርን ለማስተባበር ዩትዩብን ደግሞ ለዓለም ለመንገርና ለማሳየት እንጠቀምበታለን ›› ማለቱን ማስታወስ ይጠቅማል ፡፡ 

በግብጽ የሚታየውን ተደጋጋሚ ትግል መነሻ በማድረግም ብዙ ዘጋቢዎች ‹‹ የፌስ ቡክ አብዮት ›› እስከማለት ደርሰዋል ፡፡ በማህበራዊ ድረ ገጾች ጥናት ያደረገቸው ማርቲን ማህበራዊ ሚዲያ የትግል መነሳሳቱ እንዲጠናከርና የግዜ ማዕቀፍ እንዲያበጅ እገዛ አድርጓል ባይ ናት ፡፡ ዜጎች የጭካኔ ተግባራት ፣ የፍትህ መጣስና መዛባት፣ የሰቆቃ ህይወት በስፋት መኖሩን እንዲገነዘቡ ብሎም የፍርሃት ስነ ልቦናቸው እንዲወገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ፡፡ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው በርካታ አክቲቪስቶችም ‹‹ እነዚህ መሳሪያዎች ባይኖሩ የሙባረክ መንግስትን የመገልበጡ ሂደት በርካታ አመታቶችን ይፈልግ ነበር ›› ብለዋል ፡፡

ስለሆነም መንግስት በሁለቱ ጥቅሞቹና ጉዳቶቹ መካከል መንገዱን አስተካክሎ መጓዝ ይኖርበታል ፡፡ ችግሩን ተቀብሎ ሊያስተካክል ፣ ብርታቱን ሊመረኮዝበት እንደሆነ ሊያጤን ግድ ይለዋል ፡፡ ‹ ወንድ ወደሽ ጺም ጠልተሸ አይሆንም › የሚባለው ተረትም ቅርጹና መልዕክቱ ይኀው ነው ፡፡

››››                               ››››                                    ›››››                                  ››››

አዲስ ራዕይ መጽሄት ፡፡

የፌስ ቡክ ተጠቃሚ የሆነውን ከተማ ቀመስ ህዝብ የ 2006 ምርጤና  ነውጤ በማለት ስያሜ ይሰጣል ፡፡ ምርጦቹ  ‹ ልማታዊ ተጠቃሚዎች › የሚል የክብር ማዕረግ የሚያገኙ ሲሆን ነውጤዎቹ  ‹ ጥገኛ ተጠቃሚዎች › የሚል  ባርኖስ ይከናነባሉ ፡፡

የመጽሄቱ ውዳሴ ፡፡

ልማታዊ ተጠቃሚዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚወጡ ጸረ ልማት ዜናዎችን ፣  ዘገባዎችን ፣ ፎቶዎችንና ፊልሞችን ከፍተኛ ትዕግስት በመጠቀም አይቶ እንዳላየ በመዝጋት … እነዚህን ተውሳክና ተዛማች ሀሳቦች ባሉበት ቀጭጨው እንዲቀሩ LIKE እና  SHARE ባለማድረግ እንዲሁም COMMENT ባለመስጠት ሀገራዊ ግዴታቸውን ተወጥተዋል ፡፡

ዘላለማዊ ክብር ለመስመርተኞች !!




Monday, August 12, 2013

ጠይሟ ልዕልት !!




ጠይሟ ልዕልት
የሩጫው ድማሚት
ሰዓት ጠብቃ ስትፈነዳ
አንድም ታምራለች እንደ ጽጌሬዳ
አንድም ታርዳለች እንደ ካባው ናዳ ፡፡
ጠይሟ ቀስተ ዳመና
ባለብዙ ልዕልና
የስንቱን አይን በረገደች ?
በወቸው ጉድ በለጠጠች ::
የስንቱን ልብ አሞቀች ?
በፍቅር መዳፍ ጣለች ::
እናትስ ትውለድ ያንቺን አይነቱን አቦሸማኔ
ህዝብ የሚወድ አስተኔ  ፡፡
ለሀገር የሚሞት ወያኔ ፡፡

Sunday, July 28, 2013

‎የኃይሌ ገብረስላሴ መንገድ የት ያደርሳል ?‎



የአትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ የህይወት ቅደም ተከተል ባልተጠበቀ መልኩ መጓዝ በመጀመሩ ይመስላል ሰሞኑን በህዝቡ ውስጥ ትልቅ የመወያያ አጀንዳ ሊሆን የበቃው ፡፡ ለመሆኑ የሚጠበቀው ቅደም ተከተል ምን ነበር ? የሚል መሰረታዊ ጥያቄ እንደሚነሳ እንጠብቅ ፡፡

በአሰላ አንድ ተራራማ መንደር የተወለደው ኃይሌ ወደ ት/ቤት ለመጓዝ ረጅም ርቀት መጓዝ ይጠበቅበት ነበር ፡፡ የህይወት አርጩሜ ዘወትር እንዲሮጥ ብታስገድደውም እሱ ባያውቀውም በጥንካሬ ለሌላ ዕድል እያዘጋጀችው ቆይታለች፡፡ እናም ፤
. በ15 ዓመቱ ውድድር ጀመረ ፡፡
. ከአራት ዓመት ቆይታ በኃላ ደቡብ ኮሪያ በተካሄደው ጁኒየር ሻምፒዮን በ 5 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር ሩጫ አሸነፈ ፡፡
. ከዛማ ምኑ ቅጡ ? ሁለት ግዜ በኦሎምፒክ ፣ አራት ግዜ በአለም ሻምፒዮንሺፕ ፣ ለአራት ተከታታይ ግዜ በበርሊን ማራቶን ማሸነፍ ችሏል ፡፡ አያሌ የብሄራዊና ዓለማቀፍ ውድድሮችን የሩጫ ሪከርድ ሰባብሯል ፡፡
. በውድድር መፈተን ብቻ ሳይሆን በዕድሜ መግፋት ሲጀምር ደረጃውን ቀየረ ፡፡ በ2006 ግማሽ ማራቶን አሸነፈ ፡፡
. በ 2007 አዲስ የማራቶን ሪከርድ ማስመዝገብ ችሏል ፡፡

በ 43 ዓመቱ በሞስኮ ኦሎምፒክ በማራቶን ለመሳተፍ ይፈልጋል ፡፡ ከወጪ ቀሪ ስናወራርድ ኃይሌ በ 28 ዓመታት ውስጥ በስፖርት መድረክ በተለይም በረጅም ርቀት ውስጥ ነግሶ ቆይቷል ፡፡ ከዚህ በኃላ ይህን የሩጫ ንጉስ አብዛኛው ህዝብ ይጠብቅ የነበረው / የንግድና ኢንቨስትመት ስራው እንደጠበቀ ሆኖ / በዚሁ መደዳ እንደሚገኝ ነበር ፡፡ ማለትም ፤

. በሩጫ አስልጣኝነት
. በአትሌትክስ አማካሪነት
. በስፖርት ጥናትና ምርምር
. እንደ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ በአፍሪካ የስፖርት ተወካይነት
የሩጫው ንጉስ ግን ለ cctv ቴሌቪዥን እንዲህ አለ ‹‹ የአጭር ግዜ እቅዴ ለፓርላማ አባልነት መወዳደር ነው ፡፡ አንድ ቀን ደግሞ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት መሆን እፈልጋለሁ ››

የንጉሱ መሰረታዊ ምክንያት ?
 
አጃንስ ፕሬስ እንደዘገበው ኃይሌ ወደ ፖለቲካው መቀላቀል የሚፈልገው በፖለቲካው አማካኝነት ወደ ህብረተሰቡ ለመቅረብና ህብተረሰቡን ለመርዳት ነው ፡፡ ለፓርላማ የሚወዳደረው በግል ውክልና ነው ፡፡ ባለቤቱና ቤተሰቦቹ በኢትዮጽያ ፖለቲካ ውስጥ መሳተፉን ባይወዱለትም እሱ ግን ራስን ከፖለቲካ ማራቅ ‹‹ ትልቅ ስህተት ›› ነው ባይ ነው ፡፡ ‹‹ እዚህ እስካለንና እዚህ እስከኖርን ድረስ በርካታ ችግሮቻችንን በመለየት በመፍትሄው ዙሪያ የራሳችንን ድርሻ መወጣት አለብን ›› በማለት ጽኑ እምነቱን ለማጠናከር ሞክሯል ፡፡

ውሃ የሚቋጥረው ምክንያት የማነው ?
 
ኃይሌ እንደ ሩጫው ሁሉ በተሰማራባቸው የንግድ መስኮች ውጤታማ ነው ፡፡ በሆቴል ፣ በመኪና ንግድ ፣ በህንጻ ኪራይ ፣ በሲኒማ ቤትና በታላቁ ሩጫ ዝግጅት  እያደረጋቸው ያሉት ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችን መጠቃቀስ ይቻላል ፡፡ በቅርቡ በ 70 ሚሊየን ብር ካፒታል ወደ ቡና አምራችነት ጎራ የተቀላቀለ ሲሆን ማርን የመላክ ስራ ውስጥም ለመሳተፍ ዕቅድ እንዳለው ተመልክቷል ፡፡

የእነዚህ የተሳኩ ድምር ውጤቶች ግን በፖለቲካው መስክም ይደገማሉ ማለት ይከብዳል ፡፡ በርግጥ በኛ ሀገር ፖለቲከኛ ለመሆን የፖለቲካ ዲግሪ የግድ አለመሆኑ ያለፉት መንገዶቻችን ይጠቁማሉ ፡፡ አቶ መለስ ዜናዊም በአንድ ወቅት ለሹመት ከትምህርት ይልቅ ታማኝነት ሚዛን እንደሚደፋ አስረግጠው ተናግረዋል ፡፡ በርግጥ በእጅጉ የሚታወቀው ጆርጅ ዊሃ በርግጠኝነት አሸንፋለሁ በሚል ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውስጥ ገብቶ ያልተማረ አይመራንም … ዊሃን ያደነቅነው እግሩን እንጂ ጭንቅላቱን አይደለም በሚል የላይቤሪያ ህዝብ ካርዱን በሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ ለተከታተሉትና በዓለም ባንክ ላገለገሉት ኤለን ጆንሰን ሰጥቷል ፡፡ ዊሀም ከዛ በኃላ ሚያሚ በሚገኘው ዴሪ ዩኒቨርስቲ የቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ትምህርት መከታተል ጀምሯል ተብሏል - ዛሬ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ባይታወቅም ፡፡ እናም ለኃይሌ ስጋት የሚሆነው የትምህርት ዲግሪና / የክብር ያልሆነ / ፖለቲካዊ ዕውቀት አይሆንም ማለት ነው ፡፡ የሚከብደው ፖለቲካዊ  ተደራሽነቱን ለማረጋገጥ የመረጠበት መንገድ በእጅጉ አጠያያቂ ከመሆኑ ላይ ነው ፡፡

ኃይሌ በርካታ የመልካም አስተዳደር ህጸጾች ፣ የተንጠለጠሉ የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ፣ የሰብዓዊ መብት ጉደለቶች ፣ የድህነት ማነቆዎች ያሉበት ህብረተሰብ ጋ ደርሶ መፍትሄ ለማምጣት የመረጠበት መንገድ የግል እንደራሴ በመሆን ነው ፡፡ በሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ በግለሰብ ከተወከሉት ውስጥ ሻለቃ አድማሴ ዘለቀ ፣ አቶ በድሩ አደም እና ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እንዲሁም የተቃዋሚው ብቸኛ ተወካይ አቶ ግርማ ስይፉ ትላልቅ ሀሳቦችን ሲያሰሙ ቢቆዩም ‹ አንድ እንጨት አይነድም › የሚለውን ብሂል እውነተኛነት ከማረጋገጥ ውጪ የፈጠሩት ነገር በጉልህ የተጻፈ አይደለም ፡፡ በርግጥ በደማቅ ሙሉ ቀለም በተቀባው ፓርላማ ውስጥ ሌላ ቀጭን ሰረዝ እንዲታይ መፍጠራቸው ለተቃራኒው ወገን ሊጠቅም ይችላል ፡፡

ችግሮችን በመጠቆም ለህብረተሰቡ የድልድይነት ፣ ለመንግስት ደግሞ የመስታውነት ሚና ይጫወታሉ ቢባል እንኳ መንግስት በግል ተወካዮች የቀረቡትንና የተጠኑትን ትላልቅ ሀሳቦችና ውጥኖች ዕውቅና በመስጠት አይደለም ለተግባራዊነቱ የሚንቀሳቀሰው ፡፡ ጉዳዩ ለድርጅቱ አንድ የድጋፍ ካፖርት የሚደርብ ከሆነ በድርጅቱ ልዩ ታፔላ ዳር እንዲደርስ ይደረጋል ፡፡ እናም የትኛውም ድርጅት ቢሆን መነሻ ሀሳቡና ግጥሙ ‹‹ የተከበሩ የም/ቤት አባል የአቶ እገሌ ነው … ›› ብሎ እንደ ነጠላ ሙዚቃ እንደለቀቀ ድምጻዊ እውቅና ለመስጠት አይጨናነቅም ፡፡ ካልፈለገም ገና ከመጀመሪያው እንዳልሰማ ሆኖ የማለፍ መብቱ የተጠበቀ ነው ፡፡ በዚህ የአጣብቂኝ አካሄድ የግል ተመራጭ ህብረተሰቡን ከመስማትና ከንፈሩን ከመምጠጥ ውጪ ምን የሚያመጣው ተጽዕኖ አለ ለሚለው ጥያቄ ደፋር ምላሽ ለማምጣት ይቸግራል ፡፡ ለዚህም ነው ይህ አይነቱ የፓርላማ ውክልና እና ተፈላጊው ራዕይ ምን ያህል ውሃ የሚቋጥር ነው የሚያሰኘውም ?

የኃይሌ ሌላኛው ራዕይ ‹‹ ፕሬዝዳንት ›› መሆን ነው ፡፡ ፕሬዝዳንት በመሆንስ ህብረተሰቡን ቀርቦ ካለበት ህመም መፈወስ ይቻላል ? ፕሬዝዳንቱ ዘወትር ሩህሩህና አዛኝ ድምጾች ቢኖራቸው በገዢው ፓርቲ ፖሊሲ ፣ ስትራቴጂና ይሁንታ ላይ ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም አላቸው ? የእነዚህ ጥያቄዎች ትክክለኛ ምላሽ የሀገሪቱን የፖለቲካ ስርዓት በአግባቡ ከማወቅና ካለማወቅ የሚመነጭ ነው የሚሆነው ፡፡

የፕሬዝዳንትነት በትረ መኮንን

የኢፌዴሪ ህገመንግስት የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት ‹‹ ርዕሰ ብሄር ›› ብሎ ቢጠራም ትልቁን ስልጣን የሰጠው ለጠ/ሚ/ሩ ነው ፡፡ ጠ/ሚ/ሩን የሚሰይመው ደግሞ አብላጫ የፓርላማ ወንበር ያለው የፖለቲካ ድርጅት ነው ፡፡ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 71 መሰረት ፕሬዝዳንቱ የተሰጡት ስራዎች ሰባት ናቸው ፡፡ ከነዚህም መካከል የሁለቱ ምክር ቤቶች ዓመታዊ ስብሰባን መክፈት … ያለቀላቸውን ህጎችና ስምምነቶችን በነጋሪት ጋዜጣ እንዲወጡ ማወጅ … በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርብለትን አምባሰደሮችና ሌሎች መልዕክተኞች ሹመት ማጽደቅ … እንግዶችን ቢሮ ቁጭ ብሎ መቀበል … ሜዳሊያና ሽልማት መስጠት እና ይቅርታ ማድረግ ይገኙበታል ፡፡

እነዚህን ስራዎች ጣጣው እንዳለቀለት የአምባሳደር ሙሉ ልብስ ወይም ተፈትፍቶ ጉርሻን በጉጉት እንደሚጠብቅ የአድአ እንጀራ ልትቆጥሩት ትችላላችሁ ፡፡ የመጀመሪያው መሰረታዊ ጉዳይ ፕሬዝዳንቱ በወሳኝ ሁነቶች ውስጥ ራሱን ሊያሳትፍና እኔም ነጥብ ሊያዝለት የሚገባ ልዩ ድምጽ አለኝ ለማለት የሚያስችለው መፈናፈኛ የሌለው መሆኑ ሲሆን ሁለተኛውና ዋነኛው ግን እነዚህንም በህግ የተቀመጡ ስራዎች ለመስራት የመረጠው ፓርቲ ይሁንታ ማስፈለጉ ነው ፡፡ በህገመንግስቱ ድንጋጌ መሰረት አንድ ሰው ፕሬዝዳንት ሆኖ የሚሾመው በሁለቱ ፓርላማዎች የጋራ ስብሰባ ሁለት ሶስተኛ እጅ ካገኘ ብቻ ነው ፡፡

አንድ በምርጫም በቁንጥጫም ስልጣን የጨበጠ ፓርቲ ደግሞ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት እንዲሆንለት የሚፈልገውን ግለሰብ የሚመርጠው የአይኑ ቀለም ስላማረው ወይም ታዋቂ ስለሆነ ብቻ አይደለም ፡፡ ፖሊሲውን የሚያስፈጽም ፣ ፓርቲውን የሚያሞግስ ያለፈውን ስርዓት በጥፊ የሚያቀምስ … በክፉ ቀን ዎሽቶም ቢሆን የሚደግፈው እንዲሆን ይፈልጋል ፡፡ ከዚህ ውጪ ትላልቅ ህጸጾችን ቢመለከት እንኳ በየሄደበትና በአጋጣሚው ሁሉ ‹ ዘራፍ ! አጉራ ጠናኝ - አሁንስ መንግስቱን መሰልከኝ ! › ምናምን የሚሉ ጉርምርምታዎቹን በደረቅ ውስኪ ተጉመጥሙጦ መዋጥ ይጠበቅበታል ፡፡ ወይም ዝቅ ባለ ድምጽ የችግሩን አሳሳቢነት በትህትና መጠቆም ይኖርበታል ፡፡ ልክ እንደ ቢሮክራቱ የቢሮ ደብዳቤ - ከሰላምታ ጋር ! መባሉንም ሳይዘነጋ፡፡ለነገሩ ፕሬዝዳንቱ በተቃራነው እየተንጋደደ የሜሄድ ከሆነ ፓርቲው ለምንስ በዕጩነት ያቀርበዋል ? አጉል ባህሪው እያደር የተገለጠም ከሆነ ጸጥ እንዲል የሚያስችሉ መፍትሄዎች 1001 ያህል ስለሆኑ ብዙም አያስጨንቅም ፡፡ ስለዚህ ለፓርቲው ታማኝነቱ ወይም በውስጠ ታዋቂነት ደጋፊነቱ የግድ ይመስላል ፡፡

እንግዲህ ፕሬዝዳንትነት የገባ የወጣውን ስቆ ከመቀበል ፣ ዋንጫ ከመስጠትና የተሰፋ የመክፈቻ ንግግር ከማድረግ ፣ ውጭ ሀገር ከመጎብኘትና ከምግባረ ሰናይ ድርጅቶች የክብር ኒሻን ከመጠበቅ ዉጪ ምን የተረፈ ውጤት አለው ? በርግጥ ኃይሌ ፕሬዝዳንት ከሆነ ሊሻሻሉ ወይም ሊለወጡ የሚችሉ ጥቃቅን አሰራሮች ይጠፋሉ ማለት አይደለም ፡፡

የ First Lady ጉዳይ አንዱ ይመስለኛል ፡፡ First Lady መባል ያለበት የፕሬዝዳንቱ ወይስ የጠቅላይ ሚንስትሩ ባለቤት ? ስልጣኑን ሁሉ ጠቅልሎ የያዘው የሀገራችን ጠ/ሚ/ር ይህንን የክብር ስያሜ ቢያንስ ሚስት ላለው ፕሬዝዳንት መልቀቅ ይኖርበታል ፡፡ በዶ/ር ነጋሶ ዘመን ሚስታቸው የውጭ ዜጋ በመሆኗ ፣ ፕሬዝዳንት ግርማ ደግሞ ሚስት የሌላቸው መሆኑ እንጂ ቦታው ተቀምቶ አይደለም የሚል ያልተረጋገጠ ሀሳብም ስላለ ይህንን ዕቅድ የተሳካ ማድረግ የሚቻል ይመስላል ፡፡ እና ሚስትንና ልጆችን ይዞ በየሀገሩ መዝናናት ፣ በተከበረ የራት ግብዣ ላይ መናገርና ከአቻ ጋር መፎጋገር ፣ በማርሽ ባንድ መታጀብ ፣ በክብር ዘብ መሃል መንጎማለል ፣ የክብር መድፍ ማስተኮስ … ግዴላችሁም እቺኛው ክፍል የምታስመረቅን ሳትሆን አትቀርም ፡፡ በአጠቃላይ ግን ፕሬዝዳንት በመሆን ትርጉም ያለው ለውጥ ሊፈጠር የሚችለው ለህብረተሰቡ ነው ወይስ ለራሱ ለፕሬዝዳንቱ ክብርና ዝና ? የሚል ጥያቄ ያስከትላል ፡፡

ስውር ተጽዕኖዎች
   
                                                  
ከሁሉ አስቀድሞ እያንዳንዱ ሰው በፈለገው መስክ የመሰማራትና ህልሙን የመፈለግ መብት ያለው በመሆኑ የኃይሌን የፖለቲካ ተሳትፎ ማንም መቃወም የማይችል መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል ፡፡ ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነው እውነታ የኃይሌ የፖለቲካ ተሳትፎ ሳይሆን ያስቀመጣቸው ሀሳቦች ናቸው ፡፡ እንደራሴ ወይም ፕሬዝዳንት በመሆን ህብረተሰቡን ይበልጥ እጠቀማለሁ የሚሉት ፡፡ የሙግቱ ባቡሩም እንዴት ይቻላል ? በሚለው ሃዲድ ላይ የሚያተኩር ይሆናል ማለት ነው ፡

አሁን ባለው የፖለቲካ መዋቅር እንደሌሎች ሀገሮች በግል ተወዳድሮ ፕሬዝዳንት መሆን አይቻልም ፡፡ በጣም የሚከበርና የሚደመጥ ሴናተር ለመሆንም መንገድ የለም ፡፡ ይህ ቢቻል በርግጥም ታዋቂ ግለሰቦች ለውጥ ለመፍጠር ቅርብ ይሆኑ ነበር ፡፡ ኃይሌ እኛ በምንከተለው የፖለቲካ ስርዓት ፍላጎቱን ዕውን ለማድረግ የማይቻለው ከሆነ ቢያንስ በአንደኛው ውጤት ለመጽናናት የፈለገ ይመስላል ፡፡ ፕሬዝዳንት በመሆን ክብርና ዝና ለመጎናጸፍ ፡፡

ይህ ክብር ለአንዳንድ ታዊቂዎች ካላቸው ሀብት በላይ ነው ፡፡ ለምሳሌ ያህል የሰውነት ቅርጽ ተወዳዳሪና የፊልም አክተር የሆነው አርኖልድ ሸዋዚንገር የካሊፎርንያ ገዢ ሆኖ በየዓመቱ የተፈቀደለትን 175 ሺህ ዶላር አይቀበልም ነበር ፡፡ በሀብት ጫፍ የደረሱ አንዳንድ አትሌቶችና ስፖርተኞች ከሙያቸው ወደ ፖለቲካ ሲዞሩ ከፍተኛ ክብርና ርካታ አግኝተዋል ፡፡ ጋዜጠኛ ሲያረጅ ጸሀፊ ይሆናል እንዲሉ አትሌቶች ሩጫ በማቆሚያቸው ወቅትም ዝናቸው የሚቀጥልበትን ሰንሰለት ቢጠግኑ አይገርምም ፡፡

ለሁለት አስር ዓመታት አለማቀፍ የክሪኬት ተጫዋች ሆኖ ያገለገለው ፓኪስታናዊው ኢምራን ካህን ወደ መጨረሻው Movement For Justice የተባለ ድርጅት እስከማቋቋም ደርሶ ነበር ፡፡ በግንቦት 2013 ፓርቲው 35 መቀመጫ ሲያገኝ አንዱ ተመራጭ ሆኗል ፡፡ PEW የተባለ የምርምር ማዕከል በሰራው የ 2012 ጥናት ከአስር ፓኪስታናዊ ሰባቱ ለካህን ጥሩ አስተያየት አላቸው ፡፡

የእንግሊዙ መካከለኛ ርቀት ሯጭ ስባስቲያን ኮ አራት የኦሎምፒክ ሜዳሊያዎችን አሸንፏል ፡፡ በ1979 ሶስት የዓለም ሪኮርዶችን በ 41 ቀናት ልዩነት ውስጥ ማሻሻል ችሏል ፡፡ ኮ ራሱን ከሩጫው ዓለም ሲያገል ወግ አጥባቂውን ፓርቲ በመወከል ከ 1992 እስከ 1997 ድረስ የፓርላማ አባል ሆኖ አገልግሏል ፡፡ እንግሊዞች ይህን ድንቅ ሯጭ የህይወት ዘመን የም/ቤት አባል አድርገው ሾመዋል ፡፡ እንግሊዝ በ 2012 ለማግኘት የቋመጠችውን የኦሎምፒክ አዘጋጅነት ፉክክር በብቃት የመራ ሲሆን የኦሎምፒክ ጨዋታ ኮሚቴን እንዲመራም ኃላፊነቱን አግኝቶ ነበር ፡፡ የቢቢሲ ስፖርት ዝግጅትም በታህሳስ 2012 የዓመቱ ምርጥ ሰው በማለት ሸልሞታል ፡፡

ታዋቂው የብራዚል ተጫዋች ዚኮ በ 1990ዎቹ የስፖርት ሚንስትር እስከመሆን ደርሷል ፡፡ የቶተንሃም ተጫዋች ሮማን ፓብሊቼንኮ የፑቲንን ‹‹ United Russia  ›› ን በመወከል በ 2007 ተወዳድሮ ለከተማ ም/ቤትነት ተመርጧል ፡፡ በ 1995 የዓለማችን ምርጥ ተጫዎች የሚል ክብር ያገኘው ጆርጅ ዊሃ ለፕሬዝዳንትነት ተወዳድሮ ህልሙ በኤለን ጆንሰን ጨንግፏል ፡፡ ስለ አሉሚናቲ ማህበረሰብ በርካታ ሚስጥራዊ መጻህፍትን የደረሰው ዴቪድ አይክ ተስፋ የተጣለበት የኮቨንተሪ ሲቲ በረኛ ነበር ፡፡ 38ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጌራርልድ ፎርድ የሁለት ግዜ የአሜሪካ እግር ኳስ ሻምፒዮን ነበሩ ፡፡
ወደ ፖለቲካው ጎራ የተቀላቀሉ ሌሎች ታዋቂ አትሌቶችን መጠቃቀስ ይቻላል ፡፡ ምሩጽን አይቼ ነው ወደ ሩጫው የተገፋፋሁት የሚለው ኃይሌ አውቆም ሆኖ ሳያውቀው እነ ስባስቲያን ኮ ተጽዕኖ ቢያደርጉበት አይገርምም ፡፡

የድርጅት ጥላ
 
ከፓርላማ መራቅ ‹‹ ታላቅ ስህተት ›› ነው የሚለው ኃይሌ ከግል ተወዳዳሪነት ዉጪ የድርጅት አባልነትን የማይታሰብ መሆኑን ተናግሯል ፡፡ ምናልባት እዚህ ላይ ራሱ የተናገረው ‹‹ ታላቅ ስህተት ›› ለራሱም የሚሰራ መስሏል ፡፡
በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በግል መወዳደር የግል ታዋቂነትንና ዝናን ከመጨመር ዉጪ ፖለቲካዊ ፋይዳ እንደሌለው ከላይ አይተናል ፡፡ ኃይሌ በግሉ ከሚወዳደር ይልቅ እንደ ፓኪስታናዊው ኢምራን ካህን የራሱን ድርጅት ማቋቋም አሊያም ከገዢው ወይም ከተቃዋሚ ድርጅቶች ሰፈር ጎራ ቢል ይመረጣል ፡፡ እንደዚያ ሲሆን ነው የእውነት ህብረተሰቡን ሊቀርብና ለውጥ ሊያመጣለት የሚችለው ፡፡

ለምሳሌ ያህል ኢህአዴግ ውስጥ ታቀፈ እንበል ፡፡ የድርጅት ጥላ ካገኘ በጣም ቢያንስ ባካባተው ሰፊ ልምድ መሰረት አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ወይም ስፖርት ኮሚሽን ውስጥ በኃላፊነት ለመሾም ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል ፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ያደፈውን አሰራር ለማጥራት እንዲሁም በህልሙ የያዛቸውን አዳዲስ አሰራሮች እውን ለማድረግ ይመቻል ፡፡ ይህም ለውጥ ስለሚያስገኝ የስንት ዓመት የውጤት ጥማት ያለበትን ህብረተሰብ ታደገ ማለት ይሆናል ፡፡ ስለዚህ እውነተኛ ፖለቲከኛ ለመሆን ከቆረጠ አካሄዱ ‹‹ ታላቅ ስህተት ›› እንዳይፈጥር መመርመር ይኖርበታል ፡፡

የትኛው መስመር ?

በርግጥ ኃይሌ የትኛውን መስመር ቢከተል ነው ህብረተሰቡን ይበልጥ መቅረብና መርዳት የሚችለው ?
. ኢንቨስትመንቱን በማስፋፋት
. የበጎ አድራጎት ስራን በማጠናከር
. ሙያዊ ልምዱን በመመንዘር
. የፕሬዝዳንትነት ካባን በመላበስ …  ????????


ማስታወሻ፡- ይህ ፅሑፍ በቁም ነገር መፅሔት ቅፅ 12 ቁጥር 157 ላይ የወጣ ፅሑፍ ነው፡፡ ፅሑፉን በሌላ ሚዲያ ላይ የምትጠቀሙ ከሆነ ምንጩን እንድትጠቅሱ ትለመናላችሁ፡፡


Tuesday, July 16, 2013

ጥርስ የሚፍቁ መስሪያ ቤቶች



1 . ‹‹ እንደ ተቋም ጥፋት ስላጠፋን ይቅርታ እንጠይቃለን ›› የሚለው መግለጫ የሚጠበቅ ስለነበር የሚያስገርም አልሆነም ፡፡ አስገራሚ የሆነው የሚጠበቀው መፍትሄ ሊፈታ ያልቻለ እንቆቅልሽ መሆኑ ነው ፡፡ የተጎዳውን ህዝባዊ ስሜት ለመጠበቅ ከሞራልና ህግ አንጻርም ሊሰራበት ያልተቻለን ስልጣንን ለሚሰራ አካል ማስረከብ ግድ ነውና አመራሩ ለራሱ ቀይ ካርድ እንደሚያሳይ ተጠብቋል ፡፡
ግን አልሆነም ፡፡

‹‹ ሁለት ቢጫ ማየት በምንያህል ተሾመ ይብቃ ! ›› ሲል የአቋም መግለጫውን አሰማ ፡፡ ይህ መግለጫ ደረቅ አይሆን ዘንድም ጥቂት የእግር ኳሱና የአመራሩ አባላት በጥፋተኝነት ቅባት እንዲዋዙ ተደረገ ፡፡ የፌዴሬሽኑ አመራር አካላት በህዝብ ለቀረበላቸው የልቀቁ ጥያቄ ‹‹ በክረምት ቤት አይገኝም ! ›› በሚል ሰበብ ለራሳቸው የወራት እድሜን ጨምረዋል ፡፡ በውስጣቸው  ግን  ‹ ይህ ስልጣን በመልቀቅ ሀብታም የሆነው የአውሮፓ ፌዴሬሽን አይደለም ! › ማለታቸው ይገመታል ፡፡

መቼም ይህ ፌዴሬሽን እንደ ሁላችንም ጨዋታ ተመልካች እንጂ መንገድ አመላካች አልሆነም ፡፡ ምንም ስራ እንደሌለበት ፊውዳል ክቡር ትሪቡን ላይ ቁጭ ብሎ ጥርሱን እየፋቀ ይባስ ብሎ ግራና ቀኝ ሰው መኖሩን በመዘንጋት የቆሸሸ ምራቁን ጢቅጢቅ .. በማድረጉ ስንቱን የዋህ ህዝብ ለማዲያትና ለጨጓራ በሽታ ዳረገ ?

2 . አንድ ሰሞን ከነዳጅ መውጣትና መውረድ ጋር ተያይዞ የትራንስፖርት ታሪፍን ለህዝቡ ይገልጽ ነበር ፡፡ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን ድሃዋ አዲስ አበባ በሚያስገርም ሁኔታ ሀብታም ፎቆችን ሳይቀር ማፈራረስ ይዛለችእግረ ጠባቦቹም ሆኑ ሰፋፊዎቹ መንገዶቿ አዲሱን ሰርገኛ ለማስተናገድ በመፈራረስ ሽርጉድ አብዝተዋል ፡፡

ይህ ያልተጠበቀ ግርግር የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮን ያደናገረው ይመስላል ፡፡ አምስትና አስር ሳንቲም መጨመር የሚቻለው በእኔ እውቅና ነው ይል የነበረው ይኀው ተቋም ዛሬ ታክሲዎች 1 . 35 መንገድን 2 . 70 2 .70 መንገድን 3 . 70 በገዛ ፍቃዳቸው ሲያስገቡ ስልጣኑን ማስጠበቅ አልቻለም ፡፡ ለአብነት ያህል ከጦር ኃይሎች /ፍርድ ቤት በልደታ አድርጎ ሜክሲኮ በመድረሱ ብቻ ዋጋው መቶ ፐርሰንት መድረሱ በእጅጉ የሚያስገርም ሆኗል ፡፡

በዚህ ሁሉ የህግ ጥሰትና ዘረፋ መካከል ቢሮው ጋቢ ደርቦ ቁጭ ብሏል ፡፡ ከሶማሌ ባስመጣው ረጅም መፋቂያ ጥርሱን ደጋግሞ እየፈተገ ከራሱ ጋር እሰጥ አገባ ይዟል  ‹‹ ምን ይደረግ ታዲያ ! የልማት ጉዳይ ነው ፡፡ መንገድ በሌለበትስ ታሪፍን እንዴት ከፍና ዝቅ ማድረግ እችላለሁ ? ››
ከደረበው ጋቢ ይሁን ከግድየለሽነቱ ከመብራት ኃይል ቀጥሎ የላቀ የቸልተኝነት ኃይል እያመነጨ ይገኛል ፡፡ ይኀው ቸልታው ግን  ‹ እንኳን እናቴ ሞታ ድሮም አልቅስ አልቅስ ይለኛልየሚለውን የከተማ ነዋሪ ለጉዳት እየዳረገው ነው ፡፡ አዲሱ ሰርገኛ የሚመጣው ከሁለትና ሶስት ዓመታት በኃላ በመሆኑ ይህ ቢሮም እስከዛ ድረስ የአፉን መደገፊያ ላይጥል ነው ማለት ነው :: እስከዛ ድረስ ለሚደርሰው ብዝበዛ ማን እንደሚጠየቅ ለጸረ ሙስና ወይም ለእንባ ጠባቂ ግልባጭ ማድረግ ሳያስፈልግ አይቀርም ፡፡

3 .ገንዘብ በመቆጠባችሁ ብቻ እሸልማለሁ ማለት ከጀመረ አመታት አሳለፈ ፡፡ ስልቱም የልማት አጋር ብቻ ሳይሆን የአዲስ አሰራር መንገድ መሆኑን
ነግሮናል ፡፡

ኬር ! ብለናል ፡፡

አዲስና ዘመናዊ መንገድ ብሎ ካስተዋወቀን አሰራር ውስጥ ኤቲኤም ይገኝበታል ፡፡ ይህ ካርድ የተሰጠን ግዜ ላላፊው አግዳሚው ብቻ ሳይሆን ለራሳችንም አስር ግዜ ከኪሳችን መዥለጥ እያደረግን አስኮምኩመነው ነበር ፡፡

መሰለፍ ድሮ ቀረ ብለናል ፡፡
ብር እንደ አበሻ ጎመን ከቅርባችን ሊቀነጠስ ነው ብለናል ፡፡

ይሁን እንጂ እነዚህ ማሽኖች በአጭር ግዜ ውስጥ በበሽታ ማስነጠስ ጀመሩ ፡፡ ቀስ በቀስም የሚከበሩ ዋንጫዎች ሳይሆኑ ባዶ ቆርቆሮ መሆናቸውን አስመሰከሩ ፡፡ እንደ ወንድማቸው የመንገድ ስልክ የነሱንም ወገብ በፍልጥ የሚነርት በዛ ፡፡ የአራዳ ልጆች አናታቸውን ከፈት አድርገው ቆሻሻ ይጥሉበት ነበር ፡፡ ይህ ከመሆን ለጥቂት የተረፈው ቆርቆሮዎቹ የቆሙት ጥበቃ ያለበት አካባቢ መሆኑ ነው ፡፡ አልፎ አልፎ የሚሰሩት ደግሞ ሰው ብር በሚፈልግበት ቅዳሜና እሁድ ለጥቂቶች አገልግለው ጎተራቸው ባዶ መሆኑን ያውጃሉ ፡፡
የታመመውን ዘመናዊነት መታደግ የደከመው የኢትዮጽያ ንግድ ባንክ ነው እንግዲህ በአናቱ ላይ ስለ ቁጠባ ሳያሰልስ የሚጨቀጭቀን ፡፡ አንዳንዶች ዘወትር ለስራ የሚጠቀሙትን አንዳንዶች ወር ጠብቀው የሚያገኙትን ደመወዝ ለመቀበል ሲሄዱ ‹‹ እንኳን ደህና መጣችሁ ! ›› የሚለው ትሁት ቃል አይጠብቃቸውም ፡፡ ደንበኛን የማያስቀይመው ንግድ ባንክ ግን ተመሳሳይ ቃል አመንጭንቷል ፡፡

‹‹ ኮንኬሽን የለም ! ›› የሚል
‹‹ ዛሬም ?! ››
‹‹ ምን እናድርግ ? ቴሌ እኮ ነው ?! እጀ ሰባራ አደረገን ! ››
‹‹ ታዲያ ሌላ አማራጭ የለም ? ››
‹‹ ምን ይምጣ ? የለም ! ››
‹‹ ወይ ጌታዬ ምን ይሻል ይሆን ? ››
‹‹ ሌላ ቀን ብቅ ማለት ወይ እስኪመጣ መጠበቅ ነዋ ! ››
‹‹ መቼ ይመጣ ይሆን ? ››
‹‹ እንጃ ! ቴሌም አያውቀው ! ››

ስለ ዘመናዊነት የሚያወራው ባንክ ስራውን ከቴሌ ጋር በጋራ ተስማምቶና ተነጋግሮ እንደጀመረ ይገመታል ፡፡ ግን ጉልቤው በየቀኑ ሲቆነጥጠውና ሲያሸው ሊታገለው ሊቃወመው ሊገስጸው አልደፈረም ፡፡ ስለዚህ ብር አስቀማጩ ባንክ አስር አለቃ የአየሩ አክሮባቲክስ ቴሌ ኮሎኔል መሆናቸውን ለመገመት እንገደዳለን ፡፡ ጂኔራሎቹን ያው መገመት ይቻላል ፡፡
በዚህም ምክንያት አዳራሽ የሞሉት ባለከራባት ሰራተኞች ወንበር ላይ ተለጥጠው ጣራ የነካ ብር ተደግፈው ጥርሳቸውን መፋቅ ይጀምራሉ ፡፡ ትዕግስተኛው ህዝባችን ደግሞ ከመስታውቱ ጀርባ እጅብ ብሎ አፋፋቃቸውን በጥብቅ ይመለከታል ፡፡

‹‹ አለ መፋቂያ ! መፋቂያ  ! … የክትክታየቀረሮየዋንዛ
  የሚያሳምር  … የሚያወዛ ››

የሚል ድምጽ ስማ ስማ አለው ጆሮዬን ::