Monday, February 25, 2013

የ 12 ሰዓት ፍቅር


ልክ 12 ሰዓት ሲሆን ነቀምት ወይም የኦሮሚያ ክልል ማብቃቱን መንገዱ ላይ የተዘረጋው ገመድ ጠቆመን ፡፡ እዚህ ገመድ አጠገብ ‹‹ እንኳን ወደ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በደህና መጣችሁ ! ›› የሚል ታፔላ አልተሰቀለም ፡፡ ሁለት ጥቋቁር ረጃጅም ፖሊሶች በአካባቢው መታያታቸው በጀ እንጂ የቀጭኑ ገመድ ውክልና ለኬላ ነው ብሎ መከራከር በፍጹም አያዋጣም ፡፡ የረጅም ርቀትን አሸናፊ አትሌት ደረት የሚጠብቅ እንጂ ፡፡

የቤኒሻንጉልን ምድር ስንረግጥ መልካም አቀባበል ያደረገችልን በመጥለቅ ላይ የምትገኘው ፀሃይ ነበረች ፡፡ ከተራራው አናት ላይ ፍም ውበቷን ያለ ንፍገት በትናዎለች ፡፡ ዛፍና ዳመና ካልገረዷት አይን የሚስብ ክብነቷና ድምቀቷ ነው የሚጎላው ፡፡ በዛፍና ዳመና ስር አጮልቀን ስንመለከታት ግን በርካታ ጨረሮቿ ሌላ የውበት ህብር ፈጥረው ይታያሉ ፡፡

መኪናው ወዲህና ወዲያ ሲጠማዘዝ አንዴ በግራ አንዴ በቀኝ ጠርዝ የምትገኝ በመሆኑ እንደ ጦጣ እየዘለሉ መከታተል ግድ ይላል ፡፡ ለግዜው የቤኒሻንጉልታፔላየሆነቸው ፀሃይ ትመስጣለች ፡፡ ለጥ ባለ ሜዳ ከርቀት ስትታይ ደግሞ የውበቷን ምስጢር አንድ ሁለት እያሉ ለመቁጠር የሚገርም ዕድል ይፈጠራል ፡፡ በፀሃይዋ አካባቢ የሚገኘው ዳመና ብቻ ሳይሆን የምድር አካላቱም ማለትም ተራራው ሜዳው የገበሬ ቤቶች ደኑና ሳሩ ሁሉ አብረቅራቂ ውበት ይጎናጸፋሉ ፡፡ የዚህን ውበት መነሻና መድረሻ እንደ ኬላ ገመዱ ከዚህ እስከዚያ ድረስ ነው ብሎ ማየት መቻሉ ያስገርማል ያፍነከንካል ፡፡

ውበቱን መቋደስ ያልቻለው የደመና ክፍል ጠቋቁሮ ይታያል ፡፡ ሜዳና ተራራዎችም አጠገባቸው ከሚገኘው አብረቅራቂ አካባቢ በሶስት ሰዓት ርቀው ከምሽቱ ሶስት ሰዓትን ያስቆጠሩ ይመስላሉ ፡፡ ይህ ተቃርኖ ያስደምማል ፡፡ ይህ ተቃርኖ የፈጠረው ውበት የመምሸትና የመንጋትን ብቻ ሳይሆን የጥቁርና ነጭነት ተፈጥሯዊ ማንነታችንንም ጭምር መሆኑ ሌላው ብስራት ነው ፡፡

በዚህ ሰዓት የሚታየው ምድራዊ ገጽታም አሰደማሚ ነው ፡፡ ከብቶች ወደ ማደሪያቸው ፀጥ ባለ መንፈስ መስመር ይዘው ይጓዛሉ ፡፡ በሳር የተጎነጎኑ ድንክዬ የገበሬ ቤቶች አናት ላይ ደግሞ ቀኑን እየተሰናበቱ ይሁን ወይም የማስተዛዘኛ ጥሬ ፍለጋ ላይ የተሰማሩ ቁራዎች ለዘብ ባለ ድምጽ ያንቋርራሉ ፡፡ ቤታቸው የደረሱ ከብቶች ደግሞ ውጭ ተኮልኩለው የምሽቱን ድባብ እንደሚቃኙ አሳዳሪያቸው አጥር ጥጉን መታከክ መርጠዋል ፡፡

እዚህ እንደ ከተማ ውክቢያና መንቀዥቀዥ የለም ፡፡ ዳመናው በዝግታ ነው የሚጓዘው ፡፡ ፀሃይ ወደ ተራራ ቂጥ ስር የምንትሸራተተው በጣም በሚታይ ዝግመት ነው ፡፡ ከብቶች ወደ መስክ ሴቶች ወደ ምንጭ ሲካለቡ አይታይም ፡፡ በዚህ ጠይም የአየር ንብረትና ወርቀዘቦ ብርሃን ስር ተገኝቶ ከሰማይ እስከ ምድር ያለውን እንቅስቃሴ መቃኘት በርግጠኝነት ፍቅር ያሲዛል ፡፡ የጂጂ ዘፈን በእንደዚህ ዓይነት ስሜት ውስጥ ለሚገኝ ሰው ምን ያህል ሚዛን ደፊ ሆኖ እንደሚገኝ ማረጋገጥ አይከብድም ፡፡ደህና ሁን ከተማ ነው ያለቸው 

በፀሃይዋ ዙሪያ የሚገኘው ዳመና ሲሰባሰብና ሲበታተን ከዚያኛው ወገን በተሻለ መልኩ ይታያል ፡፡ በዚህ ግልጽ ጉዞው ደግሞ የተለያዩ ቅርጾችንና ስዕሎችን ሲያደምቅና ሲኩል መመልከት ይቻላል ፡፡

የደከመችው ሞባይሌ ስራ አልፈታችም የማታ ጀንበር የምታሳየውን ረቂቅ ውበት አንዳቅሟ ደጋግማ ታነሳለች ፡፡ ያነሳሁትን መላልሼ በማየት ደብዛዛውን እሰርዛለሁ ፡፡ ለተሻለው ደግሞ ማምሻም እድሜ ነው እንዲሉ ጋለሪ ውስጥ እንዲቆይ ይለፍ ይሰጠዋል ፡፡ ድንገት ግን አንድ ፎቶ ላይ አይኔ ፈጠጠ ፡፡ ከጀንበርዋ በላይ ከጥቁሩ ዳመና በስተቀኝ አናት ላይ ከአንገት በላይ የሆነ ስዕል ተመለከትኩ ፡፡ አይኖቹ አፍንጫው አፉ ገባ ያለ አናቱና ወረድ ያለው ፀጉሩ በግልጽ ይታያል ፡፡ ማመን ከበደኝ ፡፡ ሶስት ፎቶዎች ላይ ይኀውን ምስል ተመለከትኩ ፡፡

ገራሚና ደስ የሚል ስሜት ውስጥ ገብቻለሁ ፡፡ በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ያታከተኙ አምስት w አንድ H የተባሉ ጥያቄዎች ስርዓት ባጣ መልኩ አእምሮዬ ውስጥ ይነጥሩ ጀመር ፡፡
ይህን ስዕል ማን ሳለው ?
ይህ ስዕል ምንድን ነው ?
ይህ ስዕል እንዴት ተሳለ ?
ይህ ስዕል መቼ ተሳለ ?

በርግጥ የዚህ ስዕል ጉዳይ የተራ ግጥምጥሞሽ ውጤት ወይስ አንድ ያልታወቀ ምስጠራዊ መልዕክት መግለጫ ? እጠይቃለሁ እንጂ በቂ ምላሽ ውሰጤ ማመንጨት አልቻለም ፡፡ እኮ የምን ሚስጢር ? ከዳመናው ላይ አዘቅዝቆ የሚያየው ሰው ማነው ? አንድ ቤኒሻንጉላዊ  / በርታ፣ ጉምዝ፣ ሺናሻ… / አይኔ የፈጠረው ተራ ምስል ? 12 ሰዓት ዘወትር ሊገኝ የሚችል ተዓምር ? እኮ የምን ተዓምር ? … 12 ሰዓት ፍቅር ? የጠይም ፈጣሪ ምስል ? ወይስ በሌላኛው ዓለም የሚገኙ ሰዓሊዎች የደመና ቅብ ? ይህ ዓይነት ልዩ ፈጠራ እነሆ በረከት የሚለው ዳቬንቺ ፒካሶ ወይስ ገብረክርስቶስ ?
እንደዚህ አይነት ጉዳዮች ጥያቄ እንደሚበዛባቸው ብቻ ሳይሆን ምላሽም በቀላሉ እንደማይገኝላቸው ከልምድ ይታወቃል ፡፡ ብቻ 12 ሰዓቷ ጀንበር ከየትኛውም አዋቂ በተሻለ መልኩ ፍቅር ምን እንደሆነ በተግባራዊ ዘዴ ያስተማረች መስሎ ተሰምቶኛል ፡፡ 

ፍቅር ዕውር ነው የሚሉ ሰዎች አሉ - እውነት ከሆኑ መንገዱን ጨርቅ ያድርግላቸው ፡፡
እግዚአብሄር ፍቅር ነው የሚል አባባል አለ - ይህ 12 ሰዓት ፍቅር የፈጣሪ ስራ አለመሆኑን ማን ማረጋገጥ ይችላል ? ማንም !

ለማንኛውም ሁለቱን በተከተታይ 12 ሰዓት በፍቅር የተነሱ ፎተዎቼን ይመርምሯቸው ፡፡