ለግማሽ ፍጻሜ የደረሱት ሶስቱ የአዲስ አበባ ክለቦች
ውድድር ተጠናክሮ ቀጥሏል ፡፡ በርካታ የአገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችን በከፍተኛ ውጤት በማሸነፍ ለጠንካራ ፉክክር የደረሱትን ቴሌ፣
ውሃና ፍሳሽ እንዲሁም መብራት ኃይል ብዙዎች ‹‹ የማይበገሩ የከተማው ደርቢዎች ›› እያሉ በመጥራት ላይ ይገኛሉ ፡፡
በክለቦች ዙሪያ ሰፊ ጥናት ያደረጉት ሙያተኞች
ግን ከላይ የተጠቀሰውን ስያሜ ስሜታዊ በማለት ‹‹ The big three ›› ወይም ሶስቱ ትላልቆች በሚል ሀቀኛ ስያሜ እንዲጠሩ
እያሳሰቡ ናቸው ፡፡ ለዚህ ስያሜ መሰረት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ለመንግስት ትልቅና የማይነጥፍ የገቢ ምንጭ መፍጠራቸው ፣ ለግል
ባለሀብት ለመስጠት የማይታሰቡ መሆናቸው ፣ አንዱ በጉንፋን ሲጠቃ ሁሉም ጋ ቀኪያም ሳል መመዝገቡ ፣ ለህዝብ የእርካታ ወይን ብቻ
ሳይሆን የምሬት አውጥ መፍጠር የሚችሉ ንጥረ ነገሮች መሆናቸው እንደ ጥቂት አብነት ሊነሳ ይችላል ፡፡
የዓመቱን ሻምፒዮናነት ክብር ለመቀዳጀት ሶስቱም
ቡድኖች በደርሶ መልስ የርስ በርስ ግጥሚያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ፡፡ በቡድኖቹ መካከል ያለው ተቀራራቢ ብቃት ዋንጫው ወዴት ያመራል
የሚለውን ህዝባዊ ጥያቄ ምላሽ አልባ እንዲሆን አድርጎታል ፡፡
1 .
አንዳንድ የመብራትና ውሃፍሳሽ ደጋፊዎች ቴሌን በመፎከርና ፕሮግራሞችን ስፖንሰር በማድረግ አንደኛ እየሆነ
ነው ይሉታል ፡፡ ደንበኞቼን 18 ሚሊየን አድርሻለሁ ባለ ማግስት 18 ሺህ የችግር ፖስት ካርዶችን ያሳትማል ባይ ናቸው ፡፡ ለምሳሌ
ሁለት ሰዎች ጨዋነቱን ለመፈተን ሆን ብለው አጠገብ ለአጠገብ ሲደዋወሉ ‹‹ ደንበኛዎ በአካባቢው የለም ›› የሚል አይን ያወጣ ዉሸት
ያሰማል ፡፡ ከፈለገ የመቶ ብር ካርድ መሙላትዎ እየታወቀ ‹‹ ያለዎት
ቀሪ ገንዘብ አነስተኛ ነው ›› በማለት እንዲያፍሩበት መንገድ ይከፍታል ይሉታል ፡፡
ስራን በጥራት ከመስራት ይልቅ መቶ ምጣድ አሙቆ
እንጎቻ ለመጋገር ይንደፋደፋልም ተብሏል ፡፡ ሰዎችን በአግባቡ ማገናኘቱን ሳያረጋግጥ የሞባይል ቀፎ ሲቸረችር ይገኛል ፡፡ ትችትና
ሮሮ ሲበዛበት ደንበኞችን ለማስተንፈስ አንዳንድ ‹ ቲፖችን › ያበረክታል ፡፡ ከነዚህ መካከል ካርድ ሲሞላ የ 3፣ 10 ፣ እና
15 ደቂቃዎች መመረቅ አንደኛው ነው ፡፡ የአራዳ ልጆች ይህችን ነቄ የተባለባት ማለዘቢያ ትቶ ጠንካራ ስራ ቢሰራ ይሻለዋል እያሉ
ይገኛሉ ፡፡
ያም ሆነ ይህ በአንዱ አካባቢ ጥሩ እየተሰማ ሌላው
ዘንድ ጤናማ ግንኙነት መፍጠር ያልቻለው ቴሌ ወደፊት የመደናቆሩን ሂደት ከወረዳ አቀፍ አውርዶ ወደ ቤት ለቤት እንዳያሸጋግረው ተሰግቷል
፡፡ በዚህ አካሄዱም የወደፊት ኢትዮጽያን ማገናኘት የተባለውን መሪ ቃል ለሚገባቸው ሸጦ ‹‹ እረ አይሰማም ፤ ይቆራረጣል !
›› የተሰኘውን ሞዴል ስራ ላይ እንዳያውለው ተፈርቷል ፡፡
2 .
ህዝቡን ክረምት ላይ የፈረቃ እሸት ማስገመጥ ያስለመደው
መብራት ኃይል ዘንድሮ ምርቱን ከወዲሁ በስፋት ገበያ ላይ ማዋል ጀምሯል ፡፡ ሰፊውን የሀገሪቱ ግዛት ያለ ስስት ማጥቆሩን ተያይዞታል
፡፡ የነዋሪውን ተስፋ ለማሳደግ ለአፍታ ብልጭ ብሎ ወዲያው ድርግም የማለቱን አሰራር ተክኖበታል ፡፡ እንደ ቴሌና ውሃና ፍሳሽ ደጋፊዎች
አስተያየት ከሆነ በዚህ የብልጭ ድርግም ስልቱ በተለይም ቴሌቪዠናቸውን ያላስመዘገቡና ግብር ያልከፈሉ ነዋሪዎችን ንብረት ኃይል በማብዛት
ማፈንዳቱን ይቀጥላል ፡፡ መብራት ኃይል ስለ ቴሌቪዥን ግብር ምናገባው ? ለሚሉ አናዳጅ ጥያቄዎች የመ/ቤቱ ምላሽ ‹ ከባለ ድርሻ
አካላት ጋር እንዴት ተጣጥሞ መስራት እንደሚቻል ለማሳየት ነው › የሚል ሊሆን እንደሚችል ነው የተገመተው ፡፡
የኢቲቪ ነገር ከተነሳ የተሻለ ትኩረት ያገኙት
መዝናኛና ድራማ ፕሮግራሞች ሲተላለፉ ኃይል እያጠፋ ማበሳጨቱን እንደ ዋና የስራ ግብ ጋር አድርጎ በዕቅዱ ላይ ሳያስቀምጥ አይቀርም
፡፡ ይህ ደግሞ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር እንዴት ሆድና ጀርባ መሆን እንደሚቻል ማስተማሪያ መሆኑ ነው ፡፡ ይህ ድርጊት እየተከናወነ
የሚገኘው ደግሞ ሀገሪቱ ኃይል ለውጭ መሸጥ በጀመረችበት ግዜ መሆኑ ነው ፡፡ በዚሁ መሰረት የመ/ቤቱ መሪ ቃል ‹‹ ለውጭ አልጋ
ለውስጥ ቀጋ ›› እንዳይሆን ተሰግቷል ፡፡
3 .
በውሃና ፍሳሽ መ/ቤት ሽፋን የሚያገኘው የከተማው
ነዋሪ ከ50 ከመቶ በታች ነው ፡፡ መ/ቤቱ በመጪው ሶስት ዓመት ውስጥ ሽፋኑን መቶ ፐርሰንት እንደሚያደርሰው ደጋግሞ ተናግሯል ፡፡
እንግዲህ ቢጫውን ጀሪካን ይዞ በየሰፈሩ የሚንጦለጦለው ህዝብ ቁጥር አብላጫ አለው ማለት ነው ፡፡ እውነት ለመናገር ከታክሲና ዳቦ
ቤት ሰልፍ ይልቅ የቢጫ ጀሪካን ሰልፍ ውበት አለው ፡፡ በጩኀት ያልደነቆረና ብዙ ግዜ የመበተን አደጋ የሚያጋጥመው አይደለም ፡፡
ይህም አባ ቦኖ የተባለውን ውሃና ፍሳሽ የሚያኮራው ይመስላል ፡፡ ‹ ይህን ሁሉ ህዝብ ጠጥቶ እንዲያገሳና እንዲሸና የማደርገው እኔ
ነኝ › እንዲል ፡፡
ምናልባት ኮታው 100 ፐርሰንት እስኪደርስ ውሃና
ፍሳሽ የሚጎለው ነገር ቢጫውን ሰልፍ ህብረ ብሄራዊ የማድረግ ጉዳይ ነው ፡፡ አንድ ሃይማኖት አንድ ህዝብ የሚባለው መርህ እንደማያዋጣ
የመነገሩን ያህል በቢጫው ቀለም ብቻ ድምቀት መፍጠር አይቻልም ፡፡ በዚህም ምክንያት ይላሉ የቴሌና መብራት ደጋፊዎች መ/ቤቱ አረንጓዴና
ቀይ ጄሪካኖች ሰልፍ ውስጥ ገብተው ባንዲራ እንዲፈጥሩ እያለመ ነው ፡፡
ውሃ እንደ ቴሌ በጆሮ ፣ እንደ መብራት በአይን
የሚገባ አይደለም ፡፡ በአፍ እንጂ ፡፡ እና ጥራት ባጠረው ቁጥር በርካቶችን ላይ ታች ማሯሯጡና ለአጓጉል ሁኔታ መዳረጉ ግድ ነው
፡፡ ሰሞኑን ይህን እውነት የዘነጋው ውሃና ፍሳሽ የከተማውን የቧንቧ ውሃ እንደ ጠላ አደፍርሶ በየቤታችን ልኮታል ፡፡ ጉሽ ጠላ
ሊሆን የቀረው ከአፍ የሚተፋ ስብርባሪ እንጨቶችና ገለባዎች ብቻ አለመኖራቸው ነበር ፡፡ ነገሩ የተገለጠላቸው የአራዳ ልጆች ግን
ውሃና ፍሳሽ ‹‹ መውደድ ›› እና ‹‹ ቀሪቦ ›› ማዘጋጀት ጀምሯል እያሉ ነው ፡፡ ለማንኛውም ውሃና ፍሳሽ ገና ክረምት ሳይገባ
ክረምትን የሚያስታውስ ሆረር ውሃ በስፋት ማቅረቡን እንዳይቀጥል አስጨንቋል ፡፡
የደጋፊዎች እንካሰላንቲያና ተፎካካሪዎቹ ወደፊት
በስህተትም ሆነ በድፍረት ሊሄዱበት የሚችለው መንገድ የስጋት ቀጠና ውስጥ ይከታል ፡፡ እና ይህ ጠንካራ ዝግጅትና ትንቅንቅ ማንን
ወደ አሸናፊነት ማማ ያደርስ ይሆን ?
No comments:
Post a Comment