የታላቁ ገጣሚ ደበበ ሰይፉ የግጥም መጽሐፍ ‹ የብርሃን ፍቅር › ይሰኛል ። በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት አማካኝነት በ1980
ዓ.ም ለህትመት የበቃ ቢሆንም ዛሬም እንደ አዲስ ቢነበብ የማይጎረብጥ ይልቁንም በተክለቁመናው የሚመስጥ ስራ ነው ። ማለትም የዜማው
፣ የቃላት አጠቃቀሙ ፣ መልእክቱ ፣ የቤት አመታቱ እና የስንኝ አወራረዱ የአንባቢን ቀልብ ይስባል ።
አንባቢያንና የዘርፉ ባለሙያዎችም ተክለቁመናውን መሰረት በማድረግ ያሳደረባቸውን ስሜት በአስተያየትና በሂስ መልክ ሲጽፉ
ኖረዋል ። የማያረጅ ወይም ዘመን ተሻጋሪ ስራ ነውና ነገም ብዙ እንደሚባልለት አያጠራጥርም ።
ደበበ የመጽሐፉን ስያሜ ለምን « የብርሃን ፍቅር » እንዳለው ግን ምንም የተባለ ነገር የለም ። ምንም ያልተባለው ሚዛን
የሚደፋ ቁም ነገር ስለጠፋ አይደለም ። እንደሚመስለኝ ትችቶቹ ከተክለቁመናው ባሻገር ያለውን ገጽታ ማየት ባለመቻላቸው ነው ። ደበበ
እንደ ብዙ ገጣሚዎች አንደኛውን ትልቅ ወይም ገዢ ሃሳብ ያለው ግጥም አንስቶ ለመጽሐፍ ርዕስነት አላደረገም ፤ በውስጡ ‹ የብርሃን
ፍቅር › የሚል ግጥም የለምና ። የመጽሐፉን አጠቃላይ አንድምታ በመለካትም መዞ ያወጣው ነው ለማለት በቂ አይደለም ። ይልቁንም
ብርሃናዊ ሚስጢራትን በመስቀለኛ ሃሳቦች እንድንመረምራቸው የፈለገ ነው የሚመስለው ፤ ማለትም ርዕሰ ጉዳዩን ከቀጥታ እይታ ፣ ከተምሳሌት
፣ ከአሊጎሪ አውድና ከመሳሰሉት ፈትሸን እንድናይ ከተቻለም የተገለጸውን ብርሃን እንድንሞቅ ።
ደበበ በስሜት ብቻ ሳይሆን በእውቀትም የሚጽፍ ባለቅኔ በመሆኑ ይህንን አያስብም ብሎ መከራከር አይቻልም ። ጸሐፊ ተውኔትነቱና
ተመራማሪነቱም ይህን ሃሳብ ለመደገፍ እገዛ ያደርጋሉ ። ለምሳሌ ያህል ገጸባህሪ ፣ ሴራ ፣ መቼት እና ቃለ - ተውኔት የተባሉ ስነጽሑፋዊ
ቃላትን በመፍጠር ሙያዊ እገዛ አድርጓል ።
አጋጣሚ ሆኖ እነዚህ የአማርኛ ፍቺ ያገኙ ሙያዊ ቃላት ይጠቀሱለታል እንጂ በግጥሞቹ ውስጥም በርካታ ያልተባለላቸው ስልቶች
የሚገኙ ይመስለኛል ። አንደኛው ቃላትን በሚያዝናና መልኩ ደቅሎ መልእክትን የማስተላለፍ ጥበቡ ነው ።
ለምሳሌ ያህል ‹ ልጀቱ የዘመነችቱ › በተሰኘው ግጥሙ ውስጥ ዘማኒዋ ሱሪዋን - ሱርት ፣ ጫማዋን - ጭምት ፣ ቀበቶዋን
- ቅብትት ፣ ጃኬቷን - ጅክት ነው የምታደርገው ። እነዚህ ከስም ውስጥ የተደቀሉ መገለጫዋች የገጣሚውን ምናበ ሰፊነት ያስረዳሉ
- አንድም ቋንቋን ከመፍጠር አንድም ምስል አከሳሰትን ከማጉላት ።
እንደ እኔ እምነት የደበበ ሰይፉን ስራዎች በጥልቀት የመረመረ ባለሙያ አንድ ተጨማሪ የግጥም አይነት መታዘቡ አይቀርም ።
ከወል ፣ ሰንጎ መገን ፣ ቡሄ በሉ ፣ ሆያሆዬ እና ከመሳሰሉት ውጪ ማለቴ ነው ። ደበበ ልክ እንደ ፀጋዬ ገ/መድህን የራሱ ቀለማት
፣ አወቃቀርና ምት የሚጠቀም ባለቅኔ ይመስለኛል ። በተለይ ከግጥም አወራረዱ አንጻር የአንድ ቃል ዜማ / ሽግግር / ወይም የአንድ
ቃል መድፊያን በሚጥም መልኩ በብቸኝነት ተጠቃሚ ነው ።
ሰማይና ምድር ፣ ልጅነት ፣ በትን ያሻራህን ዘር ፣ ያቺን ሟች ቀን የተሰኙ ግጥሞች የዚህ አባባል ማሳያ ናቸው ። በ
‹ ሰማይና ምድር › ውስጥ
በጀርባዪ ተንጋልዬ
አውዬ
በቅጽበት የፈተልኩትን ለብሼ
ሞቆኝ
በእኔው አለም ነግሼ
ደልቶኝ
ከፅድቁ ገበታ ቀምሼ
ጣፍጦኝ
እያለ ይወርዳል ።
አውዬ
ሞቆኝ
ደልቶኝ
ጣፍጦኝ ... የሚሉ ነጠላ ቃላት ያነከሱ ይመስላሉ እንጂ ያለክራንች ነው የቆሙት - ለዛውም ጠብቀው ። በ ‹ ያቺን ሟች
ቀን › ውስጥም እንዲሁ ብቻቸውን ቁጭ ያሉት ትብነን !
... ትምከን ! ... የሚሉ ቃላት ርግማናዊ ግዝፈታቸው ከምላሰ
ጥቁር የሰፈር ሽማግሌዎች ወይም መጋረጃ ካገዘፋቸው ታዋቂ ጠንቋዮች የላቀ ነው ።
ይህ ሃይለኛ የአወራረድ ስልት በ ‹ ደበበ ቤት › ተይዞ መጠናት ያለበት ይመስለኛል ። ደበበ እንግዲህ እንዲህ ከምናውቀው
በላይ ብዙ ነው ። የብርሃን ፍቅር ሚስጢርነትም ሰፊ ፍቺ የሰነቀ ነው ። በመድብሉ ውስጥ 49 ግጥሞች ተካተዋል ። ከእነዚህ ውስጥ
24 ግጥሞች ብርሃንን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያነሳሉ ። 15 የሚደርሱ ግጥሞቹ ብርሃንን የሚያወሱት ፀሃይንና ጨረቃን መሳሪያ
በማድረግ ነው ። ማለትም ፀሃይና ጨረቃ በተፈላጊው ቦታና አውድ በግልጽ ተጠቅሰዋል ። ዳኢቴ ፣ አዴላንቃሞ ፣ እቴቴ ፣ ዛሬ እንኳን
፣ ብቻ መገኘትሽ ፣ ሀዘንሽ አመመኝ ፣ ይርጋለም እና የመሳሰሉትን ለአብነት መጠቃቀስ ይቻላል ።
ዘጠኝ በሚደርሱ ግጥሞች ደግሞ ‹ ብርሃን › የተወከለው ራሱን ችሎ ወይም ተምሳሌታዊ ሻማ በማብራት ነው ። ሰማይና ምድር
፣ ያቺ ቆንጂት ፣ ወለምታ ፣ ስንብት ፣ መንታ ነው ፍጥረትሽ እና የመሳሰሉት እዚህ ምድብ ወስጥ የሚወድቁ ናቸው ። ለአብነት ያህል
‹ ያቺ ቆንጂት › በሚለው ግጥም
‹ ጋሼ ላጫውትህ ትለኛለች
ያይኔን ብርሃን እየሞቀች › የሚል ተደጋጋሚ ስንኝ አለ ። እዚህ ላይ ብርሃን የተወከለው ፍቅርና መልካምነትን
ለመግለጽ ነው ።
በግጥም መድብሎች ላይ በተለይም አንድን ጉዳይ በስፋትና በጥልቀት መወቀር የተለመደ አይደለም ። ምክንያቱ የተለያየ ቢሆንም
በዋናነት ግን ገጣሚው ራሱ ሊያመነጫቸው በሚችለው ውስን ሀሳቦች ባለመርካቱ ሲሆን አልፎም ተርፎም አንባቢን አሰለቻለው ብሎ መፍራቱ
ነው ።
የብርሃን ፍቅር ብርሃናዊ ጨረሮቹን በተለያየ መልክ ሳይሰስት ነው የሚያደርሰን ። በርግጥ ለደበበ ሰይፉ ብርሃን ምንድነው
? ብርሃንን የሚያስረዳን የጨለማ ተቃርኗዊ ውጤት መሆኑን ነው ? ወይስ ከሳይንሳዊ ፣ አፈታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ዳራዎች ጋር የተያያዙ
ሃሳቦች አሉት ?
በ ‹ እሱ ነው - እሱ › ግጥሙ ላይ
እሱ ነው - እሱ
አይን ሳይኖረው
ለምን ብርሃን ኖረ የሚለው
እግር ሳይኖረው
ለምን መንገድ ኖረ የሚለው
እሱ ነው - እሱ
ከቀናቴ
ፀሃይቱን የሰረቀ
በመንገዴ
አሜከላ ያፀደቀ
እያለ የሚበሳጨው ለምንድነው ? ይህ ግጥም የምናወራበትን የ ‹ ብርሃን › ጉዳይ በሚገባ የሚገልጽ ነው ። ምክንያቱም የገጣሚውን
ያገባኛል ባይነት ደምቆ እንመለከታለን ። በተጠየቅ የሚሞግትባቸው ቃላዊ - ሃሳቦች ብርሃን ፣ መንገድ እና ፀሃይ ናቸው ። ሃሳቦቹን
በቤተዘመድ ጉባኤ አይን ካየናቸው አንድም ሶስትም ናቸው ። ገጣሚው በእውቀት ፣ እድገት እና እውነት ላይ የማይደራደር መሆኑ ይሰማናል
።
የደበበ ሰይፉ የብርሃን ትኩረት አንደኛው ምንጭነት ከህይወት ተምሳሌትነት የመቀዳቱ ጉዳይ ይመስላል ። ፈጣሪ በመጀመሪያ
ሰማይና ምድርን ከፈጠረ በኋላ የምድር ጨለማ የተሸነፈው በብርሃን ውልደት አማካኝነት ነው ። ፈጣሪ ብርሃንን የፈጠረው ለድምቀት
ብቻ አይደለም ። በብርሃን አማካኝነት ሃይል ተሞልቶ ለፕላኔታችን መቀጠል ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል ። የመሬት ሰርዓተ ምህዳር
የተመሰረተው በፀሃይ ከሚገኘው ብርሃን ነው ። ምክንያቱም አጽዋት የፀሃይ ብርሃንን ምግባቸውን ለማዘጋጀት ይጠቀሙበታል ። በሌላ
በኩል ሰውና እንስሣት ምግባቸውን ከእጽዋት ስለሚያገኙ ሰንሰለቱ የጠነከረ ነው ።
ደበበ ሰይፉ የብርሃን ሰረገላ የማይታየውን ወይም የማይደፈረውን ነገር ሁሉ እውነት ለማድረግ የሚያስችል መሳሪያ መሆኑን
የመረዳቱ ጉዳይም ርዕሰ ጉዳዩን አጥብቆ እንዲይዝ አግዞታል ።
‹ ምነዋ ባየሁኝ › በሚለው ግጥም
ምነው ባየሁኝ
መሬቷን ሰቅስቄ
ዛፉን ተራራውን ቤቷን ሰዋን ሁሉ
አንድ ላይ ጠቅልዬ
በብርሃን ፍጥነት በሚምዘገዘግ ዘንግ
ወዲያ አንጠልጥዬ
እያለ ቀስተ ዳመናንና ጨረቃን ሁሉ ቀላል መጫወቻ እንዲሆኑለት ይመኛል ። ይህ ምኞት መለኮታዊ መሻትም ጭምር ነው ። ምክንያቱም
መላዕክት የሚታዩት ብርሃን ባለበት ነው ። ብርሃንን ከመሬት ወደ ሰማይ ለመጓጓዝ እንደ ኤሌክትሮማግኔቲክ ሃይል ይጠቀሙበታል ።
ሰዋች ጸሎትና ምሰጣ ሲያከናውኑ እንደ ሻማ አይነት ብርሃናዊ ነገሮችን የሚጠቀሙትም መለኮታዊ ግንኙነት ለመፍጠር በማሰብ ነው ።
ሌላው የደበበ ግጥሞች መሰረታዊ መለያ ፀሃይንና ጨረቃን የብርሃን ምሶሶ ወይም ኪናዊ ምርኩዝ የማድረጋቸው ጉዳይ ነው ።
ከላይ እንደገለጽኩት 15 የሚደርሱ ግጥሞች ላይ ምርኩዝ ሆነው ቆመዋል ። አንባቢም በገባው መልኩ በዛቢያቸው እንዲሽከረከሩ ያደርጋቸዋል
። ገጣሚውም አልፎ አልፎ ለብቻ አንዳንዴ ደግሞ አንድ ላይ ያቀርባቸዋል ።
የጥንት ሰዋች የሁለቱን አብሮነት Duality በማለት ይገልጹታል ። ምክንያቱም
እንደ ብዙ ሀገሮች አፈታሪክ ከሆነ ፀሃይና ጨረቃ ባልና ሚስት ፣ ወንድምና እህት ወይም ወንድማማቾች ሆነው ይወከላሉ ። የስው ልጅ
ሲፈጠር ጀምሮ የሁለትዮሽ ውጤት ነው ። ሁለት እጅ ፣ ሁለት እግር ፣ ሁለት አይን ፣ ሁለት ጆሮ ወዘተ ያለው ። ይህ ጥምረት የፀሃይን
ግማሽ እና የጨረቃ ግማሽ ውህደትንም ይወስዳል ። ፀሃይ የቀኝ ጎን ስትሆን ጨረቃ የግራ ናት ፤ የቀኝ ጎን ወንድ የግራ ደግሞ ሴትነትን
ወካይ ነው ይላሉ ።
ደበበ ‹ አዴ ላንቃሞ › በተሰኘው ግጥም / አንድ የሲዳሞ ወንድ ነው / ተጠቃሹ ሰው ባሉት ሶስት ሚስቶችና ወንድ ሆኖ
በመፈጠሩ ሲደሰት እናያለን ። በደማቅ የጨረቃ ብርሃን ታጅቦ ለሶስቱም ሚስቶች ለአዳር እንደሚመጣ ትእዛዝ ሰጥቶ እንዴት ሽር ጉድ
እንደሚሉ በማሰብ ነው የሚስቀው ። ሊያድር የሚችለው ግን አንዷ ጋ ብቻ ነው ።
ብርማይቱ ጨረቃ
የብርሃን ጠበል አፍልቃ
ተፈጥሮን ስታጠምቃት
እንደገና ስትወልዳት
እያለ ነው ግጥሙ የሚዘልቀው ። እንደ ጨረቃዋ ልዩ ድምቀት ሶስቱ ሚስቶቹ ጋ በነበረው ሃያል ሙቀት እየረካ ነበር ። ምክንያቱም
ሶስቱም ‹ እኔ ጋ ነው የሚያደረው › በሚል ያሻቀበ ጉጉት ጎጆውን በፍላጎት ፍላት እንደሚያነዱት ስለማይጠረጠር ። ጨረቃዋና ሴቶቹ
በፈጠሩት ግለትም ሆነ ጾታዊ አንድነት የተመሳሰሉ ይመስላል ። በግጥሙ መሰረትም አዴ ላንቃሞ የወንድነቱን ፅድቅ አድናቂ ነውና ከጨረቃ
በትይዩ የቆመ የፀሃይ ወገን ሊሆን ይችላል ።
ደበበ በተለይም ‹ ገና በልጅነት › እና ‹ ዛሬ እንኳን › በተሰኙ ግጥሞቹ ውስጥ ፀሃይና ጨረቃን በጋራ እየገለጸ ተጠቅሞባቸዋል
። ፀሃይን ሲያነሳ ሃይልን ፣ ህይወትን ፣ ጤናን ፣ ጥልቅ የፍቅር ስሜት መገለጫነትን በመወከል ሲሆን ጨረቃን ሲገልጻት ሚስጢርን
፣ ብቸኝነትን ፣ ውበትን የመሳሰሉትን እንድናስብ በማመላከት ነው ። የደበበ ሰይፉ የብርሃን ፍቅር ብርሃን አስሶ ፣ በብርሃን ተማርኮ
ብርሃን የሚሰብክ ኪናዊ ዳመራ ነው ። ‹ የብርሃን ፍቅር › አንድ አይኑን ፀሃይ ሌላውን ጨረቃ አድርጎ ብርሃናማ መሃልየ የሚሰብክ
ኪናዊ ካህን ነው ።