እንዳንዶች እምነት ባለራዕዩ እንዳንዶች እምነት አምባገነኑ መለስ ያረፉት ነሀሴ 20/2012 ብራስልስ ውስጥ ነበር
- እነሆ አንዳንዶች ለሶስተኛው ሙት አመት ዝክር ሻማ እያበሩ ለፈጣሪ ሊፀልዩ እነሆ አንዳንዶች ርችት እየተኮሱ ፈጣሪን ሊያመሰግኑ
መንገድ ላይ ናቸው ።
አቶ መለስ ከቤተመንግስት ከተሰወሩበት - እስከተቀበሩበት እለት የነበረውን ፌስቡካዊ ልብ አንጠልጣይ ድራማ በማስታወስም
መዘከር ይቻላል ይለናል - ይህ ጽሁፍ ፡፡
አቶ መለስ በጠና ታመው ለ60 ቀናት ከቤተመንግስትና ከሀገሪቱ ሚዲያ ሲጠፉ ስውር የነበሩት ሁለት ትላልቅ ጎራዎች በአካል
ግዘፍ ነስተው መድረኩን ሲሞሉት ታየ ። በአዎንታዊና አሉታዊ ቃለተውኔቶች መፈነካከት - በምፀትና አሽሙር አርጩሜ መገራረፍ ደመቀ
። እልፈተ ዜናቸው ከተሰማ በኋላ 13 ቀናት ለሀዘን መግለጫነት ሲመደብ ሁለቱ ተጻራሪ ሀሳቦች በጥሩ ነው - መጥፎ ነው መልዕክት
እንካሰላንቲያ ተባብለዋል ፡፡ ግብዓተ መሬቱ ከተፈጸመ በኃላም በውርሳቸው ዙሪያ /legacy/ ተቃራኒ አስተያየቶች እየተደመጡ ቀጥለዋል፡፡
በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በአቶ መለስ ዜናዊ ዙሪያ ይበልጥ እየተከራከረ የመጣው መታመማቸው ከተሰማ
በኋላ ነበር ፡፡ አስቀድሞ መታመማቸው አለመገለጹ ተቃራኒው ክርክር እንዲጦዝ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል ማለት ይቻላል ፡፡ በተለይም
መቀመጫቸውን ውጭ ያደረጉ መገናኛ ብዙሐን የአቶ መለስን በጠና መታመም ደጋግመው ሲገልጹ በመንግስት በኩል ዝምታ ተመርጦ ነበር ፡፡
ይህ ዝምታ ከአቶ መለስ መሰወር ፣ ሊፈጠር ከሚችለው መደናገርና የፖለቲካ አለመረጋጋት ጋር የከፋ ውጤት ማስከተሉ የማይቀር መሆኑ
እያፈጠጠ ሲመጣ ግን መንግስት ማስተባበያ መስጠት ጀመረ ፡፡
የአቶ መለስ ደጋፊዎች ወደ ሰማይ የሚለቋቸው ወሬ ያቋቱ ሰላማዊ ፊኛዎች ከተቃራኒው ወገን በተተኮሰ የብእር ጥይት ተሸመልምለው
ቁልቁል ይወርዳሉ ፡፡ የአቶ መለስ ተቃዋሚዎች በመሪው ህይወትና ተግባር ላይ ያጠነጠኑ አደገኛ መረጃዎችን ለንባብ ሲለቁ ፣ ደጋፊዎች
የማርከሻ መድሃኒቶችን ፈጥነው ያሰራጫሉ ፡፡ ሌሎች ከመረጃው በታች በሚገኝ አስተያየት ላይ ይጠዛጠዛሉ ፡፡ አንዳንዴም ከደረጃ በታችም
ወርደው ይሰዳደባሉ ፡፡
“ አቶ መለስ በፍጥነት እየተሻላቸው ነው በቅርቡም ስራ ይጀምራሉ ! ” ለሚለው መልዕክት “ አቶ መለስ በጠና ታመዋል
፣ በቅርቡም ይሞታሉ ፡፡ የሚመጣው አስከሬናቸው ነው ” የሚል ተቃራኒ ምላሽ ይዘጋጃል ፡፡ እነዚህ ጥቅል ሀሳቦች በጣም እየቀጠኑ
“ መለስ ከሞተ ቆይቷል ! ” “ የጠላት ወሬ ነው ! መለስ አልሞቱም ! ” እስከሚለው ደረጃ አዳርሶ ነበር ፡፡
በርግጥም “ መለስ አልሞተም ! ” ለሚለው ወገን መከራከር የሚገባው መንግስት በየቀኑ መግለጫ አልሰጥም የሚል አቋም
በማራመዱ የአቶ መለስን መሞት አስቀድሞ በውስጡ የተቀበለው ህዝብ ሊበረከት ችሏል ፡፡ የሞቱ ዜናም ያልተነገረው ኢህአዴግ የተፈጠረበትን
ያለመረጋጋት ችግር ለማስተንፈስና ተኪ መሪዎችን ለመምረጥ ጊዜ መግዛት በመፈለጉ እንደሆነ የራሱን ግምት እስከመዘንዘር አድርሶታል
፡፡
በግራና ቀኝ የሚነሱ የፌስ ቡክ አስተያየቶች እየቆዩ ደግሞ አቶ መለስ መሞት የሚገባቸው ወይም ጤና የሚያስፈልጋቸው ከምን
አንጻር እንደሆነ ሁሉ መወያየት ጀምረው ነበር ፡፡ ተቃዋሚው ወገን አቶ መለስ ዜናዊ “ ዘረኛ ፣ ሀገር ሻጭ ፣ ከፋፋይ ፣ ገዳይና
አምባገነን በመሆኑ ሞት ይገባዋል ” ሲል ደጋፊው ወገን “ አቶ መለስ ዴሞክራት ፣ የልማት መሀንዲስ ፣ የአፍሪካ ድምጽ ፣ ለኢትዮጽያ
ጥቅም ያደሩና ባለራዕይ በመሆናቸው ረጅም ዕድሜና ጤና እንመኝላቸዋልን ” በማለት በአስተያየቱ ምላሽ ይሰጣል ፡፡
የአቶ መለስ የህመም መንስኤ በግልጽ አለመታወቁም በክርክሩ የሚወረወሩት ሻሞላዎች ይበልጥ የደመቀ የእሳት ብልጭታ እንዲፈጥሩ
ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ፡፡ መንግስትና ደጋፊው ወገን ቀላል ህመም ነው ለዚያውም በእረፍት መውሰድ ብቻ የሚወገድ ሲል ተቃራኒው ወገን
የአቶ መለስ ህመም ካንሰርና የጭንቅላት ዕጢ በመሆኑ ይሞታሉ የምንለው ለቀልድ አይደለም በማለት ይሟገት ነበር ፡፡
ቆይቶም ቢሆን ግን የአቶ መለስ መሞት በመንግስት ሳይቀር ተረጋገጠ ፡፡ መንግስት አሁንም ባወጣው የሀዘን መግለጫ ላይ
መሪው ለእልፈት ህይወት የተዳረጉት በኢንፌክሽን መሆኑን ነበር የገለጸው ፡፡ በምን አይነት ኤንፌክሽን ? - አይታወቅም ፡፡ ኢንፌክሽን
በራሱ ለሞት ያበቃል ? - አይታወቅም ፡፡ ለኢንፌክሽኑ መንስኤ የሆነው በሽታ ምንድነው ? - አይታወቅም ፡፡ በዚህ ደግሞ መጠዛጠዙ
ቀጠለ ፡፡
“
አቶ መለስ የሞቱት በማይድን ካንሰር ነው ”
“ ለዚህ የሚያበቃ ህመም አልነበረባቸውም ፣ የሞቱት በኢንፌክሽን ነው !”
“ የአቶ መለስ ጭንቅላት ፈነዳድቶ ነበር ! ”
“ ይህ የውሸታሞችና የጠላቶች ወሬ ነው ! ”
“ የአቶ መለስ አካል ባይበላሽ ኖሮ እንደ አቡነ ጳውሎስ መስታወት ውስጥ ሆኖ እናየው ነበር ”
“ ይህን ማድረግ - አለማድረግ የቤተሰብና የመንግስት ጉዳይ ነው ”
አቶ መለስ ለህክምና የቆዩባቸው 60 ቀናት ለኢትዮጵያዊን በግራም ሆነ በቀኝ አስጨናቂ ፣ አጓጊ ፣ አከራካሪና አጨቃጫቂ
ምዕራፍ ነበሩ ማለት ይቻላል ፡፡ ሞታቸው ተረጋግጦ አስከሬናቸው አዲስ አበባ ከገባበት ምሽት ጀምሮ ለ13 ቀናት የቆየው የሀዘንና
የማስተዛዘኛ ጊዜያት ደግሞ እንደ ሁለተኛ ምዕራፍ ሊታይ የሚችል ነው ፡፡
በዚህ ምዕራፍ ይነሱ የነበሩ ክርክሮችና ሙግቶች ይበልጥ
ጠንካራ ነበሩ ፡፡ ማህበራዊ ገጾች ያስተናግዱት የነበረው ተቃራኒ ሀሳብ በግጥም ፣ በእንጉርጉሮ ፣ በፎቶ ፣ በስዕል ፣ በጠንካራ
መፈክርና አባባሎች የታጀበ ነው ፡፡ አይተናቸው የማናውቃቸውን የአቶ መለስ ዜናዊ ልዩ ልዩ ፎቶዎች (ከልጅነት እስከ እውቀት) ሁለቱም
ወገኖች ለራሳቸው መልዕክት ማስተላለፊያነት ተጠቅመውበታል ፡፡ ደጋፊው ወገን የአቶ መለስን ጠንካራና ልማታዊ ንግግሮች እያጣቀሰ
ሀዘኑን ገልጿል ፡፡ ተቃዋሚው ወገን በበኩሉ የአቶ መለስን መጥፎ ንግግሮች በማስረጃነት እያስደገፈ የሞቱን ተገቢነት ሲያስረዳ ቆይቷል
፡፡
የአቶ መለስን አስክሬን ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝቶ የተቀበለው በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪ ሀዘኑን በእንባ እየገለጸ
መፈክር ያሰማ ነበር ፡፡ ያቺ መፈክር በእለቱ የተወለደች መስላ ለበርካታ ግዜያት በመገናኛ ብዙሐንም በፌስ ቡክም ጠንካራ ተጉዛለች
፡፡ ‹‹ መለስ አልሞተም ! ጀግና አይሞትም ! ›› የምትል ፡፡ ተቃራኒው ቡድን ለዚህ አባባል ምላሽ የሰጠው በግጥም ነበር ፡፡
“
በአመለካከት መታሰር ፣ በዘር መገፋት ካልቀረ
የአድርባይነት ቁራኛ የዘረኝነት ደዌ ካልሻረ
የይስሙላ ፍርድ ቤት የግብር ይውጣ ምርጫ
የአንድ ብሄር ፖለቲካ የአንድ ግለሰብ ብልጫ
ይህ ሁሉ አሳር እንደ አዲስማ ካለ
እውነት ብላችኋል መለስ አልሞተም አለ”
ደጋፊዎች በሀዘን ድባብ ውስጥ ቢሆኑም ውስጣቸውን በደስታ ሊያነቃቃና የአቶ መለስን የሚሊኒየም ታላቅነት ሊያበስር የሚችል
መፈክር ፈጥረዋል ፡፡ “ አባይን የደፈረ ብቸኛ ጀግና መሪ ! ” የኢትዮጽያ መሪዎች ከጥንት ጀምሮ አባይን ለመገደብ የጋለ ፍላጎት
የነበራቸው ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ከሀሳባቸው ጋር መገናኘት አልቻሉም ፡፡ ይህም ከመለስ ትልቅ ተግባራት ዋነኛው ሊሆን ግድ
ብሏል ፡፡ ተቃራኒው ቡድን ለዚህ ጠንካራ እውነትም ቢሆን ምላሽ ከመስጠት አልተቆጠበም ፡፡
“ የማይደፈር ደፈረ ግን ሞተ ተቀበረ
21 ዓመት ሙሉ ተደነሰ ተጨፈረ
ዛሬ ግን ያ ቀረ ሀጢያት ተደመረ
ተባዛ ተከመረ በሰፈሩት መሰፈር መች ቀረ ” በማለት አቀንቅኗል ፡፡
“ አባይን ደፈረ ብለን ሳንጨርሰው
ሞት ደፈረና ህዝቡን ጉድ አሰኘው ” የሚል ሽሙጥም በተመሳሳይ
መልኩ ተነቧል ፡፡ ደጋፊው ወገን ለአቶ መለስ ነፍስም በጎ ነገር የተመኘው በስነ ግጥም ነበር ፡፡
“ ክቡር ይሁን ለእሱ አምላክ ይቀበለው
ገነት ለእሱ ትሁን አፈሩ ይቅለለው ”
ይህችን የመልካም ምኞት ደብዳቤ ፌስ ቡክ ላይ የተመለከተ ሌላ ተቃራኒ ወገን
“ እኔ ብቻ ልግዛ ነውና ነገሩ
ሰማይ ቤትም ሄደው እንዳያስቸግሩ ” በማለት ምጸታዊ መልዕክት ለማስተላለፍ
ሞክሯል ፡፡
የግራው ቡድን መለስ ዜናዊን የሚገልጸው ታላቅና ጀግና መሪ በሚል ነው ፡፡ በተለይም “ ጀግና ! ” የምትለው ቃል ለጦር ሜዳውም ለቢሮ ሥራውም ውክልናዋ ደማቅ በመሆኑ ከአፍ
ላይ እንድትጠፋ አይፈልግም ፡፡ አንዱ አቀንቃኝ በስድስት ስንኞች ፣ የስንኞቹ የመጀመሪያ ፊደላት ወደታች ሲነበብ መለስ ዜናዊ የሚል ንባብ እንዲሰጥ አድርጎ
ጀግንነቱን እንደሚከተለው ገለጸው ፡፡
መቼም
የማንረሳህ ጀግናው መሪያችን
ለመኖር
ሳትጓጓ ስትሮጥ ለሀገራችን
ስንቱን
መከራ አልፈህ ስትቆም ከጎናችን
ዜናው
አለያየን ተደፋ አንገታችን
ናፍቆታችን
ከስሞ ጠቆረ ፊታችን
ዊ ላቭ
ዩ ብለን አነባን ከውስጣችን
የቀኙ ቡድን የግጥሙን መልዕክት ካጣጠመ በኋላ አቶ መለስ በፍጹም “ ጀግና ” የሚባሉበት መንገድ ትክክል አይደለም በሚል
መንፈስ ለግጥሙ ምላሽ አዘጋጀ ፡፡ እንደላይኛው ግጥም ለየት ለማድረግ ይመስላል ተራኪው ራሳቸው ‹ አቶ መለስ › እንዲሆኑ አድርጓል
፡፡
“ ጥይት በማይበሳው መስተዋት ተከብቤ
በመድፍ ፣ በመትረየስ ፣ በስናይፐር ታጅቤ
ስወጣ ስገባ የምታውቁኝ ሁሉ
ፈሪ ለእናቱ ነኝ እኔን ጀግና አትበሉ
ጀግና ቴዎድሮስ ነው የሞተው ለቃሉ ”
የሀዘኑ ጉዳይም በእጅጉ አነጋገሪ ሆኖ አልፏል ፡፡ ምናልባትም ለ13 ቀናት ያህል የተለቀሰለት የዓለም መሪ መኖሩ ያጠራጥራል
፡፡ ህዝቡ ቤተመንግስት ድረስ በመጓዝ አልቅሷል ፡፡ ያው ‹ ከልቡ ነው › ፣ ‹ ለይምሰል ነው › የሚሉ እሰጥ አገባዎች እንደተጠበቁ
ሆነው ፡፡ ሁሉም ቀበሌዎች ድንኳን ጥለው ተቀምጠዋል ፡፡ ደጋፊዎች ጥቁር እንዲለብሱ ተደርጓል ፡፡ ደረት መምታት ፣ ፊት መንጨት
፣ ጥቁር መልበስ ፣ አርባና ሰማንያ ጎጂ ባህል ናቸው በማለት መንግስት ለእድሮች ሲያስተምር ቆይቶ ለራሱ ሲሆን ድራማውን በለቅሶ
መቀጠሉ ነው ያስገረመን ብለዋል ብዙዎች ፡፡
“
እረ ይሄ ለቅሶ አለቅጥ ሆነ ? ይብቃ ! ” ተቃዋሚው አስተያየቱን መስጠቱን ቀጠለ
“
ደግሞ በዚህ ቀናችሁ ?! ለመሪያችን ሳይደክመን እናልቅሳለን ! ” ደጋፊው መለሰ
“ ክፉ ቁራኛ ሲሄድ አስለቅሶ ነው - የልምዣት ” ተቃዋሚው ምጸቱን አጠናከረ
በርግጥ ደጋፊዎች ይህን አርበ ሰፊ ለቅሶ ለሀዘንም ለፖለቲካው ድጋፍ ማግኛም ተጠቅመውበታል ፡፡ የጎንደሩ ፣ የጎጃሙ
፣ የጉምዙ ፣ የወላይታው የአለቃቀስ ስርዓትን እግረ መንገድ በየቀኑ ከሚያቀርብልን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መረዳት ችለን ነበር ፡፡
ሀዘንተኞች ለሪፖርተሮች ሲሰጡ የነበሩ አስተያየቶችም አሳዛኝም አሳፋሪም ነበር ማለት ይቻላል ፡፡ አቶ መለስን ከታሪካቸው ፣ ከማንነታቸውና
ከራዕያቸው አንጻር የሚገልጹበት መንገድ ያስተክዛል ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ‹ እኔ ሞቼ እሳቸው የሚነሱ ቢሆን ነፍሴን ለመስጠት አልራራም
› የሚሉ ሰዎች በርክተው ነበር ፡፡ ድንገት ፈጣሪ ‹ ና በል እንግዲህ ሞት ተፈርዶብኃል ! › ብሎ ቢናገር የእነዚህ ሰዎች ሽንትና
ላብ ክረምትን ባስናቀ ነበር ፡፡ ያም
ሆነ ይህ ሀገር በየተራ አልቅሷል ወይም እንዲያለቅስ የህዝብ ግንኙነት
ስራ ተሰርቷል ፡፡ ይህን መሰረት በማድረግም ደጋፊው ቡድን ጎል ክልል ሃይለኛ ቅጣት ምት እንደሚከተለው ሰነዘረ
“ መለስ ጨካኝ ነው ፣ አምባገነን ነው ይሉ የነበሩ ዛሬ ሀገር ሙሉ ሲያለቅስለት ምን ያህል የሰው መውደድ ያለውና ታላቅ
መሆኑን ሊገነዘቡት ይገባል ”
ተቃራኒው የመልስ ምቱን ያዘጋጀው ለሞተ ሰው ማዘንና ማልቀስ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴት ከመሆኑ አንጻር የመሆኑን ጉዳይ
ነበር ፡፡ እነሆ በቴስታ የወጣው ግጥማዊው መልስ ፣
“ … ክንፈር
የነከሰው
ከንፈር የሚመጠው
የነገ ተረኛ ነፍስ ይማር የሚለው
አንድም ለራሱ ነው
አንድም ለሟቹ ነው ”
በርግጥ በለቅሶ ወቅት የኢትዮጵያን ህዝብ ማንነት መበየን አስቸጋሪ ሆኖ ታይቷል ፡፡ በአቶ መለስ እና በመንግስታቸው
አገዛዝ ሲማረርና ሲያልቀስ የነበረው ሁሉ በሞታቸው ጥልቅ ሀዘኑን ገልጿል ፡፡ ይህ ድርጊት ደጋፊውንም ተቃዋሚውንም ግራ ያጋባ ነበር
፡፡ ሁለቱም ወገኖች እንዴት ? ብለው በግርምት ተመሳሳይ ጥያቄ አንስተዋል ፡፡ የተለያዩት ውጤቱ ላይ ነበር ፡፡ ደጋፊው “ ያስደስታል ! ›› ሲል ተቃዋሚው “ የማይታመን ነው ” ሲል ቆይቷል ፡፡ ለዚህም ይመስላል ደጋፊው
“ እውነትም የኢትዮጵያ ህዝብ ወርቅ ህዝብ ነው ፡፡ በጠ/ሚ/ሩ ሞት ታላቅነቱን አስመስክሯል ” በማለት ፍንድቅድቅ የሚለውን
ሀሳብ የወረወረው ፡፡ በዚህ ብቻ አላበቁም “ ሀገር ሙሉ ያለቀሰው ለጠ/ሚ/ር መለስ ከፍተኛ ፍቅር ስላለው ነው ” የሚል መልዕክትም
አስተላልፈዋል ፡፡
ለነዚህ ሁለት መሰረታዊ አባባሎች ከተቃራኒው ወገን የተወረወሩ ሁለት አጸፋዎችን እንመለክት ፡፡ አንደኛው “ ሰሞኑን
እያየን ያለነው አድርባይነት ፣ አስመሳይነት ፣ ከሃዲነት ፣ አሸቃባጭነት እና ውሸታምነት የመለስ ዜናዊ የ21 ዓመታት አገዛዝ ፍሬዎች
ናቸው ” የሚል ነው ፡፡ ሁለተኛው ምላሽ ‹ ህዝብ ማለት › በሚል ርዕስ የተገጠመ ረጅም ግጥም ነው ፡፡ የህዝቡን አደናጋሪ መልክና
በፈለገው ጊዜ የፈለገውን የመሆን ችሎታ ይገልጻል ፡፡ ጥቂቱን ቆንጥረን እናንብብ ፡፡
ይህ ህዝብ ማለት …
አንዳንዴ ግጥም ነው… አንዳንዴ ቅኔ
አንዳንዴ ንስር ነው… አንዳንዴ ዋኔ
ይህ ህዝብ ማለት መመዘኛም የለው
መለኪያው ግዜ ነው እርቦና መስፈሪያው
ሞላ ሲሉት ስፍሩ የልኩ ጢምታ
የለም አይገኝም በሚዛን ገበታ
ይሄ ህዝብ ማለት …
በበረደው በርዶ በሞቀበት ሞቆ
ሲመርም ጉፍንን ነው ልክ እንደመቅመቆ
ይህ ህዝብ ማለት ፍቺ የለው አቻ
እንዲሉ ነገር ነው ስልቻ ቀልቀሎ ፣ ቀልቀሎ ስልቻ
የሀዘኑን ስርዓት ስናነሳ በሁለቱም ወገኖች ይታይ የነበረውን ጫፍ የደረሰ አመለካከት መጥቀስ ተገቢ ይሆናል ፡፡ ደጋፊው ወገን
ከመጀመሪያው ጀምሮ ሀገሪቱ ታላቅና ጀግና መሪ በማጣቷ ሀዘኑ ሳይገደብ መከናወን ይኖርበታል ይል ነበር ፡፡ ምን ያህል እንደሚሄድ
ባላውቅም ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ እንደሚባለው ዓይነት ። ተቃራኒው ወገን አቶ መለስ እንደ ጀግናም ሆነ እንደ ሀገር መሪ
በወግ ማዕረግ መቀበር ይኖርባቸዋል ፣ ይህንም የሚደግፍ ህጋዊ የሀዘን ስርዓት አለ ፡፡ ከዚህ ውጪ መሄዱ ግን ከባህል ፣ ሃይማኖት
፣ ኢኮኖሚና ፖለቲካ አንጻር ትክክል አይደለም ባይ ነበር ፡፡ ይህን ሀሳብም ሲወረወሩ ከነበሩ አስተያየቶች መረዳት ይቻላል ፡፡
ደጋፊው ፤
“
ዝቅ ይበል ባንዲራው ከክብሩ ይወርዳል
ሀገር የሚመራ ታላቅ ጀግና ወድቋል
ይታወጃል ሀዘን ጥቁር ይለበሳል
መራር ሀዘን ገዝፎ አርምም ይሆናል ”
በተግባር ተተርጉሞ የታየው የሀዘን ስርዓትም ከግጥም በላይ ነበር ፡፡ ይህ የፈጠው ብሽቀትም ይመስላል የመረረ አጸፋ
የፈጠረው ፡፡
“
ከኛ ገለል በሉ አትተራመሱ
ጥቁር ማቃችሁን ዘላለም ልበሱ
ድንኳን ውስጥ ሆናችሁ ሙት አመት ደግሱ
ነገም አተራማሽ መርጣችሁ አንግሱ … ››
በማንኛችንም ህይወት ውስጥ የተለዩ አጋጣሚዎችና ግጥምጥሞሽ ይፈጠራሉ ፡፡ እነዚህ ግጥምጥሞሽ ደግሞ ተቀባይነት ይኑራቸውም
አይኑራቸው የራሳቸው የሆነ የተጽእኖ አሻራ ይፈጥራሉ ፡፡ ከአቶ መለስ የመጨረሻ የህይወት ጠርዝ ላይ ድንገት ጎልቶ የወጣው አበበ
ገላው የተባለው ጋዜጠኛ ድርጊት ነበር ፡፡ በትልቅ ስብሰባ ላይ “ Meles Zenawi is dictator ! Free
Eskinder Nega and all political prisoners . You are commiting crimes against
humanity ! Don’t talk about food with out freedom… ” በማለት ተቃውሞውን በሚያስፈራ ድምጽ ገለጸ ፡፡
የጋዜጠኛው ድርጊት ትክክል
ነው - አይደለም የሚሉ ሀሳቦች በወቅቱ በስፋት ተንሸራሽረዋል ፡፡ ከዚህ አጋጣሚ ጥቂት ቆይቶ የአቶ መለስ መታመም ተሰማ ፡፡ ተቃራኒው
ወገን ህመሙን ከአበበ ተቃውሞ ጋር አገናኘው ፡፡ “ አቶ መለስ የታመሙት በደረሰባቸው ድንጋጤና ሀፍረት ነው ” ተባለ ፡፡ ሌላኛው
ወገን “ ስንት መከራና ችግር ያሳለፈ መሪ በአንድ ምንነቱ በማይታወቅ
ሰው ልፍለፋ የሚታመምበት ምክንያት ቀልድ ነው ” በማለት ትችቱን አጣጣለ ፡፡
ተቃዋሚዎቹ ግን ይህን አጋጣሚ በቀላሉ ማሳለፍ አልፈለጉም ፡፡ አቶ መለስ በዓለም ፊት መሰደባቸውን እንደ ትልቅ ድል
ተመለከቱት ፡፡ ጋዜጠኛውንም እንደ ጀግና መቁጠር ጀመሩ ፡፡ በነካ እጅህ ሚኒስትር እከሌን ስደብልን ፣ ቀንደኛውን እንቶኔ አሸማቅልን
እስከ ማለት ተደረሰ ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ አቶ መለስ መሞታቸው ደግሞ ጉዳዩን አጦዘው፡፡
“አበበ ገላው መለስን በላው ! ” የሚል ግጥምም ተደረሰ
ደጋፊው ወገን አቶ መለስ የሞቱት በህመምና በእረፍት ማጣት እንጂ በአበበ ገላው ድንገተኛ ድርጊት አለመሆኑን ይረዳል
፡፡ በርግጥ አንድ የተከበረ መሪ በአንድ ጋዜጠኛ መሰደቡ አብሽቋቸዋል ፡፡ ለዚህም ይመስላል
“ አበበ ገላው ማለት የአእምሮ በሽታ ያለበት ንክ ሰው ነው ! ” በማለት የጉዳዩን ደረጃ በማጣጣያ ምላሽ የሰጡት ፡፡
ተቃዋሚው ወገን ለአበበ ምስጋና ለደጋፊው ወገን ደግሞ ምጸታዊ አጸፋውን ማሰማቱን ቀጠለ
“ አበበ ገላው እግዚአብሔር ይስጥህ አንተ ለኛ ጎልያድን እንደጣላው እንደ ዳዊት ነህ ! ” መቼም ይህ አባባል ስሜታዊ
እና የተጋነነ መሆኑ ግልጽ ነው ፡፡ ይሁን እንጂ ድክመቱ ላይ ተንተርሶ እንኳ የመልስ ምት አልተሰጠም - ከደጋፊው ወገን ፡፡
በርግጥ ደጋፊው ወገን አልፎ አልፎ በቸልታ ወይም በንቀት እያየ ያለ መልስ የሚያልፋቸው ጉዳዮች ነበሩ ፡፡ ይህም “
ለሁሉም መልስ መስጠት አንችልም ከሚለው ድርጅታዊ መርህ ተቆርሶ የተወሰደ ሊሆን ይችላል ፡፡ አንዳንዴ ግን ይህ ነገር መልስ ቢኖረው
እንዴት ጥሩ ነበር ? እንዴትስ መልስ ሊሰጠው ይችላል ? ” የሚል ጥያቄ ያጭራል ፡፡
አንድ አብነት ብቻ ላንሳ ፡፡ ተቃዋሚው ወገን ያዘጋጀው ቅጽ ነው ፡፡ ርዕሱ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የአለቃቀስ ግምገማ
ይላል ፡፡ ወረድ ብሎ
የአልቃሹ ስም ------
ቀበሌ
------
ያለቀሰበት ቋንቋ ------
እንባው የመጣበት ሰዓት ----
የእንባው መጠን ፤ ጎርፍ -- ካፊያ --- ደረቅ
የለበሰው ልብስ ቀለም ፤ ጥቁር --ነጭ -- ሌላ ቀለም
በደቂቃ ምን ያህል አለቀሰ -- የሚሉ መጠይቆችን ይዟል ፡፡
ከነዚህ መረጃዎች ወረድ ብሎ “ ለቢሮ ስራ ብቻ ” በሚል ንዑስ ርዕስ ግለሰቡ በአጠቃላይ የሚፈረጅበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡ በገምጋሚው ይሞላ ዘንድም አራት አማራጮች
ተቀምጠዋል፡፡
ግለሰቡ ፤
አስመሳይ ? ከልቡ ነው ? ያጠራጥራል ? ጭራሽ አላለቀሰም ? የሚሉ ።
ይህ ቅጽ የቢሮ አካሄድን ተከትሎ ተሰራ እንጂ ተራ ቅጽ አይደለም ፡፡ ምጸታዊ ነው ፡፡ ህዝቡ እያለቀሰ ያለው በማይታዩ
ደንቦች እንጂ በውዴታ አይደለም የሚል ፡፡ ፈጠራውም የሚናቅ አይደለም ፡፡ ይህ ደግሞ ሀገሬው በሙሉ ማልቀሱ መለስን የመውደዱ ማሳያ
ነው ከሚሉት ደጋፊዎች ሀሳብ ጋር የሚቃረን ነው ፡፡ ታዲያ ምላሽ ለምን ተነፈገው ? ስዕላዊ በሆነ መልኩ ምላሽ ሊያገኝ ቢችልስ
ምን ያህል እንደመም ነበር ? እንደ እኔ እንደ እኔ በጦፈ ክርክር ውስጥ ምላሽ ማጣት ያስቆጫል ፡፡
በሀዘኑ ወቅት ሀገሬውና ማህበራዊ ገጾች ለምን የተለያየ ገጽታ ተላበሱ የሚለውን ጥያቄ በግሌ ጠይቄያለሁ ፡፡ ህዝቡ ጸሃይና
ዝናብ ሳይበግረው በረጅም ሰልፍ ውስጥ አልፎ ለቅሶ ደርሷል ፡፡ በየቀበሌው ድንኳን እየተገኘ አንብቷል ፡፡ በመገናኛ
ብዙሐን የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጿል ፡፡ የመለስን ራዕይ ለማስቀጠል ቃል ገብቷል ፣ በስሜት ገስሏል፡፡ ፎክሯል ፡፡
በማህበራዊ ገጾች መስኮት ብቅ ሲል ግን ሁለት መልክ ይዞ ነው ፡፡ ያ የመረረ ሀዘኑ ይለዝባል ፡፡ የሚወክለው ሀዘንና
ውዳሴ ብቻ ነው ብለው ሲያስቡ የተደሰተ ፊትና በትችት የተሰላ ምላስ
አብቅሎ ይታያል ፡፡
“ የምስራች ! መለስ ሞተ ! ”
“ የወርቅ ጥላ ለማን ታቦት ላግባ ! ”
“ የኢትዮጵያን ህዝብ እንጂ ፈጣሪን ማታለል አይቻልም ! ”
እጅግ የከረሩ ሀሳቦች ይወረወራሉ ፡፡ ከመቼው ተቀያየረ ? ነው የኢትዮጵያ ህዝብ “ ነገርን ” በፈረቃ ነው የሚሰራው
? በገሃዱ ሀገራችን የታየው የሀዘን ድባብ ለምን በፌስ ቡክም ዓለም ተጽእኖ መፍጠር አልቻለም ? ብሎ መጠየቅ ግድ ያስብላል - ጥናት ይፈልጋል ።
ቀጥሎ የትችቱንና የመጠዛጠዙን ትልቅ ደረጃ ሊያሳዩ የሚችሉ ክርክሮችን እንመልከት ፡፡ ደጋፊው ወገን የበዛውን ወቀሳ
ለማስታመም የሚከተለውን ጽፏል ፡፡
“ በህይወት የሌለን ሰው መውቀስ ወይም በህይወት የሌለ ሰው ላይ በደስታ መፎከር ጀንግንነት አይደለም ፤ ሙት አይወቀሰም ፡፡ እንደ ወግ ባህላችን የጠቅላይ ሚኒስትሩን እና
የጳጳሱን ነፍስ ይማር እንበል ”
ከተቃዋሚው ወገን እንደተለመደው ምላሹ የተላከው በስነ ግጥም ነበር
“ አባ ታጠቅ ካሳን ስትረግሙ ከርማችሁ
እምዬ ሚኒሊክን ስትወቅሱ ኖራችሁ
ተፈሪ መኮንን ጨቋኝ ነው ብላችሁ
ዛሬ ቀኑ ደርሶ ዕጣ ሲደርሳችሁ
ሙት አይወቀስም አትበሉን እባካችሁ ”
ደጋፊው ወገን አቶ መለስን በክፋት የሚመነዝረው ፣ ታላቅነታቸውን የሚያጣጥለው ፣ በጥልቅ የሀዘን ወጀብ መመታት ሲገባው
የደስታና የፌሽታ ሻምፓኝ እየከፈተ የሚገኘው ከሀገር ውጭ የሚገኘው ኢትዮጽያዊ ነው ብሎ ያምናል ፡፡ የኢትዮጵያን ዕድገትና ልማት
የማይመኘው ይህ ቡድን የደርግ ኢሰፓ ርዝራዥ ወይም ስልጣንን በአቋራጭ ለማግኘት የሚቋምጥ ፊውዳል ሊሆን ይችላል ፡፡ እናም አቶ
መለስና ስርዓቱን ሊያጥላሉ የሚችሉ ነገሮችን ሁሉ መረን በወጣ መንገድ ይለጥፋል ባይ ነው ፡፡
ለምሳሌ ያህል ፤
“ መለስ ዜናዊ ታላቅ ጀግና መሪ ነው ! ” የሚለውን ቅቡልና ያገኘ አባባል ጠምዝዞ “ መለስ ዜናዊ የራሱን ሀገር ህዝብ
ስለገደለ ብቻ ጀግና ከተባለ እኔ አዶልፍ ሂትለርን ምን ልትሉኝ ነው ! ” የሚል ምጸት ያቀርባል ፡፡ አቶ መለስ ለአፍሪካ ህዝቦች
ታላቅ ተግባር ማከናወናቸውን ዓለም መስክሯል ፡፡ ከዚህ በመነሳትም
“ መለስ የአፍሪካ መሪ ነበር ! ” ለተባለው ታላቅ አባባል “ መለስን የአፍሪካ አባት ያላችሁ አሳፋሪ ካድሬዎች ማንዴላ
ሰምቶ እንዳይስቅባችሁ ” የሚል ማጣጣያ ሲያቀርብ ቆይቷል ፡፡
እንደ ብዙ ደጋፊዎች እምነት ሀገር ውስጥ ያለው ዜጋ ተመሳሳይ ስሜቱንና ቁጭቱን ሀዘን በተላበሰ መልኩ ገልጿል ፡፡ በመሆኑም
በማህበራዊ ገጾች ለተከፈተው ጥቃት ዋነኛ ተዋናይ ሊሆን አይችልም ፡፡ ምናልባት አስተዋጽኦው እንዴት ይመዘናል ? ከተባለ አለ ተባለውን
ከማራገብና ከሟሟቅ የሚዘል አይሆንም ፡፡ ለዚህም ይመስላል ከደጋፊው ቡድን
“ ይድረስ በየሀገሩ ለተበተኑ ኢትዮጵያዊያን ” በሚል ርዕስ ጠንከር ያለ ደብዳቤ የተሰራጨው ፡፡ እንመልክተው ፡፡
“ ጠ/ሚኒስትሩ ቢሞቱብን ስብዓዊም ኢትዮጵያዊም ሀዘን አዘንን ፡፡ በውጭ ያላችሁ የስጋችን ቁራጭ ፣ የአጥንታችን ፍላጭ
የሆናችሁ አንዳንድ ወገኖቻችን ‹ የፈንጠዝያ ቀን ይሁንላችሁ ! › ብላችሁ መከራችሁን ፡፡ እኛ እኮ ባህል ፣ ወግ ፣ ኃይማኖትና ስነ ምግባር ያለን ህዝቦች ነን ፡፡ መቼ
መሳቅ ፣ መቼ ማልቀስ እንዳለብን እናውቃለን ፡፡
ዴሞክራሲ ማለት መሪን መስደብና ማጓጠጥ ፣ ዴሞክራሲ ማለት ሁልጊዜም ተቃዋሚ መሆን ፣ ዴሞክራሲ ማለት ሀገርን የወከለን
መሪ በሌሎች ሀገሮች ፊት ማዋረድ መሆኑን ያስተማራችሁትን ትምህርት የገባን ዕለት ፡፡ ያኔ እንስቃለን ፡፡
ኢትዮጵያዊያን ማለት እኮ ዜግነት ለመቀየር እየተጣባበቅን ያለን አይደለንም ፡፡ ኢትዮጵያዊያን ማለት በሆስፒታል እጦት
በየጫካው የምንወለድ ፣ ሰው በአየር ሲጓዝ እኛ በመንገድ እጦት ጋራ ሸንተረሩን ስንቧጥጥ የምንኖር ፣ ሀመሮች ፣ ቡርጂዎች ፣ ኮንሶዎች
፣ ደራሼዎች ፣ ሱርማዎች ፣ ቤንሻንጉሎች ፣ አፋሮች … ስሙን እንኳ ሰምታችሁት በማታውቁት ገጠራማ አካባቢ የምንኖር ብሄረሰቦች
ነን ፡፡
አንደብቃችሁም ፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን ሰው ሲሞት ስቀን የምናውቀው ቴአትር ቤት ውስጥ ብቻ ነው ፡፡ መለስ የሞተ ዕለት
ፈንጥዙ አላችሁን ? የቱ መለስ ? እሱ እኮ በአግባቡ ሳናነበው የተዘጋ መጽሀፍ ፣ ብዙ ነገሮች ከልለውን በቅጡ ሳናየው ያመለጠን
ድንቅ ክስተት ነው…. ”
በአጠቃላይ በአቶ መለስ ስብዓዊም ሆነ ፖለቲካዊ ሰውነት ዙሪያ ያልተነሳ ጉዳይ አልነበረም ፡፡ አንዱ አምባገነን ሲል
ሌላው ዲሞክራት… እብሪተኛ ለሚላቸው የድሃ አባት … አገር ሻጭ ለሚላቸው ባለራዕይ … ዘረኛ ለሚላቸው የአፍሪካ ልጅ የሚሉ ማስተባበያዎች
ተከትሏቸዋል ፡፡
በርግጥም የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልክ ሁለት እንደነበር የሚያሳዩ
ማስረጃዎች በርካታ ናቸው ፡፡ ከታዋቂዎቹ መገናኛ ብዙሐን መካከል
የቢቢሲ እና አልጀዚራን አስተያየት እንደ አብነት ማንሳት ይቻላል ፡፡
“ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በማሳደግ ረገድ የሰሩ ፤ በሰብዓዊ መብት አያያዝ በኩል ክፉ ወቀሳ የሚሰነዘርባቸው ናቸው ”
ያለው ቢቢሲ ሲሆን “ በኢኮኖሚው ረገድ ጥሩ ውጤት በማስመዝገባቸው የሚወደሱ ፤ በጸረ ሽብር ህግ ሽፋን የተቃውም ድምጾችን በመጨፍለቃቸው
የሚወገዙ ” ሲል የገለጻቸው ደግሞ አልጀዚራ ነው ፡፡