በቅርቡ የሶማሌ ክልል ርዕሰ ከተማ ወደሆነችው
ጅጅጋ ለስራ አቅንቼ ነበር ፡፡ ከሞላ ጎደል ከተማዋን ከዚህ በፊት የማውቃት በደራ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዋ ፣ ርዕሰ ብሄርን
እንደ ሸሚዝ በመቀያየርዋ ፣ በአቧራ አፍቃሪነቷ ፣ በነዋሪዎቿ የእኩል ተናጋሪነትና የእኩል አዳማጭነት ጥበባቸው ነበር ፡፡ አሁን
አንድ የጥበቃ ስርዓት ጨምራ አገኘኃት ፡፡ ከተማዋ ሰላም ብትሆንም በየቡናቤቱ ፣ ሆቴሎች ፣ የምሽት ክለቦችና ሌሎች ተቋማት በር
ላይ ዩኒፎርም የለበሱ ወንድና ሴት ጥበቃዎች ተሰይመዋል ፡፡
በክልሉ የሚገኙ አንዳንድ ታጣቂዎች ወደ መንግስት
ስርዓት መቀላቀላቸውን በመገናኛ ብዙሃን የሰማን ቢሆንም በሰላም ሀገር ጥበቃን የማብዛት ጉዳይ እንቆቅልሽ ይፈጥራል ፡፡ በርግጥም
ታጣቂዎች ሳይታሰብ በሆቴሎችና በአንዳንድ ቦታዎች ቦንብን እንደቀልድ ጣል ያደርጋሉ ነው የተባለው ፡፡ የሶማሌ ባለስልጣናት ደግሞ
ከቢሮ በአጃቢዎች ወጥተው ሆቴል በረንዳ ላይ መወያያት ይወዳሉ ፡፡
የምዕራባዊያን ዘይቤ ይመስላል ፡፡ አጃቢዎቹ የሰጉ ዕለት ታዲያ በሆቴሉ ውስጥ የሚዝናናውን ሰው እየገፈተሩ በማስወጣት ፊትና ጀርባ
ሆነው ኤኬያቸውን ይወድራሉ ፡፡
ይህን መሰረት አድርጎ ምድረ ቡናቤትና ሆቴሎች
በር ላይ ጥበቃዎቹን ማሳየት ይኖርባቸዋል ፡፡ በጣም የሚገርመው ጥበቃዎቹ ወንበር ላይ ቁጭ አሉ እንጂ ተጠቃሚውን አይፈትሹም ፡፡
ጥቂት ወገብዋ የሚዳሰሰው ማታ ላይ አንድ ሁለት ለመቀማመስ ቡና ቤት ጎራ ሲሉ ነው ፡፡ የጥበቃዎቹን ብዛት ያየ እንኳን ጥቂት ነገር
ፈላጊ ታጣቂዎች ሌላ ወራሪ ኃይል ቢመጣ ድባቅ ተመቶ የሚመለስ ነው የሚመስለው ፡፡ ይሄ ሁሉ ሰው በአግባቡ ስራውን የማይሰራ ከሆነ
የክልሉ መንግስት ዋና ዓላማ ወጣቱን አደራጅቶ ስራ ማስያዝ ነው ማለት ነው ፡፡ ዘርፉን በጥቃቅንና አነስተኛ ጥላ ስር እንደ ኮብልስቶን
ወይም ዶሮ እርባታ የሚዋቀር ንዑስ ዘርፍ አድርገን ልንመለከት እንችላለን ፡፡ መላምታችንን በአቋም መግለጫ ስናጠቃልለው ግን
‹‹ የሶማሌ ፍተሻ - ፈታሹ በሽበሽ ፍተሻው ትንሽ ›› ከሚል መፈክር ጋ ሊሆን ነው ፡፡
ለነገሩ በርካታ መስሪያ ቤቶች በር ላይ ‹‹ ለፍተሻ
ተባበሩ ! ›› ወይም ‹‹ ለጋራ ደህንነታችን ሲባል ሁላችንም እንፈተሸ ! ›› የሚሉ መፈክሮችን ተውበው ማየት የተለመደ ነው ፡፡
በመርህ ደረጃ ትክክለኛና ብዙዎቻችንን የሚያግባቡ ናቸው ፡፡ ከተግባር አኳያ ሲፈተሹ ግን የፍተሻ እንከኖቻችን ቆጥረን ለመዝለቅ
ያስቸግረናል ፡፡ አንድ ሁለት ማሳያዎችን እያነሳን እናውጋ ፡፡
የሚያስቁ
ፍተሻዎች
ጠመንጃቸውን ግድግዳ እያስደገፉ እንግዶችን የሚፈትሹ
ጥበቃዎች አላጋጠሟችሁም ? እነዚህ በእነሱ ቤት መሳሪያቸውን ለግድግዳ
የሚያስረክቡት ማንንም ስለማያምኑ ነው ፡፡ ‹ ጠርጥር ገንፎ ውስጥ አይጠፋም ስንጥር › በተሰኘው መርሃቸው እንግዶችን የሚፈትሹ
ቢሆንም ከእንግዶቹ አንዱ ዞር ብሎ በቀላሉ መሳሪያዬን ይቀማል ብለው ግን በፍጹም አይጠራጠሩም ፡፡ በተቃራኒው መሳሪያቸውን በእንግዶች
እጅ ላይ በማስደገፍ ፍተሻቸውን የሚያቀላጥፉ አይኖሩም ማለት አይቻልም ፡፡ እነዚህ ደግሞ ሰው
አማኞች መሆናቸው ነው ‹ እንግዳ እዚህ የሚመጣው ጉዳዩን ሊተኩስ
እንጂ መሳሪያ ሊተኩስ አይደለም › በማለት ፡፡
በዚህም ምድብ ሊጠቃለሉ ከሚችሉ ጥበቃዎች አንዳንዶቹ ደግሞ ፍተሻውን በቃለ መጠይቅ
የሚጨርሱት ናቸው ፡፡ የሚጠይቁት ከፍተኛ የሆነውን የማውራት ሱሳቸውን ለማስተንፈስ ሊሆን ይችላል ፣ የሚጠይቁት መቆሙና ወዲህ ወዲያ ማለቱ አታክቷቸው እንደማስተንፈሻነት
ለመጠቀም ሊሆን ይችላል ፡፡ የሚጠይቁት የአስጊ ሰውን አይነ ውሃ በሩቁ ማወቅ ይቻላል ከሚለው ልምዳቸው በመነሳት ሊሆን ይችላል
፤ ብቻ ይጠይቃሉ
‹‹ ሽጉጥ ይዘሃል ? ››
‹‹ አልያዝኩም ›› የሚል ምላሽ ካገኙ ‹‹ ይግቡ ጌታዬ ›› ን ያስከትላሉ ፡፡
እነዚህን ሰዎች አንድ የተገረመ ጋዜጠኛ ጠጋ ብሎ ‹‹ ይህን ልበሙሉነት ከየት አዳበራችሁት ? ›› ቢላቸው ‹‹ እድሜ ለቢኤስሲ
›› የሚሉ ይመስላል ‹‹ ስራን በፍጥነት፣ በብዛትና በጥራት ይላል ሳይንሱ ! ››
‹‹ በዚህ አይነት አፈታተሸ ጥራቱ ከየት ይመጣል ? ›› ከተባሉም ቢያንስ ምሳሌያዊ
ምላሽ አያጡም ‹‹ መንግስታችን በአንድ ግዜ ሃያ ዩኒቨርስቲዎች የገነባው ጥራትን ማዕከል አድርጎ ነው እንዴ ? አይደለም ! ምሶሶዎቹ
ብዛትና ፍጥነት ናቸው ፤ ጥራት በሂደት ይመጣል ›› ለማለት አይቸገሩም
፡፡
የልብስና የሰውነት መጠንም በአንዳንድ ዋዘኛ ፈታሾች አይን የወጣላቸው መመዘኛዋች
ናቸው ፡፡ የአምባሳደር ማስታወቂያን የመሰለ ፣ ሽክ ብሎ የሚታይና ሳምሶናይት ያንጠለጠለ የተማረ ፣ የተከበረ ወይም ጨዋ ተደርጎ ስለሚቆጠር ከመልካም ፈገግታ ጋር
ወደ ውስጥ እንዲዘልቅ ይደረጋል ፡፡ አንገቱን ፣ ሆዱን ወይም መቀመጫውን በከበሩ ጠቦቶችና ሰንጋዎች ያድበለበለም ስጋት ፈጣሪ ነው
ተብሎ ስለማይገመት ለጥቂት ሰከንዶችም ቢሆን በር ላይ እንዲጉላላ አይደረግም ፡፡ ወፍራሙ ሰው ፈጣሪን ካልፈራ በስተቀር ‹‹ ና
እስቲ ማነህ ! እዚህ ተገትረህ ወዴት ነህ ? ምንድነህ ? ከምትል ይህን ቦርሳ ሰባተኛ ፎቅ አድርሰህ ጠብቀኝ ! ›› ቢል ጥበቃው
የሚያስጨንቀው ግዴታውን የሚወጣበትን በር ወለል አድርጎ መሄዱ አይደለም ፡፡ እራሱን የሚወቅሰው ‹ እኚህን የተከበሩ ባለስልጣን
እንዴት እስካሁን ሳላውቃቸው ቀረው ? › በሚለው መልስ አልባው ጥያቄው እንጂ ፡፡ ለወፋፍራም ሰዎች መታዘዝንና አክብሮትን የሚያበዙ የዚህ ምድብ ጥበቃዎች አንዳንዴም
ግራ የሆነ ተግባር ሊፈጽሙ ይችላሉ ፡፡ ለምሳሌ የሰማይ ስባሪ የሚያህለው እንግዳ ከአንድ የመነመነ ጓደኛው ጋ በሩን ሲያቋርጥ እጁን
ወይም ኮሌታውን ስበው በማስቀረት አብጠርጥረው ከላይ እስከታች ሊፈትሹት ይችላሉ ፡፡ ካስፈለገም በላዩ ላይ ‹‹ ምነው እዚህ ቆመን
ስታየን የፊልም ቤት ሬክላም መሰልንህ እንዴ ?! ›› የሚል የአሽሙር ፎጣ ጣል ሊያደርጉበት ይችላሉ ፡፡ ይሄ ሁሉ አጭር ድራማቸው
ከሲታውንም ዶፍዳፋውንም አፍ ማስከፈቱ ይጠበቃል ፡፡
የሚያናድዱ ፍተሻዎች
አንዳንድ ጥበቃዎች ስራቸውን መስራታቸውን ብቻ እንጂ እንግዳ መከበር እንዳለበት
በጥልቀት የሚረዱ አይደሉም ፡፡ የያዘውን እቃ አቧራ ላይ እንዲያስቀምጥ ሊያዙ ይችላሉ ፡፡ በአንድ ወቅት የተማሩትን ወታደራዊ ትምህርት
ለማስታወስ በሚመስል መልኩ አንዴ እጅ ወደፊት ! አንዴ አሳርፍ ! አንዴ አንድ እርምጃ ወደኃላ ሂድ ! ከማለት አይቆጠቡም ፡፡
ሽንኮራ አገዳ እየገነደሹ ወይም ቡርቱካን እየመጠጡ ወይም መሳሪያቸውን በዘይት እያጸዱ እንኳ የእንግዶችን ልብስ በፍተሻ ለመዳፈር
ወደ ኃላ አይሉም ፡፡
ከመታወቂያ ጋ የተያያዘ አናዳጅ ጉዳይም አለ ፡፡ የስራ መታወቂያ እረሱ እንበል
- እረ ዝርክርኩ መ/ቤትዋ ነገ ዛሬ እያለ ሳያዘጋጅልዋ ቀርቶም ይሆናል ፡፡ የቀበሌ መታወቂያ አሳይተው ወደ አንድ ተቋም ሊገቡ
ሲሉ ጥበቃዎች በዚህ መታወቂያ መስተናገድ እንደማይችሉ ይነግሩዋታል
፡፡ መታወቂያ የማንነት መገለጫ መሆኑን ለማስረዳት ጥረት ሲጀምሩ ‹‹ ተማሪና ስራ አጦችን አናስገባም ! ›› የሚል መከላከያና
ፍረጃ ይከተላል ፡፡
‹‹ ለምን ? ››
‹‹ በመጀመሪያ ለስራ ፈላጊዎች ማስታወቂያ ስላልወጣ ! ››
‹‹ ጓድ እኔ እኮ ስራ አጥ አይደለሁም ››
‹‹ ምንም ማረጋገጫ የለህም ጓድ ! ›› ሊባሉ ይችላሉ በመልስ ምቱ ‹‹ ተማሪስ እዚህ ምን ያደርጋል ? ››
‹‹ ይሰሙኛል እኔ ተማሪ አይደለሁም ፡፡ የመጣሁት … ››
‹‹ አንዳንዶች እንግዳ መስለው እየገቡ በየጠረጼዛው የሚያገኙትን ንብረት ሌላው
ቢቀር የሴቶችን ቦርሳ አፋፍሰው ይወጣሉ ፡፡ እህስ … ከዛ ማነው
የሚጠየቀው አልክ ? አቶ ጥበቃ ነው ፡፡ ማነው መጠቋቆሚያ የሚሆነው
አልክ ? ንጽሁ ጥበቃ ነው ፡፡ ተወኝ ብዙ አታናግረኝ ባክህ ፣ በጣም የሚገርመው ለስራ ብለው ገብተው የኤድስ የምናምን በሽተኛ
ነኝ እያሉ የልመና ወረቀት ሲያዞሩ የደረስንባቸው አሉ ፡፡ ይሄ የስራ እንጂ የልመና ቦታ ይመስልሃል ?! እንዲህ የሚያደርጉትን ደግሞ ከልምድ አውቀናቸዋል ›› ይህን የመሰለ ፈጣንና
የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ የሚደርሱ ሰዎችን በቀላሉ ማሳመን ከባድ ነው ፡፡ አጓጉል ትንታኔያቸውና ፍረጃቸው አብሻቂ መሆኑ ባያጠያይቅም
ትዕግስት ኖሮት ለሚሰማቸው ግን በኮሜድያነታቸው ፈታ ማለቱ አይቀርም ፡፡
አንዳንድ ፈታሾች ደግሞ ከአባታቸው ድብድብ ፤ ከእናታቸው ቁንጥጫን በላቀ ጥናት
ተምረው የወጡ ይመስላሉ ፡፡ ሰውነትን የሚዳስሱት እንደ ሎሚ በማሸት ነው ፡፡ ስልቱ የተደበቀ መሳሪያ ከማግኘት ጋር የሚያያይዘው
ነገር ግልጽ አይደለም ፡፡ የመሃል እግርዋን ለማስከፈት ታፋዋን ሊቆነጥጥዋት ይችላሉ ፡፡ ያለምንም መሳቀቅ የብልትዋን ፍሬ ወዲያና
ወዲህ ሊንጡት ይችላሉ ፡፡ አንዳንድ ሴቶችም በሴት ፈታሾች የማህጸን ምርመራ የመሰለ ጥልቅ ፍተሻ አልፎ አልፎ እንደሚያጋጥማቸው
ይናገራሉ ፡፡ ፈታሾቹ እነዚህን ስስ ብልቶች ስለምንጠራጠራቸው ማጉላላታችን አይታየንም ባይ ናቸው ፡፡
የጠመንጃቸውን አፈሙዝ ወደ እንግዶች አዙረው የሚሰሩትስ ? ‹‹ እረ እባክህ አፈሙዙን
አዙረው ? ›› የሚል ቅን አስተያየት ሲያጋጥማቸው በቀላሉ የሚቀበሉ አይሆንም ፡፡ ‹‹ ጥርሴን የነቀልኩት በፍተሻ ስራ ነው ፡፡
ጠመንጃ ካልነኩት አይጮህም ፤ ለዛውም ስለያዝከው ብቻ ሳይሆን ምላሱን ካልሳብከው አይጮህም ! እና ምላሱ ጋ ምን ያደርስሃል
?! ለዛውም ምላሱን እንደ እብድ ዉሻ አፍ ከፍቶ የሚተው ጥበቃ የለም ፤ ምላሱ ይዘጋል ፡፡ አንዳንዶች በር ብቻ የሚዘጋ ይመስላቸዋል
፤ ጠመንጃም ይዘጋል ፡፡ በማናውቀው ስራ ባንገባ ጥሩ ነው ! ›› የሚል ሙያዊ ትንታኔ ከመስጠት ወደ ኃላ አይሉም ፡፡
የሚያሰጉ ፍተሻዎች
ይህኛው ምድብ አስፈሪ ነው ፡፡ መቼም እስከዛሬ በሰላም የቆየነው በጠንካራ ጥበቃዎች
ዋስትና ስለተሰጠን ሳይሆን በአንድዬ ድጋፍ ነው ፡፡ ለምን ከተባለ በአግባቡ እየተጠበቅን ባለመሆኑ ይሆናል ፡፡ ብቻ ለስሙ ያህል ብብት ስር እጃቸውን
ከተው ‹ እለፍ › ማለት የሚቀናቸው ጥበቃዎች ጥቂቶች አይደሉምና ፡፡ መቼም የሽጉጥም ሆነ የቦንብ መቀመጫ ብብት እንዳልሆነ ያስማማናል
፡፡ ቦርሳ አስከፍተው በእጃቸው የሚዳስሱትን አንዳች ነገር ‹ ምሳ ነው አይደል ? መዝገበ ቃላት መሆን አለበት ! › በማለት ሌላ
ምላሽ ለመስማት ግዜ ሳይፈጥሩ እንግዳውን ሲያስገቡ ምን ይባላል ፡፡ ሌላው ችግራቸው የሚግባቡትን ወይም ሰላምተኛቸውን አለመፈተሻቸው
ነው ፡፡ በርግጥ ወደነዚህ ሰዎች ተንደርድረው የሚሄዱት እጃቸውን በሰላምታ ጥፊ ለማስጮህና በትከሻ ‹ ግጨው › ለመባባል ነው ፡፡
በአንዳንድ መ/ቤቶች ደግሞ ‹‹ ሴቶች ታማኞች ናቸው ›› በተሰኘው ያልተጻፈ ተግባራዊ ህግ ያለፍተሻ ወደ ውስጥ እንዲያልፉ ይደረጋል ፡፡ በነዚህና በመሳሰለው ምክንያት አይደለም
ሽጉጥ ታጣፊ ክላሽ ፤ አይደለም ተወርዋሪ ቦንብ ተለጣፊው ፈንጂ በየቢሮአችን ሊገባ እንደሚችል መገመት አይከብድም ፡፡
በበርካታ መስሪያ ቤቶች የሚገኙ ጥበቃዎች ግዴለሾች ፣ ስልችዋችና የተቃራኒ ጉዳይ
ደጋፊዎች ናቸው ፡፡ ይሄ ከምን መነጨ ? የሚል ጥያቄ መወርወር ብዙ ምላሽ ያስከትላል - ለአብነት Girl ን ጀርል እያለ ሲያስተምር
የተደረሰበት መምህር ‹ ምነው አንተ እንደዚህ ነው እንዴ የሚባለው ? › ሲባል ‹ በ 230 ብር ደመወዝ ዋናው ጋ እንዴት መድረስ ይቻላል › ብሏል አሉ ፡፡
ከሚያገኙት ደመወዝ በላይ የሚዘንጡና የሚዝናኑ ጥበቃዎች ካጋጠሟችሁ ምድባቸው አስጊ ውስጥ መሆናቸውን ተጠራጠሩ ፡፡ ደንበኛ የሚበዛበት
መ/ቤት ውስጥ ሰዓት አልፏል ወይም ኃላፊዎቹ የሉም በማለት በተዘዋዋሪ መደለያ ይጠይቃሉ ፡፡ ማዉጫ ያለው ዕቃ ሰበብ ፈልገው አይወጣም
በማለት በግድ ኪስዋትን ያስበረብራሉ ፡፡ በተቃራኒው መዉጫ የሌለው ዕቃ ይለፍ ሰጥተው ከሽያጭ በኃላ ስላለው ክፍያ ተራጋግተው ያስባሉ
፡፡ እጅግ ውድ ዋጋ ያላቸው የሀገር ቅርሶችን ለመዝረፍ ለሚዶልቱ ኃላፊዎችና ሰራተኞች በጥቂት መደለያ ድምጽ ለመስጠት ወደ ኃላ
አይሉም ፡፡ በብዙ መቶ ሺህ ብሮች የሚያወጡ የዝሆን ጥርሶችና ማሽኖችን በትርፍ ሰዓት ስራ አስመስለው በድፍረት አሰጭነው ለማውጣት
አይፈሩም ፡፡ መ/ቤቱ ውስጥ ያለውን ንብረት በመጠቆም የአብሪነት ሚናም ይጫወታሉ ፡፡
የተጋነኑ
ፍተሻዎች
በሚደርስብዎት መጉላላትና ውክቢያ ‹ ምነው እግሬን
በሰበረው ! › እስከማለት የሚደርሱበት አጋጣሚምም አለ ፡፡ የፍተሻው የቀጠነ ህግጋትና የፈታሾቹ ከእርስዎ በላይ መደናገር ስጋትዎ እንዲንር ያደርገዋል ፡፡ የተወካዮች ምክር ቤትና የጠ/ሚ/ር ጽቤት በዚህ ምድብ ውስጥ
ከሚገኙ ቋሚ ተሰላፊዎች መካከል እናገኛቸዋለን ፡፡ የተወካዮች ም/ቤት የፍተሻ ማሽን እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ የሚጠብቅዎት ጠ/ሚ/ሩ
ሪፖርት በሚያቀርቡበት ግዜ ነው ፡፡ ጋዜጠኛው ፣ የም/ቤት አባላት ፣ ሚኒስትሮችና ትላልቅ እንግዶች የሚገቡበት በር ተመሳሳይ ሲሆን
ያን ሁሉ ሰው የሚያስተናግዱት ሁለት ማሽኖች ናቸው ፡፡
ጫማና ቀበቶ ሲያወልቁ ወደ እስር ቤት የሚገቡ ሊመስልዎት ይችላል ፡፡ ብረት ነክ
ጉዳዮችን ሁሉ ከኪስዎ አራግፈው ይጥላሉ ፡፡ ክፉ ነገር አልያዝኩም ብለው በማሸኑ በር ሰተት ሲሉ እሳት ለባሹ እሪታውን ያቀልጠዋል
፡፡ ሁልግዜም ትላልቅ ሆቴሎች ፣ አልፎ አልፎ በራሱ በፓርላማ ማሽኑ ባልተለመደ መልኩ ድምጽ ሲያሰማ ሰውየው በሩን አልፎ በትንሷ
መዳበሻ በእጅ ተፈትሾ እንዲገባ ይደረጋል ፡፡ ፓርላማ በተለይም ጠ/ሚ/ሩ በሚመጡበት ዕለት ግን እንደዚህ አይነት ቀና ስራ አይሞከርም
፡፡ ማሽኑ በአንድ በኩል ፌዴራልና ደህንነቶች በሌላ በኩል የጩኀትና ግልምጫ እሳታቸውን ይተፋሉ እንጂ ፡፡
‹ የቀረህን ነገር ሁሉ አውልቅ ! › ሊባሉ ይችላሉ ፡፡ በአንድ ወቅት አንድ የተከበሩ
ሚኒስትር ጫማቸውን አውልቀው በባዶ እግራቸው በሩን ለማለፍ ሞከሩ ፡፡ ማሽኑ ተቃወመ ፡፡ ‹‹ ተመለስና ራስህን ፈትሽ ›› ተባሉ
እንደማንኛችንም ፡፡ እንደ ሞኝ ሁኔታውን ፈዝዤ እመለከታለሁ ፡፡ ሚኒስትሩ ፈገግ እያሉ ኪሳቸውን ዳበሱ ፤ ያገኙት ነገር አልነበረም
፡፡ ኃላ ትዝ ያላቸውን መነጽር አውልቀው በጠባብዋ በር ሰተት አሉ ፡፡ ማሽኑ እሪ አለ ፡፡ ‹‹ ሌላ ነገር ፈልግ ! ›› አለ
ሲቪል ለባሹ ጆሮ ጠቢ ፡፡ በጣም ተሳቀቅኩ ‹ አያቃቸውም ማለት ነው ? › ስል ራሴን ጠየቅኩ
የቀራቸው ኮታቸውን ማውለቅ ነው ፡፡ ኮታቸው ላይ እንኳ የተለመደውን ባለብረት ባንዲራ
አለጠፉም ፡፡ የኮቱ የውስጥ ኪስ ቁልፎች እንደማይክል ጃክሰን ጃኬት ዚፕ የበዛባት ይሆን ? ብሎ መገመት ያስቸግራል ፡፡ የማሽኑ
ሰይጣን ከሄደለት ብለው ትንሽ ቆይተው ሲገቡ ብረቱ አለቀቃቸውም ፡፡ ኮታቸውን ገልብጠው ለፈታሾቹ አሳዩ - ምንም የለብኝም እንደማለት
፡፡ እንደነገሩ ወደተከለለች ክፍል አስገቧቸው ፡፡ ስገምት እዚህ ክፍል ሊታየው የሚችለው የውስጥ ሱሪ ብቻ ነው - ምናልባትም በብረታብረት
ከተጌጠ ፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኃላ ከክህሉ ወጥተው አንድ - ካልሲያቸውን ፤ ሁለት - ጫማቸውን ፤ ሶስት - ቀበቷቸውን ፤ አራት
- ሰዓታቸውን ፤ አምስት - መነጽራቸውን ግዜ ወስደው በጸጥታ ተራ በተራ አደረጓቸው ፡፡
በዚህ ጸጥታ ውስጥ ቢሯቸውን ያስቡ ይሆን ? የሚል ሀሳብ መጣብኝ ፡፡ … ገና ወደ
በሩ እንደቀረቡ ሁለት እሳት የበሉ ፖሊሶች በሩን ወዲህና ወዲያ ወርውረው መሬት የሚያርድ ሰላምታ ሲሰጧቸው… ልበ ሙሉው ሾፌርም በመጣበት ፍጥነት ክፍተቱን ሰንጥቆ ወደ ውስጥ ሲዘልቅ… መኪናው እንደቆመ
ወይ ሹፌሩ ወይ የሆነ ጋርድ በፍጥነት ጎንበስ በማለት በሩን ከፍቶ ሲያስወርዳቸው … የያዙትን ሳምሶናይት ወይም ቦርሳ ተቀብሎ መንገድ
የሚጠርግላቸው የፕሮቶኮል ሰራተኛ … በየኮሪደሩ ‹‹ እንደምን አደሩ ክቡር ሚኒስትር ! ›› የሚሏቸው መምሪያ ኃላፊዎች … አበባ
ብቻ ማሳቀፍ የሚቀራት ፍልቅልቅዋ ጸሀፊ …
‹ የሀገሪቱን የካቢኔ አባልን እንኳ የማያምን ፍተሻ › ስል እሳቸውን በመንፈስ ወክዬ አጉረመረምኩ ፡፡
ተራዬ ደርሶ እኔም ብረት የሌለውን ጫማዬን አወለቅኩ ፡፡ ቀበቶ ፣ ሳንቲሞች ፣
ፍላሾች ፣ መቅረጸ ድምጽ ፣ ሞባይል ፣ የቢሮ ቁልፎች አንድ በአንድ ሳህኑ ላይ ዘረገፍኳቸው ፡፡ የኪሶቼን ሆድ እቃ ገልብጬ ሳጣራ
መፋቂያ ብቻ ነው የቀረው ‹ የተከበርክ መፋቂያ ! › አልኩት በአቅራቢያው አጠራር ‹ ፓርላማ
ውስጥ እንጨት ለመሆንህ ምንም ማረጋገጫ መስጠት አይቻልም ! › በማለት በዘር ከሚርቁት ጓደኞቹ ጋ ቀላቀልኩት ፡፡ አንድ ዚፕ ያለውን
የቆዳ ጃኬቴ ደግሞ ‹ እባብን ያየ በልጥ በረየ ! › የሚል ስነቃል ቢጤ ወርወር አደረግኩለትና አውልቄ ወረወርኩት ፡፡
እሳት የሚተፋው ማሽን እንደሚኒስትሩ ሊያንገላታኝ አልፈለገም ፡፡ በአንደኛ ሙከራዬ
የይለፍ ካርድ ቆረጠልኝ፡፡ ‹ ተመስገን ! መጋረጃ ውስጥ ከመግባት ያዳንከኝ … › እያልኩ በውስጤ ለመቀላለድ ስሞክር ሌላ ሲቪል
ለባሽ ጠጋ ብሎ በህገወጥ ጥያቄዎች ያጣድፈኝ ጀመር
‹ ምንድነው ስራህ ?! › ጤና ይስጥልኝን እንኳ ማስቀደም ያልፈለገ ትዕቢተኛ ቢጤ
ነው ፡፡
‹ ጋዜጠኛ ! ›
‹ ከየት ? ›
‹ ከእገሌ ድርጅት ›
‹ እስኪ ባጅህ ? › ጥበቃ ክፍሉ ስሜን አጣርቶ የሰጠኝን መግቢያ እንኳ ለማመን
የተቸገረ ዱልዱም ቢጤ ነው ፡፡
አሳየሁ
‹ ይሄ ምንድነው ? ›
‹ መቅረጸ ድምጽ ›
‹ ውስጡ ምን አለ ? ›
‹ ካሴት ›
‹ እስኪ ክፈተው ?! ›
ካሴቱን አሳየው
‹ ምነው አነሰች ? ›
‹ ስራው ነው ›
‹ የኃላውን ክፈተው ! ›
ከፈትኩት
‹ ባትሪዎቹን አውጣቸው ! ›
አውጥቼ ሰጠሁት ፡፡ አያቸው ምናልባትም አነበባቸው ወይም ደግሞ የድማሚትነት ባህሪ
እንደሌላቸው ተገነዘበ መሰል መልሶ ሰጠኝ
‹ ዝጋውና አጫውተው ! ›
የማጫወቻውን ቁልፍ ተጫንኩት
‹ ድምጹ የታል ታዲያ ? ›
‹ ባዶካሴት እኮ
ነው ?! ›
‹ ድምጽ ያለው ካሴት ይዘሃል ? ›
‹ አልያዝኩም ›
ቅር ያለው ስለመሰለኝ ‹ ሮጥ ብዬ የቴዲ አፍሮን ጃ ያስተሰርያል ካሴት ገዝቼ ልምጣ
? › ብለው በኔም ሃሳብ በእሱም ምላሽ የምዝናና መስሎኝ ነበር ፡፡ ግና በሪፖርት ቀን ከእኔ የሚጠበቀው መስማት ብሎም በሚሰማው
መሳቅ እንጂ ሳቅ መፍጠር አይደለምና ሃሳቤን ዋጥኩት
‹ እነዚህስ ምንድናቸው ? ›
‹ ፍላሽ ›
‹ ምንድነው እሱ ? ›
‹ መረጃ መያዣ ናቸው ›
‹ የምን መረጃ ? ›
‹ የጽሁፍ ፣ የድምጽ ፣ የተለያዩ … ›
ፍላሾቹን ለብቻ ያዛቸው ፡፡ አላመነኝም ወይም አላወቀውም ማለት ነው ፡፡ ምናልባትም ‹ ባዶ ካሴት የያዘው ለድምጽ ፣ ፍላሽም የያዘውም ለድምጽ
- እንዴት ያለ አራዳ ነው ? › በማለት በውስጡ ተሳልቆብኝ ይሆናል ፡፡
‹ ሞባይልህን አጥፋው ! ›
‹ ለምን ? ›
‹ ወደ ውስጥ ስለማይገባ ዝጋው ! ›
‹ ሌላ ግዜ ይገባል እኮ ?! ›
‹ ስለእሱ አያገባኝም ! ›
አሁን የጠ/ሚ/ር ጽ/ቤት ትዝ አለኝ ፡፡ ለጋዜጣዊ መግለጫ ስንሄድ የመጀመሪያው
በር ላይ በፍተሻ ታሽተን እንገባለን ፡፡ እግረ መንገዱንም ሞባይላችንን አስረክበን ፡፡ የመጀመሪያ ቀን ለምን ይሆናል ? አግባብ አይደለም ! ምናምን ! እያልን ስናለቃቅስ አንድ ሰራተኛ ‹‹ ሁለትና ሶስት ሰአት አይደል እንዴ የምትቆዩት ? እኛ ቋሚ ሰራተኞቹ
መቼ ስልካችንን ይዘን ገብተን እናውቃለን ›› ብሎ ገላገለን
‹ ነው እንዴ ?! › ብለናል በድምጽ ሳይሆን ወደ ዉጭ ባልወጣ አግራሞት ፡፡
ከዚያ ደግሞ ዋናውን በር አልፈን ወደ አዳራሽ ልንቃረብ ስንል በጣም ያማረበት ማሽን
እኛን በጉጉት ሲጠባበቅ ተመለከትን ፡፡ አሁን ምንድነው ይሄ ? አግባብ
ነው እንዴ ? ምናምን አላልንም - የቅድሙ የማጣሪያ ጨዋታ ሆኖ የአሁኑ ወደ ሩብ ግማሽ ፍጻሜ መዝለቂያ መሆኑ ነው ? ለማለትም
አልቃጣንም … ይሄ ግቢ ቀልድ አያውቅም ማለት ነው አላልንም - ይሄ ግቢ ኤምኤውን የሰራው በፍተሻ ይሆን እንዴ ? አላልንም -
አንዳንዶቻችን በውስጣችን ያልነው ‹ ይህን ምርጥ የፍተሻ ተሞክሮ
እንዴት ቀምሮ ማስፋፋት ይቻላል ! › የሚል ነበር ፡፡ ለምዶብን ፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ትዝታ ወጥተን ወደ ፓርላማ እንመለስ ፡፡
ሞባይሌን ለሚስድ ኮል የሚሆን ቀጭን ክፍተት እንኳ ሳላስተርፍ ዘግቼ ለነጭ ለባሹ
አስረከብኩ ፡፡ ከፍላሾቹ ጋ አንድ ትንሽ ኪስ ውስጥ ወረወራቸው ፡፡ ካርድ ቢጤ ተቀብዬ ወደ ውስጥ ዘለቅኩ ፡፡ ሶስት ጥያቄዎች
ተከታትለው ብቅ አሉብኝ ፡፡
1 . ይሄን ደህንነት ተሸክሜው ነበር እንዴ ? ምክንያቱም በጣም ነው የደከመኝ
2 . ይሄ ሁሉ ነገር ጥንቃቄ ነው የሚባለው ወይስ ስጋት ? ምክንያቱም ነጭ ለባሹ
ከሲአይኤ መረጃ የደረሰው ይመስላልና
3 . ሚኒስትሩን ያንገላታው ዱዳ ማሽን ይሻላል ወይስ እኔን የጨቀጨቀው ሰው ?
ምክንያቱም ምክንያት ስለማያስፈልገኝ !!!
ማስታወሻ፡- ይህ ፅሑፍ በቁም ነገር መፅሔት ላይ የወጣ ነው፡፡ ፅሑፉን በሌላ ሚዲያ ላይ የምትጠቀሙ ከሆነ ምንጩን እንድትጠቅሱ ትለመናላችሁ፡፡